በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 3

ይሖዋ ዓላማውን ይገልጣል

ይሖዋ ዓላማውን ይገልጣል

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ይሖዋ ዓላማውን የሚገልጠው ደረጃ በደረጃ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ግን እሱን ለሚፈሩት ሰዎች ብቻ ነው

1, 2. ይሖዋ ዓላማውን ለሰው ዘር የገለጠው እንዴት ነው?

 አሳቢ የሆኑ ወላጆች፣ የቤተሰባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ በሚያደርጉት ውይይት ላይ ልጆቻቸው እንዲሳተፉ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ለልጆቻቸው ምን ያህል መረጃ እንደሚያካፍሉ በጥንቃቄ ያመዛዝናሉ። የልጆቻቸውን ዕድሜ ግምት ውስጥ በማስገባት ሊረዱት የሚችሉትን ጉዳይ ብቻ ይነግሯቸዋል።

2 በተመሳሳይም ይሖዋ ዓላማውን ለሰብዓዊው ቤተሰብ ደረጃ በደረጃ ሲገልጥ ቆይቷል። ይሁንና ይህን ያደረገው ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቆ ነው። ይሖዋ በታሪክ ዘመናት በሙሉ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ እውነቶችን እንዴት እንደገለጠ በአጭሩ እንመልከት።

መንግሥቱ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

3, 4. ይሖዋ የሰው ዘር ታሪክ ምን መልክ እንደሚኖረው አስቀድሞ ወስኗል? አብራራ።

3 መጀመሪያ ላይ መሲሐዊው መንግሥት በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የተካተተ ጉዳይ አልነበረም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ የሰው ዘር ታሪክ ምን መልክ እንደሚኖረው አስቀድሞ አልወሰነም፤ ደግሞም የሰው ልጆችን የፈጠረው የመምረጥ ነፃነት አጎናጽፎ ነው። በመሆኑም ለአዳምና ለሔዋን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” በማለት ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ ገልጾላቸዋል። (ዘፍ. 1:28) በተጨማሪም ይሖዋ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በተመለከተ ያወጣውን መሥፈርት እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸው ነበር። (ዘፍ. 2:16, 17) አዳምና ሔዋን ታማኞች ሆነው ለመኖር መምረጥ ይችሉ ነበር። እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው ታማኞች ቢሆኑ ኖሮ የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም በክርስቶስ የሚመራውን መንግሥት ማቋቋም አያስፈልግም ነበር። በአሁኑ ጊዜም ምድር ይሖዋን በሚያመልኩ ፍጹም ሰዎች በተሞላች ነበር።

4 ሰይጣን እንዲሁም አዳምና ሔዋን ያስነሱት ዓመፅ ይሖዋ፣ ምድር ፍጹማን በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ያወጣውን ዓላማ እንዲለውጥ አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ዓላማውን ዳር የሚያደርስበትን መንገድ ቀየሰ። የእሱ ዓላማ፣ የመጨረሻ ማቆሚያው ላይ ለመድረስ በተወሰነ መንገድ ላይ ብቻ መጓዝ እንዳለበትና ሌሎች በሚያደርጉት ነገር መስመሩን እንደሚስት ባቡር አይደለም። ይሖዋ ዓላማውን አንድ ጊዜ ከተናገረ በኋላ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለ የትኛውም ኃይል ዓላማው እንዳይፈጸም ማገድ አይችልም። (ኢሳይያስ 55:11ን አንብብ።) አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ መንገዱ ላይ ከተጋረጠ ይሖዋ ሌላ መንገድ ይጠቀማል። a (ዘፀ. 3:14, 15) ተገቢ ሆኖ ባገኘው ጊዜ፣ ዓላማውን ለመፈጸም የሚጠቀምበትን አዲስ መንገድ በተመለከተ ለታማኝ አገልጋዮቹ አስፈላጊውን መረጃ ይሰጣል።

5. ይሖዋ በኤደን ለተነሳው ዓመፅ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

5 በኤደን የተቀሰቀሰው ዓመፅ ይሖዋ መንግሥት እንዲያቋቁም አነሳስቶታል። (ማቴ. 25:34) በሰው ልጅ ታሪክ ላይ ጨለማ ባጠላበት በዚያን ጊዜ ይሖዋ፣ የሰውን ዘር ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ እንዲሁም ሰይጣን ሥልጣን ለመንጠቅ ያደረገው ከንቱ ሙከራ ያስከተለውን ጉዳት ለማስወገድ የሚጠቀምበትን መሣሪያ በተመለከተ ብርሃን መፈንጠቅ ጀመረ። (ዘፍ. 3:14-19) ያም ሆኖ ይሖዋ ስለ መንግሥቱ የሚገልጹ ዝርዝር ጉዳዮችን በአንድ ጊዜ አላሳወቀም።

ይሖዋ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ እውነቶችን መግለጥ ጀመረ

6. ይሖዋ ምን ተስፋ ሰጥቷል? ይሁንና ሳያሳውቅ የቆየው ጉዳይ ምንድን ነው?

6 ይሖዋ የመጀመሪያውን ትንቢት በተናገረ ጊዜ እባቡን የሚጨፈልቅ አንድ ‘ዘር’ እንደሚያስነሳ ቃል ገብቷል። (ዘፍጥረት 3:15ን አንብብ።) ይሁንና የዚህ ዘርም ሆነ የእባቡ ዘር ማንነት በዚያን ጊዜ አልተገለጠም ነበር። እንዲያውም ይሖዋ ትንቢቱን በተመለከተ ለ2,000 ዓመታት ገደማ ዝርዝር መግለጫ ሳይሰጥ ቆይቷል። b

7. አብርሃም የተመረጠው ለምን ነበር? ይህስ ምን ቁልፍ ነጥብ ያስጨብጠናል?

7 ውሎ አድሮ ይሖዋ አብርሃምን በመምረጥ ተስፋ የተደረገበት ዘር በእሱ በኩል እንደሚመጣ አሳወቀ። አብርሃም የተመረጠው ‘የይሖዋን ቃል ስለሰማ’ ነው። (ዘፍ. 22:18) አብርሃም መመረጡ አንድ ቁልፍ ነጥብ ያስጨብጠናል፤ ይሖዋ ዓላማውን የሚገልጠው ለእሱ አክብሮታዊ ፍርሃት ላላቸው ሰዎች ብቻ ነው።መዝሙር 25:14ን አንብብ።

8, 9. ይሖዋ ተስፋ የተደረገበትን ዘር በተመለከተ ለአብርሃምና ለያዕቆብ የገለጠላቸው ነገር ምንድን ነው?

8 ይሖዋ በመልአክ አማካኝነት ወዳጁን አብርሃምን ባነጋገረው ወቅት፣ የተስፋው ዘር ሰው ሆኖ እንደሚመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ በመግለጽ አስፈላጊ የሆነ መረጃ ሰጥቷል። (ዘፍ. 22:15-17፤ ያዕ. 2:23) ይሁንና ይህ ሰው እባቡን የሚጨፈልቀው እንዴት ነው? እባቡ ማን ነው? ከጊዜ በኋላ የተገለጡት እውነታዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።

9 ይሖዋ፣ ተስፋ የተደረገበት ዘር የአብርሃም የልጅ ልጅ በሆነው በያዕቆብ በኩል እንዲመጣ ወሰነ፤ ያዕቆብ በአምላክ ላይ ታላቅ እምነት የነበረው ሰው ነው። (ዘፍ. 28:13-22) ይሖዋ ተስፋ የተደረገበት ዘር በያዕቆብ ልጅ በይሁዳ በኩል እንደሚመጣ በያዕቆብ አማካኝነት ገለጸ። ያዕቆብ ይህ የይሁዳ ዘር ንጉሣዊ ሥልጣንን የሚያመለክት “በትረ መንግሥት” እንደሚቀበልና ለእሱም ‘ሕዝቦች እንደሚታዘዙለት’ ትንቢት ተናግሯል። (ዘፍ. 49:1, 10) ተስፋ የተደረገበት ዘር ንጉሥ ሆኖ እንደሚገዛ ይሖዋ በዚህ ትንቢት አማካኝነት አሳውቋል።

10, 11. ይሖዋ ዓላማውን ለዳዊትና ለዳንኤል የገለጠላቸው ለምንድን ነው?

10 ይሁዳ ከኖረ ከ650 ዓመት ገደማ በኋላ ይሖዋ የይሁዳ ዘር ለሆነው ለንጉሥ ዳዊት ከዓላማው ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃ ሰጥቶታል። ይሖዋ ዳዊትን “እንደ ልቤ የሆነ” ሰው ብሎ ገልጾታል። (1 ሳሙ. 13:14፤ 17:12፤ ሥራ 13:22) ዳዊት ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ስለነበረው ይሖዋ ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፤ በዚህ ቃል ኪዳን መሠረት ከዘሮቹ መካከል አንዱ ለዘላለም እንደሚገዛ ቃል ገብቶለታል።—2 ሳሙ. 7:8, 12-16

11 ከ500 ዓመት ገደማ በኋላ ይሖዋ፣ ይህ ቅቡዕ ወይም መሲሕ በምድር ላይ የሚገለጥበትን ትክክለኛ ዓመት በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት አሳውቋል። (ዳን. 9:25) ዳንኤል በይሖዋ ፊት ‘እጅግ የተወደደ’ እንደሆነ ተገልጿል። ለምን? ምክንያቱም ዳንኤል ይሖዋን በጥልቅ ያከብርና በታማኝነት ያገለግል ነበር።—ዳን. 6:16፤ 9:22, 23

12. ዳንኤል ምን እንዲያደርግ ተነግሮት ነበር? ለምንስ?

12 ይሖዋ እንደ ዳንኤል ባሉት ታማኝ ነቢያት አማካኝነት፣ ተስፋ ስለተሰጠበት ዘር ማለትም ስለ መሲሑ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች እንዲጻፉ አድርጓል፤ ሆኖም አገልጋዮቹ በመንፈስ እየተመሩ የጻፉት ትንቢት የያዘውን የተሟላ ትርጉም የሚረዱበት ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ዳንኤል ስለ አምላክ መንግሥት መቋቋም የሚገልጽ ራእይ ካየ በኋላ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ትንቢቱን እንዲያትም ተነግሮት ነበር። ይህ ጊዜ ሲደርስ እውነተኛ እውቀት “ይበዛል።”—ዳን. 12:4

ይሖዋ እንደ ዳንኤል ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹ ስለ መሲሐዊው መንግሥት ዝርዝር መረጃ እንዲጽፉ አድርጓል

ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ላይ ብርሃን ፈነጠቀ

13. (ሀ) ተስፋ የተደረገበት ዘር ማን ነው? (ለ) ኢየሱስ ዘፍጥረት 3:15 ላይ በሚገኘው ትንቢት ላይ ብርሃን የፈነጠቀው እንዴት ነው?

13 ይሖዋ፣ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት ዘር ይኸውም ንጉሥ ሆኖ የሚገዛ የዳዊት ዘር መሆኑን በግልጽ አመልክቷል። (ሉቃስ 1:30-33፤ 3:21, 22) ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ የሰው ዘር ስለ አምላክ ዓላማ ባለው እውቀት ላይ የፀሐይ ብርሃን የፈነጠቀ ያህል ነበር። (ማቴ. 4:13-17) ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ዲያብሎስን “ነፍሰ ገዳይ” እና “የውሸት አባት” ብሎ በመጥራት ዘፍጥረት 3:14, 15 ላይ የተጠቀሰው ‘እባብ’ ማንነት በግልጽ እንዲታወቅ አድርጓል። (ዮሐ. 8:44) ኢየሱስ ለዮሐንስ በገለጠው ራእይ ላይ ‘የጥንቱን እባብ’ “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው” በማለት ገልጾታል። c (ራእይ 1:1⁠ን እና 12:9ን አንብብ።) በዚሁ ራእይ ላይ ኢየሱስ፣ ተስፋ የተደረገበት ዘር ማለትም እሱ ራሱ፣ በኤደን የተነገረውን ትንቢት በመፈጸም ሰይጣንን የሚጨፈልቀው ይኸውም ከሕልውና ውጭ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ አመልክቷል።—ራእይ 20:7-10

14-16. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የገለጠላቸው እውነት የያዘውን የተሟላ ትርጉም ሁልጊዜ ይረዱ ነበር? አብራራ።

14 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ ብዙ አስተምሯል። ይሁንና ደቀ መዛሙርቱ ማወቅ የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ ሁልጊዜ በዝርዝር አይነግራቸውም ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች ጌታቸው ዝርዝር መረጃ በመስጠት የገለጣቸውን እውነቶችም እንኳ ሙሉ በሙሉ መረዳት የቻሉት ከጊዜ በኋላ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹን እውነቶች የተረዱት ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ነው። እስቲ የተወሰኑ ምሳሌዎችን እንመልከት።

15 በ33 ዓ.ም. ኢየሱስ ለአምላክ መንግሥት ንጉሥ ድጋፍ የሚሰጡ ተባባሪ ገዢዎች ከምድር እንደሚወሰዱና መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው በሰማይ እንደሚኖሩ በግልጽ ተናግሮ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህን ጉዳይ በገለጠላቸው ጊዜ ትርጉሙን ወዲያውኑ አልተረዱትም። (ዳን. 7:18፤ ዮሐ. 14:2-5) በዚያው ዓመት ኢየሱስ መንግሥቱ የሚቋቋመው እሱ ወደ ሰማይ ከሄደ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ በምሳሌ አስረድቷል። (ማቴ. 25:14, 19፤ ሉቃስ 19:11, 12) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ቁልፍ ነጥብ አልተረዱም ነበር፤ እንዲያውም ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ “ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ብለው ጠይቀውት ነበር። ይሁንና ኢየሱስ በዚያን ጊዜ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ መስጠት አልፈለገም። (ሥራ 1:6, 7) ኢየሱስ ተባባሪ ገዢዎቹን ያቀፈው “ትንሽ መንጋ” ክፍል ያልሆኑ “ሌሎች በጎች” እንደሚኖሩም አስተምሯል። (ዮሐ. 10:16፤ ሉቃስ 12:32) የክርስቶስ ተከታዮች የሁለቱን ቡድኖች ማንነት በትክክል የተገነዘቡት መንግሥቱ በ1914 ከተቋቋመ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ነው።

16 ኢየሱስ በምድር ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረበት ጊዜ ሊነግራቸው የሚችለው ብዙ ነገር ቢኖርም ሊሸከሙት እንደማይችሉ ተገንዝቦ ነበር። (ዮሐ. 16:12) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎች ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ብዙ እውቀት እንዳገኙ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ እንዲህ ያለ እውቀት የሚበዛበት ወቅት ገና አልደረሰም ነበር።

‘በፍጻሜው ዘመን’ እውነተኛ እውቀት ይበዛል

17. ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ እውነቶችን ለመረዳት ምን ማድረግ ይኖርብናል? ሌላስ ምን ያስፈልጋል?

17 ይሖዋ ‘በፍጻሜው ዘመን’ ብዙዎች ‘መጽሐፉን በሚገባ እንደሚመረምሩና’ ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጽ ‘እውነተኛ እውቀት እንደሚበዛ’ ለዳንኤል ቃል ገብቶለታል። (ዳን. 12:4) ይህን እውቀት ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ አለባቸው። እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ግስ አንድን መጽሐፍ በጥልቀትና በጥንቃቄ የሚመረምርን ሰው ለማመልከት ይሠራበታል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ምንም ያህል በጥልቀት ብንመረምር የይሖዋን እርዳታ እስካላገኘን ድረስ ስለ መንግሥቱ የሚገልጹ እውነቶችን በሚገባ መረዳት አንችልም።ማቴዎስ 13:11ን አንብብ።

18. ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች እምነትና ትሕትና ያሳዩት እንዴት ነው?

18 ይሖዋ እስከ 1914 ባለው ጊዜ ውስጥ ስለ መንግሥቱ የሚገልጹትን እውነቶች ደረጃ በደረጃ እንደገለጠ ሁሉ በፍጻሜውም ዘመን እንዲህ ማድረጉን ቀጥሏል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 4 እና 5 ላይ እንደምንመለከተው የአምላክ ሕዝቦች ባለፉት 100 ዓመታት የተለያዩ ጉዳዮችን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ ማስተካከል አስፈልጓቸዋል። ይህ ሁኔታ የይሖዋ ድጋፍ እንደሌላቸው ያሳያል? በፍጹም! እንዲያውም የይሖዋ ድጋፍ አልተለያቸውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች እሱ የሚደሰትባቸውን ሁለት ባሕርያት ይኸውም እምነትንና ትሕትናን አሳይተዋል። (ዕብ. 11:6፤ ያዕ. 4:6) የይሖዋ አገልጋዮች በአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱት ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እምነት አላቸው። እነዚህ ተስፋዎች እንዴት እንደሚፈጸሙ በትክክል ያልተረዱባቸው ጊዜያት እንደነበሩ አምነው መቀበላቸው ትሕትናቸውን ያሳያል። በመጋቢት 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው የሚከተለው ሐሳብ ያላቸውን የትሕትና ባሕርይ ያንጸባርቃል፦ “ቃሉን የሚፈታው ጌታ ራሱ እንደሆነ እናውቃለን፤ ቃሉን ለሕዝቡ የሚፈታው በራሱ መንገድና በራሱ ጊዜ ነው።”

“ጌታ . . . ቃሉን ለሕዝቡ የሚፈታው በራሱ መንገድና በራሱ ጊዜ ነው”

19. በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ምን ነገር እንድንረዳ አስችሎናል? ለምንስ?

19 መንግሥቱ በ1914 ሲቋቋም የአምላክ ሕዝቦች ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ትንቢቶች የሚፈጸሙበትን መንገድ በተመለከተ የተሟላ እውቀት አልነበራቸውም። (1 ቆሮ. 13:9, 10, 12) አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ሲፈጸሙ ለማየት ከነበረን ጉጉት የተነሳ የተሳሳቱ መደምደሚያዎች ላይ የደረስንባቸው ጊዜያት ነበሩ። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ፣ ቀደም ባለው አንቀጽ ላይ በተጠቀሰው መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣ ሌላ ሐሳብ ጥበብ የተንጸባረቀበት መሆኑ በግልጽ ታይቷል። መጽሔቱ “‘አንድ ትንቢት ፍጻሜውን እስካላገኘ ወይም በመፈጸም ሂደት ላይ እስካልሆነ ድረስ ልንረዳው አንችልም’ የሚለውን ደንብ መከተል የሚያዋጣ ይመስላል” ይላል። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም እየተቃረበ ባለበት በዚህ ወቅት ስለ መንግሥቱ የሚገልጹ በርካታ ትንቢቶች ተፈጽመዋል፤ ደግሞም እየተፈጸሙ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ትሑትና ለመስተካከል ፈቃደኞች ስለሆኑ ይሖዋ ስለ ዓላማው የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል። በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ እውቀት በዝቷል!

ባለን ግንዛቤ ላይ የሚደረግ ማስተካከያ የአምላክን ሕዝቦች ያጠራል

20, 21. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተደረጉ አንዳንድ ማስተካከያዎች በክርስቲያኖች ላይ ምን ስሜት አሳድረው ነበር?

20 ይሖዋ ስለ እውነት ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ሲያደርግ የልባችን ሁኔታ ይፈተናል። ታዲያ እምነትና ትሕትና የሚደረጉትን ለውጦች እንድንቀበል ያነሳሱናል? በመጀመሪያው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ፈተና አጋጥሟቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በዚያን ጊዜ የምትኖር አይሁዳዊ ክርስቲያን ነህ እንበል። የሙሴን ሕግ በጥልቅ ታከብራለህ፤ እንዲሁም እስራኤላዊ በመሆንህ ትኮራለህ። በዚህ ጊዜ ሕጉ እንደተሻረና ይሖዋ ሥጋዊ እስራኤላውያንን ትቶ ከአይሁዳውያንና ከአሕዛብ የተውጣጡ መንፈሳዊ እስራኤላውያንን መሰብሰብ እንደጀመረ የሚገልጽ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የጻፈው ደብዳቤ ደረሰህ። (ሮም 10:12፤ 11:17-24፤ ገላ. 6:15, 16፤ ቆላ. 2:13, 14) ታዲያ ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር?

21 ትሑት ክርስቲያኖች ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ማብራሪያ የተቀበሉ ሲሆን የይሖዋን በረከትም አግኝተዋል። (ሥራ 13:48) ሌሎች ደግሞ በተደረጉት ማስተካከያዎች ቅሬታ ስላደረባቸው የራሳቸውን ግንዛቤ ሙጭጭ አድርገው መያዝ ፈልገው ነበር። (ገላ. 5:7-12) እነዚህ ሰዎች አመለካከታቸውን ሳይለውጡ ከቀሩ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት መብት ያመልጣቸዋል።—2 ጴጥ. 2:1

22. የአምላክን ዓላማ በተመለከተ ባለን ግንዛቤ ላይ ስለሚደረጉ ማስተካከያዎች ምን ይሰማሃል?

22 ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ይሖዋ ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ያለን ግንዛቤ እንዲጠራ አድርጓል። ለምሳሌ በጎች ከፍየሎች እንደሚለዩ ሁሉ የመንግሥቱ ዜጎችም ለምሥራቹ በጎ ምላሽ ከማይሰጡ ሰዎች የሚለዩበትን ጊዜ ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ እንድንገነዘብ ረድቶናል። በተጨማሪም የ144,000ዎቹ ቁጥር የሚሞላው መቼ እንደሆነ፣ ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የተናገራቸው ምሳሌዎች ምን ትርጉም እንዳላቸውና የመጨረሻው ቅቡዕ ሰማያዊ ሽልማቱን የሚያገኘው መቼ እንደሆነ አስተምሮናል። d እንዲህ ላሉት ማስተካከያዎች ምን ምላሽ ትሰጣለህ? ማስተካከያዎቹ እምነትህን ያጠናክሩታል? እነዚህን ማስተካከያዎች ይሖዋ ትሑት የሆነውን ሕዝቡን ማስተማሩን እንደቀጠለ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? ቀጣዩ ምዕራፍ ይሖዋ ለሚፈሩት ዓላማውን ደረጃ በደረጃ እንደሚገልጥ ያለህን እምነት ይበልጥ ያጠናክርልሃል።

a የአምላክ ስም “መሆን” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግስ የተገኘ ነው። የይሖዋ ስም፣ እሱ ቃል የገባቸውን ተስፋዎች እንደሚፈጽም ያሳያል። በገጽ 43 ላይ የሚገኘውን “የአምላክ ስም ትርጉም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b በአሁኑ ወቅት እነዚህ ዓመታት ብዙ መስለው ቢታዩንም በዚያን ዘመን የነበሩት ሰዎች ዕድሜ በጣም ረጅም እንደነበረ መዘንጋት አይኖርብንም። ለምሳሌ አዳም፣ የኖኅ አባት ላሜሕ እስከኖረበት ዘመን ድረስ ኖሯል። ላሜሕ፣ የኖኅ ልጅ ሴም እስከኖረበት ዘመን ድረስ ኖሯል። ሴም ደግሞ አብርሃም እስከኖረበት ዘመን ድረስ ኖሯል። በመሆኑም ከአዳም እስከ አብርሃም ዘመን ድረስ ያለፈው የጊዜ ርዝማኔ የአራት ሰዎች ዕድሜ ያህል ነው።—ዘፍ. 5:5, 31፤ 9:29፤ 11:10, 11፤ 25:7

c በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ሰይጣን” የሚለው ቃል አንድን አካል ለማመልከት 18 ጊዜ ተሠርቶበታል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ግን “ሰይጣን” የሚለው ቃል ከ30 ጊዜ በላይ ይገኛል። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ለሰይጣን አላስፈላጊ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ የመሲሑን ማንነት ጎላ አድርገው መግለጻቸው የተገባ ነው። መሲሑ በመጣ ጊዜ የሰይጣንን ማንነት ሙሉ በሙሉ አጋልጧል፤ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የያዙት ዘገባ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል።

d በአንዳንዶቹ ማስተካከያዎች ላይ የተሰጡትን ማብራሪያዎች ለማግኘት የሚከተሉትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ተመልከት፦ ጥቅምት 15, 1995 ከገጽ 23-28ጥር 15, 2008 ከገጽ 20-24ሐምሌ 15, 2008 ከገጽ 17-21ሐምሌ 15, 2013 ከገጽ 9-14