በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ወቅት ነቅቶ መጠባበቅ

“በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ወቅት ነቅቶ መጠባበቅ

ምዕራፍ 6

“በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ወቅት ነቅቶ መጠባበቅ

1. ነቅተን መጠባበቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

ወደ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ውስጥ ጠልቀን ገብተናል፤ ይሁን እንጂ ሕይወት አድን የሆነው ብርሃን የማብራት ሥራ የሚፈጸምበትን ‘ቀንም ሆነ ሰዓት’ አናውቅም። ኢየሱስ “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” ያለው ለዚህ ነው።— ማቴዎስ 24:3፤ 25:13

2. ከየትኛው ያልተጠበቀና የሚያበሳጭ ሁኔታ ለመዳን መጠንቀቅ ይኖርብናል?

2 አንድ ሰው በአንድ የሰርግ ድግስ ላይ ዘግይቶ ቢደርስና በሩ ተዘግቶ ቢያገኘው በጣም ይበሳጫል። ሆኖም በቅርቡ በጣም ብዙ የሆኑትን አስመሳይ ክርስቲያኖች የሚጠብቃቸው ይኸው ነው። “የሰላሙ መስፍን” ይህንን በሚከተሉት ቃላት በምሳሌ ገልጾታል:- “በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቆነጃጅት መጡና ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ እውነት እላችኋለሁ አላውቃችሁም አለ።”— ማቴዎስ 25:11, 12

3. (ሀ) 1919 ምን ዓይነት ሁኔታ የጀመረበት ጊዜ ሆነ? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖተኞች አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊ ዘይት ለመስጠት የሚችሉ ሆነው ተገኝተዋልን?

3 ከ1919 ጀምሮ እንደ “ዘይት” በሆኑት በይሖዋ ቃልና መንፈስ ቅዱስ ርዳታ ልባሞቹ የሚያበሩትን መንፈሳዊ ብርሃን ማንኛውም ሰው ሊያገኘው ይችላል። ይሁን እንጂ ሰነፎቹ መንፈሳዊውን ዘይት እኛ እንሸጣለን ብለው ከሚናገሩት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ካሉት ለመግዛት ይሞክራሉ። (ማቴዎስ 25:9) ይሁን እንጂ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖተኞች ትክክለኛው ዓይነት ዘይት የላቸውም። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሰማያዊ ሙሽራ በመሆን ስለ መገኘቱ የሚያሳየውን ብርሃን ለማብራት አልቻሉም። እነርሱ ‘በዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ውስጥ በሚደረገው ብርሃን የማብራት ሥራ ምንም ተሳትፎ ሳያደርጉ ስንሞት ወዲያውኑ እርሱን ለመገናኘት ወደ ሰማይ እንሄዳለን ብለው ይጠብቃሉ።

4. እስከዚች ዕለት ድረስ በሰነፎቹ ቆነጃጅት የተመሰሉት ምን ሳያደርጉ ቀሩ? ለምንስ?

4 በሌላው በኩል ግን “መንግሥቱን” በሚመለከት ከጦርነቱ በኋላ ለሚደረገው ዓለም አቀፋዊ ብርሃን የማብራት ሥራ ትርፍ የመንፈስ ቅዱስና የአምላክ ቃል “ዘይት” እንዳላቸው ያሳዩ እንደ መንፈሳዊዎቹ ቆነጃጅት ያሉ አንዳንዶችም ነበሩ። (ማቴዎስ 24:14) በክርስቶስ ምሳሌ ውስጥ ባሉት ሰነፍ ቆነጃጅት የተመሰሉት ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስፈላጊ በሆነው በዚህ ምሥራች ላይ ብርሃን በማብራቱ ሥራ አይካፈሉም። ብርሃን የሚሰጠው የአምላክ ቃልና የመንፈስ ቅዱሱ “ዘይት” አልነበራቸውም። ፈራጅ የሆነው ሙሽራም በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ሆኖ ይህ ጕድለት እንዳለባቸው ለማስተዋል ችሏል። ምን ዓይነት ጊዜና ሥራ በፊታቸው እንደ ተከፈተ በማስተዋላቸው ልባሞች የሆኑት ክርስቲያን ቆነጃጅት ከጦርነቱ በኋላ መካሄድ ያለበትን ሥራ ፈጥነው ተያያዙት። የሰነፎቹ ልብ ግን በዚህ ሥራ ላይ አልነበረም።

5. ሰነፎቹ ቆነጃጅት ከሙሽራው ንጉሥ ጋር አንድ ሊያደርጋቸው በሚችል አስፈላጊ በሆነ በምን ነገር ሳይሳተፉ ቀርተዋል?

5 የይሖዋን የሚታይ ድርጅት ከደገፉት ደቀ መዛሙርት ራሳቸውን በመለየታቸው ሰነፎቹ በዓለም አቀፉ የመንግሥት ምስክርነት ሥራ ሳይሳተፉ ቀርተዋል። በመጨረሻ ሃይማኖታዊ የእውቀት ብርሃን የሚሰጥ “ዘይት” አግኝተው ነበር፤ ሆኖም ዘይቱ ትክክለኛው ዓይነት አልነበረም። በተገቢው ጊዜ ለትክክለኛው ሁኔታ ብርሃን ለመስጠት አልቻለም። በዚህ ምክንያት እነርሱ የመንግሥቱን መልእክትና “አምላካችን የሚበቀልበትን ቀን” በመስበክ ላይ አይደሉም። (ኢሳይያስ 61:1–3) ቅቡዓን ቀሪዎች የሆኑት የቆነጃጅት ክፍል እንደሚያደርጉት ሰነፎቹ ቆነጃጅት ሙሽራውን ንጉሥ በምስጋና አይቀበሉም።

እኩለ ሌሊት ሲሆን መብራቱ የሚኖረው ውጤት

6, 7. (ሀ) የሙሽራዋን ክፍል አባልነት ለማሟላት በቂ ቁጥር ያላቸው ቆነጃጅት እንደተገኙ የሚያሳይ በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ ምን ነገር ተፈጸመ? (ለ) በዚያን ጊዜስ አሁን መሰብሰብ ለሚያስፈልገው ለየትኛው ክፍል ትኩረት ተደረገ?

6 በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ አንድ ጉልህ የሆነ ነገር ተከናወነ። በዚያን ጊዜ የተፈጸመው ነገር የመንፈሳዊው የክርስቶስ ሙሽራ አባልነት እንደሞላ ማለትም የእርሱን ሰማያዊ ሙሽራ ቁጥር ለመሙላት በመንፈስ የተመረጡ በቂ የሙሽራው ደቀ መዛሙርት በምድር ላይ እንደ ተገኙ አመልክቷል።

7 በዚያን ጊዜ ማለትም በ1935 በሌሎች የኢየሱስ በግ መሰል ደቀ መዛሙርት ክፍል ላይ ትኩረት መደረግ ተጀመረ። ይህም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሕዝብ ትኵረት እንዲሰጠው የተደረገው የደቀ መዛሙርት ክፍል ነበር። “አሁን በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ላይሞቱ ይችላሉ” በሚል ርዕስ ጉጉት ለነበራቸው፣ ምናልባት ግን በጥርጣሬ የተሞሉ ለሚመስሉ አድማጮች የካቲት 24, 1918 ንግግር ተሰጥቶ ነበር። በ1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ በተደረገው የይሖዋ ምስክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ‘በአንዱ እረኛ’ በኢየሱስ ክርስቶስ ስር በተባበረው አንድ “መንጋ” ውስጥ እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ስለ መሰብሰባቸው አንድ ቍርጥ ያለ አቋም ተወስዶ ነበር። (ዮሐንስ 10:16) በራእይ 7:9–17 ላይ ትንቢት የተነገረላቸው የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት ሰዎች ማንነታቸው ተገለጸ።

8. ልባሞቹ ቆነጃጅት በ1935 ምን ያላሰቡት ግዴታ መጣባቸው?

8 አሁን ‘የታናሹ መንጋ’ ቀሪዎች የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” የመሰብሰቡን ሥራ እንዲጀምሩ ግዴታ መጣባቸው። (ሉቃስ 12:32) ይህ የሆነው የኢየሱስን ሙሽራ አባላት ለማሟላት አስፈላጊ የነበረው የልባሞቹ ቆነጃጅት ቁጥር አሁን በመሙላቱ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ቆነጃጅት በአንድ ጊዜ ወደ ሰማይ አልተወሰዱም። እነርሱ ለአምላካቸው ለይሖዋ ፍጹም አቋማቸውን የሚጠብቁ ምስክሮች በመሆን ምድራዊ ጉዞአቸውን ሲጨርሱ ወደ ሰማያዊው የግብዣ አዳራሽ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል። እስከ 1935 ድረስ ባከናወኑት በታማኝነት ብርሃን የማብራት ሥራቸው ምክንያት ከ1930ዎቹ አጋማሽ በፊት ፈጽሞ አስበውት ወደማያውቁት ልዩ መብት እንዲገቡ ተደርገው ነበር።

9. በአሁኑ ጊዜ የልባሞቹ ቆነጃጅት ቀሪዎች ቍጥራቸው ምን ያህል ሆኗል?

9 ከ1935 ወዲህ ከግማሽ መቶ ዘመን በላይ የሚሆን ጊዜ አልፏል። በእነዚህም ዓመታት ውስጥ ከቆነጃጅቱ ክፍል የሆኑት የልባሞቹ ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል። በሌላው በኩል ግን የምስክርነቱ ሥራ ከ200 በላይ የሆኑትን የተለያዩ አገሮች ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተስፋፍቷል። በአሁኑ ጊዜ የቆነጃጅቱ ክፍል ቁጥር ወደ 8, 700 አካባቢ ዝቅ ብሏል።

መብራቱን ለያዙት ጥሩ እርዳታ የሚያበረክቱ ጓደኞች

10. ከሥራው ስፋት አንጻር ሲታይ የልባሞቹ ቆነጃጅት ቀሪዎች የሚፈለጉትን ሠራተኞች ሊያሟሉ ይችላሉን?

10 በምድር ዙሪያ ከ60, 000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ካሉት ከ3, 700, 000 በላይ ከሆኑት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ጋር ሲወዳደሩ የምሳሌያዊ ቈነጃጅቱ ቀሪዎች ከቍጥር አይገቡም ለማለት ይቻላል። በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ቀሪዎች እነዚህ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጉባኤዎች በሚገኙባቸው ከ200 በሚበልጡት አገሮች ውስጥ የሚከናወነውን የምስክርነት ሥራ እንዴት ሊሠሩት ይችሉ ነበር? በፍጹም አይችሉትም ነበር።

11. (ሀ) ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ማንነት መታወቅ ቆነጃጅት ነን በሚሉት መካከል ምን ነገር እንዲፈጠር አድርጓል? (ለ) ‘የክፉ ባሪያ’ ክፍል የሆኑት በቂ መንፈሳዊ ብርሃን በማጣታቸው ምክንያት ምንን ማስተዋል አልቻሉም?

11 እርግጥ ሙሽራው ጌታ ለፍርድ ወደ መቅደሱ ሲመጣ ታማኝ ሆነው የሚያገኛቸው ይኸውም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው ያገለግላሉ። በምሳሌያዊው የቆነጃጅት ክፍል ውስጥ በልባሞቹና በሰነፎቹ ቆነጃጅት መካከል መለያየት የተጀመረው በዚህን ጊዜ ነበር። እነዚህ ‘የክፉ ባሪያ’ ክፍል ተደርገው የተቆጠሩት መብራታቸውን ለማብራት በማሰሮዎቻቸው ውስጥ ብርሃን የሚሰጠው የአምላክ ቃልና የመንፈስ ቅዱሱ ዘይት የላቸውም። በዚህም ምክንያት ከ1935 ጀምሮ ‘የአንድ መንጋ’ ክፍል ለመሆን ቀደም ብለው ሲሰበሰቡ የቆዩትን የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ማንነት ለማስተዋል በቂ መንፈሳዊ ብርሃን አልነበራቸውም።— ማቴዎስ 24:45–51

12. ለሙሽራዋ ክፍል ቀሪዎች የማይለያዩ ጓደኞች የሆኑላቸው እነማን ናቸው?

12 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ኢየሱስ ‘ስለ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ የተናገረው ትንቢት የተፈጸመው በአብዛኛው የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ባበረከቱት የሥራ ድርሻ ነው። ቀሪዎቹ ከያዙአቸው መብራቶች የፈነጠቀው ብርሃን የልባቸውን ዓይኖች አብርቶላቸዋል፤ ገና በዚህ ዓለም ጨለማ ውስጥ ላሉት ለሌሎችም ይህንን ብርሃን እንዲያንጸባርቁ እርዳታ ተደርጎላቸዋል። (ከኤፌሶን 1:18 ጋር አወዳድር።) የተሟላ ቁጥር ከሚኖረው የሙሽራዋ ክፍል ጋር እርሱ ጋብቻ የሚያደርግበት ቀን እየቀረበ ሲሄድ ሙሽራ የሆነው ንጉሥ መገኘቱን እንዲያስተውሉ በሚልዮን የሚቆጠሩትን የምድር ነዋሪዎች ረድተዋቸዋል። እነርሱ ከሙሽራዋ ክፍል ቀሪዎች የማይነጣጠሉ ጓደኞቻቸው ሆነዋል።

13, 14. (ሀ) የቀሪዎቹን ጓደኞች በሚመለከት በራእይ 7:9, 10 ላይ በምሳሌ የተገለጸው ምን አስደሳች ሁኔታ ነው? (ለ) ስለዚያ ትንቢት ለተሰጠው ማብራሪያ ወዲያውኑ የተሰጠው ምላሽ ምን ነበር?

13 ከ1935 ጀምሮ የእነዚህ የሙሽራይቱ ክፍል ቀሪዎች ጓደኞች ዕጣ አስደሳች ሆኗል። ቀሪዎቹ ቀደም ሲል በገቡባቸው ታላላቅ መብቶች ብቻ ሳይሆን እነርሱ ራሳቸው በሙሽራዋ ክፍል ቀሪዎች እየተመሩ በገቡባቸው የተባረኩ መብቶቹ በጣም ይደሰታሉ።

14 በ1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ ስብሰባ ላይ የይሖዋ ሕዝቦች አንድ አስደናቂ ጥቅስ ለማስተዋል ዓይናቸው ተገለጠ። ጥቅሱ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ለሆኑት የቅቡዓኑ ጓደኞች አስደሳች ሁኔታ እንደሚመጣ የሚተነብይ ነበር። እነርሱንም ተመልከቷቸው “ነጭ ልብስ ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና (በይሖዋ አምላክ ዙፋንና) በበጉ ፊት” ቆመዋል! ለሁሉም ሰው እንዲሰማ እየጮኹ የሚናገሩትን አድምጡ:- “መዳንን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከአምላካችንና ከበጉ ነው።” (ራእይ 7:9, 10 አዓት) እነርሱም ቀደም ብለው ‘የዓለምን ኃጢአት በሚያስወግደው የአምላክ በግ’ ላይ እምነት አድርገዋል፤ በእርሱም በኩል ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነዋል፤ ይህንንም ውሳኔአቸውን ለማሳየት ተጠምቀዋል። (ዮሐንስ 1:29) ዓርብ ግንቦት 31, 1935 ስለ ራእይ 7:9–17 የተሰጠውን ማብራሪያ ካዳመጡ በኋላ በሚቀጥለው ቀን 840 የሚሆኑት ተጠምቀዋል።

15. ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምን ያህል ሰዎች ተጠምቀዋል? እነርሱስ በራእይ 7:14–17 ላይ እንዴት ተገልጸዋል?

15 በ1935 በዋሽንግተን ከተደረገው ከዚያ ስብሰባ ወዲህ ከሦስት ሚልዮን የሚበልጡት ሰዎች ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። በዚህም መንገድ በሚያነጻው የበጉ ደም በመታጠባቸው ምክንያት ነጭ የሆኑትን ልብሶች እንደለበሱ ሆነው ተገልጸዋል። እንዲሁም በሁሉም የሰው ዘር ዓለም ፊት ከሚመጣው ታላቅ መከራ መለኮታዊውን ጥበቃ አግኝተው ከመከራው የመትረፍ ተስፋ አላቸው። (ማቴዎስ 24:21, 22) ስለዚህም ከቀሪዎቹ የቆነጃጅት ክፍል ጋር በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በመሆን እንደሚያመልኩት ተደርገው ተገልጸዋል።— ራእይ 7:14–17

16. ማቴዎስ 24:14⁠ን ከመፈጸሙ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ላበረከቱት ድርሻ እጅግ በጣም ብዙ ምስጋና የሚያቀርቡት ለእነማን ነው?

16 እንግዲያው ከልዩ ልዩ የዓለም ብሔራት የተውጣጡትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩት “እጅግ ብዙ ሰዎች” በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘውን የሙሽራውን ትንቢት ለመፈጸም ስላበረከቱት እጅግ የላቀ ድርሻ የተትረፈረፈ ምስጋና ይድረሳቸው።

“በሩም ተዘጋ”

17. (ሀ) ወደ ሰርጉ ግብዣ የሚያስገባው በር የሚዘጋው መቼ ይሆናል? (ለ) የቆነጃጅቱ ቀሪዎች ክፍልና “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሆኑት ጓደኞቻቸው በአሁኑ ጊዜ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ነገር ምንድን ነው?

17 ቅቡዓኑ የቆነጃጅት ክፍል ወደ ጋብቻው ድግስ በዓል መቼ እንደሚገቡና በሩ መቼ እንደሚዘጋ በትክክል አይታወቅም። ይሁን እንጂ ያለምንም ጥርጥር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቀርቧል፤ ጊዜው እያለቀ ነው! ኢየሱስም የቆነጃጅቱን ምሳሌ “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” በሚሉት የማስጠንቀቂያ ቃላት የደመደመው ተገቢ በሆነ ምክንያት ነው።— ማቴዎስ 25:13

18. (ሀ) ሰነፎቹ ቆነጃጅት አሁን ራሳቸውን ከእነማን ጋር መድበዋል? (ለ) በቅርቡስ የትኛው የኢየሱስ ምሳሌ ፍጻሜ በእነርሱ ላይ ሊደርስ ነው?

18 በዚህም ምክንያት ሰነፎቹ ቆነጃጅት ጊዜው ሳያስቡት ከተፍ ይልባቸዋል። ልባሞቹን ቆነጃጅት ትተው በመሄዳቸው እንዲጠፋ የተፈረደበት የዚህ ዓለም ክፍል ሆነዋል፤ እንዲሁም ጠቅላላውን ምድር በሸፈነው ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ካሉት ከሌሎች ሃይማኖተኞች ሁሉ ጋር ራሳቸውን መድበዋል። በዚህም መንገድ ሙሽራው ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌው ውስጥ ባሉት በሚከተሉት ቃላት የገለጻቸው ነገሮች ይፈጸሙባቸዋል:- “በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቆነጃጅት መጡና ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።”— ማቴዎስ 25:10–12

19. እንግዲያው ሰነፎቹ ቆነጃጅት ማንን ያመለክታሉ? ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር የሚመደቡትስ ለምንድን ነው?

19 ስለዚህ የግብዣው በር ለሰነፎቹ ቆነጃጅት አይከፈትላቸውም። እነርሱም ‘በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን’ ውስጥ ወደ “መንግሥተ ሰማያት” ለመግባት ሳይበቍ የሚቀሩትን ያመለክታሉ። (ማቴዎስ 24:3፤ 25:1) ሌላ ዘይት ለመግዛት ወደ ገበያ መሄዳቸው የራሳቸው ምርጫ የሆነ ሃይማኖት መያዛቸውን ያሳያል። በዚህም ምክንያት ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ተመድበዋል።

20. (ሀ) ሰነፎቹ ቆነጃጅት ‘የአውሬው’ “አሥር ቀንዶች” ወደ ታላቂቱ ባቢሎን መዞር መጀመራቸውን ሲመለከቱ ወደ ማን ልመና ያቀርባሉ? ምንስ በማለት? (ለ) የሆነው ሆኖ ጥፋት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

20 ይህም በመሆኑ በመጨረሻው ላይ ሃይማኖታዊዋ ጋለሞታ የምትጋልበው ምሳሌያዊ “አውሬ” ‘በአሥር ቀንዶቹ’ ሲዞርባት በእርሷ ላይ ከሚደርሰው ዕጣ መካፈል ይኖርባቸዋል። (ራእይ 17:16) በአምስት ሰነፍ ቆነጃጅት የተመሰሉት እንደነዚህ ያሉት ሃይማኖተኞች ባቢሎናዊ የሆነው ሃይማኖት በፖለቲካው ሥርዓት ውስጥ ባሉት ብርቱ ኃይሎች ተቀባይነት ማጣት መጀመሩን ሲመለከቱ ወደ ሙሽራው ንጉሥ በመዞር እኛ “የመንግሥተ ሰማያት” ክፍል ነን፤ ከልባሞቹ ቆነጃጅት ጋር ወደ ሰርጉ ድግስ መግባት ይገባናል ይላሉ። እነርሱ “ጌታ” ብለው የሚጠሩት ሙሽራ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያዊ መንግሥት መግባት እንደሚገባቸው አድርጎ እንደማያውቃቸው ሲገልጽላቸው በኃይል የሚያስደነግጥ ይሆንባቸዋል። እንዲሁም እነርሱ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከሆኑት ጋር በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘቱ ተስፋ ተካፋይ አልሆኑም ነበር። ስለዚህም ለእነዚህ ሰነፍ ሃይማኖተኞች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ከመጥፋት በስተቀር ምንም የሚቀርላቸው ነገር የለም!

21. (ሀ) ወደፊት ከሚመጣው ከዚህ አስፈሪ ሁኔታ አንጻር ልባሞቹ ቆነጃጅትና ጓደኞቻቸው ምን ዓይነት አካሄድ ይከተላሉ? (ለ) “እጅግ ብዙ ሰዎች” ምን ዓይነት የአገልግሎት መብቶችን ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ?

21 ወደፊት የሚጠብቃቸው እንዴት ያለ አስፈሪ ሁኔታ ነው! ቀሪዎቹና እጅግ ብዙ የሆኑት ጓደኞቻቸው ይህንን ሁኔታ በመረዳታቸው ኢየሱስ ‘ነቅታችሁ ጠብቁ’ ሲል የሰጠውን ምክር ዘወትር ይከተላሉ። ሁልጊዜ በአምላክ መንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሆነው ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ያለ ፍርሃት ብርሃኑ እንዲያበራ ያደርጋሉ። በአጸፋውም ደስታ የተረጋገጠ ድርሻቸው ይሆናል! እንዲሁም ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ ከሆኑት መካከል በሙሽራው ንጉሥ የተሾሙቱ ‘በአዲስ ምድር’ ውስጥ መሳፍንት ሆነው የማገልገል ቦታ ይጠብቃቸዋል።— ኢሳይያስ 32:1፤ ከመዝሙር 45:16 (አዓት) ጋር አወዳድር።

22. (ሀ) የቆነጃጅቱ ምሳሌ መፈጸም ለየትኛው ሁኔታ ማረጋገጫ ሆኖ ያገለግላል? (ለ) በሙሽራው ንጉሥና በእርሱ ድንግል ሙሽራ በሚደረገው ጋብቻ የሚደሰቱት እነማን ይሆናሉ?

22 እንግዲያው ረዘም ባለ ጊዜ ላይ ይህ የአሥሩ ቆነጃጅት ምሳሌ መፈጸሙ ‘በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ውስጥ ለመኖራችን ማረጋገጫ ሆኖ ያገለግላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ቁጥራቸው ከተሟላው የሙሽራው ክፍል ጋር የሚያደርገው ጋብቻ መቅረቡን የሚያሳየውን ማረጋገጫ እንድንመለከት ብርሃን ስለ በራልን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን! በዚህ ሰማያዊ ጋብቻ ሰማይም ሆነ ጽድቅ የሰፈነበት “አዲስ ምድር” በቃል ሊገለጽ የማይቻል ደስታ ይሰማቸዋል።— ራእይ 19:6–9

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]