በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰላም መስፍን እንደሚነሳ የተሰጠ ተስፋ

የሰላም መስፍን እንደሚነሳ የተሰጠ ተስፋ

ምዕራፍ አሥር

የሰላም መስፍን እንደሚነሳ የተሰጠ ተስፋ

ኢሳይያስ 8:​19–9:​7

1. ከቃየን ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል?

ከዛሬ ስድስት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት የመጀመሪያው ሰብዓዊ ሕፃን ተወለደ። ስሙ ቃየን ሲሆን ውልደቱ በጣም ልዩ ነበር። ወላጆቹም ሆኑ መላእክት አልፎ ተርፎም ፈጣሪ ራሱም እንኳ ከዚያ ቀደም ሰብዓዊ ሕፃን ልጅ አይተው አያውቁም። ይህ አራስ ልጅ በኩነኔ ሥር ለወደቀው የሰው ዘር ተስፋ ሰጪ ሊሆን ይችል ነበር። ይሁንና ካደገ በኋላ ነፍሰ ገዳይ መሆኑ እንዴት የሚያሳዝን ነው! (1 ዮሐንስ 3:​12) ከዚያ ጊዜ ወዲህ የሰው ዘር ቁጥር ስፍር የሌላቸው የነፍስ ግድያዎች ሲፈጸሙ ተመልክቷል። የሰው ልጆች ወደ ክፋት በማዘንበላቸው እርስ በርሳቸውም ሆነ ከአምላክ ጋር ሰላም አጥተዋል።​—⁠ዘፍጥረት 6:​5፤ ኢሳይያስ 48:​22

2, 3. ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ማግኘት የምንችልበትን በር ከፍቶልናል? እንዲህ ያሉትን በረከቶች ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

2 ቃየን ከተወለደ ከአራት ሺህ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሌላ ሕፃን ተወለደ። ስሙ ኢየሱስ ሲሆን የእርሱም አወላለድ በጣም ልዩ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት ከአንዲት ድንግል ሴት የተወለደ ሲሆን በዚህ መንገድ ለመወለድ በታሪክ ብቸኛው ሰው ነው። እርሱ ሲወለድ ብዙ ቁጥር ያላቸው መላእክት “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” እያሉ በደስታ ለአምላክ የውዳሴ መዝሙር አሰምተዋል። (ሉቃስ 2:​13, 14) ኢየሱስ ግን እንደ ቃየን ነፍሰ ገዳይ አልሆነም። እንዲያውም ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላም የሚፈጥሩበትንና ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ ከፍቷል።​—⁠ዮሐንስ 3:​16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​55

3 ኢየሱስ “የሰላም መስፍን” ተብሎ እንደሚጠራ ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 9:​6 NW ) ለሰው ዘር ሲል ነፍሱን አሳልፎ በመስጠት የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኙ ያደርጋል። (ኢሳይያስ 53:​11) ዛሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማመን ከአምላክ ጋር ሰላም መፍጠርና የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት ይቻላል። ይሁን እንጂ እነዚህ በረከቶች እንዲሁ አይመጡም። (ቆላስይስ 1:​21-23) እነዚህን በረከቶች ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ይሖዋ አምላክን መታዘዝን መማር ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:​11፤ ከ⁠ዕብራውያን 5:​8, 9 ጋር አወዳድር።) በኢሳይያስ ዘመን እስራኤልና ይሁዳ ያደረጉት ነገር ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ ነበር።

ወደ አጋንንት ዘወር ማለት

4, 5. በኢሳይያስ ዘመን የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? አንዳንዶች ፊታቸውን የመለሱት ወዴት ነው?

4 በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ባለመታዘዛቸው ምክንያት አሳዛኝ ስነ ምግባራዊ ውድቀት ደርሶባቸውና ድቅድቅ ባለ መንፈሳዊ ጨለማ ተውጠው ነበር። የአምላክ ቤተ መቅደስ የሚገኝበት ደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት እንኳ ሳይቀር ሰላም አልነበረውም። የይሁዳ ሕዝብ ታማኝ ሳይሆን በመቅረቱ ምክንያት በአሦራውያን የመወረር አደጋ አንዣብቦበት የነበረ ሲሆን ከፊቱም አስቸጋሪ ጊዜያት ይጠብቁት ነበር። እርዳታ ለማግኘት ወደ ማን ዞር ይሉ ይሆን? የሚያሳዝነው ብዙዎች እርዳታ ማግኘት የፈለጉት ከይሖዋ ሳይሆን ከሰይጣን ነው። ሰይጣንን በስሙ ጠርተው አልለመኑም። ነገር ግን የጥንቱ ንጉሥ ሳውል እንዳደረገው ከሙታን ጋር ተነጋግረው ለችግራቸው መፍትሔ ለመሻት ሲሉ በመናፍስታዊ ድርጊቶች እጃቸውን አስገብተዋል።​—⁠1 ሳሙኤል 28:​1-20

5 ይባስ ብሎም አንዳንዶች ይህንን ልማድ ያበረታታሉ። ኢሳይያስ እንዲህ ያለውን ክህደት አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ፣ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን?” (ኢሳይያስ 8:​19) መናፍስት ጠሪዎች ‘ድምፃቸውን እያቃጨሉና ዝግ አድርገው እየተናገሩ’ ሰዎችን ሊያታልሉ ይችላሉ። ከሙታን መናፍስት የመጣ ነው የሚባለውን እንዲህ ያለውን ድምፅ ሕያው የሆነው ሙታን ሳቢ ራሱ አስመስሎ ሊያሰማ ይችላል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ አጋንንት ራሳቸው በቀጥታ ጣልቃ በመግባት የሞተውን ሰው መስለው ይቀርቡ ይሆናል። ሳውል በአይንዶር የነበረችው መናፍስት ጠሪ ዘንድ በሄደ ጊዜ የገጠመው ሁኔታ ይህን የሚመስል ነበር።​—⁠1 ሳሙኤል 28:​8-19

6. በተለይ ወደ መናፍስታዊ ሥራዎች ዘወር ያሉት እስራኤላውያን የሚነቀፉ የሆኑት ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ መናፍስታዊ ሥራዎችን ከልክሎ የነበረ ቢሆንም በይሁዳ ውስጥ ይህ ሁሉ ነገር ይከናወን ነበር። በሙሴ ሕግ ሥር ይህ በሞት የሚያስቀጣ ጥፋት ነበር። (ዘሌዋውያን 19:​31፤ 20:​6, 27፤ ዘዳግም 18:​9-12) ለይሖዋ የተለየ ርስት የነበሩ ሰዎች እንዲህ ያለ ከባድ ኃጢአት የሚሠሩት ለምንድን ነው? ለይሖዋ ሕግና ምክር ጀርባቸውን ስለሰጡና ‘በኃጢአት መታለል እልከኛ ስለሆኑ’ ነበር። (ዕብራውያን 3:​13) ‘ልባቸው ሰብቶና ደንድኖ’ ከአምላክ ርቀው ነበር።​—⁠መዝሙር 119:​701879 ትርጉም  *

7. ዛሬ ብዙዎች በኢሳይያስ ዘመን የነበሩትን እስራኤላውያን የሚመስሉት እንዴት ነው? ንስሐ ካልገቡስ የእነዚህ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

7 ‘የአሦራውያን ጥቃት እንዲህ አፍጥጦ እየመጣብን የይሖዋ ሕግ ለምናችን ነው?’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። እነርሱ የፈለጉት የገጠማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት ፈጣንና ቀላል የሆነ መፍትሔ ማግኘት ስለነበር ይሖዋ ፈቃዱን ይፈጽም ዘንድ እርሱን ለመጠበቅ አልፈለጉም። በዛሬው ጊዜም ቢሆን ብዙዎች የይሖዋን ሕግ ችላ ብለው ወደ መናፍስት ጠሪዎች ይሄዳሉ፣ ኮከብ ቆጣሪዎችን ያማክራሉ እንዲሁም በሌሎች የጥንቆላ ዓይነቶች ተጠቅመው ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ሕያዋን ሰዎች ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለማግኘት ሙታንን መጠየቃቸው ያኔ ሞኝነት እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ሞኝነት ነው። ንስሐ ሳይገባ በዚህ ሥራው የሚቀጥል ማንኛውም ሰው ዕጣ ፈንታው ‘ከነፍሰ ገዳዮች፣ ከሴሰኞች፣ ጣዖትንም ከሚያመልኩና ከሐሰተኛዎች’ ጋር ይሆናል። ወደፊት ሕይወት የማግኘት ሌላ ተስፋም አይኖራቸውም።​—⁠ራእይ 21:​8

የአምላክ ‘ሕግና ምስክር’

8. ዛሬ ልንመራበት የሚገባው ‘ሕግ’ እና ‘ምስክር’ ምንድን ነው?

8 ሌሎቹን ትእዛዛት ጨምሮ መናፍስታዊ ሥራዎችን የሚከለክለው የይሖዋ ሕግ ለይሁዳ ሰዎች የተሰወረ አልነበረም። በጽሑፍ የሰፈረ ነገር ነበር። ዛሬም የተሟላው ቃሉ በጽሑፍ ይገኛል። ይህም መለኮታዊ ሕጎችንና መመሪያዎችን ብቻ ሳይሆን አምላክ ከሕዝቡ ጋር ስላደረገው ግንኙነት የሚገልጹ ዘገባዎችን የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይሖዋ ከሰዎች ጋር ስላደረገው ግንኙነት የሚገልጸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ይህ ዘገባ እንደ ምሥክር ወይም ማረጋገጫ ሆኖ ስለ ይሖዋ ማንነትና ባሕርያት ያስተምረናል። እስራኤላውያን መመሪያ ለማግኘት ሙታንን ከማማከር ይልቅ መሄድ የነበረባቸው ወደ ማን ነው? ኢሳይያስ “ወደ ሕግና ወደ ምስክር” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ኢሳይያስ 8:​20ሀ) አዎን፣ እውነተኛ የእውቀት ብርሃን ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ መሄድ ያለባቸው በጽሑፍ ወደ ሰፈረው የአምላክ ቃል ነው።

9. ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች መጽሐፍ ቅዱስን የሚጠቅሱ መሆናቸው የሚፈይደው ነገር አለ?

9 ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ የነበራቸው አንዳንድ እስራኤላውያን በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል አክብሮት አለን ብለው ይናገሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ከእውነታው የራቀ የግብዝነት አነጋገር ነው። ኢሳይያስ “እንዲህም ያለውን ቃል ደጋግመው ይናገሩታል ንጋትም አይበራላቸውም” ብሏል። (ኢሳይያስ 8:​20 NW ) ኢሳይያስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ስለ የትኛው ቃል ነው? ‘ወደ ሕጉና ወደ ምስክሩ’ የሚለውን ቃል መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ዛሬ ያሉት ከሃዲዎች እንደሚያደርጉት አንዳንድ ከሃዲ እስራኤላውያን የአምላክን ቃል እየጠቀሱ ይናገሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ እንዲሁ ቃል ብቻ ነው። የይሖዋን ፈቃድ ማድረግና ንጹሕ ካልሆኑ ልማዶች መራቅ ካልታከለበት በስተቀር ጥቅሶችን መጥቀሱ ብቻውን ወደ ‘ንጋት ብርሃን’ ወይም ከይሖዋ ወደሚገኘው የእውቀት ብርሃን አይመራም። *

‘የእንጀራ ያይደለ ራብ’

10. የይሁዳ ሕዝብ ይሖዋን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረጉ መከራ የደረሰበት እንዴት ነው?

10 ይሖዋን አለመታዘዝ አእምሮ እንዲጨልም ያደርጋል። (ኤፌሶን 4:​17, 18) በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ የይሁዳ ሕዝብ እውር ማለትም ማስተዋል የሌለው ሆኖ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 2:​14) ኢሳይያስ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “እነርሱም ተጨንቀውና ተርበው ያልፋሉ” ብሏል። (ኢሳይያስ 8:​21ሀ) በተለይ በአካዝ ዘመን ሕዝቡ ታማኝነቱን በማጉደሉ የይሁዳ መንግሥት ሕልውናውን ጠብቆ መቀጠሉ ስጋት ላይ ወድቆአል። በጠላቶቻቸው ተከብበው ነበር። የአሦራውያን ሠራዊት በይሁዳ አውራጃ ያሉ ከተሞችን አንድ አንድ እያለ ተቆጣጥሯል። ጠላት ፍሬያማ የሆነውን ምድር በማውደሙ የምግብ እጥረት ተከስቷል። ብዙዎቹ “ተጨንቀውና ተርበው” ነበር። ይሁን እንጂ ምድሪቱ በሌላ ዓይነት ረሃብም ተመትታ ነበር። ከጥቂት አሥርተ ዓመታት ቀደም ብሎ አሞጽ እንደሚከተለው ሲል ተንብዮ ነበር:- “እነሆ፣ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።” (አሞጽ 8:​11) በዚህ ጊዜ ይሁዳ በእንዲህ ዓይነት መንፈሳዊ ራብ እየተሰቃየች ነበር!

11. ይሁዳ ከተሰጣት ተግሳጽ ትምህርት ታገኝ ይሆን?

11 ይሁዳ ትምህርት አግኝታ ወደ ይሖዋ ትመለስ ይሆን? ሕዝቧስ ከመናፍስታዊ ሥራዎችና ከጣዖት አምልኮ በመራቅ ‘ወደ ሕጉና ወደ ምስክሩ’ ይመለስ ይሆን? ይሖዋ ምን ምላሽ እንደሚሰጡ አስቀድሞ አውቋል። “በተራቡም ጊዜ ተቈጥተው ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይረግማሉ፣ ወደ ላይም ይመለከታሉ።” (ኢሳይያስ 8:​21ለ) አዎን፣ ብዙዎች ወደዚህ የመሩን እነርሱ ናቸው በማለት ሰብዓዊ ንጉሦቻቸውን ተወቃሽ ያደርጋሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለደረሰባቸው መከራ በሞኝነት ተነስተው ጭራሽ ይሖዋን ተወቃሽ ያደርጋሉ! (ከ⁠ኤርምያስ 44:​15-18 ጋር አወዳድር።) ዛሬም ብዙዎች በሰዎች ክፋት ምክንያት ለደረሰባቸው አሳዛኝ ሁኔታ አምላክን ተጠያቂ በማድረግ ተመሳሳይ ምላሽ ይሰጣሉ።

12. (ሀ) ይሁዳ ከአምላክ መራቋ ወደ ምን መርቷታል? (ለ) ምን በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች ይነሳሉ?

12 አምላክን መርገማቸው ለይሁዳ ነዋሪዎች ሰላም የሚያመጣ ነበርን? በፍጹም። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ወደ ምድርም ይመለከታሉ፣ እነሆም፣ መከራና ጨለማ የሚያስጨንቅም ጭጋግ አለ፤ ወደ ድቅድቅም ጨለማ ይሰደዳሉ።” (ኢሳይያስ 8:​22) አምላክን ለመውቀስ ዓይኖቻቸውን ወደ ላይ ካነሱ በኋላ መልሰው ደግሞ ተስፋ ቢስ ወደ ሆነው ሁኔታቸው ወደ ምድር ይመለከታሉ። ከአምላክ መራቃቸው ትርፉ መከራ ሆኗል። (ምሳሌ 19:​3) ታዲያ አምላክ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የገባው ተስፋስ ምን ሊሆን ነው? (ዘፍጥረት 22:​15-18፤ 28:​14, 15) ይሖዋ የገባውን ቃል ሳይፈጽም ይቀር ይሆን? ለይሁዳና ለዳዊት ቃል የተገባላቸውን ንጉሣዊ መስመር አሦራውያን ወይም ሌላ ወታደራዊ ኃይል ያከሽፈው ይሆን? (ዘፍጥረት 49:​8-10፤ 2 ሳሙኤል 7:​11-16) እስራኤላውያን እስከ መጨረሻው ድረስ ለጨለማ ኩነኔ ተዳርገው ይቀሩ ይሆን?

‘ያቃለሏት’ ምድር

13. “የአሕዛብ ገሊላ” የተባለው የትኛው አካባቢ ነው? ሌሎች ‘ያቃለሉትስ’ እንዴት ነው?

13 ቀጥሎ ኢሳይያስ በአብርሃም ዘሮች ላይ ከደረሱት ሁሉ እጅግ የከፋ ስለሆነው እንደ መቅሰፍት ያለ ክንውን በተዘዋዋሪ መንገድ ይጠቅሳል:- “ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል።” (ኢሳይያስ 9:​1) ገሊላ በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ክልል ውስጥ የሚገኝ አካባቢ ነው። በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ “የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር” እንዲሁም “የባሕር መንገድ” የተባለውን ማለትም በገሊላ ባሕር አድርጎ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር የሚያቀናውን ጥንታዊ መንገድ የሚጨምር ሆኗል። በኢሳይያስ ዘመን አካባቢው “የአሕዛብ ገሊላ” በመባል ይታወቅ ነበር። በዚህ ስም ይጠራ የነበረው ብዙዎቹ የአካባቢው ከተማዎች እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች መኖሪያ በመሆናቸው ሳይሆን አይቀርም። * ይህችን ምድር ‘ያቃለሏት’ እንዴት ነው? አረማዊ የሆኑት አሦራውያን ምድሪቱን ድል አድርገው በመያዝ እስራኤላውያኑን በምርኮ ወሰዱ ከዚያም በመላው ግዛት የአብርሃም ዝርያ ያልሆኑ አረማዊ ሰዎች አምጥተው አሰፈሩበት። በዚህ መንገድ ራሱን የቻለ የነበረው የአሥሩ ነገድ ሰሜናዊ መንግሥት ከታሪክ ገጾች ላይ ተፋቀ!​—⁠2 ነገሥት 17:​5, 6, 18, 23, 24

14. የይሁዳ “ጨለማ” ከአሥሩ ነገድ ያነሰ የሆነው እንዴት ነው?

14 ይሁዳም ብትሆን ከአሦራውያን ተጽእኖ ነፃ አልነበረችም። በዛብሎንና በንፍታሌም የተወከለው የአሥሩ ነገድ መንግሥት የገጠመው ዓይነት የማይገፈፍ “ጨለማ” ውስጥ ትገባ ይሆን? የለም አትገባም። “በኋለኛው ዘመን” ይሖዋ ደቡባዊውን የይሁዳ መንግሥት አልፎ ተርፎም በሰሜናዊው መንግሥት ይተዳደር የነበረውን ምድር ይባርካል። እንዴት?

15, 16. (ሀ) ‘የዛብሎንና የንፍታሌም’ አካባቢዎች ሁኔታ የሚለወጥበት ‘የኋለኛው ዘመን’ የትኛው ነው? (ለ) ያቃለሉት ምድር ክብር የሚላበሰው እንዴት ነው?

15 ሐዋርያው ማቴዎስ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው ዘገባ ውስጥ ለዚህ ጥያቄ መልሱን ይሰጣል። ማቴዎስ በዚህ የኢየሱስ አገልግሎት መጀመሪያ አካባቢ ስለነበሩት ሁኔታዎች ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “[ኢየሱስ] ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። በነቢዩም በኢሳይያስ:- የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፣ የባሕር መንገድ፣ በዮርዳኖስ ማዶ፣ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፣ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።”​—⁠ማቴዎስ 4:​13-16

16 አዎን በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰው ‘የኋለኛ ዘመን’ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ያከናወነበት ዘመን ነው። ኢየሱስ አብዛኛውን ምድራዊ ሕይወቱን ያሳለፈው በገሊላ ነበር። “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ በመስበክ አገልግሎቱን የጀመረው በገሊላ አውራጃ ነበር። (ማቴዎስ 4:​17) ታዋቂ የሆነውን የተራራ ስብከቱን የሰጠው፣ ሐዋርያቱን የመረጠው፣ የመጀመሪያ ተአምሩን ያከናወነው እንዲሁም ከትንሣኤው በኋላ ከ500 ለሚበልጡ ተከታዮቹ የታየው በገሊላ ነበር። (ማቴዎስ 5:​1–7:​27፤ 28:​16-20፤ ማርቆስ 3:​13, 14፤ ዮሐንስ 2:​8-11፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​6) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ‘የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር በማክበር’ የኢሳይያስን ትንቢት ፈጽሟል። እርግጥ የኢየሱስ አገልግሎት ለገሊላ ሰዎች ብቻ የተወሰነ ነበር ማለት አይደለም። ኢየሱስ በምድሪቱ በሞላ ተዘዋውሮ ምሥራቹን በመስበክ ይሁዳን ጨምሮ መላው የእስራኤል ብሔር ‘እንዲከበር አድርጓል።’

“ታላቅ ብርሃን”

17. በገሊላ “ታላቅ ብርሃን” የወጣው እንዴት ነው?

17 ማቴዎስ በገሊላ እንደሚወጣ ስለተናገረለት ‘ታላቅ ብርሃንስ’ ምን ማለት ይቻላል? ይህም ቢሆን ከኢሳይያስ መጽሐፍ የተወሰደ ሐሳብ ነው። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በጨለማ የሄደ ሕዝብ [“ታላቅ፣” NW ] ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።” (ኢሳይያስ 9:​2) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የእውነት ብርሃን በአረማዊ የሐሰት ትምህርቶች ተቀብሮ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ደግሞ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ሽረው’ ሃይማኖታዊ ወጋቸውን የሙጥኝ በማለት ችግሩን አባብሰውት ነበር። (ማቴዎስ 15:​6) ከታች ያሉት ሰዎች ‘እውር የሆኑ መሪዎችን’ እየተከተሉ ለጭቆናና ግራ መጋባት ተዳርገው ነበር። (ማቴዎስ 23:​2-4, 16) መሲሑ ኢየሱስ በተገለጠ ጊዜ ከሥር የነበሩት የብዙዎቹ ሰዎች ዓይን አስገራሚ በሆነ መንገድ ተከፈተ። (ዮሐንስ 1:​9, 12) ኢየሱስ በምድር ላይ ያከናወነው ሥራና በመሥዋዕቱ አማካኝነት የተገኙት በረከቶች በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ እንደ “ታላቅ ብርሃን” ተደርገው መገለጻቸው ትክክል ነው።​—⁠ዮሐንስ 8:​12

18, 19. ለብርሃኑ ምላሽ የሰጡ ሰዎች በታላቅ ደስታ የሚፈነድቁበት ምን ምክንያት አላቸው?

18 ለዚህ ብርሃን ምላሽ የሰጡ ሰዎች የሚደሰቱበት ብዙ ምክንያት ነበራቸው። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ሕዝብን አብዝተሃል፣ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፣ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።” (ኢሳይያስ 9:​3 ) ኢየሱስና ተከታዮቹ ባከናወኑት የስብከት እንቅስቃሴ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ይሖዋን በመንፈስና በእውነት የማምለክ ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። (ዮሐንስ 4:​24) ከአራት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ክርስትናን ተቀበሉ። በ33 እዘአ በዋለው ጰንጠቆስጤ ዕለት ሦስት ሺህ ሰዎች ተጠመቁ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ‘የወንዶቹ ቊጥር አምስት ሺህ ሆኗል።’ (ሥራ 2:​41፤ 4:​4) ደቀ መዛሙርቱ በቅንዓት ይህን ብርሃን በማንጸባረቃቸው “በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቊጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።”​—⁠ሥራ 6:​7

19 በተትረፈረፈ የመከር አዝመራ ደስ እንደሚላቸው ወይም ከታላቅ ወታደራዊ ድል በኋላ ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ብዝበዛ በመከፋፈል እንደሚደሰቱ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በተገኘው ጭማሪ ፈንድቀዋል። (ሥራ 2:​46, 47) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ይህ ብርሃን ለአሕዛብ እንዲበራ አድርጓል። (ሥራ 14:​27) ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችለው መንገድ ለእነርሱም ስለተከፈተላቸው ከየብሔራቱ የተውጣጡ ሰዎች እጅግ ደስ ብሏቸዋል።​—⁠ሥራ 13:​48

“በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ”

20. (ሀ) ምድያማውያን የእስራኤል ጠላቶች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው? ይሖዋስ እነርሱ የፈጠሩትን ስጋት ወደ ፍጻሜው ያመጣው እንዴት ነው? (ለ) ወደፊት በሚመጣው ‘የምድያም ቀን’ ኢየሱስ የአምላክ ጠላቶች የሚፈጥሩትን ስጋት የሚያስወግደው እንዴት ነው?

20 ኢሳይያስ ቀጥሎ ከተናገራቸው ቃላት መረዳት እንደምንችለው የመሲሁ እንቅስቃሴ ያስገኛቸው ውጤቶች ዘላቂ ናቸው:- “በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር የአስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል።” (ኢሳይያስ 9:​4) ከኢሳይያስ ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ምድያማውያን እስራኤላውያንን በኃጢአት ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት ከሞዓባውያን ጋር አሲረውባቸው ነበር። (ዘኍልቁ 25:​1-9, 14-18፤ 31:​15, 16) በኋላም ምድያማውያን እስራኤላውያንን በመውረር እንዲሁም መንደሮቻቸውንና እርሻዎቻቸውን በመዝረፍ ለሰባት ዓመታት ሲያሸብሯቸው ቆይተዋል። (መሳፍንት 6:​1-6) ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ይሖዋ በአገልጋዩ በጌዴዎን አማካኝነት የምድያማውያንን ሠራዊት አሳደደላቸው። ከዚያ ‘የምድያም ጊዜ’ አንስቶ የይሖዋ ሕዝቦች በምድያማውያን እጅ እንደተቸገሩ የሚገልጽ ምንም መረጃ የለም። (መሳፍንት 6:​7-16፤ 8:​28) በቅርቡም ታላቁ ጌዴዎን ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ ባሉት የይሖዋ ጠላቶች ላይ በማያዳግም ሁኔታ ክንዱን ያሳርፍባቸዋል። (ራእይ 17:​14፤ 19:​11-21) በዚህ ጊዜ በሰዎች ልዩ ችሎታ ሳይሆን በይሖዋ ኃይል ‘እንደ ምድያም ጊዜ’ የተሟላና ዘላቂ ድል ይገኛል። (መሳፍንት 7:​2-22) ከዚህ በኋላ የአምላክ ሕዝብ ዳግም በጭቆና ቀንበር አይማቅቅም!

21. የኢሳይያስ ትንቢት ጦርነት ወደፊት ምን እንደሚሆን ይናገራል?

21 የመለኮታዊው ኃይል መግለጫዎች መታየታቸው ጦርነትን እንደማወደስ ሊቆጠር አይገባም። ከሞት የተነሣውና የሰላም መስፍን የሆነው ኢየሱስ ጠላቶቹን በማጥፋት ለዘላለም የሚዘልቅ ሰላም ያሰፍናል። ቀጥሎ ኢሳይያስ ወታደራዊ ቁሶች ሙሉ በሙሉ በእሳት እንደሚበሉ ይገልጻል:- “የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፣ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፣ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል።” (ኢሳይያስ 9:​5) ሰልፈኛ ወታደሮች የሚያሰሙት የእርግጫ ድምፅ ዳግመኛ አይሰማም። በውጊያ የደነደኑት ጦረኞች በደም የተነከረ ልብስ ከእንግዲህ በኋላ አይታይም። ጦርነት ፈጽሞ አይኖርም!​—⁠መዝሙር 46:​9

“ድንቅ መካር”

22. ኢየሱስ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ምን ባለ ብዙ ዘርፍ ትንቢታዊ ስም ተሰጥቶታል?

22 መሲሕ የሚሆነው ሕፃን በተዓምራዊ ሁኔታ ሲወለድ “ይሖዋ ማዳን ነው” የሚል ትርጉም ያለው ኢየሱስ የሚል ስም ተሰጥቶታል። ይሁን እንጂ የሚጫወተውን ቁልፍ ሚናና ከፍ ያለ ቦታውን የሚገልጹ ሌሎች ትንቢታዊ ስሞችም አሉት። ከእነዚህም መካከል “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የሚል ትርጉም ያለው አማኑኤል የሚለው ስሙ ይገኝበታል። (ኢሳይያስ 7:​14 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) አሁን ደግሞ ኢሳይያስ ስለ ሌላ ትንቢታዊ ስም ይናገራል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ [“መስፍን፣” NW ] ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳይያስ 9:​6) ይህ ባለ ብዙ ዘርፍ ትንቢታዊ ስም ያዘለውን ትርጉም ተመልከት።

23, 24. (ሀ) ኢየሱስ “ድንቅ መካር” የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) ዛሬ ያሉ ክርስቲያን መካሪዎች የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

23 መካር ማለት ምክር ወይም ሐሳብ የሚያካፍል ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር በነበረበት ወቅት ድንቅ ምክሮችን ለግሷል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ሕዝቡ በትምህርቱ እንደተገረሙ’ እናነባለን። (ማቴዎስ 7:​28) የሰውን ተፈጥሮ አብጠርጥሮ የሚያውቅ ጥበበኛና የሰው ችግር የሚገባው መካሪ ነው። ምክሩ ተግሳጽና ወቀሳ ብቻ አልነበረም። ብዙውን ጊዜ በትምህርትና በፍቅራዊ መመሪያ መልክ የሚቀርብ ነበር። የኢየሱስ ምክር ሁል ጊዜም ጥበብ የሞላበት፣ ፍጹምና የማይሻር በመሆኑ ድንቅ ነው። ምክሩን ከተከተልነው ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራናል።​—⁠ዮሐንስ 6:​68

24 የኢየሱስ ምክር እንዲሁ ከራሱ ብልህ አእምሮው አፍልቆ የሚናገረው አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:​16) እንደ ሰሎሞን ሁሉ የኢየሱስም የጥበብ ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነበር። (1 ነገሥት 3:​7-14፤ ማቴዎስ 12:​42) ይህ የኢየሱስ ምሳሌ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አስተማሪዎችና መካሪዎች የሚሰጡት ትምህርት ዘወትር በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ሊያነሳሳቸው ይገባል።​—⁠ምሳሌ 21:​30

“ኃያል አምላክ” እና “የዘላለም አባት”

25. “ኃያል አምላክ” የሚለው ስም ሰማያዊ ቦታውን ስለያዘው ኢየሱስ ምን ይጠቁመናል?

25 በተጨማሪም ኢየሱስ “ኃያል አምላክ” እና “የዘላለም አባት” ነው። ይህ ማለት ግን ‘የእግዚአብሔር አባታችንን’ ማለትም የይሖዋን ሥልጣንና ቦታ ይቀማል ማለት አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 1:​2) “እርሱ [ኢየሱስ] . . . ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም።” (ፊልጵስዩስ 2:​6) ኢየሱስ ኃያል አምላክ እንጂ ሁሉን ቻይ አምላክ ተብሎ አልተጠራም። ኢየሱስ “ብቻህን እውነተኛ አምላክ” የሆንክ በማለት ልናመልከው የሚገባ ብቸኛ አምላክ አባቱ መሆኑን ስለተናገረ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ ብሎ ፈጽሞ አስቦ አያውቅም። (ዮሐንስ 17:​319080 ትርጉም ፤ ራእይ 4:​11) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “አምላክ” [god] የሚለው ቃል “ኃያል” ወይም “ብርቱ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። (ዘጸአት 12:​12፤ መዝሙር 8:​5 NW 2 ቆሮንቶስ 4:​4) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ‘በእግዚአብሔር መልክ የሚኖር’ “አምላክ” ነበር። ከትንሣኤው በኋላ፣ በፊት ከነበረውም የላቀ ቦታ በሰማይ አግኝቷል። (ዮሐንስ 1:​1 NW ፊልጵስዩስ 2:​6-11) ከዚህም በላይ “አምላክ” የሚለው መጠሪያ ተጨማሪ አንድምታ አለው። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ራሱ በእስራኤል የነበሩትን መሳፍንት “አማልክት” ብሎ ጠርቷቸዋል። (መዝሙር 82:​6፤ ዮሐንስ 10:​35) ኢየሱስ ደግሞ “በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ” ከይሖዋ ሥልጣን የተሰጠው መስፍን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:​1፤ ዮሐንስ 5:​30) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ኃያል አምላክ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።

26. ኢየሱስ “የዘላለም አባት” ተብሎ ሊጠራ የሚችለው እንዴት ነው?

26 “የዘላለም አባት” የሚለው የማዕረግ ስም መሲሐዊው ንጉሥ ለሰው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ የመስጠት ኃይልና ሥልጣን እንዳለው የሚያመለክት ነው። (ዮሐንስ 11:​25, 26) ከመጀመሪያው ወላጃችን ከአዳም የወረስነው ቅርስ ሞት ነው። ኋለኛው አዳም ኢየሱስ ግን “ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።” (1 ቆሮንቶስ 15:​22, 45፤ ሮሜ 5:​12, 18) ዘላለማዊ አባት የሆነው ኢየሱስ ለዘላለም እንደሚኖር ሁሉ ታዛዥ የሆነው የሰው ዘርም ከእርሱ አባትነት ለዘላለም መጠቀሙን ይቀጥላል።​—⁠ሮሜ 6:​9

“የሰላም መስፍን”

27, 28. ‘ለሰላሙ መስፍን’ የሚገዙ ሰዎች ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚያገኟቸው ድንቅ በረከቶች ምንድን ናቸው?

27 የሰው ልጅ የዘላለም ሕይወት ብቻ ሳይሆን ከአምላክና ከሌሎች ሰዎችም ጋር ሰላም ማግኘት ያስፈልገዋል። ራሳቸውን ‘ለሰላሙ መስፍን’ ያስገዙ ሰዎች ዛሬም እንኳ ሳይቀር ‘ሰይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውን ማጭድ ለማድረግ ቀጥቅጠዋል።’ (ኢሳይያስ 2:​2-4) በፖለቲካ፣ በድንበር፣ በዘር ወይም በኢኮኖሚ ልዩነቶች ሳቢያ ጥላቻን አያስተናግዱም። ብቻውን እውነተኛ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ በሚያቀርቡት አምልኮ በአንድነት የተሳሰሩ ሲሆን በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጭ ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይጥራሉ።​—⁠ገላትያ 6:​10፤ ኤፌሶን 4:​2, 3፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:​24

28 አምላክ በቀጠረው ጊዜ ክርስቶስ ምድር አቀፍና ጽኑ መሠረት ያለው ዘላቂ ሰላም ያሰፍናል። (ሥራ 1:​7) “ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና [“በፍትሕና፣” NW ] በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።” (ኢሳይያስ 9:​7ሀ) ኢየሱስ የሰላም መስፍንነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ፈላጭ ቆራጭ በሆነ መንገድ አይደለም። ተገዢዎቹ ነፃ ምርጫቸውን የተገፈፉና በጭቆና የሚገዙ ሰዎች አይሆኑም። ከዚህ ይልቅ ሁሉንም ነገር የሚያከናውነው “በፍትሕና በጽድቅ” ይሆናል። እንዴት ያለ የሚያጽናና ለውጥ ነው!

29. ዘላለማዊ ሰላም አግኝተን ለመደሰት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

29 የኢየሱስ ትንቢታዊ ስም ካዘለው ድንቅ አንድምታ አንጻር የዚህኛው የኢሳይያስ ትንቢት ክፍል መደምደሚያ በእርግጥ የሚያስደስት ነው። “የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል” ሲል ጽፏል። (ኢሳይያስ 9:​7ለ) አዎን፣ ይሖዋ በቅንዓት እርምጃ ይወስዳል። በግማሽ ልብ የሚሠራው ነገር የለም። ቃል የገባውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንግዲያው ዘላለማዊ ሰላም ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል ይኖርባቸዋል። እንደ ይሖዋ አምላክና የሰላም መስፍን እንደሆነው እንደ ኢየሱስ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ‘ለመልካም ሥራ የሚቀኑ’ እንዲሆኑ ምኞታችን ነው።​—⁠ቲቶ 2:​14

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ብዙዎች መዝሙር 119 ሕዝቅያስ ንጉሥ ከመሆኑ በፊት የጻፈው መዝሙር ነው ብለው ያምናሉ። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ይህ መዝሙር የተጻፈው ኢሳይያስ ትንቢት እየተናገረ ባለበት ዘመን እንደሚሆን እሙን ነው።

^ አን.9 በ⁠ኢሳይያስ 8:​20 ላይ የሚገኘው “እንዲህም ያለውን ቃል” የሚለው ሐረግ በ⁠ኢሳይያስ 8:​19 ላይ የተጠቀሰውን መናፍስታዊ ሥራ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ኢሳይያስ በይሁዳ መናፍስታዊ ሥራን የሚያስፋፉት ሰዎች ሌሎችም መናፍስት ጠሪዎችን እንዲጠይቁ መወትወታቸውን ይቀጥላሉ ማለቱ ስለሚሆን ከይሖዋ ምንም ዓይነት የእውቀት ብርሃን አያገኙም።

^ አን.13 አንዳንዶች ንጉሥ ሰሎሞን ለጢሮስ ንጉሥ ለኪራም የሰጠው 20 የገሊላ ከተሞች እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች የነበሩባቸው ሳይሆኑ አይቀሩም የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።​—⁠1 ነገሥት 9:​10-13

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ገጽ 122 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኮራዚ

ቅፍርናሆም

ቤተሳይዳ

የጌንሴሬጥ ምድር

የገሊላ ባሕር

መጌዶል

ጥብርያዶስ

የዮርዳኖስ ወንዝ

ጋዳራ

ጋዳራ

[በገጽ 119 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቃየንም ሆነ የኢየሱስ ውልደት ልዩ ነበር። መጨረሻው ያማረው ግን የኢየሱስ ብቻ ነው

[በገጽ 121 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት የከፋ ራብ ይኖራል

[በገጽ 127 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

ኢየሱስ ለምድሪቱ ብርሃን ሆኖ ነበር