በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 11

የመጀመሪያው ቀስተ ደመና

የመጀመሪያው ቀስተ ደመና

ኖኅና ቤተሰቡ ከመርከቡ እንደወጡ በመጀመሪያ ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ለአምላክ መሥዋዕት ወይም ስጦታ አቀረበ። ከታች ባለው ሥዕል ላይ ኖኅ ይህን ሲያደርግ መመልከት ትችላለህ። ኖኅ ይህን የእንስሳት ስጦታ ያቀረበው እሱንና ቤተሰቡን ከዚያ ታላቅ የጥፋት ውኃ ያዳነውን አምላክ ለማመስገን ነበር።

ይሖዋ በዚህ ስጦታ የተደሰተ ይመስልሃልን? አዎ፣ ተደስቷል። በመሆኑም ዓለምን ዳግመኛ በጥፋት ውኃ እንደማያጠፋ ለኖኅ ቃል ገብቶለታል።

ብዙም ሳይቆይ መሬቱ በሙሉ ደረቀ፤ ኖኅና ቤተሰቡም ከመርከቡ ከወጡ በኋላ አዲስ ኑሮ መኖር ጀመሩ። አምላክ ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው:- ‘ብዙ ልጆች ትወልዳላችሁ። ምድር በሰዎች እስክትሞላ ድረስ ቁጥራችሁ እየጨመረ ይሄዳል።’

ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ሰዎች ስለዚያ ታላቅ የጥፋት ውኃ ሲሰሙ እንደገና የጥፋት ውኃ ይመጣል የሚል ፍርሃት ሊሰማቸው ይችላል። ስለዚህ አምላክ ዳግመኛ መላዋን ምድር በጥፋት ውኃ እንደማያጠፋ የገባውን ቃል ሰዎች እንዲያስታውሱ አንድ ነገር አደረገ። ሰዎች ይህን እንዲያስታውሱ ለማድረግ የተጠቀመበት ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ቀስተ ደመና ነው።

ብዙውን ጊዜ ዝናብ ከዘነበ በኋላ ፀሐይ ስትወጣ ቀስተ ደመና በሰማይ ላይ ይታያል። ቀስተ ደመናዎች በጣም የሚያምሩ ብዙ ቀለሞች ሊኖሯቸው ይችላሉ። ቀስተ ደመና አይተህ ታውቃለህ? ሥዕሉ ላይ ያለውን ቀስተ ደመና አየኸው?

አምላክ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሰዎችንና እንስሳትን በሙሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ውኃ አላመጣም። ቀስተ ደመናዬን በደመናዎች ላይ አደርጋለሁ። ቀስተ ደመናው ሲወጣ ይህን የገባሁትን ቃል አስታውሳለሁ።’

እንግዲያው ቀስተ ደመና ስትመለከት ማስታወስ ያለብህ ነገር ምንድን ነው? አዎ፣ አምላክ ዳግመኛ ታላቅ የጥፋት ውኃ አምጥቶ ዓለምን እንደማያጠፋ የገባውን ቃል ማስታወስ አለብህ።