በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በክርስቶስ ገንዘብ አጠቃቀም ላይ የተደረገ መተሳሰብ

በክርስቶስ ገንዘብ አጠቃቀም ላይ የተደረገ መተሳሰብ

ምዕራፍ 7

በክርስቶስ ገንዘብ አጠቃቀም ላይ የተደረገ መተሳሰብ

1. ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ ችግሮች የሌሉበት መንግሥት የትኛው ነው? ከዚህስ መንግሥት ጋር ሒሳብ መተሳሰብ የሚኖርባቸው እነማን ናቸው?

ከአንዱ መንግሥት በስተቀር የኢኮኖሚ ችግር የሌለበት ምንም መንግሥት የለም። አብዛኞቹ መንግሥታት ከፍተኛ የገንዘብ ዕዳ አለባቸው። ይህ ችግር የማይነካው መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በስፋት የሚታወጀው “መንግሥተ ሰማያት” ነው። (ማቴዎስ 25:1) አሁንም ቢሆን ያንን መንግሥት የሚያገለግሉና የዚያ ሰማያዊ መንግሥት የወደፊት አባላት የሆኑ በምድር ላይ ይገኛሉ። በሰው ዘር ታሪክ ሁሉ በጣም አስቸጋሪ በሆነው በዚህ ጊዜ ውስጥ እነዚህ “የመንግሥተ ሰማያት” አገልጋዮች ሒሳብ እንዲያስረክቡ ተጠይቀዋል። በአደራ የተሰጣቸውን ውድ ሀብት እንዴት እንደተጠቀሙበት ከመንግሥቱ ጋር መተሳሰብ ይኖርባቸዋል።

2. ‘በሰላሙ መስፍን’ የተነገረን አንድ ምሳሌ ለመመርመር ፍላጐት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?

2 ይህንን ጉዳይ በምሳሌ ለማስረዳት ‘ከመንግሥተ ሰማያት’ ተወካዮች ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የያዘው ከረጅም ጊዜ በፊት አንድ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ዛሬ ይህን ጉዳይ ለመመርመር ፍላጐት ሊያድርብን ይገባል፤ ምክንያቱም ‘የሰላሙ መስፍን’ ሙሉ የመግዛት ሥልጣን በመያዝ በመንግሥቱ ላይ ‘መገኘቱን’ ስለሚገልጸው “ምልክት” በተናገረው ሰፊ ትንቢት ውስጥ ስለጨመረው ነው። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) በዛሬው ጊዜ የትንቢቱን ፍጻሜ ተከትለው የመጡት ውጤቶች የወደፊት ሕልውናችንን ወይም ሕይወታችንን ስለሚነኩ መላቀቅ በማይቻል ሁኔታ ውስጥ ገብተናል። “የሰላሙ መስፍን” በጎልጎታ መሥዋዕት ሆኖ ከመሞቱ ከጥቂት ቀኖች በፊት ለሐዋርያቱ ምሳሌውን የተናገረው በሚከተለው መንገድ ነበር።

የመክሊቶቹ ምሳሌ

3. ጌታቸው ከመሄዱ በፊት መክሊቶችን የተቀበሉት ባሮች እርሱ ሄዶ በነበረበት ጊዜ እንዴት አድርገው ተጠቅመውባቸው ነበር?

3 “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ፣ ለአንዱ አምስት መክሊት * ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።

4. የመክሊታቸውን ቁጥር የጨመሩትን ባሮች ጌታቸው ምን አላቸው?

4 “ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ:- ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ፣ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም:- መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታመነሃል፣ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ:- ጌታ ሆይ፣ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም:- መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታመነሃል፣ በብዙ እሾምሃለሁ፣ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።

5, 6. ሦስተኛው ባሪያ መክሊቱን ለምን እንደቀበረ ያቀረበው ሰበብ ምንድን ነው? ጌታውስ እርሱን ምን አደረገው?

5 “[በመጨረሻም] አንድ መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ:- ጌታ ሆይ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም፤ ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው:- አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፣ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፣ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር።

6 “ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አስር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት። በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”— ማቴዎስ 25:13–30

7. በመክሊቶቹ የተመሰለው ነገር ምንድን ነው?

7 በዚህ ምሳሌ ውስጥ በመክሊቶቹ የተመሰለው ምንድን ነው? በገንዘብ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሁኔታ ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ ነገር ነው። መክሊቶቹ የሚያመለክቱት ለክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የተሰጠው ተልዕኮ ነው። ከዚህ ተልዕኮ ጋር አብሮ የሚሄደው ከፍተኛ መብት ለዓለም ሕዝቦች በሙሉ መንግሥቱን በመወከል ለንጉሡ ለክርስቶስ እንደ አምባሳደር ሆኖ የመሥራቱ አጋጣሚ ነው።— ኤፌሶን 6:19, 20፤ 2 ቆሮንቶስ 5:20

8. (ሀ) ‘የሃኬተኛው’ ባሪያ ክፍል ‘በዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ውስጥ የተጣለው ወደየትኛው ጨለማ ነው? (ለ) የሰው ዘር ዓለም የአምላክን የሞገስና የበረከት ብርሃን ሊያገኝ ያልቻለው ለምንድን ነው?

8 ዛሬ ይህ ትንቢታዊ ምሳሌ ፍጻሜውን ወደሚያገኝበት መደምደሚያ ላይ እንደደረስን ምንም አያጠራጥርም። በዚህ ትውልድ ላይ በሰው ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የጨለማ ዘመን መጥቶበታል! በእርግጥም ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ውጭ “ሃኬተኛ” እና ‘የማይጠቅም’ የሆነው የባሪያ ክፍል በጌታው ትእዛዝ መሠረት ሊጣልበት የሚችል ተስማሚ የሆነ ጨለማ አለ። እንዲህ ያለው ‘በውጭ ያለ ጨለማ’ በተለይ በሃይማኖት አንጻር ሲታይ በሰው ዘር ዓለም ላይ ያለውን የጨለመ ሁኔታ ያመለክታል። የሰው ዘር ዓለም የአምላክን ሞገስና በረከት ብርሃን አላገኘም። ስለ አምላክ መንግሥት በተገለጸው የእውቀት ብርሃን ውስጥ አይደለም። ይህ የሰው ዘር ዓለም ያለው “የአምላክ ምሳሌ የሆነው የክርስቶስ ክብር የምስራች ብርሃን እንዳያበራ፣ የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ” ባሳወረው ‘በዚህ የነገሮች ሥርዓት አምላክ’ ስር ነው።— 2 ቆሮንቶስ 4:4 አዓት

9. (ሀ) በምሳሌው አፈጻጸም ላይ ‘በሰውየው’ የተመሰለው ማን ነው? እርሱስ ምን ያህል ርቆ ተጉዞ ነበር? (ለ) የእርሱን መመለስ ለማመልከትስ ምን ማስረጃ አለ?

9 ወደ ሩቅ አገር የተጓዘው በንብረቱ ውስጥ ቢያንስ ስምንት የብር መክሊቶች ባሉት የተመሰለው “ሰው” ለመመለሱ ዛሬ ያለው ማስረጃ ብዙ ነው። ይህ “ሰው” ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ወደ ሩቅ አገር ያደረገው ጉዞ በአጽናፈ ዓለማችን ውስጥ ያሉት የፀሐይ፣ የጨረቃና የከዋክብት ፈጣሪ ወደሚገኝበት ቦታ አድርሶታል። መመለሱንም ለማሳየት ዓለም አቀፍ የሆኑ ሁለት ታላላቅ ጦርነቶች ተደርገዋል፤ እነርሱንም በመከተል አነስተኛ የሆኑ ሌሎች ብዙ ጦርነቶች ምድራችንን በደም እንድትታጠብ አድርገዋታል። በትንቢት እንደተነገረው ከእነዚህ ሌላ ረሃብ፣ ቸነፈርና የመሬት መንቀጥቀጥ ደርሷል፤ የዓመፃ ብዛት መጥቷል፤ በመላውም ምድር ላይ “ይህ የመንግሥት ምስራች” እየተሰበከ ነው። ይህም ኢየሱስ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያና (የእርሱ) መገኘት ምልክት” ሲል የዘረዘረውን ሁኔታ ፈጽሞታል።— ማቴዎስ 24:3–15 አዓት

10. (ሀ) ሰውየው ወደ ሩቅ አገር የሄደው ለምን ነበር? (ለ) የሰው ዘር ዓለምስ የእርሱን መመለስ በቀጥታ ያላየው ለምን ነበር?

10 በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ ተለይቶ ባይጠቀስም እንኳ ወደ ሩቅ አገር የተጓዘው ሰው አስቀድሞ በማቴዎስ 25:1 ላይ እንደተገለጸው ይህንን ጉዞ ያደረገው “መንግሥተ ሰማያትን” ለመረከብ ነበር። በእስራኤል ላይ ይገዛ የነበረው መንግሥቱ በ607 ከዘአበ የተገለበጠበት ይሖዋ አምላክ አንደኛው የዓለም ጦርነት ቢፈነዳም እንኳ የመንግሥቱ መረገጥ በሚያቆምበት ትክክለኛ ጊዜ በ1914 ላይ መብት ያለውን የመንግሥቱን ወራሽ አንግሦታል። የአሕዛብ ብሔራት ንጉሥ ዳዊት “ጌታዬ” ብሎ የጠራው ንጉሥ ንግሥናውን ሲቀበል በሥጋዊ ዓይናቸው አላዩም። (መዝሙር 110:1) ሊያዩት ያልቻሉትም በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሩቅ አገር ከመሄዱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “ከዚህ በኋላ ዓለም አያየኝም” ብሎ ስለተናገረ ነው።— ዮሐንስ 14:19

11. (ሀ) የእርሱን መመለስና መገኘት ለማሳየት የተሰጠው ምልክት አንዱ ክፍል ምን ነበር? (ለ) ይህስ የሚከናወነው መቼ ነው?

11 ክርስቶስ በሰማይ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ለመጨበጥ ሲመጣ ለሰው ዓይኖች ስለማይታይ በሰማያዊው መንግሥቱ መገኘቱን ሰማዕት ሆኖ ከመሞቱ ከሦስት ቀን በፊት ሐዋርያቱ በጠየቁት ምልክት አማካኝነት ግልጽ ማድረግ ነበረበት። የዚህ አሳማኝ ምልክት አንዱ ክፍል የሆነው ሰውየው ከሩቅ አገር ተመልሶ ስለ እነዚህ ዋጋማ መክሊቶች ባሪያዎቹን መቆጣጠሩ ነው። ይህም ስለ ሆነ በመክሊቶቹ ለመጠቀም ጥሩ አጋጣሚ ባገኙት ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ከ1914 በኋላ የሚከናወን ነገር ነበር።

12. (ሀ) የመንግሥቱን ምስክርነት በመስጠት የመሪነቱን ቦታ የመያዙ ግዴታ የወደቀው በእነማን ላይ ነው? (ለ) የመጨረሻው መዳናቸው የተመካውስ በምን ላይ ነው?

12 ይህም ማለት “የመንግሥተ ሰማያት” ወራሾች ከሆኑት ጋር ሒሳብ መተሳሰብ ማለት ነበር። ይህም በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ በአምላክ መንፈስ የተዋጀው የክርስቲያን አካል ክፍል ቀሪዎች በሆኑት ላይ የተደረገውን ቁጥጥር ያመለክታል። (ሥራ ምዕራፍ 2) ከ1914 ጀምሮ ባለው በዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ውስጥ የእነዚህ ቀሪዎች የሆኑ በምድር ላይ ይኖራሉ። በዚያን ጊዜም “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም የመሪነቱን ቦታ የመያዝ ግዴታ የሚወድቅባቸው እነዚህ ይሆናሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10) ድነው ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንዲችሉ እስከ መጨረሻው ድረስ ታማኝ የመሆን ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (ማቴዎስ 24:13) የመጨረሻ መዳናቸውን እንዲጨብጡ ለማስቻል ዓለም አቀፍ የሆነ ስደት ቢኖርም እንኳ ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ እስከ አሁን ድረስ እንዲጸኑ አጠንክሯቸዋል። ይህም ተጨባጭ ሁኔታ እርሱ እንደተቀበላቸው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው!

መክሊቶቹን በአደራ ተረክበናል ባዮቹ ሐሰተኞች

13. (ሀ) መክሊቶቹ ተሰጥተውኛል ባይዋ ማን ናት? (ለ) በእርሷስ ላይ ምን ብለን ለመፍረድ እንገደዳለን?

13 ሕዝበ ክርስትና በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተገለጸው ሀብታም ሰው የሰጣቸውን መክሊቶች በታማኝነት በአደራ እንደተቀበለች ትናገራለች። ይሁን እንጂ ከ1914 ጀምሮ ስትከተለው የቆየችውን መንገድ ስንመለከት ምን ብለን ለመፍረድ እንገደዳለን? እንደምትናገረው ሆና አልተገኘችም ወደሚለው መደምደሚያ እንደርሳለን። በምሳሌው ላይ ለተገለጸው ሰው ታማኝነቷን በማፍረስ ራሷን የዚህ ዓለም መንግሥታት ደጋፊ አድርጋለች፤ የእነዚህ ዓለማዊ መንግሥታት ፖለቲከኞች ውሽሞቿ ናቸው። እርሷም በአሁኑ ጊዜ ከሥራ ውጭ ሆኖ ያለው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተተኪ የሆነውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ትደግፋለች።

14. ዛሬ ሕዝበ ክርስትናን የምናገኛት የት ነው?

14 ሌላው ቀርቶ ሃኬተኛ እንደሆነ ከተረጋገጠውና በጌታው ንብረት ላይ ትርፍ ካላስገኘው አንድ መክሊት የተቀበለ ባሪያ ጋር እንኳ አትስተካከልም። ስለዚህ አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1918 ወደ መደምደሚያው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ሕዝበ ክርስትና ምን ጊዜም ቢሆን ደማቅ ብርሃን ከሚበራበት ከጌታው ቤት ውጭ ባለው ጨለማ ውስጥ ያለች መሆኗ ተጋልጧል። በምሳሌያዊ አነጋገር በውጭ ባለው ዓለም በጠፍ ጨለማ ውስጥ ልቅሶዋና ጥርስ ማፋጨትዋ ቀደም ብሎ መፈጸም ጀምሯል። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቋ ባቢሎን ውስጥ ዋነኛዋ ተነቃፊ ክፍል በመሆን ፖለቲካዊ ውሽሞቿ ሲዞሩባትና ራቍቷን ሲያደርጓት ተጨማሪ ልቅሶ ይመጣባታል።

‘የክፉው ባሪያ’ ክፍል ወደ ውጭ ተጣለ

15. ሃኬተኛውን ባሪያ የሚመስሉት እነማን ናቸው? በአሁኑ ጊዜስ የት ላይ ይገኛሉ?

15 በመንፈስ የተቀቡት ቀሪዎች ክፍል የነበሩትና የመንግሥቱን ውድ ሀብት በአደራ የተቀበሉት ነገር ግን ለሚመለሰው ጌታ ትርፍ ለመጨመር ጥረት ማድረጋቸውን ያቆሙት ከጌታው ንጉሣዊ አገልግሎት ውጭ ተጥለዋል። (ማቴዎስ 24:48–51) ከዚያ በኋላ የሃኬተኛው “ክፉ ባሪያ” ክፍል ‘ይህንን የመንግሥት ምሥራች’ ሲሰብክ አላየነውም። ከዚያ ይልቅ የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማስፋፋት በመጣር ፋንታ ስለ ግል መዳናቸው ለመራቀቅ ይጥራሉ። በአሁኑ ጊዜ እነርሱ የሰው ዘር ዓለም በሚገኝበት ‘በውጭ ባለው ጨለማ’ ውስጥ ይገኛሉ። ምሳሌያዊ መክሊታቸው ከእነርሱ ተወስዶ በዚህ በቀረው “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ጊዜ ውስጥ በዚህ መክሊት ሊጠቀምበት ፈቃደኝነት ላሳየው ክፍል ተሰጥቷል።

16. (ሀ) ይህ ጊዜ በጣም አመቺ የሆነው ምሳሌያዊዎቹን መክሊቶች ለምን ዓላማ ለመጠቀም ነው? (ለ) የ“ሌሎች በጎች” ክፍል በሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ላይ የወደቀው ግዴታ ምንድን ነው?

16 “በመክሊቱ” ይኸውም መግዛት ለጀመረው ንጉሥ “አምባሳደር” በመሆኑ ልዩ መብት ወይም አጋጣሚ በመጠቀምና ደቀ መዛሙርት በማድረግ “የመንግሥቱን ምሥራች” ለማወጅ ከዚህ የበለጠ አመቺ የሆነበት ጊዜ አልነበረም። (2 ቆሮንቶስ 5:20) እንዲሁም ፍጻሜው በፍጥነት እየቀረበ ሲሄድ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” በመንፈስ የተመረጡ አምባሳደሮች ቀሪዎች በአደራ የተሰጣቸውን ውድ “መክሊት” ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙበት መርዳት ይገባቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3  ከብር የተሠራ አንድ የግሪክ መክሊት 20.4 ኪሎ ግራም ይመዝን ነበር

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 59 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሃኬተኛውን ባሪያ ጠባዮች የሚያሳዩት ሁሉ ከጌታው አገልግሎት ተባረው ወደ ጨለማ ይጣላሉ