በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መግቢያ

መግቢያ

የሴራሊዮን ተወላጅ የሆነው ዳውዳ “ያደግሁት በሰሜናዊው ክፍለ ሀገር በምትገኝ አንዲት ትንሽ መንደር ነው” በማለት ይናገራል። “አንድ ጊዜ ገና ትንሽ ልጅ ሳለሁ በቤተሰቤና በሌላ ቤተሰብ መካከል የመሬት ክርክር ተነሳ። ሁለቱም ቤተሰቦች መሬቱ ለእኛ ይገባል ባዮች ነበሩ። ለጉዳዩ እልባት ለማስገኘት አንድ ጠንቋይ ተጠርቶ መጣ። ጠንቋዩም መስተዋት አንስቶ ለአንድ ሰው አስያዘና በነጭ ጨርቅ ሸፈነው። ወዲያው የተሸፋፈነው ሰው ያንቀጠቅጠውና ያልበው ጀመር። ወደ መስተዋቱ ተመልክቶ ‘አንድ ሽማግሌ ሰው ሲመጣ ይታየኛል! ነጭ ልብስ ለብሷል። ፀጉሩ የሸበተ፣ ረጅምና ያረጀ ነው፣ የሚራመደውም ትንሽ ጎበጥ ብሎ ነው’ በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ።

“ሰውየው ይገልጽ የነበረው የወንድ አያቴን መልክ ነበር! ወዲያውም የፍርሃት ብርክ ያዘውና ‘የምናገረውን ካላመናችሁ ኑና ራሳችሁ ተመልከቱ!’ ብሎ ጮኸ። በእርግጥ ከመካከላችን ወደ መስተዋቱ ቀርቦ ለመመልከት የደፈረ ማንም አልነበረም! ጠንቋዩም በቅል ይዞት ከነበረው አስማት የተደረገበት የቅጠሎችና የውኃ ቅልቅል ረጭቶ ጸጥ አሰኘው።

“በመስተዋት በሚመለከተው ሰው አማካኝነት ‘አያቴ’ መሬቱ የሚገባው ለእኛ ቤተሰብ መሆኑን ተናገረ። ለሴት አያቴ መሬቱን ያላንዳች ስጋት ልታሳርስ እንደምትችል ነገራት። ሌላው ቤተሰብም ፍርዱን ተቀበለ። ክርክሩም በዚሁ እልባት አገኘ።”

በምዕራብ አፍሪካ ይህን የመሰሉ ተሞክሮዎች የተለመዱ ናቸው። በሌላው የዓለም ክፍል እንደሚደረገው በምዕራብ አፍሪካም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሙታን በምድር ላይ ያሉትን ሰዎች ሕይወት ሊመለከቱና ተጽዕኖም ሊያሳድሩ ወደሚችሉበት መንፈሳዊ ዓለም ያልፋሉ ብለው ያምናሉ። ይህ እምነት ትክክል ነው? ሙታን በእርግጥ በሕይወት አሉ? የማይኖሩስ ከሆነ የሙታን መንፈስ ነን ብለው የሚናገሩት እነማን ናቸው? የእነዚህን ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። የሕይወትና የሞት ጉዳይም ነው።