ከሐዘኔ ልጽናና የምችለው እንዴት ነው?
ማይክ ስለ አባቱ ሞት ሲናገር “ስሜቴን አምቄ መያዝ እንዳለብኝ ተሰምቶኝ ነበር” ይላል። ለማይክ ሐዘኑን አምቆ መያዝ የወንድነት መገለጫ ነበር። በኋላ ግን፣ ተሳስቶ እንደነበረ ተገነዘበ። ስለዚህ ጓደኛው አያቱን በሞት ባጣበት ጊዜ፣ እንዴት ሊያጽናናው እንደሚችል አውቆ ነበር። ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢሆን ኖሮ ትከሻውን መታ መታ አድርጌ ‘አይዞህ፣ ወንድ ሁን’ እለው ነበር። አሁን ግን ክንዱን ያዝ አድርጌ ‘ምንም ዓይነት ስሜት ቢሰማህ ስሜትህን አታፍን። ሐዘንህን ለመቋቋም የሚረዳህ ይህ ነው። እንድሄድ ከፈለግህ እሄዳለሁ። እንድቆይ ከፈለግህም እቆያለሁ። ስሜትህን ለመግለጽ ግን ፈጽሞ አትፍራ’ አልኩት።”
ሜሪአንም ባሏ በሞተ ጊዜ ሐዘኗን አምቃ ለመያዝ ሞክራ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ መሆን አለብኝ ብዬ እጨነቅ ስለነበር ሐዘኔን ከመግለጽ ተቆጠብኩ። በኋላ ግን ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን ስል ጠንካራ ሆኜ ለመቆም መሞከሬ እንዳልበጀኝ ተገነዘብኩ። ሁኔታዬን አመዛዘንኩና ለራሴ ‘ማልቀስ ከፈለግሽ አልቅሺ። ጠንካራ ሰው ሆነሽ ለመታየት አትሞክሪ። ሐዘንሽ ይውጣልሽ’ ማለት ጀመርኩ።”
ማይክም ሆነ ሜሪአን ‘ሐዘናችሁን አታፍኑ!’ በማለት ይመክራሉ። ደግሞም ትክክል ናቸው። ለምን? ሐዘንን መግለጽ የታመቀ ስሜትን ለማውጣት የሚያስችል ጠቃሚ መንገድ ስለሆነ ነው። የሐዘን ስሜታችሁ እንዲወጣላችሁ ማድረጋችሁ የሚሰማችሁን ጭንቀት ይቀንስላችኋል። ሐዘንን ስለ መግለጽ ትክክለኛ መረጃ ካለን፣ ማዘን ስህተት እንዳልሆነ እንረዳለን፤ ሐዘናችንን መግለጻችን ደግሞ እንድንረጋጋ ይረዳናል።
እርግጥ ነው፣ ሁሉም ሰው ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ አንድ ዓይነት አይደለም። በተጨማሪም ግለሰቡ የሞተው በድንገት አሊያም ደግሞ ለረጅም ጊዜ ከታመመ በኋላ መሆኑ፣ በሕይወት ያለው ሰው በሚሰማው ሐዘን ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ የተረጋገጠ ነገር አለ፦ ሐዘናችሁን አፍናችሁ ለመያዝ መሞከራችሁ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት ያስከትልባችኋል። ለጤናችሁ የሚበጀው ሐዘናችሁ እንዲወጣላችሁ ማድረጋችሁ ነው። ሆኖም ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ቅዱሳን ጽሑፎች አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮች ይሰጣሉ።
ሐዘናችሁ እንዲወጣላችሁ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
ስሜትን አውጥቶ መናገር ሐዘን ቀለል እንዲል የሚረዳ ጠቃሚ መንገድ ሊሆን ይችላል። ከጥንት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አንዱ የሆነው ኢዮብ፣ አሥሩም ልጆቹ ከሞቱበትና ብዙ አሳዛኝ ሁኔታዎች ከደረሱበት በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወቴን ተጸየፍኳት። አንዳች ሳላስቀር ብሶቴን አሰማለሁ [በዕብራይስጥ፣ “እለቀዋለሁ”]። በታላቅ ምሬት ኢዮብ 1:2, 18, 19፤ 10:1) ኢዮብ ጭንቀቱን አምቆ መያዝ አልቻለም ነበር። ሐዘኑን ‘መልቀቅ’ ይኸውም ‘መናገር’ አስፈልጎት ነበር። እንግሊዛዊው የቲያትር ደራሲ ሼክስፒርም በተመሳሳይ ማክቤዝ በተባለው ተውኔቱ ላይ “ሐዘንህ እንዲናገር ፍቀድለት፤ የማይናገር ሐዘን ልብን ተጭኖ ያደቅቃል” ብሏል።
እናገራለሁ!” (ስለዚህ በትዕግሥትና በሐዘኔታ ለሚያዳምጣችሁ “እውነተኛ ወዳጅ” ስሜታችሁን አውጥታችሁ መናገር፣ የተወሰነ እፎይታ ሊሰጣችሁ ይችላል። (ምሳሌ 17:17) ያጋጠሟችሁን ሁኔታዎችና ስሜታችሁን በቃላት መግለጽ፣ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን ስሜቶች መረዳትና መቋቋም እንድትችሉ ይረዳችኋል። የሚያዳምጣችሁ ሰው ሐዘን ደርሶበት የሚያውቅና ሐዘኑን በጥሩ ሁኔታ የተቋቋመ ከሆነ ደግሞ ሐዘናችሁን ለመቋቋም የሚያስችላችሁ ጠቃሚ ምክር ይሰጣችሁ ይሆናል። ልጅ የሞተባት አንዲት እናት፣ ተመሳሳይ ሐዘን የደረሰባት ሌላ ሴት ማነጋገሯ እንዴት እንደረዳት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “እንደ እኔ ዓይነት ሐዘን የደረሰባት ሴት መኖሯንና ሐዘኗን በመቋቋም እንደ ቀድሞው ሕይወቷን መምራት መቻሏን ማወቄ በጣም አበረታቶኛል።”
ስሜታችሁን አውጥታችሁ መናገር የሚከብዳችሁ ሰዎች ከሆናችሁስ? ሳኦልና ዮናታን በሞቱ ጊዜ ዳዊት በጣም ልብ የሚነካ ሙሾ ያቀናበረ ሲሆን በዚህ መንገድ ሐዘኑን ገልጿል። ይህ ሙሾ ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ ተካትቷል። (2 ሳሙኤል 1:17-27፤ 2 ዜና መዋዕል 35:25) በተመሳሳይም አንዳንዶች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን በጽሑፍ መግለጽ እንደሚቀላቸው ተገንዝበዋል። ባሏ የሞተባት አንዲት ሴት የሚሰማትን ሁሉ እንደምትጽፍና ከቀናት በኋላ፣ የጻፈችውን መልሳ እንደምታነበው ተናግራለች። ይህም ሐዘኗ እንዲወጣላት ረድቷታል።
በመናገርም ሆነ በመጻፍ ስሜታችሁን መግለጻችሁ ሐዘናችሁ እንዲወጣላችሁ ይረዳችኋል። በተጨማሪም አለመግባባትን ለማስወገድ ያስችላል። ልጅ የሞተባት አንዲት እናት እንደሚከተለው ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ልጃቸው ከሞተባቸው በኋላ የተፋቱ ባለትዳሮች እንዳሉ ሰምተን ነበር። ይህ በእኛ ላይ እንዲደርስ አልፈለግንም። ስለዚህ በምንበሳጭበትና አንዳችን ሌላውን ለመውቀስ በምንፈተንበት ጊዜ ቁጭ ብለን እንነጋገርና አንድ እልባት ላይ እንደርሳለን። ይህን በማድረጋችን ከቀድሞው ይበልጥ እንደተቀራረብን ይሰማኛል።” ስለዚህ ምን እንደሚሰማችሁ መናገራችሁ፣ እናንተ በሞት ያጣችሁትን ሰው ያጡት ሌሎች ሰዎች፣ የሚያዝኑበት መንገድና የሐዘናቸው መጠን ከእናንተ የተለየ ሊሆን እንደሚችል እንድትገነዘቡ ይረዳችኋል።
ሐዘናችሁ እንዲወጣላችሁ የሚረዳችሁ ሌላው ነገር ማልቀስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለማልቀስ ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 4) የምንወደው ሰው ሲሞት ማልቀስ እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። ሐዘን ሲደርስብን እንባ አውጥተን ማልቀስ፣ ሐዘናችንን ለመቋቋም የሚረዳ አንዱ ጠቃሚ መንገድ ነው።
አንዲት ወጣት እናቷ በሞተች ጊዜ የቅርብ ጓደኛዋ እንዴት እንደረዳቻት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፡- “ጓደኛዬ ፈጽሞ አልተለየችኝም። አብራኝ አልቅሳለች። ታዋራኝ ነበር። ስሜቴን አውጥቼ በግልጽ ልነግራት እችል ነበር፤ ይህ ደግሞ በጣም ጠቅሞኛል። አፍሬ ከማልቀስ ወደኋላ አላልኩም።” (ሮም 12:15ን ተመልከቱ።) እናንተም ብትሆኑ ማልቀሳችሁ ሊያሳፍራችሁ አይገባም። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ጨምሮ ምንም ዓይነት ኀፍረት ሳይሰማቸው ሐዘናቸውን በለቅሶ ስለገለጹ የእምነት ሰዎች ይናገራል።—ዘፍጥረት 50:3፤ 2 ሳሙኤል 1:11, 12፤ ዮሐንስ 11:33, 35
ለተወሰነ ጊዜ ስሜታችሁ እየተለዋወጠ ሊያስቸግራችሁ ይችላል። እንባችሁ ሳታስቡት በድንገት ሊፈስ ይችላል። ባሏ የሞተባት አንዲት ሴት ዕቃ ለመግዛት ወደ ገበያ አዳራሽ ስትሄድ (ብዙ ጊዜ የምትሄደው ከባሏ ጋር ነበር) በተለይ ደግሞ ባሏ ይወዳቸው የነበሩትን የምግብ ዓይነቶች እንደ ልማዷ ለማንሳት ሲቃጣት እንባዋን መቆጣጠር ያቅታት ነበር። ራሳችሁን ታገሡ። እንባችሁን መቆጣጠር እንደሚገባችሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ማልቀስ የውስጥ ሐዘን የሚገለጽበት አስፈላጊና ተፈጥሯዊ መንገድ እንደሆነ አስታውሱ።
የጥፋተኝነት ስሜትን መቋቋም
ቀደም ብሎ እንደተገለጸው አንዳንዶች፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ካጡ በኋላ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ታማኝ ሰው የነበረው ያዕቆብ፣ ልጁ ዮሴፍ “ኃይለኛ አውሬ በልቶት” እንደሞተ ባሰበ ጊዜ አምርሮ ያዘነው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ዮሴፍ የወንድሞቹን ደህንነት አይቶ እንዲመጣ የላከው ያዕቆብ ራሱ ነበር። በዚህም ምክንያት ‘ዮሴፍን ለምን ብቻውን ላክሁት? አራዊት ወደሚበዙበት አካባቢ የላክሁት ለምንድን ነው?’ ብሎ እያሰበ በጥፋተኝነት ስሜት ሳይሠቃይ አልቀረም።—ዘፍጥረት 37:33-35
ምናልባት የምትወዱትን ሰው ለሞት ያደረሰው የእናንተ ቸልተኝነት እንደሆነ ይሰማችሁ ይሆናል። ይህ ዓይነቱ የጥፋተኝነት ስሜት በእውነታ ላይ የተመሠረተ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፤ ሆኖም ሐዘን የደረሰበት ሰው እንዲህ የሚሰማው መሆኑ አዲስ ነገር እንዳልሆነ መገንዘባችሁ በራሱ ሊረዳችሁ ይችላል። እንዲህ ያለውን ስሜትም ቢሆን አምቃችሁ መያዝ አይኖርባችሁም። ምን ያህል የበደለኝነት ስሜት እንደሚሰማችሁ ለሌሎች መናገራችሁ ሐዘናችሁ እንዲወጣላችሁ ይረዳችኋል።
ይሁን እንጂ አንድን ሰው ምንም ያህል ብንወደው ሕይወቱን ልንቆጣጠርለት እንደማንችል ወይም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” እንዳያጋጥሙት መከላከል እንደማንችል መገንዘብ ይኖርብናል። (መክብብ 9:11) ከዚህም ሌላ ሟቹን ለመጉዳት ብላችሁ ያደረጋችሁት ነገር እንደሌለ ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ የምትወዱትን ሰው ቀደም ብላችሁ ሐኪም ቤት ያልወሰዳችሁት ሕመሙ ጠንቶበት እንዲሞት ፈልጋችሁ ነው? በፍጹም አይደለም! ታዲያ ለዚህ ሰው መሞት ምክንያት ሆናችኋል ማለት ይቻላል? በጭራሽ።
አንዲት እናት ልጇ በመኪና አደጋ ከሞተች በኋላ የተሰማትን የበደለኝነት ስሜት እንዴት መቋቋም እንደቻለች እንደሚከተለው በማለት ገልጻለች፦ “የላክኋት እኔ ስለነበርኩ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰቤ ምክንያታዊ እንዳልሆነ እያደር ተገነዘብኩ። ከአባቷ ጋር ሆና አንድ ጉዳይ እንድታስፈጽምልኝ መላኬ ምንም ስህተት የለውም። የሞተችው ድንገት በተከሰተ አደጋ ነው።”
ይሁን እንጂ ‘እንዲህ ብዬ ወይም እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ሆኖም ከመካከላችን ፍጹም አባት ወይም ፍጹም እናት ወይም ፍጹም ልጅ የሆነ ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለንና። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው . . . ፍጹም ሰው ነው” ይላል። (ያዕቆብ 3:2፤ ሮም 5:12) ስለዚህ ፍጹም አለመሆናችሁን አትርሱ። “እንዲህ ቢሆን ኖሮ” እያሉ የተለያዩ ሐሳቦችን ማውጠንጠን ከሐዘናችሁ ቶሎ እንዳትጽናኑ ከማድረግ በስተቀር አንዳች የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።
የሚሰማችሁ የጥፋተኝነት ስሜት በሐሳባችሁ የፈጠራችሁት ሳይሆን ትክክለኛ እንደሆነ የምታምኑበት በቂ ምክንያት ካላችሁ፣ የጥፋተኝነት ስሜታችሁ ቀለል እንዲልላችሁ የሚረዳችሁ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር እንዳለ አስታውሱ። ይህም የአምላክ ይቅርታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ማን ሊቆም ይችል ነበር? በአንተ ዘንድ በእርግጥ ይቅርታ አለና” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝሙር 130:3, 4) ያለፈውን ጊዜ ልትመልሱትም ሆነ ምንም ነገር ልትለውጡ አትችሉም። ቀደም ሲል ለፈጸማችሁት ስህተት አምላክ ይቅርታ እንዲያደርግላችሁ ልትለምኑት ግን ትችላላችሁ። ከዚያስ በኋላ? አምላክ ስህተታችሁን ፈጽሞ ይቅር እንደሚላችሁ ቃል ከገባላችሁ እናንተስ ራሳችሁን ይቅር ልትሉ አይገባችሁም?—ምሳሌ 28:13፤ 1 ዮሐንስ 1:9
የቁጣ ስሜትን መቋቋም
በሐኪሞች፣ በነርሶች፣ በወዳጆች አሊያም በሟቹ ላይ ተቆጥታችኋል? ይህም ቢሆን የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለው የተለመደ ስሜት መሆኑን ተገንዘቡ። ምናልባት የተቆጣችሁት ስሜታችሁ በእጅጉ ስለተጎዳ ሊሆን ይችላል። አንድ ደራሲ “ቁጣችሁ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ማስቀረት የምትችሉት፣ በቁጣ ተነሳስታችሁ እርምጃ በመውሰድ ሳይሆን እንደተቆጣችሁ በመገንዘብ ብቻ ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም ቁጣችሁን መግለጽ ወይም ስሜታችሁን ለሌላ ሰው ማካፈል ሊረዳችሁ ይችላል። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ሌሎች ላይ በመጮህ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለረጅም ጊዜ ታምቆ የሚቆይ ቁጣ አደገኛ እንደሆነ ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 14:29, 30) ይሁን እንጂ ስሜታችሁን ሊረዳላችሁ ከሚችል ወዳጃችሁ ጋር ብትወያዩ ልትጽናኑ ትችላላችሁ። አንዳንዶች ደግሞ የቁጣ ስሜት ሲሰማቸው ጠንከር ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ቀለል እንዲላቸው ያደርጋል።—በተጨማሪም ኤፌሶን 4:25, 26ን ተመልከቱ።
ስሜታችሁን በግልጽና በሐቀኝነት መግለጽ አስፈላጊ ቢሆንም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ስሜታችሁን ለሌሎች በመግለጽና በሌሎች ላይ የቁጣ ውርጅብኝ በማውረድ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ለሚሰማችሁ የቁጣ ስሜትና ብስጭት መንስኤው ሌሎች እንደሆኑ መግለጽ አስፈላጊ አይደለም። ስሜታችሁን ለሌሎች መግለጽ ተገቢ ቢሆንም በቁጣና በኃይለ ቃል መሆን የለበትም። (ምሳሌ 18:21) የሐዘን ስሜትን ለመቋቋም የሚያስችል አንድ ትልቅ እርዳታ አለ፤ ቀጥለን ይህን እንመለከታለን።
ከአምላክ የሚገኝ እርዳታ
መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል” የሚል ዋስትና ይሰጠናል። (መዝሙር 34:18) አዎ፣ የምትወዱት ሰው ሲሞትባችሁ ከምንም ነገር ይበልጥ እንድትጽናኑ የሚያስችላችሁ ከአምላክ ጋር ያላችሁ ዝምድና ነው። እንዴት? እስካሁን ድረስ የተዘረዘሩት ጠቃሚ ምክሮች በሙሉ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት መመሪያዎች ጋር የሚስማሙ ናቸው። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላችሁ ሊረዳችሁ ይችላል።
ከዚህም በላይ ጸሎት ያለውን ጥቅም አቅልላችሁ አትመልከቱት። መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል” ሲል ይመክረናል። (መዝሙር 55:22) የውስጥ ስሜታችሁን በአዘኔታ ለሚያዳምጣችሁ ሰው ማወያየታችሁ ሊረዳችሁ ከቻለ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ለሆነው አባታችን የልባችሁን ማፍሰሳችሁ ምን ያህል አብልጦ ይረዳችሁ!—2 ቆሮንቶስ 1:3
ጸሎት፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ከመርዳት ያለፈ ጥቅም አለው። “ጸሎት ሰሚ” የሆነው አምላክ ከልብ ለሚለምኑት አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 65:2፤ ሉቃስ 11:13) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም በሥራ ላይ ያለው ኃይሉ ደግሞ አንዱን ቀን አልፋችሁ ወደሚቀጥለው ቀን እንድትሻገሩ የሚያስችላችሁን “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጣችኋል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ዓይነት ችግር በጽናት እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው እንደሚችል አስታውሱ።
ልጇን በሞት ያጣች አንዲት ሴት፣ ጸሎት እሷና ባሏ የደረሰባቸውን ሐዘን እንዲቋቋሙ እንዴት እንደረዳቸው ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ማታ ማታ ቤታችን በምንሆንበት ጊዜ ሐዘኑ በጣም ሲከብደን ድምፃችንን ከፍ አድርገን አብረን እንጸልያለን። እሷ በሌለችበት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የጉባኤ ስብሰባ እና ትልቅ ስብሰባ ላይ ስንገኝ እንዲሁም እሷ ሳትኖር ለመጀመሪያ ጊዜ የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር በምናከናውንበት ጊዜ ሁሉ አምላክ ብርታት እንዲሰጠን እንጸልይ ነበር። ማለዳ ተነስተን፣ ከልጃችን መነጠላችንን እያሰብን በጣም በምናዝንበት ጊዜ ይሖዋ እንዲረዳን እንጸልይ ነበር። ምክንያቱ በግልጽ ባይገባኝም ወደ ቤታችን ብቻዬን በምገባበት ጊዜ ከባድ ሐዘን ይሰማኛል። ስለዚህ ብቻዬን ቤት በምመለስበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ለመረጋጋት እንዲረዳኝ እጸልይ ነበር።” ይህች ታማኝ ሴት ጸሎት በጣም እንደረዳት አጥብቃ ታምናለች። እናንተም አዘውትራችሁ የምትጸልዩ ከሆነ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ ሮም 12:12
አምላክ የሚሰጠው እርዳታ በስሜታችሁ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማጽናናት እንድንችል [አምላክ] በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል” ብሏል። መለኮታዊው እርዳታ፣ በሐዘናችሁ ምክንያት የሚሰማችሁን ሥቃይ ባያስወግድላችሁም ሐዘኑን መቋቋም እንድትችሉ ይረዳችኋል። ይህ ሲባል ግን የሐዘን እንባ ማንባታችሁን ታቆማላችሁ ወይም የምትወዱትን ሰው ትረሱታላችሁ ማለት አይደለም፤ ሆኖም ከሐዘናችሁ ልትጽናኑ ትችላላችሁ። እየተጽናናችሁ ስትሄዱ ደግሞ በእናንተ ላይ የደረሰው ነገር፣ እንደ እናንተ ሐዘን የደረሰባቸውን ሌሎች ሰዎች ራሳችሁን በእነሱ ቦታ አስቀምጣችሁ ለመርዳት ያስችላችኋል።—2 ቆሮንቶስ 1:4