በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 6

ጤናማ መዝናኛ መምረጥ የሚቻለው እንዴት ነው?

ጤናማ መዝናኛ መምረጥ የሚቻለው እንዴት ነው?

“ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።”1 ቆሮንቶስ 10:31

1, 2. በመዝናኛ ረገድ ምን ዓይነት ምርጫ ማድረግ ያስፈልገናል?

አንድ የሚጣፍጥ ፍሬ ልትበላ ስትዘጋጅ በአንድ በኩል እንደተበላሸ ትመለከታለህ። ምን ታደርጋለህ? ፍሬውን እንዳለ፣ የተበላሸውንም ጭምር ልትበላ ትችላለህ፤ ወይም ሙሉውን ፍሬ ልትጥለው ትችላለህ፤ አሊያም ደግሞ የተበላሸውን ክፍል ብቻ ቆርጠህ የቀረውን መብላት ትችላለህ። ታዲያ አንተ የትኛውን ትመርጣለህ?

2 በተወሰኑ መንገዶች መዝናኛም ከዚህ ፍሬ ጋር ይመሳሰላል። አንዳንድ ጊዜ ዘና የሚያደርግህ ነገር ትፈልጋለህ፤ ሆኖም የምታገኘው አብዛኛው መዝናኛ ከሥነ ምግባር አኳያ ሲታይ መጥፎ፣ አልፎ ተርፎም የተበላሸ ይሆንብሃል። ታዲያ ምን ታደርጋለህ? አንዳንዶች መጥፎ የሆኑትን ጨምሮ ይህ ዓለም በሚያቀርበው በማንኛውም ዓይነት መዝናኛ ለመዝናናት ፈቃደኛ ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ ጎጂ ከሆነ ነገር ሁሉ ለመራቅ ሲሉ በማንኛውም ዓይነት መዝናኛ ከመካፈል ይቆጠባሉ። አንዳንዶች ደግሞ ጎጂ ከሆኑ መዝናኛዎች በመራቅ በአንጻራዊ ሁኔታ ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች አልፎ አልፎ ይዝናናሉ። አንተስ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ ለመኖር የትኛውን መምረጥ ይኖርብሃል?

3. አሁን የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

3 አብዛኞቻችን ሦስተኛውን እንመርጣለን። መዝናኛ አስፈላጊ እንደሆነ ብንገነዘብም የምንመርጣቸው መዝናኛዎች ከሥነ ምግባር አንጻር ጤናማ መሆን እንዳለባቸው ይሰማናል። ስለሆነም ጤናማ የሆነውንና ያልሆነውን መዝናኛ እንዴት መለየት እንደምንችል መመርመር ያስፈልገናል። በመጀመሪያ ግን የመዝናኛ ምርጫችን ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ እንዴት እንደሚነካ እንመልከት።

“ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ”

4. ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን መሆናችን በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

4 በ1946 የተጠመቁ አንድ አረጋዊ የይሖዋ ምሥክር “ሁልጊዜ በጥምቀት ንግግር ላይ የምገኝ ከመሆኑም በላይ እኔ ራሴ የምጠመቅ ያህል ንግግሩን በጥሞና አዳምጣለሁ” ብለው ተናግረው ነበር። እንደዚህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? “ታማኝነቴን ጠብቄ እንድኖር በጣም የረዳኝ ራሴን ስወስን የገባሁትን ቃል ሁልጊዜ ማስታወሴ ነው” በማለት ተናግረዋል። አንተም እኚህ ወንድም በተናገሩት ሐሳብ እንደምትስማማ ጥርጥር የለውም። መላ ሕይወትህን እሱን ለማገልገል እንደምታውል ለይሖዋ ቃል የገባህ መሆኑን ሁልጊዜ ማስታወስህ እንድትጸና ይረዳሃል። (መክብብ 5:4፤ ዕብራውያን 10:7) እንዲያውም ራስህን ለይሖዋ ስትወስን በገባኸው ቃልላይ ማሰላሰልህ፣ ለአገልግሎት ባለህ አመለካከት ላይ ብቻ ሳይሆን የመዝናኛ ምርጫህን ጨምሮ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” ብሎ በጻፈ ጊዜ አበክሮ ያሳሰበው ይህን ሐቅ ነበር።1 ቆሮንቶስ 10:31

5. ዘሌዋውያን 22:18-20፣ በሮም 12:1 ላይ ያለው ሐሳብ ያዘለውን ማስጠንቀቂያ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?

5 በሕይወትህ የምታደርገው ነገር ሁሉ ለይሖዋ ከምታቀርበው አምልኮ ጋር ግንኙነት አለው። ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህን ሐቅ ለእምነት ባልንጀሮቹ አጥብቆ ለማስገንዘብ ሲል ጥልቅ ትርጉም ያለው ሐሳብ ተጠቅሟል። “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በአምላክ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው” ሲል አሳስቧቸዋል። (ሮም 12:1) ሰውነትህ ሲባል አእምሮህን፣ ልብህንና ኃይልህን ያካትታል። እነዚህን ሁሉ አምላክን ለማገልገል ትጠቀምባቸዋለህ። (ማርቆስ 12:30) ጳውሎስ ይህን የመሰለው የሙሉ ነፍስ አገልግሎት መሥዋዕት እንደሆነ ተናግሯል። “መሥዋዕት” የሚለው ቃል በውስጡ ማስጠንቀቂያ ይዟል። በሙሴ ሕግ፣ እንከን ያለበት መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም ነበር። (ዘሌዋውያን 22:18-20) በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን የሚያቀርበው መንፈሳዊ መሥዋዕት በሆነ መንገድ የጎደፈ ቢሆን አምላክ አይቀበለውም። ይሁንና ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

6, 7. አንድ ክርስቲያን ሰውነቱን ሊያጎድፍ የሚችለው እንዴት ነው? መዘዙስ ምን ሊሆን ይችላል?

6 ጳውሎስ በሮም ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችን “የአካል ክፍሎቻችሁን ለዓመፅ መሣሪያ አድርጋችሁ አታቅርቡ” ሲል መክሯል። በተጨማሪም ‘ሰውነታችሁ ዘወትር የሚፈጽመውን ሥራ ግደሉ’ ብሏቸዋል። (ሮም 6:12-14፤ 8:13) ‘ሰውነት ከሚፈጽማቸው ሥራዎች’ መካከል አንዳንዶቹን ቀደም ሲል በዚሁ ደብዳቤው ላይ ገልጾላቸዋል። ኃጢአተኛ የሆነውን የሰው ልጅ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “አፋቸውም በእርግማንና በጥላቻ ቃል የተሞላ ነው።” “እግሮቻቸው ደም ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው።” “በዓይኖቻቸው ፊት ፈሪሃ አምላክ የለም።” (ሮም 3:13-18) አንድ ክርስቲያን ‘የአካል ክፍሎቹን’ እንደነዚህ ካሉት የኃጢአት ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ቢጠቀምባቸው ሰውነቱን ያረክሳል። ለምሳሌ በዛሬው ጊዜ አንድ ክርስቲያን ሆን ብሎ ወሲባዊ ምስሎችን ወይም የብልግናና አሰቃቂ የጭካኔ ድርጊት የሚታይባቸውን ፊልሞች ቢመለከት ዓይኑን ‘ለዓመፅ [ወይም ለኃጢአት] መሣሪያ አድርጎ ማቅረብ’ ይሆንበታል። ይህን በማድረጉም መላ ሰውነቱን ያረክሳል። ከዚህ በኋላ የሚያቀርበው ማንኛውም ዓይነት አምልኮ ቅዱስ ያልሆነ መሥዋዕት ስለሚሆንበት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያጣል። (ዘዳግም 15:21፤ 1 ጴጥሮስ 1:14-16፤ 2 ጴጥሮስ 3:11) ጤናማ ባልሆኑ መዝናኛዎች ለመዝናናት መምረጥ የሚያስከትለው ኪሳራ ቀላል አይደለም።

7 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አንድ ክርስቲያን የሚመርጠው የመዝናኛ ዓይነት ከባድ መዘዝ ሊያስከትልበት ይችላል። እንግዲያው ለአምላክ የምናቀርበውን መሥዋዕት የሚያጎድፍ ሳይሆን የተሻለ መሥዋዕት እንድናቀርብ የሚረዳንን መዝናኛ እንምረጥ። አሁን ደግሞ ጤናማ የሆነውን መዝናኛ ጤናማ ካልሆነው እንዴት መለየት እንደምንችል እንመልከት።

“ክፉ የሆነውን ነገር ተጸየፉ”

8, 9. (ሀ) በአጠቃላይ ሲታይ መዝናኛን በምን ሁለት መንገዶች ልንከፍለው እንችላለን? (ለ) ከምን ዓይነት መዝናኛዎች መራቅ ይኖርብናል? ለምንስ?

8 በአጠቃላይ ሲታይ መዝናኛ በሁለት ሊከፈል ይችላል። አንደኛው ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ ሊርቁት የሚገባ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው ወይም ላይኖረው የሚችል ነው። በመጀመሪያ ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ የሚርቋቸውን የመዝናኛ ዓይነቶች እንመልከት።

9 በምዕራፍ 1 ላይ እንደተመለከትነው አንዳንድ የመዝናኛ ዓይነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተወገዙ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ናቸው። ወሲባዊ ምስሎችና ቀፋፊ የብልግና ድርጊቶች የሚታዩባቸውን ወይም ጭካኔ የሞላባቸውን አሊያም መናፍስታዊ ይዘት ያላቸውን ድረ-ገጾች፣ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ሙዚቃዎች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንደነዚህ ያሉት ወራዳ የመዝናኛ ዓይነቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሕግጋት ጋር የሚጋጩ ድርጊቶችን ጥሩ እንደሆኑ አድርገው ስለሚያቀርቡ ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ ሊርቋቸው ይገባል። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8) እንደነዚህ ካሉት መጥፎ መዝናኛዎች በመራቅ ‘ክፉ የሆነውን ነገር እንደምትጸየፍና’ አዘውትረህ ‘ከክፉ እንደምትሸሽ’ ለይሖዋ ማሳየት ትችላለህ። በዚህ መንገድ ‘ግብዝነት የሌለበት እምነት’ እንዳለህ ታስመሠክራለህ።ሮም 12:9፤ መዝሙር 34:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:5

10. መዝናኛን በተመለከተ ልናስወግደው የሚገባን አደገኛ አስተሳሰብ ምንድን ነው? ለምንስ?

10 ይሁንና አንዳንዶች የሥነ ምግባር ብልግናን በግልጽ የሚያሳዩ የመዝናኛ ዓይነቶችን መምረጣቸው ምንም ጉዳት እንደሌለው ይሰማቸው ይሆናል። ‘በፊልም ወይም በቴሌቪዥን ልየው እንጂ እኔ ፈጽሞ አላደርገውም’ የሚል ምክንያት ያቀርባሉ። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አታላይ ከመሆኑም በላይ አደገኛ ነው። (ኤርምያስ 17:9) ይሖዋ ያወገዘውን ድርጊት አዝናኝ ሆኖ ካገኘነው ‘ክፉ የሆነውን ነገር እንጸየፋለን’ ማለት እንችላለን? ክፉ ድርጊት የሚታይባቸውን መዝናኛዎች የምናዘወትር ከሆነ ስሜታችን ይደነዝዛል። (መዝሙር 119:70፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2) እንዲህ ያለው ልማድ በድርጊታችንም ሆነ ሌሎች ለሚሠሩት ኃጢአት በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

11. በገላትያ 6:7 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በመዝናኛ ረገድ እውነት መሆኑ የታየው እንዴት ነው?

11 ይህ በእርግጥም የሚደርስ ነገር ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ለመዝናናት ብለው አዘውትረው የሚያዩአቸው ነገሮች ባሳደሩባቸው ተጽዕኖ ምክንያት የሥነ ምግባር ብልግና ፈጽመዋል። ‘ሰው የሚዘራውን ያንኑ እንደሚያጭድ’ ከመከራ ተምረዋል። (ገላትያ 6:7) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን አሳዛኝ መዘዝ ማስቀረት ይቻላል። በአእምሮህ ውስጥ ንጹሕ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ብትዘራ በሕይወትህ ጥሩ ነገሮችን እንደምታጭድ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—“ ምን ዓይነት መዝናኛ መምረጥ ይኖርብኛል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርቶ በግል የሚደረግ ውሳኔ

12. ገላትያ 6:5 ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ተግባራዊ የሚሆነው እንዴት ነው? የግል ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችለን ምን መመሪያ አለን?

12 አሁን ደግሞ በአምላክ ቃል ውስጥ በቀጥታ ያልተወገዙ ወይም ትክክል ናቸው ያልተባሉ ድርጊቶች የሚታዩባቸውን የመዝናኛ ዓይነቶች እንመልከት። እንደነዚህ ዓይነቶቹን መዝናኛዎች መምረጥን በተመለከተ እያንዳንዱ ክርስቲያን የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። (ገላትያ 6:5) እንዲህ ያለ ምርጫ በምናደርግበት ጊዜ ሊረዳን የሚችል መመሪያ እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን አስተሳሰብ እንድናስተውል የሚያስችሉንን መሠረታዊ ሥርዓቶች ወይም መሠረታዊ እውነቶች ይዞልናል። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ትኩረት ሰጥተን በመመርመር፣ የመዝናኛ ምርጫችንን ጨምሮ በሁሉም ነገሮች “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ” ማስተዋል እንችላለን።ኤፌሶን 5:17

13. ይሖዋን ሊያሳዝን ከሚችል መዝናኛ እንድንርቅ የሚገፋፋን ምንድን ነው?

13 ሁሉም ክርስቲያኖች ሥነ ምግባርን በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ ወይም የማስተዋል ችሎታ በእኩል ደረጃ ሊያድግ እንደማይችል ግልጽ ነው። (ፊልጵስዩስ 1:9) ከዚህም በላይ በመዝናኛ ረገድ የሁሉም ሰው ምርጫ አንድ ዓይነት ሊሆን እንደማይችል ክርስቲያኖች ይገነዘባሉ። ስለሆነም ሁሉም ክርስቲያኖች ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ ውሳኔ ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ቢሆንም አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች አእምሯችንንና ልባችንን እንዲመሩልን በፈቀድን መጠን ይሖዋን ሊያሳዝን ከሚችል ከማንኛውም ዓይነት መዝናኛ ለመራቅ ያለን ፍላጎትም እየጨመረ ይሄዳል።መዝሙር 119:11, 129፤ 1 ጴጥሮስ 2:16

14. (ሀ) መዝናኛዎችን በምንመርጥበት ጊዜ ግምት ውስጥ ልናስገባው የሚገባን ነገር ምንድን ነው? (ለ) በሕይወታችን ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠታችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

14 መዝናኛ በምትመርጥበት ጊዜ ግምት ውስጥ ልታስገባ የሚገባህ ሌላው አስፈላጊ ነገር ጊዜህ ነው። የመረጥከው መዝናኛ ይዘት፣ ተቀባይነት አለው ብለህ የምታምነው ነገር ምን እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን በመዝናናት የምታጠፋው የጊዜ መጠን ደግሞ ቅድሚያ የምትሰጠው ለምን ነገር እንደሆነ ይጠቁማል። እርግጥ ነው፣ ለክርስቲያኖች ከመንፈሳዊ ጉዳዮች የበለጠ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንደሌለ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 6:33) ታዲያ በሕይወትህ ውስጥ ምንጊዜም ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ ለመስጠት ምን ማድረግ ትችላለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ለራሳችሁ አመቺ የሆነውን ጊዜ ግዙ” ብሏል። (ኤፌሶን 5:15, 16) በመዝናናት በምታሳልፈው ጊዜ ላይ ግልጽ የሆነ ገደብ ማበጀትህ ‘ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች፣’ ማለትም መንፈሳዊነትህን ሊያሳድጉልህ ለሚችሉ ነገሮች በቂ ጊዜ እንድታገኝ እንደሚረዳህ የተረጋገጠ ነው።ፊልጵስዩስ 1:10

15. መዝናኛዎችን በምንመርጥበት ጊዜ አስፈላጊ ነው ብለን ከምናስበው ይበልጥ ጠንቃቃ መሆናችን አስተዋይነት የሚሆነው ለምንድን ነው?

15 በተጨማሪም መዝናኛ በምንመርጥበት ጊዜ አስፈላጊ ነው ብለን ከምናስበው ይበልጥ ጠንቃቃ መሆን አስተዋይነት ነው። ይህ ምን ማለት ነው? ቀደም ብለን ያነሳነውን የፍሬውን ምሳሌ እንመልከት። ሳይታወቅህ የተበላሸውን ክፍል ላለመብላት ስትል ቆርጠህ የምትጥለው የተበላሸውን ብቻ ሳይሆን ዙሪያውን ያለውን ያልተበላሸ ክፍል ጭምር ነው። በተመሳሳይም መዝናኛ በምንመርጥበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጋችን ጥበብ ይሆናል። አስተዋይ የሆነ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በግልጽ የሚጋጩትን ብቻ ሳይሆን አጠያያቂ የሆኑ ወይም መንፈሳዊ ጤንነትን ሊጎዱ የሚችሉ ክፍሎች ያሉባቸውን መዝናኛዎች ጭምር ይርቃል። (ምሳሌ 4:25-27) የአምላክን ቃል በጥብቅ የምትከተል ከሆነ ይህን ማድረግ አስቸጋሪ አይሆንብህም።

“ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ”

መዝናኛ በምንመርጥበት ጊዜ የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋል ከመንፈሳዊ ጉዳት ይጠብቀናል

16. (ሀ) ሥነ ምግባርን በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋል የሕይወትህ ክፍል ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

16 እውነተኛ ክርስቲያኖች መዝናኛ በሚመርጡበት ጊዜ በመጀመሪያ ደረጃ ከግምት ውስጥ የሚያስገቡት የይሖዋን አስተሳሰብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ምን እንደሚሰማው እንዲሁም መሥፈርቶቹ ምን እንደሆኑ ይገልጽልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ሰለሞን ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ዘርዝሮልናል፤ ከእነሱም መካከል “ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች፣ ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች” ይገኙበታል። (ምሳሌ 6:16-19) የይሖዋ አመለካከት በአንተ አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል? መዝሙራዊው “[ይሖዋን] የምትወዱ ክፋትን ጥሉ” ሲል መክሯል። (መዝሙር 97:10) በመዝናኛ ረገድ የምታደርገው ምርጫ ይሖዋ የሚጠላውን እንደምትጠላ የሚያሳይ መሆን ይገባዋል። (ገላትያ 5:19-21) በተጨማሪም በእርግጥ ምን ዓይነት ሰው መሆንህን በይበልጥ የሚያሳየው በሰዎች ፊት የምታደርገው ሳይሆን ብቻህን በምትሆንበት ጊዜ የምታደርገው ነገር እንደሆነ መዘንጋት የለብህም። (መዝሙር 11:4፤ 16:8) በመሆኑም በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች ይሖዋ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ያለውን ስሜት ለማንጸባረቅ ከልብ የምትፈልግ ከሆነ ሁልጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ምርጫ ታደርጋለህ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋል የሕይወትህ ክፍል እየሆነ ይመጣል።2 ቆሮንቶስ 3:18

17. አንድ ዓይነት መዝናኛ ከመምረጣችን በፊት የትኞቹን ጥያቄዎች ማንሳታችን ተገቢ ይሆናል?

17 የመዝናኛ ምርጫህ ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ምን ተጨማሪ ነገር ልታደርግ ትችላለህ? ‘ይህ መዝናኛ እኔንም ሆነ በአምላክ ፊት የሚኖረኝን አቋም እንዴት ይነካል?’ ብለህ አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ፊልም ለማየት ወይም ላለማየት ከመወሰንህ በፊት ‘የዚህ ፊልም ይዘት በሕሊናዬ ላይ ምን ውጤት ያስከትላል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለዚህ ሁኔታ ሊሠሩ የሚችሉ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመልከት።

18, 19. (ሀ) በፊልጵስዩስ 4:8 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት የመዝናኛ ምርጫችን ጤናማ መሆን አለመሆኑን ለይተን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ጥሩ መዝናኛ እንድትመርጥ የሚረዱህ ሌሎች መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

18 በፊልጵስዩስ 4:8 ላይ ቁልፍ የሆነ አንድ መሠረታዊ ሥርዓት እናገኛለን። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።” እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ይህን የጻፈው መዝናኛን አስመልክቶ ሳይሆን አምላክን ደስ በሚያሰኙ ነገሮች ላይ ሊያተኩር የሚገባውን የልባችንን ሐሳብ በተመለከተ ነው። (መዝሙር 19:14) ይሁን እንጂ ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ለመዝናኛም ሊሠራ ይችላል። እንዴት?

19 ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- “የምመርጣቸው ፊልሞች፣ የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ሙዚቃዎች ወይም ሌላ ዓይነት መዝናኛዎች አእምሮዬ ‘ንጹሕ በሆነው ነገር ሁሉ’ እንዲሞላ የሚያደርጉ ናቸው?” ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ፊልም ከተመለከትክ በኋላ በአእምሮህ የሚመላለሰው ምን ዓይነት ምስል ነው? አስደሳች፣ ንጹሕና መንፈስህን የሚያድስ ከሆነ ጥሩ መዝናኛ እንደመረጥክ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ይሁን እንጂ የተመለከትከው ፊልም ንጹሕ ስላልሆኑ ነገሮች እንድታስብ ካደረገህ ምርጫህ መጥፎ፣ እንዲያውም ጎጂ ነበር ማለት ነው። (ማቴዎስ 12:33፤ ማርቆስ 7:20-23) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሕ ስላልሆኑ ነገሮች ማሰብ ውስጣዊ ሰላም ያሳጣሃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነውን ሕሊናህን ያቆሽሽብሃል፣ እንዲሁም ከአምላክ ጋር የመሠረትከውን ዝምድና ሊያበላሽብህ ይችላል። (ኤፌሶን 5:5፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:5, 19) እንዲህ ያለው መዝናኛ አንተን ራስህን ስለሚጎዳህ ከዚህ ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። * (ሮም 12:2) “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ” ብሎ ወደ ይሖዋ እንደጸለየው መዝሙራዊ ሁን።መዝሙር 119:37

የሌሎችን ጥቅም አስቀድም

20, 21. አንደኛ ቆሮንቶስ 10:23, 24 ጤናማ መዝናኛ ከመምረጥ ጋር ምን ግንኙነት አለው?

20 ጳውሎስ የግል ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ግምት ውስጥ ልናስገባው የሚገባ ቁልፍ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓት ጠቅሷል። “ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሁሉም ነገር ያንጻል ማለት ግን አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ዘወትር የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 10:23, 24) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ጤናማ መዝናኛ ከመምረጥ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ራስህን ‘ስለምመርጠው መዝናኛ ሌሎች ምን ይሰማቸዋል?’ ብለህ መጠየቅ ያስፈልግሃል።

21 የአንተ ሕሊና ‘የተፈቀደ’ ወይም ተቀባይነት ያለው እንደሆነ በሚሰማህ መዝናኛ እንድትዝናና ይፈቅድልህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው መዝናኛ የማያፈናፍን ሕሊና ባላቸው ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ከተገነዘብክ ቢቀርብህ እንደሚሻል ልትወስን ትችላለህ። ለምን? ምክንያቱም ለአምላክ ታማኝ መሆን ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው በማድረግ ‘ወንድሞችህን መበደል’ ወይም ጳውሎስ እንዳለው ‘በክርስቶስ ላይ ኃጢአት መሥራት’ ስለማትፈልግ ነው። “እንቅፋት ከመሆን ተቆጠቡ” የሚለውን ምክር ታስተውላለህ። (1 ቆሮንቶስ 8:12፤ 10:32) በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘የተፈቀደ’ ቢሆንም እንኳ ‘የሚያንጽ’ ካልሆነ መዝናኛ በመራቅ ጳውሎስ የሰጠውን አሳቢነትና ማስተዋል ያለበት ምክር ይከተላሉ።ሮም 14:1፤ 15:1

22. ክርስቲያኖች በግል ጉዳዮች ረገድ የአመለካከት ልዩነቶችን ለማስተናገድ ፈቃደኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

22 ይሁን እንጂ የሌሎችን ጥቅም የማስቀደምን ጉዳይ ከሌላ አቅጣጫም ልናየው እንችላለን። የማያፈናፍን ሕሊና ያለው አንድ ክርስቲያን በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ እሱ ስለ መዝናኛ ያለውን ጥብቅ አመለካከት ካልተቀበሉ ማለት የለበትም። እንዲህ ቢያደርግ በአንድ አውራ ጎዳና ላይ የሚያሽከረክሩ ሾፌሮች በሙሉ ከእኔ እኩል ካላሽከረከሩ ብሎ ድርቅ እንደሚል ሾፌር ይሆናል። እንዲህ ያለው አመለካከት ምክንያታዊ አይደለም። የማያፈናፍን ሕሊና ያለው ክርስቲያን፣ አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቹ በመዝናኛ ምርጫቸው ረገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እስካልተጋጩ ድረስ ከእሱ የተለየ አመለካከት ቢኖራቸውም ክርስቲያናዊ ፍቅር ምርጫቸውን እንዲያከብርላቸው ሊገፋፋው ይገባል። በዚህ መንገድ ‘ምክንያታዊነቱ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ እንዲሆን’ ያደርጋል።ፊልጵስዩስ 4:5፤ መክብብ 7:16

23. ጤናማ መዝናኛ መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?

23 ለማጠቃለል ያህል፣ ጤናማ የሆነ መዝናኛ መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? በአምላክ ቃል ውስጥ በግልጽ የተወገዙ ወራዳ የብልግና ድርጊቶችን ከሚያሳዩ የመዝናኛ ዓይነቶች ራቅ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተለይተው ካልተጠቀሱ የመዝናኛ ዓይነቶች ጋር በተያያዘ ሊሠሩ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተከተል። ሕሊናህን ከሚያቆሽሽ መዝናኛ ራቅ፤ እንዲሁም የሌሎችን በተለይም የእምነት ባልንጀሮችህን ሕሊና ሊረብሽ ከሚችል መዝናኛ ለመራቅ ፈቃደኛ ሁን። በዚህ ረገድ ያደረግከው ቁርጥ ውሳኔ ለአምላክ ክብር እንዲያመጣና አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ እንድትኖሩ የሚያስችላችሁ እንዲሆን ምኞታችን ነው።

^ አን.19 በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ሊሠሩ የሚችሉ ተጨማሪ መሠረታዊ ሥርዓቶች በምሳሌ 3:31፤ 13:20፤ በኤፌሶን 5:3, 4፤ እንዲሁም በቆላስይስ 3:5, 8, 20 ላይ ይገኛሉ።