ኢሳይያስ ይሖዋ ስለሚያከናውነው ‘እንግዳ ሥራ’ ይተነብያል
ምዕራፍ ሃያ ሁለት
ኢሳይያስ ይሖዋ ስለሚያከናውነው ‘እንግዳ ሥራ’ ይተነብያል
1, 2. እስራኤልና ይሁዳ ከስጋት ያረፉት ለምንድን ነው?
እስራኤልና ይሁዳ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከስጋት እፎይ ይላሉ። መሪዎቻቸው አደገኛ በሆነው ዓለም ውስጥ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ በማሰብ ከታላላቅና ኃያላን ብሔራት ጋር የማያዛልቅ ፖለቲካዊ ኅብረት ፈጥረዋል። የእስራኤል ዋና ከተማ የሆነችው ሰማርያ ወደ አጎራባቿ ሶርያ ዞር ብላ የነበረ ሲሆን የይሁዳዋ መዲና ኢየሩሳሌም ደግሞ ተስፋዋን የጣለችው በጨካኙ አሦር ላይ ነበር።
2 በሰሜናዊው መንግሥት ሥር ያለው ሕዝብ የወርቅ ጥጃ ማምለኩን ቀጥሏል። ይሁንና አንዳንዶቹ በአዳዲስ ፖለቲካዊ አጋሮች መታመናቸው እንዳለ ሆኖ ይሖዋም ይጠብቀናል ብለው አስበው ይሆናል። ይሁዳም እንዲሁ በይሖዋ ጥበቃ መታመን እንደምትችል አስባለች። ደግሞስ በመዲናዋ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የራሱ የይሖዋ ቤተ መቅደስ አይደለምን? ይሁን እንጂ ሁለቱንም ብሔራት ያልጠበቁት ነገር ያጋጥማቸዋል። ይሖዋ ከሥርዓት ውጭ ለሆኑት ሕዝቦቹ እንግዳ ሆኖ የሚታይ ነገር እንደሚያከናውን ኢሳይያስ በመንፈስ ተነሳስቶ ትንቢት እንዲናገር አድርጓል። እርሱ የተናገራቸው ቃላት ደግሞ ዛሬ ላለነው ለእያንዳንዳችን ትልቅ ትምህርት ያዘሉ ናቸው።
‘የኤፍሬም ሰካራሞች’
3, 4. ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት የሚኩራራው በምንድን ነው?
3 ኢሳይያስ በሚከተሉት ያልተጠበቁ ቃላት ትንቢቱን ይጀምራል:- “ለኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል፣ በወይን ጠጅ ለተሸነፉ በወፍራም [“በለምለሙ፣” የ1980 ትርጉም] ሸለቆአቸው ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብሩ ጌጥ አበባ ወዮ! እነሆ፣ በጌታ ኢሳይያስ 28:1-3
ዘንድ ኃያል ብርቱ የሆነ አለ። እንደ በረዶ ወጨፎ፣ . . . በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላል። የኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል በእግር ይረገጣል።”—4 ከአሥሩ ሰሜናዊ ነገዶች መካከል ጉልህ ስፍራ ያለው የኤፍሬም ነገድ መላውን የእስራኤል መንግሥት በመወከል ተጠርቷል። ዋና ከተማዋ ሰማርያ የምትገኘው በጣም ውብና ለዓይን ማራኪ በሆነው ‘በለምለሙ የሸለቆ ራስ’ ላይ ነው። የኤፍሬም መሪዎች መቀመጫው በኢየሩሳሌም ከሆነው ከዳዊት ንጉሣዊ አገዛዝ ነፃ መሆናቸውን እንደ ‘ክብር ጌጥ’ በመቁጠር ይኩራሩ ነበር። ይሁን እንጂ ይሁዳን ለማጥቃት ከሶርያ ጋር ወግነው የነበሩ ሰዎች በመሆናቸው መንፈሳዊ አቅላቸውን የሳቱ ‘ሰካራሞች’ ነበሩ። አሁን ከፍተኛ ግምት የሰጡት ነገር ሁሉ በወራሪዎቻቸው እግር የሚረገጥበት ጊዜ ደርሶ ነበር።—ከኢሳይያስ 29:9 ጋር አወዳድር።
5. እስራኤል የነበረችበት አደገኛ ሁኔታ ምንድን ነው? ይሁን እንጂ ኢሳይያስ ምን ተስፋ እንዳለ ገልጿል?
5 ኤፍሬም ያለበትን ይህንን አደገኛ ሁኔታ አልተገነዘበም። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በወፍራሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ጌጥ አበባ ከመከር በፊት አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ ሰው ባያት ጊዜ በእጁ እንዳለች ይበላታል።” (ኢሳይያስ 28:4) ኤፍሬም በአሦር ፊት እንደ አንድ ጣፋጭ ጉርሻ ስለሚሆን በአንድ ጊዜ ዋጥ ያደርገዋል። ታዲያ ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነውን? አብዛኛውን ጊዜ እንደሚታየው የኢሳይያስ የፍርድ ትንቢቶች ተስፋም ያዘሉ ናቸው። ብሔሩ ቢጠፋም የታመኑ ግለሰቦች በይሖዋ እርዳታ በሕይወት ይተርፋሉ። “በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለቀሩት ሕዝቡ የክብር ዘውድና የጌጥ አክሊል ይሆናል፤ በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ፣ ሰልፉን ወደ በር ለሚመልሱም ኃይል ይሆናል።”—ኢሳይያስ 28:5, 6
‘ስተዋል’
6. እስራኤል ጥፋት የደረሰባት መቼ ነው? ይሁን እንጂ ይሁዳ መፈንደቅ የማይገባት ለምንድን ነው?
6 የሰማርያ የፍርድ ቀን የመጣው በ740 ከዘአበ አሦር ምድሪቱን
ባጠፋበት ጊዜ ሲሆን በዚህ ጊዜ የሰሜናዊው መንግሥት ሕልውና አክትሟል። ይሁዳስ? በመጀመሪያ ግዛቷ በአሦር ተወርሮ ይቆይና ከጊዜ በኋላ ዋና ከተማዋን የምትደመስሰው ባቢሎን ትሆናለች። ይሁን እንጂ በኢሳይያስ የሕይወት ዘመን የይሁዳ ቤተ መቅደስና የክህነት ሥርዓቱ ሥራውን ይቀጥላል። ነቢያቶቿም ትንቢት መናገራቸውን ይቀጥላሉ። ይሁዳ በሰሜናዊ አጎራባቿ ላይ በሚደርሰው ጥፋት ልትፈነድቅ ይገባልን? በፍጹም! ይሖዋ ከይሁዳም ጋር ቢሆን ጉዳይ አለው። መሪዎቿ ዓመፀኛና እምነት የለሽ በመሆናቸው ሳይቀጣቸው አያልፍም።7. የይሁዳ መሪዎች የሰከሩት በምን መንገድ ነው? ውጤቱስ ምንድን ነው?
7 ኢሳይያስ ለይሁዳ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፣ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፣ ኢሳይያስ 28:7, 8) እንዴት ያለ አስጸያፊ ነገር ነው! በአምላክ ቤት ውስጥ ቃል በቃል መስከር ራሱ ትልቅ ነውር ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ካህናትና ነቢያት ሙሉ በሙሉ በሰብዓዊ አጋሮቻቸው ላይ ከመታመናቸው የተነሣ አእምሮአቸው ስለጨለመ መንፈሳዊ ስካር ላይ ወድቀዋል። እነርሱ የተከተሉት ጎዳና ከሁሉ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ በማሰብ ምናልባትም የይሖዋ ጥበቃ በቂ ሆኖ ባይገኝ አስፈላጊውን አስተማማኝ ድጋፍ ማግኘት የሚያስችል ዕቅድ ነድፈናል ብለው ራሳቸውን አታልለዋል። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች መንፈሳዊ አቅላቸውን በሳቱበት በዚህ ወቅት ከአፋቸው የሚወጣው በአምላክ ተስፋዎች ላይ እውነተኛ እምነት እንደሌላቸው የሚያጋልጥ ንጹሕ ያልሆነ የዓመፅ አነጋገር ነው።
በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፣ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ በራእይ ይስታሉ፣ በፍርድም ይሰናከላሉ። ማዕዱ ሁሉ ትፋትንና ርኩሰትን ተሞልቶአታል፤ ንጹሕ ስፍራ እንኳ የለም።” (8. ለኢሳይያስ መልእክት የተሰጠው ምላሽ ምን ነበር?
8 የይሁዳ መሪዎች ለይሖዋ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው? ኢሳይያስ እንደ ሕፃን እንደቆጠራቸው አድርገው በመክሰስ ያላግጡበታል:- “እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን? ትእዛዝ በትእዛዝ፣ ትእዛዝ በትእዛዝ፣ ሥርዓት በሥርዓት፣ ሥርዓት በሥርዓት፣ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው።” (ኢሳይያስ 28:9, 10) ኢሳይያስ የሚናገረው ነገር ምንኛ ተደጋጋሚና እንግዳ ሆኖባቸው ነበር! በተደጋጋሚ ‘የይሖዋ ትእዛዝ ይህ ነው! የይሖዋ ትእዛዝ ይህ ነው! የይሖዋ ሥርዓት ይህ ነው! የይሖዋ ሥርዓት ይህ ነው!’ ይላቸው ነበር። * ይሁን እንጂ በቅርቡ ይሖዋ የይሁዳን ነዋሪዎች በተግባር ‘ያነጋግራቸዋል።’ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ባዕድ ሰዎችን ማለትም የባቢሎንን ሠራዊት ይልክባቸዋል። ይህ ሠራዊት የይሖዋን “ትእዛዝ” በማስፈጸም ይሁዳን ያጠፋታል።—ኢሳይያስ 28:11-13ን አንብብ።
ዛሬ ያሉ መንፈሳዊ ሰካራሞች
9, 10. ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ለኋለኞቹ ትውልዶች ትርጉም የነበራቸው መቼና እንዴት ነው?
9 የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በጥንቶቹ እስራኤልና ይሁዳ ላይ ብቻ ነበርን? በፍጹም! ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ የኢሳይያስን ቃላት በመጥቀስ በዘመናቸው በነበረው ብሔር ላይ እንደሚሠራ ተናግረዋል። (ኢሳይያስ 29:10, 13፤ ማቴዎስ 15:8, 9፤ ሮሜ 11:8) ዛሬም ቢሆን በኢሳይያስ ዘመን ከነበረው ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ አለ።
10 ዛሬ በፖለቲካ የሚታመኑት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ናቸው። ታላላቅ የሚባሉ የዚህ ዓለም ሰዎች ከእነርሱ ጋር መመካከራቸው ስለሚያስደስታቸው በፖለቲካዊ ጉዳዮች እጃቸውን በማስገባት እንደ እስራኤልና ይሁዳ ሰካራሞች መቆም አቅቷቸው እየተንገዳገዱ ነው። ንጹሕ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከመናገር ይልቅ ከአፋቸው ርኩስ ነገር ይወጣል። መንፈሳዊ እይታቸውም ደብዝዟል። የሰውን ልጅ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመምራት አይችሉም።—ማቴዎስ 15:14
11. የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው?
11 የሕዝበ ክርስትና መሪዎች የሰው ልጅ እውነተኛ ተስፋ በሆነው በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ሲሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ሥራ መሪዎቹ የሚመለከቱት እንዴት ነው? አይገባቸውም። በእነርሱ ዓይን የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ነገር እየደጋገመ እንደሚንተባተብ ሕፃን ናቸው። የሃይማኖት መሪዎቹ እነዚህን መልእክተኞች በመናቅ ያፌዙባቸዋል። በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት አይሁዳውያን የአምላክን መንግሥት ወደ ጎን ገሸሽ ከማድረጋቸውም ሌላ መንጎቻቸው ስለዚህ ጉዳይ እንዲሰሙም አይፈልጉም። (ማቴዎስ 23:13) በመሆኑም ይሖዋ ምስኪን በሆኑት መልእክተኞቹ ብቻ እየተናገረ እንደማይቀጥል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ራሳቸውን ለአምላክ መንግሥት የማያስገዙ ሁሉ ‘የሚሰበሩበትና ተጠምደው የሚያዙበት’ ማለትም ጨርሶ የሚጠፉበት ጊዜ ይመጣል።
“ከሞት ጋር ቃል ኪዳን”
12. ይሁዳ ‘ከሞት ጋር’ ገባሁት የምትለው ‘ቃል ኪዳን’ ምንድን ነው?
12 ኢሳይያስ የሚናገረውን ነገር እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እናንተም:- ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፣ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፣ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም” ብላችኋል። (ኢሳይያስ 28:14, 15) የይሁዳ መሪዎች የፈጠሩት ፖለቲካዊ ጥምረት ከሽንፈት እንደሚያስጥላቸው በጉራ ይናገሩ ነበር። ሞት እንዳይደርስባቸው “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን” እንደገቡ ተሰምቷቸዋል። ይሁን እንጂ ከንቱ የሆነው መሸሸጊያቸው አያስጥላቸውም። አጋሮቻቸውም የሐሰት አጋሮች ናቸው። ዛሬም በተመሳሳይ ሕዝበ ክርስትና ከዓለም መሪዎች ጋር የመሠረተችው የቅርብ ወዳጅነት ይሖዋ እርሷን በፍርድ የሚጠይቅበት ጊዜ ሲደርስ ሊያስጥላት አይችልም። እንዲያውም መጥፊያዋ ይሆናል።—ራእይ 17:16, 17
13. ‘የተፈተነው የማዕዘን ድንጋይ’ ማን ነው? ሕዝበ ክርስትና ሳትቀበለው የቀረችው እንዴት ነው?
13 ታዲያ እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ዘወር ማለት ያለባቸው ወዴት ነው? ኢሳይያስ ቀጥሎ የመዘገበው ነገር ይሖዋ የሰጠውን የተስፋ ቃል ነው:- “እነሆ፣ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፣ የከበረውን፣ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፤ የሚያምንም አያፍርም። ለገመድ ፍርድን ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፤ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፣ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ።” (ኢሳይያስ 28:16, 17) ኢሳይያስ እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የታመነው ንጉሥ ሕዝቅያስ በጽዮን የነገሠ ሲሆን መንግሥቱ ሊድን የቻለው ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ በወሰደው እርምጃ እንጂ ከጎረቤቶቹ ጋር ኅብረት በመፍጠሩ አልነበረም። ይሁን እንጂ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት በሕዝቅያስ ላይ አልነበረም። ሐዋርያው ጴጥሮስ የኢሳይያስን ቃላት በመጥቀስ በሕዝቅያስ የዘር መስመር ብዙ ዘመናት ቆይቶ የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘የተፈተነ የማዕዘን ድንጋይ’ እንደሆነና በእርሱ የሚያምን ሁሉ የሚፈራበት አንዳች ምክንያት እንደሌለ ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 2:6) የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው ቢጠሩም ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ለማድረግ እምቢተኞች መሆናቸው እንዴት የሚያሳዝን ነው! ይሖዋ በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን መንግሥት እንዲያመጣ ከመጠበቅ ይልቅ በዓለም ላይ ታዋቂነትንና ሥልጣንን ለማግኘት ይጣጣራሉ።—ማቴዎስ 4:8-10
14. ይሁዳ ‘ከሞት ጋር ያደረገችው ቃል ኪዳን’ የሚፈርሰው መቼ ነው?
14 ይሖዋ የባቢሎን “የሚትረፈረፍ መቅሰፍት” በምድሪቱ ባለፈ ጊዜ የይሁዳ ፖለቲካዊ መሸሸጊያ ሐሰት መሆኑን ያጋልጣል። “ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል” ይላል ይሖዋ። “የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ። ባለፈም ጊዜ . . . ወሬውንም ማስተዋል ድንጋጤ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 28:18, 19) ይሁንና ይሖዋን እናገለግላለን እያሉ ከብሔራት ጋር በፈጠሩት ጥምረት በታመኑት ሰዎች ላይ የደረሰው ነገር ትልቅ ትምህርት ይሆናል።
15. ኢሳይያስ የይሁዳ መሸሸጊያ ደካማ እንደሆነ በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?
15 እነዚህ የይሁዳ መሪዎች አሁን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተመልከት:- “ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፤ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጐናጸፊያ ጠባብ ነው።” (ኢሳይያስ 28:20) እፎይ ብለው ጎናቸውን ለማሳረፍ የፈለጉ ያህል ነበር። ይሁን እንጂ አልተሳካላቸውም። እግራቸው ተርፎ ለብርድ ይጋለጥና እግራቸውን ወደ ላይ ሰብስበው እንዲሞቃቸው ተጠቅልለው ለመተኛት ሲፈልጉ ደግሞ መጎናጸፊያው ጠባብ ስለሆነ አይበቃቸውም። በኢሳይያስ ዘመን የነበረው የማይመች ሁኔታ ይህን የሚመስል ነበር። ዛሬም ቢሆን በሕዝበ ክርስትና የሐሰት መሸሸጊያ የሚታመኑ ሁሉ ሁኔታቸው ከዚህ የተለየ አይደለም። አንዳንዶቹ የሕዝበ ክርስትና መሪዎች በፖለቲካ በመጠላለፋቸው ምክንያት የዘር ማጽዳት ዘመቻንና የጅምላ ጭፍጨፋን በመሳሰሉት የጭካኔ ድርጊቶች ተካፋይ ሆነው መገኘታቸው እንዴት አስጸያፊ ነገር ነው!
ይሖዋ የሚያከናውነው ‘እንግዳ ሥራ’
16. የይሖዋ ‘እንግዳ ሥራ’ ምንድን ነው? ይህ ሥራ እንግዳ የሚሆነው ለምንድን ነው?
16 የመጨረሻው ውጤት የይሁዳ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተስፋ ከሚያደርጉት ፈጽሞ የተለየ ይሆናል። ይሖዋ ለይሁዳ መንፈሳዊ ሰካራሞች እንግዳ የሆነ ነገር ያከናውናል። “እግዚአብሔርም ሥራውን ማለት እንግዳ ሥራውን ይሠራ ዘንድ፣ አድራጎቱንም ማለት ያልታወቀውን አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ በፐራሲም ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፣ በገባዖንም ሸለቆ እንደ ነበረ ይቈጣል።” (ኢሳይያስ 28:21) ይሖዋ በንጉሥ ዳዊት ዘመን ለሕዝቡ በፐራሲም ተራራና በገባዖን ሸለቆ ፍልስጥኤማውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። (1 ዜና መዋዕል 14:10-16) በኢያሱ ዘመን እስራኤላውያን በአሞራውያን ላይ የተሟላ ድል እንዲቀዳጁ ሲል ይሖዋ በገባዖን ፀሐይ እንኳ እንዳትጠልቅ አድርጎላቸዋል። (ኢያሱ 10:8-14) ይህ ፍጹም እንግዳ ነገር ነበር! አሁንም ይሖዋ ይዋጋል። ይሁን እንጂ አሁን የሚዋጋው የእርሱ ሕዝብ ነን ከሚሉት ሰዎች ጋር ነው። ከዚህ ይበልጥ እንግዳ ወይም ለማመን የሚያስቸግር ነገር ይኖራልን? ኢየሩሳሌም የይሖዋ አምልኮ ማዕከልና በይሖዋ የተቀባው ንጉሥ መቀመጫ ከመሆኗ አንጻር ሲታይ ከዚህ የበለጠ እንግዳ ነገር አለ ለማለት ያስቸግራል። እስከዚህ ጊዜ ድረስ መቀመጫውን በኢየሩሳሌም ያደረገው የዳዊት ንጉሣዊ ዙፋን ተገልብጦ አያውቅም። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ ‘እንግዳ የሆነውን ሥራውን’ ማከናወኑ አይቀርም።—ከዕንባቆም 1:5-7 ጋር አወዳድር።
17. የሰዎች ፌዝ በኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ምንድን ነው?
17 በመሆኑም ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ።” (ኢሳይያስ 28:22) መሪዎቹ ቢያፌዙም የኢሳይያስ መልእክት እውነት ነው። መልእክቱን የተቀበለው መሪዎቹ በቃል ኪዳን ተዛምደነዋል ብለው ከሚናገሩለት ከይሖዋ ነው። ዛሬም የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎች ስለ ይሖዋ ‘እንግዳ ሥራ’ ሲሰሙ ያፌዛሉ። አልፎ ተርፎም በምሥክሮቹ ላይ ይደነፋሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያውጁት መልእክት እውነት ነው። እነዚህ መሪዎች ራሳቸው ቆመንለታል በሚሉት መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ነው።
18. ይሖዋ ተግሳጽን በሚዛናዊነት እንደሚሰጥ ኢሳይያስ በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?
18 ይሖዋ እነዚህን መሪዎች የማይከተሉትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በማስተካከል መልሰው ሞገሱን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። (ኢሳይያስ 28:23-29ን አንብብ።) አንድ ገበሬ እንደ ከሙን ያሉትን ጥንቃቄ የሚጠይቁ አዝርዕት በኃይል እንደማይወቃ ሁሉ ይሖዋም የሚሰጠው ተግሳጽ እንደ ግለሰቡና እንደ ሁኔታው ይለያያል። ፈላጭ ቆራጭ ወይም ጨቋኝ አይደለም። ይልቁንም እርምጃ የሚወስደው በደለኛው ከጥፋቱ እንዲታረም ለማድረግ ነው። አዎን፣ ይሖዋ የሚያቀርበውን ጥሪ የሚቀበሉ ግለሰቦች ካሉ ተስፋ አላቸው። ዛሬም እንዲሁ የሕዝበ ክርስትና ዕጣ ፈንታ በጥቅሉ ምን እንደሆነ የሚያጠያይቅ ባይሆንም ራሱን ለይሖዋ መንግሥት የሚያስገዛ ግለሰብ ከመጪው ከባድ ፍርድ ሊያመልጥ ይችላል።
ለኢየሩሳሌም ወዮ!
19. ኢየሩሳሌም “የአምላክ መሠዊያ” የምትሆነው በምን መንገድ ነው? ይህስ የሚከናወነው መቼና እንዴት ነው?
19 ይሁንና ይሖዋ ቀጥሎ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው? “ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ ለአርኤል ወዮላት! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ፣ በዓላትም ይመለሱ። አርኤልንም አስጨንቃለሁ፣ ልቅሶና ዋይታም ይሆንባታል፤ እንደ አርኤልም [“የአምላክ መሠዊያም፣” NW] ትሆንልኛለች።” (ኢሳይያስ 29:1, 2) “አርኤል” ማለት “የአምላክ መሠዊያ” ማለት ሊሆን ይችላል። እዚህ ላይ ደግሞ የሚያመለክተው ኢየሩሳሌምን መሆኑን ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያና ቤተ መቅደሱ የሚገኙት በኢየሩሳሌም ነበር። አይሁዳውያኑ በዚህ ቦታ በዓላት ማክበራቸውንና መሥዋዕት ማቅረባቸውን እንደ ልማድ ቀጥለውበት የነበረ ቢሆንም ይሖዋ በአምልኮአቸው አልተደሰተም። (ሆሴዕ 6:6) ከዚህ ይልቅ ከተማዋ ራሷ “መሠዊያ” እንደምትሆን ተናግሯል። ልክ እንደ መሠዊያ ደም ሊፈስስባትና እሳት ሊነድድባት ነው። ይሖዋ ይህ እንዴት እንደሚሆን ሳይቀር ይናገራል:- “በዙሪያሽም እሰፍራለሁ፣ በቅጥርም ከብቤ አስጨንቅሻለሁ፣ አምባም በላይሽ አቆማለሁ። ትዋረጂማለሽ፣ በመሬትም ላይ ሆነሽ ትናገሪያለሽ፣ ቃልሽም ዝቅ ብሎ ከአፈር ይወጣል፤ ድምፅሽም ከመሬት እንደሚወጣ እንደ መናፍስት ጠሪ ድምፅ ይሆናል፣ ቃልሽም ከአፈር ወጥቶ ይጮኻል።” (ኢሳይያስ 29:3, 4) ይህ ትንቢት በ607 ከዘአበ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ፍጻሜውን ያገኘው ባቢሎናውያን ከተማዋን ባጠፉና ቤተ መቅደስዋንም በእሳት ባቃጠሉ ጊዜ ነው። ኢየሩሳሌም ከተገነባችበት አፈር ጋር ተቀላቅላለች።
20. የአምላክ ጠላቶች የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
20 ይህ ወሳኝ ቀን ከመምጣቱ በፊት በነበረው ጊዜ በይሁዳ የይሖዋን ሕግ የሚታዘዙ ነገሥታት በተለያዩ ጊዜያት ተነሥተዋል። በዚህ ጊዜ ሁኔታው ምን ይመስል ነበር? ይሖዋ ለሕዝቡ ተዋግቶላቸዋል። ጠላቶቻቸው ምድሪቷን ቢሸፍኑ እንኳ “እንደ ደቀቀ ትቢያ” እና “ገለባ” ይሆናሉ። ጊዜው ሲደርስ ይሖዋ “በነጐድጓድ፣ በምድርም መናወጥ፣ በታላቅም ድምፅ፣ በዐውሎ ነፋስም፣ በወጨፎም፣ በምትበላም በእሳት ነበልባል” ይበትናቸዋል።—ኢሳይያስ 29:5, 6
21. በኢሳይያስ 29:7, 8 ላይ የሚገኘውን ምሳሌ አብራራ።
21 የጠላት ሠራዊት የኢየሩሳሌምን ንብረት ለማጋዝና በጦር ብዝበዛ ለመጥገብ ይጓጓ ይሆናል። ይሁንና አንድ የሚያባንን ነገር ይጠብቃቸዋል! በጣም ተርቦ እያለ በሕልሙ ድግስ ሲበላ እንደሚታየውና ሲነቃ ግን ይበልጥ ተርቦ እንደሚነቃ ሰው የይሁዳ ጠላቶችም እንዲሁ የጓጉለትን ንጥቂያ ሳያገኙ ይቀራሉ። (ኢሳይያስ 29:7, 8ን አንብብ።) በታመነው ንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን ኢየሩሳሌም ላይ የስጋት ደመና እንዲያንዣብብ አድርጎ የነበረው በሰናክሬም የሚመራው የአሦር ሠራዊት ምን እንደገጠመው ልብ በል። (ኢሳይያስ ምዕራፍ 36 እና 37) አንድም ሰው እጁን ማንሳት ሳያስፈልገው አስፈሪ የነበረው የአሦራውያን የጦር ሠራዊት በአንድ ሌሊት 185,000 ኃያላን ተዋጊዎቹን አጥቶ ለመመለስ ተገድዷል! በቅርቡም የማጎጉ ጎግ የጦር ሠራዊት የይሖዋን ሕዝቦች ድል የማድረግ ሐሳቡ ሕልም ብቻ ሆኖ ይቀራል።—ሕዝቅኤል 38:10-12፤ 39:6, 7
22. መንፈሳዊ ስካር ይሁዳን የጎዳት እንዴት ነው?
22 ኢሳይያስ ይህን የትንቢቱን ክፍል በሚናገርበት ወቅት የነበሩት የይሁዳ መሪዎች የሕዝቅያስን የመሰለ እምነት አልነበራቸውም። አምላካዊ አክብሮት ከሌላቸው ብሔራት ጋር በፈጠሩት ኅብረት ምክንያት መንፈሳዊ ስካር ላይ ወድቀው ነበር። “ተደነቁ ደንግጡም፤ ተጨፈኑም ዕውሮችም ሁኑ፤ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ሰከሩ፤ በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገደገዱ።” (ኢሳይያስ 29:9) እነዚህ መሪዎች መንፈሳዊ ስካር ላይ በመሆናቸው ለይሖዋ እውነተኛ ነቢይ የተገለጠለት ራእይ ያዘለውን ትክክለኛ ትርጉም ማስተዋል አይችሉም። ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል ዓይኖቻችሁን ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል። ራእዩም ሁሉ እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ:- ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ:- ታትሞአልና አልችልም ይላቸዋል፤ ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ:- ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ:- ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል።”—ኢሳይያስ 29:10-12
23. ይሖዋ ይሁዳን ወደ ፍርድ የሚያመጣት ለምንድን ነው? ይህንንስ የሚያደርገው እንዴት ነው?
23 የይሁዳ ሃይማኖታዊ መሪዎች በመንፈሳዊ ልባሞች እንደሆኑ ይናገሩ እንጂ ይሖዋን ትተዋል። ይልቁንም ትክክለኛና ስህተት ስለሆነው ነገር የራሳቸውን የተዛባ አመለካከት ያስተምራሉ። እምነት የለሽ ተግባራቸውንና የብልግና ድርጊቶቻቸውን እንዲሁም ሕዝቡ የአምላክን ሞገስ እንዲያጣ በተሳሳተ ጎዳና መምራታቸውን ደህና ነገር አስመስለው ያቀርባሉ። ይሖዋ አንድ “ድንቅ ነገር” ማለትም ‘እንግዳ ሥራ’ በማከናወን ላሳዩት ግብዝነት የእጃቸውን ይሰጣቸዋል። እንዲህ ይላል:- “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፣ በከንፈሮቹም ያከብረኛልና፣ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፣ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና ስለዚህ፣ እነሆ፣ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፣ ድንቅ ነገርን ተአምራትንም፣ እንደ ገና አደርጋለሁ፤ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፣ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች።” (ኢሳይያስ 29:13, 14) ይሖዋ የዓለም ኃይል በሆነችው በባቢሎን አማካኝነት ክህደት የተሞላው የይሁዳ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተጠራርጎ የሚጠፋበትን መንገድ ሲያመቻች ይሁዳ ያፈለቀችው ጥበብና ማስተዋል ሁሉ ይጠፋል። በራሳቸው ዓይን ጠቢብ የሆኑት የአይሁድ መሪዎች ብሔሩ እንዲባዝን ባደረጉበት የመጀመሪያው መቶ ዘመንም ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል። በዘመናችንም በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚደርሰው ነገር ከዚህ የተለየ አይሆንም።—ማቴዎስ 15:8, 9፤ ሮሜ 11:8
24. የይሁዳ ሰዎች አምላካዊ ፍርሃት የጎደላቸው መሆናቸውን ያጋለጡት እንዴት ነው?
24 ይሁን እንጂ ጉረኛ የሆኑት የይሁዳ መሪዎች እውነተኛውን አምልኮ ቢበክሉም ከቅጣት የሚያመልጡበት መንገድ የማይጠፋቸው ብልሆች እንደሆኑ አድርገው አስበው ሊሆን ይችላል። በእርግጥ ናቸው? ኢሳይያስ ጭንብላቸውን በመግፈፍ እውነተኛ ፈሪሃ አምላክ ኢሳይያስ 29:15, 16፤ ከመዝሙር 111:10 ጋር አወዳድር።) የቱንም ያህል ተሰውረው እንዳሉ ቢሰማቸው በአምላክ ዓይኖች ፊት ‘የተራቆቱና የተገለጡ’ ናቸው።—ዕብራውያን 4:13
የሌላቸውና ከዚህም የተነሣ እውነተኛ ጥበብ የጎደላቸው ሰዎች መሆናቸውን ያጋልጣል:- “ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ፣ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው:- ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል? ለሚሉ ወዮላቸው! ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን:- አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን:- አታስተውልም ይለዋለን?” (“ደንቆሮች . . . ይሰማሉ”
25. “ደንቆሮዎች” የሚሰሙት በምን ሁኔታ ነው?
25 ይሁን እንጂ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰዎች ይድናሉ። (ኢሳይያስ 29:17-24ን አንብብ፤ ከሉቃስ 7:22 ጋር አወዳድር።) “ደንቆሮች የመጽሐፍን ቃል” ማለትም በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን መልእክት ይሰማሉ። ይህ አካላዊ ፈውስን የሚያመለክት አይደለም። መንፈሳዊ ፈውስ ነው። ኢሳይያስ ስለ መሲሐዊው መንግሥት መመሥረትና በመሲሐዊው አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ተመልሶ ስለሚቋቋመው እውነተኛ አምልኮ በድጋሚ ይገልጻል። ይህ ነገር በዘመናችን የተፈጸመ ሲሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በይሖዋ ለመስተካከል ፈቃደኛ በመሆን እርሱን ማወደስን እየተማሩ ነው። እንዴት የሚያስደስት ፍጻሜ ነው! በመጨረሻ ሁሉም ሰው እስትንፋስ ያለው ሁሉ ይሖዋን የሚያወድስበትና ቅዱስ ስሙን የሚቀድስበት ቀን ይመጣል።—መዝሙር 150:6
26. ዛሬ “ደንቆሮዎች” ምን መንፈሳዊ ማሳሰቢያ ይሰማሉ?
26 ዛሬ የአምላክን ቃል የሚሰሙ “ደንቆሮዎች” የሚማሩት ምንድን ነው? ሁሉም ክርስቲያኖች በተለይም ደግሞ ጉባኤው እንደ ምሳሌ አድርጎ የሚመለከታቸው ሰዎች ‘ከወይን ጠጅ የተነሣ እንዳይስቱ’ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይማራሉ። (ኢሳይያስ 28:7) ከዚህም በላይ ስለ ሁሉም ነገር መንፈሳዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳንን የአምላክን ማሳሰቢያ መስማት ልንሰለች አይገባም። ክርስቲያኖች ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት በአግባቡ እንደሚገዙና አንዳንድ አገልግሎቶችንም ከእነርሱ እንደሚያገኙ የታወቀ ቢሆንም መዳን የሚገኘው ከይሖዋ አምላክ እንጂ ከዓለም አይደለም። በተጨማሪም በከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ላይ እንደተወሰደው የፍርድ እርምጃ አምላክ በዚህ ትውልድ ላይ የሚወስደውም እርምጃ አይቀሬ መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። ተቃውሞ ቢኖርም በይሖዋ እርዳታ ልክ እንደ ኢሳይያስ የማስጠንቀቂያ መልእክቱን ማወጃችንን መቀጠል እንችላለን።—ኢሳይያስ 28:14, 22፤ ማቴዎስ 24:34፤ ሮሜ 13:1-4
27. ክርስቲያኖች ከኢሳይያስ ትንቢት ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
27 ሽማግሌዎችና ወላጆች ሁልጊዜ ስህተት የፈጸመውን ሰው ለመቅጣት ብቻ ሳይሆን መልሶ የአምላክን ሞገስ እንዲያገኝ ለመርዳት በመጣር የይሖዋን የተግሳጽ አሰጣጥ ሊኮርጁ ይገባል። (ኢሳይያስ 28:26-29፤ ከኤርምያስ 30:11 ጋር አወዳድር።) ወጣቶችን ጨምሮ ሁላችንም ሰዎችን ለማስደሰት ስንል ብቻ በክርስትና ስም በዘልማድ መመላለስ እንደሌለብንና ይሖዋን ከልብ ማገልገል ምን ያህል አንገብጋቢ እንደሆነ ማሳሰቢያ አግኝተናል። (ኢሳይያስ 29:13) እምነት የለሽ ከሆኑት የይሁዳ ነዋሪዎች በተለየ መልኩ ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት እንዳለንና በጥልቅ እንደምናከብረው ማሳየት ይገባናል። (ኢሳይያስ 29:16) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ እንዲያርመን እንዲሁም እንዲያስተምረን እንደምንፈልግ ማሳየት ይኖርብናል።—ኢሳይያስ 29:24
28. የይሖዋ አገልጋዮች የእርሱን የማዳን ሥራ የሚመለከቱት እንዴት ነው?
28 በይሖዋና እሱ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እምነትና ትምክህት ማሳደር ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ከመዝሙር 146:3 ጋር አወዳድር።) ለአብዛኛዎቹ ሰዎች እኛ የምናሰማው የማስጠንቀቂያ መልእክት የልጅ ሥራ መስሎ ይታያቸዋል። አምላክን አገለግላለሁ በምትለው ድርጅት ማለትም በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚመጣው ጥፋት እንግዳና ለማመን የሚያዳግት ሐሳብ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘እንግዳ ሥራውን’ ያከናውናል። ይህ ምንም አያጠራጥርም። በመሆኑም በዚህ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት የአምላክ አገልጋዮች በመንግሥቱና በተሾመው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ይታመናሉ። ይሖዋ ከሚያከናውነው ‘እንግዳ ሥራ’ ጋር የሚወስደው የማዳን እርምጃ ታዛዥ ለሆነው የሰው ዘር በሙሉ ዘላለማዊ በረከት ያስገኛል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.8 በጥንቱ ዕብራይስጥ ውስጥ ኢሳይያስ 28:10 የተቀመጠው ለልጆች እንደሚነበነብ ቤት የሚመታ ግጥም ሆኖ ነበር። የኢሳይያስም መልእክት ለሃይማኖት መሪዎቹ ተደጋጋሚና የልጅ ሥራ ሆኖ ታይቷቸዋል።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 289 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕዝበ ክርስትና የታመነችው በአምላክ ሳይሆን በሰብዓዊ ገዥዎች ነው
[በገጽ 290 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባቢሎን ኢየሩሳሌምን እንድታጠፋ በፈቀደ ጊዜ ይሖዋ ‘እንግዳ የሆነ ሥራውን’ አከናውኗል
[በገጽ 298 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ደንቆሮ የነበሩ ሰዎች የአምላክን ቃል ‘የሚሰሙበት’ ጊዜ ይመጣል