በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዓመፀኞች ወዮላቸው!

ለዓመፀኞች ወዮላቸው!

ምዕራፍ አሥራ አንድ

ለዓመፀኞች ወዮላቸው!

ኢሳይያስ 9:​8–10:​4

1. ኢዮርብዓም የፈጸመው ከባድ ስህተት ምን ነበር?

የይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝብ ለሁለት መንግሥት በተከፈለ ጊዜ ሰሜናዊውን የአሥሩን ነገድ መንግሥት ኢዮርብዓም ተቆጣጠረው። አዲሱ ንጉሥ ብቃት ያለው ብርቱ ገዢ ነበር። ይሁን እንጂ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት አልነበረውም። ከዚህ የተነሣ የሰሜናዊውን መንግሥት ታሪክ በእጅጉ ያመሰቃቀለ ከባድ ስህተት ሠርቷል። እስራኤላውያን በዓመት ሦስት ጊዜ ያህል ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲሄዱ የሙሴ ሕግ ያዝዝ ነበር። በዚህ ጊዜ ደግሞ ቤተ መቅደሱ የነበረው በደቡባዊው የይሁዳ ግዛት ውስጥ ነው። (ዘዳግም 16:​16) ኢዮርብዓም ተገዢዎቹ ዘወትር እንዲህ ያለውን ጉዞ የሚያደርጉ ከሆነ ከደቡባዊ ወንድሞቻችን ጋር እንቀላቀል የሚል ሐሳብ ይመጣባቸዋል ብሎ ስለፈራ “ሁለትም የወርቅ ጥጃዎች አድርጎ:- እስራኤል ሆይ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ትወጡ ዘንድ ይበዛባችኋል፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህን አማልክቶችህን እይ አላቸው። አንዱን በቤቴል፣ ሁለተኛውንም በዳን አኖረ።”​—⁠1 ነገሥት 12:​28, 29

2, 3. ኢዮርብዓም የሠራው ስህተት በእስራኤል ላይ ያስከተለው ውጤት ምንድን ነው?

2 ለጊዜው የኢዮርብዓም ዕቅድ የሰመረለት ይመስል ነበር። ሕዝቡ ቀስ በቀስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱን ተወና ለሁለቱ ጥጃዎች ይሰግድ ጀመር። (1 ነገሥት 12:​30) ይሁን እንጂ ይህ ሃይማኖታዊ የክህደት ተግባር የአሥሩን ነገድ መንግሥት አበላሽቶታል። በኋለኛው ዘመን የተነሣውና የበኣልን አምልኮ ከእስራኤል ጠራርጎ በማስወገድ ረገድ እጅግ ከፍተኛ ቅንዓት ያሳየው ኢዩ እንኳ ሳይቀር ለወርቅ ጥጃዎቹ መስገዱን ቀጥሏል። (2 ነገሥት 10:​28, 29) አሳዛኝ የሆነው የኢዮርብዓም የተሳሳተ ውሳኔ ያስከተለው ሌላው ውጤት ምን ነበር? ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ነግሦና ሕዝቡም ለሰቆቃ ተዳርጎ ነበር።

3 ኢዮርብዓም ከሃዲ ሆኖ ስለነበር ዘሩ ምድሪቱን እንደማይገዛና በመጨረሻም ሰሜናዊው መንግሥት ከባድ ችግር ላይ እንደሚወድቅ ይሖዋ ተናግሮ ነበር። (1 ነገሥት 14:​14, 15) ደግሞም የተናገረው ቃል በትክክል ተፈጽሟል። ከእስራኤል ነገሥታት መካከል ሰባቱ ሥልጣን ላይ የቆዩት ለሁለት ዓመትና ከዚያም ላነሰ ጊዜ ሲሆን አንዳንዶቹም የገዙት ለጥቂት ቀናት ብቻ ነበር። አንድ ንጉሥ የገዛ ሕይወቱን ሲያጠፋ ስድስት ነገሥታት ደግሞ ዙፋናቸውን በገለበጡት የሥልጣን ጥመኛ ሰዎች ተገድለዋል። በተለይ በ804 ከዘአበ ካበቃው ከዳግማዊ ኢዮርብዓም ግዛት በኋላ ንጉሥ ዖዝያን በይሁዳ እየገዛ ሳለ እስራኤል አለመረጋጋት፣ ዓመፅና ግድያ ሞልቶባት ነበር። ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ለሰሜናዊው መንግሥት ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ ወይም “ቃል” የላከው ይህን ሁኔታ በመቃወም ነው። “ጌታ በያዕቆብ ላይ ቃልን ሰደደ፣ በእስራኤልም ላይ ወደቀ።”​—⁠ኢሳይያስ 9:​8 *

ትዕቢትና ኩራት የአምላክን ቁጣ ያስከትላል

4. ይሖዋ በእስራኤል ላይ የተናገረው “ቃል” ምንድን ነው? ለምንስ?

4 የይሖዋ “ቃል” ቸል ተብሎ አይታለፍም። “በትዕቢትና በልብ ኩራት . . . በኤፍሬምና በሰማርያ የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ [ቃሉን] ያውቃሉ።” (ኢሳይያስ 9:​9, 10) “ያዕቆብ፣” “እስራኤል፣” “ኤፍሬም” እና “ሰማርያ” የሚሉት ስሞች ሁሉ የሚያመለክቱት የኤፍሬም ነገድ ጉልህ ሥፍራ የያዘበትንና ዋናው ከተማ ሰማርያ የሆነውን ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት ነው። ኤፍሬም በክህደት ልቡን አደንድኖና በይሖዋ ላይ ኮርቶ ስለነበር ይሖዋ ስለዚህ መንግሥት የተናገረው ቃል ጠንካራ የፍርድ መልእክት ነው። አምላክ ክፉ መንገዳቸው ካስከተለባቸው መዘዝ አይጠብቃቸውም። የአምላክን ቃል ለመስማት ወይም በትኩረት ለመከታተል ይገደዳሉ።​—⁠ገላትያ 6:​7

5. እስራኤላውያን ይሖዋ በወሰደው የፍርድ እርምጃ እንዳልተነኩ ያሳዩት እንዴት ነው?

5 ሁኔታዎቹ እየከፉ ሲሄዱ በአብዛኛው ከጭቃ ጡብና ርካሽ ከሆኑ እንጨቶች የተሠሩ ቤቶቻቸውን ጨምሮ ሕዝቡ ከባድ ኪሳራ ላይ ይወድቃል። ከዚህ የተነሳ ልባቸው ይለሰልስ ይሆን? የይሖዋ ነቢያት የሚሉትን ሰምተው ወደ እውነተኛው አምላክ ይመለሱ ይሆን? * ኢሳይያስ የሕዝቡን ኩራት የተሞላበት ምላሽ በተመለከተ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “ጡቡ ወድቆአል፣ ነገር ግን በተወቀረ ድንጋይ እንሠራለን፤ የሾላ ዛፎች ተቈርጠዋል፣ ነገር ግን ዝግባን እንተካባቸዋለን” (ኢሳይያስ 9:​10) እስራኤላውያን ይሖዋን ከመገዳደራቸውም በላይ እንዲህ ዓይነት ከባድ መከራ እየደረሰባቸው ያለው ለምን እንደሆነ የሚነግሯቸውን ነቢያት አልተቀበሏቸውም። ‘ከሚፈረካከስ የጭቃ ጡብና ከማይረባ እንጨት የተሠራ ቤት አጥተን ይሆናል፤ እኛ ግን በተጠረበ ድንጋይና ዝግባን በመሳሰሉ እጅግ የተሻሉ ነገሮች እንገነባለን!’ እንዳሉ ያህል ነበር። (ከ⁠ኢዮብ 4:​19 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ እነርሱን ከመቅጣት ሌላ አማራጭ አልነበረውም።​—⁠ከ⁠ኢሳይያስ 48:​22 ጋር አወዳድር።

6. ሶርያና እስራኤል በይሁዳ ላይ የዶለቱትን ሐሳብ ይሖዋ ያከሸፈው እንዴት ነው?

6 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ይሖዋ የረዓሶንን ተቃዋሚዎች በላዩ ያስነሳበታል።” (ኢሳይያስ 9:​11 NW) የእስራኤሉ ንጉሥ ፋቁሔና የሶርያው ንጉሥ ረዓሶን አንድ ግንባር ፈጥረዋል። የባለ ሁለት ነገዱን የይሁዳ መንግሥት ድል አድርገው በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ ዙፋን ላይ “የጣብኤልን ልጅ” በማስቀመጥ የአሻንጉሊት መንግሥት ለመመሥረት አስበው ነበር። (ኢሳይያስ 7:​6) ይሁን እንጂ ሴራው ከሸፈ። ረዓሶን ኃያላን ጠላቶች የነበሩት ሲሆን ይሖዋም እነዚህን ጠላቶቹን ‘በላዩ’ ማለትም በእስራኤል ላይ ‘ያስነሣበታል።’ ‘በላዩ ያስነሣበታል’ የሚለው መግለጫ ኅብረታቸውን የሚያፈርስና ዓላማቸውን የሚያከሽፍ ጦርነት እንዲከፍቱበት ይፈቅዳል ማለት ነው።

7, 8. አሦራውያን ሶርያን ድል ማድረጋቸው በእስራኤል ላይ ያስከተለው ውጤት ምንድን ነው?

7 ኅብረታቸው መፍረስ የጀመረው አሦር በሶርያ ላይ ጥቃት ስትሰነዝር ነው። “የአሦርም ንጉሥ በደማስቆ [በሶርያ ዋና ከተማ] ላይ ወጣባት ወሰዳትም፣ ሕዝብዋንም ወደ ቂር አፈለሳቸው፣ ረአሶንንም ገደለ።” (2 ነገሥት 16:​9) ፋቁሔ ብርቱ የነበረውን አጋሩን በማጣቱ በይሁዳ ላይ የዶለተው ነገር መና እንደቀረ ተገነዘበ። እንዲያውም ረአሶን ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፋቁሔ ራሱ የሰማርያን ዙፋን በኃይል በገለበጠው በሆሴዕ ተገድሏል።​—⁠2 ነገሥት 15:​23-25, 30

8 ቀደም ሲል የእስራኤል አጋር የነበረችው ሶርያ የአካባቢው ኃያል በሆነችው በአሦር ሥር የምትተዳደር ግዛት ሆናለች። ይሖዋ ይህን አዲስ ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንዴት እንደሚጠቀምበት ኢሳይያስ ሲተነብይ እንዲህ ብሏል:- [ይሖዋ] ጠላቶቹን [የእስራኤልን ጠላቶች] ሶርያውያንንም ከምሥራቅ፣ ፍልስጥኤማውያንንም ከምዕራብ [“ከበስተ ኋላ፣” NW] ያንቀሳቅስበታል፤ እስራኤልንም በተከፈተ አፍ ይበሉታል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቁጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።” (ኢሳይያስ 9:​12) አዎን፣ አሁን ሶርያ የእስራኤል ጠላት ስለሆነች እስራኤል ከአሦር እና ከሶርያ ለሚሰነዘርባት ጥቃት ራሷን ማዘጋጀት ይኖርባታል። ወረራው ተሳካና አሦር በኃይል ሥልጣን ላይ በወጣው በሆሴዕ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ግብር በመጫን አገልጋይዋ አደረገችው። (ከጥቂት አሥርተ ዓመታትም በፊት አሦር ከእስራኤሉ ንጉሥ ከምናሔም ከፍተኛ መጠን ያለው ክፍያ ወስዳለች።) “እንግዶች ጉልበቱን [የኤፍሬምን] በሉት” የሚሉት የነቢዩ ሆሴዕ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!​—⁠ሆሴዕ 7:​9፤ 2 ነገሥት 15:​19, 20፤ 17:​1-3

9. ፍልስጤማውያን ጥቃት የሰነዘሩት “ከበስተ ኋላ” ነው ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

9 ፍልስጤማውያን “ከበስተ ኋላ” ወረራ እንደሚያካሂዱ ኢሳይያስ ተናግሮ የለምን? አዎን፣ መግነጢሳዊ አቅጣጫ ጠቋሚዎች ከመሠራታቸው በፊት ዕብራውያኑ አቅጣጫን የሚያመለክቱት ፊቱን ወደ ፀሐይ መውጫ ካዞረ ሰው አንጻር ሆነው ነበር። በመሆኑም ፊቱ ‘ምሥራቅ’ ሲሆን ምዕራብ ወይም የፍልስጤማውያኑ መኖሪያ የሆነው የባሕር ዳርቻ ደግሞ ‘ኋላው’ ነበር። ፍልስጤማውያን በፋቁሔ ዘመን በነበረው በአካዝ ጊዜ ይሁዳን በመውረር በይሁዳ አውራጃ የሚገኙ በርከት ያሉ ከተሞችንና የተመሸጉ አምባዎችን ተቆጣጥረው ስለነበር በኢሳይያስ 9:​12 ላይ የተጠቀሰው “እስራኤል” በዚህ አገባቡ ይሁዳንም የሚጨምር ሊሆን ይችላል። በስተ ሰሜን እንደነበረው ኤፍሬም ሁሉ ይሁዳም ክህደት ተጠናውቷት ስለነበር ይህን የይሖዋን ቅጣት መቅመስ ነበረባት።​—⁠2 ዜና መዋዕል 28:​1-4, 18, 19

‘ከራሱ እስከ ጅራቱ’ ድረስ ዓመፀኛ የሆነ ብሔር

10, 11. እስራኤል ከዓመፅዋ አልመለስም በማለትዋ ይሖዋ ምን ቅጣት ያመጣባታል?

10 ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ብዙ መከራ ቢደርስበትና የይሖዋ ነቢያት ከባድ ማስጠንቀቂያ ቢያሰሙም በይሖዋ ላይ ማመፁን ቀጥሏል። “ሕዝቡ ግን ወደ ቀሠፋቸው አልተመለሱም፣ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን አልፈለጉም።” (ኢሳይያስ 9:​13) ከዚህ የተነሣ ነቢዩ እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ እግዚአብሔር ራስንና ጅራትን፣ የሰሌኑን ቅርንጫፍና እንግጫውን በአንድ ቀን ከእስራኤል ይቆርጣል። ሽማግሌውና ከበርቴው እርሱ ራስ ነው፤ በሐሰትም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው። ይህን ሕዝብ የሚመሩ ያስቱአቸዋል፤ ተማሪዎቹም ይጠፋሉ።”​—⁠ኢሳይያስ 9:​14-16

11 ‘ራስና’ ‘ቅርንጫፍ’ የተባሉት ‘ሽማግሌውና ከበርቴው’ ማለትም የሕዝቡ መሪዎች ናቸው። ‘ጭራውና’ ‘እንግጫው’ ደግሞ መሪዎቻቸውን ደስ የሚያሰኝ ቃል የሚናገሩትን ሐሰተኛ ነቢያት ያመለክታል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሐሰተኛ ነቢያቱ በሥነ ምግባር ከሕዝቡ ሁሉ ያዘቀጡና ክፉ ከነበሩት ነገሥታት ሥር ሥር የሚሉ አጫፋሪዎች በመሆናቸው ጭራ ተብለው ተጠርተዋል።” ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ጄ ያንግ እነዚህን የሐሰት ነቢያት በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህ መሪዎች ሳይሆኑ መሪዎቹ በመሯቸው እየሄዱ የሚያጎበድዱና የሚሸነግሉ እንዲሁም እንደ ውሻ ጭራቸውን የሚቆሉ ሰዎች ናቸው።”​—⁠ከ⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​3 ጋር አወዳድር።

‘መበለቶችና አባት የሌላቸው ልጆች’ ሳይቀሩ ዓመፀኛ ሆነዋል

12. የሥነ ምግባር ብልሹነት በእስራኤል ኅብረተሰብ ውስጥ ምን ያህል ተስፋፍቶ ነበር?

12 ይሖዋ ለመበለቶችና አባት ለሌላቸው ልጆች ተሟጋች ነው። (ዘጸአት 22:​22, 23) ይሁንና አሁን ኢሳይያስ ምን እንደሚል አዳምጥ:- “ሰው ሁሉ ዝንጉና ክፉ ሠሪ ነውና፣ አፍም ሁሉ ስንፍናን ይናገራልና ስለዚህ ጌታ በጐልማሶቻቸው ደስ አይለውም፣ ለድሀ አደጎቻቸውና [“አባት ለሌላቸው ልጆችና፣” NW] ለመበለቶቻቸውም አይራራም። በዚህም ሁሉ እንኳ ቁጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።” (ኢሳይያስ 9:​17) መበለቶችንና አባት የሌላቸውን ልጆች ጨምሮ ክህደት ያልበከለው የኅብረተሰብ ክፍል አልነበረም! ይሖዋ ሕዝቡ መንገዳቸውን ይቀይሩ እንደሆነ ብሎ በማሰብ በትዕግሥት ነቢያቱን ይልካል። ለምሳሌ ያህል ሆሴዕ “በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ” በማለት ተማጽኗል። (ሆሴዕ 14:​1) ለመበለቶችና አባት ለሌላቸው ልጆች ለሚቆረቆረው አምላክ በእነርሱ ላይ ሳይቀር የፍርድ እርምጃ ማስፈጸም እንዴት የሚከብድ ነገር ነው!

13. በኢሳይያስ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ምን እንማራለን?

13 ልክ እንደ ኢሳይያስ እኛም የምንኖረው ይሖዋ በክፉዎች ላይ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ባለው አስጨናቂ ጊዜ ላይ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) እንግዲያው እውነተኛ ክርስቲያኖች የኑሮ ሁኔታቸው ምንም ዓይነት ይሁን ምን የአምላክን ሞገስ እንዳገኙ ለመቀጠል መንፈሳዊ፣ ሥነ ምግባራዊና አእምሮአዊ ንጽሕናቸውን መጠበቃቸው በጣም አስፈላጊ ነው። እያንዳንዳችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በቅንዓት እንጠብቅ። ማንኛችንም ብንሆን አንድ ጊዜ ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ካመለጥን በኋላ ዳግም ‘በኃጢአትዋ እንዳንተባበር’ እንጠንቀቅ።​—⁠ራእይ 18:​2, 4

የሐሰት አምልኮ ዓመፅን ያስፋፋል

14, 15. (ሀ) የአጋንንት አምልኮ የሚያስከትለው ውጤት ምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ የተነበየው እስራኤል ምን ቀጣይ የሆነ መከራ እንደሚደርስባት ነው?

14 የሐሰት አምልኮ ማለት የአጋንንት አምልኮ ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:​20) ከጥፋት ውኃ በፊት እንደታየው ደግሞ የአጋንንት ተጽእኖ ወደ ዓመፅ ይመራል። (ዘፍጥረት 6:​11, 12) እንግዲያው እስራኤላውያን ከሃዲዎች ሲሆኑና በአጋንንት አምልኮ ውስጥ መግባት ሲጀምሩ ምድሪቱ በዓመፅና በክፋት መታመሷ ምንም አያስገርምም።​—⁠ዘዳግም 32:​17፤ መዝሙር 106:​35-38

15 ኢሳይያስ በእስራኤል ውስጥ ክፋትና ዓመፅ መስፋፋቱን እንደሚከተለው በማለት በግልጽ አስቀምጦታል:- “ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፤ ኩርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፣ ጢሱም ተትጐልጉሎ እንደ ዓምድ ይወጣል። በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቁጣ ምድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም። ሰው በቀኙ በኩል ይነቅላል ይራብማል፤ በግራም በኩል ይበላል አይጠግብምም፤ እያንዳንዱም የክንዱን ሥጋ ይበላል፤ ምናሴ ኤፍሬምን ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ እነርሱ በአንድነት የይሁዳ ጠላቶች ይሆናሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቁጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።”​—⁠ኢሳይያስ 9:​18-21

16. የ⁠ኢሳይያስ 9:​18-21 ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?

16 ከኩርንችት ወደ ኩርንችት እንደሚዛመት እሳት ዓመፁ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በፍጥነት ‘ጭፍቅ ወደሆነው ዱር’ ይደርስና ሙሉ በሙሉ እንደተያያዘ የደን እሳት ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሆኑት ካርል እና ዴሊትሽ በወቅቱ የነበረው ዓመፅ ምን ያህል እንደነበር ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “ድብልቅልቅ ባለ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የታየ የከፋ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ነው። ርኅራኄ በሌለው መንገድ እርስ በርሳቸው ቢጨራረሱም የልባቸው አልደረሰም።” የኤፍሬምና የምናሴ ነገድ እዚህ ላይ ተለይተው የተጠቀሱት የሰሜናዊው መንግሥት ዋነኛ ወኪሎች በመሆናቸው እንዲሁም የሁለቱ የዮሴፍ ልጆች ዝርያ እንደመሆናቸው መጠን ከአሥሩ ነገዶች መካከል የበለጠ ቅርርብ ስለነበራቸው ይመስላል። እንደዚያም ሆኖ ግን እርስ በርስ መበላላታቸውን የሚያቆሙት በደቡብ ከምትገኘው ይሁዳ ጋር ሲዋጉ ብቻ ነው።​—⁠2 ዜና መዋዕል 28:​1-8

ብልሹ መሳፍንት ፍርድ ሰጪያቸው ፊት ይቀርባሉ

17, 18. በእስራኤል የሕግና የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ምን ብልሹነት ይታያል?

17 ቀጥሎ ይሖዋ ፍርድ ለመስጠት ዓይኑን የሚያሳርፈው ብልሹ በሆኑት የእስራኤል መሳፍንትና ሌሎች ባለ ሥልጣናት ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች ፍትሕ ፍለጋ ወደ እነርሱ የሚመጡትን ድሆችና ችግረኞች በመበዝበዝ ሥልጣናቸውን አላግባብ ይጠቀማሉ። ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “መበለቶችም ቅሚያቸው እንዲሆኑ፣ ድሀ አደጎችንም [“አባት የሌላቸውንም ልጆች፣” NW] ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፣ የድሀውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፣ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ፣ ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው!”​—⁠ኢሳይያስ 10:​1, 2

18 የይሖዋ ሕግ ማንኛውንም ዓይነት የፍትሕ መጓደል ያወግዛል:- “በፍርድ ዓመፃ አታድርጉ፤ ለድሀ አታድላ፣ ባለ ጠጋውንም አታክብር።” (ዘሌዋውያን 19:​15) እነዚህ ባለ ሥልጣናት ይህንን ሕግ ወደ ጎን በመተው የመበለቶችንና አባት የሌላቸውን ልጆች የመጨረሻ ጥሪት በማሟጠጥ የከፋ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ዓይን ያወጣ ሌብነት ለመፈጸም ሲሉ የራሳቸውን ‘የግፍ ትእዛዝ’ ጽፈዋል። እርግጥ ነው የእስራኤል የሐሰት አማልክት ይህን የፍትሕ መጓደል የሚያስተውሉበት ዓይን የላቸውም። ይሖዋ ግን ችላ ብሎ አያልፈውም። ይሖዋ አሁን በኢሳይያስ አማካኝነት ትኩረቱን ያደረገው በእነዚህ ክፉ መሳፍንት ላይ ነው።

19, 20. ብልሹ የሆኑት የእስራኤል መሳፍንት ሁኔታ የሚለወጠው እንዴት ነው? ‘ክብራቸውስ’ ምን ይሆናል?

19 “በተጐበኛችሁበት ቀን፣ መከራም ከሩቅ በሚመጣበት ዘመን ምን ታደርጉ ይሆን? ለረድኤትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ክብራችሁንስ ወዴት ትተዉታላችሁ? ከእስረኞች በታች ይጐነበሳሉ፣ ከተገደሉትም በታች ይወድቃሉ።” (ኢሳይያስ 10:​3, 4ሀ) መበለቶችና አባት የሌላቸው ልጆች አቤት የሚሉበት ሐቀኛ ዳኛ አያገኙም። ከዚህ አንጻር ሲታይ ይሖዋ የእስራኤልን ብልሹ መሳፍንት በተጠያቂነት ሲይዛቸው ለእርዳታ ወደ ማን ዘወር እንደሚሉ መጠየቁ ምንኛ ተገቢ ነው። አዎን፣ “በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ” መሆኑን የሚማሩበት ጊዜ ደርሷል።​—⁠ዕብራውያን 10:​31

20 የእነዚህ ክፉ መሳፍንት ‘ክብር’ ማለትም ከሥልጣናቸውና ከሀብታቸው ጋር የተያያዘው ዓለማዊ ዝና፣ ክብርና ሥልጣን ዕድሜው አጭር ነው። አንዳንዶች የጦር ምርኮኞች ሆነው ከሌሎች እስረኞች ጋር ‘ሲጎነበሱ’ ወይም ሲሰግዱ ሌሎች ደግሞ ይገደሉና አስከሬናቸው በጦር ሜዳ ግዳዮች ይሸፈናል። ‘ክብራቸው’ ያላግባብ ያካበቱትን ሀብት የሚጨምር ሲሆን ይህንንም ጠላቶቻቸው ይገፍፏቸዋል።

21. እስራኤል የደረሰባት ቅጣት የይሖዋን ቁጣ ያበርደዋልን?

21 ኢሳይያስ የመጨረሻውን የግጥም አንቀጽ የሚደመድመው እጅግ አስፈሪ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ነው:- “በዚህም ሁሉ [ብሔሩ እስካሁን ይህ ሁሉ ወዮታ ቢደርስበትም] እንኳ ቁጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።” (ኢሳይያስ 10:​4ለ) አዎን፣ ይሖዋ ገና ከእስራኤል ጋር ያልጨረሰው ነገር አለ። ዓመፀኛ በሆነው ሰሜናዊው መንግሥት ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የቅጣት ክንዱን ሳያሳርፍ የተዘረጋችው እጁ አትመለስም።

በሐሰትና የራስን ጥቅም በማሳደድ ወጥመድ አትውደቁ

22. እስራኤል ከገጠማት ነገር እኛ ምን ትምህርት እናገኛለን?

22 ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት ለእስራኤል የተናገራቸው ቃላት ኃይለኛ ነበሩ። ደግሞም ‘በከንቱ ወደ እርሱ አልተመለሱም።’ (ኢሳይያስ 55:​10, 11) የሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት የማያምር ፍጻሜ ከታሪክ መረዳት ይቻላል። ነዋሪዎቿ ምን ያህል ስቃይ እንደደረሰባቸው መገመት እንችላለን። ዛሬ ባለው የነገሮች ሥርዓት በተለይም ደግሞ ከሃዲ በሆነችው ሕዝበ ክርስትና ላይም የአምላክ ቃል እንዲሁ እንደሚፈጸም ምንም አያጠራጥርም። እንግዲያው ክርስቲያኖች ለውሸትና አምላክን ለሚቃወም ፕሮፓጋንዳ ጆሮአቸውን አለመስጠታቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! ለአምላክ ቃል ምስጋና ይግባውና እኛም እንደ ጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ እንዳንታለል ሰይጣን የሚጠቀምባቸው መሰሪ ዘዴዎች ምን እንደሆኑ ከረጅም ዘመን በፊት ግልጽ ሆነው ተቀምጠውልናል። (2 ቆሮንቶስ 2:​11) ሁላችንም ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” ማምለካችንን እንቀጥል። (ዮሐንስ 4:​24) እንደዚያ ከሆነ የተዘረጋችው እጁ ኤፍሬምን እንደመታች አምላኪዎቹን ከመምታት ይልቅ ታቅፋቸዋለች። እርሱም ገነት በምትሆነው ምድር ወደሚገኘው የዘላለም ሕይወት በሚያደርጉት ጉዞ ይደግፋቸዋል።​—⁠ያዕቆብ 4:​8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ኢሳይያስ 9:​8–10:​4 ላይ ያሉት አራት የግጥም አንቀጾች ሲሆኑ እያንዳንዳቸው የሚደመደሙት “በዚህም ሁሉ እንኳ ቁጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች” በሚለው የማስጠንቀቂያ አዝማች ነው። (ኢሳይያስ 9:​12, 17, 21፤ 10:​4) ይህ የአጻጻፍ ዘይቤ ኢሳይያስ 9:​8–10:​4ን እንደ አንድ “ቃል” አስተሳስሯቸዋል። (ኢሳይያስ 9:​8) የይሖዋ እጅ ‘ገና ተዘርግታ ያለችው’ ለእርቅ ሳይሆን ፍርድ ለመስጠት እንደሆነ ልብ በል።​—⁠ኢሳይያስ 9:​13

^ አን.5 በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ከነበሩት የይሖዋ ነቢያት መካከል ኢዩ (ንጉሡ አይደለም)፣ ኤልያስ፣ ሚካያ፣ ኤልሳዕ፣ ዮናስ፣ ኦዴድ፣ ሆሴዕ፣ አሞጽ እና ሚክያስ ይገኙበታል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 139 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

ክፋትና ዓመፅ እስራኤልን እንደ ጫካ እሳት አዳርሷታል

[በገጽ 141 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

ሌሎችን የሚበዘብዙትን ሰዎች ይሖዋ ወደ ፍርድ ያመጣቸዋል