በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ በብሔራት ላይ ቁጣውን ያፈስሳል

ይሖዋ በብሔራት ላይ ቁጣውን ያፈስሳል

ምዕራፍ ሃያ ሰባት

ይሖዋ በብሔራት ላይ ቁጣውን ያፈስሳል

ኢሳይያስ 34:​1-​17

1, 2. (ሀ) የይሖዋን የበቀል እርምጃ በተመለከተ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ለ) አምላክ የበቀል እርምጃ መውሰዱ የሚያከናውነው ዓላማ ምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ የታመኑ አገልጋዮቹን ብቻ ሳይሆን ከዓላማው ጋር የሚጣጣም ሆኖ እስካገኘው ድረስ ጠላቶቹን ጭምር ይታገሳል። (1 ጴጥሮስ 3:​19, 20፤ 2 ጴጥሮስ 3:​15) የይሖዋ ጠላቶች ትዕግሥቱን ከማድነቅ ይልቅ ዝም ያለው አቅም ስለሌለው ወይም እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ስላልሆነ ነው ብለው ያስቡ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ከ34ኛው የኢሳይያስ ምዕራፍ እንደምንረዳው ይሖዋ ጠላቶቹን ወደ ፍርድ ማምጣቱ አይቀርም። (ሶፎንያስ 3:​8) አምላክ ኤዶምያስም ሆነች ሌሎቹ ብሔራት ከልካይ ሳይኖራቸው የአምላክን ሕዝብ እንዲቃወሙ ለተወሰነ ጊዜ ፈቅዶላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ እነርሱን የሚበቀልበት ቀን ቀጥሮ ነበር። (ዘዳግም 32:​35) ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ ሉዓላዊነቱን በሚዳፈሩት የዚህ ክፉ ዓለም ክፍሎች ሁሉ ላይ ራሱ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ የበቀል እርምጃ ይወስዳል።

2 አምላክ በዋነኛነት የበቀል እርምጃ የሚወስደው ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥና ስሙን ለማስከበር ነው። (መዝሙር 83:​13-18) ከዚህም በተጨማሪ የበቀል እርምጃው አገልጋዮቹ በእርግጥም የእርሱ እውነተኛ ወኪሎች መሆናቸውን ያረጋግጣል፤ እንዲሁም አስጨናቂ ከሆኑ ሁኔታዎች ይገላግላቸዋል። ከዚህም በላይ ይሖዋ የሚወስደው የበቀል እርምጃ ሁልጊዜ ከፍትሑ ጋር የሚስማማ ነው።​—⁠መዝሙር 58:​10, 11

እናንተ አሕዛብ አድምጡ

3. ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት ለብሔራት ያቀረበው ጥሪ ምንድን ነው?

3 ይሖዋ በኤዶምያስ ላይ በሚወሰደው የበቀል እርምጃ ላይ ከማተኮሩ በፊት በኢሳይያስ አማካኝነት ለሁሉም ብሔራት ትኩረት የሚሻ አንድ ጥሪ ያቀርባል:- “እናንተ አሕዛብ ሆይ፣ ቅረቡ፣ ስሙ፤ እናንተ ወገኖች ሆይ፣ አድምጡ፤ ምድርና ሙላዋ፣ ዓለምና ከእርስዋ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ።” (ኢሳይያስ 34:​1) ነቢዩ አምላካዊ አክብሮት ስለሌላቸው ብሔራት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገር ቆይቷል። አሁን በእነርሱ ላይ ሲሰነዘር የነበረውን መለኮታዊ ውግዘት ሊያጠቃልል ነው። እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ለዘመናችን ትርጉም ይኖራቸው ይሆን?

4. (ሀ) በ⁠ኢሳይያስ 34:​1 ላይ እንደተገለጸው ብሔራት ምን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል? (ለ) ይሖዋ በብሔራት ላይ የሚያስፈጽመው ፍርድ ጨካኝ አምላክ እንደሆነ የሚያሳይ ነውን? (በገጽ 363 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

4 አዎን። የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ አምላካዊ አክብሮት የሌለው የነገሮች ሥርዓት ክፍል ከሆኑት ወገኖች ሁሉ ጋር ክርክር አለው። ይሖዋ በዓለም ዙሪያ እንዲታወጅ ያደረገውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልእክት “የምድር ወገኖች” እና “ምድር” እንዲሰሙ ጥሪ የቀረበበትም ምክንያት ይኸው ነው። ኢሳይያስ በ⁠መዝሙር 24:​1 ላይ ካሉት ጋር የሚመሳሰሉ ቃላት በመጠቀም ምድር በሞላ በዚህ መልእክት እንደምትሸፈን ተናግሯል። ይህ ትንቢት የይሖዋ ምሥክሮች ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ እየሰበኩ ባሉበት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሥራ 1:​8) ይሁን እንጂ ብሔራት አልሰሙም። እየመጣባቸው ስላለው ጥፋት የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ከቁብ አልቆጠሩትም። እርግጥ ይህ መሆኑ ይሖዋ ቃሉን እንዳያስፈጽም አያግደውም።

5, 6. (ሀ) አምላክ አሕዛብን ወደ ፍርድ የሚያመጣቸው ለምንድን ነው? (ለ) “ተራሮች ከደማቸው የተነሣ ይቀልጣሉ” የሚለው አባባል እውነት የሆነው እንዴት ነው?

5 ቀጥሎ ትንቢቱ አምላካዊ አክብሮት የሌላቸው ብሔራት የሚገጥማቸውን አስከፊ ዕጣ ይገልጻል። ይህ ደግሞ ቆየት ብሎ ከሚገለጸው የአምላክ ሕዝብ ካለው ብሩሕ ተስፋ ፈጽሞ የተለየ ነው። (ኢሳይያስ 35:​1-10) ነቢዩ እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ቁጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፣ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው። ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ፣ የሬሳቸውም ግማት ይሸታል፣ ተራሮችም ከደማቸው የተነሣ ይርሳሉ [“ይቀልጣሉ፣” NW ]።”​—⁠ኢሳይያስ 34:​2, 3

6 አሁን ትኩረት የተሰጠው የብሔራት የደም ባለ ዕዳነት ነው። በዛሬው ጊዜ ከማንም ይበልጥ ከፍተኛ የደም ዕዳ የተከመረባቸው የሕዝበ ክርስትና ብሔራት ናቸው። በሁለቱ የዓለም ጦርነቶችና በሌሎች ትናንሽ ግጭቶች ምድርን በሰው ልጆች ደም አጨቅይተዋል። ለዚህ ሁሉ ደም መፋሰስ ፍትሕን የመጠየቅ መብት ያለው ማን ነው? ከታላቁ ሕይወት ሰጪ ከፈጣሪ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (መዝሙር 36:​9) የይሖዋ ሕግ ‘ነፍስ ስለ ነፍስ’ በማለት ይደነግጋል። (ዘጸአት 21:​23-25፤ ዘፍጥረት 9:​4-6) በዚህ ሕግ መሠረት ይሖዋ የብሔራት ደም እንዲፈስስ ያደርጋል። በየሜዳው ወድቆ የቀረው አስከሬናቸው ሽታ አየሩን ይሞላዋል! በእርግጥም አሳፋሪ አሟሟት ነው! (ኤርምያስ 25:​33) የእጃቸውን ያገኙ ዘንድ የሚፈስሰው ደማቸው ተራሮችን የሚያሟሟ ወይም የሚያቀልጥ ያህል ነው። (ሶፎንያስ 1:​17) ለእነዚህ ዓለማዊ ብሔራት ወታደራዊ ኃይላቸው ሙሉ በሙሉ ወደመ ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ አንዳንድ ጊዜ በተራራ የሚመሰሉት መስተዳድሮቻቸው ወደቁ ማለት ይሆናል።​—⁠ዳንኤል 2:​35, 44, 45፤ ራእይ 17:​9

7. “ሰማያት” የተባሉት ምንድን ናቸው? ‘የሰማይ ሠራዊትስ?’

7 ኢሳይያስ ተጨማሪ ሕያው የሆነ ሥዕላዊ መግለጫ ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፣ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፣ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ [“እንደጠወለገ የወይን ቅጠልና እንደሟሸሸ የበለስ ፍሬ፣” NW ] ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል።” (ኢሳይያስ 34:​4) ‘የሰማይ ሠራዊት’ የሚለው መግለጫ ቃል በቃል ከዋክብትንና ፕላኔቶችን የሚያመለክት አይደለም። ኢሳይያስ 34 ቁጥር 5 እና 6 ላይ በእነዚያ “ሰማያት” ውስጥ በደም የሚነከር የቅጣት ሰይፍ እንዳለ ተገልጿል። በመሆኑም ይህ በሰብዓዊው ዓለም ያለን ነገር የሚያመለክት ምሳሌ መሆን ይኖርበታል። (1 ቆሮንቶስ 15:​50) የሰው ልጅ መስተዳድሮች ባላቸው የበላይ ሥልጣን ከፍ ብለው ስለሚታዩ በምድራዊው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ላይ የሚገዙ ሰማያት እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። (ሮሜ 13:​1-4) በመሆኑም ‘የሰማይ ሠራዊት’ የተባሉት የእነዚህ የሰው ዘር መንግሥታት ሠራዊቶች በጠቅላላ ናቸው።

8. ምሳሌያዊዎቹ ሰማያት “እንደ መጽሐፍ ጥቅልል” የሚሆኑት እንዴት ነው? ‘ሠራዊቶቻቸውስ’ ምን ይሆናሉ?

8 ይህ “ሠራዊት” ‘ይበሰብሳል’ ማለትም እንደ አንድ የሚበላሽ ነገር ይሻግታል። (መዝሙር 102:​26፤ ኢሳይያስ 51:​6) ከበላያችን ያለውን ሰማይ ቀና ብለን ስናየው በጥቅልል መልክ እንደሚዘጋጁትና በአብዛኛው ከውስጥ በኩል ብቻ እንደሚጻፍባቸው የጥንት የመጻሕፍት ጥቅልሎች መሀሉ ሰርጎድ ብሎ ይታየናል። በጥቅልሉ ውስጠኛ ክፍል ላይ የተጻፈው ነገር ከአንባቢው ዓይን ሲያልፍ ያለቀው ገጽ ይጠቀለላል። በተመሳሳይም ‘ሰማያት እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ተጠቅልለው ሲያልፉ’ የሰብዓዊ መስተዳድሮች ፍጻሜ ይሆናል። አርማጌዶን የታሪካቸው የመጨረሻ ገጽ ስለሚሆን ሕልውናቸው እዚያ ላይ ያከትማል። አስፈሪ መስለው የሚታዩት ‘ሠራዊቶቻቸው’ ከወይን ተክል ላይ እንደሚረግፍ ቅጠል ወይም ከበለስ ዛፍ ላይ እንደሚወድቅ ‘የሟሸሸ በለስ’ ይወድቃሉ። ጊዜ ያለፈባቸው ይሆናሉ።​—⁠ከ⁠ራእይ 6:​12-14 ጋር አወዳድር።

የበቀል ቀን

9. (ሀ) የኤዶምያስ ዝርያ ከየት የመጣ ነው? በእስራኤልና በኤዶምያስ መካከል የነበረው ግንኙነትስ ምን ይመስል ነበር? (ለ) ይሖዋ ኤዶምያስን በተመለከተ የተናገረው ነገር ምንድን ነው?

9 አሁን ደግሞ ትንቢቱ በኢሳይያስ ዘመን የነበረችውን አንዲት ብሔር ማለትም ኤዶምያስን ነጥሎ ይጠቅሳል። ኤዶማውያን ብኩርናውን መንትያው ለሆነው ወንድሙ ለያዕቆብ በእንጀራና በምስር ወጥ የሸጠው የኤሳው (የኤዶም) ዝርያዎች ናቸው። (ዘፍጥረት 25:​24-34) ያዕቆብ የብኩርናውን ቦታ ስለወሰደበት ኤሳው ለወንድሙ ከፍተኛ ጥላቻ አድሮበት ነበር። በኋላም የኤዶምያስና የእስራኤል ብሔራት የሁለት መንትያ ወንድማማቾች ልጆች ቢሆኑም እንደ ጠላት ሲተያዩ ኖረዋል። ኤዶምያስ ለአምላክ ሕዝብ ላሳየችው ለዚህ ጥላቻዋ የይሖዋን ቁጣ አትርፋለች። በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ ይላታል:- “ሰይፌ በሰማይ ሆና እስክትረካ ድረስ ጠጥታለች፤ እነሆ፣ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች። እግዚአብሔር መሥዋዕት በባሶራ፣ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተሞልታለች፣ በስብም፣ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፣ በአውራም በግ ኩላሊት ስብ ወፍራለች።”​—⁠ኢሳይያስ 34:​5, 6

10. (ሀ) ይሖዋ ‘በሰማያት ውስጥ’ ሰይፉን ሲመዝዝ አሽቀንጥሮ የሚጥለው ማንን ይሆናል? (ለ) ይሁዳ በባቢሎን ጥቃት ሲሰነዘርባት ኤዶምያስ ያሳየችው ዝንባሌ ምን ነበር?

10 ኤዶምያስ የምትገኘው ከፍ ባለ ተራራማ ቦታ ላይ ነው። (ኤርምያስ 49:​16፤ አብድዩ 8, 9, 19, 21) ያም ሆነ ይህ ይሖዋ የፍርድ ሰይፉን ‘በሰማያቱ ውስጥ’ መዝዞ የኤዶምያስን መሪዎች ከፍ ካለው ቦታቸው ሲያሽቀነጥራቸው እነዚህ ተፈጥሮአዊ መከላከያዎች የሚፈይዱት ነገር አይኖርም። ኤዶምያስ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል ያላትና የጦር ሠራዊቷም ከፍ ባሉት ተራሮች ሰንሰለት ላይ እየተሽሎከለከ የሚጠብቃት ምድር ነች። ይሁን እንጂ ኃያል የሆነችው ኤዶምያስ ይሁዳ በባቢሎን ሠራዊት በተጠቃች ጊዜ እርሷን ለመርዳት ያደረገችው ነገር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የይሁዳ መንግሥት በመገልበጡ ተደስታ ወራሪውን ኃይል አይዞህ ትል ነበር። (መዝሙር 137:​7) እንዲያውም ኤዶምያስ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሸሽተው የሚያመልጡትን አይሁዳውያን አሳድዳ እየያዘች ለባቢሎናውያን አሳልፋ ትሰጥ ነበር። (አብድዩ 11-14) የኤዶማውያኑ እቅድ እስራኤላውያን ትተውት የሚሄዱትን አገር መውሰድ ነበር። በይሖዋም ላይ በጉራ ተናግረዋል።​—⁠ሕዝቅኤል 35:​10-15

11. ይሖዋ ኤዶማውያን ለፈጸሙት ሸፍጥ የእጃቸውን የሚከፍላቸው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ ኤዶማውያን ያሳዩትን ይህ የጠላትነት ዝንባሌ ችላ ብሎ ያልፈዋልን? የለም አያልፈውም። እንዲያውም ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ጎሽ ከእነርሱ ጋር፣ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትረካለች፣ አፈራቸውም በስብ ትወፍራለች።” (ኢሳይያስ 34:​7 ) ይሖዋ በምድሪቱ የነበሩትን ታላላቆችና ታናናሾች በምሳሌያዊ መንገድ በወይፈንና በኮርማ እንዲሁም በአውራ በግና በሴት ፍየል ገልጿቸዋል። የዚህች ደም አፍሳሽ ብሔር ምድር በይሖዋ የቅጣት “ሰይፍ” አማካኝነት በሰዎች ደም ይርሳል።

12. (ሀ) ይሖዋ ኤዶምያስን ለመቅጣት መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው ማንን ነው? (ለ) ነቢዩ አብድዩ ኤዶምያስን በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል?

12 አምላክ ጽዮን በምትባለው ምድራዊ ድርጅቱ ላይ ስትፈጽመው ለቆየችው የተንኮል ድርጊት ኤዶምያስን ሊቀጣት ዓላማ አለው። ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር የበቀሉ ቀን፣ ስለ ጽዮንም ክርክር የብድራት ዓመት ነው።” (ኢሳይያስ 34:​8) ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከጠፋች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ የባቢሎኑን ንጉሥ ናቡከደነፆርን በመጠቀም በኤዶማውያን ላይ የጽድቅ የበቀል እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። (ኤርምያስ 25:​15-17, 21) የባቢሎን ሠራዊት በኤዶምያስ ላይ ሲዘምት ኤዶማውያንን የሚያስጥላቸው አይኖርም! በዚያች ተራራማ አገር ላይ የመጣ “የብድራት ዓመት ነው።” ይሖዋ በነቢዩ አብድዩ አማካኝነት እንዲህ ሲል አስቀድሞ ተናግሯል:- “በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ግፍ እፍረት ይከድንሃል፣ ለዘላለምም ትጠፋለህ። . . . አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፣ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል።”​—⁠አብድዩ 10, 15፤ ሕዝቅኤል 25:​12-14

የሕዝበ ክርስትና የጨለመ ተስፋ

13. ዛሬ ከኤዶምያስ ጋር የምትመሳሰለው ማን ናት? ለምንስ?

13 በዛሬው ጊዜም እንደ ኤዶምያስ ዓይነት ታሪክ ያስመዘገበ ድርጅት አለ። የትኛው ድርጅት ነው? በዚህ በዘመናችን የይሖዋን አገልጋዮች በመስደብና በማሳደድ ግንባር ቀደም የሆነው ማን ነው ብለን እንጠይቅ። በቀሳውስቷ አማካኝነት ይህንን ስታደርግ የኖረችው ሕዝበ ክርስትና አይደለችምን? አዎን! ሕዝበ ክርስትና በዚህ ዓለም ጉዳዮች እንደ ተራራ ከፍ ያለ ቦታ ይዛለች። በሰው ልጅ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ አለኝ ትላለች። እንዲሁም ሃይማኖቶቿ በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ጉልህ ስፍራ አላቸው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ዘመናዊቷ ኤዶምያስ በሕዝቡ ማለትም በምሥክሮቹ ላይ ስለፈጸመችው አሰቃቂ ተግባር “የብድራት ዓመት” ቀጥሮባታል።

14, 15. (ሀ) ኤዶምያስም ሆነች ሕዝበ ክርስትና ምን ይደርስባቸዋል? (ለ) የሚነድደው ዝፍትና ለዘላለም ዓለም የሚወጣው ጢስ ምን ያመለክታሉ? ሆኖም ምንን አያመለክቱም?

14 በመሆኑም የቀረውን የዚህን የኢሳይያስ ትንቢት ክፍል ስንመረምር ወደ አእምሮአችን የምትመጣው የጥንቷ ኤዶምያስ ብቻ ሳትሆን ሕዝበ ክርስትናም ጭምር ናት:- “የኤዶምያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፣ አፈርዋም ዲን ይሆናል፣ መሬትዋም የሚቃጠል ዝፍት ትሆናለች። በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፣ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል።” (ኢሳይያስ 34:​9, 10ሀ) የኤዶምያስ ምድር ደርቆ ከመሰነጣጠቁ የተነሣ አፈርዋ ዲን የሆነና ሸለቆዎቿም በውኃ ሳይሆን በዝፍት የተሞሉ ያህል ይሆናሉ። ከዚያም ይህ በቀላሉ ተቀጣጣይ የሆነ ነገር በእሳት ይያያዛል!​—⁠ከ⁠ራእይ 17:​16 ጋር አወዳድር።

15 አንዳንዶች እዚህ ጥቅስ ላይ እሳት፣ ዝፍትና ዲን መጠቀሱ እሳታማ ሲኦል ለመኖሩ ማረጋገጫ እንደሚሆን አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ኤዶምያስ ሐሳባዊ ወደሆነ አንድ እሳታማ ቦታ ተጥላ ለዘላለም እንድትቃጠል አልተደረገችም። ይልቁንም ሙሉ በሙሉ በእሳትና ዲን የተበላች ያህል እንድትወድም ወይም ከምድር ገጽ እንድትጠፋ ተደርጋለች። ትንቢቱ የሚሰጠውን መግለጫ ሲቀጥል የመጨረሻው ውጤት ‘መፍረስ፣ ባዶነትና ምናምን’ መሆን እንጂ ዘላለማዊ ቅጣት እንዳልሆነ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 34:​11, 12) ‘ለዘላለም የሚወጣውም ጢሷ’ ይህንኑ በግልጽ የሚያስረዳ ነው። አንድ ቤት ከተቃጠለ በኋላ እሳቱም ጠፍቶ እያለ ጢሱ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ መውጣቱን ይቀጥላል። ይህም ለሚመለከተው ሁሉ በአካባቢው ቃጠሎ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በኤዶምያስ ላይ ከደረሰው ጥፋት ትምህርት ስለሚያገኙ የኤዶምያስ ጢስ እስከዛሬም ድረስ ወደ ላይ እየወጣ ነው ለማለት ይቻላል።

16, 17. ኤዶምያስ ምን ትሆናለች? በእንዲህ ዓይነት ሁኔታስ የምትቀጥለው እስከ መቼ ነው?

16 የኢሳይያስ ትንቢት የኤዶምያስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ በአራዊት እንደሚተካ በመናገር የሚሰጠውን መግለጫ ይቀጥላል። ይህም አባባል ባድማ እንደምትሆን የሚያመለክት ነው:- “ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘላለም ዓለም ማንም አያልፍባትም። ጭልፊትና ጃርት ግን ይወርሱአታል፤ ጉጉትና ቁራም ይኖሩባታል፤ በላይዋም የመፍረስ ገመድና የባዶነት ቱንቢ ይዘረጋባታል። መሳፍንቶችዋን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፣ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም፤ አለቆችዋም ሁሉ ምናምኖች ይሆናሉ። በአዳራሾችዋም እሾህ በቅጥሮችዋም ሳማና አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጐን ስፍራ ትሆናለች። የምድረ በዳም አራዊት ከተኩሎች ጋር ይገናኛሉ፣ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያ ትኖራለች ለእርስዋም ማረፊያ ታገኛለች። በዚያም ዋሊያ ቤትዋን ትሠራለች እንቁላልም ትጥላለች ትቀፈቅፈውማለች ልጆችዋንም በጥላዋ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች እያንዳንዳቸው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ይሰበሰባሉ።”​—⁠ኢሳይያስ 34:​10ለ-15 *

17 አዎን፣ ኤዶምያስ ባድማ ምድር ትሆናለች። አራዊት፣ አእዋፍና እባቦች ብቻ የሚኖሩባት የተተወች ምድር ትሆናለች። ይህ ደረቅ የሆነው የምድሪቱ ሁኔታ በ⁠ኢሳይያስ 34 ቁጥር 10 ላይ እንደተገለጸው “ለዘላለም ዓለም” ይቀጥላል። ተመልሳ የምትቋቋምበት መንገድ ፈጽሞ አይኖርም።​—⁠አብድዩ 18

እርግጠኛ የሆነው የይሖዋ ቃል ፍጻሜ

18, 19. “የእግዚአብሔር መጽሐፍ” የተባለው ምንድን ነው? በዚህ “መጽሐፍ” ውስጥ ለሕዝበ ክርስትና ምን ተዘጋጅቶላታል?

18 ይህ ነገር ዘመናዊ የኤዶምያስ አምሳያ የሆነችውን ሕዝበ ክርስትናን ተስፋ ቢስ ሁኔታ እንደሚጠብቃት የሚያሳይ ነው! ሕዝበ ክርስትና ምሥክሮቹን አምርራ የምታሳድድ የይሖዋ አምላክ ክፉ ጠላት መሆኗን አሳይታለች። ይሖዋ ደግሞ ቃሉን እንደሚፈጽም ምንም ጥርጥር የለውም። ትንቢቱንና ፍጻሜውን የሚያወዳድር ማንኛውም ሰው ሁለቱንም ፍጹም አንድ ዓይነት ሆነው ያገኛቸዋል። ባድማ ሆኖ በቀረው የኤዶምያስ ምድር ላይ ያሉ እንስሳት ‘ባልንጀራቸውን እንደማያጡ’ ሁሉ የትንቢቱም ፍጻሜ የዚያን ያህል የተረጋገጠ ነው። ኢሳይያስ ወደፊት መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያጠኑ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም፤ አፌ አዝዞአልና፣ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፣ ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም። እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፣ እጁም በገመድ ከፈለችላቸው፤ ለዘላለም ይገዙአታል፣ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይቀመጡባታል።”​—⁠ኢሳይያስ 34:​16, 17

19 በሕዝበ ክርስትና ላይ እያንዣበበ ያለው ጥፋት “በእግዚአብሔር መጽሐፍ” ውስጥ በትንቢት ተነግሯል። ይህ ‘የእግዚአብሔር መጽሐፍ’ ይሖዋ በክፋት ድርጊታቸው የሚገፉበትን ጠላቶቹንም ሆነ ሕዝቡን የሚጨቁኑትን ንስሐ የማይገቡ ሰዎች ወደ ፍርድ ስለሚያመጣበት ዝርዝር ሁኔታ የሚገልጽ ነው። የጥንቷን ኤዶምያስ በተመለከተ የተጻፈው ነገር በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህም ስለ ዘመናዊቷ የኤዶምያስ አምሳያ ማለትም ስለ ሕዝበ ክርስትና የተነገረው ትንቢት በተመሳሳይ መንገድ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ያለንን ትምክህት ያጠናክርልናል። ‘መለኪያው ገመድ’ ማለትም ይሖዋ እርምጃ ለመውሰድ መሠረት የሚያደርገው ደንብ በመንፈሳዊ እየሞተች ያለችው ይህች ድርጅት ባድማ እንደምትሆን ማረጋገጫ ነው።

20. ልክ እንደ ጥንቷ ኤዶምያስ ሕዝበ ክርስትና ምን ይጠብቃታል?

20 ሕዝበ ክርስትና ፖለቲካዊ ወዳጆቿን ለማባበል የምትችለውን ሁሉ ጥረት ታደርጋለች። ይሁን እንጂ አይሳካላትም! በራእይ ምዕራፍ 17 እና 18 ላይ እንደተገለጸው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይሖዋ ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ በመላው የታላቂቱ ባቢሎን ግዛት ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ሐሳቡን ወደ ልባቸው ያስገባል። በዚህ መንገድ አስመሳዩ ክርስትና ከምድር ገጽ ላይ ተጠራርጎ ይወገዳል። የሕዝበ ክርስትና ሁኔታ በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 34 ላይ እንደተገለጸው ዓይነት የተስፋ ጭላንጭል የሌለበት ይሆናል። እጅግ ወሳኝ ለሆነው ‘የታላቁና ሁሉን የሚገዛው አምላክ የጦርነት ቀን’ እንኳ አትበቃም። (ራእይ 16:​14) እንደ ጥንቷ ኤዶምያስ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም “ለዘላለም ዓለም” ከምድር ገጽ ትወገዳለች።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 በሚልክያስ ዘመን ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቶ ነበር። (ሚልክያስ 1:​3) ሚልክያስ ኤዶማውያን ባድማ በሆነችው ምድራቸው እንደገና ለመኖር ተስፋ አድርገው እንደነበር ዘግቧል። (ሚልክያስ 1:​4) ይሁን እንጂ ይሖዋ አልፈቀደም። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ሌላ ሕዝብ ማለትም ነባዮታውያን የኤዶምያስን ምድር ወርሰዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 363 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቁጡ አምላክ ነውን?

በ⁠ኢሳይያስ 34:​2-7 ላይ ከተሰጡት ዓይነት መግለጫዎች በመነሳት ብዙ ሰዎች ይሖዋ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጸው ጨካኝና ቁጡ አምላክ ተደርጎ ነው ብለው ያስባሉ። ይህ እውነት ነውን?

የለም። አምላክ ቁጣውን የሚገልጽባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ያለ ምክንያት እንደዚያ አያደርግም። ሁልጊዜም ቁጣውን የሚገልጸው በስሜት ግንፋሎት ሳይሆን መሠረታዊ ሥርዓቶችን ድጋፍ በማድረግ ነው። ከዚህም በላይ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው አካል በመሆኑና እውነት ዘወትር ከፍ እንዲል ባለው የጸና አቋም ላይ የተመሠረተ ነው። መለኮታዊው ቁጣ አምላክ ለጽድቅና ጽድቅን ለሚያደርጉ ሰዎች ባለው ፍቅር የሚገራ ነው። ይሖዋ በጉዳዩ ዙሪያ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የሚያይ ከመሆኑም ሌላ ስለ አንድ ጉዳይ የተሟላና ያልተገደበ እውቀት ይኖረዋል። (ዕብራውያን 4:​13) ልብን ያነባል፣ የእውቀት ማነስና ግዴለሽነት እስከ ምን ድረስ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ወይም ደግሞ ሆን ተብሎ የተሠራ ኃጢአት መሆን አለመሆኑን ያውቃል። እርምጃም ሲወስድ አያዳላም።​—⁠ዘዳግም 10:​17, 18፤ 1 ሳሙኤል 16:​7፤ ሥራ 10:​34, 35

ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ለቁጣ የዘገየና ፍቅራዊ ደግነቱ የበዛ’ አምላክ ነው። (ዘጸአት 34:​6 NW ) እርሱን የሚፈራና ጽድቅን ለማድረግ የሚጥር ሰው ሁሉ ምሕረት ያገኛል። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሰዎች የወረሱት አለፍጽምና እንዳለ ስለሚገነዘብ ይህን መሠረት በማድረግ ለዚያ ሰው ምሕረት ያሳያል። ዛሬ አምላክ ይህንን ምሕረት የሚያሳየው የኢየሱስን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ነው። (መዝሙር 103:​13, 14) ኃጢአታቸውን ተገንዝበውና ንስሐ ገብተው እርሱን በእውነት የሚያገለግሉት ከሆነ ይሖዋ በተገቢው ጊዜ ቁጣውን ከእነርሱ ይመልሳል። (ኢሳይያስ 12:​1) በመሠረቱ ይሖዋ ቁጡ ሳይሆን ደስተኛ አምላክ ነው። የማይቀረብ ሳይሆን የሚቀረብ፣ ሰላማዊና በተገቢው መንገድ ወደ እርሱ የሚመጡትን የማያሸብር አምላክ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:​11) ይህ ደግሞ ምሕረት የለሽ እንዲሁም ጨካኝ ተደርገው ከሚገለጹት አረማውያን የሐሰት አማልክትና በምስሎቻቸው ላይ ከሚንጸባረቀው ባሕርይ ፈጽሞ የተለየ ነው።

[በገጽ 362 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ታላቁ ባሕር

ደማስቆ

ሲዶና

ጢሮስ

እስራኤል

ዳን

የገሊላ ባሕር

የዮርዳኖስ ወንዝ

መጊዶ

ሬማት ዘገለዓድ

ሰማርያ

ፍልስጥኤም

ይሁዳ

ኢየሩሳሌም

ልብና

ለኪሶ

ቤርሳቤህ

ቃዴስ በርኔ

የጨው ባሕር

አሞን

ረባት

ሞዓብ

ቂርሐራሴት

ኤዶም

ባሶራ

ቴማን

[በገጽ 359 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝበ ክርስትና ምድሪቱን በደም አጨቅይታለች

[በገጽ 360 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ”