በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 21

ዮሴፍን ወንድሞቹ ጠሉት

ዮሴፍን ወንድሞቹ ጠሉት

ልጁ ምን ያህል እንዳዘነና ተስፋ እንደቆረጠ ተመልከት። ይህ ልጅ ዮሴፍ ነው። ወንድሞቹ ወደ ግብፅ በመጓዝ ላይ ላሉት ለእነዚህ ሰዎች እየሸጡት ነው። ዮሴፍ በግብፅ ባሪያ ሊሆን ነው። የዮሴፍ ግማሽ ወንድሞች ይህን መጥፎ ነገር የፈጸሙት ለምንድን ነው? ይቀኑበት ስለ ነበረ ነው።

አባታቸው ያዕቆብ ዮሴፍን በጣም ይወደው ነበር። ከሌሎቹ ይበልጥ ይወደው ስለነበረ አንድ የሚያምር ረጅም ኮት ሠራለት። አሥሩ ታላላቅ ወንድሞቹ ያዕቆብ ዮሴፍን ምን ያህል እንደሚወደው ሲመለከቱ ዮሴፍን ይቀኑበትና ይጠሉት ጀመር። ይሁን እንጂ እሱን የሚጠሉበት ሌላም ምክንያት ነበራቸው።

ዮሴፍ ሁለት ሕልሞችን አየ። በሁለቱም ሕልሞቹ ላይ ወንድሞቹ ሰግደውለታል። ዮሴፍ እነዚህን ሕልሞች ለወንድሞቹ ሲነግራቸው ከበፊቱ የበለጠ ጠሉት።

ከዕለታት አንድ ቀን የዮሴፍ ታላላቅ ወንድሞች የአባታቸውን በጎች እየጠበቁ ሳለ ደህና መሆናቸውን አይቶ እንዲመጣ ያዕቆብ ዮሴፍን ላከው። የዮሴፍ ወንድሞች ዮሴፍ ወደ እነርሱ እየመጣ እንዳለ ሲመለከቱ ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ‘እንግደለው!’ አሉ። የሁሉ ታላቅ የሆነው ወንድሙ ሮቤል ግን ‘አይሆንም፣ እንዲህ አታድርጉ!’ አላቸው። በዚህ ፋንታ ዮሴፍን ያዙትና በአንድ ደረቅ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት። ከዚያም ምን ቢያደርጉት እንደሚሻል ቁጭ ብለው መመካከር ጀመሩ።

እየተመካከሩ ሳለ ጥቂት እስማኤላውያን በዚያ በኩል መጡ። ይሁዳ ግማሽ ወንድሞቹን ‘ለእስማኤላውያን እንሽጠው’ አላቸው። ያደረጉትም ይህንኑ ነበር። ዮሴፍን በ20 ብር ሸጡት። እንዴት ያለ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው!

ወንድሞቹ አባታቸውን ምን ሊሉት ይሆን? አንድ ፍየል አረዱና የዮሴፍን የሚያምር ኮት በፍየሉ ደም ውስጥ እየደጋገሙ ነከሩት። ከዚያም ኮቱን እቤት ይዘው ሄደው ለአባታቸው ለያዕቆብ አሳዩትና ‘ይህን አገኘነው። የዮሴፍ ኮት እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እየው’ አሉት።

ያዕቆብ የዮሴፍ ልብስ እንደሆነ አወቀ። ‘አንድ የዱር አውሬ ዮሴፍን በልቶት መሆን አለበት’ በማለት አለቀሰ። የዮሴፍ ወንድሞችም የፈለጉት አባታቸው እንዲህ ብሎ እንዲያስብ ነበር። ያዕቆብ እጅግ አዘነ። ለብዙ ቀናት አለቀሰ። ይሁን እንጂ ዮሴፍ አልሞተም ነበር። ዮሴፍ ወደ ግብፅ ከተወሰደ በኋላ በዚያ የተፈጸመውን ነገር እስቲ እንመልከት።