በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 24

ዮሴፍ ወንድሞቹን ፈተናቸው

ዮሴፍ ወንድሞቹን ፈተናቸው

ዮሴፍ አሥሩ ታላላቅ ወንድሞቹ አሁንም እንደ ቀድሞው ክፉዎችና ጨካኞች መሆንና አለመሆናቸውን ለማወቅ ፈለገ። ስለዚህ ‘እናንተ ሰላዮች ናችሁ። እዚህ የመጣችሁት አገራችንን ልትሰልሉ ነው’ አላቸው።

‘በፍጹም፣ እኛ ሰላዮች አይደለንም። ምንጊዜም እውነት የሆነውን ነገር የምንናገር ሰዎች ነን። ሁላችንም ወንድማማቾች ነን። 12 ነበርን። አንዱ ወንድማችን የለም። የመጨረሻው ታናሽ ወንድማችን ደግሞ እቤት ከአባታችን ጋር ነው’ አሉት።

ዮሴፍ ፈጽሞ እንዳላመናቸው አስመሰለ። ስምዖን የተባለውን ወንድማቸውን እስር ቤት አስገባውና ሌሎቹ እህል ይዘው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አደረገ። ሆኖም ‘ስትመለሱ ታናሹን ወንድማችሁን ይዛችሁት መምጣት አለባችሁ’ ብሏቸው ነበር።

በከነዓን ምድር ወደሚገኘው ቤታቸው ሲመለሱ የሆነውን ሁሉ ለአባታቸው ለያዕቆብ ነገሩት። ያዕቆብ በጣም አዘነ። ‘ዮሴፍ የለም፤ አሁን ደግሞ ስምዖን የለም። የመጨረሻውን ልጄን ብንያምን ይዛችሁት አትሄዱም’ አላቸው። ይሁን እንጂ ምግባቸው እያለቀ ሲሄድ ተጨማሪ እህል ማግኘት እንዲችሉ ብንያምን ወደ ግብፅ ይዘውት እንዲሄዱ ያዕቆብ የግድ መፍቀድ ነበረበት።

ዮሴፍ ወንድሞቹ ሲመጡ ተመለከተ። ታናሽ ወንድሙን ብንያምን በማየቱ በጣም ተደሰተ። እርግጥ ይህ ታላቅ ሰው ዮሴፍ መሆኑን አንዳቸውም አላወቁም ነበር። ዮሴፍ አሥሩን ግማሽ ወንድሞቹን ለመፈተን አንድ ነገር አደረገ።

አገልጋዮቹ የሁሉንም ስልቻዎች በእህል እንዲሞሏቸው አዘዘ። ይሁን እንጂ ዮሴፍ ማናቸውም ሳያውቁ እርሱ ብቻ የሚጠቀምበት የብር ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ እንዲከተት አደረገ። ሁሉም ጉዟቸውን ጀምረው ጥቂት እንደሄዱ ዮሴፍ አገልጋዮቹን ወደ እነርሱ ላካቸው። የዮሴፍ አገልጋዮች ተከታትለው ከደረሱባቸው በኋላ ‘የጌታችንን የብር ጽዋ የሰረቃችሁት ለምንድን ነው?’ አሉአቸው።

ወንድማማቾቹ በሙሉ ‘እኛ ጽዋውን አልሰረቅንም። ጽዋውን ከእኛ መካከል አንዱ ወስዶ ከተገኘ ያ ሰው ይገደል’ አሉ።

አገልጋዮቹ ስልቻዎቹን በሙሉ ፈተሹ፤ ከዚያም ሥዕሉ ላይ እንደምትመለከተው ጽዋውን በብንያም ስልቻ ውስጥ አገኙት። አገልጋዮቹ ‘ሌሎቻችሁ መሄድ ትችላላችሁ፤ ብንያም ግን ከእኛ ጋር መመለስ አለበት’ አሉ። አሥሩ ግማሽ ወንድሞቹ ምን ያደርጉ ይሆን?

ሁሉም ከብንያም ጋር ወደ ዮሴፍ ቤት ተመለሱ። ዮሴፍ ወንድሞቹን ‘ሁላችሁም ወደ ቤታችሁ መሄድ ትችላላችሁ፤ ብንያም ግን የእኔ ባሪያ ይሆናል’ አላቸው።

በዚህ ጊዜ ይሁዳ እንዲህ አለ:- ‘አባቴ ልጁን በጣም ስለሚወደው እሱን ሳልይዝ ወደ ቤት ከተመለስኩ መሞቱ አይቀርም። ስለዚህ እባክህ በእሱ ፋንታ እኔን ባሪያህ አድርገኝና ልጁ ወደ ቤት ይመለስ።’

ዮሴፍ ወንድሞቹ መለወጣቸውን መረዳት ይችላል። አሁን እንደ ቀድሞው ክፉዎችና ጨካኞች አይደሉም። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ምን እንዳደረገ እስቲ እንመልከት።