እንዲህ የሚሰማኝ የጤና ነው?
ሐዘን የደረሰበት አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ያደግሁት እንግሊዝ ውስጥ በመሆኑ በሰዎች ፊት ስሜቴን አውጥቼ እንዳልገልጽ ከልጅነቴ ጀምሮ ይነገረኝ ነበር። ወታደር የነበረው አባቴ አንድ ነገር ባሳመመኝ ጊዜ ኮስተር ብሎ ‘እንዳታለቅስ!’ እንዳለኝ ዛሬም ድረስ ትዝ ይለኛል። እናቴ፣ እኔንም ሆነ ወንድሞቼንና እህቶቼን (በቤታችን ውስጥ አራት ልጆች ነበርን) እቅፍ አድርጋ የሳመችበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። አባቴ ሲሞት 56 ዓመቴ ነበር። አባቴን በማጣቴ በጣም ባዝንም መጀመሪያ ላይ ማልቀስ አልቻልኩም።”
በአንዳንድ ባሕሎች ሰዎች ስሜታቸውን ያላንዳች ገደብ ይገልጻሉ። ማዘናቸውንም ሆነ መደሰታቸውን ሌሎች ሰዎች ማወቅ ይችላሉ። በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ግን (ይበልጥ ደግሞ በሰሜን አውሮፓና በብሪታንያ) ሰዎች፣ በተለይ ወንዶች ስሜታቸውን ዋጥ እንዲያደርጉ፣ ጥርሳቸውን ነክሰው ዝም እንዲሉና ሐዘናቸውንም ሆነ ደስታቸውን እንዲደብቁ ተደርገው ያድጋሉ። ይሁን እንጂ በጣም የምትወዱት ሰው በሞት ቢለያችሁ ሐዘናችሁን መግለጽ ስህተት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳለቀሱ የተገለጹ ሰዎች
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በምሥራቃዊ ሜድትራንያን አካባቢ ይኖሩ በነበሩ ዕብራዊ የሆኑ ሰዎች ነው፤ እነዚህ ሰዎች ውስጣዊ ስሜታቸውን በደንብ ይገልጹ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ሐዘናቸውን በግልጽ ያሳዩ ብዙ ሰዎችን ይጠቅሳል። ንጉሥ ዳዊት፣ ልጁ አምኖን በመገደሉ በእጅጉ አዝኗል። እንዲያውም ‘አምርሮ አልቅሷል።’ (2 ሳሙኤል 13:28-39) ዳዊት፣ ንግሥናውን ሊቀማው ሞክሮ የነበረው ከሃዲ ልጁ አቢሴሎም በሞተ ጊዜ እንኳ አልቅሷል። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል፦ “ይህም ንጉሡን [ዳዊትን] ረበሸው፤ በውጭው በር ሰገነት ላይ ወዳለው ክፍልም ወጥቶ አለቀሰ፤ ወዲያ ወዲህ እያለም ‘ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ፣ ልጄ አቢሴሎም! ምነው በአንተ ፋንታ እኔ በሞትኩ፤ ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ!’ ይል ነበር።” (2 ሳሙኤል 18:33) ዳዊት እንደ ማንኛውም አባት አዝኗል። ወላጆች ‘በልጄ ፋንታ እኔ በሞትኩ’ ብለው መመኘታቸው የተለመደ ነገር ነው። ገና በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ከወላጆቹ ቀድሞ መሞቱን መቀበል በጣም ያዳግታል።
ኢየሱስ፣ ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ምን ተሰማው? ወደ መቃብሩ ሲቃረብ አልቅሷል። (ዮሐንስ 11:30-38) ከጊዜ በኋላ ደግሞ መግደላዊት ማርያም ወደ ኢየሱስ መቃብር በቀረበች ጊዜ አልቅሳለች። (ዮሐንስ 20:11-16) በእርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የትንሣኤ ተስፋ የሚያውቅ አንድ ክርስቲያን፣ ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ ስለሚያምኑበት ነገር ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እንደሌላቸው ሰዎች መጽናናት እስከማይችል ድረስ አያዝንም። ይሁን እንጂ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን የትንሣኤ ተስፋ ቢኖረውም፣ ሰው እንደመሆኑ መጠን የሚወደው ሰው ሲሞትበት ያዝናል እንዲሁም ያለቅሳል።—1 ተሰሎንቄ 4:13, 14
ማልቀስ ወይስ አለማልቀስ?
በዛሬው ጊዜስ? ስሜታችሁን አውጥታችሁ መግለጽ ያስቸግራችኋል ወይም ያሳፍራችኋል? በዚህ ረገድ አንዳንድ አማካሪዎች ምን ይላሉ? ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት፣ ከዘመናት በፊት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ የሚያስተጋባ ነው። ባለሙያዎች፣ ሐዘናችንን ማውጣት እንጂ ማፈን ወይም ለመደበቅ መሞከር እንደማይገባን ይናገራሉ። ይህም እንዳዘኑና እንዳለቀሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን እንደ ኢዮብ፣ ዳዊትና ኤርምያስ ያሉትን የጥንት ታማኝ ሰዎች ያስታውሰናል። እነዚህ ሰዎች ስሜታቸውን አምቀው አልያዙም። ስለዚህ ራሳችሁን ከሰዎች ማግለል ጥበብ አይደለም። (ምሳሌ 18:1) እርግጥ፣ ሐዘን የሚገለጽበት መንገድ እንደየባሕሉና በአካባቢው ተስፋፍቶ እንደሚገኘው ሃይማኖታዊ እምነት ይለያያል። *
ማልቀስ ካስፈለጋችሁስ? ማልቀስ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። አልዓዛር በሞተ ጊዜ ኢየሱስ ‘እጅግ እንዳዘነና እንባውን እንዳፈሰሰ’ እናስታውስ። (ዮሐንስ 11:33, 35) ኢየሱስ ይህን ማድረጉ፣ የሚወዱት ሰው ሲሞት ማልቀስ እንግዳ ነገር አለመሆኑን የሚያሳይ ነው።
አን የተባለችው እናት ያጋጠማት ሁኔታ ይህን ሐሳብ ይደግፋል፤ ይህች እናት ሪቸል የተባለች ሕፃን ልጇን በሰደን ኢንፋንት ዴዝ ሲንድሮም (ድንገተኛ የጨቅላ ሕፃናት ሞት) አጥታለች። ባሏ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የሚያስገርመው ነገር በቀብሩ ላይ እኔም ሆንኩ አን አላለቀስንም። ሌላው ሰው ሁሉ ያለቅስ ነበር።” አንም አክላ እንዲህ ብላለች፦ “አዎ፣ በኋላ ላይ ግን ለሁለታችንም የሚበቃ ለቅሶ አልቅሻለሁ። የሐዘኑ ክብደት በጣም የተሰማኝ፣ ልጄ ከሞተች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ብቻዬን ቤት ውስጥ በነበርኩበት ቀን ይመስለኛል። የዚያን ዕለት፣ ሙሉ ቀን አለቀስኩ። ማልቀሴ እንደረዳኝ አምናለሁ። ከዚያ በኋላ ቀለል አለኝ። ልጄን በማጣቴ ማልቀስ ነበረብኝ። ልባቸው በሐዘን የተሰበረ ሰዎች እንዲያለቅሱ ሊፈቀድላቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። ሌሎች ‘አታልቅስ’ ማለታቸው የተለመደ ነገር ቢሆንም ይህ በምንም መንገድ አይረዳም።”
አንዳንዶች ምን ተሰምቷቸዋል?
አንዳንዶች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ ምን ተሰምቷቸዋል? ለምሳሌ ያህል፣ የኹዋኒታን ሁኔታ እንመልከት። ሕፃን ልጅን ማጣት ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥር ታውቃለች። አምስት ጊዜ አስወርዷት ነበር። አሁን እንደገና አረገዘች። ስለዚህ በመኪና አደጋ ምክንያት ሆስፒታል ስትገባ በጣም ተጨነቀች። ከሁለት ሳምንት በኋላ፣ የመውለጃ ጊዜዋ ከመድረሱ በፊት ምጥ ያዛት። ብዙም ሳይቆይ አንድ ኪሎ ግራም የማትሞላ ቫኔሳ የተባለች ልጅ ተወለደች። “በጣም ተደስቼ ነበር” በማለት ኹዋኒታ ታስታውሳለች። “አሁን በመጨረሻ እናት ሆንኩ!”
ይሁን እንጂ ደስታዋ በአጭሩ ተቀጨ። ከአራት ቀን በኋላ ቫኔሳ ሞተች። ኹዋኒታ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “የባዶነት ስሜት ተሰማኝ። በድንገት እናትነቴን ተነጠቅኩ። ጎዶሎ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ቤት ተመልሼ ለቫኔሳ ያዘጋጀነውን ክፍልና የገዛሁላትን ትናንሽ ካናቴራዎች
ስመለከት እጅግ አዘንኩ። ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት፣ የተወለደችበትን ቀን እያሰብኩ እተክዝ ነበር። ከማንም ጋር መገናኘት አልፈለግሁም።”ይህ ከመጠን ያለፈ ሐዘን ነው? ሌሎች ሁኔታውን መረዳት ያስቸግራቸው ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ያለ ሐዘን የደረሰባቸው እንደ ኹዋኒታ ያሉ ሰዎች እንደሚናገሩት በሕፃኑ ሞት የተሰማቸው ሐዘን፣ ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት ኖሮ ለሞተ ሰው ከሚሰማቸው ሐዘን ያላነሰ ነው። ወላጆች፣ ሕፃን ልጃቸውን መውደድ የሚጀምሩት ገና ከመወለዱ በፊት እንደሆነ ይናገራሉ። ሕፃኑ ከእናቲቱ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና አለው። ሕፃኑ በሚሞትበት ጊዜ እናቲቱ የሚሰማት፣ አንድ ሙሉ ሰው በሞት የተለያት ያህል ነው። ሌሎች መረዳት የሚኖርባቸው ይህንን ነው።
ቁጣና የጥፋተኝነት ስሜት ተጽዕኖ ሊያሳድርባችሁ የሚችለው እንዴት ነው?
አንዲት ሌላ እናት ደግሞ ስድስት ዓመት የሆነው ልጇ፣ ሲወለድ ጀምሮ በነበረበት የልብ ሕመም ምክንያት በድንገት እንደሞተ ሲነገራት ምን እንደተሰማት እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “የተመሰቃቀለ ስሜት ተሰማኝ። የመደንዘዝ፣ ነገሩን ያለማመን፣ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ፤ እንዲሁም የልጄ ሕመም ምን ያህል ከባድ መሆኑን ሳይገነዘቡ በመቅረታቸው በባለቤቴና በዶክተሩ ተናደድኩ።”
ሐዘን የሚገለጽበት አንዱ መንገድ ቁጣ ሊሆን ይችላል። የሚወደውን ሰው በሞት ያጣው ግለሰብ፣ ሐኪሞችና ነርሶች ለሟቹ የሚገባውን እንክብካቤና ሕክምና እንዳላደረጉ በማሰብ ይናደድ ይሆናል። አሊያም ወዳጆችና ዘመዶች አግባብ ያልሆነ ነገር እንደሚናገሩ ወይም እንደሚያደርጉ ስለሚሰማው በእነሱ ላይ ሊቆጣ ይችላል። አንዳንዶች፣ ሟቹ ለጤንነቱ ተገቢ ጥንቃቄ ባለማድረጉ ይናደዳሉ። ስቴላ “ባለቤቴ ይበልጥ ጥንቃቄ ቢያደርግ ኖሮ እንደማይሞት አውቅ ስለነበር በእሱ ላይ አምርሬ መቆጣቴ ትዝ ይለኛል። በጣም ታሞ እያለ ሐኪሞች የሰጡትን ማስጠንቀቂያ አልሰማም ነበር” ብላለች። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሕይወት ያሉት ሰዎች፣ ሟቹ በሞት ማንቀላፋቱ ተጨማሪ ሸክም ስለሚያስከትልባቸው ይናደዳሉ።
አንዳንዶች፣ በመቆጣታቸው ምክንያት የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል፤ በሌላ አባባል የቁጣ ስሜት ስለተሰማቸው ራሳቸውን ይኮንናሉ። ሌሎች ደግሞ የሚወዱት ሰው የሞተው በእነሱ ጥፋት እንደሆነ በማሰብ ራሳቸውን ይወቅሳሉ። “ቶሎ ሐኪም ቤት እንዲሄድ ባደርገው ኖሮ” ወይም “ሌላ ሐኪም እንዲያየው ባደርግ ኖሮ” ወይም “ጤንነቱን በሚገባ እንዲንከባከብ ብረዳው ኖሮ አይሞትም ነበር” እያሉ ራሳቸውን ይወቅሳሉ።
አንዳንዶች፣ በተለይ የሚወዱት ሰው የሞተባቸው ሳያስቡት በድንገት ከሆነ የሚሰማቸው የጥፋተኝነት ስሜት
ከዚህም አልፎ ይሄዳል። ከሟቹ ጋር የተጨቃጨቁበትን ወይም በእሱ ላይ የተቆጡበትን ጊዜ ማስታወስ ይጀምራሉ። አሊያም ለሟቹ የሚገባውን ሁሉ እንዳላደረጉለት ይሰማቸዋል።የብዙ እናቶች ሐዘን ለረጅም ጊዜ የሚቆይ መሆኑ፣ የልጅ ሞት በወላጆች ላይ በተለይም በእናቲቱ ላይ የማይሽር ሐዘን ጥሎ እንደሚያልፍ በርካታ ባለሙያዎች የሚናገሩት ሐሳብ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል።
የትዳር ጓደኛ ሲሞትባችሁ
የትዳር ጓደኛ በተለይ ብዙ ነገር አብሮ ያሳለፈ የትዳር ጓደኛ ሲሞት ከባድ ሐዘን ያስከትላል። ባለትዳሮቹ አብረው በመጓዝ፣ በመሥራት፣ በመዝናናት ብሎም እርስ በርስ በመረዳዳት የሚያሳልፉት ሕይወት ያበቃል ማለት ነው።
ዩኒስ ባሏ በልብ ድካም ምክንያት በድንገት ሲሞት ምን እንደተሰማት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በመጀመሪያው ሳምንት፣ መላ ሰውነቴ ሥራውን ያቆመ ይመስል ድንዝዝ ብዬ ነበር። መቅመስም ሆነ ማሽተት እንኳ ተስኖኝ ነበር። አእምሮዬ ግን ከቀረው ሰውነቴ እንደተነጠለ ያህል ሆኖ በሐሳብ ይብከነከን ነበር። ሐኪሞች በሲ ፒ አር [ካርዲዮፐልሙነሪ ሪሰሲቴሽን] እና በመድኃኒቶች ሕይወቱን ለማቆየት በሚጥሩበት ጊዜ አብሬው ስለነበርኩ ብዙዎች እንደሚያጋጥማቸው መሞቱን ለማመን አልተቸገርኩም። ያም ቢሆን አንድ መኪና ከገደል አፋፍ ወድቆ ሊከሰከስ ሲል ምንም ማድረግ በማልችልበት
ሁኔታ ላይ ሆኜ ብመለከት የሚሰማኝ ዓይነት ከፍተኛ ሐዘንና ብስጭት ተሰምቶኝ ነበር።”ይህች ሴት አልቅሳ ነበር? “አዎ፣ በደንብ አለቀስኩ። በተለይ የተላኩልኝን በርካታ የሐዘን መግለጫ ካርዶች በማነብበት ጊዜ አለቅስ ነበር። እያንዳንዱን ካርድ ባነበብኩ ቁጥር አለቅስ ነበር። ይህን ማድረጌ በቀሪው ቀን ሐዘኔን መቋቋም እንድችል ረድቶኛል። ሰዎች ‘እንዴት ይሰማሻል?’ እያሉ ያቀርቡልኝ የነበረው ተደጋጋሚ ጥያቄ ግን ምንም የሚፈይድልኝ ነገር አልነበረም። በጣም እንዳዘንኩ ግልጽ ነበር” ብላለች።
ዩኒስ ከሐዘኗ እንድትጽናና የረዳት ምን ነበር? “አስቤበት ባይሆንም፣ ኑሮዬን መቀጠል አለብኝ ብዬ ወሰንኩ” ብላለች። “ይሁን እንጂ ሕይወትን በጣም ይወድ የነበረው ባለቤቴ አብሮኝ አለመሆኑና መኖር የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም አለመቻሉ አሁንም ቢሆን በእጅጉ ያሳዝነኛል።”
“ሌሎች እንዲነግሯችሁ አትፍቀዱ”
ሊቭቴኪንግ—ዌን ኤንድ ሃው ቱ ሴይ ጉድባይ የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች እንደሚከተለው በማለት ይመክራሉ፦ “ምን ልታደርጉና ምን ሊሰማችሁ እንደሚገባ ሌሎች እንዲነግሯችሁ አትፍቀዱ። አንድ ሰው ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ ከሌላው ይለያል። አንዳንዶች፣ ሐዘናችሁ ከመጠን ያለፈ እንደሆነ ወይም በተገቢው መንገድ እያዘናችሁ እንዳልሆነ ሊሰማቸውና ይህን ስሜታቸውንም ሊያሳውቋችሁ ይችላሉ። ይህን ስላሏችሁ አትዘኑባቸው፤ የነገሯችሁን ግን እርሱት። ራሳችሁን አስገድዳችሁ፣ ሌሎች ሰዎች ወይም ማኅበረሰቡ በሚፈልገው መንገድ ለማዘን መሞከራችሁ ስሜታችሁን ለማረጋጋት በምታደርጉት ጥረት ረገድ እንቅፋት ይፈጥርባችኋል።”
እርግጥ እያንዳንዱ ሰው ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ ሊለያይ ይችላል። ለሁሉም ሰው የሚሆን መንገድ ለመጠቆም መሞከራችን አይደለም። ይሁን እንጂ ያዘነው ሰው፣ የተፈጠረውን ሁኔታ መቀበል ሲያቅተው አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ጊዜ ሩኅሩኅ የሆኑ ወዳጆች እርዳታ ያስፈልገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው” ይላል። ስለዚህ ሐዘን ከደረሰባችሁ የሌሎችን እርዳታ ለመጠየቅ፣ ሰዎችን ለማናገርና ለማልቀስ አትፍሩ።—ምሳሌ 17:17
ሐዘን፣ አንድን ነገር ማጣት የሚያስከትለው ጤናማ ስሜት ስለሆነ ማዘናችሁ ለሌሎች ግልጽ ሆኖ ቢታይ ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ ‘ከሐዘኔ ልጽናና የምችለው እንዴት ነው? የጥፋተኝነትና የብስጭት ስሜት የሚሰማኝ በጤና ነው? እነዚህን ስሜቶች እንዴት ላሸንፍ እችላለሁ? የምወደውን ሰው በሞት ማጣቴ የፈጠረብኝን ስሜትም ሆነ ሐዘኑን ለመቋቋም ምን ሊረዳኝ ይችላል?’ የሚሉት ተጨማሪ ጥያቄዎች መልስ ያስፈልጋቸዋል። የሚቀጥለው ክፍል ለእነዚህና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
^ አን.8 ለምሳሌ ያህል፣ በናይጄሪያ የሚኖሩት የዮሩባ ጎሣ አባላት ነፍስ ሌላ ሥጋ ለብሳ ትመለሳለች የሚል ባሕላዊ እምነት አላቸው። በዚህም ምክንያት አንዲት እናት ልጅ ሲሞትባት የመረረ ሐዘን የሚሰማት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። “ውኃው ተደፋ እንጂ ቅሉ አልተሰበረም” የሚል የተለመደ የዮሩባዎች አባባል አለ። በዮሩባዎች እምነት መሠረት፣ የውኃ መያዣ የሆነው ቅል ማለትም እናቲቱ ሌላ ልጅ ልትወልድ (ምናልባትም የሞተውን ልጅ በሌላ አካል እንደገና ልትወልደው) ትችላለች። የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸውን ‘ነፍስ አትሞትም’ ወይም ‘ነፍስ ሌላ አካል ለብሳ ትመለሳለች’ ከሚሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች የመነጩትን ወጎችና አጉል እምነቶች አይከተሉም።—መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4, 20
^ አን.61 አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ እስከ ስድስት ወር ዕድሜ የሚገኙ ሕፃናትን የሚያጠቃው ሰደን ኢንፋንት ዴዝ ሲንድሮም (ኤስ አይ ዲ ኤስ)፣ ጤነኛ የሆኑ ሕፃናት ባልታወቀ ምክንያት ድንገት መሞታቸውን ለመግለጽ የሚሠራበት ስያሜ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ሕፃኑ በሆዱ ሳይሆን በጀርባው ወይም በጎኑ ቢተኛ ይህ አደጋ እንደማይደርስበት ይታመናል። ይሁን እንጂ ኤስ አይ ዲ ኤስን ሙሉ በሙሉ ሊከላከል የሚችል አስተኛኘት የለም።