በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአዲስ አባትነት የሚተዳደር ደስተኛ ሰብአዊ ቤተሰብ

በአዲስ አባትነት የሚተዳደር ደስተኛ ሰብአዊ ቤተሰብ

ምዕራፍ 20

በአዲስ አባትነት የሚተዳደር ደስተኛ ሰብአዊ ቤተሰብ

1. የአዲስ አባትነት ጉዳይ ለሰብአዊው ቤተሰብ የምስራች የሚሆነው ለምንድን ነው?

ከአርማጌደን በኋላ ሁሉም የሰው ዘር ሁለተኛ አባትነት ይጠብቀዋል። ይህ በእርግጥ የምሥራች ነው! አዲሱ አባትነት በምድር አቀፍዋ ገነት ውስጥ ሰብአዊ ፍጽምናን በማምጣት የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲቻል ያደርጋል። ምክንያቱም አዲሱ የሰብአዊ ቤተሰብ አባት ራሱ የማይሞት ነው። በምድር ላይ እንደ ልጆቹ አድርጎ ለሚወስዳቸው ሁሉ ፍጹም ሕይወት ለመስጠት ኃይል አለው።

2. አዲስ አባትነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 አዲሱ አባትነት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት የሰው ዘር የመጀመሪያውን አባትነት ማለትም የሰውን ፈጣሪ አባትነት አጥቶአል። ከኢየሱስ ወደ መጀመሪያው ሰው ወደ አዳም የሚያደርሰው የትውልድ መስመር የሚከተለውን ዝርዝር በመስጠት ያበቃል:- “የቃይናን ልጅ፣ የሄኖስ ልጅ፣ የሴት ልጅ፣ የአዳም ልጅ፣ የእግዚአብሔር ልጅ።” — ሉቃስ 3:37, 38

3. ለሁሉም ሰብአዊ ፍጡር የይሖዋ አምላክን አባትነት ማጣቱ ምን ያህል አሳዛኝ ሆኗል?

3 የይሖዋ አምላክን አባትነት ማጣቱ ለሁሉም ሰብአዊ ቤተሰብ አሳዛኝ ውጤት አስከትሏል። የአዳም ዝርያዎች የሞትን ቅጣት ወረሱ። ጉዳዩ በሮሜ 5:12 ላይ በግልጽ ተብራርቷል:- “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንዲሁም ሁሉ ኃጢአት ስላዳረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” ይህ “አንድ ሰው” አዳም ነው፤ አውቆ ኃጢአት በመስራቱ የፈጣሪውን የይሖዋን አባትነት አጣ።

4. አዳምና የሰው ዘሮች በማን አባትነት ስር ሆኑ?

4 ከዚያ በኋላ አዳም በማን አባትነት ስር ሆነ? የሰውን ዘር ዓለምስ በማን አባትነት ስር እንዲሆን አደረገ? በሰማይና በምድር ካሉት ከሁሉም ታዛዥ የአምላክ ልጆች ቤተሰብ እንዲወጣ ባደረገው ፍጡር አባትነት ስር መሆን ይኖርበታል። ይህም የመጀመሪያውን ውሸት ለሔዋን የነገራት የሰይጣን ዲያብሎስ አባትነት ነው። ያ የይሖዋ ተቃዋሚ ይህንን ያደረገው እንዴት ነበር?

5. (ሀ) ሰይጣን ዲያብሎስ የአዳምን ሚስት ለአምላክ ታዛዥ እንዳትሆን ለማታለል በምን አማካኝነት ተጠቀመ? (ለ) አዳም ለተከተለው ጐዳና ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ የሆነው ለምንና እንዴት ነው?

5 በ2 ቆሮንቶስ 11:3 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “እባብ በተንኮሉ (በማታለል) ሔዋንን እንዳሳታት” ብሎ ጽፏል። ሰይጣን ምንም ላልተጠራጠረችው ለሔዋን ይሖዋ አምላክን ዋሽቷል ብሎ በተንኰልና በሐሰት በመክሰስ በዔደን ገነት ውስጥ የመጀመሪያውን ውሸት ለማስተላለፍ በእባብ ተጠቅሟል። (ዘፍጥረት 3:1–7፤ ዮሐንስ 8:44) አዳም ሚስቱን አላረማትም። ከእርስዋ ጋር ለመብላት እምቢ ብሎ ሁኔታውን ከብልሽት አላዳነውም። አውቆ ያጠፋው ጥፋት በእባቡ እጅ ላይ ጣለው። ተጠያቂነቱን በተገቢ ቦታ በማስቀመጥ 1 ጢሞቴዎስ 2:14 እንዲህ ይላል:- “የተታለለም አዳም አይደለም፣ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላላፍ ወደቀች።”

አባት ለመሆን የሚበቃ

6, 7. ኢየሱስ የትኛው የአባትነት አደራ ሊሰጠው እንደሚችል አሳየ? ይህንንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የሚያሳየው እንዴት ነው?

6 ‘የዚህን የነገሮች ሥርዓት አምላክ’ ለማምለክ እምቢ በማለቱ ኢየሱስ ለሰብአዊው ቤተሰብ ሁለተኛ አባትነት አደራ ሊሰጠው የሚገባው እርሱ መሆኑን አስመስክሯል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ማቴዎስ 4:1–11፤ ሉቃስ 4:1–13) በ2 ከዘአበ ሰው ሆኖ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ በኢሳይያስ 9:6 ላይ የሚገኘው ትንቢት በእርሱ ላይ ይሠራል:-

7 “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ [መስፍናዊ አገዛዝ (አዓት)] በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት የሰላም [መስፍን (አዓት)] ተብሎ ይጠራል።” ስለዚህ ይህ “የሰላም መስፍን” ለሰው ዘር “የዘላለም አባት” የመሆን ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሚናም ይጫወታል።

8. ኢየሱስ ለሰው ዘር “የዘላለም አባት” ለመሆን እርምጃ ሊወስድ የቻለው ለምንድን ነው? ይህንንስ ሐዋርያው ጳውሎስ ያረጋገጠው እንዴት ነው?

8 የአምላክ ልጅ ፍጹም ሰብአዊ ሕይወቱን መስዋዕት አድርጎ ለሰጠለት ለዚህ ሰብአዊ ቤተሰብ “የዘላለም አባት” ይሆናል። ይህ ልክ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው ነው:- “በአንድ ሰው በደል ብዙዎች ሞተዋልና ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋ (የማይገባ ደግነቱ) እና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ (የማይገባ ደግነት) የሆነው [ነፃ] ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎቹ በዛ። እንግዲህ በአንድ ሰው በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደመጣ፣ እንዲሁም በአንድ የጽድቅ [ድርጊት] ምክንያት ስጦታው [ሰዎችን ለሕይወት] ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ።”— ሮሜ 5:15, 18

9. ኢየሱስ ለሰው ዘር ሁለተኛው አዳም የሆነው እንዴት ነው? ይሁን እንጂ የሰው ዘር አባት የሚሆነው ከየትኛው ግዛት ነው?

9 በዚህ መንገድ በእነዚህ በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ፍጹም የሆነ ሚዛን ተጠብቋል። በምድር ላይ “አንድ በደል” የፈጸመው ሰው አዳም ነበር። “አንድ የጽድቅ ድርጊት” የተከናወነው ደግሞ በሌላው ብቸኛ ፍጹም ሰው ማለትም በኢየሱስ ነው። ይህም ለበደል ፈጻሚዎቹ የአዳም ዘሮች “ዘላለማዊ አባት” እንዲሆን አስችሎታል። በዚህም መንገድ ሰብአዊውን ቤተሰብ በሚመለከት ሁለተኛው አዳም ሆነ። ፍጹም ሰብአዊ ሕይወቱን መስዋዕት በማድረጉና ያን የሰብአዊ ሕይወት መብት በሰማይ ለሚኖረው ታላቅ ፈራጅ በማቅረቡ በዚሁ ምድር ላይ ለሰው ዘር እንደ ዘላለማዊ አባት ሆኖ ለማገልገል አስችሎታል። ከሞት በተነሣበት ጊዜ ወደ መንፈሳዊ ዓለም ተመልሶ ከሞት ወዳስነሣው አምላክ ቀኝ ከፍ ከፍ ተደርጎአል። ስለዚህም:- “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” ተብሎ ተገልጾአል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) አዲሱ የሰው ልጆች አባት ሕይወታቸው ተወዳዳሪ በሌለው መንገድ እንደ አዲስ እንዲጀምር ያደርጋል።

አባት የሚሆንላቸው የመጀመሪያዎቹ ሰብአዊ ፍጥረታት

10. በዚህ አሳዳጊ አባት ስር ልጆች የሚሆኑት የመጀመሪያዎቹ ሰብአዊ ፍጡራን እነማን ናቸው?

10 “የዘላለም አባት” የሆነው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ አባት የሚሆንላቸው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች እነማን እንደሚሆኑ ያሳውቃል። እንዴት? በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ለአምላክ የተወሰኑ ሰዎችን “ከታላቁ መከራ” ጠብቆ በሕይወት እንዲቀጥሉ በማድረግ ነው። እነርሱም የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ናቸው።— ራእይ 7:9, 14

11. ‘የታላቁ መከራ’ ተራፊዎች በሆኑት በግ መሰል ሰዎች ፊት ምን ምድራዊ ዕድል ተዘርግቷል?

11 “ከታላቁ መከራ” በኋላ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በተባሉት ፊት የሚዘረጋው ምድራዊ ዕድል ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነው። የዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” “ምልክት” ክፍል እንደሆነ በተገለጸው የኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ ያሉት ምሳሌያዊ ፍየሎች ከምድራዊ ሕይወት ይቆረጣሉ፤ ይህም ለእነርሱ የዘላለም ጥፋት ማለት ይሆናል። ይሁን እንጂ ገና በምድር ላይ ላሉት የክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞች ቀሪዎች በፍቅርና በታማኝነት መልካም በሚያደርጉት በግ መሰል “እጅግ ብዙ ሰዎች” ላይ ይህ አይደርስም። (ማቴዎስ 25:31–46) እነዚህ “በጎች” “ከታላቁ መከራ” ተርፈው፣ መምጣቱ አስቀድሞ ወደ ተነገረለት “የሰላም መስፍን” የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ መግባታቸው መንግሥቱ በረከቶችን ወደሚያዘንብበት ዘመን ለመግባት ያስችላቸዋል። በዚያን ጊዜ “የሰላሙ መስፍን” ምድራዊ ተገዢዎች ይሆናሉ።

12. በመንግሥቱ ምድራዊ ግዛት ውስጥ በሚገቡት ፊት የማያልቅ ሕይወት እንደ ተዘረጋ የትኞቹ ስለ ትንሣኤ የሚገልጹ የኢየሱስ ቃላት ያሳያሉ?

12 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ከማስነሳቱ በፊት የተናገራቸው ቃላት ወደ መንግሥቱ ምድራዊ ግዛት በሚገቡት ላይ ይፈጸማሉ። እርሱም:- “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” ብሏል። (ዮሐንስ 11:25, 26) ለእርሱ ባላቸው ታዛዥነት ምክንያት በንጉሡ ምድራዊ ግዛት ውስጥ ፍጹም የሆነ ሰብአዊ ሕይወት ያገኛሉ። ሌላው ቀርቶ ከኢየሱስ ጋር በጌተሰማኒ የሞተው የሐዘኔታ መንፈስ ያሳየ ክፉ አድራጊም ጭምር ገነት የመግባት ዕድል በማግኘት ይባረካል። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ “የዘላለም አባት” የሚለው ስሙ የሚያመለክታቸውን ነገሮች ሁሉ ይፈጽማል።

ለሙታን ያለው አስደሳች ተስፋ

13. የሰብአዊ ሙታን ትንሣኤ በጥንት ዘመን የታወቁ የትኞቹ ሰዎች በምድራዊ የመንግሥቱ ግዛት እንዲታዩ ያስችላል?

13 ከሁሉም የአብርሃም ዘሮች ዋነኛ ዘር የሆነው ኢየሱስ የቀድሞ አባቱ የሆነው ይህ ሰው፣ ልጁ ይስሐቅና የልጅ ልጁ ያዕቆብ በአምላክ መንግሥት ምድራዊ ግዛት እንደሚታዩ ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:31, 32) ይህ ሊሆን የሚችለው በትንሣኤ አማካኝነት ነው። ኢየሱስ እንደተናገረው በመታሰቢያ መቃብር ያሉት ሁሉም ሰብአዊ ሙታን የአምላክን ልጅ ድምጽ ሰምተው ይወጣሉ። ከዚያ በኋላ ያለው የወደፊት ሁኔታቸው ያኔ በሚወስዱት እርምጃ ላይ የተመካ ይሆናል።— ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:12–15

14. ምድራዊ ትንሣኤ ለሚያገኙት አስቀድሞ ምን መደረግ ይኖርበታል? በእነዚህ ዝግጅቶች በመጀመሪያ ተሳታፊ የሚሆኑትስ እነማን ይሆናሉ?

14 “የዘላለም አባት” በሚያስተዳድረው መንግሥት ስር በምድር ላይ ሕይወት ለማግኘት ከመቃብር ለሚወጡት የሰው ዘሮች ከፍተኛ የሆኑ ዝግጅቶች መደረግ ይኖርባቸዋል። እነዚህን ዝግጅቶች በመጀመሪያ የሚያደርጉት በአርማጌዶን ከሚደረገው “ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ላይ ከሚደረገው ጦርነት” የሚተርፉት ይሆናሉ። (ራእይ 16:14, 16) ‘የሰላሙ መስፍን’ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” በዚያን ጊዜ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሚደርስ አሁን አናውቅም፣ ይሁን እንጂ ለሥራው በቂ ሰዎች ይኖራሉ።

15. በሰው ዘር አሳዳጊ አባት ስር ብዙዎች በምን ልዩ ቦታ ያገለግላሉ?

15 መዝሙር 45 ይህ “የሰላም መስፍን” ንጉሥ እንደሆነ ይገልጻል፤ እርሱም ለሰው ዘር “የዘላለም አባት” ስለሚሆን ይህ መዝሙር ስለ እርሱ እንዲህ ይላል:- “በአባቶችህ ፋንታ ልጆች ይኖሩሃል፣ በምድርም ሁሉ መሳፍንት አድርገህ ትሾማቸዋለህ።” (መዝሙር 45:16 አዓት) እነዚህ ታማኝ “አባቶች” ትንሣኤ ከማግኘታቸው በፊትም ቢሆን ከአርማጌዶን ከሚተርፉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ውስጥ ወንዶቹ ለዚህ መስፍናዊ ሥልጣን ይሾማሉ። ከእነዚህ የወደፊት የአርማጌዶን ተራፊዎች ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት ከ60, 000 በሚበልጡት የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የየጉባኤዎቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎቶች በማካሄድ ሽማግሌዎች ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

16. (ሀ) በመስፍናዊ የበላይ ቁጥጥር ስር በመሆን የአርማጌዶን ተራፊዎች በምን የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ያገለግላሉ? (ለ) ሙታን እንደገና ስለሚመለሱበት ቅደም ተከተል ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?

16 በመስፍናዊው የበላይ ቁጥጥር ስር በመሆን የአርማጌዶን ተራፊዎች በጋለ የትብብር መንፈስ ያገለግላሉ። “በምድር ሁሉ ላይ መሳፍንት” የሚሆኑት ሁሉ ከሰማያዊው “የሰላም መስፍን” ምን መመሪያዎች እንደሚቀበሉ ገና ወደፊት ይታያል። ይህም ለሁሉም የአርማጌዶን ተራፊ ጓደኞቻቸው አስደናቂ ተሞክሮ ይሆናል። ከሞት የሚነሱትን ተስማሚ የሆነ ልብስ ለማልበስ መዘጋጀት ስለሚገባቸው ልብሶች እስቲ አስብ! ተዘጋጅቶ ወይም ተከማችቶ መቆየት ያለበትን ምግብ ሁሉ ገምት! የመጠለያ ቦታዎችም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋቸዋል። በዚህ የማዘጋጀት ሥራ ውስጥ ለሚሳተፉት ሁሉ ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! መጀመሪያ የሚነሡት እነማን ይሆናሉ? ወደ መታሰቢያ መቃብር በሄዱበት ቅደም ተከተል ፋንታ በቅርቡ ከሞቱት ጀምሮ ወደ ኋላ በመሄድ ይነሡ ይሆንን? ሰማዕቱ አቤልና በአምላክ የተወሰደው ሄኖክ እንዲሁም ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሌሎች ታማኝ ነቢያት ቀደም ብለው የመነሣት ልዩ በረከት ያገኙ ይሆን?

17. ሙታን በምድር ላይ ሕይወት ለማግኘት እንደገና የሚመለሱበትን ቅደም ተከተል የሚወስነው ማን ነው? ኃላፊነቶቹን ለመወጣት ያለውን ችሎታ የሚያመለክት ምን ማዕረግ በትንቢት ተሰጥቶታል?

17 ‘የሰላሙ መስፍን’ ይህንን ያውቃል፣ ይወስናልም። ለተዋጀው የሰው ዘር አዲስ አባት በመሆኑ ላሉበት ኃላፊነቶች ሙሉ በሙሉ ብቁ ይሆናል። በትንቢት ከተነገሩለት የማዕረግ ስሞች ውስጥ ሌላው “ኃያል አምላክ” የሚለው ነው። ይህም እርሱ ኃያል፣ በጣም ብርቱ እንደሚሆን ያሳያል። የተዋጁትን ሙታን በሙሉ የግል ስማቸውንና ባሕርያቸውን በማስታወስ ከሞት ስለሚያስነሣቸው የአምላክነቱ መግለጫ ኃያል ይሆናል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 10:42) የሰው ዘር በኖረባቸው ባለፉት 6000 ዓመታት ሰይጣን ዲያብሎስ ያመጣውን ጉዳት ሁሉ ለመጠገን ፍጹም ችሎታ ይኖረዋል።

18. (ሀ) አዳም ለኢየሱስ ክርስቶስ የቀድሞ አባት መሆን ያላስፈለገው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ለአዳም ዝርያዎች ሁለተኛ አባት ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

18 የመጀመሪያው አዳም ለሁሉም ዝርያዎቹ የሞትን ኩነኔ አወረሰ። አዳም ሰው ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ የቀድሞ አባቱ ሆኖአልን? አልሆነም፣ ኢየሱስ ከመንፈሳዊው ዓለም አምላክ ባስተላለፈው የሕይወት ኃይሉ እንድታረግዝ ከተደረገችው አንዲት ድንግል ተወለደ እንጂ ሰብአዊ አባት የለውም። በዚህ ምክንያት ኃጢአተኛው አዳም የዚህ ምድራዊ የአምላክ ልጅ አባት አልሆነም። ይሁን እንጂ ሁለተኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆኖአል። ይህ ችሎታ ስላለው የኢሳይያስን ትንቢት ለመፈጸምና በገነት ምድር ላይ ፍጹም ሰብአዊ ሕይወት ለመስጠት ለሚዋጃቸውና አባት ለሚሆንላቸው ለመጀመሪያው አዳም ዝርያዎች “የዘላለም አባት” ሊሆን ይችላል።

19. ይሖዋ አምላክ ከሰብአዊው ዘር ጋር በምን አዲስ ዝምድና ውስጥ ይገባል? በዚህ መንገድ የትኛው የሰይጣን ዲያብሎስ ዕቅድ ይከሽፋል?

19 በዚህም መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አባት ወደ ፍጽምና ለተመለሰው ሰብአዊ ቤተሰብ ሰማያዊ አያት ይሆናል። በዚህ ምክንያት ሰብአዊው ቤተሰብ ከሰማይና ከምድር ፈጣሪ ጋር ወደ አዲስ ዝምድና ይገባል። ይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማውን እንዳያሳካ የሚያደርግ ትንሽም ምክንያት እንኳ አይኖርም። በዚህ መንገድ ይሖዋ ክፉውን፣ አምላካዊ ያልሆነውን የሰይጣን ዲያብሎስ ዕቅድ ያከሽፈዋል። እንደገና የተዋጀው ሰብአዊ ቤተሰብ በሙሉ ይህንን ሐቅ እንዲገነዘበው ይደረጋል። በምድር ላይ እንደገና በምትቋቋመዋ ገነት ውስጥ የሰውን ዘር ለማሳደግ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰብአዊው ቤተሰብ አባት ሲሆን እንዴት ያለ አስደሳች ቀን ይሆናል!

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 164, 165 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ክርስቶስ ልጆች አድርጎ ለሚቀበላቸው ሁሉ ንጉሣዊ ሥልጣን ይዞ “ዘላለማዊ አባት” ይሆንላቸዋል