በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 22

ዮሴፍ እስር ቤት ገባ

ዮሴፍ እስር ቤት ገባ

ዮሴፍ ወደ ግብፅ ሲወሰድ ገና 17 ዓመቱ ነበር። እዚያም ጶጢፋር ለተባለ ሰው ተሸጠ። ጶጢፋር ፈርዖን ለተባለው የግብፅ ንጉሥ አገልጋይ ነበር።

ዮሴፍ ጌታውን ጶጢፋርን በደንብ ያገለግለው ነበር። ስለዚህ ዮሴፍ ሲያድግ ጶጢፋር በቤቱ ሁሉ ላይ ኃላፊ አድርጎ ሾመው። ይህ ከሆነ ታዲያ ዮሴፍ እዚህ እስር ቤት ውስጥ የገባው ለምንድን ነው? በጶጢፋር ሚስት ምክንያት ነው።

ዮሴፍ ሲያድግ በጣም ቆንጆ ሆነ፤ በመሆኑም የጶጢፋር ሚስት አብሯት እንዲተኛ ፈለገች። ይሁን እንጂ ዮሴፍ እንዲህ ማድረግ ትክክል እንዳልሆነ ያውቅ ስለ ነበረ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። የጶጢፋር ሚስት በጣም ተናደደች። ስለዚህ ባሏ ወደ ቤት ሲመጣ ‘ያ መጥፎ ሰው ዮሴፍ ከእኔ ጋር ሊተኛ ሞክሮ ነበር!’ በማለት ዋሽታ ነገረችው። ጶጢፋር ሚስቱን አምኖ በዮሴፍ ላይ ተቆጣ። በዚህም ምክንያት እስር ቤት አስገባው።

ብዙም ሳይቆይ የእስር ቤቱ ኃላፊ ዮሴፍ ጥሩ ሰው እንደሆነ ተገነዘበ። ስለዚህ ዮሴፍን በሌሎቹ እስረኞች ሁሉ ላይ ሾመው። ከጊዜ በኋላ ፈርዖን በወይን ጠጅ አሳላፊውና በእንጀራ ጋጋሪው ላይ ተቆጣና እስር ቤት አስገባቸው። አንድ ቀን ሌሊት ሁለቱም ለየት ያለ ሕልም አለሙ፤ ይሁን እንጂ የሕልሞቻቸውን ትርጉም አላወቁም ነበር። በሚቀጥለው ቀን ዮሴፍ ‘ያለማችሁትን ሕልም ንገሩኝ’ አላቸው። ያለሙትን ሕልም ሲነግሩት ዮሴፍ በአምላክ እርዳታ የሕልሞቻቸውን ትርጉም ነገራቸው።

ዮሴፍ የወይን ጠጅ አሳላፊውን ‘በሦስት ቀናት ውስጥ ከእስር ቤት ትወጣለህ፤ ከዚያም እንደገና የፈርዖን የወይን ጠጅ አሳላፊ ትሆናለህ’ አለው። ስለዚህ ዮሴፍ ‘ከእስር ቤት ስትወጣ ስለ እኔ ለፈርዖን ንገረውና ከዚህ ቦታ መውጣት እንድችል እርዳኝ’ አለው። ይሁን እንጂ ዮሴፍ እንጀራ ጋጋሪውን ‘በሦስት ቀናት ውስጥ ፈርዖን አንገትህን ይቆርጠዋል’ አለው።

በሦስት ቀናት ውስጥ ዮሴፍ የተናገረው ነገር ተፈጸመ። ፈርዖን የእንጀራ ጋጋሪውን አንገት ቆረጠው። የወይን ጠጅ አሳላፊው ግን ከእስር ቤት ወጥቶ ንጉሡን እንደገና ማገልገል ጀመረ። ይሁን እንጂ የወይን ጠጅ አሳላፊው ዮሴፍን ረሳው! ስለ ዮሴፍ ለፈርዖን አልነገረውም፤ በመሆኑም ዮሴፍ በእስር ቤት መቆየት ነበረበት።