በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአዲሱ ቃል ኪዳን በኋላ— የሺው ዓመት መንግሥት

ከአዲሱ ቃል ኪዳን በኋላ— የሺው ዓመት መንግሥት

ምዕራፍ 14

ከአዲሱ ቃል ኪዳን በኋላ— የሺው ዓመት መንግሥት

1, 2. (ሀ) በሚልዮን የሚቆጠሩት የአዲሱ ቃል ኪዳን አሠራር ተጠቃሚዎች በዛሬው ጊዜ ከማን ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ? (ለ) የአዲሱ ቃል ኪዳን የውል ቃላት ምን ይላሉ?

በመላው ምድር ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምንም እንኳ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ባይሆኑም ቀደም ብለው ከዚህ ቃል ኪዳን አሠራር ታላላቅ ጥቅሞችን አግኝተዋል። እነርሱ የሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን ገና ይሠራ በነበረበት ጊዜ ይኖሩ ከነበሩት እስራኤላውያን ያልሆኑ ነዋሪዎች ጋር ይመሳሰላሉ። (ዘፀአት 20:10) ታዲያ ይህ ቁጥራቸው እየጨመረ በመሄድ ላይ ባለውና ዛሬ ካሉት የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት በመሠረቱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ላይ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

2 በኤርምያስ 31:31–34 ላይ በሚገኘው ትንቢት ውስጥ የአዲሱን ቃል ኪዳን ብቃቶች የደነገገው አምላክ እንዲህ ይላል:- “ሕጌን በልቦናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።”

3. (ሀ) አሮጌው የሙሴ ቃል ኪዳን ሕግ ለእስራኤል የተሰጠው በምን መልክ ነበር? (ለ) የክርስቲያን የግሪክ ጽሑፎች መጻፍ ከመጀመራቸው በፊት አምላክ የአዲሱን ቃል ኪዳን ሕጎች እንዲጻፉ ያደረገው የት ላይ ነበር?

3 የሕጉን ቃል ኪዳን በሚመለከት ይሖዋ አምላክ መካከለኛ በነበረው በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ለሥጋዊ እስራኤላውያን “ድንጋጌዎችን የያዘውን . . . በእጅ የተጻፈ ሠነድ” ሰጥቷቸው ነበር። (ቆላስይስ 2:14 አዓት) ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን ሕግስ ምን ሊባል ይቻላል? የዚህ ቃል ኪዳን መካከለኛ ይህንን ሕግ በድንጋይ ላይ የሚቀርጸው ወይም በብራና ላይ የሚጽፈው አልነበረም። መካከለኛው የራሱ የሆኑ ምንም ጽሑፎችን አልተወም። የአዲሱ ቃል ኪዳን ሕግ ምን እንደሆነ የምናውቀው በመንፈስ ከተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይሁን እንጂ እነዚህ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በ41 እዘአ አካባቢ ከመጻፋቸው በፊትም ቢሆን ይሖዋ የአዲሱን ቃል ኪዳን ሕጉን መጻፍ ጀምሮ ነበር። መቼ? በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ነው። የጻፈውስ የት ላይ ነበር? ከረጅም ጊዜ በፊት:- “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ” ብሎ ቃል በገባበት በዚያው ነገር ላይ ነበር። — ዕብራውያን 8:10

4. አምላክ ሕጎቹን በአገልጋዮቹ ልብና አእምሮ ላይ መጻፉ ምን ጥሩ ውጤቶች ይኖሩታል?

4 እነዚህ ሕጎች በልብ ላይ የተቀረጹ በመሆናቸው የሚታዘዙአቸው ሰዎች እነርሱን ከመውደድ ወደኋላ የማለታቸው ሁኔታ የቀነሰ ነው። እነዚህ ሕጎች “በልቡናቸው” ውስጥ የሚቀመጡ ከሆኑ እነርሱን ለመርሳት የሚኖረው ዕድል ያነሰ ነው። ስለዚህም እነዚህን ሕጎች የሚጠብቁት የሚከተሉትን የመዝሙር 119:97 ቃላት ይናገራሉ:- “አቤቱ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።” ከውስጥ ስሜታቸው በመገፋፋት የእርሱ መካከለኛ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለተሰጡት ለይሖዋ ሕጎች ያላቸውን ፍቅር ያሳያሉ። ስለዚህም በትክክለኛ ግፊት በመገፋፋት እነዚህን ውድ ሕጎች ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋሉ። ይህ ነገር በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለገቡት ‘ታናሽ መንጋም’ ሆነ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ላልገቡት ነገር ግን በእርሱ ስር ላሉት የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ይሠራል።— ከ1 ዮሐንስ 5:3፤ ከዮሐንስ 14:15 ጋር አወዳድር

ስለ መንግሥቱ የተነሣው ጥያቄ በሁሉም ፊት ተደቀነ

5. የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ በማቴዎስ 24:12–14 ላይ ምን ትንቢት ተናገረ?

5 የአዲሱን ቃል ኪዳን ሕጎች የሚጠብቁት ሰዎች መካከለኛው ኢየሱስ ክርስቶስ “የዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት” ክፍል ይሆናል ብሎ በተነበየው በሚከተለው ሁኔታ እንዳይሸነፉ መጠንቀቅ አለባቸው:- “ከዓመፃም ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ምሥራች በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”— ማቴዎስ 24:3, 12–14 አዓት

6. (ሀ) ማቴዎስ 24:14 እንዲሁ ትንቢት ብቻ ነበርን? (ለ) ከትንቢት የበለጠ አድርገው የተመለከቱት እነማን ናቸው? ጽናታቸውን በሚመለከትስ ምን ሊባል ይቻላል?

6 ይህ ስለ መንግሥቱ ምድር አቀፍ ምስክርነት እንደሚሰጥ የሚገልጸው የመጨረሻው ዐረፍተ ነገር እንዲሁ ትንቢት ብቻ አይደለም። ‘በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ለሚኖሩት ደቀመዛሙርቱ የተሰጠ መመሪያ ነው። ይህም ፍቅር የለሽ የሆነውና ለአምላክ ሕግ አክብሮት እንደጎደለው በመታየቱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በዐመፅ የተሞላው ይህ የነገሮች ሥርዓት ወደ መጨረሻው ፍጻሜው እስከሚመጣ ድረስ ለትክክለኛው አካሄዳቸው የተሰጠ መመሪያ ነው። በዛሬው ጊዜ እነዚህን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት ለእነርሱ እንደተሰጠ መመሪያ አድርገው የሚወስዱት እነማን ናቸው? ከ1919 ጀምሮ እየበዙ የመጡት ታሪካዊ ማስረጃዎች በትክክል “የይሖዋ ምስክሮች ናቸው!” የሚል መልስ ይሰጣሉ። መንግሥቱን በሚመለከት ያከናወኑት የመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ዘመቻ በታሪክ መዝገብ ከፍተኛ ቦታ አለው፤ ባለፉት 67 ዓመታትም በዚህ ሥራ መጽናታቸውን አሳይተዋል። አሁንም ቢሆን ሥራው በየዓመቱ በስፋትና በኃይል በመጨመር ላይ ነው።

7, 8. (ሀ) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሰይጣን በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ያሉትን ምን ለማድረግ ሞክሮ ነበር? (ለ) ከጦርነቱ በኋላ በነበረው ጊዜ መንግሥቱን የሚመለከት ጥያቄ በሁሉም ፊት የተደቀነው እንዴት ነበር?

7 ሰይጣን ዲያብሎስ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አነስተኛ ቁጥር የነበራቸውን የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎች ጠርጎ በማጥፋት ይህንን ታላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ዘመቻ ለማገድ ሙከራ አድርጎ ነበር። ሆኖም አልተሳካለትም! በ1919 የበጋ ወቅት ላይ እንደሞቱ መስለው ከነበሩበት ሁኔታ ከነቁ በኋላ ወዲያውኑ የመጀመሪያውን ድኅረ–ጦርነት ስብሰባቸውን በዚያኑ ዓመት በመስከረም ወር በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ አድርገዋል። መስከረም 1922 በሴዳር ፖይንት በተደረገው ሁለተኛ ስብሰባ ላይ የመንግሥቱ ጥያቄ በሁሉም ፊት ተደቀነ። በዚያ “ቀኑ” ተብሎ በተሰየመው ትልቅ ስብሰባ አራተኛ ቀን ላይ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዝደንት አስደናቂ የሆነውን ንግግሩን እንደሚከተለው ብሎ በማድመቅ ወደ መጨረሻው መደምደሚያው አምጥቶት ነበር:-

8 “እንግዲያው እናንተ የልዑል አምላክ ልጆች ወደ መስኩ ተመለሱ! መሣሪያችሁን ታጠቁ! የተረጋጋችሁ ሁኑ፣ ንቁዎች ሁኑ፣ የምትንቀሳቀሱ ሁኑ፣ ጠንካሮች ሁኑ። ለጌታ ታማኞችና እውነተኛ ምስክሮች ሁኑ። ሁሉም የባቢሎን ርዝራዥ ባድማ እስከሚሆን ድረስ በትግሉ ወደፊት ግፉ። መልዕክቱን እስከ ሩቅ ድረስ በስፋት አውጁ። ዓለም ይሖዋ አምላክ እንደሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። ይህ የቀኖች ሁሉ ቀን ነው። እነሆ፣ ንጉሡ ይገዛል! እናንተ የእርሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።”

የበለጠ በማስተዋል ይሖዋን ማወቅ

9. (ሀ) ያችን የጽድቅ መንግሥት በሚመለከት ያሉት ማስረጃዎች እየጨመሩ በመሄዳቸው ሰዎች ምን አቋም መውሰድ ይኖርባቸዋል? (ለ) ተገቢውን አቋም የወሰዱት ምን እውቀት ተሰጥቷቸዋል?

9 ክርስቶስ በ1914 በመንግሥታዊ ስልጣን ከተሾመ አሁን ከ70 ዓመታት በላይ ሆኖታል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአምላክን የጽድቅ መንግሥት በሚመለከት ያለው ማስረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የዓለም ሕዝቦች የመንግሥቱን አከራካሪ ጉዳይ በሚመለከት ወይ መንግሥቱን በመደገፍ ወይም በመቃወም አቋም መውሰድ አስፈልጓቸዋል። ያንን መለኮታዊ አገዛዝ ደግፈው በቆሙት በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚከተሉት የአዲስ ኪዳን አስፈላጊ ቃላት እየተፈጸሙባቸው ነው:- “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፣ እያንዳንዱም ወንድሙን:- [ይሖዋን (አዓት)] እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና።”— ኤርምያስ 31:34

10. (ሀ) የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎች “ሌሎች በጎች” የሆኑትን መቀበል የጀመሩት በምን ስያሜ ስር በመሆን ነው? (ለ) “ሌሎች በጎች” ምን እውቀት አግኝተዋል?

10 በ1935 የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎች የመልካሙን እረኛ “ሌሎች በጎች” ሁሉም የይሖዋ ምስክሮች በመሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ባለው “አንድ መንጋ” ሕያው ወደ ሆነ አንድነት መቀበል ጀምረዋል። ከዚያም አስቀድሞ የተወሰነ ቁጥር ባይኖራቸውም “እጅግ ብዙ ሰዎች” ለመሆን መገንባት የጀመሩት “ሌሎች በጎች” በመንፈስ ከተዋጁት ቀሪዎች ጋር በመሆን ‘የአምላክን ትእዛዛት ለማክበር’ እና ‘ለኢየሱስ የመመስከሩን ሥራ’ ለመሥራት ቍርጥ ውሳኔ አድርገዋል። (ራእይ 7:9–17፤ 12:17) በዚህም መንገድ ከ1935 ጀምሮ እነዚህ “ሌሎች በጎች” ጭምር “ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ” ይሖዋን አውቀውታል።

11. ስለ ይሖዋ ያለው የክርስቲያን እውቀት በሕጉ ቃል ኪዳን ስር አይሁዶች ከነበራቸው የተለየና የተሻለ የሆነው እንዴት ነው?

11 ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ስለ ይሖዋ ያለው እውቀት በጥንቱ በሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን ስር የነበሩት አይሁዶች ከነበራቸው እውቀት የሚለየውና የተሻለ የሆነው በምን መንገድ ነው? ሰማያዊው የአዲስ ቃል ኪዳን አድራጊ በመቀጠል:- “በደላቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና” ብሎ ይነግረናል። (ኤርምያስ 31:34፤ ዕብራውያን 8:12) ይህም የሆነው አዲሱ ቃል ኪዳን የተመሠረተው በተሻለ መሥዋዕትና መካከለኛ በመሆኑ ነው። (ዕብራውያን 8:6፤ 9:11, 12, 22, 23) የተሻለው መካከለኛ ያቀረበው የተሻለው መስዋዕት በሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን ስር በዓመታዊው የስርየት ቀን ይደረግ እንደነበረው መደጋገም አያስፈልገውም። (ዕብራውያን 10:15–18) ከዚህ ሁሉ አንጻር ሲታይ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥና ከእርሱ ስር ያሉት ስለ ይሖዋ ያላቸው እውቀት በሕጉ ቃል ኪዳን ስር የነበሩት አይሁዶች ስለ አምላክ ከነበራቸው እውቀት በእርግጥም የተሻለ፣ የበለጠ የዳበረ፣ የበለጠ ጥልቀት ያለው፣ የበለጠ የተሟላ ነው።

12. ከሁሉም በላይ ይሖዋ ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ በገቡትና ከሥሩ ባሉት ላይ ምን ሥልጣን አለው?

12 ከሁሉም በላይ የቃል ኪዳኑ አድራጊ ይሖዋ አምላክ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ በሚያስገባቸውም ሆነ ከእርሱ ስር በሚያደርጋቸው ላይ ንጉሥ ነው። (ማቴዎስ 5:34, 35፤ ኤርምያስ 10:7) ኢየሱስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ከመሾሙ ከ1850 ዓመታት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ የአዲሱን ቃል ኪዳን በሚታዘዙት ላይ ይሖዋ ያለውን ንግሥና እንዲህ በማለት አመልክቶ ነበር:- “ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምሥጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፣ አሜን።”— 1 ጢሞቴዎስ 1:17

“ከታላቁ መከራ” በኋላ የሚገዛው የሺህ ዓመት መንግሥት

13. (ሀ) “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከአዲሱ ቃል ኪዳን ወደሚፈስሱት በረከቶች ሙሉ በሙሉ የሚገቡት መቼና በምን ሁኔታዎች ስር ይሆናል? (ለ) አዲሱ ቃል ኪዳን የትኛውን ታላቅ ዓላማ ይፈጽማል?

13 በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ያልገቡት ነገር ግን በዚያ ስር ያሉት የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” “ከታላቁ መከራ” በሕይወት ይተርፋሉ። ይህ የአሁኑ የተፈረደበት የነገሮች ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስና የእርሱ ተባባሪ ወራሾች በጸዳችው ምድር ላይ ለአንድ ሺህ ዓመት ስለሚገዙ ደስ ይላቸዋል። (ራእይ 7:9–14) ከዚያም የአዲሱ ቃል ኪዳን ዓላማ ይኸውም የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ወራሾች የሆኑትን ‘ለልዩ ውርሻ የተጠሩ አንድ ሕዝብ’ የማስገኘቱ ዓላማ ግቡን ይመታል። (1 ጴጥሮስ 2:9፤ ሥራ 15:14) በአምላክ መንግሥት አማካኝነትም ከጥፋት ለሚተርፉት የ“ሌሎች በጎች” ክፍል ለሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተሟሉ በረከቶች ይዘንቡላቸዋል። ሰይጣን ዲያብሎስና የማይታየው አጋንንታዊ ድርጅቱ ወደ ጥልቁ ስለሚጣሉ ጣልቃ ለመግባት አይችሉም።— ራእይ 21:1–4፤ 20:1–3

14. ከጥፋት የሚተርፉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ምን ጥሩ ዝግጅት ይኖራቸዋል?

14 ከጥፋት የሚተርፉት የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” በአዲሱ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ አዲስ ሕይወት ለመጀመር አስቀድመው ዝግጅት አድርገዋል። እንደ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎች ሁሉ እነርሱም አምላክን “ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ” ያውቁታል። (ኤርምያስ 31:34) አሁን በመግዛት ላይ ያለው ንጉሥ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ አንድ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) ስለዚህ ይህ አጽናፈ ዓለማዊ የሆነ የይሖዋ አምላክ እውቀት የዘላለም መዳንን የሚያስገኝ ይሆናል። ይህም እውነት የሚሆነው “ከታላቁ መከራ” በሕይወት ለሚተርፈው “ሥጋ” ብቻ ሳይሆን የንጉሡን ድምጽ ሰምተው ከመታሰቢያ መቃብራቸው ለሚወጡት በብዙ ቢልዮን ለሚቆጠሩት ሰብዓዊ ሙታንም ጭምር ነው። አስፈላጊ የሆነው ሁሉም የይሖዋ እውቀት ከሞት ለተነሡት ለእነዚህ ሙታን ይሰጣቸዋል።— ማቴዎስ 24:21, 22፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:11–15

15. የአዲሱ ቃል ኪዳን መፈጸም የ“ሌሎች በጎች” ክፍል ለሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ምንም ኪሣራ የማያስከትል የሚሆነው ለምንድን ነው?

15 የአምላክ አዲስ ቃል ኪዳን በታላቅ ሁኔታ ተሳክቶ መፈጸሙ ከዚህ ከተፈረደበት የነገሮች ሥርዓት ጥፋት ለሚተርፉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሆኑ በግ መሰል ሰዎች ኪሳራ የሚያስከትል አለመሆኑ ደስ ያሰኛል። ከዚህ ይልቅ እነርሱ በሚወርሷትና ወደ ምድር አቀፍ ገነትነት ለመለወጥ የመጀመሪያ ድርሻ በሚያገኙባት በጸዳችው ምድር ላይ ከዚህ የበለጡ በረከቶችን እንዲያገኙ መንገድ የሚከፍት ይሆናል። (ማቴዎስ 25:34፤ ሉቃስ 23:43) ምድርን እያበላሹአት ያሉት በቅርቡ ይወገዳሉ፤ “[ይሖዋን (አዓት)] ተስፋ የሚያደርጉት ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:9–11) ሁሉም የአዲሱን ቃል ኪዳን መፈጸም ተከትሎ የሚመጣውን ‘በሰላሙ መስፍን’ የሚገዛውን የይሖዋ አምላክን የሺህ ዓመት መንግሥት በዕልልታ ይቀበሉት!

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 119 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥቱ ምሥራች የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት በመላዋ ምድር ላይ ይሰበካል