ምዕራፍ አሥራ ሁለት
አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖር
የአምላክ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
ሰይጣን ያስነሳው ክርክር አንተንም የሚመለከተው እንዴት ነው?
ይሖዋ የሚጠላው ምን ዓይነት ሥነ ምግባር ነው?
አምላክን ደስ በሚያሰኝ መንገድ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?
1, 2. ይሖዋ የቅርብ ወዳጆቹ አድርጎ ይመለከታቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ።
ጓደኛ አድርገህ የምትመርጠው ምን ዓይነት ሰው ነው? አመለካከትህንና ፍላጎትህን የሚጋራ እንዲሁም የላቀ ግምት የምትሰጣቸውን ነገሮች ከፍ አድርጎ የሚመለከት ሰው ጓደኛህ እንዲሆን እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። በተጨማሪም እንደ ሐቀኝነትና ደግነት ያሉ ግሩም ባሕርያት ያሉት ሰው እንደሚማርክህ ጥርጥር የለውም።
2 ባለፉት የታሪክ ዘመናት አምላክ የተወሰኑ ሰዎችን የቅርብ ወዳጆቹ አድርጎ መርጧቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ አብርሃምን ወዳጄ ብሎታል። (ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:23) ዳዊት ይሖዋ የሚወደው ዓይነት ሰው ስለነበረ አምላክ “እንደ ልቤ የሆነ” ሰው ሲል ጠርቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 13:22) በተጨማሪም ነቢዩ ዳንኤል በይሖዋ ፊት ‘እጅግ የተወደደ’ ነበር።—ዳንኤል 9:23
3. ይሖዋ አንዳንድ ሰዎች ወዳጆቹ እንዲሆኑ የሚመርጠው ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ አብርሃምን፣ ዳዊትንና ዳንኤልን ወዳጆቹ አድርጎ የተመለከታቸው ለምንድን ነው? አብርሃምን ‘ቃሌን ሰምተሃል’ ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) ስለዚህ ይሖዋ፣ ያዘዛቸውን ነገር በትሕትና የሚፈጽሙ ሰዎችን ወዳጆቹ ያደርጋቸዋል። እስራኤላውያንን “ድምፄን ስሙ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ኤርምያስ 7:23) አንተም ይሖዋን ከታዘዝክ ወዳጁ መሆን ትችላለህ!
ይሖዋ ወዳጆቹን ያበረታቸዋል
4, 5. ይሖዋ ሕዝቡን የሚያበረታው እንዴት ነው?
4 ከአምላክ ጋር መወዳጀት የሚያስገኘውን ጥቅም አስበው። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት” የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እንደሚፈልግ ይናገራል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ይሖዋ ሊያበረታህ የሚችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ መዝሙር 32:8 ላይ የተገለጸ ሲሆን ጥቅሱ “[እኔ ይሖዋ] አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” ይላል።
5 የይሖዋን አሳቢነትና እንክብካቤ የሚያሳይ እንዴት ያለ ልብ የሚነካ መግለጫ ነው! ይሖዋ የሚያስፈልግህን መመሪያ የሚሰጥህ ሲሆን መመሪያውን ተግባራዊ ስታደርግ ደግሞ ጥበቃ ያደርግልሃል። አምላክ የሚያጋጥሙህን ፈታኝ ሁኔታዎች በጽናት መወጣት እንድትችል ሊረዳህ ይፈልጋል። (መዝሙር 55:22) ስለዚህ ይሖዋን በሙሉ ልብህ የምታገለግለው ከሆነ “እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ፤ እርሱ በቀኜ ስላለ አልናወጥም” ሲል እንደተናገረው መዝሙራዊ ዓይነት የመተማመን ስሜት ሊያድርብህ ይችላል። (መዝሙር 16:8፤ 63:8) አዎን፣ ይሖዋ እሱን በሚያስደስት መንገድ እንድትኖር ሊረዳህ ይችላል። ሆኖም እንደምታውቀው ይህን እንዳታደርግ መከላከል የሚፈልግ አንድ የአምላክ ጠላት አለ።
ሰይጣን ያነሳው ክርክር
6. ሰይጣን የሰው ልጆችን በተመለከተ ምን ክስ ሰንዝሯል?
6 በዚህ መጽሐፍ 11ኛ ምዕራፍ ላይ ሰይጣን ዲያብሎስ የአምላክን ሉዓላዊነት እንዴት እንደተገዳደረ ተገልጿል። ሰይጣን አምላክን ውሸታም ብሎ የከሰሰው ከመሆኑም በላይ ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር ራሳቸው ለራሳቸው የመወሰን መብት እንዳይኖራቸው መንፈጉ አግባብ እንዳልሆነ አመልክቷል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩና ምድር በዘሮቻቸው መሞላት ከጀመረች በኋላ ደግሞ ሰይጣን የመላውን የሰው ዘር ውስጣዊ ፍላጎት የሚመለከት ክርክር አንስቷል። ሰይጣን “ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት በፍቅር ተገፋፍተው አይደለም” የሚል ክስ ሰንዝሯል። “ዕድሉ ቢሰጠኝ ማንኛውም ሰው ከአምላክ እንዲርቅ ማድረግ እችላለሁ” ሲል ተከራክሯል። ኢዮብ የተባለው ሰው ታሪክ ሰይጣን እንዲህ ያለ እምነት እንዳለው ይጠቁማል። ኢዮብ ማን ነው? ሰይጣን ያነሳው ክርክር እሱን የነካውስ እንዴት ነው?
7, 8. (ሀ) ኢዮብን በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ የተለየ ያደረገው ምን ነበር? (ለ) ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግልበትን ምክንያት በተመለከተ ክርክር ያነሳው እንዴት ነው?
7 ኢዮብ ከ3,600 ዓመታት ገደማ በፊት ይኖር የነበረ ሰው ነው። ይሖዋ “በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም” ሲል የተናገረ በመሆኑ ጥሩ ሰው ነበር። (ኢዮብ 1:8) ኢዮብ አምላክን የሚያስደስት ሰው ነበር።
8 ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግልበትን ምክንያት በተመለከተ ክርክር አነሳ። ዲያብሎስ ይሖዋን እንዲህ አለው:- “[በኢዮብና] በቤተ ሰቦቹ፣ ባለው ንብረትስ ሁሉ ዙሪያ ዐጥር ሠርተህለት የለምን? የበጎቹና የላሞቹ መንጋ ምድርን ሁሉ እስኪሞሉ ድረስ የእጁን ሥራ ባርከህለታል። እስቲ፣ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ንካበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”—ኢዮብ 1:10, 11
9. ይሖዋ፣ ሰይጣን ላነሳው ክርክር ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? ለምንስ?
9 በዚህ መንገድ ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ጥቅም ስላገኘ ነው ሲል ተከራከረ። በተጨማሪም ዲያብሎስ፣ ኢዮብ ፈተና ቢደርስበት አምላክን ማገልገሉን ይተዋል በማለት ተሟገተ። ይሖዋ፣ ሰይጣን ላነሳው ክርክር ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? የተነሳው ክርክር ኢዮብ አምላክን የሚያገለግልበትን ምክንያት የሚመለከት በመሆኑ ይሖዋ፣ ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትነው ፈቀደለት። በዚህ መንገድ ኢዮብ በእርግጥ አምላክን ይወድ እንደሆነና እንዳልሆነ በግልጽ ይታያል።
ኢዮብ ተፈተነ
10. ኢዮብ ምን ፈተናዎች ደረሱበት? ሆኖም ምን አላደረገም?
10 ወዲያውኑ ሰይጣን ኢዮብን በተለያዩ መንገዶች ፈተነው። ከኢዮብ እንስሳት መካከል የተወሰኑት የተዘረፉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ አለቁ። ከአገልጋዮቹ መካከል አብዛኞቹ ተገደሉ። ይህም የኢኮኖሚ ችግር አስከተለበት። አሥሩ ልጆቹ በዐውሎ ነፋስ ሲሞቱ ደግሞ ሌላ ሐዘን ደረሰበት። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ አስከፊ ሁኔታዎች ቢደርሱበትም “ኢዮብ አልበደለም፤ በእግዚአብሔርም ላይ ክፉ አልተናገረም።”—ኢዮብ 1:22
11. (ሀ) ሰይጣን በኢዮብ ላይ ምን ሁለተኛ ክስ ሰነዘረ? ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጠ? (ለ) ኢዮብ የሚያሠቃይ በሽታ ቢይዘውም እንኳ ምን አላደረገም?
11 ሰይጣን ተስፋ አልቆረጠም። ኢዮብ ንብረቱን፣ አገልጋዮቹንና ልጆቹን ማጣቱ ያስከተለበትን መከራ መቋቋም ቢችልም እንኳ በሽታ ከያዘው አምላክን ማገልገሉን ይተዋል ብሎ ሳያስብ አልቀረም። ይሖዋ፣ ሰይጣን ኢዮብን በሚዘገንንና በጣም በሚያሠቃይ በሽታ እንዲመታው ፈቀደለት። ሆኖም ይህም እንኳ ቢሆን ኢዮብ በአምላክ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ አላደረገውም። “በዚህ ሁሉ፣ ኢዮብ በንግግሩ አልበደለም” ወይም በአምላክ ላይ ክፉ ቃል አልተናገረም።—ኢዮብ 2:10
12. ኢዮብ፣ ዲያብሎስ ላነሳው ክርክር ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?
12 ኢዮብ ይህን ሁሉ መከራ ያደረሰበት ሰይጣን መሆኑን አላወቀም ነበር። ዲያብሎስ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ያነሳውን ክርክር ባለማወቁ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ያመጣበት አምላክ መስሎት ነበር። (ኢዮብ 6:4፤ 16:11-14) ያም ሆኖ ከአቋሙ ፍንክች ባለማለት ከይሖዋ ጎን መቆሙን አሳይቷል። በመሆኑም ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ለግል ጥቅሙ ሲል ነው በማለት ያነሳው ክርክር በኢዮብ የታማኝነት አቋም ውድቅ ሊሆን ችሏል!
13. ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ መሆኑ ምን ውጤት አስገኝቷል?
13 የኢዮብ ታማኝነት ይሖዋ፣ ሰይጣን ለሰነዘረው ስድብ አዘል ውንጀላ አጥጋቢ መልስ እንዲሰጥ አስችሎታል። በእርግጥም ኢዮብ የይሖዋ ወዳጅ ነበር፤ አምላክም ላሳየው ታማኝነት ወሮታ ከፍሎታል።—ኢዮብ 42:12-17
ሰይጣን ያነሳው ክርክር አንተን የሚመለከተው እንዴት ነው?
14, 15. ሰይጣን ኢዮብን በተመለከተ ያነሳው ክርክር ሁሉንም ሰዎች ይመለከታል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
14 ለአምላክ ታማኝ የመሆንን ጉዳይ በተመለከተ ሰይጣን ያነሳው ክርክር ኢዮብን ብቻ ሳይሆን አንተንም ይመለከታል። ይሖዋ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት ምሳሌ 27:11 [የ1954 ትርጉም] ላይ የተናገራቸው ቃላት ይህን በግልጽ ያሳያሉ። ኢዮብ ከሞተ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የተጻፉት እነዚህ ቃላት ሰይጣን አምላክን መሳደቡንና አገልጋዮቹን መወንጀሉን እንዳላቆመ ያሳያሉ። ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ የምንኖር ከሆነ ሰይጣን ለሰነዘራቸው የሐሰት ክሶች መልስ በመስጠት ረገድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ የምናደርግ በመሆኑ የአምላክን ልብ ደስ እናሰኛለን። ይህን በተመለከተ አንተ ምን ይሰማሃል? በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ የሚጠይቅብህ ቢሆንም እንኳ ለዲያብሎስ የሐሰት ክሶች መልስ በመስጠት ረገድ የበኩልህን ድርሻ ማበርከት መቻልህ አያስደስትህም?
15 ሰይጣን “ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” ሲል መናገሩን ልብ በል። (ኢዮብ 2:4) ሰይጣን “ሰው” ብሎ መናገሩ ክሱ በኢዮብ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሰዎች ላይ የተሰነዘረ መሆኑን ያሳያል። ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው ነጥብ ነው። ሰይጣን አንተ ለአምላክ ባለህ ታማኝነት ላይ ጥያቄ አንስቷል። ዲያብሎስ አምላክን ለመታዘዝ አሻፈረኝ እንድትልና ችግሮች ሲያጋጥሙህ የጽድቅ ጎዳናን መከተል እንድትተው ይፈልጋል። ይህን ለማድረግ የሚሞክረው እንዴት ነው?
16. (ሀ) ሰይጣን፣ ሰዎች አምላክን ማገልገላቸውን እንዲተዉ ለማድረግ ምን ዘዴዎች ይጠቀማል? (ለ) ዲያብሎስ እነዚህን ዘዴዎች በአንተ ላይ ሊጠቀም የሚችለው እንዴት ነው?
16 ምዕራፍ 10 ላይ እንደተብራራው ሰይጣን ሰዎች አምላክን ማገልገል እንዲተዉ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። በአንድ በኩል፣ “የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ” ሆኖ ጥቃት ይሰነዝራል። (1 ጴጥሮስ 5:8) በመሆኑም ሰይጣን የሚያሳድረው ተጽዕኖ ጓደኞችህ፣ ዘመዶችህ ወይም ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና የተማርከውን ሥራ ላይ ለማዋል የምታደርገውን ጥረት እንድትተው ለማድረግ በሚሰነዝሩት ተቃውሞ ሊንጸባረቅ ይችላል። * (ዮሐንስ 15:19, 20) በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣን “የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል።” (2 ቆሮንቶስ 11:14) ዲያብሎስ አንተን ለማሳትና አምላክን ደስ በሚያሰኝ መንገድ መኖርህን እንድትተው ለማባበል የረቀቁ ዘዴዎችን ሊጠቀም ይችላል። በተጨማሪም ተስፋ ሊያስቆርጥህ ምናልባትም አምላክን ደስ ለማሰኘት ብቁ እንዳልሆንክ እንዲሰማህ ሊያደርግህ ይችላል። (ምሳሌ 24:10) ሰይጣን ‘እንደሚያገሣ አንበሳም’ ይሁን እንደ “ብርሃን መልአክ” መከራከሪያ ነጥቡ አንድ ነው:- አስቸጋሪ ሁኔታዎች ወይም አታላይ የሆኑ ፈተናዎች ሲያጋጥሙህ አምላክን ማገልገልህን ታቆማለህ ሲል ይሟገታል። ኢዮብ እንዳደረገው ሰይጣን ላነሳው ክርክር መልስ መስጠትና ለአምላክ ታማኝ መሆንህን ማረጋገጥ የምትችለው እንዴት ነው?
የይሖዋን ትእዛዛት መጠበቅ
17. የይሖዋን ትእዛዛት የምንፈጽምበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?
17 አምላክን በሚያስደስት መንገድ በመኖር ሰይጣን ላነሳው ክርክር መልስ መስጠት ትችላለህ። ይህ ምን ነገርን ይጨምራል? መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ” በማለት መልስ ይሰጠናል። (ዘዳግም 6:5) ለአምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ሲሄድ የሚፈልግብህን ነገር ለማድረግ ያለህ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነው” ሲል ጽፏል። ይሖዋን በሙሉ ልብህ የምትወድ ከሆነ ‘ትእዛዛቱ ከባድ’ አይሆኑብህም።—1 ዮሐንስ 5:3
18, 19. (ሀ) ከይሖዋ ትእዛዛት መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? (ገጽ 122 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) አምላክ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንደማይጠብቅብን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
18 የይሖዋ ትእዛዛት ምንድን ናቸው? ከትእዛዛቱ መካከል አንዳንዶቹ ልናስወግዳቸው የሚገቡ ምግባሮችን የሚመለከቱ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ገጽ 122 ላይ የሚገኘውን “ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች አስወግድ” የሚል ርዕስ ያለውን ሣጥን ተመልከት። እዚያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያወግዛቸው ምግባሮች ተዘርዝረው ታገኛለህ። ሣጥኑ ውስጥ ከተዘረዘሩት ልማዶች መካከል አንዳንዶቹን መጀመሪያ ላይ ስታያቸው ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆኑ አድርገህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም በተጠቀሱት ጥቅሶች ላይ ካሰላሰልክ በኋላ የይሖዋ ሕጎች ምን ያህል ጥበብና ማስተዋል የተንጸባረቀባቸው እንደሆኑ መረዳትህ አይቀርም። በሥነ ምግባርህ ላይ አንዳንድ ለውጦች ማድረጉ በጣም ፈታኝ ሊሆንብህ ይችላል። ይሁንና አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖር ከፍተኛ እርካታና ደስታ ያስገኛል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ደግሞም ልታደርገው የምትችለው ነገር ነው። ይህን እንዴት ማወቅ እንችላለን?
19 ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር አይጠብቅብንም። (ዘዳግም 30:11-14) ችሎታችንንና አቅማችንን ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ያውቃል። (መዝሙር 103:14) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ እሱን ለመታዘዝ የሚያስችል ብርታት ሊሰጠን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) እንዲያውም ይሖዋ መጽናት እንድትችል ለመርዳት “እጅግ ታላቅ ኀይል” ሊሰጥህ ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ጳውሎስ ብዙ ፈተናዎችን በጽናት ከተቋቋመ በኋላ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” ብሎ መናገር ችሏል።—ፊልጵስዩስ 4:13
አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን ማዳበር
20. ልታዳብራቸው የሚገቡ አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? አስፈላጊ የሆኑትስ ለምንድን ነው?
20 እርግጥ ነው፣ ይሖዋን ለማስደሰት የሚጠላቸውን ነገሮች ማስወገዱ ብቻ በቂ አይደለም። የሚወዳቸውንም ነገሮች መውደድ ያስፈልግሃል። (ሮሜ 12:9) አመለካከትህንና ፍላጎትህን የሚጋሩ እንዲሁም የላቀ ግምት የምትሰጣቸውን ነገሮች ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎችን ወዳጅ አድርገህ እንደምትመርጥ የታወቀ ነው። ይሖዋም የሚያደርገው እንዲሁ ነው። እንግዲያው ይሖዋ የሚወዳቸውን ነገሮች ውደድ። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ አምላክ ወዳጆቹ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ሰዎች በሚናገረው በመዝሙር 15:1-5 ላይ ተዘርዝረዋል። የይሖዋ ወዳጆች መጽሐፍ ቅዱስ “የመንፈስ ፍሬ” ብሎ የሚጠራቸውን ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። ከእነዚህም መካከል “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” ይገኙበታል።—ገላትያ 5:22, 23
21. አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን እንድታዳብር የሚረዳህ ምንድን ነው?
21 መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ማንበብህና ማጥናትህ አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን እንድታዳብር ይረዳሃል። በተጨማሪም አምላክ የሚፈልግብህን ነገር ማወቅህ አስተሳሰብህን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ማስማማት እንድትችል ይረዳሃል። (ኢሳይያስ 30:20, 21) ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እየጠነከረ ሲሄድ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር ያለህ ፍላጎትም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል።
22. አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖርህ ምን ውጤት ያስገኛል?
22 ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ መኖር ጥረት ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወትህ ላይ የምታደርገውን ለውጥ አሮጌውን ስብዕናህን አስወግደህ አዲስ ስብዕና ከመልበስ ጋር ያመሳስለዋል። (ቈላስይስ 3:9, 10) ይሁንና መዝሙራዊው የይሖዋን ትእዛዝ በተመለከተ “እርሱንም መጠበቅ ወሮታ አለው” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 19:11) አንተም አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖር በእጅጉ የሚክስ እንደሆነ በራስህ ሕይወት መመልከት ትችላለህ። ይህን ካደረግክ ሰይጣን ላነሳው ክርክር መልስ መስጠት የምትችል ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ልብ ደስ ታሰኛለህ!
^ አን.16 እንዲህ ሲባል ግን ተቃውሞ የሚሰነዝሩብህ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ናቸው ማለት አይደለም። ሆኖም ሰይጣን የዚህ ሥርዓት አምላክ ከመሆኑም በላይ መላው ዓለም በቁጥጥሩ ሥር ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ስለዚህ አምላክ በሚፈልገው መንገድ ለመኖር የምታደርገው ጥረት ብዙዎችን ደስ እንደማያሰኝና አንዳንዶች ተቃውሞ እንደሚሰነዝሩብህ ልንጠብቅ እንችላለን።