አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
ጋዜጣ ስታነብ፣ ቴሌቪዥን ስትመለከት ወይም ሬዲዮ ስታዳምጥ ስለ ወንጀል፣ ጦርነትና ሽብርተኝነት ትሰማለህ ወይም ትመለከታለህ። ምናልባትም አንተ ራስህ በሕመም እየተሠቃየህ ወይም የምትወደው ሰው በሞት ተለይቶህ በጣም አዝነህ ይሆናል።
እስቲ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦
-
አምላክ ይህ በእኔም ሆነ በቤተሰቤ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?
-
ችግሮቼን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ማግኘት የምችለው ከየት ነው?
-
መላው ዓለም ሰላም የሚያገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በምድር ላይ አስደናቂ ነገሮች እንደሚያደርግ ይናገራል።
-
ወደፊት ሰዎች አይሠቃዩም፣ አያረጁም እንዲሁም አይሞቱም። —ራእይ 21:4
-
“አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል።”—ኢሳይያስ 35:6
-
“የዓይነ ስውራን ዓይን ይገለጣል።”—ኢሳይያስ 35:5
- የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ። —
-
ማንም ሰው አይታመምም።—ኢሳይያስ 33:24
-
በምድር የሚኖር ሁሉ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል።—መዝሙር 72:16
ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
በዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ገጾች ላይ ያነበብካቸው ነገሮች ይፈጸማሉ ብለህ ለማመን ይከብድህ ይሆናል። ይሁንና አምላክ እነዚህን ነገሮች በቅርቡ በምድር ላይ እንደሚፈጽም ቃል ገብቷል፤ ይህን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ይህን ብቻ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችን አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለብንም ይነግረናል። እስቲ ስለሚያስጨንቁህ ነገሮች ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር። ምናልባት እንድትጨነቅ የሚያደርግህ ነገር ከገንዘብ ወይም ከቤተሰብ ጋር የተያያዘ ችግር አሊያም ያለብህ ሕመም ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ያሉብህን ችግሮች እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል፤ እንዲሁም እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ሊያጽናናህ ይችላል፦
-
አምላክ ቃል የገባውን ነገር ሁሉ እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
ይህን መጽሐፍ ማንበብህ በራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ለማወቅ እንደምትፈልግ ያሳያል። ይህ መጽሐፍ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይረዳሃል። ለአንቀጾቹ የተዘጋጁ ጥያቄዎች አሉ፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ለመረዳት ያስችልሃል። ብዙ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን መወያየት ያስደስታቸዋል። አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ እንደሚያስደስትህ ተስፋ እናደርጋለን። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የምታደርገውን ጥረት አምላክ እንዲባርክልህ እንመኛለን!