በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 5

ከዓለም የተለየን ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

ከዓለም የተለየን ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

‘የዓለም ክፍል አይደላችሁም።’ዮሐንስ 15:19

1. ኢየሱስ ሰው ሆኖ ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት አበክሮ የተናገረው ነገር ምንድን ነው?

ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት የተከታዮቹ የወደፊት ደህንነት በእጅጉ አሳስቦት እንደነበረ ገልጿል። እንዲያውም ይህን በተመለከተ ወደ አባቱ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው የተነሳ እንድትጠብቃቸው ነው። እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።” (ዮሐንስ 17:15, 16) ኢየሱስ በዚህ ከልብ የመነጨ ጸሎት ላይ፣ ተከታዮቹን በጣም እንደሚወዳቸውና በዚያው ምሽት ቀደም ሲል ለአንዳንዶቹ ‘የዓለም ክፍል አይደላችሁም’ ሲል የተናገረው ቃል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክቷል። (ዮሐንስ 15:19) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከዓለም የተለዩ ሆነው መኖራቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶት እንደነበር ግልጽ ነው።

2. ኢየሱስ የጠቀሰው “ዓለም” ምንን ያመለክታል?

2 ኢየሱስ የጠቀሰው “ዓለም” ከአምላክ የራቁትን፣ በሰይጣን የሚገዙትንና ከእሱ ለሚመነጨው የራስ ወዳድነትና የኩራት መንፈስ ባሮች የሆኑትን የሰው ልጆች በአጠቃላይ ያመለክታል። (ዮሐንስ 14:30፤ ኤፌሶን 2:2፤ 1 ዮሐንስ 5:19) በእርግጥም “[ከዚህ] ዓለም ጋር መወዳጀት ከአምላክ ጋር ጠላትነት መፍጠር” ነው። (ያዕቆብ 4:4) ታዲያ ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ በዓለም ውስጥ እየኖሩም እንኳ ከዓለም የተለዩ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? አምስት መንገዶችን እንመልከት:- በክርስቶስ ለሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ታማኝ በመሆንና ከዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ገለልተኛ በመሆን፣ የዓለምን መንፈስ በመቋቋም፣ በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ልከኛ በመሆን፣ አጥርቶ የሚያይ ዓይን ይዘን በመኖርና መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችንን በማንሳት።

ታማኝና ገለልተኛ ሆኖ መኖር

3. (ሀ) ኢየሱስ በዘመኑ ለነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ምን አመለካከት ነበረው? (ለ) የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች አምባሳደሮች ሆነው ያገለግላሉ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ጨምረህ መልስ።)

3 ኢየሱስ በዘመኑ በነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ከመካፈል ይልቅ ሙሉ በሙሉ ያተኮረው ስለ አምላክ መንግሥት፣ ማለትም ወደፊት ንጉሥ ሆኖ ስለሚያስተዳድረው መንግሥት በመስበክ ላይ ነበር። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ሉቃስ 4:43፤ 17:20, 21) ጳንጥዮስ ጲላጦስ በተባለው ሮማዊ አገረ ገዥ ፊት በቀረበ ጊዜ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ያለው በዚህ ምክንያት ነው። (ዮሐንስ 18:36) ተከታዮቹ ለክርስቶስና ለመንግሥቱ ታማኝ በመሆን እንዲሁም ይህን መንግሥት ለዓለም በማሳወቅ የእሱን አርዓያ ይከተላሉ። (ማቴዎስ 24:14) ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ አምባሳደሮች ነን፤ . . . ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን ‘ከአምላክ ጋር ታረቁ’ ብለን እንለምናለን” ሲል ጽፏል። *2 ቆሮንቶስ 5:20

4. እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ለአምላክ መንግሥት ታማኝ መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው? (“ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ገለልተኛ ነበሩ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

4 አምባሳደሮች አንድን የውጭ አገር መንግሥት የሚወክሉ በመሆናቸው በሚሠሩባቸው አገሮች የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን ጣልቃ አያስገቡም፤ ገለልተኛ ሆነው ይኖራሉ። ይሁን እንጂ አምባሳደሮች የሚወክሉትን አገር ጥቅምና ፍላጎት ያራምዳሉ። “የሰማይ ዜጎች” የሆኑት የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። (ፊልጵስዩስ 3:20) እንዲያውም መንግሥቱን በቅንዓት በመስበካቸው ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ‘ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ’ ረድተዋል። (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:31-40) እነዚህ ሌሎች በጎች ለኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ድጋፍ በመስጠት የክርስቶስ ልዑካን ሆነው ያገለግላሉ። ሁለቱም ቡድኖች አንድ መንጋ በመሆን የመሲሐዊውን መንግሥት ጉዳዮች ስለሚያራምዱ ከዚህ ዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ፍጹም ገለልተኞች ናቸውኢሳይያስ 2:2-4

5. የክርስቲያን ጉባኤ ከጥንቱ እስራኤል የሚለየው በምንድን ነው? ይህን ልዩነት በግልጽ የሚያሳየው ክርስቲያኖች ያላቸው የትኛው አቋም ነው?

5 እውነተኛ ክርስቲያኖች የገለልተኝነት አቋም የሚይዙት ለክርስቶስ ታማኝ ስለሆኑ ብቻ አይደለም። አምላክ ድንበር ከልሎ ከሰጠው የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ በተለየ እኛ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጣ የወንድማማች ማኅበር አባላት ነን። (ማቴዎስ 28:19፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ስለዚህ የየአካባቢያችንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ብንደግፍ፣ የመናገር ነፃነት ተሰምቶን የመንግሥቱን መልእክት በድፍረት መስበክ የማንችል ከመሆኑም በላይ ክርስቲያናዊ አንድነታችን አደጋ ላይ ይወድቃል። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ከዚህም በተጨማሪ ጦርነት በሚነሳበት ጊዜ እንድንወዳቸው የታዘዝነውን የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመውጋት እንነሳለን። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12) በመሆኑም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሰይፍ እንዳያነሱ ለመናገር የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበረው። ኢየሱስ ሌላው ቀርቶ ጠላቶቻቸውን እንኳ እንዲወዱ አዟቸዋል።ማቴዎስ 5:44፤ 26:52፤ “ ገለልተኛ ነኝ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

6. ራስህን ለአምላክ የወሰንክ መሆንህ ከቄሳር ጋር ያለህን ግንኙነት የሚነካው እንዴት ነው?

6 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሕይወታችንን የወሰንነው ለአምላክ እንጂ ለሰው፣ ለሰብዓዊ ተቋም ወይም ለአንድ አገር አይደለም። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:19, 20 “እናንተ የራሳችሁ አይደላችሁም፤ ምክንያቱም በዋጋ ተገዝታችኋል” ይላል። ስለሆነም የክርስቶስ አገልጋዮች ክብር በመስጠት፣ ግብር በመክፈልና በአንጻራዊ ሁኔታ በመገዛት “ለቄሳር” የሚገባውን ቢሰጡም “የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ” ይሰጣሉ። (ማርቆስ 12:17፤ ሮም 13:1-7) ይህም ይሖዋን በሙሉ ነፍስ መውደድን፣ ማምለክንና በታማኝነት መታዘዝን ይጨምራል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለአምላክ ሲሉ ለመሞት እንኳ ዝግጁ ናቸው።ሉቃስ 4:8፤ 10:27፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ ሮም 14:8

“የዓለምን መንፈስ” መቋቋም

7, 8. ‘የዓለም መንፈስ’ ምንድን ነው? ይህ መንፈስ በአንድ ሰው ላይ ‘የሚሠራው’ እንዴት ነው?

7 ክርስቲያኖች ከዓለም የተለዩ መሆናቸውን የሚያሳዩበት ሌላው መንገድ የዓለምን ክፉ መንፈስ በመቋቋም ነው። ጳውሎስ “ከአምላክ የሆነውን መንፈስ ተቀበልን እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 2:12) ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ደግሞ እንዲህ ብሏቸዋል:- “የዚህን ዓለም ሥርዓት ተከትላችሁ የአየሩ ሥልጣን ገዥ በሚፈልገው መንገድ ትመላለሱ ነበር፤ ይህም አየር በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ ያለ መንፈስ ነው።”ኤፌሶን 2:2, 3

8 የዚህ ዓለም “አየር” ወይም መንፈስ ሰዎች ለአምላክ እንዳይታዘዙ የሚገፋፋ እንዲሁም ‘የሥጋ ምኞትንና የዓይን አምሮትን’ የሚቀሰቅስ የማይታይ ኃይል ነው። (1 ዮሐንስ 2:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ይህ መንፈስ “ሥልጣን” እንዲኖረው ያደረገው፣ ኃጢአተኛ ሥጋችንን የሚማርክና መሠሪ መሆኑ እንዲሁም የሚያሳድረው ተጽዕኖ የማያባራና ልክ እንደ አየር በማንኛውም ቦታ የሚገኝ መሆኑ ነው። ከዚህም በላይ ይህ መንፈስ ‘የሚሠራው’ ራስ ወዳድነት፣ ትዕቢት፣ ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት እንዲሁም በራስ ሐሳብ የመመራትና የዓመጽ መንፈስ የመሳሰሉት አምላካዊ ያልሆኑ ባሕርያት በጊዜ ሂደት በአንድ ሰው ልብ ውስጥ እንዲያድጉ በማድረግ ነው። * በቀላል አነጋገር የዓለም መንፈስ፣ የዲያብሎስ ባሕርያት በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ቀስ በቀስ እንዲያድጉ ያደርጋል።ዮሐንስ 8:44፤ የሐዋርያት ሥራ 13:10፤ 1 ዮሐንስ 3:8, 10

9. የዓለም መንፈስ ወደ አእምሯችንና ወደ ልባችን ሊገባ የሚችለው በምን መንገዶች ነው?

9 የዓለም መንፈስ በአንተ አእምሮና ልብ ውስጥ ሥር ሊሰድ ይችላል? አዎ ይችላል፤ ይህ የሚሆነው ግን ተዘናግተህ መንፈሱ በውስጥህ እንዲሠራ ከፈቀድክለት ብቻ ነው። (ምሳሌ 4:23) አብዛኛውን ጊዜ ተጽዕኖው የሚጀምረው ስውር በሆነ መንገድ፣ ምናልባትም ጥሩ ሰዎች በሚመስሉ ሆኖም ለይሖዋ ምንም ፍቅር በሌላቸው ጓደኞች አማካኝነት ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) በተጨማሪም የዓለም መንፈስ ጥሩ ባልሆኑ ጽሑፎች፣ ወሲባዊ ሥዕሎች በሚታዩባቸው ወይም ከሃዲዎች በሚያዘጋጇቸው የኢንተርኔት ድረ ገጾች፣ በመጥፎ መዝናኛዎችና ከፍተኛ ፉክክር በሚታይባቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሊመጣ ይችላል። በአጠቃላይ ሲታይ የሰይጣንን ወይም የእሱን ዓለም አስተሳሰብ በሚያስተላልፍ በማንኛውም ሰው ወይም ነገር አማካኝነት የዚህን ክፉ መንፈስ ተጽዕኖ ልትጋብዝ ትችላለህ።

10. የዓለምን መንፈስ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

10 የዓለምን መሠሪ መንፈስ መቋቋምና ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመርዳት ባደረጋቸው ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀምና መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን አዘውትረን በመጸለይ ብቻ ነው። ይሖዋ ከዲያብሎስም ሆነ በእሱ ቁጥጥር ሥር ካለው ክፉ ዓለም በእጅጉ ይበልጣል። (1 ዮሐንስ 4:4) እንግዲያው በጸሎት አማካኝነት ከይሖዋ ጋር መቀራረባችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ልከኞች በመሆን

11. የዓለም መንፈስ በአለባበስ ረገድ እንዴት ያለ ተጽዕኖ አሳድሯል?

11 አለባበስ፣ አጋጌጥና አካላዊ ንጽሕና አንድ ሰው የሚመራበት መንፈስ ውጫዊ መገለጫዎች ናቸው። በበርካታ አገሮች የሰዎች አለባበስ ቅጥ ያጣ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ አንድ የቴሌቪዥን ተንታኝ በቅርቡ ዝሙት አዳሪዎች የሚለብሱት ልብስ ማጣታቸው እንደማይቀር ተናግሯል። አሥራ ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ልጃገረዶች እንኳ በአለባበስ ረገድ ተመሳሳይ ችግር ይታይባቸዋል። አንድ ጋዜጣ የዘመኑ አለባበስ “አብዛኛውን የሰውነት ክፍል የሚያሳይ፣ ልከኝነት ጨርሶ የማይታይበት” እንደሆነ ዘግቧል። እየተለመደ የመጣው ሌላው የአለባበስ ዓይነት ደግሞ የዓመጸኝነት መንፈስን እንዲሁም ለራስ አክብሮት ማጣትን የሚያሳይ የተዝረከረከ አለባበስ ነው።

12, 13. አለባበሳችንና አጋጌጣችን ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት የሚወስኑት የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

12 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን ጥሩ ለብሰን ማለትም ሥርዓታማ፣ ንጹሕ፣ ጨዋነት የሚንጸባረቅበትና ለሁኔታው ተስማሚ የሆነ ልብስ ለብሰን ለመታየት መፈለጋችን ተገቢ ነው። “አምላክን እናመልካለን” የሚሉ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ሊያደርጉት እንደሚገባ አለባበሳችን በማንኛውም ጊዜ ‘ልከኝነትና ማስተዋል’ የሚታይበት መሆን አለበት፤ እንዲሁም “በመልካም ሥራ” ልንዋብ ይገባል። እርግጥ ነው፣ ዋናው ግባችን ‘ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር’ እንጂ የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሳችን መሳብ አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10፤ ይሁዳ 21) አዎ፣ ከሁሉ የበለጠው ጌጣችን ‘በአምላክ ዓይን ከፍተኛ ዋጋ ያለው የተሰወረው የልብ ሰው’ እንዲሆን እንፈልጋለን።1 ጴጥሮስ 3:3, 4

13 በተጨማሪም፣ አለባበሳችንና አጋጌጣችን ሌሎች ሰዎች ለእውነተኛው አምልኮ በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል መዘንጋት የለብህም። “ልከኝነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ከሥነ ምግባር አኳያ ሲታይ ለሌሎች ስሜትም ሆነ አስተያየት አክብሮትና ግምት የመስጠትን ሐሳብ ያስተላልፋል። ስለዚህ ግባችን፣ መብታችን ነው የምንለውን ነገር ለሌሎች ሕሊና ስንል መተው ሊሆን ይገባዋል። ከምንም በላይ “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር” በማድረግ ይሖዋንና ሕዝቦቹን ለማስከበር እንዲሁም ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን ለማቅረብ እንፈልጋለን።1 ቆሮንቶስ 4:9፤ 10:31፤ 2 ቆሮንቶስ 6:3, 4፤ 7:1

አለባበሴ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ነው?

14. አለባበሳችንንና የግል ንጽሕናችንን በተመለከተ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይገባናል?

14 በተለይ በአገልግሎት በምንካፈልበት ወይም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በምንገኝበት ጊዜ ለአለባበሳችን፣ ለአጋጌጣችንና ለግል ንጽሕናችን የበለጠ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ነው። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘አለባበሴና የግል ንጽሕናዬ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት የሚስብ ነው? ሌሎችን ያሳፍራል? በዚህ ረገድ መብቴ ነው የምለው ነገር በጉባኤ ውስጥ ላገኛቸው ከምችላቸው የአገልግሎት መብቶች ይበልጥብኛል?’መዝሙር 68:6 NW፤ ፊልጵስዩስ 4:5፤ 1 ጴጥሮስ 5:6

15. የአምላክ ቃል ስለ አለባበስ፣ አጋጌጥና አካላዊ ንጽሕና ዝርዝር መመሪያዎች የማይሰጠው ለምንድን ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስ በአለባበስ፣ በአጋጌጥና በአካላዊ ንጽሕና ረገድ ክርስቲያኖች ሊከተሏቸው የሚገቡ ዝርዝር መመሪያዎችን አልያዘም። ይሖዋ የመምረጥ ነፃነታችንን ሊነፍገን ወይም የማሰብ ችሎታችንን እንዳንጠቀም ሊያደርገን አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የምናመዛዝንና ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንድንችል የማስተዋል ችሎታችንን በማሠራት ያሠለጠንን’ ጎልማሳ ሰዎች እንድንሆን ይፈልጋል። (ዕብራውያን 5:14) ከሁሉ በላይ በፍቅር፣ ማለትም ለአምላክና ለጎረቤቶቻችን ባለን ፍቅር የምንመራ ሰዎች እንድንሆን ይፈልጋል። (ማርቆስ 12:30, 31) ከዚህ ገደብ ሳናልፍ በአለባበስም ሆነ በአጋጌጥ ረገድ ሰፊ ምርጫ አለን። በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩት ደስተኛ የሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች በስብሰባዎቻቸው ላይ የሚያማምሩ ልብሶች ለብሰው መታየታቸው ለዚህ ማስረጃ ይሆናል።

ዓይናችን ‘አጥርቶ እንዲያይ’ ማድረግ

16. የዓለም መንፈስ የኢየሱስን ትምህርት የሚቃረነው እንዴት ነው? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን?

16 የዓለም መንፈስ አታላይ በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደስታን ለማግኘት ሲሉ ገንዘብንና ቁሳዊ ነገሮችን እንዲያሳድዱ ይገፋፋቸዋል። ይሁንና ኢየሱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ [አይደለም]” ብሏል። (ሉቃስ 12:15) ኢየሱስ የመናኝ ኑሮ እንድንኖር ባያበረታታም እውነተኛ ደስታና ሕይወት የሚያገኙት “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ” እንዲሁም ‘አጥርቶ የሚያይ’ ዓይን ማለትም ቀና የሆነና በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያነጣጠረ ዓይን ያላቸው እንደሆኑ አስተምሯል። (ማቴዎስ 5:3፤ 6:22, 23) ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ኢየሱስ ያስተማረውን ከልቤ አምንበታለሁ ወይስ “የውሸት አባት” የሆነው ዲያብሎስ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል? (ዮሐንስ 8:44) የምናገራቸው ነገሮች፣ ግቦቼ፣ ቅድሚያ የምሰጣቸው ነገሮችና አኗኗሬ ምን ያሳያሉ?’ሉቃስ 6:45፤ 21:34-36፤ 2 ዮሐንስ 6

17. አጥርቶ የሚያይ ዓይን ያላቸው ሰዎች ከሚያገኟቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹን ጥቀስ።

17 ኢየሱስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” ብሏል። (ማቴዎስ 11:19) አጥርቶ የሚያይ ዓይን ያላቸው ሰዎች ከሚያገኟቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹን ብቻ እንመልከት። በመንግሥቱ አገልግሎት መካፈላቸው እውነተኛ እረፍት ያስገኝላቸዋል። (ማቴዎስ 11:29, 30) ካላስፈላጊ ጭንቀቶች ነፃ ስለሚሆኑ ከአእምሮና ከስሜት ሥቃይ ይድናሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ለኑሮ የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች በማግኘታቸው ብቻ ረክተው ስለሚኖሩ ከቤተሰባቸውና ከክርስቲያን ወዳጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት የበለጠ ጊዜ ያገኛሉ። በዚህም ምክንያት ጣፋጭ እንቅልፍ ይተኛሉ። (መክብብ 5:12) በሚችሉት መንገድ ሁሉ ስለሚሰጡ፣ መስጠት የሚያስገኘውን ታላቅ ደስታም ያጣጥማሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ‘የተትረፈረፈ ተስፋ’ ያላቸው ከመሆኑም በላይ ውስጣዊ ሰላምና እርካታ ያገኛሉ። (ሮም 15:13፤ ማቴዎስ 6:31, 32) በእርግጥም እነዚህ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ በረከቶች ናቸው!

‘ሙሉውን የጦር ትጥቅ’ ማንሳት

18. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጠላታችን፣ ስለ ዘዴዎቹና ስለ ትግላችን ምን ይላል?

18 ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ የሚኖሩ ክርስቲያኖች፣ ደስታ ብቻ ሳይሆን የዘላለም ሕይወት ጭምር ሊያሳጣቸው የሚፈልገው ሰይጣን ከሚሰነዝርባቸው ጥቃት መንፈሳዊ ጥበቃ ያገኛሉ። (1 ጴጥሮስ 5:8) ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ትግል የምንገጥመው ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንግሥታት፣ ከሥልጣናት፣ ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዥዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራዎች ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።” (ኤፌሶን 6:12) “ትግል” የሚለው ቃል ውጊያችን ምሽግ ውስጥ ሆነን ከሩቅ የምናደርገው ሳይሆን ፊት ለፊት የምንገጥመው ግብግብ እንደሆነ ያመለክታል። ከዚህም በላይ “መንግሥታት፣” “ሥልጣናት” እና “የዓለም ገዥዎች” የሚሉት ቃላት ከመንፈሳዊው ዓለም የሚሰነዘረው ጥቃት በጣም የተደራጀና የታሰበበት እንደሆነ ያመለክታሉ።

19. የክርስቲያኖችን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ግለጽ።

19 ሰብዓዊ ድክመትና የአቅም ገደብ ቢኖርብንም ድል መንሳት እንችላለን። እንዴት? “ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ” በማንሳት ነው። (ኤፌሶን 6:13) ኤፌሶን 6:14-18 ይህን የጦር ትጥቅ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል:- “ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁና የጽድቅን ጥሩር ለብሳችሁ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንዲሁም የሰላምን ምሥራች እንደ ጫማ በእግሮቻችሁ በመጫማት ዝግጁ ሆናችሁ ቁሙ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን የምትችሉበትን ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ። በተጨማሪም የመዳንን ራስ ቁር እንዲሁም የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል ተቀበሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ በሁሉም ዓይነት ጸሎትና ምልጃ በማንኛውም ጊዜ በመንፈስ መጸለያችሁን ቀጥሉ።”

20. የእኛ ሁኔታ ቃል በቃል ወታደር ከሆኑት የሚለየው እንዴት ነው?

20 ይህ መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ የአምላክ ዝግጅት በመሆኑ ሁልጊዜ እስከለበስነው ድረስ ከአደጋ እንደሚጠብቀን የተረጋገጠ ነው። ረዘም ላለ ጊዜ ከውጊያ እረፍት ከሚያገኙት ወታደሮች በተለየ ክርስቲያኖች ለአፍታ እንኳን በማያባራ የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ናቸው። ትግሉ የሚያቆመው አምላክ የሰይጣንን ዓለም አጥፍቶ ክፉ መናፍስትን በሙሉ ጥልቁ ውስጥ ሲዘጋባቸው ብቻ ነው። (ራእይ 12:17፤ 20:1-3) ስለዚህ ከድክመቶችህም ሆነ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር የምትታገል ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ፤ ምክንያቱም ሁላችንም ብንሆን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ለመኖር ራሳችንን ‘መጎሰም’ ያስፈልገናል። (1 ቆሮንቶስ 9:27) እንዲያውም መጨነቅ የሚኖርብን ትግል ላይ በማንሆንበት ጊዜ ነው!

21. በመንፈሳዊው ውጊያ ድል አድራጊ መሆን የምንችለው ምን ካደረግን ብቻ ነው?

21 ከዚህም በላይ ይህን ውጊያ በራሳችን አቅም ብቻ ልናሸንፍ አንችልም። በመሆኑም ጳውሎስ “በማንኛውም ጊዜ በመንፈስ” ወደ ይሖዋ መጸለይ እንደሚያስፈልገን አሳስቦናል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋን ቃል በማጥናትና ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ አብረውን በውጊያው ከተሰለፉት “ወታደሮች” ጋር በመሰብሰብ ይሖዋን ማዳመጥ ይኖርብናል። (ፊልሞና 2፤ ዕብራውያን 10:24, 25) እነዚህን ነገሮች ሁሉ በታማኝነት የሚፈጽሙ ክርስቲያኖች ትግሉን በድል አድራጊነት መወጣት ብቻ ሳይሆን ስለ እምነታቸው ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ ጥብቅና መቆምም ይችላሉ።

ለእምነትህ ጥብቅና ለመቆም ዝግጁ ሁን

22, 23. (ሀ) ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም ምንጊዜም ዝግጁ መሆን የሚገባን ለምንድን ነው? ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ የትኛው ርዕሰ ጉዳይ ይብራራል?

22 ኢየሱስ “የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ . . . ዓለም ይጠላችኋል” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:19) ስለሆነም ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ጥብቅና ለመቆም ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል፤ ይህንንም በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ሊያደርጉ ይገባል። (1 ጴጥሮስ 3:15) ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ ጊዜ ብዙኃኑ ከሚቀበለው የተለየ አቋም የሚይዙት ለምን እንደሆነ ገብቶኛል? ከብዙዎች የተለየ አቋም እንድይዝ የሚያስገድድ ሁኔታ በሚያጋጥመኝ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስና ታማኝና ልባም ባሪያ የሚያስተምሩት ትክክል መሆኑን በሚገባ አምንበታለሁ? (ማቴዎስ 24:45፤ ዮሐንስ 17:17) በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን እንዳደርግ የሚጠይቅ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ የተለየ አቋም ለመያዝ ዝግጁ መሆን ብቻ ሳይሆን የተለየሁ በመሆኔ እኮራለሁ?’መዝሙር 34:2 NW፤ ማቴዎስ 10:32, 33

23 ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ከዓለም የተለየን ለመሆን ያደረግነው ውሳኔ ይበልጥ ስውር በሆኑ መንገዶች ፈተና ላይ ይወድቃል። ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሰይጣን የይሖዋን አገልጋዮች በዓለማዊ መዝናኛዎች አታልሎ ወደ ዓለም ለማስገባት ይሞክራል። ታዲያ ሰውነታችንን ዘና የሚያደርግና ንጹሕ ሕሊናችንን የማያቆሽሽ መዝናኛ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ምዕራፍ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ እንመረምራለን።

^ አን.3 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ጀምሮ ክርስቶስ በምድር ባለው የቅቡዓን ተከታዮቹ ጉባኤ ላይ ንጉሥ ሆኗል። (ቆላስይስ 1:13) በ1914 ደግሞ ‘በዓለም መንግሥት’ ላይ ንጉሥ ሆኖ ተሹሟል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የመሲሐዊው መንግሥት አምባሳደሮች ሆነው ያገለግላሉ።ራእይ 11:15