በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 20

ዲና ችግር አጋጠማት

ዲና ችግር አጋጠማት

ዲና ወደ እነማን እየሄደች እንዳለች ታያለህ? በከነዓን ምድር ከሚኖሩት ልጃገረዶች ጋር ለመጫወት እየሄደች ነው። አባቷ ያዕቆብ ይህን ማድረጓ ያስደስተዋልን? ይህን ጥያቄ መመለስ እንድትችል አብርሃምና ይስሐቅ ስለ ከነዓን ሴቶች ምን አመለካከት እንደነበራቸው ለማስታወስ ሞክር።

አብርሃም ልጁ ይስሐቅ ከከነዓን ሴቶች መካከል እንዲያገባ ፈልጎ ነበርን? አልፈለገም። ይስሐቅና ርብቃ ልጃቸው ያዕቆብ ከነዓናዊት ልጃገረድ እንዲያገባ ፈልገው ነበርን? አልፈለጉም። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

ይህ የሆነበት ምክንያት በከነዓን የነበሩት ሰዎች የሐሰት አማልክትን ያመልኩ ስለ ነበረ ነው። ለባልነት ወይም ለሚስትነት የሚሆኑ ጥሩ ሰዎች አልነበሩም፤ እንዲሁም የቅርብ ጓደኛ ለመሆን የሚበቁ ጥሩ ሰዎች አልነበሩም። ስለዚህ ያዕቆብ ልጁ እነዚህን ከነዓናውያን ልጃገረዶች ጓደኞቿ በማድረጓ እንደማይደሰት እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

በመሆኑም ዲና ችግር ላይ ወደቀች። ሥዕሉ ላይ የሚታየውን ዲናን እየተመለከተ ያለውን ከነዓናዊ ሰው አየኸው? ይህ ሰው ሴኬም ይባላል። ከዕለታት አንድ ቀን ዲና ልጃገረዶቹ ጋር ስትመጣ ሴኬም ወሰዳትና ከእሱ ጋር እንድትተኛ አስገደዳት። ይህ ስህተት ነበር፤ ምክንያቱም ወንድና ሴት አንድ ላይ መተኛት የሚችሉት የተጋቡ ከሆኑ ብቻ ነው። ሴኬም በዲና ላይ የፈጸመው ይህ መጥፎ ድርጊት ሌላ ብዙ ችግር አስከተለ።

የዲና ወንድሞች የተፈጸመውን ነገር ሲሰሙ በጣም ተቆጡ። ከእነርሱ መካከል ሁለቱ፣ ስምዖንና ሌዊ በጣም ተናድደው ስለ ነበረ ሰይፋቸውን ይዘው ወደ ከተማይቱ ሄዱና ሰዎቹን ሳያስቡት ያዟቸው። ስምዖንና ሌዊ እንዲሁም ወንድሞቻቸው ሴኬምንና ሌሎቹን ወንዶች በሙሉ ገደሏቸው። ያዕቆብ ልጆቹ ይህን መጥፎ ነገር በመፈጸማቸው ተቆጣ።

ይህ ሁሉ ችግር ሊደርስ የቻለው ለምንድን ነው? ዲና የአምላክን ሕጎች የማይታዘዙ ሰዎችን ጓደኞቿ በማድረጓ የተነሳ ነው። እንዲህ ዓይነት ጓደኞች እንዲኖሩን አንፈልግም፤ እንፈልጋለን እንዴ?