የበላይ አካሉ መልእክት
ይሖዋን የምትወድ ውድ አንባቢ፦
ኢየሱስ ‘እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:32) እነዚህ ቃላት ምንኛ የሚያጽናኑ ናቸው! አዎ፣ ውሸት በነገሠባቸው በእነዚህ አስቸጋሪ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ እንኳ እውነትን ማወቅ ይቻላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ ስታውቅ ምን እንደተሰማህ ታስታውሳለህ? በደስታ ፈንድቀህ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!
ይሁን እንጂ፣ ትክክለኛውን የእውነት እውቀት ማግኘትና ይህን እውነት ለሌሎች ማካፈል አስፈላጊ የሆነውን ያህል ምግባራችን ከእውነት ጋር የሚስማማ መሆኑም በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ለማድረግ ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር ይገባናል። ታዲያ ይህ ምን ይጠይቅብናል? ኢየሱስ በሞቱ ዋዜማ ምሽት ላይ የተናገራቸው ቃላት መልሱን ይሰጡናል። ለታማኝ ሐዋርያቱ “እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር እናንተም ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 15:10
ኢየሱስ ከአምላክ ፍቅር ሳይወጣ ለመኖር የቻለው የአባቱን ትእዛዛት በመጠበቁ እንደሆነ ልብ በል። እኛም ብንሆን እንዲሁ ማድረግ ይኖርብናል። ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን እውነትን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በሥራ ላይ ማዋል ያስፈልገናል። ኢየሱስ በዚያው ምሽት ላይ “እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 13:17
ይህ መጽሐፍ እውነትን በዕለት ተዕለት ሕይወትህ በሥራ ላይ እንድታውል እንዲሁም ‘የዘላለምን ሕይወት እየተጠባበቅክ ከአምላክ ፍቅር’ ሳትወጣ እንድትኖር የሚረዳህ እንዲሆን ምኞታችን ነው።—ይሁዳ 21
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል