በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 25

ቤተሰቡ ወደ ግብፅ ሄደ

ቤተሰቡ ወደ ግብፅ ሄደ

ዮሴፍ ከዚህ በኋላ ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም። አገልጋዮቹ በሙሉ ክፍሉን ለቀው እንዲወጡ አዘዛቸው። እሱና ወንድሞቹ ብቻቸውን ሲሆኑ ዮሴፍ ማልቀስ ጀመረ። ወንድሞቹ ምን ያህል እንደ ደነገጡ መገመት እንችላለን፤ ምክንያቱም እያለቀሰ ያለው ለምን እንደሆነ አላወቁም ነበር። በመጨረሻም ‘እኔ ዮሴፍ ነኝ። አባቴ አሁንም በሕይወት አለ?’ አላቸው።

ወንድሞቹ በጣም ከመደንገጣቸው የተነሳ መናገር አልቻሉም። ፍርሃት አደረባቸው። ይሁን እንጂ ዮሴፍ ‘እባካችሁ ወደ እኔ ቅረቡ’ አላቸው። ወደ እርሱ ሲቀርቡ ‘እኔ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ’ አላቸው።

ዮሴፍ ደግነት በተሞላበት ሁኔታ እንዲህ አላቸው:- ‘ወደዚህ አገር ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ። የሰዎችን ሕይወት ለማዳን ወደ ግብፅ የላከኝ አምላክ ነው። ፈርዖን በአገሪቱ ሁሉ ላይ ገዥ አድርጎ ሾሞኛል። ቶሎ ብላችሁ ወደ አባቴ ሂዱና ይህን ንገሩት። እዚህ አገር መጥቶ እንዲኖርም ንገሩት።’

ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን በሙሉ እያቀፈ ሳማቸው። ፈርዖን የዮሴፍ ወንድሞች እንደመጡ ሲሰማ ዮሴፍን እንዲህ አለው:- ‘ሰረገሎች ይውሰዱና ሄደው አባታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ይምጡ። በግብፅ ካለው ሁሉ የተሻለውን ቦታ እሰጣቸዋለሁ።’

እነርሱም ይህንኑ አደረጉ። አባቱ መላውን ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብፅ በመጣ ጊዜ ዮሴፍ ሲቀበለው ሥዕሉ ላይ ማየት ትችላለህ።

የያዕቆብ ቤተሰቦች በጣም ብዙ ሆነው ነበር። ወደ ግብፅ በመጡ ጊዜ ያዕቆብ፣ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ በጠቅላላ 70 ነበሩ። ይሁን እንጂ ሚስቶቻቸውም ነበሩ፤ በተጨማሪም ብዙ አገልጋዮች አብረዋቸው ሳይኖሩ አይቀርም። እነዚህ ሁሉ በግብፅ መኖር ጀመሩ። አምላክ የያዕቆብን ስም ለውጦ እስራኤል ብሎ ጠርቶት ስለ ነበር እነዚህ ሰዎች እስራኤላውያን ተባሉ። ቆየት ብለን እንደምንማረው አምላክ እስራኤላውያንን ለአንድ ለየት ያለ ዓላማ መርጧቸው ነበር።