በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ እጅ ከፍ ከፍ ትላለች

የይሖዋ እጅ ከፍ ከፍ ትላለች

ምዕራፍ ሃያ አንድ

የይሖዋ እጅ ከፍ ከፍ ትላለች

ኢሳይያስ 25:​1–​27:​13

1. ኢሳይያስ ለይሖዋ አድናቆት ያደረበት ለምንድን ነው?

ኢሳይያስ ለይሖዋ ያለው ፍቅር የጠለቀ ከመሆኑም ሌላ እርሱን በማወደስ ደስ ይለዋል። “አቤቱ፣ አንተ አምላኬ ነህ፤ . . . ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናለሁ” በማለት ተናግሯል። ነቢዩ ለፈጣሪው እንዲህ ዓይነት ጥልቅ አድናቆት እንዲኖረው የረዳው ነገር ምንድን ነው? ዋናው ነገር ስለ ይሖዋና ስለ ሥራዎቹ ያለው እውቀት ነው። ቀጥሎ ኢሳይያስ የተናገረው ነገር ይህ እውቀት እንዳለው ያሳያል:- “ድንቅን ነገር የዱሮ ምክርን በታማኝነትና በእውነት አድርገሃል።” (ኢሳይያስ 25:​1) ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ ኢያሱ ሁሉ ኢሳይያስም ይሖዋ የታመነና ትምክህት የሚጣልበት እንደሆነ እንዲሁም ‘ምክሩን ሁሉ’ ማለትም ዓላማ ያደረገውን ነገር እንደሚፈጽም ያውቃል።​—⁠ኢያሱ 23:​14

2. ኢሳይያስ አሁን የሚናገረው የትኛውን የይሖዋን ምክር ነው? ይህስ ምክር የተመከረው በማን ላይ ነው?

2 የይሖዋ ምክር በእስራኤል ጠላቶች ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ ይጨምራል። ቀጥሎ ኢሳይያስ የሚጠቅሰው ከእነዚህ መካከል አንዱን ይሆናል:- “ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፣ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፣ የኀጥኣንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፤ ከቶ አትሠራም።” (ኢሳይያስ 25:​2) ይህቺ በስም ያልተጠቀሰች ከተማ ማን ናት? ኢሳይያስ ምናልባት የሞዓቧን ዔር መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። ሞዓብ ለብዙ ዘመናት የአምላክ ሕዝብ ጠላት ሆና ኖራለች። * ወይም ደግሞ ጠንካራ ስለሆነች ሌላ ከተማ ስለ ባቢሎን መጥቀሱ ሊሆን ይችላል።​—⁠ኢሳይያስ 15:​1፤ ሶፎንያስ 2:​8, 9

3. የይሖዋ ጠላቶች እርሱን የሚያከብሩት በምን መንገድ ነው?

3 ይሖዋ ብርቱ በሆነችው ከተማቸው ላይ የመከረው ምክር እውን ሲሆን ጠላቶቹ የሚሰጡት ምላሽ ምን ይሆን? “ስለዚህ ኃያላኑ ወገኖች ያከብሩሃል፣ የጨካኞች አሕዛብ ከተማም ትፈራሃለች።” (ኢሳይያስ 25:​3) ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ጠላቶቹ ቢፈሩት ምንም አያስገርምም። ይሁን እንጂ የሚያከብሩት እንዴት ነው? የሐሰት አማልክቶቻቸውን እርግፍ አድርገው ትተው እውነተኛውን አምልኮ ይቀበላሉ ማለት ነው? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ እንደ ፈርዖንና ናቡከደነፆር ሁሉ የማይደፈር የበላይነቱን አምነው ለመቀበል ሲገደዱ ያከብሩታል።​—⁠ዘጸአት 10:​16, 17፤ 12:​30-33፤ ዳንኤል 4:​37

4. ዛሬ ያለችው “የጨካኞች ከተማ” ማን ነች? ይቺ ከተማም ጭምር ይሖዋን ለማክበር የምትገደደው እንዴት ነው?

4 ዛሬ “የጨካኞች አሕዛብ ከተማ” የሆነችው ‘በምድር ነገሥታት ላይ የነገሠችው ታላቂቱ ከተማ’ ማለትም “ታላቂቱ ባቢሎን” ነች። (ራእይ 17:​5, 18) የዚህች ግዛት ዋነኛ ክፍል ሕዝበ ክርስትና ነች። የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ይሖዋን የሚያከብሩት እንዴት ነው? ለምሥክሮቹ ያደረገላቸውን ድንቅ ነገሮች ሳይወዱ በግድ አምነው በመቀበል ነው። በተለይ በ1919 ይሖዋ አገልጋዮቹን በታላቂቱ ባቢሎን ተይዘውበት ከነበረው መንፈሳዊ ምርኮ ነፃ በማውጣት እጅግ ከፍተኛ ወደሆነ የሥራ እንቅስቃሴ ሲያሸጋግራቸው እነዚህ መሪዎች ‘ፍርሃት ይዟቸው ለሰማዩ አምላክ ክብር ሰጥተዋል።’​—⁠ራእይ 11:​13 *

5. ይሖዋ በእርሱ ላይ ሙሉ ትምክህት ያላቸውን ሰዎች የሚጠብቃቸው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ለጠላቶቹ የሚያስፈራ ቢሆንም ቅንና ትሑት በመሆን እርሱን ማገልገል ለሚፈልጉ ሰዎች ግን መሸሸጊያቸው ነው። ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ገዥዎች የእውነተኛ አምላኪዎችን እምነት ለመናድ የተቻላቸውን ያህል ይጥሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት ስላላቸው አይሳካላቸውም። በመጨረሻም ይሖዋ እንደ እሳት የሚፋጀውን የበረሃ ፀሐይ በደመና የመሸፈን ወይም የውሽንፍርን ኃይል በቅጥር የመመከት ያህል ተቃዋሚዎቹን በቀላሉ ዝም ያሰኛቸዋል።​—⁠ኢሳይያስ 25:​4, 5ን አንብብ።

‘ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን የሰባ ግብዣ’

6, 7. (ሀ) ይሖዋ ምን ዓይነት ግብዣ አዘጋጅቷል? የተዘጋጀውስ ለእነማን ነው? (ለ) ኢሳይያስ በትንቢት የተናገረለት የሰባ ግብዣ የምን ነገር ጥላ ነው?

6 ይሖዋ በተለይ በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹን ከአደጋ ከመጠበቅም አልፎ ይመግባቸዋል። በ1919 ሕዝቡን ነፃ ካወጣ በኋላ የሰባ የድል ግብዣ ማለትም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አዘጋጅቶላቸዋል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።”​—⁠ኢሳይያስ 25:​6

7 ይህ የሰባ ግብዣ የቀረበው በይሖዋ “ተራራ” ላይ ነው። ይህ ተራራ ምንድን ነው? “በዘመኑ ፍጻሜ” ‘አሕዛብ ሁሉ የሚጎርፉበት የእግዚአብሔር ቤት ተራራ’ ነው። የታመኑት አምላኪዎቹ ሌሎችን የማይጎዱበትና የማያጠፉበት ‘የተቀደሰው የይሖዋ ተራራ’ ነው። (ኢሳይያስ 2:​2፤ 11:​9) ይሖዋ በዚህ ከፍ ያለ የአምልኮ ሥፍራ የታመኑ ሆነው ለተገኙት ሰዎች ሁሉም ነገር የተትረፈረፈበትን የሰባ ግብዣ ያቀርባል። በአሁኑ ጊዜ ተትረፍርፈው የሚቀርቡት መልካም መንፈሳዊ ዝግጅቶች የአምላክ መንግሥት ብቸኛ የሰው ልጅ መስተዳድር በሚሆንበት ጊዜ ለሚኖሩት መልካም ሰብዓዊ ነገሮች ጥላ ይሆናሉ። በዚያ ጊዜ ረሃብ አይኖርም። ‘በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኖራል። ተራሮች በሰብል ይሸፈናሉ።’​—⁠መዝሙር 72:​8, 161980 ትርጉም

8, 9. (ሀ) ከምድር ገጽ የሚወገዱት ሁለቱ የሰው ልጅ ጠላቶች የትኞቹ ናቸው? አብራራ። (ለ) አምላክ የሕዝቡን ስድብ ለማስወገድ ምን እርምጃ ይወስዳል?

8 በአሁኑ ጊዜ አምላክ ከሚያቀርበው መንፈሳዊ ድግስ የሚቋደሱ ሰዎች ወደፊት ክብራማ ተስፋ ይጠብቃቸዋል። ቀጥሎ ኢሳይያስ የተናገረውን ነገር ልብ በል። ኃጢአትና ሞትን ‘ከመጋረጃ’ እና ‘ከመሸፈኛ’ ጋር በማነፃፀር እንዲህ ብሏል:- “በዚህም ተራራ ላይ [ይሖዋ ] በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፣ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”​—⁠ኢሳይያስ 25:​7, 8ሀ

9 አዎን፣ ኃጢአትና ሞት አይኖርም! (ራእይ 21:​3, 4) ከዚህም በላይ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በይሖዋ አገልጋዮች ላይ በሐሰት ሲሰነዘር የኖረው ስድብ ይወገዳል። “የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።” (ኢሳይያስ 25:​8ለ) ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ይሖዋ የዚህ ስድብ ምንጭ የሆነውን ሰይጣንና የእርሱን ዘር ያስወግዳል። (ራእይ 20:​1-3) የአምላክ ሕዝብ እንደሚከተለው ብሎ በደስታ ለመናገር ቢነሳሳ ምንም አያስገርምም:- “እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፣ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል።”​—⁠ኢሳይያስ 25:​9

ትዕቢተኞች ይዋረዳሉ

10, 11. ሞዓብ ከይሖዋ የሚጠብቃት የከፋ ነገር ምንድን ነው?

10 ይሖዋ የእርሱ የሆኑትን ትሑታን ያድናል። ይሁን እንጂ የእስራኤል ጎረቤት የሆነችው ሞዓብ ትዕቢተኛ ነች። ይሖዋ ደግሞ ትዕቢትን አጥብቆ ይጠላል። (ምሳሌ 16:​18) በመሆኑም ሞዓብ ለውርደት ከተፈረጁት መካከል ሆናለች። “የእግዚአብሔርም እጅ በዚህ ተራራ ላይ ታርፋለች፣ ጭድም በጭቃ [“በእበት፣” NW ] ውስጥ እንደሚረገጥ እንዲሁ ሞዓብ በስፍራው ይረገጣል። ዋናተኛም ሲዋኝ እጁን እንደሚዘረጋ፣ እንዲሁ በመካከሉ እጁን ይዘረጋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ትዕቢቱን ከእጁ ተንኰል ጋር ያዋርዳል። የተመሸገውንም ከፍ ከፍ ያለውንም ቅጥርህን ዝቅ ያደርገዋል፣ ያዋርደውማል፣ ወደ መሬትም እስከ አፈር ድረስ ይጥለዋል።”​—⁠ኢሳይያስ 25:​10-12

11 የይሖዋ እጅ ጥበቃ ለማድረግ በቅዱስ ተራራው ላይ ‘ያርፋል።’ ይሁን እንጂ ትዕቢተኛዋ ሞዓብ ትመታና “በእበት ውስጥ” ትረገጣለች። በኢሳይያስ ዘመን ማዳበሪያ እንዲሆን ሲባል ጭድ በእበት ውስጥ ይረገጥ ስለነበር ኢሳይያስ ሞዓብ ከፍ ያለና አስተማማኝ የሚመስል ቅጥር ቢኖራትም ውርደት እንደሚገጥማት መተንበዩ ነበር።

12. ሞዓብ ተነጥላ የይሖዋ የፍርድ መልእክት የተነገረባት ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ ሞዓብን ለይቶ እንዲህ ዓይነት ከባድ ምክር የመከረባት ለምንድን ነው? ሞዓባውያን የአብርሃም የወንድም ልጅና የይሖዋ አምላኪ የሆነው የሎጥ ዝርያ ናቸው። በመሆኑም ከአምላክ የቃል ኪዳን ብሔር ጋር የነበራቸው ግንኙነት የጉርብትና ብቻ ሳይሆን በደም የተሳሰረም ነበር። ይህ ሆኖ እያለ የሐሰት አማልክትን ከማምለክም አልፈው ለእስራኤላውያን የማይተኙ ጠላት ሆነውባቸው ነበር። ዕጣ ፈንታቸው ይህ መሆኑ ሲያንሳቸው ነው። ከዚህ አንጻር ሲታይ ሞዓብ ዛሬ ያሉትን የይሖዋን አገልጋዮች የሚቃወሙ ጠላቶች ትመስላለች። በተለይ ደግሞ መገኛዬ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ነው እያለች የምትናገረውንና ቀደም ብለን እንዳየነው ግን የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል የሆነችውን ሕዝበ ክርስትናን ትመስላለች።

የመዳን ዝማሬ

13, 14. ዛሬ የአምላክ ሕዝብ ያገኘው “የጸና ከተማ” ምንድን ነው? ወደዚህ እንዲገቡስ የሚፈቀድላቸው እነማን ናቸው?

13 ስለ አምላክ ሕዝብስ ምን ለማለት ይቻላል? የይሖዋን ሞገስና ጥበቃ በማግኘታቸው ተደስተው የዝማሬ ድምፅ ያሰማሉ። “በዚያም ቀን ይህ ቅኔ በይሁዳ ምድር ይዘመራል:- የጸናች ከተማ አለችን፤ ለቅጥርና ለምሽግ መድኃኒትን ያኖርባታል። እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ።” (ኢሳይያስ 26:​1, 2) እነዚህ ቃላት ጥንት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ የሚያጠያይቅ ጉዳይ ባይሆንም ዛሬም በማያሻማ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። የይሖዋ “ጻድቅ ሕዝብ” ማለትም መንፈሳዊ እስራኤል ከተማ መሰል ጠንካራ ድርጅት አግኝቷል። ይህ ለደስታና ለዝማሬ ግሩም ምክንያት ነው!

14 ወደዚህች “ከተማ” የሚገቡት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? መልሱን መዝሙሩ ላይ እናገኛለን:- “የሚታመኑት በአንተ [በአምላክ ] ነውና የምትደግፈውን ዝንባሌ እስከ መጨረሻ በሰላም ትጠብቀዋለህ። ሕዝቦች ሆይ፣ ያህ ይሖዋ የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በይሖዋ ታመኑ።” (ኢሳይያስ 26:​3, 4 NW ) ይሖዋ የሚደግፈው “ዝንባሌ” የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን የመታዘዝና በሚውተረተረው የዓለም የንግድ፣ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ሥርዓት ሳይሆን በእርሱ የመታመን ውስጣዊ ፍላጎት ነው። ብቸኛው አስተማማኝ የደህንነት አምባ “ያህ ይሖዋ” ነው። በእርሱ ላይ ሙሉ ትምክህት ያላቸው ሁሉ የይሖዋን ጥበቃ ከማግኘታቸውም ሌላ ‘ቀጣይ የሆነ ሰላም’ ይኖራቸዋል።​—⁠ምሳሌ 3:​5, 6፤ ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

15. ዛሬ ‘ከፍ ያለችው ከተማ’ የተዋረደችው እንዴት ነው? ‘የችግረኞችስ እግር የረገጣት’ እንዴት ነው?

15 ይህ የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች ከሚደርስባቸው ነገር ምንኛ የተለየ ነው! “በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፤ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፣ እስከ መሬትም ድረስ ያወርዳታል፣ እስከ አፈርም ድረስ ይጥላታል። እግር፣ የድሀ እግርም የችግረኛም አረጋገጥ፣ ትረግጣታለች።” (ኢሳይያስ 26:​5, 6) አሁንም ኢሳይያስ እየተናገረ ያለው በሞዓብ ስለምትገኝ “ከፍ ያለች” ከተማ ወይም ደግሞ እንደ ባቢሎን ስላለች በትዕቢቷ ከፍ ከፍ ያለች ሌላ ከተማ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ ‘ከፍ ያለችው ከተማ’ ሁኔታ የተገላቢጦሽ እንዲሆን አድርጓል። የእርሱ ‘ድሆችና ችግረኞች’ ይረግጧታል። በዛሬው ጊዜ ይህ ትንቢት ለታላቂቱ ባቢሎን በተለይም ደግም ለሕዝበ ክርስትና በትክክል የሚሠራ ነው። በ1919 ይህች ‘ከፍ ያለች ከተማ’ የይሖዋን ሕዝብ ለመልቀቅ ማለትም የውርደት አወዳደቅ ለመውደቅ የተገደደች ሲሆን እነርሱም በተራቸው በቁጥጥሯ ሥር አስገብታቸው የነበረችውን ይህችን ከተማ በእግራቸው ረግጠዋታል። (ራእይ 14:​8) እንዴት? ይሖዋ በእርሷ ላይ ስለሚወስደው ስለ መጪው የበቀል እርምጃ ለሕዝብ በማወጅ ነው።​—⁠ራእይ 8:​7-12፤ 9:​14-19

ጽድቅንና የይሖዋን ‘መታሰቢያ’ መመኘት

16. ኢሳይያስ ለአምላክ በነበረው ፍቅር ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

16 ከዚህ የድል ዝማሬ በኋላ ኢሳይያስ ምን ያህል የጠለቀ አምላካዊ ፍቅር እንዳለውና የጽድቅ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማገልገል ያለውን በረከት ይገልጻል። (ኢሳይያስ 26:​7-9ን አንብብ።) ነቢዩ ‘በይሖዋ ተስፋ በማድረግ’ እንዲሁም ለይሖዋ “ስም” እና “መታሰቢያ” ውስጣዊ ጉጉት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። የይሖዋ መታሰቢያ የተባለው ነገር ምንድን ነው? ዘጸአት 3:​15 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW  ] . . . ለዘላለሙ ስሜ ነው፣ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ነው።” ኢሳይያስ ለይሖዋ ስም እንዲሁም የእርሱን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎችና መንገዶች ጨምሮ ስሙ ለሚወክላቸው ነገሮች ሁሉ ከፍ ያለ ግምት አለው። ለይሖዋ ተመሳሳይ ፍቅር የሚኮተኩቱ ሁሉ የእርሱን በረከት እንደሚያገኙ ዋስትና አላቸው።​—⁠መዝሙር 5:​8፤ 25:​4, 5፤ 135:​13፤ ሆሴዕ 12:​5

17. ክፉዎች የማያገኙት መብት ምንድን ነው?

17 ይሖዋንና ከፍ ያለውን የአቋም ደረጃውን የሚወድዱት ሁሉም ሰዎች ናቸው ማለት አይደለም። (ኢሳይያስ 26:​10ን አንብብ።) ክፉዎች ወደ “ቅኖች ምድር” ማለትም በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ቅን የሆነውን መንገድ የሚከተሉት የይሖዋ አገልጋዮች ወዳሉበት ምድር እንዲገቡ ግብዣ ሲቀርብላቸው እንኳ በእልከኝነት እምቢ ይላሉ። ከዚህ የተነሣ ክፉዎች ‘የይሖዋን ግርማ አያዩም።’ የይሖዋ ስም ከተቀደሰ በኋላ ለሰው ዘር ከሚፈሰው በረከት ለመቋደስ አይታደሉም። መላዋ ፕላኔት ‘የቅኖች ምድር’ በምትሆንበት በአዲሱ ዓለም ሳይቀር ለይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚሳናቸው አንዳንዶች ይኖራሉ። የእነዚህ ሰዎች ስም በሕይወት መጽሐፍ ላይ አይጻፍም።​—⁠ኢሳይያስ 65:​20፤ ራእይ 20:​12, 15

18. በኢሳይያስ ዘመን የነበሩ አንዳንዶች በገዛ ምርጫቸው የታወሩት እንዴት ነው? ይሖዋን ‘ለማየት’ የሚገደዱትስ መቼ ይሆናል?

18 “አቤቱ፣ እጅህ ከፍ ከፍ አለች አላዩምም፤ ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፤ እሳትም ጠላቶችህን ትበላለች።” (ኢሳይያስ 26:​11) በኢሳይያስ ዘመን ይሖዋ በጠላቶቻቸው ላይ እርምጃ በመውሰድ ሕዝቡን በጠበቃቸው ጊዜ እጁ ከፍ ያለች መሆኗ ታይቷል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች ይህንን አልተገነዘቡም። በገዛ ምርጫቸው በመንፈሳዊ የታወሩት እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በመጨረሻ በይሖዋ የቅንዓት እሳት ሲበሉ ይሖዋን ‘ያዩታል’ ወይም በሌላ አባባል ማንነቱን ይገነዘባሉ። (ሶፎንያስ 1:​18) ከጊዜ በኋላ አምላክ ለሕዝቅኤል “እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” ብሎታል።​—⁠ሕዝቅኤል 38:​23

“ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋል”

19, 20. ይሖዋ ሕዝቡን የቀጣው ለምንና እንዴት ነው? ከዚህስ ቅጣት እነማን ተጠቅመዋል?

19 ኢሳይያስ የአገሩ ሰዎች ሰላምና ብልጽግና ሊያገኙ የሚችሉት በይሖዋ በረከት ብቻ እንደሆነ ያውቃል። “አቤቱ፣ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ።” (ኢሳይያስ 26:​12) ይሖዋ ይህን እያደረገላቸውና ከሕዝቡ ፊት ‘የካህናት መንግሥትና የተቀደሰ ሕዝብ’ የመሆን አጋጣሚ ዘርግቶላቸው እያለ እንኳ የይሁዳ አካሄድ ወጣ ገባ ነበር። (ዘጸአት 19:​6) ሕዝቧ በተደጋጋሚ ፊቱን ወደ ሐሰት አማልክት መልሷል። ከዚህ የተነሣ በተደጋጋሚ ጊዜ ተቀጥተዋል። ይሁን እንጂ ‘ይሖዋ የሚቀጣው የሚወደውን በመሆኑ’ እንዲህ ያለው ቅጣት የእርሱ ፍቅር መግለጫ ነው።​—⁠ዕብራውያን 12:​6

20 ብዙውን ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን የሚቀጣው “ሌሎች ጌቶች ” ማለትም ሌሎች ብሔራት እንዲገዟቸው አሳልፎ በመስጠት ነው። (ኢሳይያስ 26:​13ን አንብብ።) በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን በምርኮ እንዲወስዷቸው ፈቅዶ ነበር። ይህ ይጠቅማቸዋልን? ሥቃይ በራሱ ለአንድ ሰው የሚያመጣው ጥቅም የለም። ይሁን እንጂ ሥቃዩ የደረሰበት ሰው ከገጠመው ነገር ትምህርት አግኝቶ ንስሐ የሚገባና ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ የሚያቀርብ ከሆነ ያኔ ይጠቀማል። (ዘዳግም 4:​25-31) አምላካዊ ንስሐ የሚያሳዩ አይሁዳውያን ይኖሩ ይሆን? አዎን! ኢሳይያስ በትንቢታዊ መልክ ሲናገር “በአንተ ብቻ ስምህን እናስባለን ” ብሏል። አይሁዳውያኑ በ537 ከዘአበ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ በሌሎች ኃጢአቶች ምክንያት ተግሳጽ አስፈልጓቸው የነበረ ቢሆንም ዳግመኛ የድንጋይ አማልክትን ወደ ማምለክ ግን ዘወር አላሉም።

21. የአምላክን ሕዝብ ሲጨቁኑ የነበሩት ምን ይደርስባቸዋል?

21 ይሁዳን በምርኮ ስለወሰዱት ወገኖችስ ምን ማለት ይቻላል? “እነርሱ ሞተዋል፣ በሕይወት አይኖሩም፤ ጠፍተዋል፣ አይነሡም፤ ስለዚህ አንተ ጐብኝተሃቸዋል አጥፍተሃቸውማል፣ መታሰቢያቸውንም ሁሉ ምንምን አድርገሃል።” (ኢሳይያስ 26:​14) ባቢሎን በተመረጠው የይሖዋ ሕዝብ ላይ በፈጸመችው ጭካኔ ምክንያት መከራ ትቀበላለች። ይሖዋ ሜዶንና ፋርስን በመጠቀም ኩሩ የነበረችውን ባቢሎን ገልብጦ ሕዝቡን ከምርኮ ነፃ ያወጣል። ይህቺ ትልቅ ከተማ ባቢሎን የሞተች ያህል አቅመ ቢስ ትሆናለች። በመጨረሻም ከሕልውና ውጭ ትሆናለች።

22. በዘመናችን የአምላክ ሕዝብ የተባረከው እንዴት ነው?

22 በትንቢቱ ዘመናዊ ፍጻሜ መሠረት የተቀጡት የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች በ1919 ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ ወጥተው ወደ ይሖዋ አገልግሎት ተመልሰዋል። ኃይላቸውን አድሰው የተነሱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የስብከት ሥራቸውን በቅንዓት ማከናወኑን ተያይዘውታል። (ማቴዎስ 24:​14) ይሖዋም ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ከእነርሱ ጎን ተሰልፈው እንዲያገለግሉ በመሰብሰብ ጭማሪ እንዲያገኙ በማድረግ ባርኳቸዋል። (ዮሐንስ 10:​16) “ሕዝብን አበዛህ፣ አቤቱ፣ ሕዝብን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፣ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ። አቤቱ፣ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፣ በገሠጽሃቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ።”​—⁠ኢሳይያስ 26:​15, 16

“ይነሣሉ”

23. (ሀ) በ537 ከዘአበ የይሖዋ ኃይል አስደናቂ በሆነ መንገድ የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በ1919 እዘአ የይሖዋ ኃይል የተገለጠበት ምን ተመሳሳይ ነገር ተከናውኗል?

23 ኢሳይያስ፣ ይሁዳ በባቢሎን ሥር በምርኮ እያለች የሚገጥማትን ሁኔታ በተመለከተ ወደሚሰጠው መግለጫ ይመለሳል። ብሔሩን ለመውለድ ምጥ ከያዛትና ያለ እርዳታ መገላገል ከማትችል ሴት ጋር አመሳስሎታል። (ኢሳይያስ 26:​17, 18ን አንብብ።) የይሖዋ ሕዝብ በ537 ከዘአበ ይህን እርዳታ በማግኘቱ ቤተ መቅደሱን ለመገንባትና እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም በከፍተኛ ጉጉት ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሷል። በምሳሌያዊ ሁኔታ ብሔሩ ከሞት የተነሣ ያህል ነበር። “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፣ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፣ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፣ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም።” (ኢሳይያስ 26:​19) እንዴት ያለ ታላቅ የይሖዋ ኃይል መግለጫ ነው! ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ቃላት በ1919 በመንፈሳዊ እስራኤላውያን ላይ ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው እንዴት ታላቅ ክንውን ነበር! (ራእይ 11:​7-11) ወደፊት ደግሞ እነዚህ ቃላት በአዲሱ ዓለም ውስጥ ቃል በቃል ፍጻሜያቸውን አግኝተው በሞት እስር የተያዙት ሰዎች ‘የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው ከመታሰቢያ መቃብር የሚወጡበትን’ ጊዜ በናፍቆት እንጠብቃለን!​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29

24, 25. (ሀ) በ539 ከዘአበ የነበሩት አይሁዳውያን ራሳቸውን እንዲደብቁ የሚናገረውን የይሖዋ ትእዛዝ የጠበቁት እንዴት ሊሆን ይችላል? (ለ) በዘመናችን ‘ቤት’ የተባለው ምን ሊያመለክት ይችላል? ለዚህስ ነገር ልንኮተኩተው የሚገባን ዝንባሌ ምንድን ነው?

24 ይሁን እንጂ የታመኑ ሰዎች ኢሳይያስ ተስፋ የሰጠባቸውን መንፈሳዊ በረከቶች ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋን ትእዛዛት መጠበቅ ይኖርባቸዋል:- “ሕዝቤ ሆይ፣ ና ወደ ቤትህም ግባ፣ ደጅህን በኋላህ ዝጋ፤ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቁጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፣ እነሆ፣ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፣ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።” (ኢሳይያስ 26:​20, 21ከ⁠ሶፎንያስ 1:​14 ጋር አወዳድር።) ይህ ጥቅስ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በንጉሥ ቂሮስ የሚመራው የሜዶንና የፋርስ ኃይል በ539 ከዘአበ ባቢሎንን ድል ባደረገ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ዜኖፎን እንዳለው ከሆነ ቂሮስ ወደ ባቢሎን ሲገባ ፈረሰኞቹ “ከቤቱ በር ውጭ ያገኙትን ሁሉ እንዲገድሉ ታዝዘው ስለነበር” ሁሉም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ ትእዛዝ አስተላልፎአል። በዚህ ትንቢት ላይ የተጠቀሰው “ቤት” በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ካሉት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩት የይሖዋ ሕዝብ ጉባኤዎች ጋር የቅርብ ትስስር ያለው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉት ጉባኤዎች ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ሳይቀር በሕይወታችን ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወታቸውን ይቀጥላሉ። (ራእይ 7:​14) እንግዲያው ለጉባኤ ጤናማ አመለካከት መያዛችንና አዘውትረን መሰብሰባችን ምንኛ አንገብጋቢ ነው!​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

25 በቅርቡ የሰይጣን ዓለም ፍጻሜ ይሆናል። በዚህ አስፈሪ ወቅት ይሖዋ ሕዝቡን የሚያስጥለው እንዴት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። (ሶፎንያስ 2:​3) ይሁን እንጂ በሕይወት መትረፋችን የተመካው በይሖዋ ላይ ባለን እምነት እንዲሁም ለእርሱ በምናሳየው ታማኝነትና ታዛዥነት ላይ እንደሆነ እናውቃለን።

26. በኢሳይያስ ዘመን የነበረው “ሌዋታን” ማንን ያመለክታል? በዘመናችንስ? ይህ ‘የባሕር ዘንዶ’ ምን ይገጥመዋል?

26 ኢሳይያስ ያንን ጊዜ አሻግሮ በመመልከት እንዲህ በማለት ይተነብያል:- “በዚያም ቀን እግዚአብሔር ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን ጠማማውንም እባብ ሌዋታንን በጠንካራ በታላቅም በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፣ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል።” (ኢሳይያስ 27:​1) በትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ ወቅት “ሌዋታን” የተባሉት እስራኤላውያን የተበታተኑባቸው እንደ ባቢሎን፣ ግብጽና አሦር ያሉት አገሮች ናቸው። እነዚህ አገራት ጊዜው ሲደርስ የይሖዋ ሕዝብ ወደ ትውልድ አገሩ እንዳይመለስ ሊያግዱት አይችሉም። ይሁን እንጂ የዘመናችን “ሌዋታን” ማን ነው? “የቀደመው እባብ” የተባለው ሰይጣንና መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ለመዋጋት መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበት ምድር ላይ ያለው የእርሱ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ይመስላል። (ራእይ 12:​9, 10፤ 13:​14, 16, 17፤ 18:​24) “ሌዋታን” በ1919 በአምላክ ሕዝብ ላይ የነበረውን የበላይነት ያጣ ሲሆን በቅርቡም ይሖዋ ‘በባሕር ያለውን ዘንዶ ሲገድል’ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል። እስከዚያው ድረስ ግን “ሌዋታን” የይሖዋን ሕዝብ ለማጥቃት የሚሞክረው ማንኛውም ነገር አይከናወንለትም።​—⁠ኢሳይያስ 54:​17

‘የተወደደ የወይን ቦታ’

27, 28. (ሀ) የይሖዋ የወይን ቦታ መላዋን ምድር የሞላት በምን ነገር ነው? (ለ) ይሖዋ የወይን ቦታውን የሚጠብቀው እንዴት ነው?

27 ቀጥሎ ደግሞ ኢሳይያስ ነፃ የወጣውን የይሖዋ ሕዝብ ፍሬያማነት በሌላ መዝሙር ግሩም አድርጎ ይገልጸዋል:- “በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤ ሁልጊዜ አጠጣዋለሁ፤ ማንም እንዳይጐዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ።” (ኢሳይያስ 27:​2, 3) በእርግጥም የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎችና በትጋት የሚሠሩት ተባባሪዎቻቸው መላዋን ምድር በመንፈሳዊ ፍሬ ሞልተዋታል። ይህ ለደስታና ለዝማሬ የሚሆን እንዴት ግሩም ምክንያት ነው! ለተገኘው ውጤት ሁሉ የሚመሰገነው የወይን ቦታውን በፍቅር የሚንከባከበው ይሖዋ ነው።​—⁠ከ⁠ዮሐንስ 15:​1-8 ጋር አወዳድር።

28 አዎን፣ የይሖዋ የመጀመሪያ ቁጣ አሁን በደስታ ተተክቷል! “አልቈጣም፤ እሾህና ኩርንችት በእኔ ላይ ምነው በሰልፍ በነበሩ! በእነርሱ ላይ ተራምጄ በአንድነት ባቃጠልኋቸው ነበር። ወይም ጉልበቴን ይያዝ፣ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ።” (ኢሳይያስ 27:​4, 5) ይሖዋ የወይን ተክሉ ‘የተወደደውን ወይን’ አትረፍርፎ መስጠቱን ይቀጥል ዘንድ የወይን ቦታውን ሊያበላሹ የሚችሉ እንደ አረም ያሉ ተጽዕኖዎችን ሁሉ ይጨፈጭፋል እንዲሁም በእሳት ያቃጥላል። እንግዲያውስ ማንም ሰው የክርስቲያን ጉባኤን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ማድረግ አይኖርበትም! ይልቁንም ሰው ሁሉ የይሖዋን ሞገስና ጥበቃ ለማግኘት በመጣጣር ‘የይሖዋን ጉልበት ሊይዝ ይገባል።’ ይህን በማድረግ ከአምላክ ጋር ሰላም ይፈጥራል። ይህ ጉዳይ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሣ ኢሳይያስ ሁለት ጊዜ ጠቅሶታል። ውጤቱስ ምን ይሆናል? “በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፣ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ።” (ኢሳይያስ 27:​6) * የዚህ ጥቅስ ፍጻሜ የይሖዋን ኃይል የሚያረጋግጥ እንዴት ድንቅ ማስረጃ ነው! ከ1919 ወዲህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መላዋን ምድር ‘በፍሬ’ ማለትም በሚገነባ መንፈሳዊ ምግብ ሞልተዋታል። ከዚህ የተነሣ ከእነርሱ ጋር አብረው ‘ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡ’ በሚልዮን የሚቆጠሩ ታማኝ የሆኑ ሌሎች በጎች ከጎናቸው ተሰልፈዋል። (ራእይ 7:​15) በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ እነዚህ ሰዎች የአምላክን ከፍ ያሉ የአቋም ደረጃዎች ደስ ብሏቸው ያከብራሉ። ይሖዋም ጭማሪ በመስጠት እነርሱን መባረኩን ቀጥሏል። ‘ከፍሬው’ ለመካፈል እንዲሁም በምናሰማው የውዳሴ ድምፅ አማካኝነት ይህንን ፍሬ ለሌሎች ለማዳረስ ያገኘነው መብት ታላቅ መሆኑን ፈጽሞ ልንዘነጋው አይገባም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ዔር የሚለው ስም “ከተማ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

^ አን.28 ኢሳይያስ 27:​7-13  በገጽ 285 ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ተብራርቷል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 285 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ነፃነትን የሚያበስር “ታላቅ መለከት”

በ607 ከዘአበ ይሖዋ ከሥርዓት ውጭ የሆነውን ሕዝቡን በግዞት በትር በቀጣ ጊዜ የይሁዳ ስቃይ በዝቶ ነበር። (ኢሳይያስ 27:​7-11ን አንብብ።) የሕዝቡ ኃጢአት የእንስሳ መሥዋዕት ሊያስተሰርየው የሚችል አልነበረም። በመሆኑም በግ ወይም ፍየል ‘እንደሚነዳ ’ ወይም በዓውሎ ንፋስ ‘እንደሚወገድ’ ቅጠል ይሖዋ እስራኤላውያንን ከምድራቸው አባርሯቸዋል። ከዚያ በኋላ በአንስታይ ፆታ የተጠሩ ደካማ ሕዝቦች ሳይቀሩ በምድሪቱ የቀረውን መበዝበዝ ችለዋል።

ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕዝቡን ከምርኮ ነፃ የሚያወጣበት ጊዜ ደረሰ። አንድ ገበሬ የዛፉ ምርኮኛ የሆኑ ያህል በወይራ ዛፍ ላይ የተንጠለጠሉትን ፍሬዎች ከዛፍ ላይ እንደሚያስለቅቅ ሁሉ ይሖዋም ሕዝቡን ነፃ ያወጣል። “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ፈሳሽ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ እህሉን ይወቃል፣ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፣ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፣ በአሦርም የጠፉ፣ በግብጽ ምድርም የተሳደዱ ይመጣሉ፣ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ።” (ኢሳይያስ 27:​12, 13) ቂሮስ በ539 ከዘአበ ካገኘው ድል በኋላ በአሦርና በግብጽ ያሉትን ጨምሮ በግዛቱ ያሉትን አይሁዳውያን በሙሉ በነፃ የሚያሰናብት ድንጋጌ ያወጣል። (ዕዝራ 1:​1-4) አንድ “ታላቅ መለከት” ለአምላክ ሕዝቦች የዘመረው የነፃነት ዝማሬ ያስተጋባ ያህል ነበር።

[በገጽ 275 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች”

[በገጽ 277 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባቢሎን እስረኞች በነበሩ ሰዎች እግር ተረግጣለች

[በገጽ 278 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ወደ ቤትህ ግባ’