ምዕራፍ 17
የማይመሳሰሉ መንትዮች
እዚህ ላይ የሚታዩት ሁለቱ ልጆች አይመሳሰሉም፤ ይመሳሰላሉ እንዴ? ስማቸውን ታውቀዋለህ? እያደነ ያለው ኤሳው ሲሆን በጎች እየጠበቀ ያለው ልጅ ደግሞ ያዕቆብ ነው።
ኤሳውና ያዕቆብ የይስሐቅና የርብቃ መንትያ ልጆች ናቸው። ኤሳው ጎበዝ አዳኝ ሲሆን ለቤተሰቡ ምግብ እንዲሆን ያደነውን ይዞ ይመጣ ስለ ነበረ አባቱ ይስሐቅ በጣም ይወደው ነበር። ርብቃ ግን ያዕቆብን ይበልጥ ትወደው ነበር፤ ምክንያቱም ያዕቆብ ረጋ ያለና ጨዋ ልጅ ነበር።
አያታቸው አብርሃም ገና አልሞተም ነበር፤ በመሆኑም አብርሃም ስለ ይሖዋ ሲናገር መስማት ያዕቆብን ምንኛ ያስደስተው እንደነበረ መገመት እንችላለን። በመጨረሻ አብርሃም በ175 ዓመቱ ሞተ፤ አብርሃም ሲሞት መንትዮቹ 15 ዓመት ሆኗቸው ነበር።
ኤሳው 40 ዓመት ሲሞላው በከነዓን ምድር ከነበሩት ሴቶች መካከል ሁለቱን አገባ። ይስሐቅና ርብቃ ኤሳው እንዲህ በማድረጉ በጣም አዘኑ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሴቶች ይሖዋን አያመልኩም ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን ኤሳው በወንድሙ በያዕቆብ ላይ በጣም እንዲቆጣ ያደረገው አንድ ነገር ተፈጸመ። ይስሐቅ ትልቁን ልጁን የሚባርክበት ጊዜ ደርሶ ነበር። ኤሳው የያዕቆብ ታላቅ ስለ ነበር በረከቱን የምቀበለው እኔ ነኝ ብሎ አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ኤሳው ቀደም ሲል በረከቱን ማግኘት የሚቻልበትን መብት ለያዕቆብ ሸጦለት ነበር። በተጨማሪም ሁለቱ ወንዶች ልጆች ሲወለዱ አምላክ በረከቱን የሚቀበለው ያዕቆብ እንደሆነ ተናግሮ ነበር። የተፈጸመውም ነገር ይኸው ነበር። ይስሐቅ በረከቱን ለልጁ ለያዕቆብ ሰጠው።
በኋላ ኤሳው ይህን ሲሰማ በያዕቆብ ላይ ተቆጣ። በጣም ስለ ተናደደ ያዕቆብን እገድለዋለሁ ሲል ዛተ። ርብቃ ይህን ስትሰማ በጣም ተጨነቀች። ስለዚህ ባሏን ይስሐቅን ‘ያዕቆብም የከነዓንን ሴቶች የሚያገባ ከሆነ በጣም አሳዛኝ ይሆናል’ አለችው።
በዚህ ጊዜ ይስሐቅ ልጁን ያዕቆብን ጠራውና እንዲህ አለው:- ‘ከከነዓን ሴቶች አታግባ። በካራን ወደሚገኘው አያትህ ወደ ባቱኤል ቤት ሂድ። ከልጁ ከላባ ሴቶች ልጆች መካከል አግባ።’
ያዕቆብ አባቱ ያለውን ሰምቶ ወዲያውኑ ዘመዶቹ ወደሚኖሩበት ወደ ካራን ረጅሙን መንገድ መጓዝ ጀመረ።