በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የሰላሙ መስፍን” አምላክ “ለሁሉም ሰው ሁሉን ነገር ይሆናል”

“የሰላሙ መስፍን” አምላክ “ለሁሉም ሰው ሁሉን ነገር ይሆናል”

ምዕራፍ 22

“የሰላሙ መስፍን” አምላክ “ለሁሉም ሰው ሁሉን ነገር ይሆናል”

1. በሰማይም ሆነ በምድር ላሉት ለሁሉም ሌሎች ፍጥረታት ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ የተወው በምንድን ነው?

ከትንሣኤው በኋላ ብዙም ሳይቆይ “የሰላሙ መስፍን” ከደቀመዛሙርቱ ለአንዲቱ “እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ” ብሎአት ነበር። (ዮሐንስ 20:17) በእነዚህ ቃላት ሰማያዊው አባቱ እርሱ የሚያመልከው ብቸኛው አምላኩ እንደሆነ አሳውቋል። በዚህ ዓይነቱ አምልኮ በሰማይና በምድር ለሚገኙት ለሌሎች ፍጥረቶች በሙሉ ምሳሌ ትቶአል።

2, 3. (ሀ) 1 ቆሮንቶስ 15:24–26, 28 ኢየሱስ ለአባቱ ያሳየውን ልዩ የመገዛት ሁኔታ የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) ታላቁ ውጤቱስ ምን ይሆናል?

2 “የሰላሙ መስፍን” የመላው አጽናፈ ዓለም ዓይነተኛ የበላይ ገዥ ለሆነው አምላክ በአንድ ልዩ መንገድ ራሱን በታማኝነት ሲያስገዛ ፍጹም ለሚደረገው ለሁሉም የሰው ዘር እንዴት ያለ ታላቅ ምሳሌ ይሆናል! ይህም በሰው ዘር ላይ በሚገዛበት በሺህ ዓመት ግዛቱ መደምደሚያ ላይ ለመላው ምድር ሰላምን፣ ዋስትና ያለውን ሕይወትና ስምምነትን በሚመልስበት ጊዜ ተወዳዳሪ በማይገኝለት መንገድ የሚታይ ይሆናል። ስለዚህም ነገር በማይሳሳተው ትንቢት ውስጥ እንደሚከተለው የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል:-

3 “በኋላም መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉ ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። [አምላክ] ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን [አምላክ ለሁሉም ሰው ሁሉን ነገር] ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።” (1 ቆሮንቶስ 15:24–26, 28) ወይም ዘ አምፕሊፋይድ ባይብል የቁጥር 28⁠ን የመጨረሻ ክፍል እንደተረጎመው “ስለዚህ አምላክ ሁሉ በሁሉ ይሆናል፤ ይህም ሲባል ለሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር የሁሉም የበላይ፣ በሕይወት ውስጥ የሚኖርና የሚቆጣጠር ኃይል ይሆናል።”

4. (ሀ) የምድር ነዋሪዎች አሳዳጊ አባታቸው ላሳየው ምሳሌ ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው? (ለ) በዚያን ጊዜ ምን አዲስ የመገዛት ሁኔታ ይኖራል?

4 “የሰላሙ መስፍን” በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ መንግሥቱን ለአምላኩ ሲያስረክብ የምድር ነዋሪዎች አሳዳጊው አባታቸው ያደረገውን ይህንን ድርጊት እንዲገነዘቡ ይደረጋል። እርሱን እንደ ንጉሣዊ ምሳሌያቸው በማድረግ ከሁሉም በላይ ለሆነው አምላክ በተመሳሳይ መንገድ በአዲስ ሁኔታ ራሳቸውን ያስገዛሉ። አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ለይሖዋ በፍቅራዊ መንገድ ተገዥነታቸውን ያሳያሉ፤ አዎን ከዚያን ጊዜ በኋላ በሚጸልዩበትም ጊዜ እንኳ ቢሆን የኢየሱስ ክህነታዊ አገልግሎቶች ሳያስፈልጓቸው በሙሉ ቅንነትና እውነት ያመልካሉ።

5. የኢየሱስ ክርስቶስ 144, 000 ተባባሪ ነገሥታት እንዴት ያለ ዝንባሌ ያሳያሉ?

5 ከሁሉም በላይ የሆነው አምላክ በዚህ መንገድ እንደገና በሰማይም ሆነ በምድር ምንም ንጉሣዊ ተወካይ ሳይኖረው አጽናፈ ዓለማዊ ንጉሥ ይሆናል። ቀጥሎም ኢየሱስ ከምድር የዋጃቸው 144, 000 ተባባሪ ነገሥታት ከሁሉም በላይ በሆነው ንጉሣዊ ገዥ ፊት ይንበረከካሉ፤ በዚህም ተጨማሪ ሁኔታ የአጽናፈ ዓለም የበላይ ገዥነቱን ያውቁለታል።

በሁሉም የሰው ዘር ላይ የሚመጣ የመጨረሻ ፈተና

6. (ሀ) በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ ታዛዥ የማይሆኑት ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? (ለ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ አባቱ የሚያስተላልፋቸው ሰዎች ሁኔታ ምን ይሆናል?

6 ኢየሱስ ክርስቶስ ይሖዋን እንደ መጨረሻው የበላይ ፈራጅ አድርጎ በመቀበል በሺው ዓመት ግዛቱ ወቅት ያከናወነውን ሥራ ይሖዋ ተመልክቶ የተደሰተበት መሆኑን እንዲገልጽ ይፈልጋል። ይህ ዓይነቱ የመለኰታዊ ሞገስ መግለጫ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚያ አገዛዝ ወቅት ከጽድቅ ብቃቶቹ ጋር ለመስማማት እምቢ የሚሉትና ለንጉሡ አንታዘዝም የሚሉ ሁሉ አስቀድመው ይጠፋሉ። በዚህም መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻው ዳኛ ለይሖዋ አምላክ የሚያስረክባቸው ወደ ሰብአዊ ፍጽምና የደረሱት ታዛዦች ይሆናሉ።

7. (ሀ) ኢየሱስ መንግሥቱን መልሶ ካስረከበ በኋላ መርማሪ የሆነ ፈተና የሚደርስበት ምንድን ነው? (ለ) ፍጹም የተደረገው የሰው ዘር በዚህ ፈተና የሚፈተነው እንዴት ይሆናል?

7 በዚህም ነጥብ ላይ ከአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ከይሖዋ አምላክ ጋር በተያያዘ ሰዎች ያላቸው የአምልኮ ታማኝነት የቱን ያህል ጽናት እንዳለው የሚፈተንበት ጊዜ ይሆናል። በኢዮብ ላይ ከታየው ሁኔታ አንፃር የሚነሣው ጥያቄ:- እነዚህ ሰዎች አምላክን የሚወዱትና የሚያመልኩት እርሱ ስላደረገላቸው መልካም ነገሮች ብቻ ነው ወይስ እርሱን የሚወዱት ራሱ ባለው ሁኔታ ማለትም ትክክለኛው የአጽናፈ ዓለም የበላይ ገዥ በመሆኑ ነው? (ኢዮብ 1:8–11) ይሁን እንጂ ፍጹም የሚደረገው የሰው ዘር የልብ ታማኝነታቸው የሚፈተነው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ለአንድ ሺህ ዓመት ታስረው ከቆዩበት ከጥልቁ “ለጥቂት ጊዜ” ይፈታሉ በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ራእይ 20:3) ወደ ጥሩ ሁኔታ የተመለሰውን የሰው ዘር ዲያብሎስ እንዲፈትናቸው በመፍቀድ ክርስቶስ ወደ ፍጽምና ያደረሳቸው የሰው ልጆች በግለሰብ ደረጃ ለአምላክ እንከን የሌለው የታማኝነት አቋም ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። — ከኢዮብ 1:12 ጋር አወዳድር

8. (ሀ) ሰይጣንና አጋንንቱ ከጥልቁ ሲለቀቁ ምን ለማድረግ ይጥራሉ? (ለ) በዲያብሎስና በአጋንንቱ እንዲታለሉ የሚፈቅዱት ምን እርምጃ ይወስዳሉ?

8 ከሰባት ሺህ ዓመታት በፊት ሰይጣን ዲያብሎስ ፍጹም የነበሩትን አዳምንና ሔዋንን የራስ ወዳድነትን መንገድ በመከተል ኃጢአት እንዲሠሩ በማድረግ ሊያሳስታቸው ችሎ ነበር። ሰይጣንና አጋንንቱ ከጥልቁ ከተለቀቁ በኋላ በምን የፈተና ዘዴዎች እንዲጠቀሙ ይሖዋ እንደሚፈቅድላቸው ቅዱሳን ጽሑፎች አይናገሩም። ይሁን እንጂ ለስስትና ከአምላክ ውጭ ሆኖ በራስ ለመመራት ምኞት ማራኪ ነገር እንደሚኖር ምንም አያጠራጥርም። በይሖዋ የበላይ ገዥነት ላይ ያመፀው ዲያብሎስ ከሰው ዘሮች ውስጥ ዓመፀኞችን ለማግኘት ዓላማ አድርጎ ይነሣል። እነዚህ ከእስር የተለቀቁ አጋንንታዊ ኃይሎች ምን ያህል እንደሚሳካላቸው በትክክል አልተገለጸም፤ ይሁን እንጂ ታላቅ ጭፍራ ሊባሉ የሚችሉ በቂ ሰብአዊ ዓመፀኞች ይኖሯቸዋል። ፍጹም በተደረገው ማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት በዚያን ጊዜ የሚፈጽመው ኃጢአት በማወቅ ስለሚሆን ሆን ተብሎ በፈቃድ የሚሠራ ይሆናል። ይህም ብቻውን እውነተኛ ሕያው አምላክ ከሆነው ፈጣሪ አምልኮ መውጣትንና ከሰይጣን ዲያብሎስ ወገን መሰለፍን ያመለክታል። (ራእይ 20:7, 8) በዚህ ምክንያት ለእነዚህ ዓመፀኞች ይሖዋ “ለሁሉም ሰው ሁሉም ነገር” አይሆንላቸውም።

9. (ሀ) ለይሖዋ አምላክ ያላቸውን ፍጹም የታማኝነት አቋም የማይጠብቁት ምን ይሆናሉ? (ለ) የማይታየው ዓለም ከዓመፀኞች የሚጸዳው እንዴት ነው? (ሐ) በዚያን ጊዜ በመላው ሰማይና በምድር ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ታላቅ ሁኔታ ምንድን ነው?

9 ይሁን እንጂ ታማኝ የሆኑት ሰዎች እነዚያ የተታለሉ ብሔርተኞች በሚያመጧቸው ክርክሮችና ግፊቶች አይበገሩም። ታማኞቹ ያለምንም ማመንታት በራሳቸው ሁኔታ ላይ ይሖዋ “ለሁሉም ሰው ሁሉን ነገር” እንዲሆንላቸው ይመርጣሉ። ለፍትህ ሲባል የይሖዋ የበላይነት በጥብቅ መከበር ይኖርበታል። ስለሆነም በምድር ላይ በሰይጣናዊ ግፊት የወደቁት ዓመፀኞች በሙሉ ለዘላለም ከሕልውና ውጭ ይደረጋሉ። ይህም ግልግል ይሆናል! የማይታየው የፍጥረት ግዛትም ቢሆን ከዓመፀኞች ነፃ መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ የአጽናፈ ዓለሙን ንጽሕና ወደ ፍጻሜው ለማምጣት ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንታዊ ጭፍሮቹ ድምጥማጣቸው ይጠፋል፣ ከሕልውና ውጭም ይደረጋሉ። በዚህ መንገድ ሰማያትና ምድር ከማንኛውም የኃጢአት ምልክት ጨርሶ ይጸዳሉ። (ራእይ 20:9, 10) የይሖዋ ቅድስና በየትም ቦታ ያሸንፋል። (ከዘካርያስ 14:20 ጋር አወዳድር) ከሁሉም በላይ የሆነው አምላክ ቅዱስ ስም በሰማይና በምድር ይቀደሳል። በሰማይና በምድር የሚኖሩት ሁሉ ታላቅ ፈቃዱን በደስታ ያደርጋሉ።

10. ምድር ለዘላለም ሌላ ፕላኔት ያላገኘው የተለየ ሁኔታ የሚኖራት በምን መንገዶች ነው?

10 ምንም እንኳ መኖሪያ የምትሆነው ፕላኔት ምድራችን ብቻ ላትሆን ብትችልም ምድር ወሰን በሌለው ኅዋ ውስጥ የሚገኝ ሌላ ፕላኔት ያላገኘውን ክብር ለዘላለም ታገኛለች። ይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን በማያከራክር መንገድ ያረጋገጠባት ፕላኔት እርሷ ብቻ ትሆናለች። ይህ የይሖዋ እርምጃ ዘላለማዊና አጽናፈ ዓለማዊ የሕግ መመሪያ ይሆናል። የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ላይ በሚደረገው ጦርነት’ ውጊያ ያካሄደባት ብቸኛ ፕላኔት ትሆናለች። የፕላኔቷን ነዋሪዎች ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ይሖዋ ውድ ልጁን ሰው እንዲሆንና እንዲሞት ያደረገባት ብቸኛ ፕላኔት ትሆናለች። ይሖዋ ‘የአምላክ ወራሾች እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ እንዲሆኑ 144, 000 ነዋሪዎችዋን ከእርስዋ የሚወስድባት ብቸኛ ፕላኔት ትሆናለች። — ሮሜ 8:17

ሱራፌሎች፣ ኪሩቤሎችና መላእክት

11, 12. (ሀ) ኢሳይያስ በራእይ የተመለከተው ምን ዓይነት መንፈሳዊ ፍጥረቶችን ነው? (ለ) እነዚህስ ለእኛ ለሰዎች ምን የማድረግ ፍላጎት አላቸው?

11 የሁሉም ፍጥረታት ማለትም የሰማይና የምድር ፍጥረታት ታላቅ ፈጣሪ የሆነው አምላክ ከክርስቶስ ጋር ወራሾች ለሆኑት ለ144, 000ዎቹ ብቻ ሳይሆን በሰማያዊ ግዛቱ ውስጥ ለሚገኙት ለሌሎችም ጭምር “ሁሉን ነገር” ይሆንላቸዋል። በኢሳይያስ መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ላይ ሰማያዊውን የፍርድ ችሎት በትንሹ እንድናይ ተደርገናል። በዚያም ላይ እንዲህ እናነባለን:- “[ይሖዋን (አዓት)] በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፣ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፣ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለቱ ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፣ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፣ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ:- ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የሠራዊት ጌታ [ይሖዋ (አዓት)] ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።” — ኢሳይያስ 6:1–3

12 ኢሳይያስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሆነውን አካል በሰማያዊ ዙፋን ተቀምጦ ክብራማ ሱራፌሎች ሲያገለግሉት በማየቱ ምንኛ በከፍተኛ ሁኔታ ተባርኮ ነበር! ራእዩ እንዴት ያለ አስፈሪ ግርማ ነበረው! እነዚያ ሱራፌሎች እንዴት ያለ ታላቅ ቦታ እንዳላቸው ይገልጻል ምክንያቱም አምላክ በቅድስናው ወደር የለሽ ነው። ሱራፌሎቹ እርሱን ሦስት ጊዜ ቅዱስ እያሉ በመጥራት ስለ ቅድስናው መስክረዋል። አምላክ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ የይሖዋ አምላኪዎችም ቅዱስ እንዲሆኑ ሱራፌሎች ለመርዳት ፍላጎት አላቸው። — ኢሳይያስ 6:5–7

13. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን ሌላ ዓይነት መንፈሳዊ ፍጥረቶችን ይገልጥልናል? (ለ) ይሖዋስ ከእነርሱ አንጻር እንዴት ሆኖ ተገልጾአል?

13 በዚህ ምድር ላይ የይሖዋ አምላክን ኃይል የሚያሳዩ የተለያዩ ፍጥረታት እንዳሉ ሁሉ በመንፈሳዊውም ዓለም ሕይወት ያላቸው ሌሎች ዓይነት ፍጥረታት አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ በመብረር በጣም ፈጣኖች የሆኑ ክብራማ ኪሩቤሎች እንደሆኑ ይገልጻል። (መዝሙር 18:10፤ ከዕብራውያን 9:4, 5 ጋር አወዳድር) አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ በመውሰድ በቅዱሱ የሰማይ አምላክ ላይ ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ፈጣሪ በምሥራቅ በኩል ወደ ተድላ ገነት መልሶ በሚያስገባው መንገድ ላይ ኪሩቤልንና “የምትገለባበጥ የነልባል ሰይፍን” አቁሞ እንደነበረ ዘፍጥረት 3:24 ያሳያል። ይሖዋ “በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ” ተብሎም ተነግሮአል። (መዝሙር 99:1፤ ኢሳይያስ 37:16) በዚህ መንገድ ዙፋኑ ከኪሩቤሎች በላይ እንደሆነ ታይቷል።

14. (ሀ) ሌሎች ሊታለፉ የማይችሉት የትኞቹ መንፈሳዊ ፍጥረቶች ናቸው? (ለ) ቁጥራቸውስ ምን ያህል ብዙ ነው?

14 ስፍር ቁጥር ከሌላቸው መንፈሳዊ ፍጥረቶች መካከል የማይታለፉት መላእክት ናቸው። በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ መላእክት አሉ። (ዳንኤል 7:9, 10) ከእነርሱም መካከል በምድር የሚገኙትን የይሖዋን አምላኪዎች ለማገልገል የተመደቡ መላእክት አሉ። ኢየሱስ ማንም ሰው ከይሖዋ አምላኪዎች መካከል አንዱን እንዳያሰናክል አስጠንቅቋል፤ ምክንያቱም “መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ” ብሎአል። (ማቴዎስ 18:10፤ ዕብራውያን 1:14) ኢየሱስ በምድረበዳ 40 ቀናት ከጾመና ዲያብሎስ ያቀረባቸውን ሦስት ወሳኝ ፈተናዎች በድል አድራጊነት ከተቋቋመ በኋላ ከስቶ የነበረውንና የተራበውን የኢየሱስን አካላዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ማገልገሉ ለመላእክቱ እንዴት ያለ መብት ነበር! — ማቴዎስ 4:11

15, 16. (ሀ) በሰማይና በምድር የሚኖረውን ቤተሰባዊ አንድነት ግለጽ። (ለ) ፈተናውን በአሸናፊነት የሚያልፉት ወደ ፍጽምና የደረሱ ሰዎች ከይሖዋ ምን ሽልማት ይሰጣቸዋል? (ሐ) ይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማው ተከናውኖ ሲመለከት ምን ይሰማዋል?

15 በላይ በሰማያዊው ዓለም ውስጥ ያሉት ክብራማ መንፈሳዊ ነዋሪዎች እርስ በርሳቸው ወንድማማች ይሆናሉ፤ እንዲሁም በዚህ ምድር ላይ ፍጹም የሚሆነው ሰብአዊ ቤተሰብ እርስ በርሱ ወንድማማችና እህትማማች ይደረጋል። አዳምና ሔዋን ከይሖዋ አምላክ የፈጣሪነት እጆች በወጡበት ጊዜ በፈጣሪያቸው ‘መልክና ምሳሌ’ እንደነበሩት ሁሉ እነዚህም በከፍተኛ ደረጃ የአምላክን መልክና ምሳሌ ይይዛሉ። (ዘፍጥረት 1:26, 27) ፍጹም የተደረጉት ሰዎች የመጨረሻውን ፈተና ካለፉ በኋላ ለዘላለም የመኖር መብት ይሰጣቸዋል፤ እንዲሁም “ለእግዚአብሔር ልጆች” በመሆን በሚያገኙት ክብራማ ነፃነት ይደሰታሉ። በሰማይና በምድር የተባበረው የይሖዋ ቤተሰብ ክፍል ይሆናሉ። — ሮሜ 8:21

16 ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያው ዓላማው ግቡን ሲመታ ማለትም ሁሉም ነገር እርሱ አስቀድሞ በወሰነው መሠረት ከእርሱ ጋር የማይበጠስ ፍቅራዊ አንድነት ወደሚያገኙበት ደረጃ ሲደርሱ እንዴት ያለ ደስታ ይሰማው ይሆን!

17. ከዚህ ሁሉ አንጻር ሲታይ ከመዝሙራዊው ቃላት ጋር የሚስማማ ምን ነገር ከማድረግ ሊቆጠብ የማይችለውስ ማን ነው?

17 ከዚህ ሁሉ አንጻር ሲታይ ይህንን አስደናቂ የሆነ የዓላማ አምላክ ከመባረክ ሊቆጠብ የሚችል ማን ነው? መዝሙራዊው ከሰው በላይ ለሆኑት ፍጡሮች “ቃሉን የምትፈጽሙ፣ ብርቱዎችና ኃያላን፣ የቃሉን ድምጽ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፣ [ይሖዋን (አዓት)] ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፣ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፣ [ይሖዋን (አዓት)] ባርኩ” በማለት መናገሩ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ አይደለም። — መዝሙር 103:20, 21

18. መዝሙራዊው የመዝሙራትን መጽሐፍ የሚደመድመው እንዴት ነው?

18 በደስታ የፈነደቀው በመንፈስ የተመራ መዝሙራዊ የመዝሙርን መጽሐፍ በሚከተሉት የማሳሰቢያ ቃላት ይደመድመዋል:- “እናንተ ሰዎች ያህን አመስግኑ! አምላክን በቅዱሱ ቦታው አመስግኑት። በኃይሉ ሰማይ አመስግኑት። በታላቅነቱ ብዛት መጠን አመስግኑት። በመለከት ድምፅ አመስግኑት። በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት። በከበሮና በሽብሸባ አመስግኑት። በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት። ድምጹ መልካም በሆነ ጽናጽል አመስግኑት። እልልታ ባለው ጽናጽል አመስግኑት። እስትንፋስ ያለው ሁሉ ያህን ያመስግነው። እናንተ ሰዎች ያህን አመስግኑት!” — መዝሙር 150:1–6 አዓት

19. (ሀ) በዚያን ጊዜ አጽናፈ ዓለም በምን ማሠሪያ ይተባበራል? (ለ) የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ በመጨረሻ ምን ይላሉ?

19 በመጨረሻም መላው አጽናፈ ዓለም፣ ለዘላለም ጸንቶ በሚኖር ፍጹም ማሠሪያ ይኸውም ልጆቹ ከሁሉም ነገር በላይ ስለሚያፈቅሩትና ስለሚወዱት ለሰማያዊው አባት በሚሰጡት በአንዱ የአምልኮ ማሠሪያ ምክንያት አንድ ይሆናል። አዎን፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረቶች በሙሉ በመጨረሻ ልክ ሱራፌሎች እንዳሉት “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የሠራዊት ጌታ [ይሖዋ (አዓት)] ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች” ይላሉ። ከዚህ በኋላ “የሰላሙ መስፍን” አምላክ በእርግጥም ለዓለምና ለዘላለም “ለሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር” ይሆናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 188, 189 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጠቅላላው አጽናፈ ዓለም የሁሉ የበላይ በሆነው ፈጣሪ አምልኮ ሰላማዊ አንድነት ይኖረዋል