በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” የተገኘው የእውቀት ብርሃን

ስለ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” የተገኘው የእውቀት ብርሃን

ምዕራፍ 5

ስለ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” የተገኘው የእውቀት ብርሃን

1. “የሰላሙ መስፍን” በዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ስለሚከናወን ስለ የትኛው የላቀ ጋብቻ ትንቢት ተናገረ? በየትኛውስ ምሳሌ ላይ?

“የነገሮችን ሥርዓት ፍጻሜ” በሚመለከት ‘የሰላሙ መስፍን’ በማቴዎስ 24:38 ላይ ‘ወንዶች እንደሚያገቡና ሴቶችም እንደሚዳሩ’ ተናግሯል። ይሁን እንጂ በዚያኑ ጊዜ በሰማይ ከሁሉ የላቀ ብልጫ ያለው ጋብቻ ይጀምራል። ይህም ኢየሱስ መብራት ስለያዙ አሥር ደናግል በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ጋብቻ ነው። — ማቴዎስ 24:3፤ 25:1–12

2. (ሀ) ይህ ምሳሌያዊ የሆነ ጋብቻ የተከናወነው በየትኛው የቀኑ ክፍል ላይ ነው? (ለ) ከጋብቻው ሥነ ሥርዓት በኋላ ምን ይከተላል? ብርሃን ይገኝ የነበረውስ እንዴት ነበር?

2 ይህ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የሚደረገው በመካከለኛው ምሥራቅ ነው። ሥርዓቱ የሚከናወነውም ወደ እኩለ ሌሊት ሊጠጋ አቅራቢያ በጣም ከመሸ በኋላ ነበር። በመጀመሪያ የሙሽራይቱና የሙሽራው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ይከናወንና ወደ ሰርጉ ቤት የሚደረገው ጉዞ ይቀጥላል። በመንገዱ ላይ የመንገድ መብራቶች አልነበሩም። በበዓሉ ጉዞ የሚካፈሉት ሰዎች መብራት ያዘጋጁ ነበር፣ ተመልካቾችም ለአዲሶቹ ተጋቢዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ጉዞው ሲደረግ ቆመው ሊመለከቱ ይችሉ ነበር።

3, 4. (ሀ) በማጀቡ ጉዞ ለመሳተፍ ፍላጐትን ያሳዩት እነማን ናቸው? ከምንስ ዝግጅቶች ጋር? (ለ) የዚህ ምሳሌ መፈጸም ለየትኛው ሁኔታ ማረጋገጫ ይጨምርለታል? (ሐ) ደስተኞች ለመሆን የምንችለው ምን ብናደርግ ነው?

3 ባላቸው ተፈጥሮአዊ የሴትነት ዝንባሌ ቆነጃጅት የሰርግ ነገር ይስባቸዋል። ስለዚህ ጉዞው በሚደረግበት መንገድ ላይ አሥር ቆነጃጅት ሰርገኛው እነርሱ ወዳሉበት ቦታ እስከሚደርስ ድረስ እየጠበቁ ናቸው። እነርሱም በዓሉን ደማቅ ለማድረግ ይመኛሉ፤ በዚህም ምክንያት ሁሉም የተለኰሱ የእጅ መብራቶችን ይዘው መጥተዋል፤ ይሁን እንጂ ለመብራቱ የሚሆን መጠባበቂያ ዘይት የያዙት አምስቱ ብቻ ነበሩ። እነዚህ አምስቱ ቆነጃጅት ልባሞች ነበሩ። የዚህ ምሳሌ አፈጻጸም በአሁኑ ጊዜ ትኩረታችንን ሊስበው ይገባል፤ ምክንያቱም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አነጋገር ይህ ምሳሌ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ፍጻሜ ላይ እንዳለን በበለጠ ስለሚያረጋግጥ ነው። — ማቴዎስ 25:13

4 እኛም ልባሞች ከሆንና የዚህን ከጋብቻዎች ሁሉ የበለጠ ጋብቻ የመጨረሻ ሁኔታና ከሁኔታው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ገጽታዎች ካስተዋልን ደስተኞች ልንሆን እንችላለን! በዛሬው ጊዜ ወደ ሰርጉ ግብዣ እንዲገቡ ፈቃድ በማግኘት ሞገስ ያገኙት እነማን ናቸው? እኛስ እንኖርበት ይሆን? እስቲ እንመልከት!

5. በአሥሩ ቆነጃጅት መካከል ልዩነትን የፈጠረው ሁኔታ ምንድን ነው? ሙሽራው በዘገየበት ጊዜስ ምን ሆነ?

5 ኢየሱስ ስለ አሥሩ ቆነጃጅት የሰጠው ምሳሌ የሰውን ዘር ሁሉ ከሚባርከው የዓለም መንግሥት ይኸውም ‘ከመንግሥተ ሰማያት’ ጋር ግንኙነት አለው። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።” — ማቴዎስ 25:1–5

6. (ሀ) አሥሩ ቆነጃጅት ማንን ያመለክታሉ? (ለ) በምሳሌው ውስጥ ሙሽራይቱ ያልተጠቀሰችው ለምንድን ነው?

6 እነዚህ አሥር ቆነጃጅት ማንን ያመለክታሉ? እነርሱ የመንፈሳዊውን ሙሽራ የኢየሱስ ክርስቶስን የወደፊት ሙሽራ አባላትን ያመለክታሉ። በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ ሴቷ ሙሽራ አለመገለጿ በዚህ ምክንያት እንደሆነ አያጠራጥርም፤ እዚህ ላይ የታየው ሙሽራው ብቻ ነው። ስለዚህ ቆነጃጅቱ አንድን ሌላ ቡድን እንደሚያመለክቱ አድርገን በማሰብ ስለ ማብራሪያው ግራ ሊገባን አይገባም።

7. ሙሽራው ሙሽራዋን መጥቶ ለመውሰድ እንደዘገየ መስሎ የታያት በየትኛው ወቅት ላይ ነበር? ለምንስ?

7 የወደፊቶቹ የሙሽራይቱ ክፍል አባሎች ከሰማያዊው ሙሽራ ጋር በጋብቻ መተባበር ልክ እንደተጠበቀው “በተወሰነው የአሕዛብ ዘመን” መዝጊያ በ1914 ላይ አልተፈጸመም። (ሉቃስ 21:24) በመሠረቱ ምንም እንኳ በሰማያዊው መንግሥት ላይ የመገኘቱ ሁኔታ በ1914 ቢፈጸምም ለእነርሱ ሙሽራው ከመምጣት እንደዘገየ መስሎ ታይቷቸው ነበር። እነዚያ በሐዘን የተሞሉ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ዓመታት የቆነጃጅቱ ክፍል በደረሰባቸው ሁኔታ ምክንያት ልክ በጣም እንደጨለመ ሌሊት ሆነው ነበር።

8. (ሀ) በምሳሌያዊ አነጋገር በቆነጃጅቱ ላይ እንቅልፍ እንቅልፍ የማለትና የመተኛት ሁኔታ የደረሰው እንዴት ነበር? (ለ) ሙሽራው ወደ መቅደሱ የመጣው ለምን ዓላማ ነበር? ይህስ የሙሽራዋን ክፍል የሚያሳስበው ለምንድን ነው?

8 በምሳሌያዊ አነጋገር በቆነጃጅቱ በኩል እንቅልፍ እንቅልፍ የማለትና የመተኛት ሁኔታ ታየ። የሰውን ዘሮች ሁሉ ለመባረክ ስለሚመጣው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ለሕዝብ ሲደረግ የነበረው የምስራቹ ስብከት እንደቆመ ያህል ነበር። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት የመጨረሻው ዓመት አንስቶ በእነዚህ ምሳሌያዊ ቆነጃጅት ላይ ወሳኝ የሆነ የፍርድ ጊዜ ጀምሮ ነበር። ይህም የሆነው በመግዛት ላይ ያለው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መንፈሳዊ ቤተመቅደስ በመምጣቱ ነው። ወደዚያ እንደደረሰም ለይሖዋ አምላክ የቤተመቅደስ አገልግሎት ለማቅረብ የተሾሙትን ለማንጻት የፍርድ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ። (ሚልክያስ 3:1–3) እንደ ሰማያዊ ሙሽራ በመሆን አስቀድሞ ሞተው የነበሩትን ተቀባይነት ያገኙ የሙሽራ ክፍል አባሎች ወደ ራሱ ወደ ሰማይ ለመቀበል የሚገለጥበት ጊዜ ይህ ነበር።

9. የቆነጃጅቱ ክፍል ከነበሩበት የበድንነት ሁኔታ የሚነቍበት ጊዜ መቼ ነበር? ለምንስ?

9 ስምንቱ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትናንሽ ጽሑፎች ማኅበር ዋነኛ አባላት በ1919 ፍትሕ ከጎደለው እስር ከተለቀቁ በኋላ በምድር ላይ ገና በሕይወት ያሉት የቆነጃጅቱ ክፍል ከበድንነት የእንቅልፍ ሁኔታቸው የሚነሱበት ትክክለኛው ጊዜ ነበር። በመላው ምድር ላይ የእውቀት ብርሃን የማብራቱ ሥራ ከፊታቸው ይጠብቃቸው ነበር። መብራታቸውን አብርተው ወደ መንፈሳዊ መቅደሱ የመጣውን ሙሽራ የሚቀበሉበት ጊዜ ይህ ነበር። ይህም የሆነው ከሁሉም አሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች ከተራሮች ጫፍ በላይ ከፍ ከፍ ወዳለው ወደ “ይሖዋ ቤት” እንዲጎርፉ ሲባል ነው።— ኢሳይያስ 2:1–4

መብራታቸውን አዘጋጅተው መጠባበቅ

10. ልባሞቹ ቆነጃጅት በያዙት ማሰሮ ውስጥ የነበረው ዘይት ምንን ያመለክታል?

10 ከቆነጃጅቱ ክፍል ታማኞች የሆኑት በማሰሮአቸው ውስጥ ለመብራት የሚሆን መጠባበቂያ ዘይት ይዘው መጥተዋል። መብራታቸውን እንደገና ለመሙላት ምንም አልዘገዩም። እየነደደ ብርሃን ለመስጠት የሚያገለግለው ፈሳሽ የእውቀት ብርሃን ሰጭ የሆነውን የይሖዋን ቃልና መንፈስ ቅዱስን ያመለክታል። እንግዲያው ከልባሞቹ ቆነጃጅት ማሰሮዎች ውስጥ የተቀዳው ዘይት ምን ያመለክታል? በተጻፈው ቃሉ ላይ ብርሃንን እንዲፈነጥቅ ተቀማጭ ሆኖ የተዘጋጀላቸውን የይሖዋን መንፈስ መጠን ያመለክታል። የሙሽራው ደቀመዛሙርት የሆኑት በመንፈስ የተወለዱት ቅቡዓን ቀሪዎች ከጦርነቱ በኋላ ባለው ጊዜ ‘መንግሥተ ሰማያትን’ በሚመለከት በመላው ምድር ላይ ብርሃን የማብራቱን ሥራ ለመጀመር ዝግጁ በነበሩበት ጊዜ በውስጣቸው ይህ የመንፈስ መጠን ነበራቸው።

11. ዘይቱ የተቀመጠባቸው ምሳሌያዊ ማሰሮዎች ምን ነበሩ?

11 ማሰሮዎቹ ምሳሌያዊውን የመብራት ዘይት በውስጣቸው የያዙትን በምሳሌው ላይ የተገለፁትን ልባም ቆነጃጅት ያመለክታሉ። ይህም ሲባል የቆነጃጅቱ ክፍል በመንፈስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀቡት ገና ያን ጊዜ ነው ማለት አይደለም። ቆነጃጅቱ በመንፈሱ ራሳቸውን አይቀቡም። ይህንን የሚያደርገው እርሱ ነው!— ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:16–21

12. (ሀ) በልባሞቹ ቆነጃጅት ላይ የትኛው የኢዮኤል ትንቢት የሚፈጸምበት ጊዜ መጥቶ ነበር? (ለ) በመብራቶቻቸው ብርሃን እንዲያበሩ የሚያደርጉበት ጊዜ የደረሰው መቼ ነው?

12 ልባሞቹ ቆነጃጅት ስለ ‘መንግሥተ ሰማያት’ በዓለም ዙሪያ የእውቀት ብርሃን እንዲፈነጥቁ ለተሰጣቸው ሰፊ ሥራ ድጋፍ እንዲሆናቸው ኢዩኤል 2:28, 29 በእነርሱ ላይ ተፈጽሟል። እነዚህን ጥቅሶች ሐዋርያው ጴጥሮስ የጠቀሳቸው በሚከተለው መንገድ ነበር:- “እግዚአብሔር ይላል:- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራዕይ ያያሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ።” (ሥራ 2:17) ስለዚህም ከ1919 ጀምሮ ልባሞች የሆኑት የምሳሌያዊዎቹ የቆነጃጅት ክፍል የመብራት ዕቃቸውን መያዝ ማለትም ራሳቸውን ማዘጋጀት ነበረባቸው። ይህን ያደረጉት አሁንም ገና በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ላሉት ሁሉ ብርሃንን ለማብራት ነው። በአምላክ ቃልና መንፈስ እየተመሩ በሚከተሉት የሕይወት ጐዳና ምክንያት “በዓለም እንደ ብርሃን” ሆነዋል። (ፊልጵስዩስ 2:15) በዚህ ምክንያት ሙሽራው ሁሉም የሙሽራይቱ ክፍል አባሎች በምድር ላይ ከሞቱ በኋላ ወደ ራሱ ወደ ሰማያዊ መንግሥቱ ለመውሰድ ሲዘጋጅ የእርሱን ፈለግ መከተል ጀመሩ።— ማቴዎስ 5:14–16

የመንፈሳዊ ስንፍና ውጤቶች

13. ልባሞቹ ቆነጃጅት ሰነፎቹ ላቀረቡላቸው ልመና መልስ የሰጡት እንዴት ነው?

13 ከቆነጃጅቱ ክፍል የሆኑት ሰነፎችስ ምን ሆኑ? ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ሰነፎቹም ልባሞቹን:- መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።”— ማቴዎስ 25:8, 9

14. ዘይታቸውን ለማካፈል እምቢ ያሉት ቆነጃጅት ስስታሞች ሳይሆኑ ልባሞች የነበሩት ለምንድን ነው?

14 ዘይታቸውን ለሰነፎቹ ለማካፈል እምቢ ያሉት ልባሞች እንጂ ስስታሞች አልነበሩም። እነርሱም ለሙሽራው ሲሉ በዙሪያቸው ባለው ጨለማ ላይ ብርሃናቸውን ለማብራት የነበራቸውን የመልካም ምኞት መግለጫ የሆነውን የመጀመሪያውን ዓላማቸውን ለመፈጸም ባደረጉት ቁርጥ ውሳኔ መጽናታቸው ነበር። በመንፈሳዊ ሰነፎች የሆኑትን ለመርዳት ሲሉ ለራሳቸው የያዙትን የተወሰነ መጠን ያለውን የይሖዋ መንፈስ ለእነርሱ በማካፈል አቋማቸውን እንዲያላሉ በምንም መንገድ አይገደዱም። እንደነዚህ ያሉት ሰነፎች በ1919 ወደሚከፈቱት የአገልግሎት መብቶች ወዲያውኑ ለመግባት ራሳቸውን አላዘጋጁም ነበር።

15. (ሀ) የሰላሙ ጊዜ ሲጀምር ከቆነጃጅቱ መካከል የመንፈሳዊ ስንፍና ዝንባሌዎችን ማሳየት የጀመሩት እነማን ነበሩ? (ለ) ልባሞቹ ቆነጃጅት በመንፈሳዊ ሰነፍ የሆኑትን ቆነጃጅት ለመርዳት ያልቻሉት ለምንድን ነው?

15 የሰላሙ ወቅት በሚጀምርበት ጊዜ ራሳችንን ወስነን ተጠምቀናል ይሉ ከነበሩት ተባባሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ መንፈሳዊ ስንፍና ማሳየት ጀመሩ። ከመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዝዳንት ከቻርልስ ቴዝ ራስል ሞት በኋላ በአዲሱ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት በጄ. ኤፍ. ራዘርፎርድ ከሚመራው የይሖዋ አምላክ የሚታይ መሣሪያ ጋር በመሆን አዲስ ወደተፈጠሩት ሁኔታዎች መንፈስ ሳይገቡ ቀሩ። በእርግጥም ልባቸው ነገሮች እየተከናወኑ ካሉበት መንገድ ጋር የተስማማ አልነበረም። ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር ግንኙነት ለሚያደርግበት መንገድ አድናቆት እንደጎደላቸው አሳዩ። በዚህ ምክንያት ልባሞቹን ቆነጃጅት የሚመስሉት ደቀ መዛሙርት ራሳቸውን የበለጠ እያገለሉ በሄዱት በእነዚህ ሰነፎች ልብ ውስጥ ልባዊ የሆነ እውነተኛ የትብብር መንፈስ ለማስገባት አልቻሉም።

16. የሰነፎቹ ቆነጃጅት መንፈሳዊ ስንፍና ገሃድ መውጣት የጀመረው እንዴት ነበር?

16 በዚህ መንገድ መንፈሳዊው ስንፍናቸው ገሃድ መውጣት ጀመረ። እንዴት? ሙሽራው መገኘቱን የሚያሳዩ አዲስ የተፈጠሩ ሁኔታዎች ወደፊት እየገፉ በሚሄዱበትና መንፈሳዊው ብርሃን በጣም አስፈላጊ በነበረበት በዚያ ታላቅ ወቅት ላይ ምሳሌያዊውን ዘይት ለመያዝ ባለመቻላቸው ነው። ስለዚህ በምሳሌያዊ አነጋገር እያንዳንዱ መብራቱን ቦግ አድርጎ በማብራት እርሱን ለመቀበል የሚወጣበት ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ መብራታቸው እየጠፋባቸው በሄዱት ሰነፍ ቆነጃጅት የተመሰሉት ከልባሞቹ ተለይተው ሄዱ።

17. በማቴዎስ 25:10 ላይ እንደተጠቀሰው በሰነፎቹ ቆነጃጅት በተመሰሉት ላይ ምን ሊጠገን የማይችል ኪሳራ ደረሰባቸው?

17 ከቆነጃጅቱ ክፍል እንደሆነ አድርጎ ራሱን ይቆጥር የነበረ አንድ ሰው እንደገና የማይደገመውን መንፈሳዊውን ሙሽራ ኢየሱስ ክርስቶስን የመቀበል ልዩ መብትና አጋጣሚ ሲያጣ እንዴት ያለ ሊጠገን የማይችል ኪሳራ ይደርስበታል! እንደዚህ ያለው ኪሳራ በዘመናዊዎቹ ቆነጃጅት ላይ ደርሷል። ኢየሱስ በምሳሌው ላይ ቀጥሎ የተናገራቸው ተጨማሪ ቃላት ይህን ያሳያሉ:- “ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፣ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፣ ደጁም ተዘጋ።”— ማቴዎስ 25:10

18. (ሀ) በዚህ መቶ ዘመን ውስጥ ሰነፎቹ ቆነጃጅት ሳይተባበሩ የቀሩት በየትኛው መብት ነው? (ለ) ሰነፎቹ በሰርጉ ላይ በሚደረገው ጉዞና ወደ ድግሱ ለመግባት ጊዜው ያለፈባቸው ለምንድን ነው?

18 በዘመናዊዎቹ ሰነፍ ቆነጃጅት ላይ እንዴት ያለ አሳዛኝ ነገር ደረሰባቸው! በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ድቅድቅ ጨለማ ባለበት በዚህ ጊዜ በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ለተቀመጡትና “በታላቁ ሁሉን በሚችለው አምላክ ቀን በሚሆነው ጦርነት” የሞት ጥላ ውስጥ ላሉት ሰዎች ብርሃን በማብራቱ ሥራ ሳይካፈሉ ቀርተዋል! (ራእይ 16:14) መንገዳቸውን ብሩህ ለማድረግ በምሳሌያዊው መብራታቸው ውስጥ ዘይት ስለሌላቸው ትተው ለመሄድና በጨለማ ውስጥ እየተደናበሩ ለመጓዝ ተገደዋል። በዚህም ምክንያት ደማቅ ብርሃን ወደሚያበራበት የሰርግ ድግስ ሙሽራውን ተከትሎ በበሩ ለመግባት በሚደረገው አስደሳች ጉዞ በሰዓቱ አልደረሱም። በሰማያዊው መንግሥት ከእርሱ ጋር ለመጋባት እንደተሰለፉ አድርጎ የሚያሳውቃቸውን መለያ አጥተዋል። በተወሰነው ሰዓት ላይ “ዝግጁ” ሆነው አልተገኙም። እንዴት ያለ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሆነዋል!

19. ይህንን ጉዳይ እስከ መደምደሚያው ድረስ በመከታተላችን ምን ተሞክሮ ይጠብቀናል?

19 ሙሽራው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ምሳሌ የመጨረሻ ክፍል ውስጥ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በተለይ በዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ላይ ለምንኖረው ሕያው በሆነ መንገድ ተገልጾልናል። እንግዲያው አሁን ጉዳዩን በበለጠ እንከታተለው! በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንደምንመለከተው ይህንን ካደረግን ደስታን የሚቀሰቅስ የእውቀት ብርሃን እናገኛለን።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 45 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰነፍ ደናግሎቹን የሚመስሉ ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ አይገቡም