በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 13

የአምላክ ወዳጅ የሆነው አብርሃም

የአምላክ ወዳጅ የሆነው አብርሃም

ሰዎች ከዚያ የጥፋት ውኃ በኋላ ኑሯቸውን ከመሠረቱባቸው ቦታዎች አንዱ ዑር ይባል ነበር። ይህ ቦታ ጥሩ ጥሩ ቤቶች ያሉበት የታወቀ ከተማ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ በከተማው ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች የሐሰት አማልክትን ያመልኩ ነበር። በባቤልም ውስጥ ሳሉ ይህንኑ ያደርጉ ነበር። በዑርና በባቤል ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይሖዋን ያገለግሉ እንደነበሩት እንደ ኖኅና እንደ ልጁ ሴም አልነበሩም።

በመጨረሻ፣ ያ የጥፋት ውኃ ከደረሰ ከ350 ዓመታት በኋላ ታማኙ ኖኅ ሞተ። በዚህ ሥዕል ላይ የምታየው ሰው የተወለደው ኖኅ ከሞተ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው። ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና የነበረው ሰው ነበር። ይህ ሰው አብርሃም ይባላል። በዑር ከተማ ከቤተሰቡ ጋር ይኖር ነበር።

ከዕለታት አንድ ቀን ይሖዋ አብርሃምን ‘ከዘመዶችህ ተለይተህ ዑርን ለቀህ ውጣ፤ እኔም ወደማሳይህ አገር ሂድ’ አለው። አብርሃም አምላክን በመታዘዝ በዑር የነበረውን ምቾት የተሞላበት ኑሮ ትቶ ወጥቷልን? አዎ፣ ወጥቷል። አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ተብሎ ሊጠራ የቻለውም ሁልጊዜ አምላክን ይታዘዝ ስለነበረ ነው።

አብርሃም ዑርን ለቆ ሲወጣ ከቤተሰቡ መካከል አንዳንዶቹ አብረውት ሄደዋል። አባቱ ታራ አብሮት ሄዷል። የወንድሙ ልጅ ሎጥም አብሮት ሄዷል። የአብርሃም ሚስት የሆነችው ሣራም እንዲሁ አብራው ሄዳለች። ከጊዜ በኋላ ካራን ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ደረሱ፤ በዚያም ታራ ሞተ። ከዑር በጣም ርቀው ሄደው ነበር።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አብርሃምና ቤተሰቡ ካራንን ለቀቁና ከነዓን ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ሄዱ። እዚያም ከደረሱ በኋላ ይሖዋ ‘ለልጆችህ የምሰጣቸው ምድር ይህ ነው’ አለው። አብርሃምም በከነዓን ምድር በድንኳን ውስጥ ይኖር ጀመር።

አምላክ አብርሃምን ይረዳው ስለ ነበር የበጎቹና የእንስሳቱ መንጋ እየበዛ ሄደ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ አገልጋዮችም ነበሩት። ይሁን እንጂ እሱና ሣራ የራሳቸው ልጆች አልነበሯቸውም።

አብርሃም 99 ዓመት ሲሆነው ይሖዋ ‘የብዙ አሕዛብ አባት አደርግሃለሁ’ ብሎ ቃል ገባለት። ይሁን እንጂ አብርሃምና ሣራ በጣም አርጅተው ልጅ መውለድ በማይችሉበት ዕድሜ ላይ እያሉ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?