በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አባትና ዓመፀኛ ልጆቹ

አባትና ዓመፀኛ ልጆቹ

ምዕራፍ ሁለት

አባትና ዓመፀኛ ልጆቹ

ኢሳይያስ 1:​2-9

1, 2. ይሖዋ ዓመፀኛ ልጆች ሊኖሩት የቻሉት እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

እንደ ማንኛውም አፍቃሪ አባት ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አሟልቶላቸዋል። ምግብ፣ ልብስ እና መጠለያ በመስጠት ለብዙ ዓመታት ተንከባክቧቸዋል። አስፈላጊ ሆኖ በተገኘም ጊዜ ተግሳጽ ሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ ቅጣቱ ‘በመጠን እንጂ’ ከልክ ያለፈ አልነበረም። (ኤርምያስ 30:​11) ይህ አፍቃሪ አባት “ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፣ እነርሱም ዐመፁብኝ ” ብሎ ሲናገር ምን ያህል አዝኖ እንደነበር መገመት እንችላለን።​—⁠ኢሳይያስ 1:​2ለ

2 እዚህ ላይ የተጠቀሱት ዓመፀኛ ልጆች የይሁዳ ሰዎች ሲሆኑ የተከፋው አባት ደግሞ ይሖዋ አምላክ ነው። እንዴት ያሳዝናል! ይሖዋ የይሁዳን ሰዎች እየተንከባከበ በአሕዛብ መካከል ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል። ከጊዜ በኋላ በነቢዩ ሕዝቅኤል በኩል “ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ በአስቆጣ ቁርበትም ጫማ አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ በሐርም ከደንሁሽ” በማለት ያደረገላቸውን አስታውሷቸዋል። (ሕዝቅኤል 16:​10) ይሁንና በአጠቃላይ ሲታይ የይሁዳ ሰዎች ይሖዋ ያደረገላቸውን ነገር አላደነቁም። እንዲያውም ዓምፀውበታል።

3. ይሖዋ ስለ ይሁዳ ዓመፅ ሰማያትንና ምድርን የሚያስመሠክረው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ ዓመፀኛ የሆኑትን ልጆቹን በሚመለከት ይህን ከማለቱ አስቀድሞ “እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፣ ምድርም አድምጪ” ያለበት ጥሩ ምክንያት ነበረው። (ኢሳይያስ 1:2ሀ) ከዚህ ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ አለመታዘዝ የሚያስከትለውን መዘዝ በተመለከተ ለእስራኤላውያን ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ሰማይና ምድር ምሥክር ነበሩ ለማለት ይቻላል። ሙሴ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትገቡባት ምድር ፈጥናችሁ እንድትጠፉ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ አስመሰክራለሁ።” (ዘዳግም 4:​26) በዚህ በኢሳይያስ ዘመን ደግሞ ይሖዋ የማይታዩትን ሰማያትና የምትታየውን ምድር የይሁዳ ሕዝብ ለሚፈጽመው ዓመፅ እማኝ አድርጓቸዋል።

4. ይሖዋ ራሱን ለይሁዳ ያቀረበው እንደ ምን አድርጎ ነው?

4 የጉዳዩ ክብደት ቀጥተኛ ምክር መስጠትን የሚጠይቅ ነበር። ጊዜ በማይሰጠው እንዲህ ያለ ሁኔታ እንኳ ይሖዋ ራሱን ለይሁዳ ሕዝብ ያቀረበው በዋጋ እንደገዛቸው ባለቤታቸው አድርጎ ሳይሆን እንደ አንድ አፍቃሪ አባት አድርጎ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባውና ስሜት የሚነካ ነው። የይሁዳን ሕዝብ፣ ልጆቹ አስቸጋሪ የሆኑበት አባት ምን ዓይነት ሐዘን እንደሚሰማው በማሰብ ጉዳዩን ከዚያ አንጻር እንዲያዩት እየተማጸናቸው ነበር ለማለት ይቻላል። ምናልባትም በይሁዳ የነበሩ አንዳንድ ወላጆች እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ በራሳቸው ላይ ደርሶባቸው ሊሆን ስለሚችል በዚህ ምሳሌ ተነክተው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ በይሁዳ ላይ ያለውን ቅሬታ ሊናገር ነው።

ማስተዋል የሌላቸው እንስሳት ተሻሉ

5. ከእስራኤላውያን በተቃራኒ በሬና አህያ በተወሰነ መጠን ታማኝ መሆናቸውን የሚያሳዩት በምን መንገድ ነው?

5 ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል እንዲህ አለ:- “በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም፣ ሕዝቤም አላስተዋለም።” (ኢሳይያስ 1:3) * በሬና አህያ ጭነት ለመጎተት የሚያገለግሉ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ የተለመዱ እንስሳት ናቸው። በእርግጥም ደግሞ እነዚህ ተራ እንስሳት እንኳ በተወሰነ መጠን ታማኝነት የሚያሳዩና ጌታ እንዳላቸው የሚገነዘቡ መሆናቸው ከአይሁዳውያኑ የተሠወረ አልነበረም። በዚህ ረገድ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ በመካከለኛው ምሥራቅ በምትገኝ አንድ ከተማ አመሻሹ ላይ ምን ነገር እንዳስተዋሉ ልብ በል:- “ከብቶቹ ወደ ከተማዋ ቅጥር እንደገቡ ወዲያውኑ በየፊናቸው ያቀናሉ። እያንዳንዱ በሬ ባለቤቱንና ወደ ቤቱ የሚወስደውን መንገድ ጠንቅቆ ያውቃል። ጠባብና ጠመዝማዛ በሆኑት ግራ የሚያጋቡ መንገዶች ትንሽ እንኳ አይደናገርም። አህያውም ቢሆን ቀጥ ብሎ ወደ በሩ በመሄድ ‘ወደ ጌታው ጋጣ’ ያመራል።”

6. የይሁዳ ሕዝብ ሳያስተውል የቀረው እንዴት ነው?

6 በኢሳይያስ ዘመን እንዲህ ያሉትን ነገሮች ማየት የተለመደ በመሆኑ ይሖዋ ሊያስተላልፈው የፈለገው መልእክት ግልጽ ነበር:- አእምሮ የሌለው እንስሳ እንኳ ጌታውንና ጋጣውን ለይቶ ካወቀ የይሁዳ ሕዝብ ይሖዋን ስለተወበት ምክንያት ምን ሰበብ ሊያቀርብ ይችላል? በእርግጥም ‘አላስተዋሉም።’ ብልጽግናቸው ብሎም ሕልውናቸው የተመካው በይሖዋ ላይ መሆኑን በማስተዋል ረገድ አእምሮ አጥተው ነበር ለማለት ይቻላል። ይሖዋ በዚህ ጊዜም እንኳ የይሁዳን ሰዎች “ሕዝቤ” ብሎ መጥራቱ በእርግጥ ምህረቱን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው!

7. ለይሖዋ ዝግጅቶች አድናቆት እንዳለን ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

7 ይሖዋ ላደረገልን ነገር ሁሉ አድናቆት ሳናሳይ ቀርተን ማስተዋል የጎደለን ሆነን መገኘት አንፈልግም! ከዚህ ይልቅ “አቤቱ፣ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ” ያለውን መዝሙራዊ ዳዊትን መምሰል ይኖርብናል። (መዝሙር 9:​1) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ቅዱሱን ማወቅ ማስተዋል ነው’ በማለት ስለሚናገር ዘወትር ስለ ይሖዋ መማራችን ይህን ለማድረግ የሚያበረታታ ሆኖ እናገኘዋለን። (ምሳሌ 9:10) ከይሖዋ የምናገኛቸውን በረከቶች በተመለከተ በየዕለቱ ማሰላሰል አመስጋኞች እንድንሆንና ሰማያዊ አባታችንን ችላ እንዳንል ይረዳናል። (ቆላስይስ 3:​15) ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “ምስጋናን የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ።”​—⁠መዝሙር 50:​23

‘በእስራኤል ቅዱስ’ ላይ የተሰነዘረ ትልቅ ስድብ

8. የይሁዳ ሕዝብ “ኃጢአተኛ ወገን” ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ለምንድን ነው?

8 ኢሳይያስ ጠንከር ያሉ ቃላት በመጠቀም ስለ ይሁዳ ብሔር የሚናገረውን መልእክት ቀጠለ:- “ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ [“የበደል ብዛት የተጫናችሁ፣” 1980 ትርጉም ]፣ ክፉዎች ዘር፣ ርኩሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፣ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል።” (ኢሳይያስ 1:​4) የክፋት ድርጊቶች ተጠራቅመው ከባድ ሸክም ሊሆኑ ይችላሉ። በአብርሃም ዘመን ይሖዋ የሰዶምና ገሞራ ኃጢአት “እጅግ ከብዳለች” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 18:​20) በወቅቱ በይሁዳ ሕዝብ ላይ የሚታየውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር። ኢሳይያስ ‘የበደል ብዛት የተጫናቸው’ መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም “ክፉዎች ዘር፣ ርኩሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ” በማለት ጠርቷቸዋል። አዎን፣ የይሁዳ ሰዎች እንደ አጥፊ ልጅ ሆነው ነበር። “ወደ ኋላቸው እየሄዱ ተለይተዋል” ወይም ኒው ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን እንዳስቀመጠው ከሰማያዊ አባታቸው “ፈጽሞ ርቀዋል።”

9. ‘የእስራኤል ቅዱስ’ የሚለው ሐረግ መልእክት ምንድን ነው?

9 የይሁዳ ሰዎች የተከተሉት መጥፎ ጎዳና “ለእስራኤል ቅዱስ” ከፍተኛ ንቀት እንዳላቸው የሚያሳይ ነበር። በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ 25 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ የሚገኘው የዚህ ሐረግ መልእክት ምንድን ነው? ቅዱስ መሆን ማለት ንጹሕና የጠራ መሆን ማለት ነው። የይሖዋ ቅድስና አቻ አይገኝለትም። (ራእይ 4:​8) እስራኤላውያን በሊቀ ካህናቱ ጥምጥም ላይ ባለው የሚያንጸባርቅ የወርቅ ምልክት ላይ የተቀረጸውን “ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚል ጽሕፈት ባዩ ቁጥር ይህንን እውነት ያስታውሱ ነበር። (ዘጸአት 39:​30) በመሆኑም ኢሳይያስ ይሖዋን “የእስራኤል ቅዱስ” ብሎ ሲጠራው የይሁዳን ኃጢአት ክብደት ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱ ነበር። እንዲያውም እነዚህ ዓመፀኞች እየጣሱ የነበረው “ሰውነታችሁን ቀድሱ፣ ቅዱሳንም ሁኑ፣ እኔ ቅዱስ ነኝና” የሚለውን ለአባቶቻቸው የተሰጠውን ትእዛዝ ነው!​—⁠ዘሌዋውያን 11:​44

10. ‘ለእስራኤል ቅዱስ’ አክብሮት እንደጎደለን የሚያሳዩ ነገሮችን ከማድረግ የምንርቀው እንዴት ነው?

10 ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች እንደ ይሁዳ ሰዎች “የእስራኤልን ቅዱስ” ከማቃለል ፈጽሞ መራቅ ይኖርባቸዋል። የይሖዋን ቅድስና መኮረጅ አለባቸው። (1 ጴጥሮስ 1:​15, 16) ‘ክፉ የሆነውን ነገር መጥላት’ ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 97:​10) እንደ ፆታ ብልግና፣ ጣዖት አምልኮ፣ ስርቆትና ስካር ያሉት ርኩስ ልማዶች የክርስቲያን ጉባኤን ሊያቆሽሹ ይችላሉ። እነዚህን ልማዶች ለመተው ፈቃደኛ የማይሆኑ ሰዎች ከጉባኤ የሚወገዱበት ምክንያትም ይኸው ነው። ንስሐ ሳይገቡ እንዲህ ባለው የቆሸሸ ጎዳና የሚቀጥሉ ሰዎች በመጨረሻ የአምላክ ንጉሣዊ መስተዳድር ከሚያመጣቸው በረከት ተካፋይ የመሆን አጋጣሚያቸውን ያጣሉ። በእርግጥም እንዲህ ያሉት ክፉ ሥራዎች በሙሉ ‘ለእስራኤል ቅዱስ’ እንደ ትልቅ ስድብ ናቸው።​—⁠ሮሜ 1:​26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 5:​6-11፤ 6:​9, 10

ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ የታመመ

11, 12. (ሀ) ይሁዳ የነበረችበትን አስከፊ ሁኔታ ግለጽ። (ለ) ለይሁዳ ልናዝንላት የማይገባው ለምንድን ነው?

11 ቀጥሎ ኢሳይያስ የይሁዳ ሰዎች የነበሩበትን ሕመም በመጠቆም ለማስረዳት ሞክሯል። እንዲህ አለ:- “ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሠፋላችሁ?” በሌላ አባባል ኢሳይያስ ‘እስካሁን የተሰቃያችሁት አይበቃምን? በዓመፃችሁ በመቀጠል በራሳችሁ ላይ ለምን ተጨማሪ ጉዳት ታስከትላላችሁ?’ በማለት እየጠየቃቸው ነበር። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኖአል። ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም።” (ኢሳይያስ 1:​5, 6ሀ) ይሁዳ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ ታምማ ነበር። በመንፈሳዊ ሁኔታ ከራስ ፀጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ በደዌ ተመትታለች። እንዴት አስከፊ ውጤት ነው!

12 ለይሁዳ ልናዝንላት ይገባልን? በፍጹም! ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት መላው የእስራኤል ብሔር አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ቅጣት በተመለከተ ተገቢውን ማስጠንቀቂያ አግኝቶ ነበር። ማስጠንቀቂያው በከፊል እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በክፉ ቁስል ጉልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል።” (ዘዳግም 28:​35) በምሳሌያዊ ሁኔታ ይሁዳ እየደረሰባት ያለው ስቃይ የተከተለችው የማናለብኝነት ጎዳና ውጤት ነው። የይሁዳ ሰዎች ይሖዋን ታዝዘው ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ባልደረሰባቸው ነበር።

13, 14. (ሀ) ይሁዳ ምን ዓይነት ጉዳት ደርሶባታል? (ለ) ይሁዳ የደረሰባት ጉዳት የዓመፀኝነት ጎዳናዋን መለስ ብላ እንድትመለከት አድርጓታልን?

13 ኢሳይያስ፣ ይሁዳ ስላለችበት አሳዛኝ ሁኔታ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ቁስልና እበጥ የሚመግልም [“የተተለተለ፣” NW ] ነው፤ አልፈረጠም፣ አልተጠገነም፣ በዘይትም አልለዘበም።” (ኢሳይያስ 1:​6ለ) እዚህ ላይ ነቢዩ ስለ ሦስት ዓይነት ጉዳት ተናግሯል:- ቁስል (እንደ ሰይፍ ወይም ቢላዋ ባለ ስለት የተቆረጠ)፣ እበጥ (በድብደባ ምክንያት የተቆጣ ሰውነት)፣ የተተለተለ (የሚድንም የማይመስል አፉን የከፈተ ትኩስ ቁስል) ናቸው። እዚህ ላይ የተሰጠው መግለጫ የቅጣት ዓይነት የተፈራረቀበትንና ምንም ሰውነት ያልተረፈውን ሰው የሚያመለክት ነው። በእርግጥም ይሁዳ የነበረችበት ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነው።

14 ይሁዳ የነበረችበት አሳዛኝ ሁኔታ ወደ ይሖዋ እንድትመለስ አነሳስቷታልን? በፍጹም! ይሁዳ በ⁠ምሳሌ 29:​1 ላይ እንደተገለጸው ዓመፀኛ ሆና ነበር:- “ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፣ ፈውስም የለውም።” ብሔሩ ፈውስ የማይገኝለት ሆኖ ነበር። ኢሳይያስ እንደገለጸው ቁስሏ “አልፈረጠም፣ አልተጠገነም፣ በዘይትም አልለዘበም።” * ይሁዳ ገና አፉን ከከፈተና ካልታሸገ መላ አካልን ከሚያዳርስ ቁስል ጋር የተመሳሰለች ያህል ነው።

15. ራሳችንን ከመንፈሳዊ ሕመም መጠበቅ የምንችለው በምን መንገዶች ነው?

15 በይሁዳ ላይ ከደረሰው ነገር በመማር ራሳችንን ከመንፈሳዊ በሽታ መጠበቅ ይኖርብናል። እንደ አካላዊው ሕመም ሁሉ ይህም ቢሆን ማንኛችንንም ሊያጠቃ ይችላል። ደግሞስ በሥጋ ምኞት የማይፈተን ማን አለ? ስግብግብነትና ከልክ ያለፈ የተድላ ምኞት በልባችን ውስጥ ሥር ሊሰዱ ይችላሉ። በመሆኑም ራሳችንን ‘ክፋትን መጸየፍን’ እና ‘ከመልካም ነገር ጋር መተባበርን’ ማስለመድ ይኖርብናል። (ሮሜ 12:​9) በተጨማሪም በዕለታዊ ሕይወታችን የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ማፍራት ይኖርብናል። (ገላትያ 5:​22, 23) ይህንን በማድረግ ከራስ ጠጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ በመንፈሳዊ በሽታ የተመታችው ይሁዳ ከገጠማት ዓይነት ሁኔታ እንጠበቃለን።

ባድማ የሆነ ምድር

16. (ሀ) ኢሳይያስ የይሁዳን ምድር የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንዶች እነዚህ ቃላት የተነገሩት በንጉሥ አካዝ የግዛት ዘመን መሆን አለበት የሚሉት ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ እነዚህን ቃላት እንዴት ልንረዳቸው እንችል ይሆናል?

16 አሁን ኢሳይያስ ከጤና ጋር የተያያዘ ምሳሌውን ተወት በማድረግ ስለ ይሁዳ ምድር መናገር ጀምሯል። ጦርነት ጠባሳ ጥሎበት የሄደውን ሜዳ ትኩር ብሎ እየተመለከተ እንዳለ ሰው እንዲህ ይላል:- “ምድራችሁ ባድማ ናት፤ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፤ እርሻችሁንም በፊታችሁ ሌሎች ይበሉታል፤ ባዕድ እንዳፈረሳት ምድር ባድማ ሆነች።” (ኢሳይያስ 1:​7 ) እነዚህ ቃላት በኢሳይያስ መጽሐፍ መጀመሪያ አካባቢ ተጠቅሰው ይገኙ እንጂ የተነገሩት ግን በኋለኛው የነቢዩ ዕድሜ ምናልባትም በክፉው ንጉሥ በአካዝ ዘመን ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ምሁራን አሉ። የዖዝያን የግዛት ዘመን ብልጽግና የነበረበት በመሆኑ እንዲህ ያለው አስከፊ ገጽታ በዚያ ወቅት ሊኖር አይችልም ይላሉ። የኢሳይያስ መጽሐፍ የጊዜውን ቅደም ተከተል ጠብቆ ነው የተጻፈው ብሎ በእርግጠኝነት ለመናገርም አይቻልም። ይሁን እንጂ ስለ ባድማነት የሚናገሩት የኢሳይያስ ቃላት ትንቢታዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢሳይያስ ከላይ ያለውን ነገር ሲናገር በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የተሠራበትን ዘዴ መጠቀሙ ሊሆን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ ፊት የሚሆኑት ነገሮች ልክ እንደተፈጸሙ ሆነው የተገለጹበት ቦታ ያለ ሲሆን ይህም የትንቢቱ ፍጻሜ የማይቀር መሆኑን ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው።​—⁠ከ⁠ራእይ 11:​15 ጋር አወዳድር።

17. ይሁዳ ባድማ እንደምትሆን የሚናገረው ትንቢታዊ መግለጫ ለይሁዳ ሕዝብ እንግዳ የማይሆንበት ለምንድን ነው?

17 ያም ሆነ ይህ ይሁዳ ባድማ እንደምትሆን የሚናገረው ትንቢታዊ መግለጫ ለዚህ አንገተ ደንዳናና የማይታዘዝ ሕዝብ ድንገተኛ ነገር አልነበረም። ካልታዘዙ ምን እንደሚገጥማቸው ይሖዋ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት እንደሚከተለው ሲል አስጠንቅቋቸው ነበር:- “ምድሪቱን የተፈታች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባት ጠላቶቻችሁም በእርስዋ የተነሣ ይደነቃሉ። እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፣ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፣ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።”​—⁠ዘሌዋውያን 26:​32, 33፤ 1 ነገሥት 9:​6-8

18-20. በ⁠ኢሳይያስ 1:​7, 8 ላይ የሚገኙት ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት መቼ ነው? በዚያ ጊዜ ይሖዋ ‘ጥቂቶችን ያስቀረው’ እንዴት ነው?

18 በ⁠ኢሳይያስ 1:​7, 8 ላይ የሚገኙት ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት እስራኤል በጠፋችበትና በይሁዳም ላይ ከፍተኛ ጥፋትና ስቃይ ባስከተለው የአሦራውያን ወረራ ወቅት ነው። (2 ነገሥት 17:​5, 18፤ 18:​11, 13፤ 2 ዜና መዋዕል 29:​8, 9) ይሁን እንጂ ይሁዳ ሙሉ በሙሉ አልጠፋችም። ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፣ በዱባ አትክልትም ውስጥ እንዳለ ጎጆ፣ እንደ ተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች።”​—⁠ ኢሳይያስ 1:​8

19 በዚህ ሁሉ ውድመት መሃል ‘የጽዮን ሴት ልጅ’ ማለትም ኢየሩሳሌም ሳትጠፋ ትቀራለች። ይሁን እንጂ እርሷም ብትሆን በወይን ቦታ እንዳለ ደሳሳ ቤት ወይም በዱባ አትክልት ውስጥ እንዳለ የጠባቂ ዳስ ብቻዋን ተጋልጣ ትታያለች። አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ምሁር የአባይን ወንዝ ተከትለው ሲጓዙ ያዩአቸው ተመሳሳይ ዳሶች የኢሳይያስን ቃላት እንዲያስታውሱ አድርገዋቸዋል። እነዚሁኑ ዳሶች “ነፋስ መከለያ ቢጤ” ሲሉ ጠርተዋቸዋል። በይሁዳ የመከር መሰብሰቢያው ወቅት ካለፈ በኋላ እነዚህ ዳሶች እንዲሁ ተትተው ይወላልቃሉ። በድል አድራጊው የአሦራውያን ሠራዊት ፊት ኢየሩሳሌም የቱንም ያህል አቅመ ቢስ መስላ ብትታይ ሕልውናዋን ጠብቃ ትቆያለች።

20 ኢሳይያስ ይህንን ትንቢታዊ መልእክት እንደሚከተለው በማለት ይደመድማል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፣ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር።” (ኢሳይያስ 1:​9) * ይሖዋ በመጨረሻ ይሁዳን በአሦራውያን ክንድ ከመደቆስ ይታደጋታል። ሰዶምና ገሞራ እንደጠፉት ይሁዳ ሙልጭ ብላ አትጠፋም። በሕይወት ትቀጥላለች።

21. ባቢሎን ኢየሩሳሌምን ካጠፋች በኋላ ይሖዋ ‘ጥቂት ቀሪዎችን’ የተወው ለምንድን ነው?

21 ከአንድ መቶ የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ ይሁዳ እንደገና ሌላ አደጋ አጠላባት። ሕዝቡ በአሦራውያን አማካኝነት ከተሰጠው ተግሳጽ አልተማረም። “እነርሱ ግን . . . በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፣ ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።” ከዚህም የተነሣ ‘ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ የእግዚአብሔር ቁጣ በእነርሱ ላይ ሆነ።’ (2 ዜና መዋዕል 36:​16) የባቢሎናውያኑ ንጉሠ ነገሥት ናቡከደነፆር ይሁዳን ድል አድርጎ ተቆጣጠራት። በዚህ ጊዜ ግን “በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ” ያለ ነገር እንኳ አልቀረላትም። ኢየሩሳሌም ሳትቀር ተደመሰሰች። (2 ዜና መዋዕል 36:​17-21) ያም ሆኖ ይሖዋ ‘ጥቂቶች እንዲተርፉ አድርጓል።’ የይሁዳ ሰዎች 70 ዓመት በግዞት ቢቆዩም ይሖዋ የብሔሩ ሕልውና እንዲቀጥል በተለይ ደግሞ ተስፋ የተሰጠበት መሲህ የሚገኝበት የዳዊት መስመር እንዳይጠፋ አድርጓል።

22, 23. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋ ‘ጥቂት ቀሪዎችን’ የተወው ለምንድን ነው?

22 እስራኤላውያን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የደረሰባቸው መከራ የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ሆነው የተቀበሉት የመጨረሻው መከራ ነበር። ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ሆኖ በመጣ ጊዜ ብሔሩ ሊቀበለው ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ይሖዋም እነርሱን ሳይቀበላቸው ቀርቷል። (ማቴዎስ 21:​43፤ 23:​37-39፤ ዮሐንስ 1:​11) ይሖዋ ከዚህ በኋላ በምድር ላይ የተለየ ሕዝብ አይኖረውም ማለት ነውን? በፍጹም። ሐዋርያው ጳውሎስ ኢሳይያስ 1:​9 ሌላ ፍጻሜ እንደሚኖረው ጠቁሟል። ከሰፕቱጀንት ትርጉም በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኢሳይያስም እንደዚሁ:- ጌታ ፀባዖት ዘር ባላስቀረልን እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር ብሎ አስቀድሞ ተናገረ።”​—⁠ሮሜ 9:​29

23 በዚህ ወቅት በሕይወት የተረፉት በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ያመኑ አይሁዳውያን ነበሩ። በኋላ ግን ያመኑ አሕዛብም ከእነርሱ ጋር ተቀላቅለዋል። አንድ ላይ ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ የተባለውን አዲሱን የእስራኤል ብሔር መሥርተዋል። (ገላትያ 6:​16፤ ሮሜ 2:​29) በ70 እዘአ በአይሁዳውያን የነገሮች ሥርዓት ላይ ከደረሰው ጥፋት የተረፈው ይህ ‘ዘር’ ነው። በእርግጥም ደግሞ ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ ዛሬም ከእኛ ጋር አለ። ዛሬ “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ለመሆን የበቁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ያመኑ ሰዎች ከብሔራት ተውጣጥተው ከእነርሱ ጋር በመተባበር ላይ ናቸው።​—⁠ራእይ 7:​9

24. እስከ ዛሬ በሰው ዘር ላይ ከደረሱት ጥፋቶች ሁሉ ከከፋው ጥፋት በሕይወት ለመትረፍ የሚፈልጉ ሰዎች ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

24 በቅርቡ ይህ ዓለም ከአርማጌዶን ጦርነት ጋር ፊት ለፊት ይፋጠጣል። (ራእይ 16:​14, 16) ይህ አሦራውያንም ሆነ ባቢሎናውያን ይሁዳን መውረራቸው ካደረሰው ጉዳት እንዲሁም በ70 እዘአ ሮማውያን በይሁዳ አውራጃ ላይ ካደረሱት ውድመት እጅግ የሚከፋ ቢሆንም በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ። (ራእይ 7:​14) እንግዲያውስ ሁላችንም ኢሳይያስ ስለ ይሁዳ የተናገራቸውን ቃላት መመርመራችን ምንኛ አንገብጋቢ ነው! እነዚህ ቃላት በዚያ ዘመን የነበሩትን ሰዎች ሕይወት ለማትረፍ አስችለዋል። ዛሬም ቢሆን የሚያምኑትን ሰዎች ሕይወት ሊያተርፉ ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 እዚህ ጥቅስ ላይ “እስራኤል” የሚለው መጠሪያ የሚያመለክተው ሁለቱን ነገድ የይሁዳ መንግሥት ነው።

^ አን.14 ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት በዘመኑ የነበረውን የሕክምና ልማድ የሚያንጸባርቁ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ የሆኑት ኢ ኤች ፕላመትረ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “መግል የያዘውን ቁስል ‘ማሰር’ ወይም ‘ማፍረጥ’ ፈሳሹን ለማውጣት የሚደረግ የመጀመሪያ እርምጃ ነው፤ ከዚያም በሕዝቅያስ ሁኔታ እንደታየው (ምዕ. xxxviii. 21) መድኃኒት የሚሆን ነገር ተደርጎበት ‘ይጠገናል።’ ከዚያም ምናልባት በሉቃስ x. 34 ላይ እንዳለው ቁስሉን ለማጽዳት ሲባል እንደ ዘይት ያሉ ወይም ቁስሉን የሚመዘምዙ ሌሎች ፈሳሾች ይደረጉበታል።”

^ አን.20 በሲ ኤፍ ካይል እና በኤፍ ዴሊሽ የተዘጋጀው ኮሜንታሪ ኦን ዚ ኦልድ ቴስታመንት እንዲህ ይላል:- “የነቢዩ ንግግር እዚህ ላይ ትንሽ ቆም ብሏል። እዚህ ቦታ ላይ ለሁለት ክፍል መለየቱን የምናውቀው በኢሳይያስ 1 ቁጥር 9 እና 10 መካከል በተተወው ክፍት ቦታ ነው። ክፍት ቦታ በመተው ወይም የተጀመረውን መስመር ድንገት በማቋረጥ ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ ክፍሎችን የመለየት ዘዴ የአናባቢ ወይም የአደማመፅ ምልክቶችን ከመጠቀም አንጻር ሲታይ በጣም ጥንታዊ በሆነ ልማድ ላይ የተመሠረተ ነው።”

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዶምና ገሞራ ባድማ ሆነው እንደቀሩት ይሁዳ ለዘላለም ባድማ ሆና አትቀርም