በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 27

አንድ ክፉ ንጉሥ ግብፅን መግዛት ጀመረ

አንድ ክፉ ንጉሥ ግብፅን መግዛት ጀመረ

እዚህ ላይ የምታዩአቸው ሰዎች ሠራተኞቹን በኃይል አስገድደው እያሠሯቸው ነው። አንዱን ሠራተኛ በጅራፍ እየገረፈ ያለውን ሰው ተመልከት! ሠራተኞቹ እስራኤላውያን ተብለው የሚጠሩት የያዕቆብ ዘሮች ናቸው። እንዲሠሩ እያስገደዷቸው ያሉት ሰዎች ደግሞ ግብፃውያን ናቸው። እስራኤላውያን የግብፃውያን ባሪያዎች ሆኑ። ይህ የሆነው እንዴት ነው?

ትልቁ የያዕቆብ ቤተሰብ ለብዙ ዓመታት በግብፅ ውስጥ በሰላም ኖረ። በግብፅ አገር ከንጉሡ ከፈርዖን ቀጥሎ ታላቅ ሰው የነበረው ዮሴፍ አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርግላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ሞተ። እስራኤላውያንን የማይወድ አንድ አዲስ ፈርዖን በግብፅ ላይ ነገሠ።

ይህ ክፉ ፈርዖን እስራኤላውያንን ባሪያዎች አደረጋቸው። ክፉና ጨካኝ የሆኑ ሰዎችን በላያቸው ላይ አለቃ አድርጎ ሾመባቸው። እነዚህ ሰዎች ለፈርዖን ከተሞችን እንዲገነቡ በማድረግ እስራኤላውያንን ከባድ ሥራ ያሠሯቸው ነበር። ያም ሆኖ ግን የእስራኤላውያን ቁጥር እየጨመረ ይሄድ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግብፃውያን፣ እስራኤላውያን በጣም ይበዙና ኃይለኞች ይሆናሉ የሚል ስጋት አደረባቸው።

ፈርዖን ምን እንዳደረገ ታውቃለህ? እስራኤላውያን እናቶችን ያዋልዱ የነበሩትን ሴቶች ‘የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ግደሉት’ አላቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሴቶች ጥሩ ሰዎች ነበሩ፤ ሕፃናቶቹን አልገደሏቸውም።

ስለዚህ ፈርዖን ሕዝቡን በሙሉ እንዲህ ሲል አዘዘ:- ‘ከእስራኤላውያን የሚወለዱትን ወንዶች ልጆች ግደሏቸው። ሴቶቹን ሕፃናት ብቻ አትግደሏቸው።’ ይህ ጭካኔ የተሞላበት ትእዛዝ አይደለምን? ከተወለዱት ወንዶች ልጆች መካከል አንዱ እንዴት ከሞት እንደዳነ እስቲ እንመልከት።