በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የሰላሙን መስፍን” አርማጌዶን ከፊቱ ይጠብቀዋል

“የሰላሙን መስፍን” አርማጌዶን ከፊቱ ይጠብቀዋል

ምዕራፍ 2

“የሰላሙን መስፍን” አርማጌዶን ከፊቱ ይጠብቀዋል

1, 2. (ሀ) አምላክ ነቢዩ ኢሳይያስ ምን አስደናቂ የሆኑ ቃላትን እንዲናገር በመንፈስ አነሳሥቶ መራው? (ለ) እነዚህስ ቃላት መፈጸም የጀመሩት መቼ ነበር?

ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት በስምንተኛው መቶ ዘመን ነቢዩ ኢሳይያስ ለአምላክ ሕዝቦች እንደሚከተለው ብሎ እንዲጽፍ በመንፈስ ተመርቶ ነበር:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ (መስፍን) ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”— ኢሳይያስ 9:6, 7

2 እነዚህ አስደናቂ ቃላት በ2 ከዘ.አ.በ. መጨረሻ ላይ መፈጸም ጀመሩ። ይህም የሆነው በኢየሩሳሌም ከተማ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ሲገዛ የነበረው የንጉሥ ዳዊት ዝርያ ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ ነበር።

ለሰላሙ ፍጻሜ ለሌለው መንግሥት የተደረገ ቃል ኪዳን

3. (ሀ) አምላክ ከንጉሥ ዳዊት ጋር ምን ቃል ኪዳን አደረገ? (ለ) ይሖዋ “የሰላም መስፍን” የሚለውን ስም የሰጠው ለየትኛው የንጉሥ ዳዊት ዝርያ ነው?

3 ዳዊት ለእስራኤል አምላክ አምልኮት በነበረው ቅንዓት ምክንያት ይሖዋ በእርሱ የትውልድ መስመር በኩል ስለሚመጣ ዘላለማዊ መንግሥት ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። (2 ሳሙኤል 7:1–16) ይህም ቃል ኪዳን በአምላክ መሐላ የተደገፈ ነበር። (መዝሙር 132:11, 12) በዚያ ቃል ኪዳን መሠረት የዳዊት መንግሥት ለመጭው ‘ለሰላሙ መስፍን’ መንግሥት መሠረት መጣል ነበረበት። ይሖዋ “የሰላም መስፍን” የሚለውን ስያሜ የሰጠው ‘የዳዊት ልጅ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ’ ነው።— ማቴዎስ 1:1

4. (ሀ) የኢየሱስ ምድራዊ እናት የሆነችው ማን ናት? (ለ) ይህንን በሚመለከት መልአኩ ገብርኤል ምን አላት?

4 የኢየሱስ እናት በንጉሥ ዳዊት ንጉሣዊ መስመር ውስጥ የተወለደች ሴት ነበረች። የዳዊት ዙፋን ዘላለማዊ ወራሽ የሚሆነውን ቃል የተገባለትን ልጅ በፀነሰች ጊዜም ድንግል ነበረች። ይህ ፅንስ የጀመረው ዮሴፍ እርሷን እንደ ሚስቱ አድርጎ ከመውሰዱ በፊት ነበር። (ማቴዎስ 1:18–25) መልአኩ ገብርኤል ድንግል ለነበረችው ለማርያም እንደሚከተለው ሲል ገልጾላት ነበር:- “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ (ይሖዋ አዓት) አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”— ሉቃስ 1:31–33

5. ነቢዩ ኢሳይያስ ‘የሰላሙን መስፍን’ አገዛዝ በሚመለከት ምን ትንቢት ተናገረ?

5 ነቢዩ ኢሳይያስ ‘የሰላሙን መስፍን’ በሚመለከት “በዳዊት ዙፋን ላይ ለሚኖረው ንጉሣዊ ሥልጣኑና ለሰላሙ ፍጻሜ የሌለው፣ ግዛቱ ሰፊ የሆነ ነው” ብሎ የተናገረው ለዚህ ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ስለዚህ ከዳዊት ጋር በተደረገው ቃል ኪዳን መሠረት ይህ መንግሥት ለሰላሙ ፍጻሜ የማይኖረው ዘላለማዊ መንግሥት ይሆናል። ዙፋኑ “ለዘላለም” ሊቆም ይገባዋል!

6. (ሀ) የመንግሥቱን ቃል ኪዳን ለመፈጸም አምላክ ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን ምን አደረገ? (ለ) ኢየሱስ “የሰላም መስፍን” በመሆን መግዛት የጀመረው መቼ ነው?

6 ይህንን የመንግሥት ቃል ኪዳን ለማስፈጸም ሁሉን የሚችለው አምላክ ኢየሱስን ሰማዕት በሆነ በሦስተኛው ቀን ላይ ከሞት አስነሣው። ይህም የሆነው በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በአይሁዳውያኑ የኒሳን ወር በ16ኛው ቀን ነበር። ከሞት ለተነሣው የአምላክ ልጅ የዓይን ምስክር በመሆን ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ “በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” አለ። (1 ጴጥሮስ 3:18) የሁሉ የበላይ የሆነው አምላክ እርሱን በቀኙ እስከ ማስቀመጥ ድረስ ከፍ ከፍ አደረገው። በዚያም ከአሕዛብ ዘመን ወይም “ከተወሰነው የአሕዛብ ዘመን” ፍጻሜ ይኸውም ከ1914 የጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ አንስቶ እርሱ “የሰላም መስፍን” በመሆን ሲገዛ ቆይቷል።— ሉቃስ 21:24

7. (ሀ) ኢየሱስ ከግዛቱ መጀመሪያ ጀምሮ ምን ገጥሞታል? (ለ) ለአሕዛብ ሁሉ የኢየሱስን ንግሥና የሚያውጁት እነማን ናቸው? ይህስ የምን ትንቢት ፍጻሜ ነው?

7 ሰማያዊ ግዛቱን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ምድርን ለመግዛት በተነሣው አከራካሪ ጉዳይ በተደረጉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች ላይ እንደ ታየው እርሱን አጥብቆ የሚጠላ ዓለም ገጥሞታል። በአሁኑ ጊዜም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፊት ለፊቱ ተጋርጦበታል። በምድር ዙሪያ ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምስክሮች በሚሰብኩት የመንግሥት ምሥራች እወጃ አማካኝነት በሰማያት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የመጀመሩ ጉዳይ የሁሉንም ሕዝቦች ትኩረት እንዲያገኝ ተደርጓል። ይህም “የሰላሙ መስፍን” ራሱ በማቴዎስ 24:14 ላይ እንደምናነበው “ይህ የመንግሥት (ምሥራች አዓት) በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሎ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው።

8. ወደዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” በጣም ጠልቀን ገብተናል ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?

8 ዓለምን ጠቅልሎ የሚገዛው ማን ነው የሚለው ጥያቄ በቅርቡ መልስ ማግኘት ይኖርበታል። “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በ1914 ከተፈጸሙበት ከ70 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ አሁን “በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ውስጥ ጠልቀን ገብተናል። የ1914ቱ ትውልድ በኢየሱስ የተተነበዩትንና ትርጉም ያላቸውን የዓለም ሁኔታዎች ሲጀምሩ ተመልክቷል። (ማቴዎስ 24:3–14) ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ እንደማያልፍ ተናግሯል። በአሁኑ ጊዜም ዕድሜው ወደ ማብቃቱ በጣም ተቃርቧል።— ማቴዎስ 24:34

9, 10. (ሀ) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ትንቢታዊ ሐሳብ ወደ እኛ የተላለፈው እንዴት ነው (ለ) ራእይ 16:13, 14, 16 ስለ ሐርማጌዶን ወይም ስለ አርማጌዶን ምን ነገር ይተነብያል?

9 ታዲያ ከፊታችን የተደቀነው ምንድን ነው? ‘የሰላሙ መስፍን’ ምን ሁኔታ ይጠብቀዋል? ይህንን ሁኔታ ራሱ ከአምላክ በመቀበልና ከሸመገለው ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር በመልአኩ አማካይነት ግንኙነት በማድረግ በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው መጽሐፍ ይኸውም በራእይ ወይም በአፖካሊፕስ መጽሐፍ ውስጥ በትንቢት አስነግሯል። (ራእይ 1:1, 2) ይህ ትንቢት የተነገረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር መጨረሻ አካባቢ ነበር። በራእይ 16:13, 14, 16 ላይ ኢየሱስ ሐዋርያው ዮሐንስን ስለ ሐርማጌዶን ወይም ስለ አርማጌዶን የሚከተለውን ጉልህ ትርጉም ያለው መግለጫ እንዲናገር አድርጎታል:-

10 “ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሦስት በመንፈስ አነሳሽነት የሚነገሩ ርኩሳን ቃላት ሲወጡ አየሁ፤ ምልክት እያደረጉ በአጋንንት መንፈስ አነሳሽነት የሚነገሩ ቃላት ናቸውና፣ በታላቁም ሁሉን በሚችለው በአምላክ ቀን ወደሚሆነው ጦርነት እንዲያስከትቷቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ። በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ አስከተቷቸው።” (አዓት)

ምሳሌያዊው “የመጊዶ ተራራ”

11. (ሀ) አርማጌዶን የሚለው ስም ምን ትርጉም አለው? እንደዚህ ተብሎ የሚጠራ መልክዓ ምድራዊ ቦታስ ነበረን? (ለ) የጥንቱ የመጊዶ ከተማ ታሪካዊ ትርጉም ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? (ሐ) መጊዶ የሚለው ስም ምን ሁለት ዓይነት ትርጉም ያለው ሆነ?

11 ሐርማጌዶን ወይም አርማጌዶን የሚለው የዕብራይስጥ ስም “የመጊዶ ተራራ” ማለት ነው። በጥንት ጊዜም ሆነ በዘመናችን የመጊዶ ተራራ ተብሎ የሚጠራ ምንም መልክዓ ምድራዊ ቦታ የለም። ስለዚህም በምሳሌያዊ አነጋገር በተሞላው እንደ ራእይ ባለው መጽሐፍ ውስጥ ቃሉ ምሳሌያዊ ትርጉም አለው ማለት ነው። ይህስ ትርጉም ምን መሆን ይኖርበታል? አዎን፣ “የጦር ሠራዊቶች ክምችት” የሚል የስም ትርጉም ያለው በከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኘው የመጊዶ ከተማ ታላቅ ታሪካዊ ግምት የሚሰጠው ነው። በዓለማዊና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ውስጥ ይህ ስም ወሳኝ የሆኑ ጦርነቶች ትዝታዎችን ይቀሰቅሳል። ለምን? በወቅቱ ከተማው ስትራተጂያዊ የሆነውን በአውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ መካከል ያለውን መተላለፊያ መንገድ ይቆጣጠር ስለ ነበረ ነዋሪዎቹ ወራሪዎችን ገትረው ሊይዙና ወደፊት የሚያደርጉትን ግስጋሴ ለማገድ ምቹ ሆኖላቸው ነበር። በዚህም ምክንያት መጊዶ ሁለት ዓይነት ትርጉም ያለው ስፍራ ሆኖ ነበር። ይኸውም ለአንደኛው ወገን አሳዛኝ የሆነ ሽንፈት ለሌላው ወገን ደግሞ ክብራማ የሆነ ድል ነው።

12, 13. (ሀ) በመስፍኑ በባርቅ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ከመጊዶና አጠገቡ ከነበረው ወንዝ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የታወቀው እንዴት ነበር? (ለ) ባርቅና ዲቦራ የዘመሩት የድል መዝሙር በዚህ ድል ውስጥ አምላክ የነበረውን ድርሻ የሚገልጸው እንዴት ነው?

12 የእስራኤላውያን መሳፍንት በነበሩበት ዘመን የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ከመጊዶና ከዚያ ቅርብ ከሆነው ከቂሶን ወንዝ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ተጠቅሷል። በመስፍኑ በባርቅና በነቢይቱ በዲቦራ ዘመን አምላክ ከመጊዶ ጎረቤት ለነበሩት ለተመረጡት ሕዝቡ የማይረሳ ድል ሰጥቶአቸው ነበር። መስፍኑ ባርቅ 10, 000 ሰዎች ብቻ ሲኖሩት በጦር አዛዡ በሲሣራ የሚመራው የጠላት ሠራዊት ደግሞ ከእግረኛው ጦር በተጨማሪ 900 በፈረስ የሚጎተቱ የጦር ሠረገሎች ነበሩት። ይሖዋ ለሕዝቦቹ ደጋፊ ሆኖ በጦርነቱ ውስጥ ጣልቃ በመግባት የማይገፉ ይመስሉ የነበሩትን የጠላት ሠረገሎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግና የሚጠራርግ ጎርፍ አመጣ። በሲሣራ ሠራዊት ላይ ተዓምራዊ ሽንፈት ከደረሰ በኋላ ባርቅና ዲቦራ ለአምላክ በዘመሩት የድል መዝሙር ውስጥ በዚህ የጠላት ድል አምላክ የነበረውን ድርሻ እንደሚከተለው ብለው ጠቅሰዋል:-

13 “ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፤ በዚያን ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤ የብር ዘረፋም አልወሰዱም። ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። ከዱሮ ዘመን ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው።”— መሳፍንት 5:12, 19–21

14. በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከዚያ የድል መዝሙር ውስጥ ከመጭው የአርማጌዶን ጦርነት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ለሚቀርበው ጸሎት የሚሠሩት የትኞቹ የመዝጊያ ቃላት ናቸው?

14 በመጊዶ ከተገኘው ከዚያ ጥንታዊ ድል በኋላ ባርቅና ዲቦራ መዝሙራቸውን ሲዘጉ የተጠቀሙባቸው በመንፈስ መሪነት የተዘመሩ ቃላት ያለ አንዳች ጥርጥር ከመጭው የአርማጌዶን ጦርነት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ለሚቀርበው ጸሎት የሚሠሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እነርሱም እንዲህ ብለው ዘመሩ:- “(ይሖዋ ሆይ አዓት)፣ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፣ እንዲሁ ይሁኑ።”— መሳፍንት 5:31 *

ብሔራት ወደ አርማጌዶን እየተሰበሰቡ ነው

15. (ሀ) እንግዲያው አርማጌዶን ምን ዓይነት ቦታ ነው? (ለ) ብሔራትን በአርማጌዶን ወደሚሆነው ጦርነት የሚያስከትታቸው ርኩስ ፕሮፓጋንዳ አንዱ ምንጩ ምንድን ነው?

15 ስለዚህ መጊዶ ወሳኝ ጦርነቶች የተካሄዱበት ቦታ ነበር። በዚህም መሠረት አርማጌዶንም በራእይ 16:13, 14 ላይ በተገለጹት ቀስቃሽ ኃይሎች ገፋፊነት በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ሁሉም ዓለማዊ ብሔራት የሚሰለፉበት የጦር ሜዳ ይሆናል ቢባል ምክንያታዊ ነው። ብሔራትን ለጦር የሚያስከትቱት “በመንፈስ አነሳሽነት የሚነገሩት ቃላት” የሚያመለክቱት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተገለጸው ርኩስ ከሆነው ጓጉንቸር ጋር የሚመሳሰለውንና በአሁኑ ጊዜ እንደ ጓጉንቸር ድምፅ የሚነገረውን ርኩስ ፕሮፓጋንዳ ነው። እንደዚህ ላለው ርኩስ የሆነ ፕሮፓጋንዳ አንዱ ምንጭ ታላቁ ‘ቀይ ዘንዶ’ ነው። ራእይ 12:1–9 ይህ “ዘንዶ” ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል።

16. በራእይ 16:13 ላይ የተገለጸው “አውሬ” ምን ያመለክታል?

16 ሌላው የርኩስ ፕሮፓጋንዳ ምንጭ “አውሬው” ነው። በራእይ 16:13 ላይ ይህ ምሳሌያዊ “አውሬ” ከዲያብሎሳዊው “ዘንዶ” ጋር ተዛምዷል። በራእይ 20:10 መሠረት ይህ “አውሬ” ከምሳሌያዊው “ዘንዶ” ጋር ባለው ኅብረት ምክንያት ለዘላለም ይጠፋል። “አውሬውም” “ዘንዶው” አምላክ የሆነለትን የዚህን ዓለም የፖለቲካ ሥርዓት በጠቅላላ ያመለክታል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እርሱም የዚህን ዓለም የተለያዩ ፖለቲካዊ መንግሥታትን ያጠቃልላል።— ከዳንኤል 7:17፤ 8:20, 22 ጋር አወዳድር።

17. ‘ከአውሬው’ የሚወጣው ጓጉንቸር መሰል ፕሮፓጋንዳ ውጤቱ ምንድን ነው?

17 እንደዚህ ያለው የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት የራሱ የሆነ ልዩ ፕሮፓጋንዳ አለው። እንደ ጓጕንቸር ጩኸት የሚያስተጋባው ይህ ፕሮፓጋንዳ “ከዘንዶው አፍ” ከሚመጣው አጋንንታዊ ቃል ጋር ተዳምሮ “ነገሥታትን” ይኸውም የዓለምን የፖለቲካ ኃይሎች በአርማጌዶን ላይ ወደሚካሄደው “ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ላይ ወደሚደረገው ጦርነት” ለማስከተት ያገለግላል።

18. (ሀ) ሐርማጌዶን የሚለው ስም ምንን ያመለክታል? (ለ) ተራራ ምንን ሊያመለክት ይችላል?

18 እንግዲያው አርማጌዶን ወሳኝ የሆነ ጦርነት የሚከናወንበትን የዓለም ሁኔታ ያመለክታል። የፖለቲካ ገዥዎች በአንድ ላይ በመሆን የአምላክን ፈቃድ ወደ መቃወም የሚደርሱበትንና በዚህም ምክንያት አምላክ በዓላማው መሠረት መልሶ የማጥቃት ርምጃ የሚወስድበትን የዓለምን ጉዳዮች የመጨረሻ ከፍተኛ ሁኔታ ያመለክታል። ስለዚህም የወደፊቱ ሁኔታ የሚወሰነው ይህ ፍልሚያ በሚያስከትላቸው ውጤቶች ይሆናል። መጊዶ ይገኝበት በነበረው መልክዓ ምድራዊ ቦታው ላይ ምንም ተራራ አልነበረም። ይሁን እንጂ ተራራ በዚያ በሚሰበሰቡት በሁሉም ወታደራዊ ኃይሎች በቀላሉ ከሩቅ ሊታይ የሚችለውን አንድ ጐላ ያለ የመሰብሰቢያ ቦታ ሊያመለክት ይችላል።

19, 20. በአርማጌዶን የይሖዋ ሰማያዊ ኃይሎች የጦር አዛዥ የሚጠቀምበት የጦር ስልት ምን ይሆናል? ከምንስ ውጤት ጋር?

19 የይሖዋ ተዋጊ ኃይሎች ጦር አዛዥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለአያሌ ዓመታት የዓለም ገዥዎችና የተዋጊ ኃይሎቻቸው ወደ አርማጌዶን እየገሰገሱ በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ተመልክቷል። ሆኖም እርሱ በነጠላ አንድን የተለየ ንጉሥና ወታደራዊ ኃይሎቹን ለይቶ አንድ በአንድ ለመምታትና በዚህም የጠላትን ኃይሎች በትንሽ በትንሹ ለመጨረስ አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ግን በአንድ ላይ እንዲሰበሰቡና የጦር ኃይላቸውን አስተባብረው የመጨረሻው ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል እንዲኖራቸው በቂ ጊዜ ፈቅዶላቸዋል። ድፍረት የተሞላበት ዓላማው ሁሉንም በአንድ ጊዜ ለመምታት ነው!

20 በዚህ መንገድ በእነርሱ ላይ አንፀባራቂ ድል ይቀዳጃል። ይህም ዋነኛ አለቃውና አዛዡ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ክብርን ሲያመጣለት እርሱ “የነገሥታት ንጉሥ፤ የጌቶች ጌታ” መሆኑን በማያከራክር ሁኔታ ያረጋግጥለታል። — ራእይ 19:16

[የግርጌ ማስታወሻ]

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]