በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 18

ለዘላለም የአምላክ ወዳጅ ሁን!

ለዘላለም የአምላክ ወዳጅ ሁን!

ወዳጅ ማፍራት ጥረት ይጠይቃል፤ ወዳጅነቱንም ጠብቆ ማቆየትም ጥረት ይጠይቃል። የአምላክ ወዳጅ ለመሆንና ያንንም ወዳጅነት ጠብቀህ ለማቆየት የምታደርገው ጥረት በእጅጉ ይባረካል። ኢየሱስ ለሚያምኑበት “እውነትም አርነት [“ነፃነት፣” NW] ያወጣችኋል” በማለት ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 8:32) ይህ ምን ማለት ነው?

አሁንም እንኳ ነፃነት ልታገኝ ትችላለህ። ሰይጣን ከሚያስፋፋው የሐሰት ትምህርቶችና ውሸት ነፃ ልትሆን ትችላለህ። ይሖዋን የማያውቁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እያጠቃ ካለው ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ነፃ ልትሆን ትችላለህ። (ሮሜ 8:22) የአምላክ ወዳጆች ‘ከሞት ፍርሃት’ እንኳ ሳይቀር ነፃ ናቸው።—ዕብራውያን 2:14, 15

በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ነፃነት ታገኛለህ። ወደፊት የምታገኘው ነፃነት እንዴት ያለ አስደናቂ ነፃነት ነው! ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ከጦርነት፣ ከህመምና ከወንጀል ነፃ ትሆናለህ። ከድህነትና ከረሃብ ነፃ ትሆናለህ። ከእርጅናና ከሞት ነፃ ትሆናለህ። ከፍርሃት፣ ከጭቆናና ከፍትሕ መጓደል ነፃ ትሆናለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” ይላል።—መዝሙር 145:16

የአምላክ ወዳጆች ለዘላለም ይኖራሉ። የዘላለም ሕይወት አምላክ ወዳጁ ለመሆን ለሚፈልጉ ሁሉ የሚሰጠው ውድ ስጦታ ነው። (ሮሜ 6:23) መጨረሻ የሌለው ሕይወት ለአንተ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ!

ብዙ ነገሮችን ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ይኖርሃል። ምናልባት የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት መማር ትፈልግ ይሆናል። ወይም ሥዕል መሣል ወይም ዓናፂነት መማር ትፈልግ ይሆናል። ምናልባት ስለ እንስሳት ወይም ስለ ዕፅዋት መማር ትፈልግ ይሆናል። ወይም ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝና የተለያዩ ቦታዎችንና ሰዎችን ማየት ትፈልግ ይሆናል። የዘላለም ሕይወት ማግኘት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማድረግ ያስችላል!

ብዙ ወዳጆችን ለማፍራት የሚያስችል ጊዜ ይኖርሃል። ለዘላለም መኖር የአምላክ ወዳጅ ከሆኑ ሌሎች በርካታ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ ያስችላል። ከልዩ ተሰጥዖቻቸውና ከመልካም ባሕርያታቸው ጋር ትተዋወቃለህ። እነርሱም የአንተ ወዳጆች ይሆናሉ። ትወዳቸዋለህ እነርሱም ይወዱሃል። (1 ቆሮንቶስ 13:8) መጨረሻ የሌለው ሕይወት ማግኘት በምድር ላይ ከሚኖር ከእያንዳንዱ ሰው ጋር ወዳጅ ለመሆን የሚያስችል ጊዜ ይሰጥሃል! ከሁሉም የሚበልጠው ደግሞ ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። ለዘላለም የአምላክ ወዳጅ እንድትሆን እንመኝልሃለን!