በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጉሡ ያሳየው እምነት ተካሰ

ንጉሡ ያሳየው እምነት ተካሰ

ምዕራፍ ሃያ ዘጠኝ

ንጉሡ ያሳየው እምነት ተካሰ

ኢሳይያስ 36:​1–39:​8

1, 2. ሕዝቅያስ ከአካዝ የተሻለ ንጉሥ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ ሲሆን ዕድሜው 25 ዓመት ነበር። ምን ዓይነት ገዥ ይወጣው ይሆን? የአባቱን የንጉሥ አካዝን ፈለግ በመከተል ተገዥዎቹ የሐሰት አማልክትን እንዲያገለግሉ ያደርግ ይሆን? ወይስ ቅድመ አያቱ ንጉሥ ዳዊት እንዳደረገው ሕዝቡን በይሖዋ አምልኮ ይመራቸው ይሆን?​—⁠2 ነገሥት 16:​2

2 ሕዝቅያስ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ‘በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን ማድረግ’ እንደሚፈልግ በግልጽ ታይቷል። (2 ነገሥት 18:​2, 3) በመጀመሪያው ዓመት የይሖዋ ቤተ መቅደስ እንዲታደስና የቤተ መቅደሱ አገልግሎት እንዲቀጥል ትእዛዝ ሰጠ። (2 ዜና መዋዕል 29:​3, 7, 11) ከዚያም ታላቅ የማለፍ በዓል አዘጋጅቶ አሥሩን ሰሜናዊ የእስራኤል ነገዶች ጨምሮ መላው ብሔር በበዓሉ ላይ እንዲገኝ ግብዣ አቀረበ። እንዴት የማይረሳ ታላቅ በዓል ነበር! ከንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንዲህ ያለ በዓል ተደርጎ አያውቅም።​—⁠2 ዜና መዋዕል 30:​1, 25, 26

3. (ሀ) ሕዝቅያስ ባዘጋጀው የማለፍ በዓል ላይ የተገኙት የእስራኤልና የይሁዳ ነዋሪዎች ምን እርምጃ ወስደዋል? (ለ) ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች በማለፍ በዓሉ ላይ የተገኙት ሰዎች ከወሰዱት ቆራጥ እርምጃ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

3 የማለፍ በዓሉ ሲደመደም በዚያ ተገኝተው የነበሩት ሰዎች ሐውልቶቹንና የማምለኪያ አጸዶቹን እንዲሁም የኮረብታ መስገጃዎቹንና የሐሰት አማልክቶቻቸውን መሠዊያ በማፈራረስ እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ወደ ከተማዎቻቸው ተመልሰዋል። (2 ዜና መዋዕል 31:​1) ቀደም ሲል ከነበራቸው ሃይማኖታዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ይህ ትልቅ ለውጥ ነበር! ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘መሰብሰባቸውን አለመተዋቸው’ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከዚህ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። የጉባኤ ስብሰባዎችም ሆኑ የወረዳና የልዩ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባን የመሳሰሉት ትላልቅ ስብሰባዎች ማበረታቻ ለማግኘትና በወንድማማች ኅብረትና በአምላክ መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለመነቃቃት’ ጉልህ ድርሻ አላቸው።​—⁠ዕብራውያን 10:​23-25

እምነት ሲፈተን

4, 5. (ሀ) ሕዝቅያስ ከአሦር ቀንበር ነፃ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ሰናክሬም በይሁዳ ላይ የወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ምንድን ነው? ሕዝቅያስስ በኢየሩሳሌም ላይ ሊሰነዘር የሚችለውን ቅጽበታዊ ጥቃት ለማስቀረት ምን እርምጃ ወስዷል? (ሐ) ሕዝቅያስ ኢየሩሳሌምን ከአሦራውያን ለመከላከል ዝግጅት ያደረገው እንዴት ነው?

4 ኢየሩሳሌም ከባድ ፈተናዎች ይጠብቋታል። ሕዝቅያስ ከሃዲ የነበረው አባቱ አካዝ ከአሦራውያን ጋር ገብቶት የነበረውን ኅብረት አፍርሷል። ከዚህም በላይ የአሦራውያን አጋር የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንንም መትቷል። (2 ነገሥት 18:​7, 8) ይህም የአሦሩን ንጉሥ አስቆጥቶት ነበር። በመሆኑም እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እንዲህም ሆነ፤ በንጉሡ በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጥቶ ወሰዳቸው።” (ኢሳይያስ 36:​1) ሕዝቅያስ ምሕረት የለሽ የሆነው የአሦር ሠራዊት ከሚሰነዝረው ቅጽበታዊ ጥቃት ኢየሩሳሌምን ለመከላከል በማሰብ ይመስላል ለሰናክሬም ከፍተኛ መጠን ያለው ግብር ማለትም 300 መክሊት ብርና 30 መክሊት ወርቅ ለመክፈል ተስማማ። *​—⁠2 ነገሥት 18:​14

5 በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ውስጥ ይህን ግብር ለመስጠት የሚያስችል በቂ መጠን ያለው ወርቅና ብር ስላልነበረ ሕዝቅያስ በቤተ መቅደሱ ያገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ አሰባስቧል። በወርቅ በተለበጠው የቤተ መቅደስ በር ላይ ሳይቀር የነበረውን ወርቅ አስቆርጦ ለሰናክሬም ልኳል። ይህ አሦራውያንን አርክቷቸዋል። ሆኖም ለጊዜው ብቻ ነበር። (2 ነገሥት 18:​15, 16) አሦራውያን ብዙም ሳይቆዩ እንደገና ፊታቸውን ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመልሱ ሕዝቅያስ ተገንዝቦ እንደነበር ከሁኔታዎቹ ለመረዳት ይቻላል። በመሆኑም አንዳንድ ዝግጅቶች መደረግ ነበረባቸው። ሕዝቡ ወራሪው የአሦር ኃይል ውኃ እንዳያገኝ ውኃ ያለባቸውን ቦታዎች ሁሉ ደፈነ። በተጨማሪም ሕዝቅያስ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ከማጠናከሩም ሌላ ‘ተወንጫፊ መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን’ ጨምሮ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቶችን አስገነባ።​—⁠2 ዜና መዋዕል 32:​4, 5 NW

6. ሕዝቅያስ የታመነው በማን ነው?

6 ይሁን እንጂ ሕዝቅያስ የታመነው በረቀቀ የጦር ስልት ወይም በቅጥሮች ሳይሆን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ነበር። የጦር አለቆቹን እንዲህ በማለት አሳስቧቸዋል:- “ጽኑ፣ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፣ አትደንግጡ። ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ‘ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናንቷል።’ (2 ዜና መዋዕል 32:​7, 8) ከኢሳይያስ ምዕራፍ 36 እስከ 39 ድረስ ተመዝግበው በሚገኙት የኢሳይያስ ትንቢቶች ውስጥ የተካተቱት ልብ የሚያንጠለጥሉ ክንውኖች ሲብራሩ ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር።

የራፋስቂስ ዲስኩር

7. ራፋስቂስ ማን ነው? ወደ ኢየሩሳሌምስ የተላከው ለምንድን ነው?

7 ሰናክሬም ከተማዋ እጅዋን እንድትሰጥ ይጠይቅ ዘንድ ራፋስቂስን (ይህ ወታደራዊ ማዕረግ እንጂ የሰውዬው የግል መጠሪያ ስም አይደለም) ከሌሎች ሁለት ሹማምንት ጋር አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። (2 ነገሥት 18:​17) እነዚህ ሰዎች ከከተማው ውጭ ከሕዝቅያስ መልእክተኞች ማለትም ከቤቱ አዛዥ ከኤልያቄም፣ ከጸሐፊው ከሳምናስና ከአሳፍ ልጅ ከታሪክ ጸሐፊው ከዮኣስ ጋር ተገናኙ።​—⁠ኢሳይያስ 36:​2, 3

8. ራፋስቂስ ኢየሩሳሌም ለውጊያ እንዳትነሳ ለማድረግ የሞከረው እንዴት ነው?

8 የራፋስቂስ ዓላማ ግልጽ ነበር። ይኸውም ኢየሩሳሌም ያለ ውጊያ እጅዋን እንድትሰጥ ማሳመን ነው። ገና ከመጀመሪያው በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር እንዲህ አለ:- “ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው? . . . አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው?” (ኢሳይያስ 36:​4, 5) ከዚያም ራፋስቂስ ፍርሃት ላይ የወደቁትን አይሁዳውያን ማንም የሚያስጥላቸው እንደሌለ በማሳሰብ ተሳለቀባቸው። እርዳታ ለማግኘት ወደ ማን ዘወር ማለት ይችላሉ? ‘የተቀጠቀጠ የሸንበቆ በትር’ ወደ ሆነው ወደ ግብጽ? (ኢሳይያስ 36:​6) በዚህ ወቅት ግብጽ እንደተቀጠቀጠ ሸንበቆ ሆና ነበር። እንዲያውም ቀድሞ የዓለም ኃይል የነበረችው ግብጽ ለጊዜው በኢትዮጵያ ድል ተደርጋ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በግብጽ ፈርዖን እንዲሆን የተሰየመው ንጉሥ ቲርሐቅም ቢሆን ግብጻዊ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ነበር። እርሱም በአሦር እጅ መውደቁ አይቀርም። (2 ነገሥት 19:​8, 9) በመሆኑም ግብጽ ራሷን እንኳ ማዳን ስለማትችል ለይሁዳ የምትፈይድላት ምንም ነገር አይኖርም።

9. ራፋስቂስ ይሖዋ ሕዝቡን ትቷል ብሎ እንዲደመድም ያደረገው ምንድን ነው? ይሁን እንጂ እውነታው ምን ነበር?

9 ቀጥሎ ደግሞ ራፋስቂስ ይሖዋን ስላሳዘናችሁት ስለ ሕዝቡ አይዋጋም ሲል ተከራከረ። “አንተም:- በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትለኝ፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን:- በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን?” (ኢሳይያስ 36:​7) አይሁዳውያን የኮረብታ መስገጃዎቹንና በምድሪቱ የነበሩትን መሠዊያዎች ማፍረሳቸው ወደ ይሖዋ መመለሳቸውን እንጂ ይሖዋን መተዋቸውን የሚያሳይ አልነበረም።

10. ይሁዳን የሚከላከሉት ሰዎች ቁጥር ጥቂትም ሆነ ብዙ ለውጥ የማያመጣው ለምንድን ነው?

10 ቀጥሎ ደግሞ ራፋስቂስ አይሁዳውያኑን በወታደራዊ ኃይሉ እጅግ እንደሚበልጣቸውም አሳሰባቸው። “የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ” በማለት በትዕቢት ተገዳደራቸው። (ኢሳይያስ 36:​8) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሁዳ የሰለጠኑ ፈረሰኞች ብዙ ወይም ጥቂት መሆናቸው የሚያመጣው ለውጥ ነበርን? የይሁዳ መዳን የተመካው በወታደራዊ ጥንካሬዋ ላይ ባለመሆኑ ይህ የሚያመጣው ለውጥ አልነበረም። ምሳሌ 21:​31 ይህንን ጉዳይ ሲገልጽ “ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል [“መዳን፣” NW] ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” ይላል። ከዚያም ራፋስቂስ የይሖዋ በረከት ያለው ከአይሁዳውያን ጋር ሳይሆን ከአሦራውያን ጋር እንደሆነ ሊያስረዳ ሞከረ። ይህ ባይሆንማ ኖሮ አሦራውያን ይህንን ያህል ወደ ይሁዳ ክልል ዘልቀው መግባት ባልቻሉ ነበር ሲል ተከራክሯል።​—⁠ኢሳይያስ 36:​9, 10

11, 12. (ሀ) ራፋስቂስ ‘በአይሁድ ቋንቋ’ መናገሩን መቀጠል የፈለገው ለምን ነበር? ያዳምጡት የነበሩትን አይሁዳውያንስ ሊፈትናቸው የሞከረው እንዴት ነው? (ለ) የራፋስቂስ አነጋገር በአይሁዳውያኑ ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል?

11 የሕዝቅያስን ወኪሎች ያሳሰባቸው የራፋስቂስ ቃል ከተማው ቅጥር አናት ላይ ሆነው በሚሰሙት ሰዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ነበር። በመሆኑም የአይሁድ ባለ ሥልጣናቱ “እኛ እንሰማለንና እባክህ፣ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን” ሲሉ ጠየቁ። (ኢሳይያስ 36:​11) ይሁንና ራፋስቂስ በሶርያ ቋንቋ የመናገር ሐሳብ አልነበረውም። እርሱ የፈለገው ግን አይሁዳውያኑ እጃቸውን እንዲሰጡ በማድረግ ኢየሩሳሌምን ያለ ውጊያ እጃቸው ውስጥ ማስገባት ስለነበር በሰዎቹ ውስጥ ጥርጣሬና ፍርሃት መዝራት ፈልጓል! (ኢሳይያስ 36:​12) በመሆኑም አሦራዊው ሰው “በአይሁድ” ቋንቋ መናገሩን ቀጠለ። የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች “ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ” ሲል አስጠነቀቀ። ከዚያም በመቀጠል አይሁዳውያኑ በአሦራውያን ግዛት ሥር ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራቸው የሚያሳይ መግለጫ በመስጠት አድማጮቹን ሊፈትናቸው ሞከረ:- “ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፣ ከጉድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፣ እህልና የወይን ጠጅ፣ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው።”​—⁠ኢሳይያስ 36:​13-17

12 በአሦራውያን ወረራ ምክንያት እህል መዝራት ስላልቻሉ በዚህ ዓመት አይሁዳውያን የሚሰበስቡት መከር የለም። በከተማው ቅጥር ላይ ሆነው ለሚያዳምጡት ሰዎች ብዙ ውኃ ያለው የወይን ፍሬ መብላትና ቀዝቃዛ ውኃ መጠጣት የሚለው ሐሳብ ልብ የሚሰርቅ መሆን አለበት። ይሁንና ራፋስቂስ የአይሁዳውያኑን ወኔ ማዳከሙን ገና አላበቃም።

13, 14. ራፋስቂስ እንዳለው ሳይሆን የሰማርያና የይሁዳ ሁኔታ የተለያየ የነበረው እንዴት ነው?

13 ራፋስቂስ ከነገር ኮሮጆው ውስጥ ሌላ የቃላት መርዙን ይመዝዛል። ሕዝቅያስ “እግዚአብሔር ያድነናል” ቢላቸው እንኳ እንዳያምኑት አይሁዳውያኑን አስጠነቀቀ። ራፋስቂስ የሰማርያ አማልክት አሥሩን ነገድ በአሦር እጅ ከመውደቅ ሊያስጥሉ እንዳልቻሉ አሳሰባቸው። አሦር ስላሸነፋቸው ሌሎች የአሕዛብ አማልክትስ ምን ለማለት ይቻላል? “የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ?” ሲል ጠየቀ። “የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?”​—⁠ኢሳይያስ 36:​18-20

14 እርግጥ የሐሰት አማልክትን የሚያገለግለው ራፋስቂስ አንድ ያልተረዳው ነገር ቢኖር በከሃዲዋ ሰማርያና በሕዝቅያስ ትተዳደር በነበረችው ኢየሩሳሌም መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን ነው። የሰማርያ የሐሰት አማልክት የአሥሩን ነገድ መንግሥት የሚያስጥሉበት ምንም ኃይል አልነበራቸውም። (2 ነገሥት 17:​7, 17, 18) በሌላ በኩል ግን በሕዝቅያስ የምትመራው ኢየሩሰሌም ለሐሰት አምልኮ ጀርባዋን ሰጥታ ይሖዋን ወደ ማገልገል ዘወር ብላ ነበር። ይሁን እንጂ ሦስቱ የአይሁዳውያኑ ወኪሎች ይህን ጉዳይ ለራፋስቂስ ለማስረዳት አልሞከሩም። “እነርሱም ዝም አሉ፣ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።” (ኢሳይያስ 36:​21) ኤልያቄም፣ ሳምናስ እና ዮአስ ወደ ሕዝቅያስ ተመልሰው ስለ ራፋስቂስ ቃል ኦፊሴላዊ ሪፖርት አቀረቡ።​—⁠ኢሳይያስ 36:​22

ሕዝቅያስ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ

15. (ሀ) አሁን ሕዝቅያስ ምን ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበታል? (ለ) ይሖዋ ለሕዝቡ ማረጋገጫ የሰጠው እንዴት ነው?

15 አሁን ንጉሥ ሕዝቅያስ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበታል። ኢየሩሳሌም ለአሦር በሰላም እጅዋን ትሰጣለች? ከግብጽ ጋር ኅብረት ትፈጥራለች? ወይስ ራሷን ችላ ውጊያ ትገጥማለች? ሕዝቅያስ ትልቅ ውጥረት ውስጥ ገብቷል። በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ይሖዋን እንዲጠይቁ ኤልያቄምና ሳምናስን ከሽማግሌዎችና ከካህናቱ ጋር በመላክ እርሱ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ገባ። (ኢሳይያስ 37:​1, 2) የንጉሡ መልእክተኞች ማቅ ለብሰው ወደ ኢሳይያስ በመምጣት እንዲህ አሉ:- “ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ . . . ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፣ አምላክህ እግዚአብሔርም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ።” (ኢሳይያስ 37:​3-5) አዎን፣ አሦራውያን እየተገዳደሩ ያሉት ሕያው የሆነውን አምላክ ነው! ይሖዋ መዘባበታቸውን ይመለከት ይሆን? ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት ለአይሁዳውያኑ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል:- “የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፣ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። እነሆ፣ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፣ ወሬንም ይሰማል፣ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 37:​6, 7

16. ሰናክሬም የላከው ደብዳቤ ምንድን ነው?

16 ይህ በእንዲህ እንዳለ ራፋስቂስ ንጉሡ በልብና በሚያደርገው ውጊያ ከሰናክሬም ጎን እንዲሠለፍ ተጠራ። ሰናክሬም የኢየሩሳሌምን ጉዳይ በኋላ ይመለስበታል። (ኢሳይያስ 37:​8) ያም ሆኖ የራፋስቂስ መሄድ የሕዝቅያስን ጭንቀት የሚቀንስ አልነበረም። ሰናክሬም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እጃቸውን ለመስጠት እምቢተኛ ከሆኑ ምን ሊጠብቃቸው እንደሚችል በመግለጽ የማስፈራሪያ ደብዳቤዎች ልኳል። “እነሆ፣ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? አባቶቼ ያጠፉአቸውን . . . የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? የሐማት ንጉሥ፣ የአርፋድ ንጉሥ፣ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ?” (ኢሳይያስ 37:​9-13) እንደ አሦራውያኑ አባባል ከሆነ ጥቃቱን ለመከላከል መሞከር ፋይዳ ቢስ ነገር ነው። እንዲያውም የባሰ ችግር መጋበዝ ይሆናል!

17, 18. (ሀ) ሕዝቅያስ ይሖዋ እንዲጠብቃቸው ለመጠየቅ ያነሳሳው ነገር ምን ነበር? (ለ) ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ለአሦራውያን መልስ የሰጠው እንዴት ነው?

17 የሚያደርገው ውሳኔ የሚያስከትለው ውጤት ያሳሰበው ሕዝቅያስ የሰናክሬምን ደብዳቤ ቤተ መቅደስ ውስጥ በይሖዋ ፊት ዘረጋው። (ኢሳይያስ 37:​14) ይሖዋ የአሦራውያኑን ዛቻ እንዲሰማ በመማጸን ያቀረበውን ልባዊ ጸሎት በሚከተሉት ቃላት ደምድሟል:- “እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፣ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ አድነን።” (ኢሳይያስ 37:​15-20) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ሕዝቅያስን ያሳሰበው ትልቁ ነገር የእርሱ መዳን ሳይሆን አሦራውያን ኢየሩሳሌምን ድል ቢያደርጓት በይሖዋ ስም ላይ የሚከመረው ነቀፋ ነበር።

18 ይሖዋ ለሕዝቅያስ ጸሎት መልስ የሰጠው በኢሳይያስ በኩል ነበር። ኢየሩሳሌም የሚመጣውን መጠበቅ እንጂ ለአሦር እጅዋን መስጠት የለባትም። ኢሳይያስ ለሰናክሬም እንደሚናገር ሆኖ ይሖዋ ለአሦራውያን የተናገረውን መልእክት በድፍረት አሰምቷል:- “ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፣ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ [በማላገጥ] ራስዋን ነቅንቃብሃለች።” (ኢሳይያስ 37:​21, 22) ቀጥሎ ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ያህል ነበር:- ‘በእስራኤል ቅዱስ ላይ የምትዘባበት አንተ ማን ነህ? ሥራህን አውቃለሁ። ልብህ ትልቅ ነው፤ ጉራህም ማብቂያ የለውም። በወታደራዊ ኃይልህ ታምነህ ብዙ ቦታዎችን ይዘሃል። ይሁን እንጂ የማትበገር አይደለህም። ዕቅድህን ሁሉ መና አስቀረዋለሁ። ድል አደርግሃለሁ። በሌሎች ላይ እንዳደረግኸውም አደርግብሃለሁ። በአፍንጫህ ስናጋ አስገብቼ ወደ አሦር እመልስሃለሁ!’​—⁠ኢሳይያስ 37:​23-29

“ይህም ምልክት ይሆንልሃል”

19. ይሖዋ ለሕዝቅያስ የሰጠው ምልክት ምንድን ነው? ይህስ ምን ማለት ነው?

19 ሕዝቅያስ የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ምን ዋስትና አለው? ይሖዋ እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቷል:- “ይህም ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፣ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ ታጭዱማላችሁ፣ ወይንንም ትተክላላችሁ ፍሬውንም ትበላላችሁ።” (ኢሳይያስ 37:​30) ዙሪያቸውን ለተከበቡት አይሁዳውያን ይሖዋ ምግብ የሚያገኙበትን መንገድ ያዘጋጃል። በአሦራውያን ወረራ ምክንያት እህል መዝራት ባይችሉም ካለፈው ዓመት መከር የቀረውን ቃርሚያ ይበላሉ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የሰንበት ዓመት በመሆኑ የነበሩበት ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ ምድሪቱ ማረፍ ነበረባት። (ዘጸአት 23:​11) ይሖዋ ሕዝቡ ድምፁን ቢታዘዙ ምድሪቱ ለእነርሱ የሚበቃ ፍሬ እንደምትሰጥ ቃል ገብቷል። ከዚያም በቀጣዩ ዓመት እንደተለመደው ዘርተው በድካማቸው ፍሬ ደስ ይላቸዋል።

20. ከአሦራውያን ጥቃት የሚያመልጡት ሰዎች ‘ወደ ታች ሥር የሚሰዱትና ፍሬ የሚያፈሩት’ እንዴት ነው?

20 ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ ሕዝቡን በቀላሉ ሊነቀል ከማይችል ተክል ጋር በማወዳደር ይናገራል:- “ያመለጠው የይሁዳ ቤት . . . ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፣ ወደ ላይም ያፈራል።” (ኢሳይያስ 37:​31, 32) አዎን፣ በይሖዋ የሚታመኑ ሁሉ የሚፈሩበት አንዳች ምክንያት አይኖርም። እነርሱንም ሆኑ ልጆቻቸውን ከምድሪቱ የሚነቅላቸው አይኖርም።

21, 22. (ሀ) ሰናክሬምን በተመለከተ ምን ትንቢት ተነግሯል? (ለ) ይሖዋ ስለ ሰናክሬም የተናገራቸው ቃላት የተፈጸሙት መቼና እንዴት ነው?

21 አሦራውያን በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚሰነዝሩት ዛቻስ ምን ለማለት ይቻላል? ይሖዋ እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል:- “ወደዚች ከተማ አይመጣም፣ ፍላጻንም አይወረውርባትም፣ በጋሻም አይመጣባትም፣ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም። በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፣ ወደዚችም ከተማ አይመጣም።” (ኢሳይያስ 37:​33, 34) ከነጭራሹ በአሦርና በኢየሩሳሌም መካከል ምንም ዓይነት ውጊያ አይደረግም። የሚያስገርመው ያለ ውጊያ የሚሸነፉት አሦራውያን እንጂ አይሁዳውያን አይሆኑም።

22 ይሖዋ ልክ በተናገረው መሠረት አንድ መልአክ በመላክ ምርጥ የተባለውን የሰናክሬም ሠራዊት 185,000 ወታደሮች ገድሏል። ይህ የተከናወነው በልብና ይመስላል። ሰናክሬም ከእንቅልፉ ሲነቃ የሠራዊቱ መሪዎች፣ አዛዦችና ኃያላን ተገድለዋል። ሰናክሬም ኃፍረት ተከናንቦ ወደ ነነዌ ተመለሰ። ይህ ከባድ ሽንፈት ቢገጥመውም የሐሰት አምላኩን ናሳራክን ማምለኩን ቀጥሏል። ሰናክሬም ከጥቂት ዓመታት በኋላ በናሳራክ መቅደስ ውስጥ ሲሰግድ ሳለ በሁለት ወንድ ልጆቹ ተገደለ። በድን የሆነው ናሳራክ በዚህ ጊዜም ሊታደገው ሳይችል ቀርቷል።​—⁠ኢሳይያስ 37:​35-38

የሕዝቅያስ እምነት ይበልጥ ተጠናከረ

23. ሰናክሬም መጀመሪያ በይሁዳ ላይ ሲዘምት ሕዝቅያስ ምን ችግር ገጥሞት ነበር? ይህ ችግር ሊያስከትል የሚችለውስ ቀውስ ምን ነበር?

23 ሰናክሬም በይሁዳ ላይ በተነሳበት በመጀመሪያው አጋጣሚ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ እንደሚሞት ነገረው። (ኢሳይያስ 38:​1) የ39 ዓመቱ ንጉሥ የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፋው። ያሳሰበው የራሱ ደህንነት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡ የወደፊት ዕጣም ጭምር ነበር። ኢየሩሳሌምና ይሁዳ የአሦራውያን ወረራ አጥልቶባቸዋል። ሕዝቅያስ ከሞተ ውጊያውን ማን ይመራል? እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሕዝቅያስ ንግሥናውን የሚረከበው ወንድ ልጅ አልነበረውም። ሕዝቅያስ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ይሖዋ ምሕረት እንዲያሳየው ተማጸነ።​—⁠ኢሳይያስ 38:​2, 3

24, 25. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቅያስ ጸሎት ምላሽ በመስጠት ሞገሱን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በ⁠ኢሳይያስ 38:​7, 8 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ምን ተዓምር አከናውኗል?

24 ይሖዋ ኢሳይያስን ሌላ መልእክት አስይዞ በጠና ወደ ታመመው ንጉሥ ሲልከው ኢሳይያስ እግሩ ገና ከቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ አልወጣም ነበር:- “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፣ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ። አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፣ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ።” (ኢሳይያስ 38:​4-6፤ 2 ነገሥት 20:​4, 5) ይሖዋ አንድ እንግዳ የሆነ ምልክት በመስጠት ይህንን ቃሉን ያረጋግጥለታል:- “እነሆ፣ በአካዝ የጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋር የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 38:​7, 8ሀ

25 እንደ ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ ገለጻ ከሆነ በንጉሣዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ ደረጃ አለ። ደረጃው ወደ ላይ የቆሙ አምዶች ሳይኖሩት አይቀርም። የፀሐይ ጨረር አምዶቹ ላይ ሲያርፍ ጥላቸው ደረጃው ላይ ይታያል። በደረጃው ላይ የሚታየውን የጥላውን ሂደት በመከታተል ሰዓቱ ምን ያህል እንደሆነ መገመት ይቻላል። አሁን ይሖዋ አንድ ተዓምር ሊያከናውን ነው። ጥላው በተለመደው መንገድ በደረጃዎቹ ላይ ወደታች ከወረደ በኋላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለሳል። እንዲህ ያለ ነገር ከቶ ማን ሰምቶ ያውቃል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ፀሐይም በጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ የወረደበት አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።” (ኢሳይያስ 38:​8ለ) ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሕዝቅያስ ከሕመሙ ዳነ። የዚህም ነገር ወሬ እስከ ባቢሎን ድረስ ተሰማ። የባቢሎን ንጉሥ ይህን ነገር ሲሰማ እውነቱን ለማረጋገጥ መልእክተኞቹን ወደ ኢየሩሳሌም ላከ።

26. የሕዝቅያስ ዕድሜ መራዘሙ ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዱ ምንድን ነው?

26 ሕዝቅያስ በተዓምራዊ መንገድ ጤናውን ካገኘ ከሦስት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያ ወንድ ልጁ ምናሴ ተወለደ። ምናሴ ግን ካደገ በኋላ ለአምላክ ርኅራኄ አድናቆት ሳያሳይ ቀርቷል። በአምላክ ርኅራኄ ባይሆን እርሱም ባልተወለደ ነበር! ይልቁንም ምናሴ አብዛኛውን ሕይወቱን ያሳለፈው በይሖዋ ዓይን እጅግ ክፉ የሆነ ነገር በመሥራት ነው።​—⁠2 ዜና መዋዕል 32:​24፤ 33:​1-6

የተሳሳተ ውሳኔ

27. ሕዝቅያስ ይሖዋ ላደረገለት ነገር ያለውን አድናቆት ያሳየው እንዴት ነው?

27 ሕዝቅያስ እንደ ቅድመ አያቱ እንደ ዳዊት የእምነት ሰው ነበር። ለአምላክ ቃል ከፍ ያለ ግምት ነበረው። ከ⁠ምሳሌ 25:​1 መረዳት እንደሚቻለው ዛሬ ከምሳሌ 25 እስከ 29 ያሉት የምሳሌ መጽሐፍ ምዕራፎች እንዲጠናቀሩ አድርጓል። አንዳንዶች መዝሙር 119⁠ንም ያቀናበረው እርሱ ነው ይላሉ። ሕዝቅያስ ከሕመሙ ከዳነ በኋላ ያቀናበረው ልብ የሚነካ መዝሙር ስሜቱን የሚገልጽ ሰው እንደነበር ያሳያል። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ሊያደርገው ከሚችለው ከማንኛውም ነገር የላቀው ‘በዕድሜው ዘመን ሁሉ’ ይሖዋን በቤተ መቅደሱ ማወደስ እንደሆነ ገልጿል። (ኢሳይያስ 38:​9-20) ስለ ንጹሕ አምልኮ ሁላችንም እንዲሁ ሊሰማን ይገባል!

28. ሕዝቅያስ በተዓምራዊ መንገድ ከተፈወሰ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያደረገው የተሳሳተ ውሳኔ ምን ነበር?

28 ሕዝቅያስ የታመነ ቢሆንም ፍጹም አልነበረም። ይሖዋ ከሕመሙ ከፈወሰው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባደረገው ውሳኔ ከባድ ስህተት ሠርቷል። ኢሳይያስ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ ታምሞ እንደ ተፈወሰ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ላከለት። ሕዝቅያስም ደስ አለው፣ ግምጃ ቤቱንም፣ ብሩንና ወርቁንም፣ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፣ መሣርያም ያለበትን ቤት ሁሉ፣ በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው፤ በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም።”​—⁠ኢሳይያስ 39:​1, 2 *

29. (ሀ) ሕዝቅያስ ሀብቱን ለባቢሎን ልዑክ ሲያስጎበኝ ምን አስቦ ሊሆን ይችላል? (ለ) የሕዝቅያስ የተሳሳተ ውሳኔ የሚያስከትለው መዘዝ ምን ይሆናል?

29 አሦር በይሖዋ መልአክ ከፍተኛ ሽንፈት ከገጠመው በኋላም ቢሆን ባቢሎንን ጨምሮ ብዙ ብሔራትን ያስፈራራ ነበር። ሕዝቅያስ የወደፊት አጋር ሊሆነኝ ይችላል ብሎ በማሰብ የባቢሎንን ንጉሥ ለማስደመም ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚፈልገው የይሁዳ ነዋሪዎች ከጠላቶቻቸው ጋር ግንባር እንዲፈጥሩ ሳይሆን በእርሱ እንዲታመኑ ነው! በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ይሖዋ የሕዝቅያስን የወደፊት ዕጣ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፣ በቤትህ ያለው ሁሉ፣ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፣ . . . ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ።” (ኢሳይያስ 39:​3-7) አዎን፣ ሕዝቅያስ በሀብቱ ሊያስደምመው ያሰበው ብሔር ራሱ ከጊዜ በኋላ የኢየሩሳሌምን ግምጃ ቤት በመበዝበዝ ዜጎቿን ባሪያ ያደርጋቸዋል። ሕዝቅያስ ግምጃ ቤቱን ለባቢሎናውያን ማስጎብኘቱ የስስት ፍላጎታቸውን ይበልጥ ከማነሳሳት በቀር የፈየደው ነገር የለም!

30. ሕዝቅያስ ጥሩ ዝንባሌ ያሳየው እንዴት ነው?

30 ሕዝቅያስ ግምጃ ቤቱን ለባቢሎናውያን ስላስጎበኘበት አጋጣሚ ሲናገር ይመስላል 2 ዜና መዋዕል 32:​26 እንዲህ ይላል:- “ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኩራት ሰውነቱን አዋረደ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።”

31. የሕዝቅያስ ሁኔታ ምን ይመስላል? ይህስ ምን ያስተምረናል?

31 ሕዝቅያስ አለፍጽምና ቢኖርበትም የእምነት ሰው ነበር። አምላኩ ይሖዋ ስሜት ያለው ሕያው አምላክ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ሕዝቅያስ የሚያስጨንቅ ነገር በገጠመው ጊዜ ከልቡ ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። ይሖዋም ጸሎቱን ሰምቶለታል። በቀረው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ ይሖዋ አምላክ ሰላም የሰጠው ሲሆን ሕዝቅያስም ስለዚህ ነገር አመስጋኝ ነበር። (ኢሳይያስ 39:​8) ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ለእኛ ይህን ያህል እውን ሆኖ ሊታየን ይገባል። ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ እንደ ሕዝቅያስ ጥበብ እንዲሰጠንና መውጫውን እንዲያሳየን “ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን” ይሖዋን እንለምን። (ያዕቆብ 1:​5) ጽናታችንንና በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማሳየታችንን ከቀጠልን አሁንም ሆነ ወደፊት ‘አጥብቀው ለሚፈልጉት ሁሉ ዋጋ እንደሚሰጥ’ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።​—⁠ዕብራውያን 11:​6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ዛሬ ባለው የዋጋ ተመን መሠረት ከ9.5 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ያወጣል።

^ አን.28 ሰናክሬም ድል ከተደረገ በኋላ የአካባቢው ብሔራት ወርቅ፣ ብርና ሌሎችንም ውድ ነገሮች በስጦታ መልክ ለሕዝቅያስ አምጥተውለታል። በ⁠2 ዜና መዋዕል 32:​22, 23, 27 ላይ “ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር” እንደሆነለትና “በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ” እንዳለ እናነባለን። ይህ ስጦታ ምናልባት ለአሦራውያን ግብር በሰጠበት ጊዜ አራቁቶት የነበረውን ግምጃ ቤቱን ለማሟላት ሳያስችለው አልቀረም።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 383 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ሕዝቅያስ ኃያሉ አሦር በተጋፈጠው ጊዜ በይሖዋ ታምኗል

[በገጽ 384 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 389 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሡ የይሖዋን ምክር ለመስማት ወደ ኢሳይያስ መልእክተኞችን ሰድዷል

[በገጽ 390 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝቅያስ አሦራውያን የሽንፈት ጽዋ ተጎንጭተው የይሖዋ ስም እንዲከበር ጸልዮአል

[በገጽ 393 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ መልአክ 185,000 አሦራውያንን ገድሏል