በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 10

ታላቁ የጥፋት ውኃ

ታላቁ የጥፋት ውኃ

ከመርከቡ ውጪ ያሉት ሰዎች ልክ እንደ ቀድሟቸው ዕለታዊ ተግባራቸውን ያከናውኑ ነበር። በዚህም ጊዜ እንኳ የጥፋት ውኃው ይመጣል የሚል እምነት አልነበራቸውም። እንዲያውም ከበፊቱ ይበልጥ ሳያሾፉ አይቀርም። ይሁን እንጂ እንዳሾፉ መቀጠል አልቻሉም።

በድንገት ውኃ ከሰማይ መውረድ ጀመረ። ከሰማይ ይወርድ የነበረው ውኃ ከባልዲ እንደሚገለበጥ ውኃ ያህል ነበር። ኖኅ የተናገረው ትክክል ነበር! ነገር ግን አሁን ማንም ሰው ወደ መርከቡ መግባት አይችልም። ይሖዋ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶታል።

ብዙም ሳይቆይ መሬቱ ሁሉ በውኃ ተሸፈነ። ውኃው ልክ እንደ ትልልቅ ወንዞች ሆኖ ነበር። ዛፎችን እየነቃቀለ፣ ትላልቅ ድንጋዮችን እያንከባለለና ኃይለኛ ድምፅ እያሰማ ይሄድ ነበር። ሰዎቹ በጣም ፈሩ። ከፍ ወዳሉ ቦታዎች መውጣት ጀመሩ። ምነው ኖኅን በሰማነውና በሩ ክፍት ሳለ ወደ መርከቡ በገባን ኖሮ ብለው ሳይቆጩ አይቀርም! ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የሚችሉበት ጊዜ አልፏል።

ውኃው እየጨመረና ወደ ላይ ከፍ እያለ መጣ። 40 ቀንና 40 ሌሊት ዘነበ። ውኃው ወደ ተራሮችም ላይ መውጣት ጀመረና ብዙም ሳይቆይ በጣም ረጃጅም የሆኑትንም ተራሮች ሸፈናቸው። አምላክ እንደተናገረው ከመርከቡ ውጪ የነበሩት ሰዎችም ሆኑ እንስሳት በሙሉ ሞቱ። በመርከቡ ውስጥ ያሉት ሁሉ ግን በደህና ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር።

ኖኅና ልጆቹ መርከቡን ጥሩ አድርገው ሠርተውት ነበር። ውኃው መርከቡን ብድግ አደረገው፤ መርከቡም በውኃው ላይ ተንሳፈፈ። ከዕለታት አንድ ቀን ዝናቡ መዝነብ ካቆመ በኋላ ፀሐይ ወጣች። ይህን ማየቱ ምንኛ የሚያስደስት ነበር! ምድር በሙሉ በውኃ ተሸፍና ነበር። የሚታየው ነገር በውኃው ላይ የሚንሳፈፈው መርከብ ብቻ ነበር።

እነዚያ ግዙፍ ሰዎች ጠፍተዋል። ከዚህ በኋላ ሰዎችን መጉዳት አይችሉም። ሁሉም ከእናቶቻቸውና ከቀሩት ክፉ ሰዎች ጋር ሞተዋል። ይሁን እንጂ አባቶቻቸው ምን ደርሶባቸው ይሆን?

የእነዚህ ግዙፍ ሰዎች አባቶች እንደኛ ዓይነት ሰዎች አልነበሩም። ሰው ሆነው በምድር ላይ ለመኖር ከሰማይ የወረዱ መላእክት ናቸው። ስለዚህ የጥፋት ውኃው ሲመጣ ከቀሩት ሰዎች ጋር አብረው አልጠፉም። ለብሰውት የነበረውን ሰብአዊ አካል ተዉና መላእክት ሆነው ወደ ሰማይ ተመልሰው ሄዱ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የአምላክ መላእክት ቤተሰብ አባሎች እንዲሆኑ አልተፈቀደላቸውም። ስለዚህ የሰይጣን መላእክት ሆኑ። እነዚህን መላእክት መጽሐፍ ቅዱስ አጋንንት ብሎ ይጠራቸዋል።

አምላክ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በዚህ ጊዜ የጥፋት ውኃው መጉደል ጀመረ። ከአምስት ወራት በኋላ መርከቧ በአንድ ተራራ ጫፍ ላይ አረፈች። ከዚያም ብዙ ቀናት አለፉ፤ በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ሰዎችም የተራራዎችን ጫፎች መመልከት ቻሉ። ውኃው አሁንም እየጎደለ እየጎደለ ሄደ።

ከዚያም ኖኅ ቁራ ተብሎ የሚጠራ አንድ ጥቁር አሞራ ከመርከቡ አወጣና ወደ ውጪ ሰደደው። ቁራው ወዲያና ወዲህ ሲበር ይቆይና የሚያርፍበት ቦታ ስለማያገኝ ተመልሶ ይመጣ ነበር። በተደጋጋሚ እንዲህ ሲያደርግ ይቆይና ተመልሶ መርከቡ ላይ ያርፍ ነበር።

ኖኅ መሬቱ ደርቆ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ፈልጎ ነበር፤ ስለዚህም ቀጥሎ አንድ ርግብ ላከ። ይሁን እንጂ ርግቧም የምታርፍበት ቦታ ስላላገኘች ተመልሳ መጣች። ኖኅ ለሁለተኛ ጊዜ መልሶ ላካት፤ በዚህ ጊዜ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ተመለሰች። ስለዚህ ኖኅ ውኃው መጉደሉን አወቀ። ኖኅ ርግቧን ለሦስተኛ ጊዜ ሲልካት መኖር የምትችልበት ደረቅ ምድር አገኘች።

ይህ ከሆነ በኋላ አምላክ ኖኅን አነጋገረው። ‘ከመርከቡ ውጣ። ቤተሰብህን ሁሉና እንስሳቱን ይዘህ ውጣ’ አለው። መርከቡ ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ ቆይተው ነበር። ስለዚህ በሕይወት ተርፈው በምድር ላይ እንደገና ለመኖር ከመርከቡ በመውጣታቸው ምን ያህል ደስ እንዳላቸው መገመት እንችላለን!