በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 32

አሥሩ መቅሰፍቶች

አሥሩ መቅሰፍቶች

ሥዕሎቹን ተመልከት። እያንዳንዳቸው ይሖዋ በግብፅ ላይ ያመጣውን መቅሰፍት ያሳያሉ። በመጀመሪያው ሥዕል ላይ አሮን የናይልን ወንዝ በበትሩ ሲመታው መመልከት ትችላለህ። ወንዙን ሲመታው የወንዙ ውኃ ወደ ደም ተለወጠ። ዓሦቹ ሞቱ፤ ወንዙም መሽተት ጀመረ።

ከዚህ ቀጥሎ ይሖዋ እንቁራሪቶች ከናይል ወንዝ እንዲወጡ አደረገ። እንቁራሪቶቹ በየትም ቦታ ነበሩ፤ በምድጃዎች፣ በመጋገሪያዎችና በአልጋዎች ሁሉ ላይ ነበሩ። እንቁራሪቶቹ ሲሞቱ ግብፃውያን ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም በእነሱ የተነሣ ገማች።

ከዚያም አሮን መሬቱን በበትሩ መታው፤ አቧራውም ተለወጠና ትንኝ ሆነ። ትንኞቹ የሚበሩና የሚናከሱ ትናንሽ ተባዮች ናቸው። እነዚህ ትንኞች በግብፅ ምድር ላይ ሦስተኛው መቅሰፍት ነበሩ።

የተቀሩት መቅሰፍቶች የጎዱት ግብፃውያንን ብቻ ነበር፤ እስራኤላውያንን አልነኳቸውም። አራተኛው መቅሰፍት የግብፃውያንን ቤቶች በሙሉ የወረሩት ትልልቅ ዝንቦች ነበሩ። አምስተኛው መቅሰፍት የደረሰው በእንስሶቹ ላይ ነበር። ብዙዎቹ የግብፃውያን ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች ሞቱ።

ከዚህ ቀጥሎ ሙሴና አሮን አመድ አፈሱና ወደ ላይ በተኑት። ይህም በሰዎቹና በእንስሳቱ ላይ በጣም የሚያም ቁስል አመጣባቸው። ይህ ስድስተኛው መቅሰፍት ነበር።

ከዚህ በኋላ ሙሴ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ ይሖዋም ነጎድጓድና በረዶ አወረደ። ይህ በግብፅ ምድር ታይቶ የማያውቅ ኃይለኛ የበረዶ ዝናብ ነበር።

ስምንተኛው መቅሰፍት የአንበጦች መንጋ ነበር። ያን ያህል እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አንበጦች ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ በኋላ ታይቶ አያውቅም። ከበረዶው የተረፈውን ሁሉ በሉት።

ዘጠነኛው መቅሰፍት ጨለማ ነበር። ለሦስት ቀናት ምድሪቱን ድቅድቅ ጨለማ ሸፍኗት ነበር፤ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ቦታ ግን ብርሃን ነበር።

በመጨረሻም አምላክ ሕዝቡ የበራቸውን ጉበንና መቃን የፍየል ወይም የበግ ጠቦት ደም እንዲቀቡ አዘዛቸው። ከዚያም የአምላክ መልአክ በግብፅ ምድር አለፈ። መልአኩ ደሙን ሲያይ በዚያ ቤት ውስጥ ያለውን ማንም ሰው አይገድልም ነበር። ይሁን እንጂ የአምላክ መልአክ በበራቸው ጉበንና መቃን ላይ ደም በሌለባቸው ቤቶች ሁሉ የሚገኙትን የሰውና የእንስሳት በኩሮችን ገደላቸው። ይህ አሥረኛው መቅሰፍት ነበር።

ከዚህ ከመጨረሻው መቅሰፍት በኋላ ፈርዖን እስራኤላውያንን እንዲሄዱ ነገራቸው። የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ለመሄድ ተዘጋጅተው ስለነበረ በዚያው ሌሊት ከግብፅ ለመውጣት ጉዞ ጀመሩ።