ምዕራፍ ስድስት
ስንሞት ምን እንሆናለን?
1-3. ሰዎች ሞትን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች ይጠይቃሉ? አንዳንድ ሃይማኖቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች ምን መልስ ይሰጣሉ?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‘ሞት የማይኖርበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። (ራእይ 21:4) በምዕራፍ 5 ላይ፣ ኢየሱስ የከፈለልን ቤዛ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን መንገድ እንደከፈተልን ተምረናል። ይሁንና አሁንም ሰዎች ይሞታሉ። (መክብብ 9:5) በመሆኑም ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ የሚለውን ጥያቄ ማንሳታችን ተገቢ ነው።
2 በተለይ ደግሞ የምንወደውን ሰው በሞት በምናጣበት ወቅት የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ እንፈልጋለን። ‘የት ሄዶ ይሆን? እኛን እያየን ይሆን? ሊረዳን ይችላል? እንደገና እናገኘው ይሆን?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል።
3 ሃይማኖቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ የተለያየ ነው። አንዳንድ ሃይማኖቶች ‘ጥሩ ሰው ከሆንክ ወደ ሰማይ ትሄዳለህ’፤ ‘መጥፎ ሰው ከሆንክ ደግሞ ገሃነም ገብተህ ትቃጠላለህ’ ብለው ያስተምራሉ። ሌሎች ሃይማኖቶች ‘ስትሞት መንፈስ ትሆንና ከሞቱ ዘመዶችህ ጋር አብረህ ትኖራለህ’ ብለው ይናገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሰዎች ከሞቱና ፍርድ ከተሰጣቸው በኋላ ሌላ ሰው ወይም እንስሳ ሆነው እንደገና ይወለዳሉ ብለው ያምናሉ።
4. አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ሞትን በተመለከተ የሚያስተምሩት ትምህርት አንድ ዓይነት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
4 ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርት እንዲሁ ሲታይ የተለያየ ሊመስል ይችላል። ሆኖም አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርት ዞሮ ዞሮ አንድ ዓይነት ነው። ‘አንድ ሰው ሲሞት ከእሱ ተለይታ የምትኖር ነገር አለች’ ብለው ያስተምራሉ። ይሁንና ይህ እውነት ነው?
ስንሞት ምን እንሆናለን?
5, 6. ስንሞት ምን እንሆናለን?
5 ይሖዋ ስንሞት ምን እንደምንሆን ያውቃል፤ አንድ ሰው ሲሞት ሕይወቱ እንደሚያበቃ ገልጾልናል። ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው። አንድ ሰው ሲሞት ከእሱ ተለይታ በሌላ ስፍራ የምትኖር ረቂቅ ነገር የለችም። * በመሆኑም ስንሞት ስሜታችንም ሆነ ትዝታችን ሁሉ ይጠፋል፤ ማየትና መስማት እንዲሁም ማሰብ አንችልም።
6 ንጉሥ ሰለሞን “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” በማለት ጽፏል። የሞቱ ሰዎች መውደድም ሆነ መጥላት አይችሉም፤ “በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።” (መክብብ 9:5, 6, 10ን አንብብ።) በተጨማሪም መዝሙር 146:4 ሰው ሲሞት ‘ሐሳቡ ሁሉ እንደሚጠፋ’ ይናገራል።
ኢየሱስ ስለ ሞት ምን ብሏል?
7. ኢየሱስ ሞትን የገለጸው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ የቅርብ ጓደኛው አልዓዛር በሞተ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል” ብሏቸው ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ቃል በቃል አልዓዛር ተኝቷል ማለቱ አልነበረም። ምክንያቱም ኢየሱስ “አልዓዛር ሞቷል” ሲል በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 11:11-14) ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። ኢየሱስ፣ አልዓዛር ወደ ሰማይ እንደሄደም ሆነ ከሞቱ ቤተሰቦቹ ጋር እንደተገናኘ አልተናገረም። በተጨማሪም ‘አልዓዛር በገሃነም እየተሠቃየ ነው’ አላለም፤ ሌላ ሰው ወይም እንስሳ ሆኖ ዳግመኛ እንደሚወለድም አልነገራቸውም። ከዚህ ይልቅ አልዓዛር ከባድ እንቅልፍ የወሰደው ያህል ነበር። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም ሞትን ከከባድ እንቅልፍ ጋር ያመሳስሉታል። መጽሐፍ ቅዱስ እስጢፋኖስ እንደተገደለ ሲገልጽ “በሞት አንቀላፋ” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 7:60) ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን አንዳንድ ክርስቲያኖች ‘በሞት እንዳንቀላፉ’ ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 15:6
8. አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው እንዲሞቱ እንዳልሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
8 አምላክ፣ አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው ለተወሰኑ ዓመታት ኖረው እንዲሞቱ ነው? በፍጹም! ይሖዋ የፈጠራቸው ሙሉ ጤንነት ኖሯቸው ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ነው። የሰው ልጆች በተፈጥሯቸው ለዘላለም የመኖር ፍላጎት አላቸው፤ ይሖዋ ሰዎችን የፈጠረው በዚህ መንገድ ነው። (መክብብ 3:11) ወላጆች፣ ልጆቻቸው እንዲታመሙና እንዲሞቱ አይፈልጉም፤ ይሖዋም ለእኛ ያለው ስሜት ተመሳሳይ ነው። ታዲያ አምላክ የፈጠረን ለዘላለም እንድንኖር ከሆነ የምንሞተው ለምንድን ነው?
የምንሞተው ለምንድን ነው?
9. ይሖዋ፣ ለአዳምና ለሔዋን የሰጣቸው ትእዛዝ ተገቢ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
9 በኤደን የአትክልት ስፍራ ይሖዋ አዳምን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ እስክትረካ ድረስ መብላት ትችላለህ። ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ ግን አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍጥረት 2:9, 16, 17) ይህን ግልጽ የሆነ መመሪያ መታዘዝ ከባድ አልነበረም። አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው ይሖዋ በመሆኑ ለእነሱ የሚጠቅመውን ነገር የሚያውቀው እሱ ነው፤ ደግሞም ይሖዋ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለአዳምና ለሔዋን የመንገር መብት አለው። አዳምና ሔዋን ይሖዋን በመታዘዝ የእሱን ሥልጣን እንደሚያከብሩና እሱ ለሰጣቸው ነገሮች ሁሉ አመስጋኝ እንደሆኑ ማሳየት ይችሉ ነበር።
10, 11. (ሀ) ሰይጣን፣ አዳምንና ሔዋንን የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥሱ ያደረጋቸው እንዴት ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን ያደረጉት ነገር ይቅር ሊባል የማይችለው ለምንድን ነው?
10 የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን ይሖዋን አልታዘዙም። ሰይጣን ሔዋንን “በእርግጥ አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ ብሏችኋል?” ሲል ጠየቃት። ሔዋንም እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን። ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ ፍሬ በተመለከተ አምላክ ‘ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።”—ዘፍጥረት 3:1-3
11 ከዚያም ሰይጣን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም። አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።” (ዘፍጥረት 3:4-6) ሰይጣን እንዲህ ያለው፣ ሔዋን መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በራሷ መወሰን እንደምትችል አድርጋ እንድታስብ ስለፈለገ ነው። በተጨማሪም የይሖዋን ትእዛዝ ብትጥስ እንደማትሞት በመንገር አታለላት። ሔዋን፣ ሰይጣን የነገራትን በማመን ፍሬውን በላች፤ ከዚያም ለባሏ ሰጠችው። አዳምና ሔዋን፣ ይሖዋ ፍሬውን እንዳይበሉ እንዳዘዛቸው ያውቃሉ። ፍሬውን መብላታቸው የተሰጣቸውን ግልጽና ቀላል ትእዛዝ ሆን ብለው እንደጣሱ የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም በሰማይ ለሚኖረው አፍቃሪ አባታቸው አክብሮት እንደሌላቸው ይጠቁማል። በእርግጥም አዳምና ሔዋን ያደረጉት ነገር ይቅር ሊባል የማይችል ነው!
12. ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሲሠሩ በጣም አዝኖ መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው?
12 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለፈጣሪያቸው አክብሮት አለማሳየታቸው በጣም ያሳዝናል! አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አሉህ እንበል፤ እነሱን ለማሳደግ ብዙ የለፋህ ቢሆንም ካደጉ በኋላ አንተን መታዘዝ ትተው የፈለጉትን ቢያደርጉ ምን ይሰማሃል? በጣም እንደምታዝን የታወቀ ነው!
13. ይሖዋ “ወደ አፈር ትመለሳለህ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
13 አዳምና ሔዋን ይሖዋን ባለመታዘዛቸው ለዘላለም የመኖር መብታቸውን አጥተዋል። ይሖዋ አዳምን “አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 3:19ን አንብብ።) አዳም ከመፈጠሩ በፊት አፈር ነበር፤ ሲሞትም ተመልሶ አፈር ይሆናል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 2:7) አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ሞተ፤ በመሆኑም ሕይወት የሌለው ወይም በድን ሆኗል።
14. የምንሞተው ለምንድን ነው?
14 አዳምና ሔዋን አምላክን ታዘው ቢሆን ኖሮ እስከ ሮም 5:12) ይሁንና አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ይህ አልነበረም። አምላክ የሰው ልጆች እንዲሞቱ አይፈልግም፤ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን “ጠላት” በማለት ይጠራዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:26
ዛሬ በሕይወት ይኖሩ ነበር። ሆኖም የእሱን ትእዛዝ በመጣስ ኃጢአት ስለሠሩ ለተወሰኑ ዓመታት ከኖሩ በኋላ ሞቱ። ኃጢአት ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የወረስነው ከባድ በሽታ ነው ሊባል ይችላል። ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን ስለምንወለድ እንሞታለን። (እውነት ነፃ ያወጣናል
15. ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ነፃ የሚያወጣን እንዴት ነው?
15 ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ከሐሰት ትምህርቶች ነፃ ያወጣናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሞቱ ሰዎች ሥቃይም ሆነ ሐዘን እንደማይሰማቸው ይናገራል። የሞቱ ሰዎችን ልናናግራቸው አንችልም፤ እነሱም ቢሆኑ እኛን ሊያናግሩን አይችሉም። በተጨማሪም ልንረዳቸው አንችልም፤ እነሱም ሊረዱን አይችሉም። የሞቱ ሰዎች ሊጎዱን ስለማይችሉ እነሱን መፍራት አይገባንም። ይሁንና አንዳንድ ሃይማኖቶች አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ከእሱ ተለይታ ስለምትኖር ለቄሶች ወይም ለሃይማኖት መሪዎች ገንዘብ በመክፈል የሞተውን ሰው መርዳት እንደምንችል ያስተምራሉ። ስለ ሞት እውነቱን ስናውቅ ግን እነዚህ ሰዎች በሚናገሩት ውሸት አንታለልም።
16. አንዳንድ ሃይማኖቶች ስለ ሞቱ ሰዎች ምን የሐሰት ትምህርት ያስተምራሉ?
16 ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት በመጠቀም እኛን ለማታለል ይሞክራል። ለምሳሌ አንዳንድ ሃይማኖቶች፣ ስንሞት ከእኛ ተለይታ በሌላ ስፍራ የምትኖር ነገር እንዳለች ያስተምራሉ። የአንተም ሃይማኖት የሚያስተምረው እንዲህ ነው? ወይስ የሚያስተምረው ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው? ሰይጣን እንዲህ ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን ተጠቅሞ ሰዎች ከይሖዋ እንዲርቁ እያደረገ ነው።
17. ይሖዋ ሰዎችን በገሃነም ያቃጥላል ብሎ ማሰብ እሱን እንደመሳደብ ይቆጠራል የምንለው ለምንድን ነው?
17 ብዙ ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርት ዘግናኝ ነው። በገሃነም ለዘላለም እንደሚቃጠሉ ያስተምራሉ። ይህ ይሖዋን እንደመሳደብ ይቆጠራል። ይሖዋ፣ ሰዎችን እንዲህ ባለ መንገድ ፈጽሞ አያሠቃይም! (1 ዮሐንስ 4:8ን አንብብ።) አንድ ወላጅ የልጁን እጅ በእሳት በማቃጠል ቢቀጣው ምን ይሰማሃል? ‘በጣም ጨካኝ ነው’ ብለህ ማሰብህ አይቀርም። እንዲህ ዓይነቱን ሰው እንደምትጠላው የታወቀ ነው። ሰይጣንም ስለ ይሖዋ እንዲህ እንዲሰማን ይፈልጋል!
ለምሳሌ አንዳንዶች፣ ክፉ ሰዎች18. የሞቱ ሰዎችን ልንፈራ የማይገባው ለምንድን ነው?
18 አንዳንድ ሃይማኖቶች፣ ሰዎች ሲሞቱ መንፈስ እንደሚሆኑ ይናገራሉ። እነዚህ መናፍስት ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ወዳጆች ወይም ጨካኝ ጠላቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ልናከብራቸው እንዲሁም ልንፈራቸው እንደሚገባ ያስተምራሉ። ብዙ ሰዎች ይህን የሐሰት ትምህርት አምነው ተቀብለዋል። የሞቱ ሰዎችን ስለሚፈሩ ይሖዋን ማምለክ ሲገባቸው የሙታን መናፍስትን ያመልካሉ። የሞቱ ሰዎች ምንም ስሜት እንደሌላቸውና ምንም እንደማያውቁ አስታውስ፤ በመሆኑም ልንፈራቸው አይገባም። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ፈጣሪያችን ነው። እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ስለሆነ ሊመለክ የሚገባው እሱ ብቻ ነው።—ራእይ 4:11
19. ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
19 ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን የተለያዩ ሃይማኖቶች ከሚያስተምሩት የሐሰት ትምህርት ነፃ ያወጣናል። ይህን እውነት መገንዘባችን ይሖዋ ሕይወታችንንና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ቃል የገባቸውን አስደሳች ተስፋዎች ለመረዳት ያስችለናል።
20. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንማራለን?
20 ኢዮብ የተባለ በጥንት ዘመን የኖረ የአምላክ አገልጋይ “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?” የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር። (ኢዮብ 14:14) በእርግጥ የሞተ ሰው እንደገና በሕይወት ሊኖር ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በጣም አስደሳች ነው። የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህን ያብራራል።
^ አን.5 አንዳንድ ሰዎች፣ ‘ሰው ከሞተ በኋላ ከእሱ ተለይታ የምትኖር ነፍስ ወይም መንፈስ አለች’ ብለው ያምናሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። ይህን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት ተጨማሪ ሐሳብ 17ን እና 18ን ተመልከት።