በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ዋስትና ላለው ሕይወት ያለው ምኞት

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ዋስትና ላለው ሕይወት ያለው ምኞት

ምዕራፍ 1

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ዋስትና ላለው ሕይወት ያለው ምኞት

1, 2. ሁሉም የሰው ዘር በአስቸኳይ የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?

እኛ በዚህ ምድር ላይ የምንፈልገው ነገር ሰላምና ዋስትና ያለው ኑሮ ነው። የዚህ የሚያጓጓ ሁኔታ አስፈላጊነት ከዛሬ ይልቅ በጣም አስቸኳይ የሆነበት ጊዜ አልነበረም። ይህ አባባል ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በምድር ዙሪያ ለሚገኙት ለጠቅላላው የሰው ዘር ቤተሰቦችም ጭምር ይሠራል።

2 በአሁኑ ጊዜ ያለው የምድር ሕዝብ ከጊዜያት ሁሉ በበለጠው ጊዜ ውስጥ እየኖረ ነው የምንለው ለዚህ ነው! ‘የምንኖረው በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በጣም አስፈሪ በሆነው የኑክሌር መሣሪያዎች ዘመን ውስጥ ስለሆነ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

3. (ሀ) ብሔራት የኑክሌር ቦምብ ለመያዝ የፈለጉበት ምክንያት ምን እንደሆነ ነው የሚናገሩት? (ለ) ማንኛውም ተራ ሰው የግድ ምን እንደሚያስፈልግ ሊታየው ይችላል?

3 ቢያንስ ቢያንስ ስምንት አገሮች የኑክሌር ቦምብ ለመስራት የሚችሉ መሆናቸው ተገልጿል። እንደዚሁም በ2, 000 ዓመት ላይ 31 አገሮች የኑክሌር መሣሪያዎች ሊኖሩአቸው እንደሚችሉ ተገምቷል። የመጨረሻዎቹን ከፍተኛ ቦምቦች ለምን ለመያዝ እንደሚፈልጉ የሚያቀርቡት ምክንያት ራስን ለመጠበቅና ተመሳሳይ የሆኑ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቁት መንግሥታት ለሚያደርሱት የኑክሌር ጥቃት አጸፋ ለመመለስ ነው የሚል ነው። በዓለም ላይ እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች በመኖራቸው ሁሉም አገሮች እርስ በርስ የግድ እየተቻቻሉ ጐን ለጐን መኖር እንዳለባቸው ማንኛውም ተራ ሰው ሊያስበው የሚችል ነገር ነው።

4. ሰዎች ዋስትና ያለው ሕይወት ለማግኘት የሚያደርጓቸውን ጥረቶች ባያግደውም እንኳን ፈጣሪ ይህንን በተመለከተ ምን ዓላማ አለው?

4 ይሁን እንጂ እኛ የምንፈልገው ሰው ሠራሽ የሆነውን ተራ ሰላምና ከእርሱም ጋር ሰው ሊያመጣው የሚችለውን ዋስትና ያለው ኑሮ ነውን? ምንም እንኳን ፈጣሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምንና ዋስትና ያለውን ሕይወት ለማምጣት ሰው የሚያደርገውን ጥረት ባያግደውም ለሰላምና ዋስትና ላለው ኑሮ ያለንን የተፈጥሮ ምኞት ለማርካት የራሱ የሆነ ፍጹም መንገድ አለው። እርሱን ለማምለክ የሚፈልጉት ዋስትና ያለው ሕይወት አግኝተው እንዳይኖሩ የሚበጠብጧቸውን ሁሉ ጠራርጎ ለማጥፋት የራሱ የሆነ የተቀጠረ ጊዜ አለው። ይህን ለማድረግ የተቀጠረው የእርሱ ጊዜ መቅረቡን በማወቃችን ምንኛ ደስተኞች ለመሆን እንችላለን!

5. ምድርን በሚመለከት በመንፈስ አነሣሽነትና መሪነት የጻፈው መዝሙራዊ ምን አለ? ፈጣሪ ለሰው ያለው ዓላማስ ምንድን ነው?

5 ብጥብጥ የበዛበት የሰው ታሪክ ከታየባቸው በሺህ ከሚቆጠሩት ዓመታት በኋላ ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት ለማግኘት በምድር ዙሪያ የጋለ ምኞት ቢኖር የሚጠበቅ ነገር ነው። ሰው በሕይወት መኖር ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ምድር የሰው መኖሪያ ቦታ ሆና ቆይታለች። በመንፈስ የተመራው መዝሙራዊ “የሰማያት ሰማይ (ለይሖዋ አዓት) ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ብሏል። (መዝሙር 115:16) ሰው ከመጀመሪያው ጀምሮ አምላክ በሰጠው ምድራዊ ቤቱ ውስጥ የተሟላ ኑሮ አግኝቶ እንዲደሰት የፈጣሪ ፍቅራዊ ዓላማ ነበር።

6. የመጀመሪያው ሰውና ዘሮቹ እንደ አምላክ ሊሆኑ የሚችሉት በምን መንገድ ነበር?

6 በዘፍጥረት 2:7 በሚገኘው የፍጥረት ታሪክ መሠረት “አምላክ ሰውን ከምድር አፈር ሰራው፤ በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” (አዓት) የሰውን ዓይነት የሕይወት ደረጃ ያገኘ ወይም ሰው ያለውን የብቃት ደረጃ ያገኘ ይኸውም የመግዛት ችሎታን በመጠቀም እንደ አምላክ ሊሆን የቻለ ሌላ ምንም ፍጥረት በምድር ላይ አልነበረም። ከዚህም በላይ ይህ የመግዛት ችሎታ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ፍጡሮች ተወስኖ የሚቀር ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ የሚገኙት ዘሮቻቸውም ሊጠቀሙበትና ሊያገኙት የሚችሉት ነገር ነበር።

7. አዳም ሚስት ያገኘው እንዴት ነው? ይህች ፍፁም የሆነች ፍጡር ወደ እርሱ ስትቀርብ ምን አለ?

7 ለዚህም ዓላማ ሲል ፈጣሪ ለአዳም አንዲት ሚስት ሰጠው። እርሷም ለወደፊቶቹ ሰብዓውያን የምድር ነዋሪዎች ሁሉ እናት የምትሆን ነበረች። ሰውየው ይህች ፍፁም ፍጡር በፊቱ ቀርባ ሲመለከት እንደሚከተለው ሊል የቻለው ለዚህ ነው:- “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፤ ሥጋም ከሥጋዬ ናት።” ስለዚህም አንድን ወንድ ለማመለከት ኢሽ ተብሎ የሚተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ሴትን ለማመልከት በሚጠቀምበት አጠራር ኢሽሻህ ብሎ ጠራት።— ዘፍጥረት 2:21–23

8. ፈጣሪ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓውያን ባልና ሚስት ምን መመሪያዎችን ሰጣቸው?

8 ፈጣሪያቸውና ሰማያዊ አባታቸው ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት:- “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ግዙአትም” ብሏቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ይህ አሠራር የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጡራን ታሪክ ውስጥ ፍፁም አዲስ የሆነ ነገር ነበር። በማይታዩት ሰማያት ያሉት መንፈሳዊ ነዋሪዎች ወደ ህልውና የመጡት በመዋለድ አልነበረም።

9. መዝሙር 8:4, 5 መለኮታዊውን የነገሮች ዝግጅት እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?

9 ስለዚህም ምድር በተፈጠረችበት ጊዜ ‘አጥቢያ ኮኮቦች በአንድነት መዘመራቸውና የአምላክም ልጆች ሁሉ እልል ማለታቸው’ ምንም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። (ኢዮብ 38:7) በዚያን ጊዜ በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ሁሉም ሰላማዊና ስምምነት ያለው ነበር። በመዝሙር ምዕራፍ ስምንት ውስጥ መዝሙራዊው በመለኮታዊው የነገሮች አደረጃጀት በመመሰጥ ሰውን በሚመለከት እንዲህ አለ “ሰውን አምላክን መሰል ከሆኑት በጥቂት እንዲያንስ አደረግኸው፣ የክብርና የግርማ ዘውድ ጫንህለት።” (ቁጥር 4, 5 አዓት) በዚህ መዝሙር መሠረት አምላክ በዚህ ምድር ላይ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከሰው ሥር አድርጓቸዋል።

ተቀናቃኝ የሆነ የበላይ ገዥነት ጀመረ

10. (ሀ) የመጀመሪያው ሰብዓዊ ሕፃን ከመፀነሱ በፊት ምን ነገር ተቀሰቀሰ? (ለ) ስለዚህ በሰው ዘር ላይ ምን ሊቋቋም ቻለ?

10 የሚገርመው ግን የመጀመሪያው ሰብዓዊ ልጅ ከመጸነሱ በፊት በአጽናፈ ዓለማዊው የይሖዋ አምላክ ድርጅት ውስጥ አመጽ ተቀሰቀሰ። የሰው ዘር ከይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ድርጅት ከተለየና ከተገነጠለ ይህ ሁኔታ በሰው ዘር ላይ አዲስ የበላይ ገዥነት፣ አዲስ የሆነ የላቀ አገዛዝ ወደ ማቋቋም ሊመራ የሚችል ነበር። ተቀናቃኝ የበላይ ገዥነት ሊቋቋም ይችላል። ይህ እንዲሆን ግን የይሖዋ አምላክን ስም በውሸት የሚያጠፋ የመጀመሪያው የሐሰት ቃል መነገር ነበረበት።

11. ስለ ይሖዋ አምላክ የተሳሳተ መግለጫ በመስጠቱ የመጀመሪያው ዓመፀኛ ምን ሆነ?

11 የመጀመሪያው ውሸት መነገሩ አምላክን በመቃወም አመጸኛ የሆነውን ይህንን ፍጡር የመጀመሪያው ሐሰተኛ፣ የመጀመሪያው ዲያብሎስ ወይም ስም አጥፊ አደረገው። ከእርሱ ጋር ሲነጻጸር በጣም ልዩ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” አለ። (ዮሐንስ 14:6) ለሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም፤ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”— ዮሐንስ 8:44

12. (ሀ) ዲያብሎስ የመጀመሪያው ውሸት እንዲነገር ያደረገው እንዴት ነበር? ይህስ በሔዋን ላይ ያስከተለው ውጤት ምን ነበር? (ለ) አዳም የተከለከለውን ፍሬ ሲበላ ውጤቱ ምን ሆነ?

12 በዔድን የአትክልት ቦታ ወይም በደስታ ገነት ውስጥ ዲያብሎስ በእባብ አማካኝነት በመናገር የመጀመሪያውን ውሸት ለመጀመሪያዋ ሴት አቀረበላት። እርሱም ፈጣሪዋ ሐሰተኛ ነው በማለት የሔዋንን የአእምሮ ሰላም በጠበጠው። ለካስ የማላውቀው ነገር አለ ብላ በማሰብ የስጋት ስሜት አሳደረባት፤ በዚህም ምክንያት ከተከለከለው ፍሬ ወሰደችና በላች። በኋላም በባሏ በአዳም ላይ በማየል ከተከለከለው ፍሬ ከእርሷ ጋር እንዲካፈልና በይሖዋ አምላክ ላይ ባደረገችው አመጽ እንዲተባበራት አደረገችው። (ዘፍጥረት 3:1–6) ታዛዥ ሳይሆኑ የቀሩት ባልና ሚስት ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ሰላም አጡና የስጋት ኑሮ ለመኖር ከደስታ ገነት ተባረሩ። ሮሜ 5:12 ይህንን አሳዛኝ የነገሮች ሁኔታ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል:- “ስለዚህም ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት እንዲሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።”

13. በዛሬው ጊዜ ሁላችንም ማድረግ የሚኖርብን ምርጫ ምንድን ነው?

13 የጊዜያችን ሁኔታ ቁርጥ ያለ ምርጫ እንድናደርግ ይጠይቅብናል። ይህም ተቀናቃኝ በሆነው “የዚህ የነገሮች ሥርዓት አምላክ” በሰይጣን ዲያብሎስ የበላይነትና የአጽናፈ ዓለሙ የበላይና ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ የበላይ ገዥነት መካከል የሚደረግ ምርጫ ነው።— 2 ቆሮንቶስ 4:4 መዝሙር 83:18 አዓት

ከአምላክ ጋር ደስታ የሚሰጥ ሰላም ማግኘት የሚቻልበት መንገድ

14. አሁንም ቢሆን ልናገኘው የምንችለው ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት ምንድን ነው?

14 አብዛኞቹ የሰው ዘሮች ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አሁን ባለው በጣም አሳዛኝ የሰብዓዊ ነገሮች ሁኔታም እንኳን ቢሆን አምላኪዎቹ በመጠኑ ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት ለማግኘት እንዲችሉ ያዘጋጀውን ዝግጅት ለመቀበልም ሆነ ለማመን ስለማይፈልጉ ራሳቸውን ለጕዳትና ለሥቃይ ዳርገዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ “ሰላምን የሚሰጥ አምላክ ነው” ስለዚህም አሁን ሊከሽፍ ወደማይችለው ወደዚህ ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት መግባቱ የተባረከ መብታችን ነው። (ሮሜ 16:20 አዓትፊልጵስዩስ 4:6, 7, 9) ይሖዋ ምን ጊዜም ትምክህት የሚጣልባቸውን ተስፋዎቹን በመፈጸም አሁንም እንደ አንድ አካል ሆነው ለሚሠሩት ለምድራዊ አገልጋዮቹ ወይም ለሚታየው ድርጅቱ ይህን ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት ሰጥቷል። ይህም በምድር ላይ ካለው የሚታይ ድርጅቱ ጋር የቅርብ ግንኙነት በማድረግ ብቻ ልናገኘው የምንችለው ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት ነው።

15. አምላክ አንድ ድርጅት እንዳለው ማሰቡ ምክንያታዊ ያልሆነ ነገር ነውን? ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የተቀበለው ነገር ምንድን ነው?

15 አምላክ እርሱ ከሌሎች ለይቶ የሚቀበለው አንድ ድርጅት፣ አንድ የተደራጀ ሕዝብ የለውም ብሎ ማመኑ ግልጽ ከሆኑት የቅዱሳን ጽሑፎች ትምህርቶች ጋር አይስማማም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አባቱ የሚታይ ድርጅት እንዳለው አምኖ ተቀብሏል። በ33 እዘአ እስከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ድረስ የአምላክ የተደራጀ ሕዝብ የነበረው በሙሴ ሕግ ሥር ከይሖዋ አምላክ ጋር በገባው የቃል ኪዳን ዝምድና መሠረት የአይሁዳውያኑ ድርጅት ነበር።— ሉቃስ 16:16

16. (ሀ) ሙሴ መካከለኛ የነበረው በማንና በማን መካከል ነበር? (ለ) ታላቁ ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ የሆነው በማንና በማን መካከል ነው?

16 ልክ ጥንታዊው የእስራኤል ሕዝብ መካከለኛ በነበረው በሙሴ በኩል ከይሖዋ አምላክ ጋር በቃል ኪዳን ዝምድና ውስጥ እንደነበረ ሁሉ የመንፈሳዊው እስራኤል ሕዝብ ይኸውም “የአምላክ እስራኤል” በአንድ መካከለኛ በኩል የቃል ኪዳን ዝምድና አለው። (ገላትያ 6:16) ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ ከእርሱ ጋር ይሠራ ለነበረው ክርስቲያን:- “አንድ እግዚአብሔር አለና በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛ ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ብሎ እንደጻፈለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:5) ሙሴ በይሖዋ አምላክና በጠቅላላው የሰው ዘር መካከል መካከለኛ ነበርን? አልነበረም፣ እርሱ መካከለኛ የነበረው በአብርሃም፣ በይስሐቅ እንዲሁም በያዕቆብ አምላክና የእነርሱ ሥጋዊ ተወላጆች በሆኑት በዘሮቻቸው መካከል ነበር። በተመሳሳይም ታላቁ ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስ በይሖዋ አምላክና በሁሉም የሰው ዘር መካከል ያለ መካከለኛ አይደለም። እርሱ መካከለኛ የሆነው በሰማያዊው አባቱ በይሖዋ አምላክና 144, 000 ብቻ የሆኑ የተወሰኑ አባሎች ባሉት በመንፈሳዊ እስራኤል መካከል ነው። ይህ መንፈሳዊ ሕዝብ የይሖዋ በግ መሰል ሰዎች የተሰባሰቡበት አንድ ትንሽ መንጋ ነው።— ሮሜ 9:6፣ ራእይ 7:4

‘ከታናሹ መንጋ’ በተጨማሪ በሌሎችም ላይ እረኛ ነው

17. (ሀ) ይሖዋ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምን ሥራ ሰጥቶታል? (ለ) ኢየሱስ የሰማያዊውን መንግሥት ለሚወርሱት ምን አላቸው?

17 በመዝሙር 23:1 ላይ የጥንቱ እስራኤል ንጉሥ ዳዊት “ይሖዋ እረኛዬ ነው። ምንም አይጎድልብኝም” (አዓት) ብሎ እንዲጽፍ በመንፈስ ተመርቶ ነበር። ከሁሉም በላይ የሆነው እረኛ ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን “መልካሙ እረኛ” እንዲሆን ሾሞታል። (ዮሐንስ 10:11) በሉቃስ 12:32 ላይ ኢየሱስ እርሱ መልካም እረኛ ለሆነላቸው ሰዎች ሲናገር:- “አንተ ታናሽ መንጋ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ” ብሏቸው ነበር።

18. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ለናታኒምና እስራኤላዊ ላልሆኑት የሰለሞን አገልጋዮች አምሳያ የሆኑት እነማን ናቸው? (ለ) እነርሱስ ከእነማን ጋር የቅርብ ግንኙነት መሥርተዋል?

18 በጥንት ዘመን ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የቅርብ ግንኙነት መሥርተው የነበሩት አይሁዳዊ ያልሆኑት ናታኒምና እስራኤላዊ ያልሆኑት የሰለሞን አገልጋዮች ልጆች ነበሩ። (ዕዝራ 2:43–58፣ 8:17–20) ዛሬም በተመሳሳይ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ነገር ግን መንፈሳዊ እስራኤላውያን ያልሆኑ ወንዶችና ሴቶች አሉ። ይሁን እንጂ ‘ራሱን ለሁሉም ተመጣጣኝ ቤዛ አድርጎ በሰጠው’ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ በመወሰናቸው ከመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6 አዓት) በዛሬው ጊዜ እነዚህ ሰዎች ሰማያዊውን መንግሥት የሚወርሱትን 144, 000 መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ቁጥር በብዙ ይበልጣሉ።

19. ‘ከታናሹ መንጋ’ በተጨማሪ በሌሎችም ላይ እረኛ እንደሚሆን ለማሳየት ኢየሱስ ክርስቶስ ምን አለ?

19 ስለዚህም አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ በኩል ምድራዊ ወራሾች ለመሆን በሚመጡት በጣም ታላቅ በሆኑ በግ መሰል መንጋ ላይ እረኛ ሆኖ እንዲሠራ ተወስኖ ነበር። እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ በአእምሮው ይዟቸው የነበረው እነዚሁኑ ነበር:- “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።” እነዚህን “ሌሎች በጎች” በአእምሮው በመያዝ ሐዋርያው ዮሐንስም ስለ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ጻፈ:- “እርሱ የኃጢአታችን ማስተሰሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።”— ዮሐንስ 10:16፣ 1 ዮሐንስ 2:2

20. (ሀ) ‘የሌሎች በጎች’ ቁጥር ‘ከታናሹ መንጋ’ ቀሪዎች ጋር ሲወዳደር እንዴት ነው? (ለ) የመልካሙ እረኛ አባታዊ እንክብካቤ ለሁሉም ምን ያስገኝላቸዋል?

20 በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ በጎች የሆኑት የ“ታናሹ መንጋ” ቀሪዎች አባላት ነን የሚሉ 8, 700 የሚያህሉ ሰዎች አሉ። በሌላ በኩል ግን የመልካሙን እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ራሳቸውን የወሰኑ ሰዎች አሉ። እነዚህም በምድር ዙሪያ ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ ይገኛሉ። የዚህ መልካም እረኛ አባታዊ እንክብካቤ ለሁሉም ምን ያስገኝላቸዋል? ሰላምንና አስተማማኝ ሕይወትን ማግኘት ማለት ነው! በመሀከላቸው ሰላም ባይኖራቸው ኖሮ በመካከላቸው ልባዊ የሆነ አንድነትና ሊበጠስ የማይችል ኅብረት ባልኖረም ነበር። መንፈሳዊ ጥቅሞችን በሚመለከት እርስ በርሳቸው የጋራ የሆነ ፍቅራዊ መተሳሰብ ባይኖራቸው ኖሮ አሁን ያላቸውን ዋስትና ያለው ኑሮ አያገኙም ነበር። ስለዚህም በመላው ምድር ላይ ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት እንዲመጣ ያላቸው ምኞት አሁንም ቢሆን ሊፈጸምላቸው ጀምሮአል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰው ለሰላምና ዋስትና ያለው ኑሮ ለማግኘት ያለውን ፍላጐት ለማርካት ፈጣሪ ፍጹም የሆነ የራሱ መንገድ አለው