በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መመሪያና ጥበቃ ለማግኘት በይሖዋ ታመኑ

መመሪያና ጥበቃ ለማግኘት በይሖዋ ታመኑ

ምዕራፍ አሥራ ስድስት

መመሪያና ጥበቃ ለማግኘት በይሖዋ ታመኑ

ኢሳይያስ 20:​1-6

1, 2. በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በአምላክ ሕዝብ ላይ ተጋርጦ የነበረው አደጋ ምንድን ነው? ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ ጥበቃ ለማግኘት የታመኑት በማን ነበር?

ቀደም ባሉት የዚህ መጽሐፍ ምዕራፎች ውስጥ እንደተገለጸው የአምላክ ሕዝብ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከባድ ማስፈራሪያ ተሰንዝሮበት ነበር። ደም የተጠሙት አሦራውያን በመንገዳቸው ላይ ያገኙትን ከተማ ሁሉ አንድ አንድ እያሉ እያወደሙ ስለነበር የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ደቡባዊው የይሁዳ መንግሥትም የጥቃት ዒላማ መሆኑ አይቀርም። የምድሪቱ ነዋሪዎች ከዚህ አደጋ ጥበቃ ለማግኘት ወደ ማን ዞር ይሉ ይሆን? ከይሖዋ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና የመሠረቱ በመሆናቸው መታመን ያለባቸው በእርሱ ነው። (ዘጸአት 19:​5, 6) ንጉሥ ዳዊት ያደረገው ይህንኑ ነበር። “እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬ መድኃኒቴ ነው” ሲል ተናግሯል። (2 ሳሙኤል 22:​2) ይሁንና ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበሩት ብዙዎቹ ይሖዋን እንደ አምባቸው አድርገው ሳይታመኑበት ቀርተዋል። እያንዣበበባቸው ከነበረው የአሦር የወረራ ስጋት ግብጽና ኢትዮጵያ ሊታደጓቸው እንደሚችሉ ተስፋ በማድረግ በእነዚህ ብሔራት ወደ መታመን አዘንብለው ነበር። በጣም ተሳስተዋል።

2 ይሖዋ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካኝነት ግብጽን ወይም ኢትዮጵያን መሸሸጊያ ለማድረግ መሞከር አደገኛ እንደሚሆን አስጠንቅቋል። ነቢዩ በመንፈስ አነሳሽነት የተናገራቸው ቃላት በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች በጣም አስፈላጊ ትምህርት ያዘለ ሲሆን ለእኛም ቢሆን በይሖዋ መታመንን በተመለከተ ትልቅ ትምህርት ይዞልናል።

የደም ምድር

3. አሦር ለወታደራዊ ኃይል ምን ዓይነት ቦታ ትሰጥ እንደነበር ግለጽ።

3 አሦራውያን በወታደራዊ ጥንካሬያቸው የሚታወቁ ነበሩ። ኤንሸንት ሲቲስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “ኃይልን ያመልካሉ። ጸሎታቸውንም የሚያቀርቡት ግዙፍ ለሆኑት የድንጋይ ምስሎች፤ ለአናብስትና ለጎሾች ሲሆን የእነዚህ ምስሎች ፈርጣማ እግሮች፣ የንሥር ክንፍና የሰው ጭንቅላት የኃይል፣ የድፍረትና የድል ተምሳሌት ተደርገው ይታዩ ነበር። የብሔሩ ዋና ተግባር ውጊያ ሲሆን ቀሳውስቱም ቀንደኛ የጦርነት ቆስቋሾች ነበሩ።” የመጽሐፍ ቅዱሱ ነቢይ ናሆም የአሦራውያን ዋና ከተማ የነበረችውን ነነዌን ‘የደም ከተማ’ ብሎ የጠራት ያለ ምክንያት አልነበረም።​—⁠ናሆም 3:​1

4. አሦራውያን በሌሎች ብሔራት ልብ ውስጥ ሽብር ይለቅቁ የነበረው እንዴት ነው?

4 የአሦራውያን የጦር ስልት የተለየ ዓይነት ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ነበር። በዚያ ዘመን የተሠሩ ውቅር ምስሎች አሦራውያን ተዋጊዎች ምርኮኞቻቸውን በአፍንጫቸው ወይም በከንፈራቸው ውስጥ መንጠቆ አስገብተው ሲነዷቸው ያሳያሉ። የአንዳንዶቹን ምርኮኞች ዓይን በጦር አጥፍተዋል። አንድ ተቀርጾ የተገኘ ጽሑፍ የአሦራውያን ሠራዊት የምርኮኞቹን የአካል ክፍል ቆራርጦ ከከተማዋ ውጭ አንድ የጭንቅላት ሌላ ደግሞ የእጅና እግር ክምር ስለሠራበት የጦር ውሎ ይተርካል። የምርኮኞቹ ልጆች በእሳት እንዲቃጠሉ ይደረግ ነበር። እንዲህ ያለው የአሦራውያን ጭካኔ በሌሎች ዘንድ የሚያሳድረው ፍርሃት ሠራዊታቸውን ለመግጠም የሚነሱትን ልብ ሁሉ በፍርሃት በማራድ አሦራውያኑ ለሚያገኙት ወታደራዊ ድል አስተዋጽኦ አድርጎ መሆን አለበት።

ከአዛጦን ጋር የተደረገ ውጊያ

5. በኢሳይያስ ዘመን የነበረው ኃያል የአሦር ንጉሥ ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ የሚናገረው ነገር ትክክለኛነት የተረጋገጠውስ እንዴት ነው?

5 በኢሳይያስ ዘመን በንጉሥ ሳርጎን ይመራ የነበረው የአሦር ግዛት ኃይሉ እጅግ ገንኖ ነበር። * ተቺዎች የዚህን ገዥ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ሌላ የትም ቦታ ተጠቅሶ ስላላገኙት ለብዙ ዓመታት ሕልውናውን ሲጠራጠሩ ኖረዋል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ አርኪኦሎጂስቶች የሳርጎንን ቤተ መንግሥት በቁፋሮ በማግኘታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛነት ተረጋግጧል።

6, 7. (ሀ) ሳርጎን በአዛጦን ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ትእዛዝ የሰጠበት ምክንያት ምን ሳይሆን አይቀርም? (ለ) የአዛጦን ድል መመታት የፍልስጥኤምን አጎራባች አገሮች የሚነካው እንዴት ነው?

6 ኢሳይያስ፣ ሳርጎን ካደረጋቸው ወታደራዊ ዘመቻዎች መካከል ስለ አንዱ በአጭሩ ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል:- ‘የአሦር ንጉሥ ሳርጎን ተርታንን ሰደደ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ አዛጦንን ወግቶ ያዛት።’ (ኢሳይያስ 20:​1) * ሳርጎን በፍልስጥኤማውያኑ የአዛጦን ከተማ ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ትእዛዝ ያስተላለፈው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ፍልስጥኤም የግብጽ አጋር ነች። ከዚህም ሌላ የዳጎን ቤተ መቅደስ መቀመጫ የሆነችው አዛጦን የምትገኘው ከግብጽ ተነስቶ በፍልስጤም በኩል በሚያልፈው በባሕር ዳርቻው አቅራቢያ ባለው ጎዳና ላይ ነበር። ከዚህ የተነሣ ከተማዋ የምትገኘው ቁልፍ ቦታ ላይ ነበር። ይህችን ከተማ መቆጣጠር ግብጽን ድል ለማድረግ መንገድ እንደሚጠርግ ትልቅ እርምጃ ሊታይ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የአሦራውያን መዛግብት እንደሚጠቁሙት የአዛጦን ንጉሥ የነበረው አዙራይ በአሦር ላይ ሴራ ጠንስሶ ነበር። በመሆኑም ሳርጎን ዓመፀኛውን ንጉሥ ከቦታው በማስወገድ ታናሽ ወንድሙን አሂሚታይን በዙፋኑ ላይ አስቀምጧል። ያም ሆኖ ግን ችግሩ አልተፈታም። ሌላ ዓመፅ በመፈንዳቱ ሳርጎን ጠንከር ያለ እርምጃ ወስዷል። በአዛጦን ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ትእዛዝ በማስተላለፉ ከተማዋን ከብበው ድል አደረጓት። ኢሳይያስ 20:​1 የሚጠቅሰው ይህንን ሳይሆን አይቀርም።

7 የአዛጦን ድል መመታት በአጎራባቾቿ በተለይም ደግሞ በይሁዳ ላይ የስጋት ደመና እንዲያጠላ የሚያደርግ ነበር። ይሖዋ ሕዝቡ ‘በሥጋ ክንድ’ ማለትም በግብጽ ወይም በስተደቡብ ባለችው በኢትዮጵያ ወደ መታመን እንደሚያዘነብሉ ያውቃል። ከዚህ የተነሣ ኢሳይያስ በተግባራዊ መግለጫ የተደገፈ አንድ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ እንዲያስተላልፍ ላከው።​—⁠2 ዜና መዋዕል 32:​7, 8

‘ራቁቱንና ባዶ እግሩን’

8. ኢሳይያስ በመንፈስ አነሳሽነት የሰጠው በድርጊት የተደገፈ ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?

8 ይሖዋ ኢሳይያስን “ሂድ፣ ማቅህን ከወገብህ አውጣ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ ” ብሎታል። ኢሳይያስ ይሖዋ ያለውን ያደርጋል። “እንዲህም አደረገ፣ ራቁቱንም ባዶ እግሩንም ሄደ።” (ኢሳይያስ 20:​2) ማቅ ብዙውን ጊዜ ነቢያት የሚለብሱት መናኛ ልብስ ሲሆን አንዳንዴ ይህን ልብስ የሚያደርጉት ከማስጠንቀቂያ መልእክት ጋር በተያያዘ ነው። አደጋ ሲመጣ ወይም አንድ ዓይነት አደጋ እንዳንዣበበ የሚገልጽ ወሬ በሚሰማበት ጊዜም ይለበስ ነበር። (2 ነገሥት 19:​2፤ መዝሙር 35:​13፤ ዳንኤል 9:​3) ኢሳይያስ ራቁቱን ሄዷል ሲባል ምንም ዓይነት ልብስ ሰውነቱ ላይ አልነበረውም ማለት ነውን? የግድ እንደዚያ ነው ማለት አይደለም። “ራቁት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ከፊል ሰውነትን መሸፈንን ወይም ብጣሽ ጨርቅ ብቻ ጣል አድርጎ መሄድንም ሊያመለክት ይችላል። (1 ሳሙኤል 19:​24የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ስለዚህ ኢሳይያስ የውጨኛውን መጎናጸፊያ አውልቆ በጊዜው የተለመደ የነበረውን እንደ ቁምጣ ያለውን የውስጥ ሱሪ ብቻ ለብሶ ሊሆን ይችላል። በአሦራውያን የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎች ላይ ወንድ ምርኮኞች ብዙውን ጊዜ የሚሳሉት እንደዚያ ተደርገው ነው።

9. የኢሳይያስ ድርጊት ያዘለው ትንቢታዊ ትርጉም ምንድን ነው?

9 ኢሳይያስ ያደረገው ያልተለመደ ነገር ምን ትርጉም እንዳለው ተገልጿል:- “እግዚአብሔርም አለ:- ባሪያዬ ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፣ እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብጽንና የኢትዮጵያን ምርኮ፣ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፣ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፣ ለግብጽ ጉስቁልና ይነዳቸዋል።” (ኢሳይያስ 20:​3, 4) አዎን፣ ብዙም ሳይቆይ ግብጽና ኢትዮጵያ በምርኮ ይወሰዳሉ። የሚተርፍ አይኖርም። ‘ጎበዛዝቱና ሽማግሌዎቹ’ ማለትም ሕፃናቱና አረጋውያኑ ሳይቀሩ ንብረታቸው ተገፍፎ በግዞት ይወሰዳሉ። ይሖዋ በዚህ አሰቃቂ የሆነ ሥዕላዊ መግለጫ አማካኝነት የይሁዳ ነዋሪዎች በግብጽና በኢትዮጵያ መታመናቸው ከንቱ እንደሆነ አስጠንቅቋል። የእነዚህ ብሔራት ውድቀት ‘ለራቁትነት’ ማለትም ለከፋ ውርደት ይዳርጋቸዋል!

ተስፋ መና ይቀራል፣ ውበት ይረግፋል

10, 11. (ሀ) ግብጽና ኢትዮጵያ አሦርን መቋቋም እንዳልቻሉ ስትመለከት ይሁዳ የምትሰጠው ምላሽ ምን ይሆናል? (ለ) የይሁዳ ነዋሪዎች በግብጽና በኢትዮጵያ ወደ መታመን የሚያዘነብሉት ለምን ሊሆን ይችላል?

10 ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ፣ ሕዝቡ መሸሸጊያ ይሆኑናል ብለው ተስፋ ያደረጉባቸው ግብጽና ኢትዮጵያ በአሦራውያን ፊት አቅመ ቢስ መሆናቸውን ሲያዩ ምን ምላሽ እንደሚሰጡ የሚጠቁም ትንቢታዊ መግለጫ ሰጥቷል። “እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም [“ከውበታቸውም፣” NW ] ከግብጽ የተነሣ ይፈራሉ ያፍሩማል። በዚያም ቀን በዚች ባሕር ዳርቻ የሚቀመጡ:- እነሆ፣ ከአሦር ንጉሥ እንድን ዘንድ ለእርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ እኛስ እንዴት እናመልጣለን? ይላሉ።”​—⁠ኢሳይያስ 20:​5, 6

11 ይሁዳ ከግብጽና ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ስትወዳደር እንዲሁ በባሕር ዳርቻ የምትገኝ አነስተኛ መሬት ብቻ ሆና ነው የምትታየው። ምናልባትም በዚህች ‘የባሕር ዳርቻ’ የሚኖሩት አንዳንዶቹ በግብጽ ውበት ማለትም አስገራሚ በሆኑት ፒራሚዶቿ፣ ጎላ ብለው በሚታዩት ቤተ መቅደሶቿ እንዲሁም የአትክልት ስፍራዋ፣ የጓሮ ተክልና ኩሬ ባላቸው ትላልቅ ቪላ ቤቶቿ ልባቸው ሳይማልል አይቀርም። ዕጹብ ድንቅ የሆነው የግብጽ የግንባታ ጥበብ ግብጽ የተረጋጋችና የማትበገር መስላ እንድትታይ ያደረጋት ይመስላል። በእርግጥም ይህች ምድር ጨርሳ ልትወድም አትችልም! አይሁዳውያኑ በኢትዮጵያ ቀስተኞች፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞችም ሳይማረኩ አልቀሩም።

12. ይሁዳ ልትታመን የሚገባት በማን ነው?

12 ኢሳይያስ ከሰጠው በድርጊት የተደገፈ ማስጠንቀቂያና ከይሖዋ የትንቢት ቃል አንጻር የአምላክ ሕዝብ ነን የሚሉና በግብጽና በኢትዮጵያ ወደ መታመን ዘወር ያሉ ሁሉ በጉዳዩ ላይ አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል። ትምክህታቸውን በምድራዊው ሰው ላይ ከማድረግ ይልቅ በይሖዋ ላይ ማድረጋቸው ምንኛ የተሻለ ይሆናል! (መዝሙር 25:​2፤ 40:​4) ከጊዜ በኋላ ይሁዳ በአሦር እጅ ብዙ መከራ አይታለች። በኋላም ቤተ መቅደሷና መዲናዋ በባቢሎን ሲወድም ተመልክታለች። ይሁንና ልክ እንደ አንድ ግዙፍ ዛፍ ጉቶ ‘አንድ አሥረኛ’ “የተቀደሰ ዘር” ቀርቶላታል። (ኢሳይያስ 6:​13) ጊዜው ሲደርስ የኢሳይያስ መልእክት በይሖዋ መታመናቸውን ለቀጠሉት ጥቂቶች እምነታቸውን በእጅጉ የሚያጠናክር ነገር ይሆናል!

በይሖዋ ታመኑ

13. ዛሬ እምነት ያላቸውም ሆኑ የማያምኑት ሰዎች በየትኞቹ ተጽእኖዎች ይነካሉ?

13 ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ መታመን ከንቱ ስለመሆኑ የተናገረው ማስጠንቀቂያ እንዲሁ ያለፈ ታሪክ ብቻ አይደለም። ለዘመናችንም ቢሆን ጠቃሚ ትምህርት አለው። ዛሬ የምንኖረው ‘አስጨናቂ በሆነ ዘመን’ ላይ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) የገንዘብ ችግር፣ ሥር የሰደደ ድህነት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የሕዝብ ዓመፅ እንዲሁም ቀላልና ከባድ ግጭቶች በአምላክ አገዛዝ ላይ በሚያላግጡት ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ይሖዋን በሚያመልኩት ላይ ጭምር ከባድ ችግር ይፈጥራሉ። አሁን ከእያንዳንዱ ሰው ፊት የሚደቀነው ጥያቄ ‘እርዳታ ለማግኘት ዘወር የምለው ወደ ማን ነው?’ የሚል ይሆናል።

14. በይሖዋ ብቻ መታመን የሚኖርብን ለምንድን ነው?

14 አንዳንዶች ዛሬ ሰብዓዊ ብልሃትንና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለሰው ልጅ ችግሮች እልባት መስጠት እንደሚቻል በሚናገሩ በገንዘብ ማግኛ ዘዴ የተካኑ ሰዎች፣ ፖለቲከኞችና ሳይንቲስቶች ቀልባቸው ይወሰድ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በግልጽ “በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 118:​9) የሰው ልጅ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የሚወጥነው ነገር ሁሉ ምንም ፋይዳ አይኖረውም። ኤርምያስ ምክንያቱን በግልጽ ሲያስቀምጥ እንዲህ ብሏል:- “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።”​—⁠ኤርምያስ 10:​23

15. ለተጨነቀው የሰው ዘር ብቸኛው ተስፋ ማን ነው?

15 እንግዲያውስ የአምላክ አገልጋዮች ጥንካሬና ጥበብ መስሎ በሚታየው ነገር ወይም በዚህ ዓለም ጥበብ ልባቸው እንዲወሰድ መፍቀድ አይኖርባቸውም። (መዝሙር 33:​10፤ 1 ቆሮንቶስ 3:​19, 20) ለተጨነቀው የሰው ልጅ ብቸኛው ተስፋ ፈጣሪያችን ይሖዋ ነው። በእርሱ የሚታመኑ ይድናሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት እንደጻፈው “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”​—⁠1 ዮሐንስ 2:​17

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ታሪክ ጸሐፊዎች ይህ ንጉሥ ዳግማዊ ሳርጎን ነው ይላሉ። “ቀዳማዊ ሳርጎን” ተብሎ ይጠራ የነበረው የአሦር ንጉሥ ሳይሆን ቀደም ብሎ የነበረ የባቢሎን ንጉሥ ነው።

^ አን.6 “ተርታን” የሰው ስም ሳይሆን የአሦራውያን ጦር ጠቅላይ አዛዥ የሚጠራበት ማዕረግ ነው። በንጉሠ ነገሥታዊው ግዛት ሁለተኛውን ከፍተኛ ሥልጣን የያዘ ሰው እንደነበር እሙን ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 209 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሦራውያን አንዳንዶቹን ምርኮኞቻቸውን ያሳውሩ ነበር

[በገጽ 213 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንዶች የሰው ልጅ ባስመዘገባቸው ውጤቶች ልባቸው ይማረክ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በይሖዋ መታመን የተሻለ ነው