በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጉሡና መሳፍንቱ

ንጉሡና መሳፍንቱ

ምዕራፍ ሃያ አምስት

ንጉሡና መሳፍንቱ

ኢሳይያስ 32:​1-​20

1, 2. በሙት ባሕር ስለተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል ይዘት ምን ለማለት ይቻላል?

በ1940ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በፍልስጥኤም ምድር በሙት ባሕር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ዋሻ ውስጥ አስደናቂ የጥቅልሎች ስብስብ ተገኝቷል። የሙት ባሕር ጥቅልሎች በመባል የሚታወቁት እነዚሁ ቅጂዎች ከ200 ከዘአበ እስከ 70 እዘአ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፉ ይታመናል። ከእነዚህ መካከል በጣም በሰፊው የሚታወቀው ጥንካሬ ባለው ቆዳ ላይ በዕብራይስጥ የተጻፈው የኢሳይያስ ጥቅልል ነው። ይህ ጥቅልል የተሟላ ነው ለማለት ይቻላል። ይዘቱም ቢሆን ከዚያ በኋላ 1, 000 ዓመት ቆይተው ከተዘጋጁት የማሶራዊ ቅጂዎች እምብዛም አይለይም። በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱሱ ይዘት ሳይዛባ በትክክል እንደተላለፈ ማስረጃ ሆኗል።

2 በሙት ባሕር የተገኘውን የኢሳይያስ ጥቅልል በሚመለከት አንድ ትኩረት የሚስብ ነገር አለ። ዛሬ ኢሳይያስ ምዕራፍ 32 ተብሎ በሚታወቀው ክፍል ኅዳግ ላይ ቅጂውን ያዘጋጀው ጸሐፊ “x” የሚል ምልክት አድርጎበታል። ጸሐፊው ይህንን ምልክት ያደረገው ለምን እንደሆነ አናውቅም። ይሁን እንጂ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለየት ያለ ነገር እንዳለው እናውቃለን።

በጽድቅና በፍትህ ማስተዳደር

3.በኢሳይያስና በራእይ መጻሕፍት ውስጥ በትንቢት የተነገረለት አስተዳደር የትኛው ነው?

3 ኢሳይያስ ምዕራፍ 32 የሚጀምረው በጊዜያችን አስገራሚ ፍጻሜውን ስለሚያገኝ አንድ አስደሳች ትንቢት በመናገር ነው:- “እነሆ፣ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፣ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ።” (ኢሳይያስ 32:​1) “እነሆ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱሱ የመጨረሻ ትንቢታዊ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ተመሳሳይ ቃል አጋኖ ያስታውሰናል:- “በዙፋንም የተቀመጠው:- እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ።” (ራእይ 21:​5፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በኢሳይያስና በራእይ መጻሕፍት መካከል የ900 ዓመት ያህል ልዩነት ቢኖርም ሁለቱም ስለ “አዲስ ሰማይ” እና “አዲስ ምድር” ብሩህ የሆነ መግለጫ ይሰጣሉ። ይህ አዲስ ሰማይ በ1914 ሰማያዊ ሥልጣኑን ከያዘው ከንጉሡ ከኢየሱስ ክርስቶስና “ከምድር ከተዋጁት” 144, 000 ተባባሪዎቹ የተውጣጣ አዲስ መስተዳድር ሲሆን አዲሱ ምድር ደግሞ አንድነት ያለው ምድር አቀፍ የሰው ዘር ኅብረተሰብ ነው። * (ራእይ 14:​1-4፤ 21:​1-4፤ ኢሳይያስ 65:​17-25) ይህ ጠቅላላ ዝግጅት እውን ሊሆን የቻለው በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው።

4. በዛሬው ጊዜ ያለው የአዲሱ ምድር አስኳል የትኛው ነው?

4 ሐዋርያው ዮሐንስ የእነዚህን 144, 000 ተባባሪ ገዥዎች የመጨረሻ መታተም በራእይ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ።” የአዲሱ ምድር አስኳል በቁጥር እጅግ ጥቂት ከሆኑት የ144, 000ዎቹ አረጋውያን ቀሪዎች ጎን የተሰበሰበውና በሚልዮን የሚቆጠረው ይህ እጅግ ብዙ ሕዝብ ነው። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች በፍጥነት ወደ እኛ እየገሰገሰ ካለው ታላቅ መከራ በሕይወት በማለፍ በገነቲቱ ምድር ላይ ትንሣኤ ከሚያገኙት የታመኑ ሰዎች እንዲሁም ተነሥተው እምነታቸውን እንዲያሳዩ አጋጣሚ ከሚሰጣቸው በቢልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ጋር ይቀላቀላሉ። እምነት እንዳላቸው የሚያረጋግጡ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ይባረካሉ።​—⁠ራእይ 7:​4, 9-17፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

5-7. በትንቢት የተነገረላቸው ‘መሳፍንት’ በአምላክ መንጋ መካከል ምን ሚና ይጫወታሉ?

5 ይሁን እንጂ ይህ በጥላቻ የተሞላ ዓለም እስካለ ድረስ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። በአመዛኙ ይህን ጥበቃ የሚያገኙት ‘በፍትሕ ከሚያስተዳድሩት’ “መሳፍንት” ነው። እንዴት ድንቅ ዝግጅት ነው! ‘መሳፍንቱ’ በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ በሚከተሉት አስደሳች ቃላት ተገልጸዋል:- “ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።”​—⁠ኢሳይያስ 32:​2

6 በዓለም ዙሪያ ጭንቀት በነገሠበት በአሁኑ ዘመን የይሖዋን በጎች በመንከባከብና ከይሖዋ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ ፍትሕን በማስፈጸም ‘ለመንጋው የሚጠነቀቁ’ “መሳፍንት” ማለትም ሽማግሌዎች ያስፈልጋሉ። (ሥራ 20:​28) እንደነዚህ ያሉት “መሳፍንት” በ⁠1 ጢሞቴዎስ 3:​2-7 እና በ⁠ቲቶ 1:​6-9 ላይ የተዘረዘረውን ብቃት ማሟላት ይኖርባቸዋል።

7 ኢየሱስ አስጨናቂ ስለሆነው ‘የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ በገለጸበት ታላቅ ትንቢት ውስጥ “አትሸበሩ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:​3-8 NW ) የኢየሱስ ተከታዮች ዛሬ ባለው አደገኛ የዓለም ሁኔታ የማይሸበሩት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ከቅቡዓንም ሆነ ‘ከሌሎች በጎች’ ወገን የሆኑ “መሳፍንት” በታማኝነት መንጋውን በመጠበቅ ላይ ስለሆኑ ነው። (ዮሐንስ 10:​16) የጎሳ ጦርነትንና የጅምላ ጭፍጨፋን በመሳሰሉ አስፈሪ ወቅቶች ሳይቀር ያላንዳች ፍርሃት ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ይንከባከባሉ። የአምላክ ቃል በሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሚያንጽ እውነት በመጠቀም በመንፈሳዊ በተራቆተው በዚህ ዓለም ውስጥ ያዘኑትን ሰዎች መንፈስ ለማደስ ይጥራሉ።

8. ይሖዋ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑትን “መሳፍንት” እያሰለጠናቸውና እየተጠቀመባቸው ያለው እንዴት ነው?

8 ባለፉት 50 ዓመታት ‘መሳፍንቱ’ ያላቸው ቦታ ይበልጥ ጉልህ ሆኗል። ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት “መሳፍንት” ‘የአለቃው’ ቡድን ሆነው ሥልጠና እያገኙ ሲሆን ከታላቁ መከራ በኋላ ከመካከላቸው ብቃት ያላቸው በአዲሱ ምድር ውስጥ በአስተዳደር ሥራ ለማገልገል ዝግጁ ይሆናሉ። (ሕዝቅኤል 44:​2, 3፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13) በመንግሥቱ አገልግሎት ቀዳሚ ሆነው እየሠሩ መንፈሳዊ መመሪያና ማነቃቂያ በመስጠት ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ለመንጋው “እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” እረፍትን የሚሰጡ መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው። *

9. ዛሬ ‘መሳፍንት’ እንደሚያስፈልጉ የሚያሳዩት ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

9 አደገኛ በሆኑት በእነዚህ የሰይጣን ክፉ ዓለም የመጨረሻ ቀናት ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለው ጥበቃ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5, 13) ዛሬ የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችና የተጣመመ ፕሮፓጋንዳ እንደ ኃይለኛ ነፋስ የሚነፍሱበት ጊዜ ነው። በብሔራት መካከልም ሆነ በየአገራቱ እርስ በርስ የሚደረገው ጦርነት እንዲሁም በይሖዋ አምላክ የታመኑ አምላኪዎች ላይ በቀጥታ የሚሰነዘረው ጥቃት እንደ ዐውሎ ነፋስ እያስገመገመ ነው። ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ድርቅ በተመታው ዓለም ውስጥ መንፈሳዊ ጥማቸውን ለማርካት ንጹህ የሆነውና ያልተበረዘው የእውነት የወንዝ ፈሳሽ ያስፈልጋቸዋል። የሚያስደስተው ደግሞ ይሖዋ በመግዛት ላይ ያለው ንጉሡ በዚህ የችግር ወቅት በቅቡዓን ወንድሞቹና በተባባሪዎቻቸው የሌሎች በጎች “መሳፍንት” በመጠቀም ለተጨነቁትና ተስፋ ለቆረጡት ሰዎች አስፈላጊውን ማበረታቻ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። በዚህ መንገድ ይሖዋ ጽድቅና ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል።

ዓይን፣ ጆሮና ልብን ተክሎ መከታተል

10. ሕዝቡ መንፈሳዊ ነገሮችን ‘ያይና’ ‘ይሰማ’ ዘንድ ይሖዋ ምን ዝግጅት አድርጓል?

10 እጅግ ብዙ ሰዎች ለይሖዋ ቲኦክራሲያዊ ዝግጅት ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው? ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “የሚያዩትም ሰዎች ዓይኖች አይጨፈኑም፣ የሚሰሙትም ጆሮች ያደምጣሉ።” (ኢሳይያስ 32:​3) ባለፉት ዓመታት ይሖዋ ውድ አገልጋዮቹን ሲያስተምራቸውና ወደ ጉልምስና እንዲደርሱ ሲረዳቸው ቆይቷል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚካሄዱት የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤትና ሌሎች ስብሰባዎች፣ የአውራጃ ስብሰባዎች፣ ብሔራት አቀፍና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እንዲሁም ‘መሳፍንቱ’ መንጋውን በእንክብካቤና በፍቅር እንዲይዙ የሚያገኙት ልዩ ሥልጠና በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች የተገነባ አንድነት ያለው ምድር አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ለመመሥረት አስችሏል። እነዚህ እረኞች የሚኖሩት በየትኛውም የምድር ክፍል ቢሆን ይበልጥ ግልጽ እየሆነ የሚሄደውን የእውነት ቃል በተመለከተ ባለን ግንዛቤ ላይ ለሚደረገው ማስተካከያ ዓይኖቻቸው ክፍት ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናቸውን በመጠቀም ሁልጊዜ ለመስማትና ለመታዘዝ ዝግጁ ናቸው።​—⁠መዝሙር 25:​10

11. በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝብ የሚናገረው በጥርጣሬ አፉ እየተሳሰረ ሳይሆን በእርግጠኝነት የሆነው ለምንድን ነው?

11 ከዚያም ትንቢቱ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች [“የችኩሎች፣” NW ] ልብ እውቀትን ታስተውላለች፣ የተብታቦችም ምላስ ደኅና አድርጋ ትናገራለች።” (ኢሳይያስ 32:​4) ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ማናችንም ብንሆን መቸኮል አይኖርብንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በቃሉ የሚቸኩለውን ሰው ብታይ፣ ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው።” (ምሳሌ 29:​20፤ መክብብ 5:​2) ከ1919 በፊት የይሖዋ ሕዝብ ጭምር በባቢሎናዊ ሐሳቦች ቆሽሾ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ዓመት አንስቶ ይሖዋ ስለ ዓላማው ይበልጥ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። በወቅቱ የገለጠላቸው እውነት የታሰበበት እንጂ የችኮላ እንዳልነበር ተረድተዋል። አሁን ይህን እውነት የሚናገሩት በጥርጣሬ አፋቸው እየተሳሰረ ሳይሆን በፍጹም እርግጠኝነት ነው።

‘ሰነፍ ሰው’

12. ዛሬ ያሉት ‘ሰነፎች’ እነማን ናቸው? ልግስና የሚጎድላቸውስ በምን መንገድ ነው?

12 ቀጥሎ ደግሞ የኢሳይያስ ትንቢት ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ነገር ይጠቅሳል:- “ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ከበርቴ [“ለጋስ፣” NW ] ተብሎ አይጠራም፣ ንፉግም ለጋስ [“ሥርዓት የለሹም የተከበረ ሰው፣” NW ] አይባልም። ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል።” (ኢሳይያስ 32:​5, 6ሀ) “ሰነፍ” የተባለው ማን ነው? ንጉሥ ዳዊት ይህን ጉዳይ ጠበቅ አድርጎ ለማስገንዘብ የፈለገ ይመስል ሁለት ጊዜ ያህል “ሰነፍ በልቡ:- አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፣ ጐሰቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም” በማለት መልሱን ይሰጣል። (መዝሙር 14:​1፤ 53:​1) በእርግጥም ደግሞ ጭራሹኑ በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች ይሖዋ የሚባል አምላክ የለም ብለው ይናገራሉ። በማንም ፊት ተጠያቂነት እንደሌለባቸው የሚያስቡ “ምሁራን” እና ሌሎች ሰዎች ደግሞ በተግባራቸው አምላክ የለም ያሉ ያህል ነው። በእነዚህ ሰዎች ዘንድ እውነት የለም። በልባቸውም የልግስና ሐሳብ የለም። የፍቅርን ወንጌል አያውቁም። ከእውነተኛ ክርስቲያኖች በተቃራኒ የተቸገሩትን ለመርዳት ያዘግማሉ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ ቸል ይሏቸዋል።

13, 14. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ከሃዲዎች ጎጂ የሆነ ነገር የሚሠሩት እንዴት ነው? (ለ) ከሃዲዎች የተራቡትና የተጠሙት ሰዎች ምን እንዳያገኙ ይከለክሏቸዋል? ይሁን እንጂ የመጨረሻው ውጤት ምን ይሆናል?

13 ከእነዚህ ሰነፎች መካከል ብዙዎች የአምላክን እውነት የሚደግፉትን ሰዎች ይጠላሉ:- “ክህደት ይፈጽምና በይሖዋ ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ ልቡ ጎጂ የሆነውን ነገር ያደርጋል።” (ኢሳይያስ 32:​6ለ NW ) ይህ አባባል ዛሬ ላሉት ከሃዲዎች ፍጹም ተስማሚ ነው! በበርካታ የአውሮፓና የእስያ አገሮች ውስጥ ከሃዲዎች ከሌሎች የእውነት ተቃዋሚዎች ጋር በማበር የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ ለማሳገድ ወይም የተወሰነ ዕቀባ እንዲጣልበት ለማድረግ ለባለ ሥልጣናት ዓይን ያወጣ ውሸት ያሠራጫሉ። ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ትንቢት የተናገረለት “ክፉ ባሪያ” ያሳየውን ዓይነት መንፈስ ያንጸባርቃሉ:- “ያ ክፉ ባሪያ ግን:- ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፣ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፣ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፣ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”​—⁠ማቴዎስ 24:​48-51

14 እስከዚያው ድረስ ግን ከሃዲዎች ‘የተራበችውንም ሰውነት ባዶ ያደርጋሉ ከተጠማም ሰው መጠጥን ይቈርጣሉ።’ (ኢሳይያስ 32:​6ሐ) የእውነት ጠላት የሆኑ ሰዎች እውነትን የተራበው ሕዝብ መንፈሳዊ ምግብ እንዳያገኝ የተጠማውም እርካታ የሚሰጠውን የመንግሥቱን መልእክት ውኃ እንዳይጠጣ ለማድረግ ይጥራሉ። ይሁን እንጂ የመጨረሻው ውጤት ይሖዋ በአንድ ሌላ ነቢይ አማካኝነት ለሕዝቡ ከተናገረው ነገር የተለየ አይሆንም:- “ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፣ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፣ ይላል እግዚአብሔር።”​—⁠ኤርምያስ 1:​19፤ ኢሳይያስ 54:​17

15. በተለይ ዛሬ ‘ሥርዓት የሌላቸው’ የሆኑት እነማን ናቸው? ምን ነገር ‘በሐሰት ይናገራሉ?’ ውጤቱስ ምንድን ነው?

15 ከ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አንስቶ የሥነ ምግባር ብልግና በሕዝበ ክርስትና አገሮች ውስጥ በእጅጉ ተስፋፍቷል። ለምን? ትንቢቱ አንደኛው ምክንያት ምን እንደሆነ አስቀድሞ ተናግሯል:- “የንፉግም [“ሥርዓት የሌለው ሰው፣ NW ] ዕቃ ክፉ ናት፤ ችግረኛ ቅን ነገርን በተናገረ ጊዜ እንኳ እርሱ በሐሰት ቃል ድሀውን ያጠፋ ዘንድ ክፉን አሳብ ያስባል [“የብልግናን ሐሳብ ያካፍላል፣” NW ]።” (ኢሳይያስ 32:​7 ) በእነዚህ ቃላት ፍጻሜ መሠረት በተለይ ብዙዎቹ ቀሳውስት ከጋብቻ በፊት ስለሚፈጸመው የፆታ ግንኙነት፣ ሳይጋቡ አብሮ ስለመኖር እንዲሁም ስለ ግብረ ሰዶም ባጠቃላይ ስለ “ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ” ያላቸው አመለካከት ልቅ ሆኗል። (ኤፌሶን 5:​3) በዚህ መንገድ መንጎቻቸውን በሐሰት ቃላቸው ‘ያጠፋሉ።’

16. እውነተኛ ክርስቲያኖችን ደስተኛ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው?

16 ከዚህ በተቃራኒ ግን ቀጥሎ ነቢዩ የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ምንኛ መንፈስ የሚያድስ ነው! “ለጋስ ግን ምክሩ ስለ ልግስና ነው፤ ለልግስናም ይኖራል።” (ኢሳይያስ 32:​8 NW ) ኢየሱስ ራሱ እንደሚከተለው በማለት ልግስናን አበረታትቷል:- “ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፣ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።” (ሉቃስ 6:​38) ሐዋርያው ጳውሎስም እንደሚከተለው በማለት ለጋስ መሆን ያለውን በረከት ጠቁሟል:- “እርሱ ራሱ:- ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባች[ኋል]።” (ሥራ 20:​35) እውነተኛ ክርስቲያኖች ደስተኛ የሚሆኑት ቁሳዊ ሀብት ወይም በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ ስላላቸው ሳይሆን የአምላካቸውን የይሖዋን ምሳሌ በመኮረጅ ለጋስ በመሆናቸው ነው። (ማቴዎስ 5:​44, 45) ትልቁ የደስታቸው ምንጭ ‘ስለ አምላክ ክብር የሚናገረውን ወንጌል’ ለሌሎች ለማሳወቅ ሲሉ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ በማቅረብ የአምላክን ፈቃድ መፈጸማቸው ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​11

17. ኢሳይያስ የጠቀሳቸው ‘ተማምነው የሚቀመጡ ሴቶች’ በዛሬው ጊዜ እነማንን ይመስላሉ?

17 የኢሳይያስ ትንቢት እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፣ ተነሡ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፣ ንግግሬን አድምጡ። እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ሆይ፣ ወይንን መቁረጥ ይጠፋልና፣ ፍሬም ማከማቸት አይመጣምና ከዓመትና ከጥቂት ቀን በኋላ ትንቀጠቀጣላችሁ። እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፣ ተጠንቀቁ፤ ተማምናችሁም የምትቀመጡ ሆይ፣ ተንቀጥቀጡ።” (ኢሳይያስ 32:​9-11ሀ) የእነዚህ ሴቶች ሁኔታ ዛሬ አምላክን እናመልካለን እያሉ በአገልግሎቱ ቀናተኛ ያልሆኑትን ሰዎች ያስታውሰናል። እንዲህ ያሉት ሰዎች የሚገኙት ‘የጋለሞታዎች እናት በሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን’ ውስጥ ነው። (ራእይ 17:​5) ለምሳሌ ያህል በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ሥር ያሉት አባላት ሁኔታ ኢሳይያስ ስለ እነዚህ “ሴቶች” ከሰጠው መግለጫ ጋር ተመሳሳይ ነው። በቅርቡ ስለሚጠብቃቸው ፍርድና መንቀጥቀጥ ምንም የማይጨነቁ “ዓለመኞች” ናቸው።

18. ‘ማቅ እንዲታጠቁ’ የታዘዙት እነማን ናቸው? ለምንስ?

18 ከዚያም ጥሪው ለሐሰት ሃይማኖቶች ይቀርባል:- “ልብሳችሁን አውልቁ፣ ዕራቁታችሁን ሁኑ፣ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ። ስለ ተወደደችውም እርሻ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ። በሕዝቤ ምድር ላይ፣ በደስታ ከተማ ባሉት በደስታ ቤቶች ሁሉ ላይ እሾህና ኩርንችት ይወጣባቸዋል።” (ኢሳይያስ 32:​11ለ-13) “ልብሳችሁን አውልቁ፣ ዕራቁታችሁን ሁኑ” የሚለው መግለጫ ጨርሶ ዕርቃንን መሆን ማለት አይመስልም። ጥንት ከታች እጀ ጠባብ አድርጎ ከውጭ ሌላ መጎናጸፊያ መደረብ የተለመደ ነበር። መጎናጸፊያው ብዙውን ጊዜ መለያ ምልክት ነበር። (2 ነገሥት 10:​22, 23፤ ራእይ 7:​13, 14) በመሆኑም ትንቢቱ በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ሰዎች የአምላክ አገልጋይ ለመምሰል ያደረጉትን መጎናጸፊያ አውልቀው በቅርቡ ስለሚመጣባቸው ፍርድ የተሰማቸውን ሐዘን ለመግለጽ ማቅ እንዲለብሱ ማዘዙ ነበር። (ራእይ 17:​16) የአምላክ “የደስታ ከተማ” ነኝ በምትለው ሕዝበ ክርስትና ሥር በታቀፉት ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ውስጥም ሆነ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ክፍል በሆኑት የተቀሩት ሃይማኖቶች ውስጥ ምንም ዓይነት መለኮታዊ ፍሬያማነት አይታይም። በእንቅስቃሴ ቀጠናቸው የሚበቅለው ነገር “እሾክና ኩርንችት” ብቻ ይሆናል። ይህ ደግሞ ዞር ብለው የማያዩት የተረሳ አካባቢ መሆኑን የሚያመለክት ነው።

19. ኢሳይያስ ያጋለጠው የትኛውን ‘የኢየሩሳሌም’ ክህደት ነው?

19 ይህ አስፈሪ ዕጣ በከሃዲዋ “ኢየሩሳሌም” ላይ በአጠቃላይ የሚደርስ ነበር:- “አዳራሹ ወና ትሆናለችና፣ የብዙ ሰውም ከተማ ትለቀቃለችና፣ አምባውና [“ዖፌልና፣” NW ] ግንቡም ለዘላለም ዋሻ፣ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፣ የመንጎችም ማሰማርያ [“ሜዳ፣” NW ] ይሆናልና።” (ኢሳይያስ 32:​14) አዎን፣ ዖፌል ሳትቀር ተጠቅሳለች። ዖፌል ኢየሩሳሌም ውስጥ የምትገኝ ከፍ ያለችና ከተማዋን ለመጠበቅ ቁልፍ የሆነች ቦታ ናት። ዖፌል ሜዳ ትሆናለች ማለት ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ትወድማለች ማለት ነው። ከኢሳይያስ ቃላት መረዳት እንደሚቻለው ከሃዲዋ “ኢየሩሳሌም” ማለትም ሕዝበ ክርስትና የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ ንቁ አይደለችም። ከእውነትና ከፍትሕ ፈጽሞ የራቀች መንፈሳዊ ምድረ በዳና የለየላት አውሬ ሆናለች።

ፈጽሞ የተለየ ክብራማ ሁኔታ!

20. የአምላክ መንፈስ በሕዝቡ ላይ መፍሰሱ የሚኖረው ውጤት ምንድን ነው?

20 ቀጥሎ ደግሞ ኢሳይያስ የይሖዋን ፈቃድ ለሚያደርጉ ሰዎች ልብን ደስ የሚያሰኝ ተስፋ ይሰጣል። በአምላክ ሕዝብ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥፋት የሚዘልቀው “መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፣ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፣ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 32:​15) የሚያስደስተው ከ1919 ወዲህ የይሖዋ መንፈስ በሕዝቡ ላይ በሰፊው የፈሰሰ ሲሆን ፍሬያማ የሆነው የቅቡዓን ምሥክሮች እርሻ እንደገና እንዲለማና እየጨመረ የሚሄደው የሌሎች በጎች ዱር እንዲገኝ ያደረገ ያህል ሆኗል። ብልጽግናና ዕድገት ዛሬ በምድር ላይ ያለው ድርጅቱ መለያ ሆነዋል። ሕዝቡ ስለ መጪው ምድር አቀፍ መንግሥት ሲያውጅ ተመልሶ በተቋቋመው መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ‘የእግዚአብሔር ክብርና የአምላካችን ግርማ’ ይንጸባረቃል።​—⁠ኢሳይያስ 35:​1, 2

21. ዛሬ ጽድቅ፣ ጸጥታና መታመን የሚገኘው የት ነው?

21 አሁን ደግሞ ይሖዋ የሚሰጠውን ክብራማ የሆነ ተስፋ አዳምጥ:- “ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፣ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል። የጽድቅም ሥራ ሰላም፣ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል።” (ኢሳይያስ 32:​16, 17) ዛሬ የይሖዋ ሕዝብ ያገኘውን መንፈሳዊ ሁኔታ የሚጠቁም ተስማሚ መግለጫ ነው! በጥላቻ፣ በዓመፅና በከፋ መንፈሳዊ ድህነት ከተከፋፈለው አብዛኛው የሰው ዘር በተቃራኒ እውነተኛ ክርስቲያኖች “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ ቢሆኑም ምድር አቀፍ አንድነት አላቸው። ወደፊት እውነተኛ ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበት ሁኔታ ለዘላለም እንደሚኖሩ በመተማመን ዛሬ ከአምላክ ጽድቅ ጋር ተስማምተው ይኖራሉ፣ ይሠራሉ፣ ያገለግላሉ።​—⁠ራእይ 7:​9, 17

22. በአምላክ ሕዝብና በሐሰት ሃይማኖት አባላት መካከል ያለው ልዩነት ምን ይመስላል?

22 ኢሳይያስ 32:​18 በመንፈሳዊ ገነት ውስጥም ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።” ለአስመሳይ ክርስቲያኖች ግን “በረዶ . . . በዱር ላይ ይወርዳል፣ ከተማም ፈጽማ ትዋረዳለች።” (ኢሳይያስ 32:​19) አዎን፣ የይሖዋ ፍርድ በጣም ኃይለኛ እንደሆነ የበረዶ ወዠብ አስመሳይ የሆነችውን የሐሰት ሃይማኖት ከተማ በመምታት እንደ ዱር ያለውን ደጋፊዋን ለማዋረድና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ተዘጋጅቷል!

23. ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ያለው ምድር አቀፍ ሥራ የትኛው ነው? በዚህ ሥራ ስለሚካፈሉትስ ምን ተብሏል?

23 ይህ የትንቢቱ ክፍል ሲደመድም እንዲህ ይላል:- “እናንተ የበሬና የአህያ እግር እየነዳችሁ በውኃ ሁሉ አጠገብ የምትዘሩ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW ] ናችሁ።” (ኢሳይያስ 32:​20) በሬና አህያ ጥንት የአምላክ ሕዝብ መሬቱን ለማረስና ዘር ለመዝራት የሚጠቀምባቸው የሸክም እንስሳት ነበሩ። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝብ የማተሚያ ማሽኖችን፣ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን፣ ዘመናዊ ሕንፃዎችንና የማጓጓዣ ዘዴዎችን ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ አንድነት ያለውን ቲኦክራሲያዊ ድርጅት በመጠቀም በቢልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያትማል እንዲሁም ያሠራጫል። ፈቃደኛ የሆኑ ሠራተኞች እነዚህን ጽሑፎች በመጠቀም ቃል በቃል “በውኃ ሁሉ አጠገብ” በመላዋ ምድር የመንግሥቱን የእውነት ዘር ይዘራሉ። እስከ ዛሬ ድረስ አምላክን የሚፈሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች የተሰበሰቡ ሲሆን ሌሎች ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም እየመጡ ነው። (ራእይ 14:​15, 16) በእርግጥም ሁሉም “ደስተኛ” ናቸው ሊባሉ ይችላሉ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በ⁠ኢሳይያስ 32:​1 ላይ የተጠቀሰው “ንጉሥ” በመጀመሪያ ያመለክት የነበረው ንጉሥ ሕዝቅያስን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 32 ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜ ከንጉሡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተያያዘ ነው።

^ አን.8 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን የመጋቢት 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13-18 ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 331 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሙት ባሕር የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል 32ኛ ምዕራፍ “X” የሚል ምልክት ተደርጎበታል

[በገጽ 333 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እያንዳንዱ ‘መስፍን ’ ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ፣ ከዝናብ እንደ መጠለያ፣ በበረሃ እንዳለ ውኃ እንዲሁም ከፀሐይ እንደሚያስጥል ጥላ ነው

[በገጽ 338 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ክርስቲያን ምሥራቹን ለሌሎች በማካፈል ትልቅ ደስታ ያገኛል