ትምህርት 17
ወዳጅነትህን ጠብቀህ ለማቆየት አንተ ራስህ ወዳጅ መሆን አለብህ
ወዳጅነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። ስለ ይሖዋ ይበልጥ እየተማርክ በሄድክ መጠን ለእርሱ የሚኖርህ ፍቅር የዚያኑ ያህል እያደገ ይሄዳል። ለአምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ሲሄድ እርሱን ለማገልገል ያለህ ፍላጎትም እያደገ ይሄዳል። ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንድትሆን ይገፋፋሃል። (ማቴዎስ 28:19) ከይሖዋ ምሥክሮች ደስተኛ ቤተሰብ ጋር በመቀላቀል ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ለዘላለም ጠብቀህ ማቆየት ትችላለህ። ታዲያ ምን ማድረግ አለብህ?
የአምላክን ሕግጋት በመጠበቅ ለአምላክ ፍቅር እንዳለህ ማሳየት ይገባሃል። “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።”—1 ዮሐንስ 5:3
የተማርካቸውን ነገሮች በሥራ ላይ አውል። ኢየሱስ ይህንን ጉዳይ በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ታሪክ ተናግሯል። አንድ ጠቢብ ሰው ቤቱን በዓለት ላይ ሠራ። አንድ ሰነፍ ሰው ደግሞ ቤቱን በአሸዋ ላይ ሠራ። ከባድ ዝናብ በዘነበ ጊዜ በዓለት ላይ የተሠራው ቤት ከመፍረስ ተረፈ። በአሸዋ ላይ የተሠራው ግን ሙሉ በሙሉ ፈረሰ። ኢየሱስ ትምህርቱን ሰምተው የሚያደርጉት ቤቱን በዓለት ላይ የሠራውን ሰው ይመስላሉ በማለት ተናገረ። ይሁን እንጂ ትምህርቱን ሰምተው የማያደርጉት ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራውን ሰነፍ ሰው ይመስላሉ። የትኛውን ሰው መምሰል ትፈልጋለህ?—ማቴዎስ 7:24-27
መጠመቅ። “ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ።”—ሥራ 22:16
በአምላክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መካፈል። “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት [“በሙሉ ነፍስ፣” NW] አድርጉት።”—ቆላስይስ 3:23