በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ

በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ

ምዕራፍ አሥራ ሦስት

በመሲሑ ግዛት የሚገኝ መዳንና ደስታ

ኢሳይያስ 11:​1–12:​6

1. የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ በኢሳይያስ ዘመን የነበረበት መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ።

በኢሳይያስ ዘመን የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ የነበረበት መንፈሳዊ ሁኔታ መጥፎ ነበር። እንደ ዖዝያንና ኢዮአታም ባሉት የታመኑ ነገሥታት የግዛት ዘመን ሳይቀር ከሕዝቡ መካከል በኮረብታ መስገጃዎች አምልኮ የሚያካሂዱት ሰዎች ቁጥር ጥቂት አልነበረም። (2 ነገሥት 15:​1-4, 34, 35፤ 2 ዜና መዋዕል 26:​1, 4) ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ከበኣል አምልኮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ከምድሪቱ ማጽዳት አስፈልጎት ነበር። (2 ዜና መዋዕል 31:​1) ይሖዋ ሕዝቡ ወደ እርሱ እንዲመለስ አጥብቆ ማሳሰቡና ቅጣት እንደሚያገኛቸው ማስጠንቀቁ ምንም አያስገርምም!

2, 3. ይሖዋ ታማኝነት በጠፋበት ጊዜ እርሱን ለማገልገል ለሚፈልጉ ሁሉ የሚሰጠው ማበረታቻ ምንድን ነው?

2 ያም ሆኖ ግን ሁሉም የለየላቸው ዓመፀኞች ነበሩ ማለት አይደለም። ይሖዋ የታመኑ ነቢያት ነበሩት። እነርሱን የሚያዳምጡም አንዳንድ አይሁዳውያን እንደ ነበሩ እሙን ነው። ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች የሚነግራቸው የሚያጽናና ቃል አለ። ነቢዩ ኢሳይያስ በአሦራውያን ወረራ ወቅት ይሁዳ ስለሚደርስባት አስከፊ ብዝበዛ ከገለጸ በኋላ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ድንቅ ክፍሎች መካከል አንዱ የሆነውንና በመሲሑ ግዛት ሥር ስለሚገኙት በረከቶች የሚገልጸውን ክፍል በመንፈስ አነሳሽነት ጽፏል። * ከበረከቶቹ መካከል ጥቂቶቹ አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ በተመለሱ ጊዜ በጥቂቱ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ይሁን እንጂ ትንቢቱ በአጠቃላይ ዛሬ የላቀ ፍጻሜውን ያገኛል። ኢሳይያስና ሌሎች በእርሱ ዘመን የነበሩ የታመኑ አይሁዳውያን እነዚህን በረከቶች በዓይናቸው ለማየት እንዳልታደሉ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች እንደሚፈጸሙ በእምነት ተጠባብቀዋል። ወደፊት ደግሞ ከትንሣኤ በኋላ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ሲፈጸሙ ይመለከታሉ።​—⁠ዕብራውያን 11:​35

3 ዛሬ ያሉትም የይሖዋ ሕዝቦች ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። በፍጥነት እያዘቀጠ በመሄድ ላይ ያለው የዓለም የሥነ ምግባር ደረጃ፣ በመንግሥቱ መልእክት ላይ የሚሰነዘረው ጠንካራ ተቃውሞ እንዲሁም የግል ድክመቶች ሁሉንም ይፈታተኗቸዋል። ኢሳይያስ ስለ መሲሑና ስለ ግዛቱ የተናገረው ድንቅ ነገር የአምላክን ሕዝብ ሊያበረታና እንዲህ ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲወጡ ሊያግዛቸው ይችላል።

መሲሕ​—⁠ብቃት ያለው መሪ

4, 5. ኢሳይያስ የመሲሑን መምጣት በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል? ማቴዎስ ጠቅሶ የተናገረው የትኞቹን የኢሳይያስ ቃላት ነው?

4 ከኢሳይያስ ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ሌሎች ዕብራውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ስለ መሲሑ ማለትም ይሖዋ ወደ እስራኤል ስለሚልከው እውነተኛ መሪ መምጣት ተናግረው ነበር። (ዘፍጥረት 49:​10፤ ዘዳግም 18:​18፤ መዝሙር 118:​22, 26) አሁን ደግሞ ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ይገልጻል። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ ከሥሩም ቁጥቋጥ ያፈራል። ” (ኢሳይያስ 11:​1ከ⁠መዝሙር 132:​11 ጋር አወዳድር።) “በትር” እና “ቁጥቋጥ” የሚሉት ሁለቱም መግለጫዎች መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በዘይት በተቀባው በእሴይ ልጅ በዳዊት በኩል የሚመጣ የእሴይ ዘር እንደሆነ የሚያመለክቱ ናቸው። (1 ሳሙኤል 16:​13፤ ኤርምያስ 23:​5፤ ራእይ 22:​16) እውነተኛው መሲሕ ማለትም ከዳዊት ቤት የሚወጣው ይህ “ቁጥቋጥ” ሲመጣ መልካም ፍሬዎችን ያፈራል።

5 ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ኢየሱስ ነው። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማቴዎስ ኢየሱስ “ናዝራዊ” ተብሎ መጠራቱ የነቢያት ቃል ፍጻሜ ነው ብሎ ሲጽፍ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢሳይያስ 11:​1ን መጥቀሱ ነበር። ኢየሱስ ያደገው በናዝሬት ከተማ በመሆኑ ናዝራዊ ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ስም በ⁠ኢሳይያስ 11:​1 ላይ ከተጠቀሰው “ቁጥቋጥ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር የሚዛመድ ነው። *​—⁠ማቴዎስ 2:​23የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፤ ሉቃስ 2:​39, 40

6. በትንቢት የተነገረው መሲሑ ምን ዓይነት ገዥ እንደሚሆን ነው?

6 መሲሑ ምን ዓይነት ገዥ ይወጣው ይሆን? አሥሩን ነገድ ሰሜናዊ የእስራኤል መንግሥት እንዳጠፉት አሦራውያን ጨካኝና ያሻውን የሚያደርግ ንጉሥ ይሆናልን? በፍጹም አይሆንም። መሲሑን በተመለከተ ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል። ” (ኢሳይያስ 11:​2, 3ሀ) መሲሑ የተቀባው በዘይት ሳይሆን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው። ይህ የሆነው ኢየሱስ ሲጠመቅ ዮሐንስ እያየ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በእርግብ አምሳል በወረደበት ጊዜ ነበር። (ሉቃስ 3:​22) ኢየሱስ የይሖዋ መንፈስ ‘አርፎበታል።’ በጥበብ፣ በማስተዋል፣ በምክር፣ በኃይልና በእውቀት ያከናወናቸው ነገሮች ይህንኑ የሚያንጸባርቁ ናቸው። እነዚህ አንድ ገዥ ሊኖረው የሚገቡ እንዴት ያሉ ግሩም ባሕርያት ናቸው!

7. ኢየሱስ ለታመኑ አገልጋዮቹ የሰጠው ተስፋ ምንድን ነው?

7 የኢየሱስ ተከታዮችም መንፈስ ቅዱስ ሊቀበሉ ይችላሉ። ኢየሱስ በአንድ ወቅት ሲያስተምር እንዲህ ብሏል:- “እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” (ሉቃስ 11:​13) በመሆኑም አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት አይኖርብንም። እንዲሁም እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን መልካም ፍሬዎቹን ከመኮትኮት መቆጠብ አይገባንም። (ገላትያ 5:​22, 23) ይሖዋ የኢየሱስ ተከታዮች የሚገጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሳካ መንገድ እንዲወጡ ለመርዳት ሲል ‘ላይኛይቱን ጥበብ’ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና እንደሚሰማ ቃል ገብቷል።​—⁠ያዕቆብ 1:​5፤ 3:​17

8. ኢየሱስ ይሖዋን በመፍራት ደስ የሚለው እንዴት ነው?

8 በመሲሑ ላይ የሚንጸባረቀው የይሖዋ ፍርሃት ምንድን ነው? ኢየሱስ የአምላክን ኩነኔ በመፍራት ይሸበራል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ መሲሑ ለአምላክ ያለው ፍርሃት በፍቅርና በአክብሮት ላይ የተመሠረተ ነው። አምላክን የሚፈራ አንድ ሰው እንደ ኢየሱስ ሁልጊዜ አምላክን “ደስ የሚያሰኘውን” ለማድረግ ይጥራል። (ዮሐንስ 8:​29) ኢየሱስ በየዕለቱ ጤናማ በሆነ መንገድ ይሖዋን በመፍራት ከመመላለስ የበለጠ ደስታ እንደሌለ በቃልም ሆነ በድርጊት አስተምሯል።

ጻድቅና መሐሪ የሆነ ፈራጅ

9. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የመፍረድ ሥልጣን ላላቸው ወንዶች ኢየሱስ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

9 ኢሳይያስ ስለ መሲሑ ባሕርይ ተጨማሪ ነገርም ተንብዮአል:- “ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፣ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም።” (ኢሳይያስ 11:​3ለ) ችሎት ፊት መቅረብ ቢኖርብህና እንዲህ ዓይነት ዳኛ ብታገኝ ደስ አይልህም? መሲሑ የሰው ዘር ሁሉ ፈራጅ ሆኖ ሲሠራ በሐሰት የመከራከሪያ ነጥቦች፣ ችሎትን ለማደናገር በሚሰነዘሩ መሠሪ ሐሳቦች፣ በወሬ ወይም እንደ ሀብት ባሉ ውጫዊ ነገሮች አይታለልም። ማታለያዎችን ለይቶ ያውቃል እንዲሁም እምብዛም ከማይማርኩ ውጫዊ ሁኔታዎች በስተጀርባ ያለውን ይመለከታል። ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ማለትም ‘ስውር የሆነውን ማንነት’ ያስተውላል። (1 ጴጥሮስ 3:​4የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ይህ ወደር የማይገኝለት የኢየሱስ ምሳሌ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የመፍረድ ሥልጣን ላላቸው ሁሉ ግሩም አርዓያ ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​1-4

10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ እርማት የሚሰጠው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ለክፉዎች የሚሰጠው ፍርድ ምንድን ነው?

10 እነዚህ የመሲሑ ድንቅ ባሕርያት በሚያስተላልፈው የፍርድ ውሳኔ ላይ ተጽእኖ የሚኖራቸው እንዴት ነው? ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ያስረዳል:- “ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ በአፉም በትር ምድርን ይመታል፣ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፣ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል። ”​—⁠ኢሳይያስ 11:​4, 5

11 ኢየሱስ ተከታዮቹ እርማት ባስፈለጋቸው ጊዜ እርማቱን የሚሰጠው ሙሉ ጥቅም ማግኘት በሚያስችላቸው መንገድ ነበር። ይህም ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ክፋትን ልማዳቸው ያደረጉ ሰዎች ጠንከር ያለ ፍርድ እንደሚያገኛቸው ሊጠብቁ ይችላሉ። አምላክ ይህን የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍርድ በሚያመጣበት ጊዜ መሲሑ በክፉዎች ሁሉ ላይ የጥፋት ፍርድ በማስተላለፍ ከአፉ በሚወጣው የማይሻር ቃሉ “ምድርን ይመታል።” (መዝሙር 2:​9፤ ከ⁠ራእይ 19:​15 ጋር አወዳድር።) በመጨረሻ የሰውን ዘር ሰላም የሚያደፈርስ ኃጢአተኛ ፈጽሞ አይኖርም። (መዝሙር 37:​10, 11) ጽድቅን በወገቡ የታጠቀውና ታማኝነትን የጎኑ መቀነት ያደረገው ኢየሱስ ይህን ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል አለው።​—⁠መዝሙር 45:​3-7

በምድር ላይ የሚኖረው ለውጥ

12. አንድ አይሁዳዊ ከባቢሎን ወደ ተስፋይቱ ምድር መመለስን ሲያስብ ምን ነገሮች ወደ አእምሮው ሊመጡ ይችሉ ይሆናል?

12 እስቲ አሁን ደግሞ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ ቂሮስ ያወጣውን ድንጋጌ ስለሰማ አንድ እስራኤላዊ አስብ። በባቢሎን የነበረውን የተደላደለ ኑሮ ትቶ ወደ ትውልድ አገሩ ለመሄድ ረጅሙን ጉዞ ይያያዘው ይሆን? እስራኤላውያን ከምድሪቱ ርቀው በነበሩባቸው 70 ዓመታት ባዶውን የቀረው መሬት አረም ወርሶታል። እነዚህ ቦታዎች የቀበሮ፣ የነብር፣ የአንበሳና የድብ መፈንጫ ሆነዋል። እባቦችም መኖሪያቸው አድርገውታል። ወደ አገራቸው የሚመለሱት አይሁዳውያን ሕይወት ወተት፣ የሱፍ ፀጉርና ሥጋ በሚሰጧቸው የቤት እንስሳት እንዲሁም ጠምደው በሚያርሱበት በሬ ላይ የተመካ መሆን ሊኖርበት ነው። እነዚህ ከብቶች ለአራዊት ሲሳይ ይሆኑባቸው ይሆን? ሕፃናትስ በእባብ ይነደፉ ይሆን? በመንገድ ላይ ከሸመቁ ወንበዴዎች የሚገጥማቸው አደጋስ?

13. (ሀ) ኢሳይያስ ምን አስደሳች ነገር ገልጿል? (ለ) ኢሳይያስ የተናገረለት ሰላም አራዊት ከሚፈጥሩት ስጋት እፎይታ በማግኘት ብቻ እንደማይወሰን እንዴት እናውቃለን?

13 ከዚህ ቀጥሎ አምላክ በምድሪቱ የሚያሰፍነውን ሁኔታ በተመለከተ ኢሳይያስ እጅግ አስደሳች የሆነ መግለጫ ይሰጣል። እንዲህ ብሏል:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፣ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፣ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና። ” (ኢሳይያስ 11:​6-9) እነዚህ ቃላት ልብ የሚነኩ አይደሉምን? እዚህ ላይ የተገለጸው ሰላም ይሖዋን ከማወቅ የሚገኝ እንደሆነ ልብ በል። እንግዲያው አራዊት ከሚፈጥሩት ስጋት እረፍት ከማግኘት የበለጠ ነገርን የሚጨምር ይሆናል። ከይሖዋ የሚገኘው እውቀት እንስሳትን ሊለውጣቸው አይችልም። ሰዎችን ግን ይለውጣል። እስራኤላውያኑ ወደ ትውልድ አገራቸው ሲጓዙም ሆነ ተመልሳ በምትቋቋመው ምድራቸው ሲኖሩ ከአራዊት ወይም እንደ አውሬ ካሉ ሰዎች ጥቃት ይደርስብናል ብለው የሚሰጉበት ምክንያት አልነበረም።​—⁠ዕዝራ 8:​21, 22፤ ኢሳይያስ 35:​8-10፤ 65:​25

14. የ⁠ኢሳይያስ 11:​6-9 የላቀ ፍጻሜ ምንድን ነው?

14 ይሁን እንጂ ይህ ትንቢት ከዚህ የላቀ ፍጻሜ አለው። በ1914 መሲሑ ኢየሱስ በሰማያዊው የጽዮን ተራራ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። በ1919 ‘የአምላክ እስራኤል’ ቀሪዎች ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ወጥተው እውነተኛውን አምልኮ መልሶ በማቋቋሙ ሥራ ተካፋይ ሆነዋል። (ገላትያ 6:​16) በመሆኑም ኢሳይያስ ስለ ገነት የተናገረው ትንቢት ዘመናዊ ፍጻሜውን ማግኘት የሚችልበት በር ተከፍቷል። “ትክክለኛ እውቀት” ማለትም ከይሖዋ የሚገኘው እውቀት የሰዎችን ባሕርይ ለውጧል። (ቆላስይስ 3:​9, 10 NW ) ቀደም ሲል ዓመፀኛ የነበሩ ሰዎች ሰላማዊ ሆነዋል። (ሮሜ 12:​2፤ ኤፌሶን 4:​17-24) የኢሳይያስ ትንቢት ቁጥራቸው በፍጥነት እያደገ የሚሄደውን ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች የሚጠቀልል ሆኖ በመገኘቱ እነዚህ ክንውኖች በዛሬው ጊዜ ያሉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት የሚነኩ ሆነዋል። (መዝሙር 37:​29፤ ኢሳይያስ 60:​22) እነዚህ ሰዎች ምድር ልክ በመጀመሪያው የአምላክ ዓላማ መሠረት የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት የሚኖርባት ገነት የምትሆንበትን ጊዜ በናፍቆት መጠባበቅን ተምረዋል።​—⁠ማቴዎስ 6:​9, 10፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

15. የ⁠ኢሳይያስ ቃላት በአዲሱ ዓለም ውስጥ ቃል በቃል ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ ብለን መጠበቅ እንችላለን? አብራራ።

15 ተመልሳ በምትቋቋመው በዚህች ገነት ውስጥ የኢሳይያስ ትንቢት ተጨማሪና ምናልባት ቃል በቃል የሚከናወን ፍጻሜ ይኖረው ይሆን? እንደዚያ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። ትንቢቱ በመሲሐዊው አገዛዝ ሥር ለሚኖሩት ሰዎች የሚሰጠው ማረጋገጫ ወደ አገራቸው ለተመለሱት አይሁዳውያን ከሰጠው የተለየ አይደለም። እነርሱም ሆኑ ልጆቻቸው ከማንኛውም ምንጭ ማለትም ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ጥቃት ይደርስብናል የሚል ስጋት አይኖርባቸውም። በመሲሑ ንጉሣዊ አስተዳደር ሥር መላው የምድር ነዋሪ አዳምና ሔዋን በኤድን ገነት የነበራቸው ዓይነት ሰላማዊ ሁኔታ ያገኛል። እርግጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በኤድን የነበረው ሕይወት ምን ይመስል እንደነበርም ሆነ ወደፊት በምትመጣው ገነት ውስጥ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖር ዝርዝር መግለጫ አይሰጡም። ይሁንና ጥበበኛና አፍቃሪ ንጉሥ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አስተዳደር ሥር ሁሉም ነገር መሆን እንዳለበት ሆኖ እንደሚገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

በመሲሑ አማካኝነት ተመልሶ የተቋቋመው ንጹሕ አምልኮ

16. በ537 ከዘአበ ለአምላክ ሕዝቦች እንደ ምልክት የሆነላቸው ምን ነበር?

16 ለመጀመሪያ ጊዜ በንጹሕ አምልኮ ላይ ጥቃት የተሰነዘረው ሰይጣን በተሳካ ሁኔታ አዳምና ሔዋንን ኤድን ገነት ውስጥ በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ ባነሳሳበት ጊዜ ነው። እስከዛሬም ድረስ ሰይጣን የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ከአምላክ የማራቅ ግቡን ገፍቶበታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ከምድር ገጽ እንዲጠፋ በፍጹም አይፈቅድም። ይህ ከስሙ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። ደግሞም እርሱን ስለሚያገለግሉት ሰዎች ያስባል። ከዚህ የተነሳ በኢሳይያስ በኩል አንድ ትልቅ ተስፋ ሰጥቷል:- “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል። ” (ኢሳይያስ 11:​10) ዳዊት የአገሪቱ መዲና አድርጓት የነበረችው ኢየሩሳሌም በ537 ከዘአበ የተበታተኑት አይሁዳውያን ታማኝ ቀሪዎች ተመልሰው ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተሰባሰቡባት ምልክት ሆናለች።

17. ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲሁም በዚህ በእኛ ጊዜ ‘አሕዛብን ለመግዛት የተነሣው’ እንዴት ነው?

17 ይሁን እንጂ ትንቢቱ ከዚህ የበለጠ ትርጉም አለው። ቀደም ሲልም እንደተገለጸው ይህ ትንቢት ከአሕዛብ ሁሉ ለተውጣጡ ሰዎች እውነተኛ አለቃ ስለሚሆነው ስለ መሲሑ አገዛዝ የሚጠቁም ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በእርሱ ዘመን አሕዛብ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቦታ እንደሚኖራቸው ለማመልከት ከሰፕቱጀንት ትርጉም ኢሳይያስ 11:​10ን በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኢሳይያስ:- የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ ይላል።” (ሮሜ 15:​12) ይሁን እንጂ ትንቢቱ በዚህ ብቻ አይወሰንም። በዘመናችንም ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች የመሲሑን ቅቡዓን ወንድሞች በመደገፍ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንደሚያሳዩ የሚያረጋግጥ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 61:​5-9፤ ማቴዎስ 25:​31-40

18. በዘመናችን ኢየሱስ እንደ ምልክት የሆነው እንዴት ነው?

18 ትንቢቱ በዚህ ዘመን በሚኖረው ፍጻሜ ውስጥ “በዚያም ቀን” ሲል ኢሳይያስ የተናገረለት ጊዜ የጀመረው መሲሑ የአምላክ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ ዙፋን ላይ በተቀመጠበት በ1914 ነው። (ሉቃስ 21:​10፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ ራእይ 12:​10) ከዚያ ጊዜ ወዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመንፈሳዊ እስራኤልና የጽድቅ መስተዳድር እንዲሰፍን ለሚናፍቁ አሕዛብ ሁሉ ግልጽ ምልክት ሆኗል። ኢየሱስ አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረው የመንግሥቱ ምሥራች በመሲሑ አመራር ለሁሉም ብሔራት ሲዳረስ ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:​14፤ ማርቆስ 13:​10) ይህ ምሥራች ያስገኘው ውጤት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ . . . ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ራሳቸውን ለመሲሑ በማስገዛት ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር በንጹሕ አምልኮ እየተባበሩ ነው። (ራእይ 7:​9) ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በይሖዋ መንፈሳዊ “የጸሎት ቤት” ከቅቡዓኑ ጋር ለመተባበር መጉረፋቸው ለመሲሑ ‘ማረፊያ’ ማለትም ለአምላክ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ክብር የሚጨምር ነው።​—⁠ኢሳይያስ 56:​7፤ ሐጌ 2:​7

ይሖዋን የሚያገለግል አንድነት ያለው ሕዝብ

19. ይሖዋ በምድር ዙሪያ ተበታትነው የነበሩትን የሕዝቡን ቀሪዎች መልሶ የሰበሰበባቸው ሁለት አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?

19 ቀጥሎ ደግሞ ኢሳይያስ እስራኤላውያን ኃያል በሆነ ጠላታቸው እጅ ወድቀው በነበረበት አንድ ወቅት ይሖዋ ነፃ እንዳወጣቸው አስታውሷቸዋል። ይሖዋ ብሔሩን ከግብጽ ባርነት ነፃ ያወጣበት ይህ ታሪክ ከታመኑ አይሁዳውያን ልብ ውስጥ ምን ጊዜም የማይጠፋ ነው። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ የቀረውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦርና ከግብጽ፣ ከጳትሮስና ከኢትዮጵያ፣ ከኤላምና ከሰናዖር ከሐማትም፣ ከባሕርም ደሴቶች ይመልስ ዘንድ ጌታ እንደ ገና እጁን ይገልጣል። ለአሕዛብም ምልክትን ያቆማል፣ ከእስራኤልም የተጣሉትን ይሰበስባል፣ ከይሁዳም የተበተኑትን ከአራቱ የምድር ማዕዘኖች ያከማቻል። ” (ኢሳይያስ 11:​11, 12) ይሖዋ የታመኑ የእስራኤልና የይሁዳ ቀሪዎችን በእጁ ደግፎ ያወጣቸው ያህል ከተበታተኑባቸው አገሮች ሰብስቦ በሰላም ወደ አገራቸው ይመልሳቸዋል። ይህ ትንቢት በ537 ከዘአበ በጥቂቱ ፍጻሜውን ያገኛል። ይሁንና ዋነኛ ፍጻሜው ምንኛ ታላቅ ይሆናል! በ1914 ይሖዋ በዙፋን ላይ የተቀመጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን ‘ለአሕዛብ ምልክት’ አድርጎ አስነስቶታል። ከ1919 ጀምሮ ‘የአምላክ እስራኤል’ ቀሪዎች በአምላክ መንግሥት ሥር ሆነው በንጹሕ አምልኮ ለመካፈል በጉጉት ወደዚህ ምልክት ጎርፈዋል። ይህ ልዩ የሆነ መንፈሳዊ ብሔር “ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ” የተውጣጣ ነው።​—⁠ራእይ 5:​9

20. የአምላክ ሕዝብ ከባቢሎን ሲመለስ ምን ዓይነት አንድነት ይኖረዋል?

20 አሁን ደግሞ ኢሳይያስ ተመልሶ ስለተቋቋመው ብሔር አንድነት መግለጫ ይሰጣል። ሰሜናዊውን መንግሥት ኤፍሬም ደቡባዊውን ደግሞ ይሁዳ በሚል ስያሜ በመጥራት እንዲህ ይላል:- “የኤፍሬምም ምቀኝነት ይርቃል፣ ይሁዳንም የሚያስጨንቁ ይጠፋሉ፤ ኤፍሬምም በይሁዳ አይቀናም፣ ይሁዳም ኤፍሬምን አያስጨንቅም። በምዕራብም በኩል በፍልስጥኤማውያን ጫንቃ ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፣ የምሥራቅንም ልጆች በአንድነት ይበዘብዛሉ፤ በኤዶምያስና በሞዓብም ላይ እጃቸውን ይዘረጋሉ፣ የአሞንም ልጆች ለእነርሱ ይታዘዛሉ። ” (ኢሳይያስ 11:​13, 14) አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ሲመለሱ ለሁለት የተከፈለ ብሔር መሆናቸው ያከትማል። የሁሉም የእስራኤል ነገድ አባላት በአንድነት ወደ ምድራቸው ይመለሳሉ። (ዕዝራ 6:​17) ከዚህ በኋላ በመካከላቸው ቅሬታም ሆነ ጥላቻ አይኖርም። ኅብረት ያለው አንድ ሕዝብ በመሆን በዙሪያቸው ባሉት ብሔራት መካከል ያሉ ጠላቶቻቸውን ድል ይነሣሉ።

21. ዛሬ የአምላክ ሕዝብ ያለው አንድነት ልዩ የሆነው እንዴት ነው?

21 ከዚህ ይበልጥ አስገራሚ የሆነው ግን ‘የአምላክ እስራኤል’ ያለው አንድነት ነው። አሥራ ሁለቱ የመንፈሳዊ እስራኤል ምሳሌያዊ ነገዶች ወደ 2, 000 ለሚጠጉ ዓመታት ለአምላክ እንዲሁም ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ባላቸው ፍቅር ላይ በተመሠረተ አንድነት ተሳስረው ኖረዋል። (ቆላስይስ 3:​14፤ ራእይ 7:​4-8) ዛሬ መንፈሳዊ እስራኤላውያንም ሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች በጠቅላላ በመሲሐዊው አገዛዝ ሥር በሌሎች የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የማይታየውን ሰላምና ዓለም አቀፍ አንድነት አግኝተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ሰይጣን በአምልኳቸው ውስጥ እጁን ለማስገባት የሚያደርገውን ጥረት ለመከላከል አንድ መንፈሳዊ ግንባር ፈጥረዋል። ኢየሱስ ለአሕዛብ ሁሉ ስለ መሲሐዊው መንግሥት እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው ይፈጽማሉ።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

እንቅፋቶቹ ይወገዳሉ

22. ይሖዋ ‘የግብጻውያንን የባሕር ወሽመጥ የሚቆርጠው’ እና ‘እጁን በወንዙ ላይ የሚያወዛውዘው’ እንዴት ነው?

22 ለእስራኤላውያኑ ከምርኮ መመለስ ቃል በቃልም ይሁን በምሳሌያዊ መንገድ እንቅፋት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች ነበሩ። እነዚህን እንቅፋቶች ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ይሆን? ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም የግብጽን ባሕር [“ወሽመጥ፣” NW ] ያጠፋል፤ በትኩሱም ነፋስ እጁን በወንዙ ላይ ያነሣል፣ ሰባት ፈሳሾችንም አድርጎ ይመታዋል፣ ሰዎችም በጫማቸው እንዲሻገሩ ያደርጋቸዋል። ” (ኢሳይያስ 11:​15) ሕዝቦቹ እንዳይመለሱ እንቅፋት የሆኑትን ነገሮች ሁሉ የሚያስወግድላቸው ይሖዋ ራሱ ነው። እንደ ቀይ ባሕር ወሽመጥ (የስዊዝ ባሕረ ገብ ምድር) ወይም ለመሻገር እንደማይደፈረው እንደ ትልቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ያለው ከባድ ችግር እንኳ ሳይቀር ስለሚወገድ ሰዎች ጫማቸውን ሳያወልቁ እነዚህን ውኃዎች መሻገር የቻሉ ያህል ይሆናል!

23. ‘ከአሦር ጎዳና ይሆንላቸዋል’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

23 በሙሴ ዘመን ይሖዋ እስራኤላውያን ከግብጽ አምልጠው ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያቀኑበትን መንገድ አዘጋጅቶላቸው ነበር። አሁንም ከዚያ ጋር የሚመሳሰል ነገር ያደርጋል:- “ከግብጽም በወጣ ጊዜ ለእስራኤል እንደ ነበረ፣ ለቀረው ለሕዝቡ ቅሬታ ከአሦር ጐዳና ይሆናል።” (ኢሳይያስ 11:​16) ይሖዋ ከግዞት ተመላሾቹን ከተያዙበት አገር እስከ ትውልድ አገራቸው ድረስ ስለሚመራቸው በአውራ ጎዳና ላይ የሄዱ ያህል ነው። ተቃዋሚዎች ሊያስቆሟቸው ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ አምላካቸው ይሖዋ ከእነርሱ ጋር ይሆናል። ዛሬም እንዲሁ ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ጓደኞቻቸው ጠንካራ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም በድፍረት ወደፊት ይገፋሉ! እነርሱ ከዘመናዊው አሦር ማለትም ከሰይጣን ዓለም ነፃ ወጥተው ሌሎችም እንዲወጡ ይረዳሉ። ንጹህ አምልኮ ድል እንደሚያደርግና እንደሚያብብ ያውቃሉ። ይህ የአምላክ እንጂ የሰው ሥራ አይደለም።

የመሲሑ ተገዢዎች የሚያገኙት ወሰን የሌለው ደስታ!

24, 25. የይሖዋ ሕዝብ የሚያሰማው የውዳሴና የምስጋና ድምፅ ምንድን ነው?

24 የይሖዋ ቃል በመፈጸሙ ሕዝቡ የሚሰማውን ደስታ ኢሳይያስ ውብ በሆነ መንገድ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በዚያም ቀን:- አቤቱ፣ ተቈጥተኸኛልና፣ ቁጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፣ አጽናንተኸኛልምና አመሰግንሃለሁ . . . ትላለህ።” (ኢሳይያስ 12:​1, 2 ) ይሖዋ አስቸጋሪ በሆነው ሕዝቡ ላይ የሚወስደው የቅጣት እርምጃ ጠንከር ያለ ነው። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ከእርሱ ጋር ያለውን ዝምድና የመጠገንና ንጹሕ አምልኮን መልሶ የማቋቋም ዓላማውን ከዳር ያደርሳል። ይሖዋ የታመኑትን አምላኪዎቹን መጨረሻ ላይ እንደሚያድናቸው ቃል ገብቷል። አድናቆታቸውን መግለጻቸው ምንም አያስገርምም!

25 ተመልሰው የተቋቋሙት እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ያላቸው ትምክህት በከፍተኛ ደረጃ በመጠናከሩ እንዲህ ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል:- “እነሆ፣ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር [“ያህ ይሖዋ፣” NW ] ኃይሌና ዝማሬዬ [“ብርታቴ፣” NW ] ነውና፣ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ። ውኃውንም ከመድኃኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ። ” (ኢሳይያስ 12:​2, 3) ሰፕቱጀንት ትርጉም ቁጥር 2 ላይ የሚጠቀመው “ውዳሴ” የሚል ቃል ነው። አምላኪዎቹ ‘ከያህ ይሖዋ’ ስላገኙት መዳን ከፍ ያለ የውዳሴ መዝሙር ያሰማሉ። “ያህ” የሚለው የይሖዋ ስም አኅጽሮታዊ መጠሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከፍተኛ የውዳሴና የአመስጋኝነትን ስሜት ለመግለጽ ተሠርቶበታል። “ያህ ይሖዋ” የሚለውን መግለጫ መጠቀሙ ማለትም መለኮታዊውን ስም በሁለት መልኩ ደግሞ መጥራቱ ለአምላክ የሚቀርበውን ውዳሴ መጠን ከፍ የሚያደርግ ነው።

26. ዛሬ የአምላክን ሥራ ለአሕዛብ የሚያሳውቁት እነማን ናቸው?

26 የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች ያገኙትን ደስታ ለራሳቸው ብቻ ይዘው መቀመጥ አይችሉም። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይተነብያል:- “በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ:- እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ። ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ። ” (ኢሳይያስ 12:​4, 5) ከ1919 ወዲህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻቸውን ሆነው ‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራቸውን የእርሱን በጎነት ሲናገሩ’ የቆዩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ ‘የሌሎች በጎች’ ጓደኞቻቸው በዚህ ሥራ ተባብረዋቸዋል። እነርሱ ለዚሁ ዓላማ የተለየ “የተመረጠ ትውልድ፣ . . . ቅዱስ ሕዝብ” ናቸው። (ዮሐንስ 10:​16፤ 1 ጴጥሮስ 2:​9) ቅቡዓን የይሖዋ ቅዱስ ስም ከፍ ከፍ ማለቱን የሚያውጁ ሲሆን ይህ ስም በምድር ሁሉ እንዲታወቅ በማድረጉም ሥራ ይካፈላሉ። ይሖዋ ለመዳናቸው ባደረገው ዝግጅት በመደሰት ረገድ የይሖዋን አምላኪዎች በሙሉ ግንባር ቀደም ሆነው ይመራሉ። ሁኔታው ኢሳይያስ እንደሚከተለው ሲል በደስታ እንደገለጸው ነው:- “አንቺ በጽዮን የምትኖሪ ሆይ፣ የእስራኤል ቅዱስ በመካከልሽ ከፍ ከፍ ብሎአልና ደስ ይበልሽ እልልም በዪ። ” (ኢሳይያስ 12:​6) የእስራኤል ቅዱስ የተባለው ይሖዋ አምላክ ራሱ ነው።

የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት ተጠባበቁ!

27. ክርስቲያኖች የተስፋቸውን መፈጸም ሲጠባበቁ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ናቸው?

27 በዛሬው ጊዜ ‘የአሕዛብ ምልክት’ ወደሆነው ማለትም በአምላክ መንግሥት መንበረ ሥልጣኑን ወደ ጨበጠው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጎርፈዋል። የዚህ መንግሥት ተገዢዎች በመሆናቸው እንዲሁም ይሖዋ አምላክንና ልጁን በማወቃቸው በእጅጉ ደስ ይላቸዋል። (ዮሐንስ 17:​3) አንድነት ባለው ክርስቲያናዊ ወዳጅነታቸው እጅግ የሚደሰቱ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች መለያ ምልክት የሆነውን ሰላም ጠብቀው ለመቀጠል ይጥራሉ። (ኢሳይያስ 54:​13) ያህ ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም አምላክ ስለመሆኑ የጸና እምነት ስላላቸው ስለ ተስፋቸው እርግጠኞች ናቸው። እንዲሁም ይህንን ተስፋቸውን ለሌሎች ሰዎች በማካፈላቸው እጅግ ደስ ይላቸዋል። እያንዳንዱ የይሖዋ አምላኪ ኃይሉን ሁሉ አምላክን ለማገልገልና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ለማበረታታት እንዲጠቀምበት ምኞታችን ነው። ሁላችንም የኢሳይያስን ቃላት በልባችን በመሰወር በይሖዋ መሲሕ አማካኝነት በሚገኘው መዳን ደስ ይበለን!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 “መሲሕ” የሚለው ስያሜ “የተቀባ” የሚል ትርጉም ካለው ማሺያህ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። ተመሳሳዩ የግሪክኛ ቃል ክሪስቶስ ወይም “ክርስቶስ” ነው።​—⁠ማቴዎስ 2:​4 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

^ አን.5 “ቁጥቋጥ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ኔሰር ሲሆን “ናዝራዊ” የሚለው ደግሞ ኖስሪ ነው

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 158 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መሲሑ በንጉሥ ዳዊት አማካኝነት የሚመጣ የእሴይ “በትር” ነው

[በገጽ 162 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 170 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሙት ባሕር ጥቅልል ላይ የሚገኙት የ⁠ኢሳይያስ 12:​4, 5 ቃላት (ጎላ ብለው የሚታዩት የአምላክ ስም የሚገኝባቸው ቦታዎች ናቸው)