በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 14

አምላክ የአብርሃምን እምነት ፈተነው

አምላክ የአብርሃምን እምነት ፈተነው

አብርሃም ምን እያደረገ እንዳለ ታያለህ? ቢላዋ ይዟል፤ ልጁን ለማረድ የተዘጋጀ ይመስላል። እንዲህ እያደረገ ያለው ለምንድን ነው? እስቲ በመጀመሪያ አብርሃምና ሣራ እንዴት ልጅ ሊያገኙ እንደቻሉ እንመልከት።

አምላክ ልጅ ትወልዳላችሁ ብሎ ቃል ገብቶላቸው እንደነበረ አስታውስ። ሆኖም አብርሃምና ሣራ በጣም አርጅተው ስለነበረ ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ ሊሆን አይችልም ተብሎ የሚታሰበውን ነገር አምላክ ሊያደርገው እንደሚችል አብርሃም እምነት ነበረው። የተፈጸመው ነገር ምን ነበር?

አምላክ ለአብርሃም ቃል ከገባለት በኋላ አንድ ዓመት ሙሉ አለፈ። ከዚያም አብርሃም 100 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሞልቷቸው እያለ ይስሐቅ የሚባል ወንድ ልጅ ወለዱ። አምላክ የገባውን ቃል ጠብቋል!

ይሁን እንጂ ይስሐቅ ካደገ በኋላ ይሖዋ የአብርሃምን እምነት ፈተነው። ‘አብርሃም!’ ብሎ ጠራው። አብርሃምም ‘አቤት!’ ሲል መለሰ። ከዚያም አምላክ እንዲህ አለው:- ‘አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደማሳይህ ተራራ ሂድ። በዚያ ቦታም ልጅህን አርደህ መሥዋዕት አድርገህ አቅርብልኝ።’

አብርሃም ልጁን በጣም ይወደው ስለ ነበር እነዚህን ቃላት ሲሰማ ምንኛ አዝኖ ይሆን! አምላክ የአብርሃም ልጆች በከነዓን ምድር እንደሚኖሩ ቃል ገብቶ እንደነበረ አስታውስ። ታዲያ ይስሐቅ ከሞተ ይህ እንዴት ሊፈጸም ይችላል? አብርሃም አልገባውም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን አምላክን ታዝዟል።

አብርሃም ወደ ተራራው ከወጣ በኋላ ይስሐቅን አሰረውና በሠራው መሠዊያ ላይ አጋደመው። ከዚያም ልጁን ለማረድ ቢላዋውን አነሳ። ሆኖም ልክ አብርሃም ቢላዋውን እንዳነሳ የአምላክ መልአክ ‘አብርሃም አብርሃም!’ ብሎ ጠራው። አብርሃምም ‘አቤት!’ ሲል መለሰ።

አምላክ እንዲህ አለው:- ‘ልጁን አትረደው ወይም ምንም ነገር አታድርግበት። አንድያ ልጅህን አልከለከልኸኝምና በእኔ ላይ እምነት እንዳለህ አውቄያለሁ።’

አብርሃም በአምላክ ላይ እንዴት ያለ ታላቅ እምነት ነበረው! ይሖዋ የሚሳነው ነገር እንደሌለና ሌላው ቀርቶ ይሖዋ ይስሐቅን ከሞት ሊያስነሳው እንደሚችል ያምን ነበር። ይሁን እንጂ አብርሃም ይስሐቅን እንዲሠዋው አምላክ አልፈለገም። ስለዚህ አምላክ አንድ በግ በዚያው አካባቢ በሚገኝ ቁጥቋጦ ውስጥ ገብቶ እንዲያዝ አደረገና አብርሃም በልጁ ፋንታ ይህን በግ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ነገረው።