በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመከራ ጊዜ በይሖዋ ታመኑ

በመከራ ጊዜ በይሖዋ ታመኑ

ምዕራፍ ዘጠኝ

በመከራ ጊዜ በይሖዋ ታመኑ

ኢሳይያስ 7:​1–8:​18

1. ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ኢሳይያስ ምዕራፍ 7 እና 8⁠ን በመመርመራቸው የሚጠቀሙት ለምንድን ነው?

ኢሳይያስ ምዕራፍ 7 እና 8 ፍጹም ተቃራኒ ስለሆኑ ሁለት ሁኔታዎች የሚገልጹ ምዕራፎች ናቸው። ኢሳይያስና አካዝ ለይሖዋ የተወሰነ ብሔር አባላት ሲሆኑ ሁለቱም ከአምላክ የተቀበሉት ኃላፊነት ነበራቸው። አንዱ ነቢይ ሌላው ደግሞ የይሁዳ ንጉሥ ነበሩ። ይሁዳ ብርቱ ከሆነ የጠላት ኃይል የተሰነዘረባት ዛቻ በሁለቱም ሰዎች ፊት የተጋረጠ አስፈሪ ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ በይሖዋ ላይ በመታመን ዛቻውን ሲጋፈጥ አካዝ ፍርሃት እንዲያሸንፈው ፈቅዷል። የሰጡት ምላሽ የተለያየ የሆነው ለምንድን ነው? ዛሬም ክርስቲያኖች በጥላቻ ዓይን በሚያዩአቸው ኃይሎች የተከበቡ በመሆናቸው እነዚህ ሁለት የኢሳይያስ ምዕራፎች ምን ትምህርት እንደያዙ መመርመራቸው ተገቢ ይሆናል።

ከፊታቸው የተጋረጠ ውሳኔ

2, 3. ኢሳይያስ በመክፈቻው ቃላት ጠቅለል አድርጎ የገለጸው ነገር ምንድን ነው?

2 አንድ ሠዓሊ አንድ አዲስ ሥዕል ለመሳል በብሩሹ ነካ ነካ በማድረግ ንድፉን እንደሚያስቀምጥ ሁሉ ኢሳይያስም ሊተርከው ያሰበውን ክንውን መጀመሪያና መጨረሻ በጥቂት ቃላት በመግለጽ ይጀምራል:- “እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፣ ሊያሸንፉአትም አልቻሉም።”​—⁠ኢሳይያስ 7:​1

3 ጊዜው በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነው። አካዝ አባቱን ኢዮአታምን ተክቶ የይሁዳ ንጉሥ ሆኗል። የሶርያው ንጉሥ ረአሶንና የሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ንጉሥ ፋቁሔ ሠራዊት ይሁዳን በመውረር ከባድ ጥቃት ይሰነዝራል። በመጨረሻም ኢየሩሳሌምን ራሷን ይከብባሉ። ይሁን እንጂ ከበባው ይከሽፋል። (2 ነገሥት 16:​5, 6፤ 2 ዜና መዋዕል 28:​5-8) ለምን? ይህን በኋላ እንመለስበታለን።

4. የአካዝና የሕዝቡ ልብ በፍርሃት የተሞላው ለምንድን ነው?

4 ቀደም ሲል በውጊያው ወቅት “ለዳዊትም ቤት:- ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል የሚል ወሬ ተነገረ፤ የእርሱም ልብ የሕዝቡም ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ።” (ኢሳይያስ 7:​2) አዎን፣ ሶርያውያንና እስራኤላውያን ጥምረት እንደፈጠሩና ጦራቸውም በወቅቱ በኤፍሬም (በእስራኤል) ምድር እንደሠፈረ መስማት ለአካዝና ለሕዝቡ የሚያስፈራ ነገር ነበር። የሰፈሩት ከኢየሩሳሌም የሁለት ወይም የሦስት ቀን መንገድ ብቻ ርቀው ነበር!

5. ዛሬ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች ከኢሳይያስ ጋር የሚመሳሰሉት በምን መንገድ ነው?

5 ይሖዋ ለኢሳይያስ እንዲህ ብሎታል:- “አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኩሬ መስኖ ጫፍ ውጡ።” (ኢሳይያስ 7:​3) እስቲ አስበው! በዚህ ጊዜ ንጉሡ ራሱ የይሖዋን ነቢይ ሊፈልግና መመሪያ ለማግኘት ሊጥር ሲገባው ነቢዩ ንጉሡ ድረስ መሄድ አስፈልጎታል! ያም ሆኖ ግን ኢሳይያስ ይሖዋን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ነበር። በተመሳሳይም ዛሬ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች በዚህ ዓለም ተጽእኖ ፍርሃት ላይ ወደ ወደቁት ሰዎች ይሄዳሉ። (ማቴዎስ 24:​6, 14) በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለእነዚህ የምሥራቹ ሰባኪዎች ጉብኝት ምላሽ በመስጠት በይሖዋ ላይ የሚደገፉ መሆናቸውን ማሳየታቸው እንዴት ደስ ይላል!

6. (ሀ) ነቢዩ ለንጉሥ አካዝ ያስተላለፈው ምን የሚያበረታታ መልእክት ነው? (ለ) ዛሬ ያለው ሁኔታ ምን ዓይነት ነው?

6 ኢሳይያስ ንጉሡ አካዝን ያገኘው ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጭ ሆኖ ከፊቱ ለሚጠብቀው ከበባ ለመዘጋጀት የከተማዋን የውኃ ምንጭ ሲቃኝ ነበር። ኢሳይያስ የይሖዋን መልእክት ነገረው:- “ተጠበቅ፣ ዝምም በል፤ ስለ እነዚህ ስለሚጤሱ ስለ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች [“ጉማጆች፣” የ1980 ትርጉም]፣ ስለ ሶርያና ስለ ረአሶን ስለ ሮሜልዩም ልጅ ቁጣ አትፍራ፣ ልብህም አይድከም።” (ኢሳይያስ 7:​4) ከዚህ ቀደም ብሎ ወራሪዎቹ ይሁዳን ባወደሙበት ጊዜ ቁጣቸው እንደሚፋጅ የእሳት ነበልባል ነበር። አሁን ግን ‘እንደሚጤሱ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች’ ሆነዋል። አካዝ የሶርያውን ንጉሥ ረአሶንንም ሆነ የእስራኤሉን ንጉሥ የሮሜልዩን ልጅ ፋቁሔን መፍራት አያስፈልገውም። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለብዙ መቶ ዘመናት የሕዝበ ክርስትና መሪዎች በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ኃይለኛ ስደት ሲያደርሱ ኖረዋል። ይሁንና ዛሬ ሕዝበ ክርስትና በተወሰነ መጠን እንደተቃጠለ የእንጨት ጉማጅ ሆናለች። የቀራት ዕድሜም አጭር ነው።

7. የኢሳይያስም ሆነ የልጁ ስም ለተስፋ ምክንያት የሚሆነው ለምንድን ነው?

7 በአካዝ ዘመን የኢሳይያስ መልእክቱ ብቻ ሳይሆን የእርሱና የልጁ ስም ትርጉምም በይሖዋ ለሚታመኑ ሰዎች ተስፋ የሚሰጥ ነበር። ይሁዳ አደጋ አንዣብቦባት እንደነበር ምንም አያጠያይቅም። ሆኖም “የይሖዋ ማዳን” የሚል ትርጉም ያለው ኢሳይያስ የሚለው ስም ይሖዋ እንደሚያድናቸው የሚጠቁም ነበር። ኢሳይያስ ያሱብ የሚባለውን ወንድ ልጁን ይዞት እንዲሄድ ይሖዋ የነገረው ሲሆን የስሙም ትርጉም ‘ጥቂት ቀሪዎች ይመለሳሉ’ የሚል ነው። የይሁዳ መንግሥት በመጨረሻ ሲወድቅ እንኳ አምላክ ምሕረት በማሳየት ቀሪዎች ወደ ምድራቸው እንዲመለሱ ያደርጋል።

በብሔራት መካከል የሚደረግ ውጊያ ብቻ አልነበረም

8. በኢየሩሳሌም ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በብሔራት መካከል የሚደረግ ውጊያ ብቻ አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው?

8 ይሖዋ የይሁዳ ጠላቶች የነደፉትን ስልት በኢሳይያስ አማካኝነት ይፋ አውጥቶታል። “ወደ ይሁዳ እንውጣ እናስጨንቀውም፣ እንስበረውም፣ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት ብለው” አቅደው ነበር። (ኢሳይያስ 7:​5, 6) የሶርያና እስራኤል ኅብረት የነደፈው ዕቅድ ይሁዳን ድል አድርጎ በመያዝ የዳዊት ልጅ የሆነውን አካዝን በራሳቸው ሰው መተካት ነበር። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው በኢየሩሳሌም ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በብሔራት መካከል የሚደረግ ጦርነት ብቻ አልነበረም። በሰይጣንና በይሖዋ መካከል የሚደረግ ትግል ሆኖ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ አምላክ ከንጉሥ ዳዊት ጋር ቃል ኪዳን በመግባት ልጆቹ የይሖዋን ሕዝብ እንደሚገዙ ዋስትና ሰጥቶት ነበር። (2 ሳሙኤል 7:​11, 16) ሰይጣን በኢየሩሳሌም ዙፋን ላይ ሌላ ሥርወ መንግሥት ማስቀመጥ ከቻለ እንዴት ታላቅ ድል ይሆንለታል! ምናልባትም ይሖዋ ከዳዊት መስመር ‘የሰላም መስፍን’ የሆነ ዘላለማዊ ወራሽ እንዲነሣ ለማድረግ ያወጣውን ዓላማ ማጨናገፍ ይችል ይሆናል።​—⁠ኢሳይያስ 9:​6, 7

የይሖዋ ፍቅራዊ ማረጋገጫ

9. ለአካዝም ሆነ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ድፍረት ሊሰጣቸው የሚገባው የትኛው ማረጋገጫ ነው?

9 ሶርያና እስራኤል የዶለቱት ነገር ይሳካላቸው ይሆን? አይሳካላቸውም። ይሖዋ “ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 7:​7) ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት፣ በኢየሩሳሌም ላይ የታቀደው ከበባ እንደሚከሽፍ ብቻ ሳይሆን “በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራልና ሕዝብ አይሆንም” ሲልም ተናግሯል። (ኢሳይያስ 7:​8) አዎን፣ በ65 ዓመታት ውስጥ እስራኤል ሕዝብ መሆኗ ያከትማል። * ቁርጥ ያለ ጊዜ ተጠቅሶ የተሰጠው ይህ ዋስትና አካዝን ሊያበረታው ይገባል። በተመሳሳይም ዛሬ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች የሰይጣን ዓለም የቀረው ጊዜ እየተሟጠጠ መሆኑን በማወቃቸው ይበረታታሉ።

10. (ሀ) ዛሬ እውነተኛ ክርስቲያኖች የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለአካዝ ያቀረበለት ግብዣ ምንድን ነው?

10 ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል የሚከተለውን ነገር መናገሩ ምናልባት አካዝ ፊት ላይ የተነበበው ስሜት ጥርጣሬ ሳይሆን እንዳልቀረ ይጠቁማል። “ባታምኑ አትጸኑም።” ይሖዋ በትዕግሥት ‘ለአካዝ ተጨማሪ ነገር መንገሩን ቀጠለ።’ (ኢሳይያስ 7:​9, 10) እንዴት ግሩም ምሳሌ ነው! ዛሬ ብዙ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ፈጣን ምላሽ የማይሰጡ ቢሆንም ደጋግመን ስንሄድ ‘ተጨማሪ ነገር በመንገር’ የይሖዋን ምሳሌ መኮረጃችን ምንኛ የተገባ ይሆናል። ቀጥሎ ይሖዋ አካዝን እንዲህ ብሎታል:- “ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለምን።” (ኢሳይያስ 7:​11) አካዝ ከይሖዋ ምልክት ሊጠይቅና ይሖዋም የዳዊትን ቤት እንደሚጠብቅ ዋስትና ለመስጠት ሲል የጠየቀውን ምልክት ሊያሳየው ይችል ነበር።

11. ‘አምላክህ’ የሚለው የይሖዋ አነጋገር ምን ዋስትና ይሰጣል?

11 ይሖዋ ‘ከአምላክህ ምልክትን ለምን’ እንዳለ ልብ በል። ይሖዋ እንዴት ደግ ነው። አካዝ በዚህ ጊዜ የሐሰት አማልክትን የሚያመልክና አስጸያፊ የሆኑ አረማዊ ልማዶችን የሚከተል ሰው እንደነበር ተገልጿል። (2 ነገሥት 16:​3, 4) አካዝ እንደዚህ ዓይነት መጥፎ አካሄድና የፍርሃት ዝንባሌ ቢኖረውም ይሖዋ ራሱን የአካዝ አምላክ ብሎ ጠርቷል። ይህም ይሖዋ ሰዎችን ፊት ለመንሳት እንደማይቸኩል ያረጋግጥልናል። ስህተት የፈጸሙትን ወይም እምነታቸው የደከመባቸውን ለመደገፍ ፈቃደኛ ነው። ይህ የአምላክ ፍቅር ማረጋገጫ አካዝ በይሖዋ ላይ እንዲደገፍ ያነሳሳው ይሆን?

ከጥርጣሬ ወደ አለመታዘዝ

12. (ሀ) አካዝ ምን ዓይነት የንቀት አመለካከት ነበረው? (ለ) አካዝ ፊቱን ወደ ይሖዋ ከማዞር ይልቅ ለእርዳታ የሄደው ወደ ማን ነው?

12 አካዝ “አልለምንም፣ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” በማለት በእንቢተኝነት መልስ ሰጠ። (ኢሳይያስ 7:​12) እዚህ ላይ አካዝ “አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት” የሚለውን የሕጉን ቃል መጠበቁ አልነበረም። (ዘዳግም 6:​16) ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ በሰይጣን በተፈተነ ጊዜ ይህንኑ ሕግ ጠቅሶ ነበር። (ማቴዎስ 4:​7) አካዝን ግን ይሖዋ የጋበዘው ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲመለስ ሲሆን ምልክት በማሳየት እምነቱን ሊያጠነክርለት ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ አካዝ ጥበቃ ማግኘት የፈለገው ከሌላ ወገን ነው። ንጉሡ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ አሦር በመላክ ከሰሜን ወገን የተነሱበትን ጠላቶቹን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ የጠየቀው በዚህ ጊዜ ይመስላል። (2 ነገሥት 16:​7, 8) ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶርያና የእስራኤል ጥምር ሠራዊት በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከበባውን ጀምሮ ነበር።

13. በኢሳይያስ 7 ቁጥር 13 ላይ ምን ለውጥ እናስተውላለን? ይህስ ምን ያመለክታል?

13 ንጉሡ እምነት በማጣቱ ምክንያት ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፣ ስሙ፤ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ።” (ኢሳይያስ 7:​13) አዎን፣ ምንም የማይሰሙ ግትሮች መሆናቸው ይሖዋን ሊያደክመው ይችላል። አሁን ነቢዩም “አምላኬን” እንጂ “አምላክህን” እንዳላለ ልብ በል። እንዴት ትልቅ ለውጥ ነው! አካዝ ለይሖዋ ጀርባውን ሰጥቶ ወደ አሦራውያን በመመለሱ ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነት ማደስ የሚችልበትን ግሩም አጋጣሚ አጥቷል። እኛም ብንሆን ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ስንል ቅዱስ ጽሑፋዊ እምነቶቻችንን በማላላት ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ልንሠዋ አይገባም።

የአማኑኤል ምልክት

14. ይሖዋ ከዳዊት ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ታማኝ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

14 ይሖዋ ከዳዊት ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ምን ጊዜም ታማኝ ነው። ምልክት ለማሳየት ፈቃደኛ ነበር። አሁንም ምልክት ያሳያል! ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፣ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች።”​—⁠ኢሳይያስ 7:​14-16

15. ስለ አማኑኤል የተነገረው ትንቢት ለየትኞቹ ሁለት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል?

15 ወራሪዎቹ የዳዊትን የንግሥና መስመር ያቋርጡታል የሚል ፍርሃት ለነበረባቸው ሁሉ እነሆ አንድ ጥሩ ምሥራች አለ። “አማኑኤል” ማለት “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ነው ማለት ነው። አምላክ ከይሁዳ ጋር በመሆኑ ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳን ውድቅ እንዲሆን አይፈቅድም። ከዚህም በተጨማሪ አካዝና ሕዝቡ የተነገራቸው ይሖዋ የሚያደርገው ነገርን ብቻ ሳይሆን መቼ እንደሚያደርገውም ጭምር ነው። ሕፃኑ አማኑኤል ገና ክፉውንና ደጉን መለየት ከመቻሉ በፊት ጠላቶቻቸው ይጠፋሉ። ይህም ደግሞ በትክክል ተፈጽሟል!

16. ይሖዋ በአካዝ ዘመን የአማኑኤልን ማንነት ግልጽ ያላደረገው ለምን ሊሆን ይችላል?

16 መጽሐፍ ቅዱስ አማኑኤል የማን ልጅ እንደሆነ የሚጠቅሰው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ሕፃኑ አማኑኤል ምልክት ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑና ኢሳይያስም ቆየት ብሎ እርሱና ልጆቹ “ምልክት” እንደሆኑ ስለጠቀሰ አማኑኤል የነቢዩ ልጅ ሊሆን ይችላል። (ኢሳይያስ 8:​18) ምናልባትም ይሖዋ የአማኑኤልን ማንነት በአካዝ ዘመን በግልጽ ሳይናገር የቀረው በኋለኛው ዘመን የሚመጡት ትውልዶች ከታላቁ አማኑኤል ጋር እንዳያምታቱት በማለት ይሆናል። ይህ ማን ነው?

17. (ሀ) ታላቁ አማኑኤል ማን ነው? ልደቱስ ምን ያመለክታል? (ለ) ዛሬ የአምላክ ሕዝብ ‘አምላክ ከእኛ ጋር ነው’ በማለት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መናገር የሚችሉት ለምንድን ነው?

17 አማኑኤል የሚለው ስም ከኢሳይያስ መጽሐፍ ውጭ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘው አንድ ጊዜ ይኸውም በ⁠ማቴዎስ 1:​23 ላይ ብቻ ነው። ስለ አማኑኤል መወለድ የተነገረው ትንቢት የዳዊት ዙፋን ሕጋዊ ወራሽ የሆነውን የኢየሱስን መወለድ እንደሚያመለክት አድርጎ እንዲጽፍ ይሖዋ ማቴዎስን በመንፈሱ አነሳስቶታል። (ማቴዎስ 1:​18-23) የመጀመሪያው አማኑኤል መወለድ አምላክ የዳዊትን ቤት እንዳልተወ የሚያሳይ ምልክት ነበር። በተመሳሳይም የታላቁ አማኑኤል ማለትም የኢየሱስ መወለድ አምላክ የሰውን ዘር ወይም ከዳዊት ቤት ጋር የገባውን የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳልተወ የሚያሳይ ምልክት ነው። (ሉቃስ 1:​31-33) በወቅቱ የይሖዋ ዋነኛ ወኪል በሰው ዘር መካከል ተገኝቶ ስለነበር ማቴዎስ በትክክል “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ነው ማለት ይችል ነበር። ዛሬ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ያለው ኢየሱስ በምድር ላይ ከሚገኘው ጉባኤው ጋር ነው። (ማቴዎስ 28:​20) በእርግጥም የአምላክ ሕዝቦች “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ነው ብለው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙበት ተጨማሪ ምክንያት አላቸው።

ታማኝ አለመሆን የሚያስከትላቸው ተጨማሪ መዘዞች

18. (ሀ) ኢሳይያስ ቀጥሎ የሚናገራቸው ቃላት አድማጮቹን የሚያርበተብቱ የሆኑት ለምንድን ነው? (ለ) ብዙም ሳይቆይ ምን ለውጥ ይከሰታል?

18 ኢሳይያስ መጨረሻ የተናገራቸው ቃላት የሚያጽናኑ ቢሆኑም ቀጥሎ የሚናገራቸው ቃላት ግን ሰሚዎቹን የሚያርበተብቱ ናቸው:- “እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው።” (ኢሳይያስ 7:​17) አዎን፣ በአሦራውያኑ ንጉሥ እጅ የመውደቅ አደጋ እያንዣበበባቸው ነበር። በጭካኔያቸው በሚታወቁት አሦራውያን እጅ የመውደቁ ሐሳብ ለአካዝና ለሕዝቡ እንቅልፍ የሚነሳ ነገር ሆኖባቸው መሆን አለበት። አካዝ ከአሦራውያን ጋር ወዳጅነት መመሥረቱ ከእስራኤልና ከሶርያ እጅ እንደሚያስጥለው አስቦ ነበር። በእርግጥም ደግሞ የአሦር ንጉሥ እስራኤልንና ሶርያን በመውጋት ለአካዝ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል። (2 ነገሥት 16:​9) ፋቁሔና ረአሶን የኢየሩሳሌም ከበባቸውን ለመተው የሚገደዱበት ምክንያት ይህ እንደሆነ አያጠራጥርም። በዚህ መንገድ የሶርያና የእስራኤል ኅብረት ኢየሩሳሌምን መቆጣጠር ሳይችል ይቀራል። (ኢሳይያስ 7:​1) ይሁንና አሁን ኢሳይያስ ጥላቸው ለተገፈፈው ለእነዚሁ አድማጮቹ ትጠብቀናለች ያሏት አሦር አስገባሪያቸው እንደምትሆን እየነገራቸው ነው!​—⁠ከ⁠ምሳሌ 29:​25 ጋር አወዳድር።

19. ይህ ታሪካዊ ድራማ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ምን ማስጠንቀቂያ ይዟል?

19 ይህ እውነተኛ ታሪክ የያዘ ዘገባ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ይሆናቸዋል። ተጽዕኖዎች ሲደርሱብን ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመጣስ የይሖዋን ጥበቃ ወደ ጎን ገሸሽ ለማድረግ እንፈተን ይሆናል። ከቀጣዮቹ የኢሳይያስ ቃላት በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ይህ አርቆ አለማሰብ አልፎ ተርፎም በገዛ እጅ ለጥፋት መዳረግ ነው። ነቢዩ የአሦራውያን ወረራ በምድሪቱና በሕዝቡ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት በመግለጽ ይቀጥላል።

20. ‘ዝምቦቹና’ ‘ንቦቹ’ እነማን ናቸው? ምንስ ያደርጋሉ?

20 ኢሳይያስ የሚናገረውን ነገር በአራት ይከፍለዋል። እያንዳንዱ ክፍል ‘በዚያ ቀን’ ማለትም አሦራውያን በይሁዳ ላይ ጥቃት በሚሰነዝሩበት ጊዜ ስለሚሆነው ነገር የሚተነብይ ነው። “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በግብጽ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝምብ በአሦርም አገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል። ይመጡማል፣ እነርሱም ሁሉ በበረሀ ሸለቆ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በእሾህ ቁጥቋጦ ሁሉ ላይ በማሰማርያውም ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ።” (ኢሳይያስ 7:18, 19) የግብጽና የሶርያ ሠራዊት እንደ ዝንብና ንብ መንጋ ትኩረታቸውን በተስፋይቱ ምድር ላይ ያደርጋሉ። ይህ እንዲሁ መጥቶ የሚያልፍ ወረራ ብቻ አይሆንም። ‘ዝምቦቹና’ ‘ንቦቹ’ በየጥጉና በየቀዳዳው ሁሉ ተሰግስገው በምድሪቱ ይሰፍራሉ።

21. የአሦራውያን ንጉሥ እንደ ምላጭ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?

21 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጉር ይላጨዋል፤ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይበላል።” (ኢሳይያስ 7:​20) አሁን የተጠቀሰው ትልቁን ስጋት የፈጠረው አሦር ብቻ ነው። አካዝ ሶርያንና እስራኤልን ‘እንዲላጭለት’ የአሦራውያኑን ንጉሥ ይቀጥረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ከኤፍራጥስ አካባቢ ‘የተከራየው ምላጭ’ በይሁዳ ላይ ይነሣና የይሁዳን ራስ ብቻ ሳይሆን ጢሙን ሳይቀር ይላጨዋል!

22. እያንዣበበ የነበረው የአሦር ወረራ የሚያስከትለውን ውጤት ለማመልከት ኢሳይያስ ምን ምሳሌ ተጠቀመ?

22 ውጤቱስ ምን ይሆናል? “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሰው አንዲት ጊደርን ሁለት በጎችንም ያሳድጋል፤ ከሚሰጡት ወተት ብዛት የተነሣ ቅቤ ይበላል፤ በአገሪቱም መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል።” (ኢሳይያስ 7:​21, 22) አሦራውያን ምድሪቱን ‘በሚላጩበት’ ጊዜ የሚቀሩት ሰዎች በጣም ጥቂት ከመሆናቸው የተነሣ ለምግብነት የሚያገለግሉ እንስሳት ቁጥር በጣም አነስተኛ ይሆናል። የሚበላው “ቅቤና ማር” ብቻ ይሆናል። ከዚያ ውጭ ወይን፣ ዳቦ ወይም ሌላ መሠረታዊ ምግብ አይኖርም። ኢሳይያስ የምድሪቱን ባድማነት አጋንኖ ለመግለጽ የፈለገ ይመስል ሦስት ጊዜ ያህል በጣም ፍሬያማ የነበረው መሬት ኩርንችትና አረም እንደሚበቅልበት ተናግሯል። ከከተማው ውጭ ለመሄድ የሚቃጣ ካለ በጥሻው ውስጥ የሚያደቡትን አራዊት ለመከላከል ‘ፍላጻና ቀስት’ ያስፈልገዋል። የተመነጠሩት መሬቶች የበሬና የበግ መራገጫ ይሆናሉ። (ኢሳይያስ 7:​23-25) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው በራሱ በአካዝ ዘመን ነው።​—⁠2 ዜና መዋዕል 28:​20

የማያሻማ ትንበያ

23. (ሀ) አሁን ደግሞ ኢሳይያስ ምን እንዲያደርግ ታዝዟል? (ለ) የሰሌዳው ምልክት በሌላ ማረጋገጫ የተደገፈው እንዴት ነው?

23 አሁን ኢሳይያስ በወቅቱ ወደ ነበረው ሁኔታ መለስ ይላል። ኢየሩሳሌም ገና በሶርያና በእስራኤል ጥምር ሠራዊት ተከብባ ያለች ቢሆንም ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “እግዚአብሔርም:- ታላቅ ሰሌዳ ወስደህ:- ምርኮ ፈጠነ፣ ብዝበዛ ቸኰለ [“ማሄር ሻላል ሃሽ ባዝ፣” NW] ብለህ በሰው ፊደል ጻፍበት። የታመኑትን ሰዎች ካህኑን ኦርዮንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ አለኝ።” (ኢሳይያስ 8:​1, 2) ማሄር ሻላል ሃሽ ባዝ የሚለው ስም ትርጉም “ምርኮ ፈጠነ፣ ብዝበዛ ቸኮለ” የሚል ነው። ኢሳይያስ በማኅበረሰቡ መካከል ያሉ ሁለት የተከበሩ ሰዎች ይህን ስም በትልቅ ሰሌዳ ላይ ሲጽፍ ምሥክር እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህም በኋላ የሰነዱን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ምልክት በሌላ ሁለተኛ ምልክት መረጋገጥ ነበረበት።

24. የማሄር ሻላል ሃሽ ባዝ ምልክት በይሁዳ ሕዝብ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊኖረው ይገባል?

24 ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “ወደ ነቢይቱም ቀረብሁ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች። እግዚአብሔርም:- ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና ስሙን:- ምርኮ ፈጠነ፣ ብዝበዛ ቸኰለ [“ማሄር ሻላል ሃሽ ባዝ፣” NW] ብለህ ጥራው አለኝ።” (ኢሳይያስ 8:​3, 4) ትልቁ ሰሌዳም ሆነ አዲስ የተወለደው ሕፃን አሦራውያን ይሁዳን ያስጨነቋትን ሶርያንና እስራኤልን በቅርቡ እንደሚበዘብዙ የሚያረጋግጥ ምልክት ሆነው ያገለግላሉ። ይሁንና በቅርቡ ሲባል ምን ያህል ቅርብ ነው? ሕፃኑ ብዙ ልጆች መጀመሪያ የሚማሯቸውን ‘አባባ’ እና ‘እማማ’ የሚሉትን ቃላት ከመማሩ በፊት ነው። እንዲህ ያለው የማያሻማ ትንበያ ሕዝቡ በይሖዋ ላይ ያለውን ትምክህት ሊገነባለት ይገባ ነበር። ወይም ደግሞ አንዳንዶች በኢሳይያስና በልጁ ላይ እንዲያፌዙ ሊያነሳሳቸው ይችል ይሆናል። ብቻ ሁኔታው ምንም ይሁን ምን የኢሳይያስ ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።​—⁠2 ነገሥት 17:​1-6

25. በኢሳይያስ ዘመንና በዛሬው ጊዜ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

25 ክርስቲያኖች ኢሳይያስ ከሰጠው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ታሪካዊ ድራማ ውስጥ ኢሳይያስ ኢየሱስን እንደሚያመለክትና የኢሳይያስ ልጅ ደግሞ ለኢየሱስ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርት ጥላ እንደሆነ ገልጾልናል። (ዕብራውያን 2:​10-13) ኢየሱስ በምድር ላይ ባሉት ቅቡዓን ተከታዮቹ አማካኝነት በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት ‘ነቅቶ የመኖርን’ አስፈላጊነት ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ሲያሳስብ ቆይቷል። (ሉቃስ 21:​34-36 NW) በተመሳሳይም ንስሐ የማይገቡ ተቃዋሚዎች ስለሚጠብቃቸው ጥፋት ማስጠንቀቂያ ቢነገራቸውም ብዙውን ጊዜ እንዲህ ላለው ማስጠንቀቂያ የሚሰጡት ምላሽ ፌዝ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:​3, 4) በኢሳይያስ ዘመን ከጊዜ ጋር ተያይዘው የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው አምላክ ለዘመናችን ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ‘በትክክል እንደሚፈጸምና እንደማይዘገይ’ ዋስትና ይሆነናል።​—⁠ዕንባቆም 2:​3

አውዳሚ የሆነ “ውኃ”

26, 27. (ሀ) ኢሳይያስ የተነበየው ስለ ምን ነገር ነው? (ለ) የኢሳይያስ ቃላት ዛሬ ላሉት የይሖዋ አገልጋዮች የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው?

26 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ማስጠንቀቂያውን ይቀጥላል:- “ይህ ሕዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውኃ ጠልቶአልና፣ ረአሶንንና የሮሜልዩንም ልጅ ወዶአልና ስለዚህ፣ እነሆ፣ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ፣ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ፣ ያመጣባቸዋል፤ መስኖውንም ሁሉ ሞልቶ ይወጣል፣ በዳሩም ሁሉ ላይ ይፈስሳል፤ እየጐረፈም ወደ ይሁዳ ይገባል፤ እያጥለቀለቀም ያልፋል፣ እስከ አንገትም ይደርሳል፤ አማኑኤል ሆይ፣ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች።”​—⁠ኢሳይያስ 8:​5-8

27 “ይህ ሕዝብ” ማለትም የሰሜናዊው እስራኤል መንግሥት ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ወደ ጎን ገሸሽ አድርጓል። (2 ነገሥት 17:​16-18) ለእነርሱ በቀስታ እንደሚወርደው የኢየሩሳሌም የውኃ ምንጭ እንደሆነው እንደ ሰሊሆም ውኃ ሆኖባቸው ነበር። ከይሁዳ ጋር ባደረጉት ውጊያ በጣም ተኩራርተዋል። ይሁን እንጂ ለዚህ ንቀታቸው ሳይቀጡ አይቀሩም። ይሖዋ አሦራውያን ሶርያንና ግብጽን ‘እንዲያጥለቀልቋቸው’ ወይም እንዲወርሯቸው ይፈቅዳል። በቅርቡም ዛሬ ያሉ የዓለም ፖለቲካዊ ወገኖች የሐሰት ሃይማኖትን ግዛት እንዲያጥለቀልቋት ይፈቅዳል። (ራእይ 17:​16፤ ከ⁠ዳንኤል 9:​26 ጋር አወዳድር።) ቀጥሎ ኢሳይያስ እንደገለጸው ከፍተኛ መጠን ያለው “ውኃ” ‘ወደ ይሁዳ ይገባና እስከ አንገት’ ማለትም የይሁዳ ራስ (ንጉሥ) መቀመጫ እስከሆነችው እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ይደርሳል። * በጊዜያችንም በሐሰት ሃይማኖት ላይ ፍርዱን የሚያስፈጽሙት ፖለቲካዊ ወገኖች በተመሳሳይ መንገድ የይሖዋን አገልጋዮች ‘እስከ አንገታቸው’ ድረስ በመክበብ በእነርሱ ላይ ይነሣሉ። (ሕዝቅኤል 38:​2, 10-16) ውጤቱስ ምን ይሆናል? በእስራኤል ዘመን የሆነው ነገር ምን ነበር ብለን እንጠይቅ? አሦራውያን የከተማዋን ቅጥር አልፈው ገብተው የአምላክን ሕዝቦች ጠራርገው አጥፍተዋቸው ነበርን? የለም አላጠፏቸውም። አምላክ ከእነርሱ ጋር ነበር።

አትፍሩ​—⁠‘አምላክ ከእኛ ጋር ነው!’

28. ጠላቶቻቸው የቱንም ያህል ቢፍጨረጨሩ ይሖዋ ለአይሁዳውያን ምን ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል?

28 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- [የአምላክን የቃል ኪዳን ሕዝብ የተቃወማችሁ] አሕዛብ ሆይ፣ እወቁና ደንግጡ፤ እናንተም ምድራችሁ የራቀ ሁሉ፣ አድምጡ፤ ታጠቁ፣ ደንግጡ፤ ታጠቁ፣ ደንግጡ። ተመካከሩምክራችሁም ይፈታል፤ ቃሉን ተናገሩ፣ ቃሉም አይጸናም፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።” (ኢሳይያስ 8:​9, 10) ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአካዝ ልጅ በሆነው በታመነው ንጉሥ ሕዝቅያስ የግዛት ዘመን እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። አሦራውያን ኢየሩሳሌምን ለመያዝ ያስፈራሩ በነበረበት ጊዜ የይሖዋ መልአክ 185,000 ወታደሮቻቸውን ገድሏል። በእርግጥም አምላክ ከሕዝቡና ከዳዊት የንግሥና መስመር ጋር ነበር። (ኢሳይያስ 37:​33-37) በመጪው የአርማጌዶን ጦርነት ወቅትም ይሖዋ በተመሳሳይ መንገድ ታላቁን አማኑኤልን በመላክ ጠላቶቹን ማድቀቅ ብቻ ሳይሆን በእርሱ የሚታመኑትን ሰዎች ያድናል።​—⁠መዝሙር 2:​2, 9, 12

29. (ሀ) በአካዝ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን በሕዝቅያስ ዘመን ከነበሩት የሚለዩት እንዴት ነው? (ለ) ዛሬ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ሃይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥምረት ከመፍጠር የሚርቁት ለምንድን ነው?

29 በሕዝቅያስ ዘመን ከኖሩት አይሁዳውያን በተለየ መልኩ በአካዝ ጊዜ የነበሩት በይሖዋ ጥበቃ ላይ እምነት አልነበራቸውም። ከሶርያና እስራኤል ኅብረት ራሳቸውን ለመከላከል እንደ ትልቅ መመኪያ አድርገው የተመለከቱትና የላቀ ግምት የሰጡት ከአሦራውያን ጋር መዋዋልን ወይም ‘መዶለትን’ ነበር። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ ‘የዚህን ሕዝብ መንገድ’ ማለትም በሰፊው የሚከተሉትን ጎዳና እንዲያጋልጥ ይሖዋ ‘በእጁ’ ይገፋፋዋል። እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “መፈራታቸውንም አትፍሩ፣ አትደንግጡ። ነገር ግን የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን።” (ኢሳይያስ 8:​11-13) ዛሬ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮችም ይህን በአእምሮአቸው በመያዝ ከሃይማኖታዊ ምክር ቤቶችና ፖለቲካዊ ማኅበራት ጋር ከመዶለት ወይም በእነርሱ ከመታመን ይቆጠባሉ። የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ እነርሱን ለመጠበቅ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ሙሉ ትምክህት አላቸው። ደግሞስ ‘ይሖዋ ከእኛ ጋር ከሆነ ሰው ምን ያደርገናል?’​—⁠መዝሙር 118:​6

30. በይሖዋ የማይታመኑ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

30 ኢሳይያስ ይሖዋ በእርሱ ለሚታመኑ “መቅደስ” ማለትም ከለላ እንደሚሆን ደግሞ ደጋግሞ መጥቀሱን ቀጥሏል። በተቃራኒው ደግሞ እርሱን አንቀበልም ያሉ ሰዎች “ይሰናከላሉ፣ ይወድቁማል፣ ይሰበሩማል፣ ይጠመዱማል፣ ይያዙማል።” እዚህ ላይ በአምላክ የማይታመኑ ሰዎች የሚገጥማቸውን እጣ ፈንታ በግልጽ የሚያመለክቱ አምስት ግሶች ተቀምጠዋል። (ኢሳይያስ 8:​14, 15) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተመሳሳይ መንገድ ኢየሱስን ለመቀበል አሻፈረን ያሉት ሰዎች ተሰናክለው ወድቀዋል። (ሉቃስ 20:​17, 18) ዛሬም ሰማያዊ ዙፋኑን ከያዘው ንጉሥ ከኢየሱስ ጎን መቆም የተሳናቸው ሁሉ የሚጠብቃቸው ዕጣ ከዚህ የተለየ አይደለም።​—⁠መዝሙር 2:​5-9

31. ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢሳይያስንና የእርሱን ትምህርት የሚያዳምጡትን ሰዎች ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

31 በኢሳይያስ ዘመን የተሰናከሉት ሁሉም ሰዎች አልነበሩም። ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “ምስክሩን እሰር፤ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ሕጉን አትም። ከያዕቆብም ቤት ፊቱን የመለሰውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፣ እተማመንበትማለሁ።” (ኢሳይያስ 8:​16, 17) ኢሳይያስና የእርሱን ትምህርት የሚከተሉ ሁሉ የአምላክን ሕግ አይተዉም። ዓመፀኛ የነበሩት ያገራቸው ልጆች እምቢ ቢሉና ይሖዋ ፊቱን ቢያዞርባቸውም እነርሱ በይሖዋ መታመናቸውን ይቀጥላሉ። እኛም በይሖዋ የሚታመኑትን ሰዎች ምሳሌ እንከተል። እውነተኛውን አምልኮ ሙጥኝ በማለት በኩል የእነርሱ ዓይነት ቁርጠኝነት ይኑረን!​—⁠ዳንኤል 12:​4, 9፤ ማቴዎስ 24:​45፤ ከ⁠ዕብራውያን 6:​11, 12 ጋር አወዳድር።

“ምልክት” እና “ተአምራት”

32. (ሀ) ዛሬ እንደ ‘ምልክትና ተአምራት’ ሆነው የሚያገለግሉት እነማን ናቸው? (ለ) ክርስቲያኖች ከዓለም የተለዩ ሆነው መታየት ያለባቸው ለምንድን ነው?

32 አሁን ደግሞ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “እነሆ፣ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።” (ኢሳይያስ 8:​18) አዎን፣ ኢሳይያስ፣ ያሱብና ማሄር ሻላል ሃሽ ባዝ ይሖዋ ይሁዳን በሚመለከት ለነበረው ዓላማ ምልክት ሆነው አገልግለዋል። ዛሬም በተመሳሳይ ኢየሱስና ቅቡዓን ወንድሞቹ ምልክት ሆነው ያገለግላሉ። (ዕብራውያን 2:​11-13) በተጨማሪም ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” በሥራቸው ያግዟቸዋል። (ራእይ 7:​9, 14፤ ዮሐንስ 10:​16) እርግጥ አንድ ምልክት ዋጋ የሚኖረው በዙሪያው ካሉት ነገሮች ለየት ብሎ የሚታይ ከሆነ ብቻ ነው። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች እንደ ምልክት የማገልገል ተልዕኮአቸውን መፈጸም የሚችሉት ሙሉ በሙሉ በይሖዋ በመታመንና ዓላማውን በድፍረት በማወጅ ከዚህ ዓለም ልዩ ሆነው ሲታዩ ብቻ ነው።

33. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ለማድረግ ቆርጠዋል? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ጸንተው መቆም የሚችሉት ለምንድን ነው?

33 እንግዲያው ሁላችንም የዚህን ዓለም ሳይሆን የአምላክን የአቋም ደረጃዎች እንጠብቅ። “የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን” በተመለከተ ለታላቁ ኢሳይያስ ለኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠውን ተልእኮ እየፈጸምክ ያለ ፍርሃት ምልክት ሆነህ መታየትህን ቀጥል። (ኢሳይያስ 61:​1, 2፤ ሉቃስ 4:​17-21) የአሦራውያን ጎርፍ ምድርን ሲያጥለቀልቅ ውኃው እስከ አንገታችን ቢደርስ እንኳ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተጠርገው አይወሰዱም። ‘አምላክ ከእኛ ጋር ነውና’ ጸንተን እንቆማለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ስለሚያገኝበት መንገድ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 62 እና 758 ተመልከት።

^ አን.27 አሦር ክንፉን ሲዘረጋ ‘የአገሩን ስፋት እንደሚሸፍን’ ወፍ ተደርጎ ተገልጿል። በዚህ መንገድ ምድሩ የቱንም ያህል ስፋት ቢኖረው በአሦራውያን ሠራዊት ይሸፈናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 103 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢሳይያስ ከይሖዋ የተሰጠውን መልእክት ለአካዝ ሲያደርስ ያሱብን ይዞ ሄዷል

[በገጽ 111 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢሳይያስ በሰሌዳ ላይ “ማሄር ሻላል ሃሽ ባዝ” ብሎ የጻፈው ለምንድን ነው?