ለዘመናችን የሚሆን መልእክት ያስተላለፈ ጥንታዊ ነቢይ
ምዕራፍ አንድ
ለዘመናችን የሚሆን መልእክት ያስተላለፈ ጥንታዊ ነቢይ
1, 2. (ሀ) ዛሬ በዓለም ላይ ምን አሳዛኝ ሁኔታዎች እናያለን? (ለ) አንድ የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የኅብረተሰቡን መፍረክረክ በተመለከተ የተሰማቸውን ስጋት የገለጹት እንዴት ነው?
ዛሬ የሰውን ልጅ ከገጠሙት ችግሮች ለመገላገል የማይናፍቅ ማን አለ? ይሁንና ጉጉታችን ሁሉ የውኃ ሽታ ሆኖ የቀረበት ጊዜ ስፍር ቁጥር የለውም! ስለ ሰላም ብናልምም ጦርነት የጎን ውጋት ሆኖብናል። ሕግና ሥርዓት ሰፍኖ ለማየት ብንመኝም እያደር እየጨመረ የሚሄደውን ዝርፊያ፣ የግዳጅ ወሲብና የነፍስ ግድያ መግታት አልቻልንም። ጎረቤቶቻችንን ልናምናቸው እንደሚገባ ቢሰማንም ለጥበቃ ስንል በሮቻችንን እንቆልፋለን። ልጆቻችንን ስለምንወዳቸው በሥነ ምግባር ኮትኩተን ለማሳደግ ብንፈልግም አብዛኛውን ጊዜ ለእኩዮቻቸው መጥፎ ተጽዕኖ በቀላሉ ሲሸነፉ እናያለን።
2 አጭር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ‘በመከራ የተሞላ’ ነው ሲል ከተናገረው ከኢዮብ ጋር ሙሉ በሙሉ እንስማማ ይሆናል። (ኢዮብ 14:1) በተለይ የሰው ልጅ ኅብረተሰብ ካሁን ቀደም ታይቶ በማያውቅ መጠን እየተፈረካከሰ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ይህ አባባል ይበልጥ እውነት ሆኖ ይታያል። አንድ የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ዛሬ ቀዝቃዛው ጦርነት አብቅቷል። የሚያሳዝነው ግን ዓለም በዘር፣ በጎሳና በሃይማኖት ምክንያት የሚወሰዱ የበቀል እርምጃዎችና የጭካኔ ተግባሮች መድረክ ሆናለች። . . . የሥነ ምግባር መስፈርቶቻችን እጅግ ከመዳከማቸው የተነሣ ዛሬ ብዙዎቹ ወጣቶቻችን ለግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥ ከመዳረግም አልፈው የችግር አዘቅት ውስጥ ገብተዋል። የወላጆች ግዴለሽነት፣ ፍቺ፣ በልጆች ላይ የሚፈጸም በደል፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች እርግዝና፣ ትምህርት ማቆም፣ ሕገ ወጥ መድኃኒቶችና በየመንገዱ የሚፈጸመው ዓመፅ ያስከተሉትን ውጤት እያጨድን ነው። ቤታችን እንደ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ እንቆጥረው ከነበረው ከቀዝቃዛው ጦርነት ተርፎ አሁን በምስጥ እየተበላ እንዳለ ያክል ነው።”
3. ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ የሚሰጠን በተለይ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ነው?
3 ይሁን እንጂ ምንም ተስፋ የለንም ማለት አይደለም። አምላክ 2, 700 ከሚያህሉ ዓመታት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ይኖር የነበረ አንድ ሰው በመንፈስ ተነሳስቶ ዛሬ ላለንበት ዘመን ልዩ ትርጉም ያላቸውን ተከታታይ ትንቢቶች እንዲናገር አድርጓል። እነዚህ መልእክቶች ኢሳይያስ በተባለው በዚያ ነቢይ ስም በተሰየመው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። ኢሳይያስ ማን ነበር? የዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት ገደማ የተመዘገበው ትንቢቱስ ዛሬ ለመላው የሰው ልጅ ብርሃን ይፈነጥቃል የምንለው ለምንድን ነው?
ሥርዓት አልበኝነት በነገሠበት ዘመን የኖረ ጻድቅ ሰው
4. ኢሳይያስ ማን ነበር? የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ያገለገለውስ መቼ ነበር?
4 ኢሳይያስ “የአሞጽ ልጅ ” * መሆኑን በመጽሐፉ የመጀመሪያ ቁጥር ላይ ካስተዋወቀ በኋላ “በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ” የአምላክ ነቢይ ሆኖ እንዳገለገለ ይነግረናል። (ኢሳይያስ 1:1) በዚህ መሠረት ኢሳይያስ ከ46 ለማያንሱ ዓመታት በይሁዳ ብሔር መካከል የአምላክ ነቢይ ሆኖ አገልግሏል። እንደዚያ ከሆነ አገልግሎቱን የጀመረው በንጉሥ ዖዝያን የግዛት ዘመን ማብቂያ ላይ ማለትም በ778 ከዘአበ ገደማ መሆን አለበት።
5, 6. የኢሳይያስን የቤተሰብ ሕይወት በተመለከተ ምን ነገር እውነት ነበር ለማለት ይቻላል? ለምንስ?
5 ስለ ሌሎች ነቢያት ከምናውቀው ነገር ጋር ሲወዳደር ስለ ኢሳይያስ የግል ሕይወት የምናውቀው ነገር በጣም ውስን ነው። ባለትዳር እንደነበርና ሚስቱን “ነቢይቱ” ብሎ እንደጠራት እናውቃለን። (ኢሳይያስ 8:3) ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክለሲያስቲካል ሊትሬቸር የሚል ስያሜ ያለው የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፔዲያ እንዳለው ከሆነ ይህ አጠራር የኢሳይያስ የትዳር ሕይወት “ከሥራው ጋር የሚስማማ ብቻ ሳይሆን በጥብቅ የተቆራኘም” እንደነበር ይጠቁማል። እንደ አንዳንዶቹ አምላካዊ ፍርሃት የነበራቸው የእስራኤል ሴቶች ሁሉ የኢሳይያስም ሚስት የራሷ የነቢይነት ሚና ኖሯት ሊሆን ይችላል።—መሳፍንት 4:4፤ 2 ነገሥት 22:14
6 ኢሳይያስና ሚስቱ ቢያንስ ሁለት ወንዶች ልጆች የነበሯቸው ሲሆን የልጆቻቸው ስም የየራሱ ትንቢታዊ ትርጉም ነበረው። ኢሳይያስ ክፉ ለነበረው ለንጉሥ አካዝ የአምላክን መልእክት ለማድረስ በሄደበት ጊዜ የበኩር ልጁ ያሱብ አብሮት ነበር። (ኢሳይያስ 7:3) ኢሳይያስና ሚስቱ የይሖዋን አምልኮ የቤተሰብ ሕይወታቸው ክፍል አድርገውት እንደነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይህ ዛሬ ላሉት ባለ ትዳሮች እንዴት ግሩም ምሳሌ ነው!
7. በኢሳይያስ ዘመን በይሁዳ የነበረው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ግለጽ።
7 ኢሳይያስና ቤተሰቡ የኖሩት በይሁዳ ታሪክ ሥርዓት አልበኝነት በነገሠበት ዘመን ነበር። ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና በጉቦ መፍረድ በእጅጉ ተስፋፍቶ የነበረ ሲሆን ግብዝነት የኅብረተሰቡን ሃይማኖታዊ መዋቅር አፍረክርኮት ነበር። የኮረብታዎቹ አናት ለሐሰት አማልክት በቆሙ መሠዊያዎች ተሸፍኖ ነበር። አንዳንዶቹ ነገሥታት ሳይቀሩ አረማዊ አምልኮዎችን አራምደዋል። ለምሳሌ አካዝ በተገዢዎቹ መካከል የነበረውን የጣዖት አምልኮ በቸልታ ከመመልከትም አልፎ ለከነዓናውያኑ አምላክ ለሞሎክ መሥዋዕት አድርጎ ‘ልጁን በእሳት በማሳለፍ’ ራሱም ጭምር የዚህ አምልኮ ተሳታፊ ሆኗል። * (2 ነገሥት 16:3, 4፤ 2 ዜና መዋዕል 28:3, 4) እንግዲህ ይህ ሁሉ የተፈጸመው ከይሖዋ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና በነበረው ሕዝብ መካከል ነበር!—ዘጸአት 19:5-8
8. (ሀ) ንጉሥ ዖዝያንና ኢዮአታም ምን ምሳሌ ትተዋል? ሕዝቡስ በእነሱ መንገድ ተመርቷልን? (ለ) ኢሳይያስ ዓመፀኛ በሆነው ሕዝብ መካከል ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው?
8 ጥቂት ገዥዎችን ጨምሮ በኢሳይያስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድ መሞከራቸው የሚያስመሰግን ነበር። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ‘በይሖዋ ፊት ቅን ነገር ያደረገው’ ንጉሥ ዖዝያን ነው። በእርሱ የግዛት ዘመን እንኳ ሕዝቡ “በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።” (2 ነገሥት 15:3, 4) ንጉሥ ኢዮአታምም ‘በይሖዋ ፊት ቅን ነገር አድርጓል።’ ይሁን እንጂ ‘ሕዝቡ ገና ይበድል ነበር።’ (2 ዜና መዋዕል 27:2) አዎን፣ ኢሳይያስ ትንቢታዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው በአብዛኛዎቹ ዓመታት የይሁዳ መንግሥት የነበረበት መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቡ ከነገሥታቶቻቸው የሚመጣውን ማንኛውንም በጎ ተጽዕኖ ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም። ለዚህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ የአምላክን መልእክት ማድረስ ቀላል ሥራ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ባለ ጊዜ ኢሳይያስ ቅንጣት አላመነታም። “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ብሏል።—ኢሳይያስ 6:8
የመዳን መልእክት
9. የኢሳይያስ የስሙ ትርጉም ምንድን ነው? ይህስ ከመጽሐፉ ጭብጥ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
9 የኢሳይያስ የስሙ ትርጉም “የይሖዋ ማዳን” ማለት ሲሆን የመልእክቱም ጭብጥ ይኸው ነው ለማለት ይቻላል። አንዳንዶቹ የኢሳይያስ ትንቢቶች የፍርድ መልእክት ያዘሉ መሆናቸው አይካድም። ያም ሆኖ በመጽሐፉ ውስጥ የጎላው የመዳን መልእክት ነው። ኢሳይያስ በተደጋጋሚ ጊዜ ይሖዋ በባቢሎን ምርኮ ያሉትን እስራኤላውያን እንዴት ነፃ እንደሚያወጣቸው እንዲሁም ቀሪዎቹ ወደ ጽዮን ተመልሰው ምድሪቱን የቀድሞ ውበቷን እንዲያላብሷት እንደሚያደርግ ተናግሯል። ኢሳይያስ ለእርሱ የተወደደች ስለነበረችው ኢየሩሳሌም ትንቢቶች ለመናገርና ለመጻፍ መብት በማግኘቱ እጅግ እንደተደሰተ ምንም አያጠራጥርም!
10, 11. (ሀ) የኢሳይያስ መጽሐፍ ዛሬ የእኛን ትኩረት የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የኢሳይያስ መጽሐፍ ትኩረታችን መሲሑ ላይ እንዲያርፍ የሚያደርገው እንዴት ነው?
10 ይሁን እንጂ እነዚህ የፍርድና የመዳን መልእክቶች ለእኛ ምን ዳንኤል 9:25፤ ዮሐንስ 12:41) ኢየሱስ የሚለው ስም ትርጉም “ይሖዋ ማዳን ነው” ማለት ስለሆነ ኢየሱስና ኢሳይያስ የሚሉት ስሞች ተመሳሳይ ትርጉም ሊኖራቸው የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው።
ትርጉም አላቸው? ደስ የሚለው ነገር ኢሳይያስ ትንቢት የተናገረው ለሁለቱ ነገድ የይሁዳ መንግሥት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መልእክቱ ለእኛ ዘመን ልዩ ትርጉም አለው። ኢሳይያስ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ለምድራችን እንዴት ታላላቅ በረከቶችን እንደሚያመጣ የሚጠቁም አስገራሚ መግለጫ ይሰጣል። በዚህ ረገድ አብዛኛው የኢሳይያስ መጽሐፍ የሚያተኩረው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በሚሆነውና በትንቢት በተነገረለት መሲሕ ላይ ነው። (11 እርግጥ ኢየሱስ የተወለደው ከኢሳይያስ ዘመን በኋላ ሰባት መቶ ዓመታት ቆይቶ ነው። ይሁንና በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች በጣም ዝርዝርና ትክክለኛ ከመሆናቸው የተነሣ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን የኖረ የዓይን ምሥክር የጻፋቸው ነው የሚመስሉት። ከዚህ በመነሳት አንድ ጽሑፍ የኢሳይያስ መጽሐፍ አንዳንድ ጊዜ “አምስተኛ ወንጌል” እየተባለ እንደሚጠራ ጠቅሷል። በመሆኑም ኢየሱስና ሐዋርያቱ የመሲሁን ማንነት በግልጽ ለማሳወቅ ከኢሳይያስ መጽሐፍ በጣም ብዙ ጊዜ መጥቀሳቸው ምንም አያስገርምም።
12. የኢሳይያስን መጽሐፍ በጉጉት ማጥናት ያለብን ለምንድን ነው?
12 ኢሳይያስ ‘ንጉሥ በጽድቅ ስለሚነግሥበትና’ መሳፍንት በፍትሕ ስለሚያስተዳድሩበት “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” አስገራሚ መግለጫ ሰጥቷል። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 65:17, 18፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በዚህ መንገድ የኢሳይያስ መጽሐፍ መንበረ ሥልጣኑን በጨበጠው ንጉሥ በመሲሑ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የሚተዳደረውን የአምላክ መንግሥት በተመለከተ አስደሳች ተስፋ ይሰጣል። በእያንዳንዱ ዕለት ‘የይሖዋን ማዳን’ በደስታ እየተጠባበቅን እንድንኖር ይህ እንዴት ያለ ግሩም ማበረታቻ ነው! (ኢሳይያስ 25:9፤ 40:28-31) እንግዲያው በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን አስደናቂ መልእክት በጉጉት እንመርምር። ይህንን ስናደርግ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለን ትምክህት ይበልጥ ይጠናከራል። ይሖዋ በእርግጥ የመዳናችን አምላክ ስለ መሆኑ ያለን ጽኑ እምነት እንዲያድግም ይረዳናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 የኢሳይያስ አባት የሆነው አሞጽና በዖዝያን የግዛት ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ትንቢት ይናገር የነበረው እንዲሁም በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን መጽሐፍ በስሙ የጻፈው አሞጽ ሊምታቱብን አይገባም።
^ አን.7 አንዳንዶች ‘በእሳት ማሳለፍ’ የሚለው አባባል የሚያመለክተው አንድን የመንጻት ሥርዓት ነው ይላሉ። ይሁንና ከጥቅሱ አገባብ መረዳት እንደሚቻለው ይህ ሐረግ የሚናገረው ቃል በቃል ስለቀረበ መሥዋዕት ነው። በከነዓናውያንና ከሃዲ በነበሩ እስራኤላውያን ዘንድ ልጆችን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ የተለመደ ነገር መሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም።—ዘዳግም 12:31፤ መዝሙር 106:37, 38
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ኢሳይያስ ማን ነበር?
የስሙ ትርጉም:- “የይሖዋ ማዳን ”
የቤተሰብ ሕይወቱ:- ባለትዳርና ቢያንስ የሁለት ወንዶች ልጆች አባት
የመኖሪያ ቦታው:- ኢየሩሳሌም
ያገለገለባቸው ዓመታት:- ከ778 ከዘአበ ገደማ አንስቶ ከ732 ከዘአበ በኋላ እስካለው ጊዜ ድረስ ከ46 ለማያንሱ ዓመታት
በእሱ ዘመን የነበሩ የይሁዳ ነገሥታት:- ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝ፣ ሕዝቅያስ
በእሱ ዘመን የነበሩ ነቢያት:- ሚክያስ፣ ሆሴዕ፣ ዖዴድ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢሳይያስና ሚስቱ የይሖዋን አምልኮ የቤተሰብ ሕይወታቸው ክፍል አድርገውት ነበር