በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 14

የአምላክን መንግሥት ብቻ በታማኝነት መደገፍ

የአምላክን መንግሥት ብቻ በታማኝነት መደገፍ

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

የአምላክ ሕዝቦች ለመንግሥቱ ታማኝ መሆን ስለሚፈልጉ ምንጊዜም ቢሆን የዓለም ክፍል አይሆኑም

1, 2. (ሀ) የኢየሱስ ተከታዮች እስከ ዛሬ ድረስ የሚመሩበት መሠረታዊ ሥርዓት የትኛው ነው? (ለ) ጠላቶች እኛን ለማጥፋት ሙከራ ያደረጉት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

 ኢየሱስ፣ ጲላጦስ በተባለው ትልቅ ሥልጣን ያለው ፈራጅ ፊት በቀረበበት ወቅት የተናገረውን ነገር ዛሬም ድረስ እውነተኛ ተከታዮቹ ይመሩበታል። የአይሁድ ብሔር አስተዳዳሪ ለሆነው ለዚህ ሰው እንዲህ ብሎታል፦ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።” (ዮሐ. 18:36) በእርግጥ ጲላጦስ ኢየሱስን አስገድሎታል፤ ሆኖም ድሉ ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። ምክንያቱም ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል። የታላቋ ሮም ነገሥታት፣ የክርስቶስን ተከታዮች ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም ድካማቸው ከንቱ ሆኗል። ክርስቲያኖች የመንግሥቱን መልእክት ጥንት በነበረው ዓለም በሙሉ አሰራጭተዋል።—ቆላ. 1:23

2 በታሪክ ዘመናት ከኖሩት ሁሉ ኃያል የሆኑ አንዳንድ ሠራዊቶች የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተቋቋመ በኋላ የአምላክን ሕዝቦች ከምድር ገጽ ለማጥፋት ሞክረው ነበር። ይሁንና አንዳቸውም ቢሆኑ አልተሳካላቸውም። በርካታ መንግሥታትና የፖለቲካ አንጃዎች ከሌሎች ጋር በሚያደርጉት ውጊያ ከእነሱ ጎን እንድንሰለፍ ሊያስገድዱን ሞክረዋል። እኛን ለመከፋፈል ያደረጉት ሙከራ ግን መና ሆኗል። በዛሬው ጊዜ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች በሁሉም አገሮች ይገኛሉ ማለት ይቻላል። ያም ቢሆን እውነተኛ በሆነ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ስለታቀፍን አንድነት አለን፤ በመሆኑም በዓለም የፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ፈጽሞ ጣልቃ ባለመግባት የገለልተኝነት አቋም እንይዛለን። አንድነታችን የአምላክ መንግሥት እየገዛ እንደሆነ እንዲሁም ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገዢዎቹን እየመራቸውና እያጠራቸው ብሎም ጥበቃ እያደረገላቸው መሆኑን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው። ንጉሣችን ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ቀጥሎ እንመለከታለን፤ እንዲሁም “የዓለም ክፍል [ሳንሆን]” ለመኖር በምናደርገው ጥረት ኢየሱስ በፍርድ ቤት ድሎች እንድናገኝ ረድቶናል፤ እምነት ከሚያጠናክሩት ከእነዚህ ድሎች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመርምር።—ዮሐ. 17:14

ትልቅ ቦታ የተሰጠው ጉዳይ

3, 4. (ሀ) የአምላክ መንግሥት ሲወለድ ምን ሁኔታዎች ተከናወኑ? (ለ) በወቅቱ የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች፣ ገለልተኝነት ሲባል ምን እንደሚጨምር ሙሉ በሙሉ ተረድተው ነበር? አብራራ።

3 የአምላክን መንግሥት መወለድ ተከትሎ በሰማይ ጦርነት የተነሳ ሲሆን ሰይጣንም ወደ ምድር ተወርውሯል። (ራእይ 12:7-10, 12ን አንብብ።) በዚሁ ጊዜ በምድር ላይም ጦርነት ተቀስቅሷል፤ ይህ ጦርነት የአምላክ ሕዝቦች ታማኝነት እንዲፈተን አድርጓል። የአምላክ ሕዝቦች የዓለም ክፍል ባለመሆን ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር። ያም ቢሆን በማንኛውም ፖለቲካዊ ጉዳይ ውስጥ ጨርሶ አለመግባት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መጀመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ አልተረዱም ነበር።

4 ለምሳሌ ያህል፣ በ1904 የታተመው ሚሌኒያል ዶውን  a የተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 6 ክርስቲያኖች በጦርነት ከመካፈል እንዲታቀቡ አበረታትቷቸዋል። ይሁንና አንድ ክርስቲያን የጦር ሠራዊቱ አባል እንዲሆን ከተመለመለ፣ ውጊያን የማይጨምር ምድብ እንዲሰጠው ለማድረግ መጣር እንዳለበት የሚገልጽ ሐሳብ ወጥቶ ነበር። ይህን ማድረግ ካልቻለና ወደ ጦር ሜዳ ከተላከ ደግሞ የሰው ሕይወት ማጥፋት የለበትም። በ1905 የተጠመቀውና በብሪታንያ የሚኖረው ወንድም ኸርበርት ሲንየር በዚያ ጊዜ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች በጣም ግራ ተጋብተው ነበር፤ የጦር ሠራዊቱን ተቀላቅሎ ውጊያን የማይጨምሩ ሌሎች አገልግሎቶችን ማከናወን ትክክል መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መመሪያ አልነበረም።”

5. በመስከረም 1, 1915 መጠበቂያ ግንብ ላይ ከወጣው ሐሳብ አንስቶ ምን ማስተካከያ ማድረግ ተጀመረ?

5 ይሁን እንጂ በመስከረም 1, 1915 መጠበቂያ ግንብ ላይ ከወጣው ሐሳብ አንስቶ፣ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ተጀመረ። ይህ መጠበቂያ ግንብ፣ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት በተባለው መጽሐፍ ላይ ስለወጣው ሐሳብ ሲናገር “እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ የገለልተኝነት አቋማችንን የሚያስጥስ እንዳይሆን እንሰጋለን” ብሎ ነበር። ይሁንና አንድ ክርስቲያን የደንብ ልብስ ለመልበስና ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆነ እንደሚገደል ቢነገረውስ? መጠበቂያ ግንቡ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ለሰላሙ ልዑል ታማኝ በመሆናችንና የእሱን ትእዛዝ ለመጣስ አሻፈረን በማለታችን የተነሳ መገደል፣ እነዚህን ምድራዊ ነገሥታት ስናገለግል እና እነሱን ስንደግፍ እንዲሁም የሰማዩን ንጉሣችንን ትምህርት እንደካድን የሚያስቆጥር ነገር ስናደርግ ከመገደል የከፋ ነው? መሞታችን ካልቀረ በሰማይ ላለው ንጉሣችን ታማኝ በመሆናችን መሞትን እንመርጣለን።” መጠበቂያ ግንቡ እንዲህ ያለ ጠንከር ያለ መልእክት የያዘ ቢሆንም መደምደሚያው ላይ “የዚህ ዓይነት አካሄድ እንድትከተሉ እየተጫንናችሁ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሐሳብ ማቅረባችን ነው” ብሏል።

6. ከወንድም ኸርበርት ሲንየር ምሳሌ ምን ትምህርት አገኘህ?

6 አንዳንድ ወንድሞች የጦር ሠራዊት አባል መሆን ስህተት እንደሆነ ስለገባቸው ይህን አለማድረጋቸው የሚያስከትለውን መዘዝ ለመጋፈጥ ዝግጁ ሆኑ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ወንድም ኸርበርት ሲንየር እንዲህ ብሏል፦ “ጥይቶችን ከመርከብ ላይ ማውረድም [ውጊያን የማይጨምር አገልግሎት] ሆነ ጥይቶቹን የሚተኩሰውን መሣሪያ ማጉረስ ለእኔ ምንም ልዩነት የላቸውም።” (ሉቃስ 16:10) ወንድም ሲንየር ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት በመግለጽ አልዋጋም በማለቱ ወደ ወህኒ ቤት ወረደ። በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በብሪታንያ በሚገኘው በሪችመንድ ወህኒ ቤት ለተወሰነ ጊዜ ያህል የታሰሩ 16 ሰዎች ነበሩ፤ ከእነዚህ መካከል ወንድም ሲንየርና ሌሎች 4 ወንድሞች እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ሰዎች ይገኙበታል፤ እነዚህ ሰዎች ከጊዜ በኋላ 16ቱ የሪችመንድ እስረኞች በመባል ይጠሩ ነበር። በአንድ ወቅት ወንድም ሲንየርና ሌሎቹ እስረኞች በድብቅ ወደ ፈረንሳይ የጦር ግንባር ተላኩ። በዚያም በጥይት ተመትተው እንዲገደሉ ተፈረደባቸው። ወንድም ሲንየርንና ሌሎቹን እስረኞች አሰልፈው በተኳሾቹ ፊት እንዲቆሙ አደረጓቸው፤ ሆኖም ሳይገደሉ ቀሩ። ቅጣቱ ተለውጦ አሥር ዓመት እንዲታሰሩ ተፈረደባቸው።

“የጦርነት ዳመና በሚያንዣብብበት ወቅት እንኳ የአምላክ ሕዝቦች ከሰው ሁሉ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተምሬያለሁ።”​—ሳይመን ክሬከር (አንቀጽ 7ን ተመልከት)

7. ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት ወቅት የአምላክ ሕዝቦች ምን ነገር ተገንዝበው ነበር?

7 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት ወቅት በአጠቃላይ የይሖዋ ሕዝቦች፣ ገለልተኛ መሆን ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ይበልጥ ግልጽ ሆኖላቸው ነበር። (ማቴ. 26:51-53፤ ዮሐ. 17:14-16፤ 1 ጴጥ. 2:21) ለምሳሌ ያህል፣ የኅዳር 1, 1939 መጠበቂያ ግንብ “ገለልተኝነት” የሚል በጣም አስፈላጊ የሆነ ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር፤ ርዕሱ እንዲህ ይላል፦ “በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝብ ሊከተሉት የሚገባው መመሪያ ይህ ነው፦ በብሔራት መካከል ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ጥብቅ የሆነ የገለልተኝነት አቋም ሊኖራቸው ይገባል።” ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት ከጊዜ በኋላ ያገለገለው ወንድም ሳይመን ክሬከር መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ይህን ርዕስ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “የጦርነት ዳመና በሚያንዣብብበት ወቅት እንኳ የአምላክ ሕዝቦች ከሰው ሁሉ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተምሬያለሁ።” ይህ መንፈሳዊ ምግብ የቀረበው በተገቢው ጊዜ ነበር፤ የይሖዋ ሕዝቦች ለአምላክ መንግሥት ያላቸውን ታማኝነት የሚፈታተን ከባድ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ወቅት ያንን መቋቋም እንዲችሉ አዘጋጅቷቸዋል።

የስደት “ወንዝ” አጋጠማቸው

8, 9. ሐዋርያው ዮሐንስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

8 ሐዋርያው ዮሐንስ፣ የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተወለደ በኋላ ዘንዶው ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስ በምሳሌያዊ መንገድ ከአፉ ወንዝ እንዲወጣ በማድረግ የአምላክን መንግሥት ደጋፊዎች ጠራርጎ ለማጥፋት እንደሚሞክር ትንቢት ተናግሮ ነበር። b (ራእይ 12:9, 15ን አንብብ።) ታዲያ ዮሐንስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ከ1920ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የአምላክ ሕዝቦች ድንገተኛ በሆነ የስደት ማዕበል ሲንገላቱ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሰሜን አሜሪካ እንደነበሩት ብዙ ወንድሞች ሁሉ ወንድም ክሬከርም ለአምላክ መንግሥት ታማኝ በመሆኑ እስር ቤት ተወርውሮ ነበር። እንዲያውም በጦርነቱ ወቅት በሃይማኖታቸው ምክንያት በውጊያ ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከታሰሩት ሰዎች መካከል ከሁለት ሦስተኛ የሚበልጡት የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ።

9 የመንግሥቱ ተገዢዎች የሚኖሩት የትም ይሁን የት፣ ዲያብሎስና ወኪሎቹ እነዚህ ሰዎች ታማኝነታቸውን እንዲያጓድሉ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች በፍርድ ቤቶች እንዲሁም የአመክሮ ጉዳዮችን በሚያዩ ኮሚቴዎች ፊት እንዲቀርቡ ተደርገዋል። የገለልተኝነት አቋማቸውን ለመጠበቅ ባደረጉት ቁርጥ ውሳኔ የተነሳ ታስረዋል፣ ተደብድበዋል እንዲሁም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በጀርመን ያሉ የአምላክ ሕዝቦች “ሃይል ሂትለር” (ሂትለር አዳኝ ነው) ለማለት ወይም በጦርነት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። በናዚ የግዛት ዘመን 6,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የታሰሩ ሲሆን ከ1,600 በላይ የሚሆኑ ጀርመናውያንና ሌላ ዜግነት ያላቸው ክርስቲያኖች በሚያሠቃዩዋቸው ሰዎች ተገድለዋል። ያም ቢሆን ዲያብሎስ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ዘላቂ የሆነ ጉዳት ማድረስ አልቻለም።—ማር. 8:34, 35

‘ምድሪቱ ወንዙን ዋጠችው’

10. “ምድሪቱ” እነማንን ታመለክታለች? የአምላክን ሕዝቦች የረዳቻቸውስ እንዴት ነው?

10 ሐዋርያው ዮሐንስ የጻፈው ትንቢት እንደሚያሳየው “ምድሪቱ” (በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ምክንያታዊ አመለካከት ያላቸው ወገኖች) የስደቱን “ወንዝ” በመዋጥ የአምላክን ሕዝቦች ትረዳቸዋለች። ይህ የትንቢቱ ክፍል ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ባሉት አሥርተ ዓመታት “ምድሪቱ” የመሲሐዊውን መንግሥት ታማኝ ደጋፊዎች ብዙ ጊዜ ረድታቸዋለች። (ራእይ 12:16ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የተለያዩ ፍርድ ቤቶች የይሖዋ ምሥክሮች ወታደራዊ አገልግሎት ያለመስጠት እንዲሁም ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ዝግጅቶች ያለመካፈል መብታቸው እንዲከበርላቸው አድርገዋል። እስቲ በመጀመሪያ ይሖዋ ወታደራዊ አገልግሎት ከመስጠት ጋር በተያያዘ ሕዝቦቹ በፍርድ ቤት ታላቅ ድል እንዲያገኙ ካደረገባቸው አጋጣሚዎች አንዳንዶቹን እንመልከት።—መዝ. 68:20

11, 12. ወንድም ሲኩሬላ እና ወንድም ትሊሚኖስ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ነበር? ውጤቱስ ምን ሆነ?

11 ዩናይትድ ስቴትስ። አንቶኒ ሲኩሬላ እንዲሁም አምስት ወንድሞቹና እህቶቹ ያደጉት በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ነው። አንቶኒ ሲኩሬላ 15 ዓመት ሲሆነው ተጠመቀ። ከዚያም 21 ዓመት ሲሆነው ለወታደራዊ አገልግሎት ወደሚመለምለው ቦርድ በመሄድ ወንጌላዊ መሆኑን አሳወቀ። ከሁለት ዓመት በኋላ ይኸውም በ1950 ደግሞ ‘ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው የማይፈቅድለት’ በሚል እንዲመዘገብ አመለከተ። የፌዴራሉ የምርመራ ቢሮ የወንድም ሲኩሬላን ጥያቄ የሚቃወም ሪፖርት ባያቀርብም የፍትሕ ቢሮው የወንድምን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀረ። ወንድም ሲኩሬላ በተለያዩ ጊዜያት ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተመለከተው፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለወንድም ሲኩሬላ በመፍረድ የታችኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን ሽሮታል። ይህ ውሳኔ፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎችንም የሚጠቅም ነው።

12 ግሪክ። ያኮቮስ ትሊሚኖስ የወታደር የደንብ ልብስ ለመልበስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ባለሥልጣናትን አልታዘዝክም የሚል ክስ ቀርቦበት በ1983 እንዲታሰር ተፈረደበት። ከእስር ከተለቀቀ በኋላ የሒሳብ ሠራተኛ ሆኖ ለመሥራት ፈቃድ እንዲሰጠው ቢያመለክትም የወንጀል ሪከርድ ስላለው አልተፈቀደለትም። በመሆኑም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደው፤ ሆኖም በግሪክ ያሉት ፍርድ ቤቶች በእሱ ላይ ስለፈረዱ ወደ አውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ይግባኝ አለ። አሥራ ሰባት ዳኞችን ያቀፈው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻው ከፍተኛ ችሎት፣ በ2000 ለወንድም ትሊሚኖስ ፈረደለት፤ ይህ ውሳኔ በሌሎች ላይም መድልዎ እንዳይፈጸም የሚከላከል ነው። ይህ ብይን ከመሰጠቱ በፊት በግሪክ የሚኖሩ ከ3,500 የሚበልጡ ወንድሞች በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት በመታሰራቸው የወንጀል ሪከርድ ነበረባቸው። እንዲህ ዓይነት ጥሩ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ግሪክ፣ እነዚህ ወንድሞች ከወንጀል ሪከርድ ነፃ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሕግ አወጣች። በተጨማሪም ሁሉም የግሪክ ዜጎች በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት መብታቸው እንዲከበር የሚያደርገው ከተወሰነ ዓመታት በፊት የወጣ ሕግ፣ የግሪክ ሕገ መንግሥት ሲሻሻል ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን ተደርጓል።

“ወደ ፍርድ ቤቱ ከመግባቴ በፊት ወደ ይሖዋ አጥብቄ ጸለይኩ፤ ከዚያም ይሖዋ ሲያረጋጋኝ ተሰማኝ።”​—ኢቫይሎ ስቴቫኖፍ (አንቀጽ 13ን ተመልከት)

13, 14. ከኢቫይሎ ስቴቫኖፍ እና ከቫሃን ባያትያን ጋር ከተያያዙት የፍርድ ቤት ጉዳዮች ምን ትምህርት የምናገኝ ይመስልሃል?

13 ቡልጋሪያ። ኢቫይሎ ስቴቫኖፍ በ1994 በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እንዲያገለግል ሲመለመል የ19 ዓመት ልጅ ነበር። ኢቫይሎ ሠራዊቱን ለመቀላቀልም ሆነ በጦር ሠራዊቱ ሥር ያለ ውጊያን የማይጨምር አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም የ18 ወራት እስር ተፈረደበት፤ እሱ ግን በሕሊናው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ያለመካፈል መብቱ እንዲከበርለት ይግባኝ አለ። ከጊዜ በኋላ ጉዳዩ ወደ አውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ተላለፈ። ጉዳዩ በዚህ ፍርድ ቤት ከመታየቱ በፊት በ2001 ባለሥልጣናቱ ከወንድም ስቴቫኖፍ ጋር ስምምነት ላይ ደረሱ። የቡልጋሪያ መንግሥት፣ ለወንድም ስቴቫኖፍ ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ለሆኑ የቡልጋሪያ ዜጎች በሙሉ ምሕረት አደረገላቸው። c

14 አርሜንያ። ቫሃን ባያትያን በ2001 ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚገደድበት ዕድሜ ላይ ደረሰ። d በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ለማገልገል ሕሊናው እንደማይፈቅድለት ቢገልጽም በአገሪቱ ያሉት ፍርድ ቤቶች በሙሉ ጥያቄውን ውድቅ አደረጉት። ሁለት ዓመት ተኩል እንዲታሰር ስለተፈረደበት መስከረም 2002 ወህኒ ወረደ፤ ሆኖም ለአሥር ወር ከሁለት ሳምንት ከታሰረ በኋላ ተለቀቀ። በዚህ መሃል ወንድም ባያትያን ጉዳዩን ወደ አውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ነበር፤ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ተመለከተው። ይሁን እንጂ ጥቅምት 27, 2009 ይሄኛውም ፍርድ ቤት በእሱ ላይ ፈረደበት። ይህ ውሳኔ በአርሜንያ ያሉ ተመሳሳይ ችግር የደረሰባቸው ወንድሞችም ትልቅ ሽንፈት ያጋጠማቸው እንዲመስል ያደረገ ነበር። ይሁን እንጂ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻው ከፍተኛ ችሎት ይህን ብይን እንደገና ተመለከተው። ሐምሌ 7, 2011 ይህ ፍርድ ቤት ቫሃን ባያትያንን የሚደግፍ ብይን ሰጠ። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ አንድ ሰው በሃይማኖታዊ እምነቱ ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው የማይፈቅድለት ከሆነ የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት እንዲከበር በሚያዝዘው አንቀጽ መሠረት መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ ሲወስን ይህ የመጀመሪያው ነው። ይህ ውሳኔ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ምክር ቤት አባላት በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች መብትም እንዲከበር አድርጓል። e

በአርሜኒያ ያሉ ወንድሞች፣ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከፈረደላቸው በኋላ ከእስር ተፈትተዋል

ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች

15. የይሖዋ ሕዝቦች ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች ለመካፈል ፈቃደኛ የማይሆኑት ለምንድን ነው?

15 የይሖዋ ሕዝቦች ለመሲሐዊው መንግሥት ታማኝ መሆናቸውን የሚያሳዩት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆን ብቻ አይደለም፤ ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች እንዲካፈሉ ሲጠየቁም ይህን እንደማያደርጉ በአክብሮት ይገልጻሉ። በተለይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳ በኋላ ብሔራዊ ስሜት በመላው ምድር ተስፋፍቷል። የብዙ አገራት ዜጎች ለትውልድ አገራቸው ታማኝ መሆናቸውን የሚገልጸውን ሐረግ እንዲደግሙ፣ ብሔራዊ መዝሙር እንዲዘምሩ ወይም ለአገራቸው ባንዲራ ሰላምታ እንዲሰጡ ይጠበቅባቸዋል። እኛ ግን አምልኮ የምናቀርበው ለይሖዋ ብቻ ነው። (ዘፀ. 20:4, 5) በዚህም ምክንያት እንደ ጎርፍ ያለ ስደት አጋጥሞናል። ይሖዋ በዚህ ጊዜም ቢሆን “ምድሪቱ” ከሚደርስብን ስደት የተወሰነውን እንድትውጠው አድርጓል። ይሖዋ በክርስቶስ በመጠቀም በዚህ ረገድ አስደናቂ ድል እንድንቀዳጅ ያደረገባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት።—መዝ. 3:8

16, 17. ሊሊያን እና ዊልያም ጎባይቲስ ምን አጋጠማቸው? ከእነሱ ጋር ከተያያዘው የፍርድ ሂደት ምን ትምህርት አግኝተሃል?

16 ዩናይትድ ስቴትስ። በ1940 የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በማይነርስቪል ስኩል ዲስትሪክት እና በጎባይቲስ መካከል በተካሄደው ክርክር 8 ለ1 በሆነ ድምፅ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ፈረደ። የ12 ዓመቷ ሊሊያን ጎባይታስ f እና 10 ዓመት የሆነው ወንድሟ ዊልያም፣ ለይሖዋ ታማኝ መሆን ስለፈለጉ ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ወይም ለአገራቸው ታማኝ መሆናቸውን የሚገልጸውን ሐረግ ለመድገም ፈቃደኛ አልሆኑም። በዚህም የተነሳ ከትምህርት ቤት ተባረሩ። ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የታየ ሲሆን ፍርድ ቤቱም፣ ትምህርት ቤቱ የወሰደው እርምጃ “ብሔራዊ አንድነትን” የሚያስጠብቅ በመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚስማማ እንደሆነ ገለጸ። ይህ ውሳኔ መተላለፉ ከፍተኛ የስደት ማዕበል እንዲነሳ አደረገ። ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ልጆችም ከትምህርት ቤት ተባረሩ፤ በሥራ ላይ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከሥራ ገበታቸው ተፈናቀሉ፤ እንዲሁም በብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ሕዝቡ ከባድ ጥቃት አደረሰባቸው። ዘ ለስተር ኦቭ አወር ካንትሪ የተባለው መጽሐፍ “ከ1941 እስከ 1943 ባለው ጊዜ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰው ስደት በሃያኛው መቶ ዘመን በአሜሪካ ውስጥ ከታዩት ሃይማኖታዊ አለመቻቻሎች ሁሉ የከፋው ነው” በማለት ተናግሯል።

17 ይሁንና የአምላክ ጠላቶች ያገኙት ድል ጊዜያዊ ነበር። በ1943 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከጎባይቲስ ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሌላ ክስ ተመለከተ። ይህ ጉዳይ ዌስት ቨርጂኒያ ስቴት ቦርድ ኦቭ ኤጁኬሽን እና ባርኔት በመባል ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደላቸው። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ ራሱ ያሳለፈውን ውሳኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሲለውጥ በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ነው። ከዚህ ውሳኔ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ላይ በግልጽ ሲካሄድ የነበረው ጥቃት በእጅጉ ቀንሷል። ይህ የፍርድ ሂደት የሁሉም የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች መብት ይበልጥ እንዲከበር አድርጓል።

18, 19. ፓብሎ ባሮስ፣ እንደተናገረው እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? ሌሎች የይሖዋ አገልጋዮችስ የእሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

18 አርጀንቲና። የስምንት ዓመቱ ፓብሎ ባሮስ እና የሰባት ዓመቱ ኡጎ ባሮስ ባንዲራ ሲሰቀል በሚደረገው ሥነ ሥርዓት ላይ አንካፈልም በማለታቸው በ1976 ከትምህርት ቤት ተባረሩ። በአንድ ወቅት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ፓብሎን የገፈተረችው ከመሆኑም በላይ ጭንቅላቱ ላይ መትታዋለች። ሁለቱን ልጆች ከትምህርት ሰዓት ውጭ ለአንድ ሰዓት ያህል እንዲቆዩ ያደረገቻቸው ሲሆን ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች ላይ እንዲካፈሉ ለማስገደድ ሞክራ ነበር። ፓብሎ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ምን ያህል ከባድ እንደነበር ሲያስታውስ “ይሖዋ ባይረዳኝ ኖሮ፣ ታማኝነቴን እንዳላላ የደረሰብኝን ጫና መቋቋም አልችልም ነበር” ብሏል።

19 ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቢወሰድም ዳኛው፣ ትምህርት ቤቱ ፓብሎንና ኡጎን ማባረሩ ትክክል እንደሆነ ገለጸ። ይሁንና ጉዳዩ ለአርጀንቲና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተባለ። በ1979 ይህ ፍርድ ቤት የታችኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር እንዲህ ብሏል፦ “የተሰጠው ቅጣት [ከትምህርት ቤት መባረር] ሕገ መንግሥቱ ከሚሰጠው የመማር መብት (አንቀጽ 14) እና አገሪቱ ካለባት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመስጠት ግዴታ (አንቀጽ 5) ጋር የሚጋጭ ነው።” ይህ ድል ወደ 1,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆችን ጠቅሟል። ከትምህርት ቤት ሊባረሩ የነበሩ አንዳንድ ልጆች እንዳይባረሩ የተደረገ ሲሆን እንደ ፓብሎና ኡጎ ያሉት ልጆች ደግሞ ወደ ሕዝብ ትምህርት ቤት ተመለሱ።

በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በፈተና ወቅት ታማኝ ሆነዋል

20, 21. ከሮኤል እና ከኤምሊ ጋር የተያያዘው የፍርድ ጉዳይ እምነትህን ያጠናከረልህ እንዴት ነው?

20 ፊሊፒንስ። በ1990 የ9 ዓመቱ ሮኤል ኤምብራሊናግ g እና 10 ዓመት የሆናት እህቱ ኤምሊ እንዲሁም ከ65 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ለባንዲራ ሰላምታ ባለመስጠታቸው ከትምህርት ቤት ተባረሩ። የሮኤልና የኤምሊ አባት ሌኦናርዶ ስለ ጉዳዩ ከትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ቢሞክርም ጥረቱ አልተሳካም። ሁኔታዎቹ እየተባባሱ ሲሄዱ ሌኦናርዶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ አለ። ሌኦናርዶ ገንዘብም ሆነ እሱን ወክሎ የሚከራከርለት ጠበቃ አልነበረውም። በመሆኑም ቤተሰቡ፣ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጣቸው አጥብቀው ጸለዩ። በዚህ ሁሉ ጊዜ ልጆቹ ይሾፍባቸውና ይሰደቡ ነበር። ሌኦናርዶ ስለ ሕግ ብዙ እውቀት ስላልነበረው በክርክሩ መርታት እንደሚችል አልተሰማውም ነበር።

21 ደስ የሚለው ግን በአገሪቱ ታዋቂ በሆነ የሕግ አማካሪ ድርጅት ውስጥ ይሠራ የነበረ ፌሊኖ ጋናል የተባለ ጠበቃ ቤተሰቡን ወክሎ ፍርድ ቤት ቀረበ። ይህ ጉዳይ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ፌሊኖ ጋናል የይሖዋ ምሥክር ሆኗል፤ ከሚሠራበት ድርጅትም ለቅቆ ነበር። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ በአንድ ድምፅ ለይሖዋ ምሥክሮች የፈረደላቸው ሲሆን ልጆቹ ከትምህርት ቤት እንዲባረሩ የተላለፈው ትእዛዝም እንዲሻር ወስኗል። በዚህ ጊዜም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች አቋማቸውን እንዲያላሉ የተደረገው ጥረት ከሽፏል።

ገለልተኛ መሆናችን አንድነት እንዲኖረን አድርጓል

22, 23. (ሀ) ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው በርካታ ድሎችን በፍርድ ቤት ልንጎናጸፍ የቻልነው ለምንድን ነው? (ለ) በሰላም የሚኖር ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ያለን መሆኑ ምን ያረጋግጣል?

22 የይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው በርካታ ድሎችን በፍርድ ቤት ሊጎናጸፉ የቻሉት ለምንድን ነው? በፖለቲካ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አናደርግም። ያም ቢሆን በተለያዩ አገራትና ፍርድ ቤቶች ያሉ ፍትሐዊ አመለካከት ያላቸው ዳኞች፣ እልኸኛ የሆኑ ተቃዋሚዎቻችን የሚያደርሱብንን ከባድ ስደት አስቁመውልናል፤ ይህንን ሲያደርጉ የየአገሩ ሕገ መንግሥት በሚተረጎምበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ አድርገዋል። ከእነዚህ ድሎች በስተጀርባ ክርስቶስ እንዳለ ምንም ጥርጥር የለውም። (ራእይ 6:2ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ጉዳዮቻችንን ፍርድ ቤት የምናቀርበው ለምንድን ነው? ይህን የምናደርገው የሕግ ሥርዓቱን ለማሻሻል ሳይሆን ንጉሣችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ያለምንም እንቅፋት ማገልገል ስለምንፈልግ ነው።—ሥራ 4:29

23 ዓለም በፖለቲካዊ ግጭቶች እየተከፋፈለ እንዲሁም ሥር በሰደደ ጥላቻ እየታመሰ ባለበት በዚህ ዘመን እየገዛ ያለው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተከታዮቹ የገለልተኝነት አቋማቸውን ጠብቀው ለመመላለስ የሚያደርጉትን ጥረት ባርኮታል። ሰይጣን እኛን በመከፋፈል ድል ለማድረግ ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም። የአምላክ መንግሥት “ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት [ለመማር]” ፈቃደኛ ያልሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሰብስቧል። በእርግጥም በሰላም የሚኖር ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ያለን መሆኑ በራሱ እንደ ተአምር የሚቆጠር ነው፤ ይህም የአምላክ መንግሥት እየገዛ እንደሆነ የሚያሳይ የማያሻማ ማረጋገጫ ነው!​—ኢሳ. 2:4

a ይህ ጥራዝ አዲስ ፍጥረት ተብሎም ይጠራል። ሚሌኒያል ዶውን የሚባሉት ጥራዞች ከጊዜ በኋላ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ተብለዋል።

b ይህን ትንቢት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 27 ከገጽ 184-186 ተመልከት።

c በዚህ ስምምነት መሠረት የቡልጋሪያ መንግሥት፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሰዎች ሁሉ በሲቪል አስተዳደር ሥር ያለ፣ ምትክ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጡ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል።

d ሙሉውን ታሪክ ለማግኘት በኅዳር 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “የአውሮፓ ፍርድ ቤት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ሰዎች መብት አስከበረ“ የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

e የአርሜንያ መንግሥት ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ከ450 በላይ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮችን አስሯል። ኅዳር 2013 ከእነዚህ ወጣቶች የመጨረሻዎቹ ከእስር ተለቅቀዋል።

f የዚህ ቤተሰብ ስም በፍርድ ቤቱ መዝገብ ላይ ሲሰፍር ስህተት ነበረው።

g የዚህ ቤተሰብ ስም በፍርድ ቤቱ መዝገብ ላይ ሲሰፍር በስህተት ኤብራሊናግ ተብሎ ነበር።