በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በዚያም የሚቀመጥ ታምሜአለሁ አይልም’

‘በዚያም የሚቀመጥ ታምሜአለሁ አይልም’

ምዕራፍ ሃያ ስድስት

‘በዚያም የሚቀመጥ ታምሜአለሁ አይልም’

ኢሳይያስ 33:​1-​24

1. የ⁠ኢሳይያስ 33:​24 ቃላት የሚያጽናኑ የሆኑት ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ” ኖሯል ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 8:​22) የሕክምናው ሳይንስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም ሕመምና ሞት ለሰው ዘር መቅሰፍት መሆናቸውን ቀጥለዋል። እንግዲያው በዚህኛው የኢሳይያስ ትንቢት ክፍል መደምደሚያ ላይ የሚገኘው ተስፋ እንዴት ግሩም ነው! እስቲ አስበው “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ” የማይልበት ጊዜ ይመጣል። (ኢሳይያስ 33:​24) ይህ ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼና እንዴት ነው?

2, 3. (ሀ) የእስራኤል ብሔር የታመመው በምን መንገድ ነው? (ለ) አምላክ አሦርን እንደ ተግሳጽ “በትር” የተጠቀመበት እንዴት ነው?

2 ኢሳይያስ ይህንን የጻፈው የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ በመንፈሳዊ ሕመም ላይ ወድቆ በነበረበት ወቅት ነው። (ኢሳይያስ 1:​5, 6) በክህደትና በሥነ ምግባር ብልግና በእጅጉ ተጠላልፈው ስለነበር ይሖዋ አምላክ ጠንከር ያለ ተግሳጽ መስጠት አስፈልጎት ነበር። አሦር ይህንን ተግሳጽ ለመስጠት እንደ ይሖዋ “በትር” ሆኖ አገልግሏል። (ኢሳይያስ 7:​17፤ 10:​5, 15) በመጀመሪያ ሰሜናዊው የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት በ740 ከዘአበ በአሦራውያን እጅ ወደቀ። (2 ነገሥት 17:​1-18፤ 18:​9-11) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ የአሦሩ ንጉሥ ሰናክሬም በደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰነዘረ። (2 ነገሥት 18:​13፤ ኢሳይያስ 36:​1) ግዙፉ የአሦር ሠራዊት በምድሪቱ ያገኘውን ሁሉ እየጠራረገ ሲመጣ የይሁዳም ሙሉ በሙሉ መጥፋት አይቀሬ ይመስል ነበር።

3 ይሁን እንጂ አሦር የአምላክን ሕዝብ ከመቅጣት ሥራው አልፎ ዓለምን በቁጥጥሩ ሥር የማስገባት ሕልሙን እውን ለማድረግ መሯሯጥ ጀምሮ ነበር። (ኢሳይያስ 10:​7-11) ይሖዋ በሕዝቡ ላይ የሚፈጸመውን ጭካኔ በዝምታ ያልፈው ይሆን? ብሔሩ ከመንፈሳዊ ሕመሙ የሚፈወስበት መንገድ ይኖር ይሆን? በኢሳይያስ ምዕራፍ 33 ላይ ይሖዋ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እናገኛለን።

የሚበዘብዘውን መበዝበዝ

4, 5. (ሀ) አሦር ምን የተገላቢጦሽ የሆነ ነገር ይገጥመዋል? (ለ) ኢሳይያስ የይሖዋን ሕዝብ በመወከል ምን ጸሎት አቅርቧል?

4 ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “አንተ ሳትበዘበዝ የምትበዘብዝ በአንተም ላይ ሸፍጥ ሳይፈጸም የምትሸፍጥ ወዮልህ! መበዝበዝን እንደተውህ ትበዘበዛለህ፤ ሸፍጥን እንደተውህ ሸፍጥ ይሠሩብሃል።” (ኢሳይያስ 33:​1 NW ) ኢሳይያስ በቀጥታ እየተናገረ ያለው በዝባዥ ስለሆነው ስለ አሦር ነው። ይህ ጠብ አጫሪ ብሔር በሥልጣን ዘመኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት የማይበገር መስሎ ይታይ ነበር። የይሁዳን ከተሞች እያወደመና የይሖዋን ቤት ሃብት ሳይቀር ጠራርጎ በመውሰድ ‘እርሱ ሳይበዘበዝ ሌላውን በዝብዟል።’ ይህንንም ሲያደርግ እርሱን የሚቀጣ ያለ አይመስልም ነበር! (2 ነገሥት 18:​14-16፤ 2 ዜና መዋዕል 28:​21) ይሁን እንጂ አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ይሆናል። ኢሳይያስ “ትበዘበዛለህ” ሲል በድፍረት ተናግሯል። ይህ ትንቢት የታመኑ ለነበሩት ሰዎች ምንኛ የሚያጽናና ነው!

5 በዚያ አስፈሪ ወቅት የታመኑ የይሖዋ አምላኪዎች ለእርዳታ ወደ ይሖዋ ዞር ማለት ነበረባቸው። በመሆኑም ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “አቤቱ፣ ማረን፤ አንተን ተማምነናል፤ ጥዋት ጥዋት [የብርታትና የመደገፊያ ] ክንድ በመከራም ጊዜ ማዳን ሁነን። ከፍጅት ድምፅ ወገኖች ሸሹ፣ በመነሣትህም አሕዛብ ተበተኑ።” (ኢሳይያስ 33:​2, 3) ኢሳይያስ ይሖዋ ከዚያ ቀደም ብዙ ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ሕዝቡን እንዲታደግ መጸለዩ ተገቢ ነበር። (መዝሙር 44:​3፤ 68:​1) ኢሳይያስ ይህን ጸሎት ካቀረበ በኋላ አፍታም ሳይቆይ ይሖዋ ለዚህ ጸሎት ስለሚሰጠው ምላሽ ትንቢት ተናግሯል!

6. አሦር ምን ነገር ይገጥመዋል? ይህስ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?

6 “አንበጣ እንደሚሰበስብ ምርኮአችሁ [የአሦራውያን ምርኮ ] ትሰበሰባለች፣ ኩብኩባም እንደሚዘልል ሰዎች ይዘልሉበታል።” (ኢሳይያስ 33:​4) አውዳሚ ተባይ ለይሁዳ አዲስ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ አሁን ውድመት የሚደርስባቸው የይሁዳ ጠላቶች ናቸው። አሦር አሳፋሪ ሽንፈት ይደርስበትና ወታደሮቹ ከፍተኛ ምርኮ ለይሁዳ ነዋሪዎች ብዝበዛ ትተው ለመሸሽ ይገደዳሉ! በጭካኔው የሚታወቀው አሦር አሁን በተራው ለብዝበዛ መዳረጉ ተገቢ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 37:​36

የዘመናችን አሦር

7.(ሀ) በመንፈሳዊ የታመመችው እስራኤል በዛሬው ጊዜ ከማን ጋር ልትነጻጸር ትችላለች? (ለ) ሕዝበ ክርስትናን ለማጥፋት ለይሖዋ እንደ “በትር” ሆኖ የሚያገለግለው ማን ነው?

7 የኢሳይያስ ትንቢት ለዘመናችን የሚሠራው እንዴት ነው? በመንፈሳዊ ሕመም ተይዞ የነበረው የእስራኤል ሕዝብ ከሃዲ ከሆነችው ሕዝበ ክርስትና ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይሖዋ እስራኤልን ለመቅጣት አሦርን እንደ “በትር” እንደተጠቀመበት ሁሉ ሕዝበ ክርስትናንም ሆነ የቀረውን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ማለትም ‘ታላቂቱ ባቢሎንን’ ለመቅጣት ‘በበትር’ ይጠቀማል። (ኢሳይያስ 10:​5፤ ራእይ 18:​2-8) ይሖዋ እንደ “በትር” የሚጠቀመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራትን ይሆናል። ይህ ድርጅት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሰባት ራስና አሥር ቀንድ ባለው ቀይ አውሬ ተመስሏል።​—⁠ራእይ 17:​3, 15-17

8. (ሀ) ዛሬ ያለው የሰናክሬም አምሳያ ማን ነው? (ለ) የዘመናችን ሰናክሬም ልቡን አደንድኖ የሚነሣው ማንን ለማጥቃት ነው? ውጤቱስ ምን ይሆናል?

8 የዘመናችን አሦር በሐሰት ሃይማኖት ግዛት ውስጥ ሲፈነጭ የሚያቆመው ያለ አይመስልም። ሰይጣን ዲያብሎስ የሰናክሬም ዓይነት ዝንባሌ በመያዝ ጥቃት ለመሰንዘር ልቡን አደንድኖ ይነሳል። ጥቃቱን የሚሰነዝረው ግን ቅጣት በሚገባቸው ከሃዲ ድርጅቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ጭምር ነው። ታላቂቱ ባቢሎንን ከሚጨምረው የሰይጣን ዓለም የወጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከይሖዋ የተቀቡ መንፈሳዊ ልጆች ቀሪዎች ጋር በመተባበር ከይሖዋ መንግሥት ጎን ለመቆም መርጠዋል። “የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን እውነተኛ ክርስቲያኖች ለእርሱ ስለማያጎበድዱ ተቆጥቶ መጠነ ሰፊ ጥቃት ይሰነዝርባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:​4፤ ሕዝቅኤል 38:​10-16) ይህ ጥቃት እጅግ አስፈሪ እንደሚሆን ምንም ባያጠራጥርም የይሖዋ ሕዝብ በፍርሃት የሚርበተበትበት አንዳችም ምክንያት የለም። (ኢሳይያስ 10:​24, 25) አምላክ ‘በመከራ ጊዜ እንደሚያድናቸው’ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። በሰይጣንና በጭፍሮቹ ላይ ጥፋት በማምጣት እጁን ጣልቃ ያስገባል። (ሕዝቅኤል 38:​18-23) በጥንት ዘመን እንደሆነው ሁሉ የአምላክን ሕዝብ ለመበዝበዝ የሚሞክሩ ወገኖች ራሳቸው ይበዘበዛሉ! (ከ⁠ምሳሌ 13:​22ለ ጋር አወዳድር።) የይሖዋ ስም ይቀደሳል። በሕይወት የሚተርፉትም ሰዎች ‘ጥበብንና እውቀትን እንዲሁም ይሖዋን መፍራትን ’ በመፈለጋቸው ይባረካሉ።​—⁠ኢሳይያስ 33:​5, 6ን አንብብ።

ለእምነት የለሾች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

9. (ሀ) የይሁዳ ‘ኃያላንና’ “የሰላም መልእክተኞች” ምን ያደርጋሉ? (ለ) አሦራውያን ለይሁዳ የሰላም ጥሪ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?

9 ይሁንና በይሁዳ ውስጥ ያሉት እምነት የለሽ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ኢሳይያስ በአሦራውያን አማካኝነት ሊመጣ ስላለው ጥፋት የሚያስፈራ መግለጫ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 33:​7ን አንብብ ) የይሁዳ ወታደራዊ ‘ኃያላን ’ በአሦራውያን ግስጋሴ ፍርሃት ውስጥ ወድቀው ይጮኻሉ። ጦርነት ወዳድ ከሆኑት አሦራውያን ጋር ስለ ሰላም እንዲደራደሩ የተላኩት ዲፕሎማቶች ማለትም “የሰላም መልክተኞች ” የገጠማቸው ፌዝና ውርደት ነበር። ተልእኳቸው ባለመሳካቱ አምርረው ያለቅሳሉ። (ከ⁠ኤርምያስ 8:​15 ጋር አወዳድር።) ጨካኝ የሆኑት አሦራውያን ቅንጣት ታክል አያዝኑላቸውም። (ኢሳይያስ 33:​8, 9ን አንብብ።) ከይሁዳ ነዋሪዎች ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ከመጤፍም አይቆጥሩትም። (2 ነገሥት 18:​14-16) አሦራውያን የይሁዳ ‘ከተሞችን ’ አንኳስሰው በማየትና ለሰብዓዊ ሕይወት ደንታ ቢስ በመሆን ‘ይንቋቸዋል።’ ሁኔታው በጣም አስከፊ ከመሆኑ የተነሣ ምድሪቷ ሳትቀር ያለቀሰች ያህል ይሆናል። ሊባኖስ፣ ሳሮን፣ ባሳን እና ቀርሜሎስ ጭምር በጥፋቷ ያዝናሉ።

10. (ሀ) የሕዝበ ክርስትና ‘ኃያላን’ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ የሚታየው እንዴት ነው? (ለ) በሕዝበ ክርስትና የጭንቀት ቀን እውነተኛ ክርስቲያኖችን የሚጠብቃቸው ማን ይሆናል?

10 በቅርቡም ብሔራት በሃይማኖቶች ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ብቅ እንደሚሉ ምንም ጥርጥር የለውም። በሕዝቅያስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ይህንን አጥፊ ኃይል በሰብዓዊ አቅም ለመመከት መሞከር የማይታሰብ ነው። የሕዝበ ክርስትና ‘ኃያላን’ ማለትም ፖለቲከኞቿ፣ የመዋዕለ ነዋይ አማካሪዎቿ ወይም ተሰሚነት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ሊታደጓት አይችሉም። የሕዝበ ክርስትናን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል የተመሠረቱት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ‘ቃል ኪዳኖች’ ወይም ስምምነቶች ይፈርሳሉ። (ኢሳይያስ 28:​15-18) በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥፋቱን ለማስቀረት የሚደረገው ሩጫም ቢሆን አይሰምርም። የሕዝበ ክርስትና ንብረትና መዋዕለ ነዋይ ሲወረስ ወይም ሲወድም የንግድ እንቅስቃሴዎች ይገታሉ። በዚህ ጊዜ ለእርሷ ወዳጃዊ ስሜት ያለው ቢኖር እንኳ አስተማማኝ ርቀት ላይ ቆሞ ሕልፈቷን እያየ ከማልቀስ በስተቀር ማድረግ የሚችለው ነገር አይኖርም። (ራእይ 18:​9-19) እውነተኛው ክርስትና ከሐሰተኛው ጋር ተጠራርጎ ይጠፋ ይሆን? በፍጹም። ይሖዋ ራሱ የሚከተለውን ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “አሁን እነሣለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ አሁን እከበራለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ።” (ኢሳይያስ 33:​10) በመጨረሻው ይሖዋ እንደ ሕዝቅያስ ላሉት የታመኑ ሰዎች ሲል እጁን ጣልቃ በማስገባት የአሦራውያኑን ግስጋሴ ይገታል።​—⁠መዝሙር 12:​5

11, 12. (ሀ) የ⁠ኢሳይያስ 33:​11-14 ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት መቼና እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ቃል ለዛሬው ጊዜ የሚሆን ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?

11 ከሃዲ የሆኑት ሰዎች ይህንን ዓይነት ከለላ እናገኛለን ብለው ሊታመኑ አይችሉም። ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “ገለባን ትፀንሳላችሁ፣ እብቅንም ትወልዳላችሁ፤ እስትንፋሳችሁ የምትበላችሁ እሳት ናት። አሕዛብም እንደ ተቃጠለ ኖራ፣ ተቈርጦም በእሳት እንደ ተቃጠለ እሾህ ይሆናሉ። እናንተ በሩቅ ያላችሁ የሠራሁትን ስሙ፣ እናንተም በቅርብ ያላችሁ ኃይሌን እወቁ። በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች ፈሩ፤ መንቀጥቀጥ ዝንጉዎቹን ያዘ፤ ከምትበላ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ? ለዘላለምም ከምትነድድ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ?” (ኢሳይያስ 33:​11-14) እነዚህ ቃላት ይሁዳ ከአዲሷ ጠላት ከባቢሎን ጋር ስለምትፋጠጥበት ጊዜ የሚናገሩ ናቸው። ከሕዝቅያስ ሞት በኋላ ይሁዳ ተመልሳ በክፉ ሥራዋ ትዘፈቃለች። በቀጣዮቹ ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በይሁዳ የነበረው ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሄዶ መላውን ብሔር በአምላክ የቁጣ እሳት ለመበላት ዳርጎታል።​—⁠ዘዳግም 32:​22

12 ዓመፀኛ የሆኑት ሰዎች የአምላክን ፍርድ ለመቀልበስ ያቀዱትና የወጠኑት ሴራ ሁሉ እንደ እብቅ ሆኖ ቀርቷል። እንዲያውም የብሔሩ የኩራትና የዓመፀኝነት መንፈስ ወደ ጥፋት እንደሚያመሩ የሚያመላክት ይሆናል። (ኤርምያስ 52:​3-11) ክፉዎች ‘እንደተቃጠለ ኖራ’ ፈጽሞ ይጠፋሉ! ዓመፀኞቹ የይሁዳ ነዋሪዎች በላያቸው የሚያንዣብበውን ይህን ጥፋት ሲያስቡት በፍርሃት ይርዳሉ። ይሖዋ ከሃዲ ለሆነችው ይሁዳ የተናገረው ቃል ዛሬ የሕዝበ ክርስትና አባላት ያሉበትን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። የአምላክን ማስጠንቀቂያ የማይቀበሉ ከሆነ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ጊዜ አስፈሪ ነው።

‘በጽድቅ መመላለስ’

13. ‘በጽድቅ መመላለሳቸውን ለሚቀጥሉ’ ሰዎች ምን ቃል ተገብቶላቸዋል? ይህስ በኤርምያስ ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

13 ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ በተቃራኒው እንዲህ ይላል:- “በጽድቅ የሚሄድ [“መመላለሱን የሚቀጥል፣” NW  ] ቅን ነገርንም የሚናገር፣ በሽንገላ የሚገኝ ትርፍን የሚንቅ፣ መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚያራግፍ፣ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮቹን የሚያደናቁር፣ ክፋትንም ከማየት ዓይኖቹን የሚጨፍን ነው። እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፣ ውኃውም የታመነች ትሆናለች።” (ኢሳይያስ 33:​15, 16) ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጊዜ በኋላ እንደገለጸው “ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፣ በደለኞችንም . . . ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።” (2 ጴጥሮስ 2:​9) ኤርምያስ እንዲህ ያለውን የማዳን እጅ አይቷል። በባቢሎን ከበባ ወቅት ሕዝቡ ‘ከፍርሃት ጋር እንጀራ በሚዛን ለመብላት’ ተገድዶ ነበር። (ሕዝቅኤል 4:​16) አንዳንድ ሴቶች የልጆቻቸውን ሥጋ ሳይቀር በልተዋል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:​20) ይሁን እንጂ ይሖዋ ኤርምያስን ተንከባክቦታል።

14. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ‘በጽድቅ መመላለሳቸውን መቀጠል’ የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም እንዲሁ በየዕለቱ የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች በመጠበቅ ‘በጽድቅ መንገድ መመላለሳቸውን መቀጠል’ አለባቸው። (መዝሙር 15:​1-5) ‘ቅን የሆነውን ነገር መናገርና’ ከሐሰት መራቅ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 3:​32) ማጭበርበርና ጉቦ በብዙ አገሮች የተለመደ ነገር ሊሆን ቢችልም ‘በጽድቅ መንገድ ለሚመላለስ’ ሰው ግን አስጸያፊ ነው። በተጨማሪም ክርስቲያኖች በንግድ ሥራዎቻቸው ‘ንጹሕ ሕሊና’ ሊኖራቸውና ሐቀኝነት ከጎደላቸው ወይም ከማጭበርበር ድርጊቶች ለመራቅ ከልብ ሊጥሩ ይገባል። (ዕብራውያን 13:​18፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​9, 10) እንዲሁም አንድ ሰው ‘ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮውን የሚከለክልና ክፋትን ከማየት ዓይኖቹን የሚጨፍን’ ከሆነ በሙዚቃና በመዝናኛ ምርጫው ረገድ ጠንቃቃ ይሆናል። (መዝሙር 119:​37) ይሖዋ በፍርዱ ቀን የእርሱን የአቋም ደረጃ ጠብቀው የሚመላለሱትን አምላኪዎቹን ተንከባክቦ በሕይወት ይጠብቃቸዋል።​—⁠ሶፎንያስ 2:​3

ንጉሣቸውን መመልከት

15. በምርኮ የነበሩትን የታመኑ አይሁዳውያን የሚያበረታቸው የትኛው ተስፋ ነበር?

15 ቀጥሎ ኢሳይያስ ብሩህ ስለሆነው ተስፋ ይጠቅሳል:- “ዓይኖችህ ንጉሥን በውበቱ ያዩታል፤ እነርሱም በሩቅ ያለች ምድርን ያዩአታል። ልብህም:- ጸሐፊ ወዴት አለ? መዛኝስ ወዴት አለ? ግንቦቹንስ የቈጠረ ወዴት አለ? ብሎ የሚያስፈራ ነገር ያስባል። ጨካኝን ሕዝብ፣ ቋንቋው ለማስተዋል ጥልቅ የሆነውንና አንደበቱ ለማስተዋል ጸያፍ የሆነውን ሕዝብ፣ አታይም።” (ኢሳይያስ 33:​17-19) ምንም እንኳ በሩቅ የሚታይ ተስፋ ቢሆንም የታመኑት አይሁዳውያን በባቢሎን በሚቆዩባቸው ረጅም አሥርተ ዓመታት ውስጥ እንዲበረቱ የሚያስችላቸው ወደፊት ስለሚነሳው መሲሐዊ ንጉሥና ስለ መንግሥቱ የተነገረው ተስፋ ይሆናል። (ዕብራውያን 11:​13) መሲሐዊው አገዛዝ እውን ሲሆን የባቢሎናውያን ጭቆና ብዙ ዘመናት ያለፈው የድሮ ትዝታ ብቻ ይሆናል። ከአሦራውያን ጥቃት በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች በደስታ ስሜት “ጨካኞቹ ገዥዎች የት አሉ? ቀረጥ ያስከፈለንና ያስገበረን ማን ነበር?” በማለት ይጠይቃሉ።​—⁠ኢሳይያስ 33:​18 ሞፋት

16. የአምላክ ሕዝብ መሲሐዊውን ንጉሥ ‘ማየት’ የቻለው ከመቼ ጀምሮ ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?

16 ኢሳይያስ ከባቢሎን ምርኮ እንደሚመለሱ ዋስትና የሚሰጥ ቃል የተናገረ ቢሆንም አይሁዳውያን በግለሰብ ደረጃ ይህኛው የትንቢቱ ክፍል ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ሲያገኝ ለመመልከት ትንሣኤ እስኪያገኙ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ዛሬ ያሉት የአምላክ አገልጋዮችስ? የይሖዋ ሕዝብ ከ1914 ወዲህ መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን መንፈሳዊ ውበቱን ተላብሶ ‘ለማየት’ ወይም ለማስተዋል ችለዋል። (መዝሙር 45:​2፤ 118:​22-26) ከዚህም የተነሣ ከሰይጣን ክፉ ሥርዓት ጭቆናና ቁጥጥር ነፃ ወጥተዋል። የአምላክ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ጽዮን ሥር እውነተኛ መንፈሳዊ ደህንነት አግኝተዋል።

17. (ሀ) ጽዮንን በተመለከተ ምን ተስፋ ተሰጥቷል? (ለ) ይሖዋ ስለ ጽዮን የሰጣቸው ተስፋዎች በመሲሐዊው መንግሥት እና በምድር ባሉ ደጋፊዎቹ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?

17 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “የበዓላችንን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤ ዓይኖችህ የሰላም ማደሪያ፣ ካስማውም ለዘላለም የማይነቀል አውታሩም ሁሉ የማይበጠስ፣ የማይወገድ ድንኳን የሆነውን ኢየሩሳሌምን ያያሉ። እግዚአብሔር በዚያ የሰፉ ወንዞችና የመስኖች ስፍራ ሆኖ ከእኛ ጋር በግርማ ይሆናል፤ የሚቀዘፉ መርከቦች [“ሠራዊት፣” NW ] አይገቡባትም፣ ታላላቆችም መርከቦች አያልፉባትም።” (ኢሳይያስ 33:20, 21) ኢሳይያስ የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ሊነቀል ወይም ሊጠፋ እንደማይችል ዋስትና ይሰጠናል። ከዚህም በላይ እንዲህ ያለው ከለላ ዛሬ በምድር ላይ ላሉት የአምላክ መንግሥት ደጋፊዎች ሁሉ እንደሚዘረጋ ግልጽ ነው። በግለሰብ ደረጃ ብዙዎች ከባድ ፈተና ቢደርስባቸውም የአምላክ መንግሥት ተገዥዎችን በቡድን ደረጃ ለማጥፋት የሚደረግ ማንኛውም ጥረት እንደማይሳካ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል። (ኢሳይያስ 54:​17) እንደ መስኖ ያለ ውኃ የሚያልፍበት ጉድጓድ ወይም ቦይ አንድን ከተማ ከጥቃት እንደሚከላከል ሁሉ ይሖዋም ሕዝቡን ይጠብቃል። በእነርሱ ላይ የሚነሣ ማንኛውም ዓይነት ጠላት እንደ ‘መርከበኞች ሠራዊት’ ወይም እንደ ‘ታላላቆች መርከቦች’ እንኳ ኃያል ቢሆን ጥፋት ይገጥመዋል!

18. ይሖዋ የትኛውን ኃላፊነቱን ይወጣል?

18 ይሁንና የአምላክን መንግሥት የሚያፈቅሩ ሰዎች መለኮታዊ ጥበቃ እንደሚያገኙ ይህን ያህል እርግጠኛ መሆን የሚችሉት ለምንድን ነው? ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ያስረዳል:- “እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፣ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፣ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል።” (ኢሳይያስ 33:​22) ይሖዋ የእርሱን ሉዓላዊ የበላይነት አምነው የተቀበሉ ሕዝቦቹን የመጠበቅና የመምራት ኃላፊነቱን ይወጣል። እነዚህ ሰዎች ይሖዋ ሕግ የማውጣት ብቻ ሳይሆን የማስፈጸምም ሥልጣን እንዳለው በመገንዘብ በመሲሐዊው ንጉሥ አማካኝነት ለሚመራው አገዛዙ ራሳቸውን በፈቃደኛነት ያስገዛሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ጽድቅንና ፍትሕን የሚወድድ አምላክ በመሆኑ በልጁ አማካኝነት የሚመራው አገዛዙ ለአምላኪዎቹ ሸክም አይሆንባቸውም። ይልቁንም ከዚህ አገዛዝ በታች በመሆናቸው ‘ራሳቸውን ይጠቅማሉ።’ (ኢሳይያስ 48:​17) ይሖዋ ታማኞቹን በፍጹም አይጥልም።​—⁠መዝሙር 37:​28 NW 

19. ኢሳይያስ በይሖዋ የታመነ ሕዝብ ላይ የሚነሱት ጠላቶች ጥረት እንደማይሳካ የገለጸው እንዴት ነው?

19 ኢሳይያስ የታመነውን የይሖዋ ሕዝብ በጠላትነት ለሚመለከቱት ሰዎች እንዲህ ይላቸዋል:- “ገመዶችህ ላልተዋል፣ ደቀላቸውንም አላጸኑም፣ ሸራውንም መዘርጋት አልቻሉም። በዚያን ጊዜ የብዙ ምርኮ ብዝበዛ ተከፈለ፤ አንካሶች እንኳ ብዝበዛውን በዘበዙ።” (ኢሳይያስ 33:​23) ወደ አምላክ ሕዝብ የሚቀርብ ጠላት ሁሉ ገመዱ እንደላላ፣ ደቀሉ እንደሚነቃነቅና ሸራውን እንዳልዘረጋ የጦር መርከብ በይሖዋ ፊት ውጤት አልባና አቅመ ቢስ ይሆናል። የአምላክ ጠላቶች በሚጠፉበት ጊዜ ብዙ ብዝበዛ ስለሚኖር የአካል ጉዳተኞች እንኳ ሳይቀሩ በብዝበዛው ይካፈላሉ። እንግዲያው ይሖዋ በመጪው ‘ታላቅ መከራ’ ወቅት በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በጠላቶቹ ላይ ድል እንደሚቀዳጅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠ራእይ 7:​14

ፈውስ

20. የአምላክ ሕዝብ ምን ዓይነት ፈውስ ያገኛል? መቼ?

20 ይህኛው የኢሳይያስ ትንቢት ክፍል የሚደመደመው ልብን ደስ በሚያሰኝ ተስፋ ነው:- “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም፣ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።” (ኢሳይያስ 33:​24) ኢሳይያስ እዚህ ላይ እየተናገረለት ያለው ሕመም ከኃጢአት ወይም ‘ከበደል’ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በዋነኝነት የሚያመለክተው መንፈሳዊ ሕመምን ነው። በእነዚህ ቃላት የመጀመሪያ ደረጃ ፍጻሜ መሠረት ይሖዋ ብሔሩ ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ከወጣ በኋላ ከመንፈሳዊ ሕመሙ እንደሚፈወስ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 35:​5, 6፤ ኤርምያስ 33:​6፤ ከ⁠መዝሙር 103:​1-5 ጋር አወዳድር።) ከምርኮ ተመላሾቹ አይሁዳውያን የቀድሞ ኃጢአታቸው ይቅር ስለተባለላቸው እውነተኛውን አምልኮ በኢየሩሳሌም መልሰው ያቋቁማሉ።

21. ዛሬ ያሉ የይሖዋ አምላኪዎች መንፈሳዊ ፈውስ የሚያገኙት በምን መንገዶች ነው?

21 ይሁንና የኢሳይያስ ትንቢት በዘመናችንም ተፈጻሚነት ይኖረዋል። ዛሬ ያለው የይሖዋ ሕዝብም መንፈሳዊ ፈውስ አግኝቷል። ነፍስ አትሞትም፣ ሥላሴ እና የሲኦል እሳት የሚሉትን ከመሳሰሉት የሐሰት ትምህርቶች ነፃ ወጥተዋል። ከሥነ ምግባር ብልግና እንዲላቀቁና ጥሩ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ የሚረዳቸውን የግብረገብ መመሪያ ያገኛሉ። እንዲሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምሥጋና ይግባውና በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ኖሯቸው ንጹህ ሕሊና ለማግኘት በቅተዋል። (ቆላስይስ 1:​13, 14፤ 1 ጴጥሮስ 2:​24፤ 1 ዮሐንስ 4:​10) ይህ መንፈሳዊ ፈውስ አካላዊ ጥቅምም አለው። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች ከፆታ ብልግናና ከትንባሆ ውጤቶች በመራቃቸው በፆታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎችና ከአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ተጠብቀዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​18፤ 2 ቆሮንቶስ 7:​1

22, 23. (ሀ) ኢሳይያስ 33:​24 ወደፊት ምን ታላቅ ፍጻሜ ይኖረዋል? (ለ) ዛሬ ያሉ እውነተኛ አምላኪዎች ቁርጥ ውሳኔ ምንድን ነው?

22 ከዚህም በተጨማሪ በ⁠ኢሳይያስ 33:​24 ላይ የሚገኙት ቃላት ከአርማጌዶን በኋላ በሚኖረው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥም ታላቅ ፍጻሜ ይኖራቸዋል። የሰው ልጅ በመሲሐዊው መንግሥት አገዛዝ ሥር ከሚያገኘው መንፈሳዊ ፈውስ በተጨማሪ ታላቅ አካላዊ ፈውስ ያገኛል። (ራእይ 21:​3, 4) የሰይጣን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ምድር ሳለ ያከናወናቸውን ዓይነት ተዓምራት በምድር ዙሪያ እንደሚከናወኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ዕውራን ያያሉ፣ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፣ አንካሳውም በእግሮቹ ይራመዳል! (ኢሳይያስ 35:​5, 6) ይህም ከታላቁ መከራ በሕይወት የተረፉት ሰዎች በሙሉ ምድርን ወደ ገነትነት በመለወጡ ታላቅ ሥራ መካፈል የሚችሉበትን አጋጣሚ ይከፍታል።

23 ከጊዜ በኋላ ትንሣኤ ሲጀምር ደግሞ ከሞት የሚነሱት ሰዎች ጥሩ ጤና ኖሯቸው እንደሚነሱ ምን አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ቤዛው ይበልጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሄድ የሰውን ልጅ ፍጽምና ደረጃ ላይ እስከማድረስ ድረስ ተጨማሪ አካላዊ ጥቅሞች ይኖሩታል። ጻድቃን ‘በሕይወት ኖረዋል’ ሊባል የሚችለው በዚህ ጊዜ ነው። (ራእይ 20:​5, 6) በዚያ ጊዜ በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ ‘ታምሜአለሁ የሚል አይኖርም።’ እንዴት አስደሳች ተስፋ ነው! ዛሬ ያሉ እውነተኛ አምላኪዎች በሙሉ ቁርጥ ውሳኔያቸው የዚህን ትንቢት ፍጻሜ ከሚያጣጥሙት ሰዎች መካከል መገኘት መሆን ይኖርበታል!

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 344 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢሳይያስ በትምክህት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል

[በገጽ 353 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለቤዛዊ መሥዋዕቱ ምስጋና ይግባውና የይሖዋ ሕዝብ በእርሱ ፊት ንጹህ አቋም ለማግኘት በቅቷል

[በገጽ 354 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአዲሱ ዓለም ውስጥ ታላቅ አካላዊ ፈውስ ይከናወናል