በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ባቢሎን ወደቀች!’

‘ባቢሎን ወደቀች!’

ምዕራፍ አሥራ ሰባት

‘ባቢሎን ወደቀች!’

ኢሳይያስ 21:​1-17

1, 2. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ጭብጥ ምንድን ነው? ይሁን እንጂ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ያለው አስፈላጊ የሆነ ንዑስ ጭብጥ ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ባቢሎን መውደቅ የሚናገረውን ጭብጥ የሚያዳብረው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጉልህ ዜማና አጠቃላይ ስልቱን የሚያጠናክሩ ንዑስ ዜማዎች ካሉት ታላቅ የሙዚቃ ሥራ ጋር ሊመሳሰል ይችል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ዋና ጭብጥ አለው። ይህም በመሲሐዊው ንጉሣዊ መስተዳድር አማካኝነት የይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ነው። ተደጋግመው የሚጠቀሱ ሌሎች አስፈላጊ ጭብጦችም አሉት። ከእነዚህ መካከል አንዱ የባቢሎን መውደቅ ነው።

2 ይህ ጭብጥ በመጀመሪያ በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 13 እና 14 ላይ ተጠቅሷል። ከዚያም በኢሳይያስ ምዕራፍ 21 እንዲሁም በኢሳይያስ ምዕራፍ 44 እና 45 ላይ በድጋሚ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ ኤርምያስ ይህንኑ ጭብጥ ያሰፋው ሲሆን የራእይ መጽሐፍ ደግሞ ታላቁ መደምደሚያው ምን እንደሚመስል ገልጿል። (ኤርምያስ 51:​60-64፤ ራእይ 18:​1–19:​4) መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር የሚያጠና እያንዳንዱ ሰው በአምላክ ቃል ውስጥ ስለሚገኘው ስለዚህ በጣም አስፈላጊ የሆነ ንዑስ ጭብጥ ሊያስብ ይገባል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 21 በትንቢት የተነገረውን የዚችን ታላቅ የዓለም ኃይል ውድቀት በተመለከተ አንዳንድ አስገራሚ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ በመሆኑ በዚህ ረገድ ጠቃሚ ድርሻ አለው። ወደ በኋላ ኢሳይያስ ምዕራፍ 21 ውስጥ ጎላ ብሎ የተገለጸውን ሌላ በጣም አስፈላጊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ እንመረምራለን። ይህን ጭብጥ መመርመራችን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ልናሳየው ስለሚገባን ትጋት እንድናስብ ያነሳሳናል።

“ከባድ ራእይ”

3. ባቢሎን ‘በባሕር አጠገብ ያለች ምድረ በዳ’ የተባለችው ለምንድን ነው? ይህስ ስያሜ የወደፊት ዕጣዋን በተመለከተ ምን የሚጠቁመው ነገር አለ?

3 ኢሳይያስ ምዕራፍ 21 የሚጀምረው ስለ አንድ መዓት በማስታወቅ ነው:- “በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ሸክም። ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚወጣ፣ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረ በዳ ይወጣል።” (ኢሳይያስ 21:​1) ባቢሎን በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ ተንሠራፍታና ምሥራቃዊ ግዛቷን በሁለቱ ታላላቅ ወንዞች ማለትም ከኤፍራጥስና ከጢግሮስ መካከል አድርጋ ተቀምጣለች። በእርግጥ ከባሕሩ ትንሽ ትርቃለች። ታዲያ ‘በባሕር አጠገብ ያለ ምድረ በዳ’ የተባለችው ለምንድን ነው? ባቢሎን ያለችበት አካባቢ በየዓመቱ በውኃ መጥለቅለቅ ምክንያት ሰፊ ረግረጋማ “ባሕር” ይፈጥር ስለነበረ ነው። ይሁን እንጂ ባቢሎናውያን መከላከያ ግድብ፣ የውኃውን ፍሰት የሚቆጣጠሩበት መተላለፊያና ቦይ መሥራትን የሚጠይቅ ውስብስብ የሆነ ግንባታ በማከናወን ይህን የውኃ ምድረ በዳ ተቆጣጥረውታል። ይህንንም ውኃ ከተማዋን ከጥቃት ለመከላከል በጥበብ ተጠቅመውበታል። ሆኖም ባቢሎንን ከመለኮታዊው ፍርድ ሊያስጥላት የሚችል ሰብዓዊ ጥበብ አይኖርም። መጀመሪያም ምድረ በዳ ነበረች አሁን ተመልሳ ምድረ በዳ ትሆናለች። አንዳንድ ጊዜ በደቡብ ከሚገኘው ምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ይነፍስ እንደነበረው አስከፊ ዓውሎ ነፋስ ጥፋት ወደ እርሷ በፍጥነት በመገስገስ ላይ ነው።​—⁠ከ⁠ዘካርያስ 9:​14 ጋር አወዳድር።

4. በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ስለ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚናገረው ራእይ ‘ከውኃዎች’ እና ‘ከምድረ በዳ’ ጋር የተያያዘው እንዴት ነው? ‘ውኃዎቹስ’ ምን ያመለክታሉ?

4 በዚህ መጽሐፍ 14ኛ ምዕራፍ ውስጥ እንዳየነው የጥንቷ ባቢሎን ዘመናዊ አምሳያ አለቻት። እሷም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት የሆነችው “ታላቂቱ ባቢሎን” ነች። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ታላቂቱ ባቢሎንም ‘ከምድረ በዳ’ እና ‘ከብዙ ውኃዎች’ ጋር ተያይዛ ተገልጻለች። ሐዋርያው ዮሐንስ ታላቂቱ ባቢሎንን እንዲያይ ወደ በረሃ ተወስዷል። ‘ወገኖችንና ብዙ ሰዎችን አሕዛብን፣ ቋንቋዎችንም’ በሚያመለክቱ “ውኃዎች” ላይ እንደ ተቀመጠች ተነግሮታል። (ራእይ 17:​1-3, 5, 15) እስከ ዛሬ ድረስ የሕዝብ ድጋፍ ለሐሰት ሃይማኖት ሕልውና ቁልፍ ሚና ሲጫወት ቢቆይም በመጨረሻ ግን እነዚህ “ውኃዎች” ሊያስጥሏት አይችሉም። እንደ ጥንቷ አምሳያዋ ባዶ፣ የተጣለች እና ባድማ ትሆናለች።

5. ባቢሎን “ሸፍጠኛ” እና “አጥፊ” የሚል ስም ለማትረፍ የበቃችው እንዴት ነው?

5 በኢሳይያስ ዘመን ባቢሎን ገና ኃያል መንግሥት አልሆነችም ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ጊዜው ሲደርስ ሥልጣንዋን አላግባብ እንደምትጠቀምበት አስቀድሞ ተመልክቶ ነበር። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ከባድ ራእይ ተነገረኝ፤ ሸፍጠኛው ይሸፍጣል፣ በዝባዡም ይበዘብዛል።” (ኢሳይያስ 21:​2ሀ NW) በእርግጥም ደግሞ ባቢሎን ይሁዳን ጨምሮ ድል አድርጋ የያዘቻቸውን ብሔራት ታጠፋለች እንዲሁም ሸፍጥ ትፈጽምባቸዋለች። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ይበዘብዛሉ፣ ቤተ መቅደስዋን ይዘርፋሉ፣ ሕዝብዋንም በምርኮ ወደ ባቢሎን ያግዛሉ። በዚያም እነዚህ ምስኪን ምርኮኞች ሸፍጥ ይፈጸምባቸዋል፤ በእምነታቸው ይፌዝባቸዋል እንዲሁም ወደ ትውልድ አገራቸው የመመለስ ተስፋቸው ሁሉ ይጨልምባቸዋል።​—⁠2 ዜና መዋዕል 36:​17-21፤ መዝሙር 137:​1-4

6. (ሀ) ይሖዋ መቋጫ የሚያበጅለት ትካዜ የትኛው ነው? (ለ) ባቢሎን ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ በትንቢት የተነገረላቸው ብሔራት የትኞቹ ናቸው? ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

6 በእርግጥም ባቢሎን ከፊቷ አስቸጋሪ ጊዜ እንደሚጠብቃት የሚጠቁመው ይህ “ከባድ ራእይ” ሲያንሳት ነው። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ኤላም ሆይ፣ ውጪ፤ ሜዶን ሆይ፣ ክበቢ፤ ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ።” (ኢሳይያስ 21:​2ለ) በዚህች ሸፍጠኛ ግዛት ሲጨቆኑ የነበሩ ሁሉ እፎይ ይላሉ። በመጨረሻ ትካዜያቸው ሁሉ ያበቃል! (መዝሙር 79:​11, 12) ይህን እፎይታ የሚያገኙት እንዴት ነው? ኢሳይያስ በባቢሎን ላይ ጥቃት የሚከፍቱትን ሁለት ብሔራት ስም ጠቅሷል። እነርሱም ኤላምና ሜዶን ናቸው። ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ ማለትም በ539 ከዘአበ የፋርሱ ቂሮስ የፋርስንና የሜዶንን ጥምር ኃይል በመምራት በባቢሎን ላይ ይዘምታል። ከ539 ከዘአበ ትንሽ ቀደም ብሎ የፋርስ ንጉሠ ነገሥታት የኤላምን ግዛት ቢያንስ በከፊል በቁጥጥራቸው ሥር ስለሚያስገቡት የፋርስ ሠራዊት ኤላማውያንንም የሚጨምር ይሆናል። *

7. ኢሳይያስ ያየው ራእይ የነካው እንዴት ነው? ይህስ ምን መልእክት አለው?

7 ይህ ራእይ በእርሱ ላይ የነበረውን ውጤት በተመለከተ ኢሳይያስ የሰጠውን መግለጫ ልብ በል:- “ስለዚህ ወገቤ ሕመም ተሞላ፤ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፤ ከሕመሜ የተነሣ አልሰማም፣ ከድንጋጤም የተነሣ አላይም። ልቤ ተንበደበደ፣ ድንጋጤ አስፈራኝ፣ ተስፋ ያደረግሁትም ድንግዝግዝታ መንቀጥቀጥ ሆነብኝ።” (ኢሳይያስ 21:​3, 4) ነቢዩ ቀኑ ድንግዝግዝ የሚልበትን ጊዜ ለማሰላሰል የሚያመች ፀጥ ያለ ጊዜ በመሆኑ ይወድደው የነበረ ይመስላል። አሁን ግን ያንን ውበቱን አጥቶ የፍርሃት፣ የሕመምና የመንቀጥቀጥ ጊዜ ሆኖበታል። ምጥ እንደያዛት ሴት ጭንቀቱ በዝቷል። ልቡም ‘ተንበድብዷል።’ አንድ ምሁር “ልቤ ተንበደበደ” የሚለው ይህ አገላለጽ “የስሜት መታወክንና ጤናማ ያልሆነ የልብ ምትን” እንደሚያመለክት በመግለጽ “ልቤ ድው ድው አለ” ብለው ተርጉመውታል። ይህን ያህል የተጨነቀው ለምንድን ነው? የኢሳይያስ ስሜት ትንቢታዊ መልእክት ያለው ይመስላል። በ539 ከዘአበ ጥቅምት 5/6 ምሽት ላይ ባቢሎናውያን ተመሳሳይ ሽብር ላይ ይወድቃሉ።

8. በትንቢት በተነገረው መሠረት ጠላቶቻቸው ከቅጥሩ ውጭ ሠፍረው የነበረ ቢሆንም ባቢሎናውያኑ ምን እያደረጉ ነበር?

8 በዚያች የቁርጥ ቀን ምሽት ባቢሎናውያን ሽብር ይሆናል ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ምንም ነገር አይኖርም። ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ማዕዱን ያዘጋጃሉ፣ ምንጣፉንም ይዘረጋሉ፣ ይበሉማል፣ ይጠጡማል።” (ኢሳይያስ 21:​5ሀ) አዎን፣ ዕብሪተኛው ንጉሥ ብልጣሶር ትልቅ ግብዣ አዘጋጅቷል። በሺህ ለሚቆጠሩት መኳንንቱ እንዲሁም በጣም ብዙ ለሆኑት ሚስቶቹና ቁባቶቹ የሚሆን አዳራሽ ተነጥፏል። (ዳንኤል 5:​1, 2) እነዚህ በፈንጠዝያ የተጠመዱ ሰዎች የጠላት ሠራዊት ከቅጥሩ ውጭ እንዳለ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ከተማቸው ፈጽሞ የምትበገር እንዳልሆነች ተሰምቷቸዋል። ግዙፍ ቅጥሯና ጥልቅ የሆነው የውኃ ቦይ ከተማቸው በጠላት እጅ እንዳትወድቅ ይከላከላል። ስፍር ቁጥር የሌላቸው አማልክቶቿስ የት ሄደው። ስለዚህ “ይበሉማል፤ ይጠጡማል።” ብልጣሶር የጠጣው መጠጥ ራሱ ላይ ወጣ። የሰከረው ግን እርሱ ብቻ አይመስልም። ቀጥሎ ካሉት የኢሳይያስ ትንቢታዊ ቃላት መረዳት እንደሚቻለው ከፍተኛ ባለ ሥልጣናቱ ከነበሩበት የስካር ድንዛዜ የሚያባንናቸው ነገር አስፈልጎ ነበር።

9. ‘ጋሻውን መቀባት’ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

9 “እናንተ መሳፍንት ሆይ፣ ተነሡ፣ ጋሻውን አዘጋጁ [“ቀቡ፣” NW ]።(ኢሳይያስ 21:​5ለ) ፈንጠዝያው ድንገት ተቋረጠ። መሳፍንቱ ለመንቃት ተገደዱ! አረጋዊው ነቢይ ዳንኤል ተጠርቶ ሲመጣ ይሖዋ፣ ኢሳይያስ በተናገረው መሠረት የባቢሎኑን ንጉሥ ብልጣሶርን እንዴት ሽብር ላይ እንደጣለው በግልጽ ተመልክቷል። የሜዶን፣ የፋርስና የኤላማውያን ጥምር ኃይል የከተማዋን መከላከያ ደርምሶ ሲገባ የንጉሡ መኳንንት በግራ መጋባት ስሜት ተዋጡ። ባቢሎን ቅጽበታዊ አወዳደቅ ወደቀች! ይሁንና “ጋሻውን ቀቡ” የሚለው አነጋገር ምንን የሚያመለክት ነው? የአንድ ብሔር ንጉሥ ምድሪቱን የሚከላከልና የሚጠብቅ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ንጉሡን እንደ ጋሻ አድርጎ የሚጠቅስበት ጊዜ አለ። * (መዝሙር 89:​18 NW ) በመሆኑም ይህ የኢሳይያስ ጥቅስ አዲስ ንጉሥ እንደሚያስፈልግ እየተነበየ እንዳለ እሙን ነው። ለምን? ምክንያቱም ብልጣሶር “በዚያ ሌሊት” ተገድሏል። በዚህ መንገድ ‘ጋሻውን መቀባት’ ወይም አዲስ ንጉሥ መሾም አስፈልጎ ነበር።​—⁠ዳንኤል 5:​1-9, 30

10. ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ሸፍጠኛ ስለሆነችው ባቢሎን ከተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ ምን ማጽናኛ ማግኘት ይችላሉ?

10 እውነተኛውን አምልኮ የሚያፈቅሩ ሁሉ ከዚህ ዘገባ ማጽናኛ ያገኛሉ። የዘመናችን ባቢሎን ማለትም ታላቂቱ ባቢሎንም እንደ ጥንቷ አምሳያዋ ሸፍጠኛና አጥፊ ነች። ዛሬም ቢሆን የሃይማኖት መሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እንዲታገድ ወይም ስደት እንዲደርስባቸው አለዚያም የቅጣት ያህል የከበደ ቀረጥ እንዲጣልባቸው ለማድረግ ያሴራሉ። ይሁን እንጂ ይህ ትንቢት እንደሚያሳስበን ይሖዋ እንዲህ ያለውን የጥፋት ሥራ ሁሉ ይመለከታል። ደግሞም ሳይቀጣ አያልፍም። እርሱን እንወክላለን እያሉ የማይገባ ድርጊት የሚሠሩትንና የአምላክን ሕዝብ የሚያንገላቱትን ሃይማኖቶች በሙሉ ወደ ፍጻሜያቸው ያመጣቸዋል። (ራእይ 18:​8) ይህ ሊሆን ይችላልን? እምነታችንን ለመገንባት የጥንቷን ባቢሎንና የዘመናዊ አምሳያዋን ውድቀት በተመለከተ እርሱ የተናገራቸው ማስጠንቀቂያዎች እንዴት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ብቻ መመልከቱ በቂ ይሆናል።

‘ወደቀች!’

11. (ሀ) የአንድ ጉበኛ ኃላፊነት ምንድን ነው? ዛሬስ እንደ ጉበኛ ሆኖ ሲሠራ የቆየው ማን ነው? (ለ) የአህዮቹና የግመሎቹ የጦር ሠረገሎች ማንን የሚወክሉ ናቸው?

11 ቀጥሎ ይሖዋ ነቢዩን ያነጋግረዋል። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ጌታ እንዲህ ብሎኛልና:- ሂድ ጉበኛም አቁም፣ የሚያየውንም ይናገር።” (ኢሳይያስ 21:​6) እነዚህ ቃላት የዚህን ምዕራፍ ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ ጭብጥ ያስተዋውቁናል። ይህም ጠባቂውን ወይም ጉበኛውን የሚመለከት ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ንቁ” በማለት አጥብቆ ስላሳሰበ ይህ ዛሬ ያሉትን እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። “ታማኝና ልባም ባሪያ” የአምላክን የፍርድ ቀን መቅረብና በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ ያሉትን አደገኛ ሁኔታዎች በተመለከተ ስላየው ነገር ከማስጠንቀቅ ቦዝኖ አያውቅም። (ማቴዎስ 24:​42, 45-47) ኢሳይያስ በራእይ የተመለከተው ጉበኛ የሚያየው ነገር ምንድን ነው? “ባለ ሁለት የጦር ፈረስ ሠረገላ፣ የአህዮች የጦር ሰረገላ፣ የግመሎች የጦር ሰረገላ ተመለከተ። ይህንንም ባየ ጊዜ በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተከታተለ።” (ኢሳይያስ 21:​7 NW ) እዚህ ላይ የተጠቀሱት የጦር ሰረገሎች እያንዳንዳቸው በሰልፍ ሆነው ለጦር እንደተዘጋጁ ፈረሶች በፍጥነት የሚገሰግሱ ሰረገሎችን ረድፍ የሚያመለክቱ ይመስላል። የአህዮቹና የግመሎቹ የጦር ሰረገሎች ይህን ጥቃት ለመሰንዘር አንድ ሆነው የሚዘምቱትን የሜዶንና የፋርስ ኃይሎች የሚያመለክት ተስማሚ መግለጫ ነው። ከዚህም በላይ የፋርስ ሠራዊት አህዮችንና ግመሎችን ለጦርነት ይጠቀም እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል።

12. ኢሳይያስ በራእይው ውስጥ የተመለከተው ጉበኛ ምን ዓይነት ባሕርይ አሳይቷል? ዛሬስ እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የሚገባቸው እነማን ናቸው?

12 ስለዚህ ጉበኛው እንደሚከተለው ሲል ሪፖርት ለማድረግ ተገድዷል። “ጌታ ሆይ፣ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፣ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ፤ እነሆም፣ በፈረሶች የሚቀመጡ፣ ሁለት ሁለት ሁነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ [“እንደ አንበሳ፣” NW ] ጮኸ ” (ኢሳይያስ 21:​8, 9ሀ) በራእይ ውስጥ የታየው ጉበኛ “እንደ አንበሳ” በድፍረት ጮዃል። እንደ ባቢሎን ባለ የማይበገር ብሔር ላይ እንዲህ ያለ የፍርድ መልእክት ማወጅ በእርግጥም ድፍረት ይጠይቃል። ከዚሁ ጋር ጽናትም አስፈላጊ ነው። ጉበኛው ምንም ትጋቱ ሳይቀንስ ዘወትር ቀንና ሌሊት በማማው ላይ ይቆማል። በተመሳሳይም በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ያለው የጉበኛው ክፍል ድፍረት እና ጽናት አስፈልጎታል። (ራእይ 14:​12) ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች እነዚህ ባሕርያት ያስፈልጓቸዋል።

13, 14. (ሀ) የጥንቷ ባቢሎን ምን ገጥሟታል? ጣዖቶቿስ የደቀቁት በምን መንገድ ነው? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን ተመሳሳይ ውድቀት የደረሰባት እንዴትና መቼ ነው?

13 ኢሳይያስ በራእይ የተመለከተው ጉበኛ የጦር ሰረገሎች ሲገሰግሱ ተመልክቷል። ዜናው ምንድን ነው? “እርሱም መልሶ:- ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፣ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ።” (ኢሳይያስ 21:​9ለ) እንዴት የሚያስፈነድቅ ሪፖርት ነው! የአምላክን ሕዝቦች ያጠፋችው ይህች ሸፍጠኛ መጨረሻዋ ውድቀት ሆኗል! * ሆኖም የባቢሎን የተቀረጹ ምስሎችና ጣዖታት የደቀቁት በምን መንገድ ነው? የሜዶ ፋርስ ወራሪዎች ወደ ባቢሎን ቤተ መቅደሶች በመግባት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ጣዖታት ይከሰክሷቸው ይሆን? የለም፣ እንደዚያ ማድረግ አያስፈልጋቸውም። የባቢሎን ጣዖታት ከተማዋን መከላከል የማይችሉ አቅመ ቢስ መሆናቸው መጋለጡ ራሱ እንደ ደቀቁ ያህል ነው። ባቢሎን የአምላክን ሕዝቦች መጨቆኗ ሲያከትም መውደቋ እውን ይሆናል።

14 ስለ ታላቂቱ ባቢሎንስ ምን ማለት ይቻላል? በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአምላክ ሕዝቦች የሚጨቆኑበትን ሴራ በመጠንሰስ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በተሳካ መንገድ በግዞት ይዛቸው ነበር። የስብከት ሥራቸው ሙሉ በሙሉ ተገትቶ ነበር ለማለት ይቻላል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ ኃላፊነት የነበራቸው ሌሎች ወንድሞች በሐሰት ክስ ወኅኒ ወርደው ነበር። ይሁን እንጂ በ1919 ሁኔታው በአስገራሚ ሁኔታ ተቀለበሰ። የታሠሩት ኃላፊዎች ተፈቱ፣ የዋናው መሥሪያ ቤት ቢሮዎችም ተከፍተው ሥራ ጀመሩ፣ የስብከቱም ሥራ እንደገና ተንቀሳቀሰ። በዚህ መልኩ ታላቂቱ ባቢሎን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የነበራት የበላይነት ሲያከትም መውደቋ እውን ሆኗል። * አንድ መልአክ በ⁠ኢሳይያስ 21:​9 ላይ ያሉትን ቃላት በመጠቀም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ይህንን የባቢሎን ውድቀት ሁለት ጊዜ አውጆአል።​—⁠ራእይ 14:​8፤ 18:​2

15, 16. የኢሳይያስ ወገኖች ‘እንደተወቃ’ ያህል የሆኑት እንዴት ነው? ኢሳይያስ ለእነርሱ ከነበረው ስሜት ምን እንማራለን?

15 ኢሳይያስ ይህን ትንቢታዊ መልእክት የሚደመድመው ስለ ገዛ ሕዝቡ የተሰማውን ሐዘን በመግለጽ ነው። እንዲህ ይላል:- “እናንተ በአውድማዬ ላይ የተወቃችሁ የአውድማዬ ልጆች ሆይ፣ ከእስራኤል አምላክ ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሰማሁትን ነገርኋችሁ።” (ኢሳይያስ 21:​10) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መውቃት ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ለአምላክ ሕዝብ የሚሰጠውን ተግሳጽና የሚካሄድበትን የማጥራት ሥራ ነው። የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ‘የአውድማ ልጆች’ እንደሚሆኑ ተገልጿል። አውድማው ኃይል መጠቀምን በሚጠይቅ መንገድ ስንዴው ከገለባው ተለይቶ ተፈላጊው የተጣራ ዘር ብቻ የሚቀርበት መሬት ነው። ኢሳይያስ ለሕዝቡ በተሰጠው ተግሳጽ መደሰቱ አልነበረም። እንዲያውም ወደፊት ‘የአውድማው ልጆች’ ለሚሆኑት ለእነዚህ ሰዎች አዝኖላቸዋል። ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ መላ ሕይወታቸውን የሚገፉት በባዕድ አገር ምርኮኞች ሆነው ነው።

16 ይህ ለሁላችንም ጥሩ ማሳሰቢያ ሊሆነን ይችላል። ዛሬም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ኃጢአት ለፈጸሙ ሰዎች አያዝኑ ይሆናል። ኃጢአት ሠርተው ተግሳጽ የሚሰጣቸውም ብዙውን ጊዜ ተግሳጹን ለመቀበል ያንገራግሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕዝቡን የሚቀጣው እነርሱን ለማጥራት ብሎ እንደሆነ ካሰብን የሚሰጠንን ተግሳጽም ሆነ ተግሳጹን በትሕትና የሚቀበሉትን ሌሎች ሰዎች አናቃልልም እንዲሁም ተግሳጹን ለመቀበል አናንገራግርም። አምላካዊ ተግሳጽ ሲሰጠን የአምላክ የፍቅር መግለጫ እንደሆነ በማሰብ እንቀበለው።​—⁠ዕብራውያን 12:​6

ጉበኛውን መጠየቅ

17. ኤዶም “ዱማ” ተብላ መጠራቷ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?

17 በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 21 ውስጥ የሚገኘው ትንቢታዊ መልእክት የጉበኛውን ሁኔታ ይገልጻል። እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “ስለ ኤዶምያስ [“ዱማ፣” NW ] የተነገረ ሸክም። አንዱ ከሴይር:- ጉበኛ ሆይ፣ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ጉበኛ ሆይ፣ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ብሎ ጠራኝ።” (ኢሳይያስ 21:​11) ዱማ የምትገኘው የት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በዚህ ስም የሚጠሩ በርካታ ከተሞች እንደነበሩ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ መጥቀስ የተፈለገው ከእነዚህ ከተሞች መካከል የትኛውንም አይደለም። ዱማ በሴይር የምትገኝ ከተማ አልነበረችም። ሴይር የኤዶም ሌላ ስሟ ነው። ይሁን እንጂ “ዱማ” ማለት “ዝምታ” ማለት ነው። ስለዚህ በፊተኛው ሸክም ላይ እንደተገለጸው ለአካባቢው የተሰጠው ስም የወደፊት ዕጣ ፈንታውን የሚጠቁም ነው። ለረጅም ጊዜ የአምላክ ሕዝብ ጠንቀኛ ጠላት ሆና የኖረችው ኤዶም መጨረሻዋ ዝምታ ይሆናል። ይህም ወደ መቃብር በመውረዷ የሚከተላት ዝምታ ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን አንዳንዶች ለማወቅ ባላቸው ጉጉት ተነሣስተው ስለ ወደፊቱ ጊዜ ይጠይቃሉ።

18. “ይነጋል ደግሞም ይመሻል” የሚለው ቃል በጥንቷ ኤዶም ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

18 የኢሳይያስ መጽሐፍ በተጻፈበት ዘመን ኤዶም የምትገኘው ኃያል በነበረው የአሦር ሠራዊት ጎዳና ላይ ነበር። በኤዶም የነበሩ አንዳንዶች የጭቆናው ሌሊት አልፎ ቀን የሚወጣላቸው መቼ እንደሆነ ለማወቅ ጓጉተዋል። መልሱ ምን ይሆናል? “ጉበኛውም:- ይነጋል ደግሞም ይመሻል . . . አለ።” (ኢሳይያስ 21:​12ሀ ) ኤዶም አይቀናትም። የንጋት ጮራ ከአድማስ ባሻገር ይፈነጥቃል። ይሁን እንጂ እንዲሁ የሚያጓጓ ብቻ ነው እንጂ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ አይሆንም። ወዲያው የንጋቱን ጮራ ተከትሎ ምሽት ማለትም ጭቆና ያለበት የጨለማ ጊዜ ይመጣል። የኤዶምን የወደፊት ዕጣ የሚያሳይ እንዴት ተስማሚ መግለጫ ነው! የአሦራውያን ጭቆና ያበቃል ሆኖም ባቢሎን በአሦር እግር ተተክታ የዓለም ኃይል በመሆን የኤዶምን አብዛኛውን ክፍል ትደመስሳለች። (ኤርምያስ 25:​17, 21፤ 27:​2-8) ይህ ዑደት ይደጋገማል። የባቢሎናውያን ጭቆና በፋርሳውያን ከዚያም በግሪካውያን ይተካል። ከዚያም ኤዶማዊ ዝርያ ያለው ሄሮድስ በኢየሩሳሌም ሥልጣን በሚይዝበት የሮማውያን ዘመን ጥቂት ‘የንጋት’ ጊዜ ይኖራል። ይሁን እንጂ ይህ ‘የንጋት ጊዜ’ ብዙ አይዘልቅም። በመጨረሻ ኤዶም ከታሪክ ገጾች ትደመሰስና እስከ ወዲያኛው በዝምታ ትዋጣለች። በዚህ ጊዜ ዱማ የሚለው ስም ፍጹም ተስማሚ ይሆናል።

19. ጉበኛው “ትጠይቁ ዘንድ ብትወዱ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ” ሲል ምን ማለቱ ሊሆን ይችላል?

19 ጉበኛው አጭር የሆነውን መልእክቱን የሚደመድመው በሚከተሉት ቃላት ነው:- “ ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ” (ኢሳይያስ 21:​12ለ) ‘ተመልሳችሁ ኑ’ የሚለው መግለጫ ኤዶም ከፊቷ መቋጫ የሌለው ‘ምሽት’ እንደሚፈራረቅባት የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ይህ አገላለጽ “ተመለሱ” ተብሎም ሊተረጎም ስለሚችል ነቢዩ በብሔሩ ላይ ከሚመጣው ጥፋት ማምለጥ የሚፈልጉ ኤዶማውያን ንስሐ መግባትና ወደ ይሖዋ ‘መመለስ’ እንዳለባቸው መናገሩ ሊሆን ይችላል። ብቻ በዚህም ሆነ በዚያ ጉበኛው ተጨማሪ ነገር እንዲጠይቁ እየጋበዛቸው ነው።

20. በ⁠ኢሳይያስ 21:​11, 12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ቃል ዛሬ ላለው የይሖዋ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ያዘለ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

20 ይህ አጭር አዋጅ በዛሬው ጊዜ ለሚገኘው የይሖዋ ሕዝብ ከፍተኛ ትርጉም አለው። * የሰው ዘር በመንፈሳዊ በመታወሩና ከአምላክ በመራቁ ምክንያት ወደዚህ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት በሚያመራው ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደገባ እናውቃለን። (ሮሜ 13:​12፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​4) በዚህ የጨለማ ጊዜ የሰው ልጅ ሰላምና መረጋጋት ሊያመጣ ይችላል የሚል ምንም ዓይነት የተስፋ ጭላንጭል ቢፈነጥቅ የከፋ የጨለማ ጊዜ አስከትሎ የሚመጣ ማታለያ ከመሆን አያልፍም። እውነተኛ ንጋት ማለትም የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሚጠባበት ጊዜ እየቀረበ ነው። ይሁን እንጂ ሌሊቱ እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ በመንፈሳዊ ንቁዎች በመሆንና የዚህ ብልሹ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ እንደቀረበ በድፍረት በማወጅ የጉበኛውን ክፍል አመራር መከተል ይኖርብናል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:​6

ደረቁ ምድር ጨለማ ዋጠው

21. (ሀ) “ስለ ደረቅ ምድር የተነገረ ሸክም” የሚለው ሐረግ ምን ሌላ መልእክት ያዘለ እንዲሆን ታስቦ ሊሆን ይችላል? (ለ) የድዳን ተጓዦች እነማን ናቸው?

21 የ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 21 የመጨረሻው ሸክም የተነገረው ስለ ‘ደረቅ ምድር’ ነው። እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “ስለ ዓረብ [“ደረቅ ምድር፣” NW ] የተነገረ ሸክም። የድዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፣ በዓረብ ዱር ውስጥ ታድራላችሁ።” (ኢሳይያስ 21:​13) የተነገረው ሸክም በርካታ የዓረብ ነገዶችን የሚመለከት በመሆኑ ደረቅ ምድር የሚለው መግለጫ የዓረብ ምድርን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። አንዳንድ ጊዜ “ደረቅ ምድር” የሚለው ቃል “ምሽት” ተብሎም ተተርጉሟል። በዕብራይስጥ ሁለቱም ተመሳሳይ ቃላት ናቸው። አንዳንዶች ይህ አካባቢው ድቅድቅ ጨለማ እንደሚውጠው ማለትም የችግር ጊዜ እንደሚጠብቀው የሚጠቁም ውስጠ ወይራ ንግግር ነው የሚል እምነት አላቸው። ይህ ሸክም የሚጀምረው በምሽት ስለሚታይ ትዕይንት በመግለጽ ነው። ይህም ጉልህ ስፍራ ያለው የዓረብ ጎሳ ማለትም የድዳን ነጋዴዎች ስለሚያደርጉት ጉዞ ይገልጻል። እነዚህ ተጓዦች የንግድ መስመሮችን ተከትለው ቅመማ ቅመም፣ ዕንቁ እና ሌሎችን ውድ ንብረቶች በመያዝ ከአንዱ የበረሃ ገነት ወደ ሌላው የሚጓዙ ናቸው። እዚህ ላይ ግን ምቹ የሆነውን ጎዳናቸውን ትተው ምሽቱን ተሸሽገው ለማሳለፍ እንደተገደዱ ሰዎች ተደርገው ተገልጸዋል። ለምን?

22, 23. (ሀ) በዓረብ ነገዶች ላይ ሊወድቅባቸው ያለው ከባድ ሸክም ምንድን ነው? ይህስ በእነርሱ ላይ የሚያስከትለው ውጤት ምን ይሆናል? (ለ) ይህ ችግር የሚመጣበት ጊዜ ምን ያህል ቅርብ ነው? ይህንን የሚያመጣባቸውስ ማን ነው?

22 ኢሳይያስ ስለ ሁኔታው እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “በቴማን የምትኖሩ ሆይ፣ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ፤ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው። ከሰይፍ፣ ከተመዘዘው ሰይፍ፣ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና።” (ኢሳይያስ 21:​14, 15) አዎን፣ በእነዚህ የዓረብ ነገዶች ላይ የሚያደቅቅ የጦርነት ሸክም ይወድቅባቸዋል። ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ በሚያገኘው የክልሉ አካባቢ የምትገኘው ቴማን ለምስኪኖቹ የጦር ምርኮኞች ውኃና ዳቦ ለማምጣት ትገደዳለች። ይህ ችግር የሚመጣው መቼ ይሆን?

23 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ጌታ እንዲህ ብሎኛልና:- እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፤ ከቀስተኞች ቁጥር የቀሩት፣ የቄዳር ልጆች ኃያላን፣ ያንሳሉ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።” (ኢሳይያስ 21:​16, 17 ) ቄዳር በጣም ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነገድ ከመሆኑ የተነሣ አንዳንድ ጊዜ መላውን የዓረብ ምድር እንደሚወክል ተደርጎ ይገለጻል። ይሖዋ የዚህ ጎሳ ቀስተኞችና ኃያላን ቁጥራቸው እንደሚመናመንና ጥቂት ብቻ እንደሚቀሩ ወስኗል። መቼ? አንድ ምንደኛ ከተከፈለው ጊዜ አስበልጦ እንደማይሠራ ሁሉ “በአንድ ዓመት ውስጥ” ይሆናል እንጂ ከዚያ አያልፍም። ይህ ሁሉ ነገር በትክክል ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ሁለት የአሦራውያን ገዥዎች ማለትም ዳግማዊ ሳርጎንና ሰናክሬም የዓረብ ምድርን ተቆጣጥረናል ብለው በየፊናቸው ተናግረዋል። ደግሞም ሁለቱም ቢሆኑ አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው በእነዚህ ኩሩ የዓረብ ነገዶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው ሊሆን ይችላል።

24. ኢሳይያስ ስለ ዓረብ ምድር የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

24 ይሁን እንጂ ይህ ትንቢት አንድም ሳይቀር ፍጻሜውን እንዳገኘ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በዚህ ሸክም መደምደሚያ ላይ ከተነገሩት “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሯልና” ከሚሉት ቃላት ይበልጥ ይህንን እውነት በግልጽ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ ይኖራል። በኢሳይያስ ዘመን ለነበሩት ሰዎች ባቢሎን አሦርን ድል አድርጋ ሥልጣን ላይ ትወጣለች ከዚያም በአንዲት ምሽት አስረሽ ምችው ትገለበጣለች የሚለው መልእክት የማይታመን መስሎ ታይቷቸው ሊሆን ይችላል። ኃያል የነበረችው ኤዶምም በሞት ዝምታ ትዋጣለች ወይም ባለጠጋ የሆነው የዓረብ ምድር የችግርና የእጦት ጨለማ ይወድቅበታል የሚለው መልእክትም ቢሆን የማይታመን ሊመስላቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ይፈጸማል ብሎ ተናግሯል፤ ደግሞም ይፈጸማል። ዛሬ ይሖዋ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት እንዳልነበረ እንደሚሆን ይነግረናል። ሊሆን ይችላል ሳይሆን በእርግጠኝነት ይሆናል። ይሖዋ ራሱ ተናግሯል!

25. የጉበኛውን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

25 እንግዲያው እንደ ጉበኛው እንሁን። ከፍ ባለ ማማ ላይ ቆሞ ከአድማስ ባሻገር የሚመጣውን አደጋ በዓይኑ እንደሚያማትር ሰው ንቁዎች ሆነን እንቀጥል። ከታመነው የጉበኛ ክፍል ማለትም ዛሬ በምድር ላይ ከቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በቅርብ ተባብረን እንሥራ። ክርስቶስ በሰማይ እየገዛ ስለመሆኑ በቅርቡም የሰው ልጅ ከአምላክ የራቀበትን ረጅም የጨለማ ሌሊት ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣው እንዲሁም ከዚያ በኋላ እውነተኛው ንጋት ማለትም ምድር ገነት የምትሆንበት የሺህ ዓመት ግዛት እንደሚጠባ ያገኘናቸውን በርካታ ማስረጃዎች በተመለከተ በድፍረት በመናገር ከጎናቸው እንቁም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ “የአንሻን ንጉሥ” እየተባለ የሚጠራበት ጊዜ ነበር። አንሻን ደግሞ በኤላም ውስጥ የምትገኝ አውራጃ ወይም ከተማ ነበረች። በኢሳይያስ ዘመን ማለትም በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበሩት እስራኤላውያን ኤላምን ሊያውቋት ቢችሉም ፋርስን ላያውቋት ይችላሉ። ይህም ኢሳይያስ ፋርስ ከማለት ይልቅ ኤላም የሚለውን ስም ለመጠቀም የመረጠበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለን ይሆናል።

^ አን.9 ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች “ጋሻውን ቀቡ” የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው የቆዳ ጋሻዎች የሚወረወሩትን አብዛኛዎቹን ፍላጻዎች እንዲያንሸራትቱ ሲባል ከውጊያው በፊት በዘይት ይቀቡ የነበረበትን ጥንታዊ ልማድ ነው ይላሉ። ይህ ፍቺ ትክክል ሊሆን ቢችልም ከተማዋ በወደቀችበት በዚያ ዕለት ምሽት ግን ባቢሎናውያን ጋሻቸውን ዘይት በመቀባት ለጦርነት የሚዘጋጁበት ይቅርና የሚዋጉበት ጊዜ እንኳን እንዳልነበራቸው ልብ ሊባል ይገባል!

^ አን.13 ኢሳይያስ የባቢሎንን መውደቅ በተመለከተ የተናገረው ትንቢት ፍጹም ትክክለኛ ከመሆኑ የተነሣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ታሪኩ ከተፈጸመ በኋላ የተጻፈ መሆን አለበት እስከ ማለት ደርሰዋል። ይሁን እንጂ የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁር የሆኑት ኤፍ ዴሊትሽ እንዳሉት አንድ ነቢይ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ከመቶ ዓመታት በኋላ የሚሆነውን ነገር ከወዲሁ ሊተነብይ እንደሚችል ካመንን እንዲህ ያለውን ግምታዊ ሐሳብ መሰንዘር አስፈላጊ አይሆንም።

^ አን.14 ራእይ​—⁠ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 163-8ን ተመልከት።

^ አን.20መጠበቂያ ግንብ መጽሔት በታተመባቸው የመጀመሪያ 59 ዓመታት ውስጥ ኢሳይያስ 21:​11ን በሽፋኑ ላይ ይዞ ይወጣ ነበር። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል ለመጨረሻ ጊዜ ያሳተመው በጽሑፍ ታትሞ የወጣ ስብከትም ጭብጥ ያደረገው ይህንኑ ጥቅስ ነበር። (በፊተኛው ገጽ ላይ የሚገኘውን ሥዕል ተመልከት።)

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 219 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ይበሉማል፣ ይጠጡማል።”

[በገጽ 220 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጉበኛውም . . . “እንደ አንበሳ ጮኸ ”

[በገጽ 222 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ቀኑን ሁሉ ዘወትር . . . ቆሜአለሁ ሌሊቱንም ሁሉ”