ትምህርት 3
ስለ አምላክ መማር ይኖርብሃል
የአምላክ ወዳጅ ለመሆን ከፈለግህ ስለ እርሱ መማር ይኖርብሃል። ወዳጆችህ ስምህን ያውቁታል? በስምህስ ይጠሩሃል? አዎን። አምላክም ስሙን እንድታውቅና ስሙን እንድትጠራ ይፈልጋል። የአምላክ ስም ይሖዋ ነው። (መዝሙር 83:18 NW፤ ማቴዎስ 6:9) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ስለሚወድደውና ስለሚጠላው ነገር መማር አለብህ። ወዳጆቹንና ጠላቶቹን ለይተህ ማወቅ ይኖርብሃል። አንድን ሰው በደንብ ለማወቅ ጊዜ ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ለመማር ጊዜ መመደብ ጥበብ እንደሆነ ይናገራል።—ኤፌሶን 5:15, 16
የአምላክ ወዳጆች እርሱን የሚያስደስቱትን ነገሮች ያደርጋሉ። እስቲ ስለ ወዳጆችህ አስብ። መጥፎ ባሕርይ የምታሳያቸውና የማይወዱትን ነገር የምታደርግ ብትሆን ከአንተ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት የሚቀጥሉ ይመስልሃል? በፍጹም! በተመሳሳይም የአምላክ ወዳጅ መሆን ከፈለግህ እርሱን የሚያስደስተውን ነገር ማድረግ ይኖርብሃል።—ዮሐንስ 4:24
ከአምላክ ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርት የሚረዱህ ሁሉም ሃይማኖቶች አይደሉም። የአምላክ የቅርብ ወዳጅ የሆነው ኢየሱስ ስለ ሁለት መንገዶች ተናግሯል። አንደኛው መንገድ ሰፊና በሰዎች የተሞላ ነው። ይህ መንገድ ወደ ጥፋት ይወስዳል። ሌላኛው መንገድ ደግሞ ጠባብ ሲሆን የሚጓዙበትም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። ይህ መንገድ ወደ ዘላለም ሕይወት ይወስዳል። ይህም የአምላክ ወዳጅ ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ እርሱ የሚመለክበትን ትክክለኛ መንገድ መማር አለብህ ማለት ነው።—ማቴዎስ 7:13, 14