በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 19

ያዕቆብ ትልቅ ቤተሰብ አለው

ያዕቆብ ትልቅ ቤተሰብ አለው

እስቲ ይህን ትልቅ ቤተሰብ ተመልከት። እነዚህ የያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ናቸው። ያዕቆብ ሴቶች ልጆችም ነበሩት። ከልጆቹ መካከል የእነማንን ስም ታውቃለህ? እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እነማን እንደሆኑ እንመልከት።

ልያ ሮቤልን፣ ስምዖንን፣ ሌዊንና ይሁዳን ወለደች። ራሔል ምንም ልጆች ባለመውለዷ በጣም አዘነች። ስለዚህ አገልጋይዋን ባላን ለያዕቆብ ሰጠችው፤ ባላም ዳንና ንፍታሌም የሚባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደች። ከዚያም ልያም እንደዚሁ አገልጋይዋን ዘለፋን ለያዕቆብ ሰጠችው፤ ዘለፋም ጋድንና አሴርን ወለደች። በመጨረሻም ልያ እንደገና ሁለት ወንዶች ልጆችን ማለትም ይሳኮርንና ዛብሎንን ወለደች።

ከጊዜ በኋላ ራሔል ልጅ መውለድ ቻለች። የወለደችውንም ልጅ ዮሴፍ ብላ ጠራችው። ቆየት ብለን ስለ ዮሴፍ ብዙ የምንማረው ነገር ይኖራል፤ ምክንያቱም ዮሴፍ ታላቅ ሰው ሆኗል። ያዕቆብ ከራሔል አባት ከላባ ጋር ሲኖር የወለዳቸው 11 ልጆች እነዚህ ናቸው።

ያዕቆብ ጥቂት ሴቶች ልጆችም ነበሩት፤ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሰው የአንዷን ስም ብቻ ነው። እርሷም ዲና ትባላለች።

ያዕቆብ ከላባ ተለይቶ ወደ ከነዓን ለመመለስ የወሰነው ጊዜ ደረሰ። ስለዚህ ትልቅ ቤተሰቡንና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የበጎቹንና የከብቶቹን መንጎች አንድ ላይ ሰበሰበና ረጅሙን ጉዞ መጓዝ ጀመረ።

ያዕቆብና ቤተሰቡ ወደ ከነዓን ሲመለሱ ራሔል ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች። ይህ የሆነው በጉዞ ላይ እያሉ ነበር። በዚህ ጊዜ ራሔል በጣም ተሠቃይታ ነበር፤ በመጨረሻም ስትወልድ ሞተች። ይሁን እንጂ ሕፃኑ ደህና ነበር። ያዕቆብ ብንያም ብሎ ጠራው።

መላው የእስራኤል ሕዝብ የተገኘው ከእነርሱ ስለሆነ የአሥራ ሁለቱን የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ስም ማስታወስ ይኖርብናል። እርግጥ፣ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች የሚጠሩት በአሥሩ የያዕቆብ ወንዶች ልጆችና በሁለቱ የዮሴፍ ወንዶች ልጆች ስም ነው። እነዚህ ሁሉ ልጆች ከተወለዱም በኋላ ይስሐቅ ለብዙ ዓመታት ኖሯል። በጣም ብዙ የልጅ ልጆች በማየቱ ተደስቶ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ የልጅ ልጁ የሆነችው ዲና ምን እንደደረሰባት እስቲ እንመል⁠ከት።