በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አጋንንት በአምላክ ላይ ማመፅን ያበረታታሉ

አጋንንት በአምላክ ላይ ማመፅን ያበረታታሉ

አንዳንድ ልማዶች ሙታን ሊመለከቱን ይችላሉ በሚለው ሐሰት ላይ የተመሠረቱ ናቸው

ታዲያ ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎችን ለማሳሳት ይህን ያህል የሚጥሩት ለምንድን ነው? በዓመፃቸው እንድንተባበራቸው ስለሚፈልጉ ነው። እነሱን እንድናመልክ ይፈልጋሉ። የእነሱን ውሸት አምነን ይሖዋ የማይወዳቸውን ነገሮች እንድናደርግ ይፈልጋሉ። ከእነዚህ ይሖዋ ከማይወዳቸው ተግባሮች ብዙዎቹ ከሙታን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ልማዶች የሚመለከቱ ናቸው።

የሚወዱት ሰው ሲሞት በጣም ያሳዝናል። ይህን ሐዘን መግለጽም የተለመደም የተገባም ነው። ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር ሲሞት ‘እንባውን አፍስሷል።’—ዮሐንስ 11:35

ከሞት ጋር ዝምድና ያላቸው ልማዶች ብዙ ሲሆኑ በዓለም በሙሉ የተለያየ መልክ አላቸው። ብዙዎቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር አይጋጩም። አንዳንዶቹ ልማዶች ግን ሙታን በሕይወት ይኖራሉ፣ ያልሞቱትን ሰዎችም ሊመለከቱ ይችላሉ በሚለው አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። አስከሬኑን አጅቦ ሲጨፍሩ ማደር፣ ገደብ የለሽ ለቅሶና የተንዛዙ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ሁሉ የሚመነጩት የሙታንን መንፈስ ላለማስቀየም ከመፍራት ነው። ነገር ግን ‘ሙታን ምንም ስለማያውቁ’ እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች የሚያደርጉ ሰዎች የሰይጣንን ሐሰት ያስፋፋሉ።—መክብብ 9:5

ሌሎች ልማዶች ደግሞ ሙታን የእኛ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል በሚለው ሐሰት ላይ የተመሠረቱ ናቸው

ሌሎች ልማዶች ወይም ክብረ በዓሎች ደግሞ ሙታን የሕያዋንን እርዳታ ስለሚፈልጉ ፍላጎታቸው ካልተፈጸመ ሕያዋንን ይጎዳሉ ከሚለው እምነት የመነጩ ናቸው። በአንዳንድ አገሮች አንድ ሰው ከሞተ በ40 ቀኑ ወይም በዓመቱ ድግስና መሥዋዕት ይደረግለታል። ይህን ማድረግ ሟቹ ወደ መንፈሳዊው ዓለም እንዲሻገር ይረዳዋል ተብሎ ይታመናል። ሌላው የተለመደ ድርጊት ደግሞ ለሟቹ ምግብና መጠጥ ማስቀመጥ ነው።

እነዚህ ነገሮች ሰይጣን ስለ ሙታን የተናገረውን ሐሰት ስለሚያስፋፉ ስህተት ናቸው። ይሖዋ በአጋንንት ትምህርቶች ላይ ከተመሠረቱ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ነገር ብናደርግ ይደሰትበታል? በጭራሽ!—2 ቆሮንቶስ 6:14-18

የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች የሰይጣንን ሐሰት በሚደግፉ ልማዶች በምንም መንገድ አይካፈሉም። ከዚህ ይልቅ በሕይወት ያሉ ሰዎችን በፍቅር በመርዳትና በማጽናናት ሥራ ላይ ያተኩራሉ። አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከይሖዋ በስተቀር ማንም ሊረዳው እንደማይችል ያውቃሉ።—ኢዮብ 14:14, 15

መናፍስትነት በይሖዋ የተወገዘ ድርጊት ነው

አንዳንድ ሰዎች በቀጥታ ወይም በሰብአዊ አገናኝ አማካኝነት ከአጋንንት ጋር ይገናኛሉ። ይህም መናፍስትነት ተብሎ ይጠራል። ቩዱ፣ ጥንቆላ፣ አስማት፣ ምዋርትና ሙታንን መጠየቅ ሁሉም የመናፍስትነት የተለያዩ ገጽታዎች ናቸው።

አምላክ እነዚህን መጥፎ ድርጊቶች ይቃወማል። ያልተከፋፈለና ለእሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንዲሰጠው ይፈልጋል።—ዘፀአት 20:5

መጽሐፍ ቅዱስ “ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው” በማለት እነዚህን ነገሮች ያወግዛል።—ዘዳግም 18:10-12

ይሖዋ ከእነዚህ ድርጊቶች እንድንርቅ ይህን ያህል አበክሮ የሚያስጠነቅቀን ለምንድን ነው?

ይሖዋ ከማንኛውም ዓይነት መናፍስትነት እንድንርቅ የሚያስጠነቅቀን ለራሳችን ደህንነት ሲል ነው። እሱ ሰዎችን ይወዳል፣ ያስብላቸዋልም። ከአጋንንት ጋር ማንኛውም ዓይነት ንክኪ ያላቸው ሰዎች ሥቃይ እንደሚደርስባቸው ያውቃል።

ከአጋንንት ጋር ንክኪ ስለኖራቸው ችግር ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንዷ በብራዚል አገር መናፍስት ጠሪ የነበረችው ኒልዳ ናት። አጋንንቱ ሕይወቷን አመሰቃቀሉባት። እንዲህ በማለት ታሪኳን ትናገራለች፦ “ዛሮቹ ካደሩብኝ በኋላ . . . እንደፈለጋቸው ሊያዙኝ ጀመሩ። በየጊዜው ራሴን ስቼ ከቆየሁ በኋላ እንደገና ራሴን ወደማወቅ እመለስ ነበር። የአእምሮ ችግር ስለደረሰብኝ ሆስፒታል ገባሁ። ነርቮቼ እስኪነኩ ድረስ አጋንንቱ ከመጠን በላይ አሠቃዩኝ። እንቅልፍ የሚያስወስዱ መድኃኒቶችን መውሰድና ያለማቋረጥ መጠጣትና ማጨስ ጀመርኩ። ይህም ለዓመታት ቀጠለ።”

የመናፍስትነት ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ መጨረሻቸው አያምርም። ቤታቸውን፣ ነፃነታቸውን፣ ሕይወታቸውንም እንኳ ሳይቀር ሊያጡ ይችላሉ

ኒልዳ ከጊዜ በኋላ በይሖዋና በምድር ላይ ባሉት ምሥክሮቹ እርዳታ ከአጋንንትና ከተጽዕኗቸው ተላቅቃ ጥሩና ጤናማ ኑሮ ትኖራለች። “ሰው ሁሉ ላንዳፍታም እንኳ [ከክፉ] መናፍስት ጋር በምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረው አበረታታለሁ” ትላለች።